Wednesday, July 19, 2017

ከዚህ የሚበልጥ ምን ሃይማኖታዊ እና አገራዊ ተልዕኮ አለ?

ከዚህ የሚበልጥ ምን ሃይማኖታዊ እና አገራዊ ተልዕኮ አለ?
------------
እነዚህ ሕጻናት በዚሁ በአሜሪካን አገር ያደጉ እና ለዲቁና የበቁ 8 ሕጻናትና ልጆች ናቸው። እነዚህን ልጆች ያስተማሩና ለዚህ ክብር ያበቁ ካህናትና መምህራን በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ቢያንስ እንዲህ ደስታችንን በመግለጽ ለአገልግሎታቸው ያለንን ክብር እናስታውቃቸው እንጂ ዋጋን የሚከፍል፣ የሰውን ዋጋ የማያስቀር አምላክ በበረከት እንደሚጎበኛቸው የታወቀ ነገር ነው። «ቃሉ የታመነ» ስለሆነ።

Wednesday, July 12, 2017

ሳውል-ቅዱስ ጳውሎስ፤ ከደማስቆ በር እስከ ቀጥተኛይቱ መንገድ

ጠቅለል ያለ መግቢያ ስለ ሳውል ….
(ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ)
ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመ ስሙ ሳውል ነው። አይሁዳዊ ነው። የተማረና ሊቅ፤ ለይሁዲነቱ እና ለእምነቱ ታላቅ ቅንዓት ያለው ሰው ነበር። በመምህሩ በገማልያል እግር ስር ተቀምጦ የተማረ ምጡቅ ሊቅ። ከቅንዓቱ የተነሣ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የሚተጋ ሰው። ትውልደ ነገዱ ከዕብራውያን ዘር ከብንያም ነገድ የተገኘ ሲሆን ሀገረ ሙላዱ (የተወለደበት) በንግዷ ታዋቂ በሆነችው በጠርሴስ ነው። ትውልዱ ዕብራዊ ቢሆንም አባቱ የሮማዊነትን ዜግነት የተቀበለ በመሆኑ ሳውልም ሮማዊ ዜግነት ነበረው ማለት ነው። ሮማዊ ዜግነት በዘመኑ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የዜግነት መታወቂያ ነበር። በዘመናችን እንዳለው የየትኛው አገር ዜጋ (ፓስፖርት?) እንበለው ይሆን?
ይህ በትውልድ አይሁዳዊነት በዜግነት ደግሞ ሮማዊነት ያለው ሳውል የተባለ ሰው ገና በልጅነቱ ገማልያል በሚባል መምህር እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረ ሲሆን በመምህሩ አማካይነትም «ፈሪሳዊነትን» የተቀበለ ምሁር ሆኖ አደገ። በ30 ዓመቱ የአይሁድ ሸንጎ አባል መሆኑ የሚያሳየው ምን ያህል የተማረ እና ሕግ አዋቂ መሆኑን ነው። ጌታ ባስተማረበት ዘመን የነበረ ሰው እንደመሆኑ ስለ ጌታ ትምህርት፣ ስለ ሐዋርያቱ ስብከት ጠንቅቆ ያውቃል፤ ሰምቷልም።

Tuesday, May 16, 2017

ሦስቱ የቤታችን «አርዕስተ ኃጣውዕ»፡- ሙስና፣ ዘረኝነት (መለካዊነት) እና የተሐድሶ ቅሰጣ

- አንዱ ከአንዱ ጋር ይመጋገባል፣
- አንዱ ለሌላው ማደግ እና መጎልበት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል፣
- ቤተ ክርስቲያናችን በነዚህ ሦስት ጦሮች ተሰቅዛለች፣
አጠቃሎ
በዚህ ዘመን ያሉት መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተናዎች ዓይን ያወጣ ዝርፊያና ጉቦ (ሙስና)፣ በወንዘኝነት ላይ የተመሠረተ ጥቁር ዘረኝነት እና እርሱ የወለደው መለካዊት እንዲሁም የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት ለመበረዝ እየተስፋፋ ያለ ኑፋቄ («ተሐድሶ») ናቸው። ይህ ማለት ሌሎች ችግሮች የሉብንም እነዚሁ ብቻ ናቸው ከሚል ደፋር ድምዳሜ የመጣ ሳይሆን አንኳር የሆኑትን እና እርስበርሳቸው የሚመጋገቡትን ችግሮች ለማንሣት ያደረግኹት ሙከራ መሆኑን በማሳሰብ ልጀምር።
በርዕሴ ላይ እንዳስቀመጥኹት መምህራን «አርዕስተ ኃጣውዕ» ብለው የሚያስተምሩት ሰይጣን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረባቸው እና መድኃኒታችን ድል የነሣቸውን ፈተናዎች መሆኑን አንባብያንን ላስታውስ። እነዚህ ሦስት የኃጢአት ራሶች («አርዕስተ ኃጣውዕ») የሚባሉት ትዕቢት፣ ፍቅረ ንዋይ እና ሥሥት ናቸው። ጌታችንም ትዕቢትን በትሕትና፣ ሥሥትን በትዕግስት፣ ፍቅረ ንዋይን በጸሊአ ንዋይ ድል በመንሣቱ ለእኛ አርአያ ሆኖናል። (ማቴ፬፡፲፩) ዛሬ ደግሞ ድል ልንነሣቸው የሚገቡን ሦስቱ ፈተናዎቻችን ሙስና፣ ዘረኝነት እና ኑፋቄ ተጋርጠውብናል።