Thursday, December 29, 2011

የሰው አገሩ - ምግባሩ

ይህ ጽሑፍ ለብፁዕ አቡነ አብርሃም ሽኝት ለተዘጋጀ መጽሔት ተጻፈ እና እዚያም ላይ የወጣ ነው።
(ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ):- አበው ሲተርቱ “የሰው አገሩ - ምግባሩ” ይላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ካስቀመጥነው “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል” (“መጽሐፈ ምሳሌ221) ወይም በሌላ ሥፍራ “መልካም ሽቱ መልካም ስም … ይሻላል” (መጽሐፈ መክብብ 7፤1) ካለው ጋር አንድ ነው። መልካም ስም እና ምግባር የተባሉት ሁለቱ ቃላት በአነጋገር የተለያዩ በመንፈስ ግን አንድነት ያላቸው አገላለጾች ናቸው። ምግባር ከአገር፣ መልካም ስምም ከመልካም ሽቱ እና ከብዙ ባለ ጠግነት እንደሚበልጥ ተገልጿል።

Monday, December 26, 2011

የአገር ናፍቆት

ይህንን ነገር እንድጽፍበት ካሰብኩ ቆይቻለኹ። መቸም ውጪ አገር ያለ ሰው በሙሉ በጋራ አንድ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የአገር ናፍቆት ነው። በቅርቡ ከአገሩ ከወጣው ጀምሮ 30 እና 40 ዘመን በሰው አገር እስከኖረው ሰው ድረስ አገሩን፣ ቀዬውን የማይናፍቅ የለም። እናም ጽሑፍ ጻፍ ሲባል በቶሎ የሚመጣለት ርዕስ ይኸው ነው የሚሆነው። እኔም ብዙ ጊዜ ነሽጦኝ ያውቃል። አሁን እንዳነሳው ያደረጉኝ ግን ሁለት አጋጣሚዎች ናቸው።

Friday, December 9, 2011

መልኬ ናፈቀኝ

(ኖቬምበር 16/2001፤ ድሬስደን፣ ጀርመን/ READ IN PDF)
እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው፤
መልኬ ነው ናፍቆቴ ጥቁሩ የቀይ ዳማን
ጠይም አሳ መሳይ ብስ ቀይ በርበሬን፣
ቸኮሌት መልክ ያለው የበሰለ ወይን፣
እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው።

Monday, December 5, 2011

ጫፍ እና ጫፍ

(ኤፍሬም እሸቴ/ READ IN PDF):-  Polarization (መወጠር ልበለው? ወይም ጫፍ እና ጫፍ መቆም?) የሚለው ቃል በአሜሪካ ሚዲያ ተደጋግመው ከሚጠሩት ቃላት እና ሐረጎች መካከል ተጠቃሽ ነው። አገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት እየመረመሩ ትርፍና ኪሳራውን ሌት-ተቀን፣ ሰባቱንም ቀን (24/7 እንደሚባለው) የሚያሰሉት ጋዜጠኞች እና ምሑራን ሁለቱንም የአገሪቱን ዐበይት ፓርቲዎች ማለትም ሪፐብሊካኑንም ዲሞክራቶቹንም የሚተቹት ፖለቲካውን ወጥረው ወጥረው ወደ ጫፍ፣ ወዳለመግባባት፣ ወዳለመቀራረብ፣ “ሰጥቶ መቀበል”ን ወደ መግፋት ወሰዱት  እያሉ ነው።

Thursday, December 1, 2011

“ሴክስ ቱሪዝም” ያውም እስከ ሰዶማዊነት ድረስ?


(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ READ IN PDF)

በዚህ ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ በሚደረግ እና ሰዶማዊነትንና ሰዶማውያንን “ለመከላከል” ቀድሞ በተጠራ የ"International Conference on AIDS and STLs in Africa – ICASA" ቅድመ ጉባኤ ምክንያት ሚዲያዎች እና ጦማሪዎች ሐሳባቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ “የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ” የተባለው በአገራችን የሚገኙ ዋና ዋና ቤተ እምነቶች በጋራ የሚሳተፉበት ጥምረትም ተቃውሞውን ገልጿል። ይሁን እንጂ የ ICASAን ጉባኤ በዋነኝነት የሚያዘጋጀው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉባኤው ጋዜጣዊ መግለጫውን ከሚሰጥበት ሥፍራ ሚኒስትሩን በመላክ መግለጫ እንዳይሰጥ አድርጓል። በወቅቱ ጋዜጠኞች ያነሷቸው ፎቶግራፎችም በፖሊሶች እንደ ተደመሰሱ ሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎች የጡመራ መድረኮች ዘግበዋል።

Monday, November 21, 2011

የአለንጋ ነገር

 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ OPEN IN PDF)
ቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ አንድ የተከበሩ ዳኛ ሰሞኑን የመገናኛ ብዙሃን ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ ሆነው ሰንብተዋል። ሰውዬው መነጋገሪያ ለመሆን የበቁት በሰጡት ፍርድ ወይም ባሳለፉት ውሳኔ ሳይሆን የ16 ዓመት ልጃቸውን በመግረፋቸው ምክንያት ነበር። ድርጊቱ የተፈጸመው የዛሬ ሰባት ዓመት ቢሆንም በስውር የተቀረጸው ቪዲዮ ግን ዩ-ቲዩብ ላይ የተለቀቀው አሁን በቅርቡ በመሆኑ ርእሰ ጉዳዩ ትኩስ ዜና ለመሆን በቅቷል። ነገሩ እንዲህ ነው። (WATCH THE VIDEO)


Monday, November 7, 2011

iPod, iPhone, iPad …. iSad


(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- የስቲቭ ጃብስን (Steve Jobs) መሞት ስሰማ ልክ እንደማውቀው ሰው፣ እንደ ቅርብ ወዳጅ ሁሉ፣ በጣም እዝን አልኩኝ።  ሲ.ኤን.ኤን ስቲቭ ከሞተ “30 ደቂቃ ሆነው” እያለ ነበር ዜናውን የሚያትተው። አከታትሎ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጀምሮ ታላላቅ ሰዎች በሙሉ “የተሰማቸውን ሐዘን” መግለጽ ቀጠሉ። የልጅነት ጓደኛው እና የእርሱ ቢጤ “ጂኒየስ” የሆነው ቢል ጌትስ/ Bill Gates/፣ ወጣቱ የፌስቡክ መሥራች “ዙከርበርግ”/ Zuckerberg/፣ የአፕል ካምፓኒ ቦርድ ወዘተ ዓለም አንድ ታላቅ የፈጠራ ሰው ማጣቷን እየገለጹ መስክረዋል።  በርግጥም ታላቅ የፈጠራ ሰው እንደነበረ ሥራዎቹ ምስክሮች ናቸው።

Monday, October 24, 2011

እኛ፣ 99 ፐርሰንቶቹ

(ኤፍሬም እሸቴ):- “ግብጻውያን ወደ ታህሪር አደባባይ የወጡበትን እና ከብዙ ደም መፋሰስ በኋላ በፈረጠም አገዛዛቸው ጥንታዊቱን ምስርን አስጨንቀው የገዟትን ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣናቸው አሽቀንጥረው የጣሉበትን ምክንያት ብዙ አሜሪካውን ይረዳሉ፤ በደመ ነፍስም ቢሆንም ይስማሙበታል። የራሳቸው ወገኖች “ዎል ስትሪት”ን ለመቆጣጠር የተነሡበትንምክንያት ግን ሁሉ በአንድ ልብ አልተገነዘቡትም” ይላል የኒውዮርክ-ታይምሱ ጦማሪ (Damon Winter/The New York Times) ዴሞን ዊንተር።

Thursday, October 20, 2011

የጋዳፊ የወርቅ ሽጉጥ

ጋዳፊ እና ቤተሰቡ ሊቃወሙት የወጡትን የራሱን ዜጎች የገለጸበት አንድ ቃል ብትኖር “አይጦች” የምትለዋ የጽርፈት ቃል ነበረች። በመጨረሻ ግን እንደ አይጥ ጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ራሱ ኮሎኔል ጋዳፊ ሆነ። የወርቅ ሽጉጡም ብትሆን ከጠላቶቹ እጅ አላተረፈችውም። ሊቢያን በብረት እጁ አድምቶ፣ ሕዝቧን እየጨፈጨፈ የኖረው (1969-2011) “ብራዘር ሊደር/ Brother Leader” በትውልድ መንደሩ ጎዳናዎች ላይ አስከሬኑ ተጎተተ። የዲክቴተሮች አስቀያሚ መጨረሻ፦ ባለ ወርቅ ሽጉጥ እንደጨበጡ፣ አስከሬናቸው እንደ ውሻ ሜዳ ላይ መጣል።

Wednesday, October 12, 2011

ቃላት እና ቋንቋ እንደየዘመኑ፣ እንደየመንደሩ፣ እንደየመንግሥቱ

(ኤፍሬም እሸቴ):- ሁል ጊዜም አዲስ ዘመን አዲስ ቃል እና አገላለጽ ይዞ ይመጣል። አዲሱ ቃል መምጣቱ ሳይታወቅ የሚረሳውን ያህል አንዳንድ አገሮችና ባሕሎች ግን እነዚህን አዳዲስ ቃላት የመመዝገብ እና የማጥናት ልምድ አላቸው። የዓመቱን አዲስ አባባልና ቃል መርጠውም ያስታውቃሉ። አዲስ በሚታተም መዝገበ ቃላት ውስጥም ያስገባሉ። ለምሳሌ በ2010 በዚህ መልክ መነጋገሪያ ከነበሩት መካከል ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት የጆን ማኬይን ምክትል ወይዘሮ ሣራ ፔሊን አንዷ ናቸው።  ሴቲዮዋ በንግግር መካከል ተሳስተው የተናገሩት ቃል የ2010 ምርጥ አዲስ ቃል (“New Oxford American Dictionary 2010's Word of the Year”) ተብሎ አዲስ የ“American lexicon” ለመሆን በቅቷል።

Tuesday, October 11, 2011

ጋብቻ - ኢትዮጵያ፤ ፍቺ - አሜሪካ

(ኤፍሬም እሸቴ):- እዚህ አሜሪካን ውስጥ ከሚታተሙት እና እኔም ከምወዳቸው ጋዜጦች መካከል አንዱ “USA Today/ ዩ.ኤስ.ኤ ቱዴይ” የተባለው (እና የድሮውን “የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ”ን የሚያስታውሰኝ) ጋዜጣ አንዱ ነው። ፖለቲካም፣ ማሕበራዊ ሕይወትም፣ ቴክኖሎጂም፣ ስፖርትም፣ ቢዝነስም … ሁሉም ሁሉም በአጭር-በአጭሩ እና ቅልብጭ ባለ እንግሊዝኛ የሚታተምበት ጋዜጣ ነው። (የዛሬዪቱ ኢትዮጵያም እንደዚህ ነበረ ማለቴ አይደለም)።

Friday, September 9, 2011

“To Fear or Not To Fear”፤ 9/11

በዚህ ሰሞን ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሚዲያዎችን ሁሉ ያጥለቀለቀ የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በየሚዲያው በመተላለፍ ላይ ናቸው። የመጀመሪያው “ሂዩሪኬን አይሪን”/ “ማዕበል-አይሪን” መጣሁ መጣሁ  ባለችበት ባለፈው ወቅት ሲከናወን የቆየው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰሞኑን አሥረኛ ዓመቱ በደረሰው የ9/11 ጥቃት ዙሪያ ያለው ነው። ብዙ ሰው በእንደዚህ ዓይነቱ “ማስጠንቀቂያ” ላይ ያለው አመለካከት ይህንን ጽሑፍ ጋብዟል።


Sunday, August 21, 2011

“ንዴት ማረቅ” (Anger Management)


ዓለም እና ሕይወቷ በሙሉ ፈጣሪ እና አስተዳዳሪ አለው። እንኳን ይህቺ የምንኖርባት ዓለም፣ ሕዋው ከነግሳንግሱ፣ ከረቂቁ ፍረት እስከ ግዙፉ አሰስ ገሰሱ፣ በዓይን ሚታየው እስከማይታየው ድረስ ፈጥሮ የሚገዛው፣ ባለቤት አለው። በዘፈቀደ የመጣ፣ በዘፈቀደ የሚከወን ነገር የለም። የኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት የአስኳላው ትምህርት እግሩን አስረዝሞ ከመግባቱ ከሺህ ዓመታት ጀምሮ ይህንን የፍጥረት ዑደት እና ሥርዓት እያራቀቁ እና እያመሰጠሩ ሲያስተምሩ ኖረዋል፣ ያስተምራሉም። አዲሱ ዘመነኛ የአስኳላ ትውልድ ያጣውና እያጣው ያለው ይህ አገርኛ ፍልስፍና እና ሥነ ተፈጥሮ ከመጻሕፍት ልብ ውስጥ ብቻ ወደሚገኝበት፣ ልክ እንደ ሉሲ ከሙዚ ወይም እንደ አክሱም ሐውልት  ለአንክሮ ለተዘክሮ ብቻ የሚደነቀር ለመሆን በሚፍገመገምበት በዚህ ዘመን ከጥንቱ አስተምህሮ ውስጥ ሁሌም የምፈልገው አንድ ቃለ ምሥጢር አለኝ።

Saturday, August 20, 2011

በረከተ ደብረ ታቦር


ጌታዬ
እንደ ሙሴ አንደበተ ጎልዳፋ ብሆን፤ አንተ አንደበት ሆንከኝ።
እንደ ኤልያስ እኔ ብቻ ለአንተ የቆምኩ መስሎኝ ብታበይ ስለ ብዙዎቹ ወዳጆችህ ብለህ ማርከኝ፤
እንደ ጴጥሮስ ቸኩዬ ወድጄህ ቀድሜ ብከዳህ፤ በንስሐ ዕንባ ተቀበልከኝ፤ አብልጠህ አከበርከኝ፤
እንደ ያዕቆብ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ ቢጸናብኝ፤ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ሰጥተህ ፈወስከኝ፤
እንደ ዮሐንስ ብታፈቅረኝ የእናትህን ጣዕም በአንደበቴ ፍቅሯን በልቤ ሳልክልኝ፤ በአማላጅነቷ ጠበቅኸኝ።

ጌታዬ፦ ስለ ቸርነትህ በደብረ ታቦር ክብርህን የገለጥክላቸው የነዚህ ወዳጆችህ ፀጋ በረከት ይድረሰኝ።
አሜን

Saturday, July 30, 2011

እርግና እና እርጅና ….

በዚህ በፈረንጁ አገር በስደት ያለነው ወጣቶቹና ጎልማሶቹ እንዲሁም ልጆቻችን ብቻ አይደሉም። ብዙ ዕድሜ የጠገቡ አረጋውያንና አረጋውያትም ተሰድደዋል። በተለይም እንደ ዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ባለ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ነጠላ ለብሰው ወዲያ ወዲህ የሚሉ እናቶችን፣ ከዘራ ቢጤ ጨብጠው በአባታዊ ግርማ ሞገስ በቀስታ የሚራመዱ ኢትዮጵያዊ አባቶችን ማየት የተለመደ ነው።

Wednesday, July 13, 2011

ት/ቤት ሲዘጋ … በአሜሪካ

በዚህ በአሜሪካ አሁን በጋ (Summer) ነው። ብዙ ሠራተኞች እረፍት ለመውጣት ጥሩ አጋጣሚ አድርገው የሚጠቀሙበት ጊዜ ይህ የበጋው ወራት ነው። ት/ቤትም ተዘግቷል። ልጆቹ በሙሉ በየመንገዱ፣ በየመዝናኛው ይተረማመሳሉ። በተለይ ወደ ማታ ላይ ሕጻናቱን አምጥቶ የሚያፈሳቸው ማን እንደሆነ እንጃ።

Friday, June 24, 2011

ቅድሚያ ለራስ


የአሜሪካ ሬዲዮኖችና ቴሌቪዥኖች አብዛው ዘገባቸው ስለ አካባቢያቸው ነው። “የአካባቢ” የሚባሉት ሚዲያዎች ቀርቶ “አገር አቀፍ” የሚባሉትም እንኳን ሲጀምሩም ሲጨርሱም ስለ ከተማቸውና መንደራቸው፣ ግፋ ካለም አገራቸው ነው የሚያወሩት። በሌላ አገር ከሚጠፉ የሰው ነፍሶች ይልቅ በመንደራቸው የጠፋች ውሻ ጉዳይ የተሻለ ተደማጭነት ሊኖራት ይችላል። በሌላው ዓለም ከሚጀመር ትልቅ ጦርነት ይልቅ በዚያው በአካባቢው ያለ የወንጀልና ወንጀለኛ ዜና ወይም ታሪክ የበለጠ ተደማጭነት/ታዪነት አለው።

ከዋሺንግተን ዲሲ እስከ አትላንታ


በሜይ የመጨረሻ ሰኞ ቀን፣ አሜሪካ “Memorial Day/ ሚሞሪያል ዴይ” ብላ የምታከብረውን በዓል አስታክኬና አጋጣሚውን ተጠቅሜ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ያዘጋጀው 13ኛ ዓመታዊ ጉባኤው ላይ ለመካፈል ወደ አትላንታ ጉዞ ላይ ነበርኩ። “Long Weekend/ ሎንግ ዊክ ኤንድ” ወይንም አርብ እና ሰኞን ሥራ ባለመግባት ከሚከበሩት አሜሪካውያን ከሚወዷቸው በዓላት አንዱ በመሆኑ ሰዉ ሁሉ ወደ መንገድ ይወጣል። በአውሮፕላንም፣ በመኪናም፣ በባቡርም በተገኘው ሁሉ ይቺን አራት የእረፍት ቀን ለመጠቀም ቤተሰብም ሆነ ወንድና ሴት ላጤዎች ከከተማዎች ወደ ውጪ የሚጓዙበት ጊዜ ነው። በየከተማው የሚቀሩትም ቢሆኑ ለመዝናኛነቱ ይወዱታል።

Thursday, June 16, 2011

ሥልጠና:- ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል 6)


መቸም ዝም ብዬ ለመጥፋቴ ከልብ ይቅርታ ከመጠየቅ ውጪ ሌላ ምን እላለኹ። ምንም አልሞላልኝ ብሎ ሰነበተ። ይኼ የብላቴ ነገር እንዲህ አስቸጋሪ ይሆናል ብዬ መቼ ገመትኩ። ድሮም ጥይት ያለበት ነገር። የት እንደቆምን ሳትረሱ የምትቀሩ አይመስለኝም። ያለፈውን ክፍል እንድትመለከቱ ከመጋበዝ ውጪ እርሱን በመከለስ ጊዜያችሁን ማጥፋት አልፈልግም። በዚህ ክፍል “ስለ ወታደራዊው ሥልጠናና ገጠመኛችን” ለማንሳት ፍላጎት ነበረኝ። እነሆ።

 ሥልጠና

በብላቴ ሥልጠናው የሚጀምረው ከቲዎሪ ነው።  የቀለም ትምህርት ልትሉት ትችላላችሁ። ሁሉም ነገር ትምህርት አለው። አንዳንዱ ትምህርት እና አቀራረቡ ራሱን ሊቅ አድርጎ ለሚቆጥረው ተማሪ አስቂኝ ነበር። ለምሳሌ የሕክምና ተማሪዎች ባሉበት በእኛ ብርጌድ “የመጀመሪያ የሕክምና ርዳታ” አሰጣጥ ትምህርት ሲሰጥ ብዙው ተማሪ የጉምጉምታ ሳቅ ያሰማ ነበር። በርግጥ ሌሎቻችን ገና ለገና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ስለሆንን በጅምላ ራሳችንን እያስኮፈስን እንጂ መምህራኑ የሚያስተምሩትን ቀድመን ያወቅን ሆነን አልነበረም። እንዲያው ይህ ራስን የማስኮፈስ ነገር ከተነሣ ጥቂት ልበልበት። የሚቀየሙኝ አንባብያን፣ የያን ጊዜ ዘማቾች ካሉ ከወዲሁ ይቅርታቸውን እጠይቃለሁ።

Sunday, May 15, 2011

"የስም ነገር"

አሜሪካ የራሷ የስም አሰጣጥና አጠራር ያላት የምትገርም ሀገር ናት። አሜሪካ ረዥም ስም አትወድም። አሜሪካ ሰዎች ትቀበላለች ይባል እንጂ ስትቀበል የራሷን ስም አውጥታ ነው። በየዘመኑ ወደ አሜሪካ የመጡ ስደተኛ ሕዝቦች በሙሉ የራሳቸውን ማንነት እና ስም አወጣጥ እንደጠበቁ ነገር ግን መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ስማቸውን አሜሪካዊ አድርገዋል። “አሌክሳንደር የነበረው አሌክስ፣ ክሪስቲያን የነበረው ክሪስ ወይም “አል” ብለው የሚጀምሩ የተለያዩ ስሞችን በማሳጠር “አል” የሚለውን ብቻ በመውሰድ የራሳቸውን ስያሜ ይፈጥራሉ። (Al Gore/ አል ጎርን ያስታውሷል)። ታዲያ ለአዲሱ ስም ዳቦ አትቆርስም፣ አታስቆርስም። ረዝሞና ረዛዝሞ የተቀመጠ ስም እንዲያጥር በፍቅሯ ታስገድዳለች። ይህንን ሁሉ ማሻሻያ የሚያደርጉት በአብዛኛው በስመ ተጸውዖ (መጠሪያ) ስማቸው ላይ እንጂ በቤተሰባቸው ስም ላይ አይደለም።

Friday, May 13, 2011

ይቅርታ፤ "አለኹ"


ሰላም ጤና ይስጥልኝ። የብላቴን ታሪክ አምስተኛ ፎርማታ ላይ ገትሬው በመጥፋቴ ይቅርታ፤ ለጻፋችሁልኝ ኢ-ሜይል በሙሉ አመሰግናለኹ። ያገሬ ሰው “የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ ነው” እንደሚለው የጊዜ እጥረት እና አለመመቻቸት ይዞኝ ነው። ክፍል ስድስትን እቀጥላለኹ፣ ሳልውል ሳላድር። ለዛሬው ደግሞ ትዝታውን እንዲያካፍለኝ ጠይቄው የነበረው የያኔው የጅማ መምህራን ኮሌጅ ተማሪ፣ የዛሬው ቀሲስ፣ ስንታየሁ አባተ ነው። እነሆ።
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የዛሬ ሃያ ዓመት ወቅቱ ዘመነ ፋሲካ ነበር። የጂማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም አስተዳደር ድንገተኛ ትእዛዝ አስተላለፈ። በአዲስ አበባ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ባደረጉት ዉሳኔ መሠረት ዕጩ መምህራኑ ወደ ብላቴ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ መሄድና መሰልጠን አለባችሁ በማለት ከጭራ የቀጠነ ትእዛዝ አስተላለፈ። ለተማሪው የመወያያ ጊዜና ዕድል እንኳን አልተሰጠም።

Thursday, April 21, 2011

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል አምስት)

ቢጫ ወባ፣ “ሻምበል ደቤ” እና ዱካክ 
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል አምስተኛ ክፍል ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ከክፍል አንድ እስከ አራት ያሉትን ማንበብ አይርሱ። 
-----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ዘንግቼ አልፌው የነበረ እና አንድ ወንድሜ ያስታወሰኝን የ1983 ዓ.ም የስቅለት በዓል ጉዳይ ላካፍላችሁ።  ልክ እንደ 1984 ዓ.ምሕረቱ የሚያዚያ 16 ዕለተ ኪ/ምህረት ስቅለት፤ እንደ 1997 ዓ.ም ሚያዚያ 21፣ እንደ 1999 ዓ.ም መጋቢት 28 የአማኑኤል ቀን፣ እንዲሁም በጻድቁ አቡነ ተ/ሃይማኖት ቀን እንደዋለው የመጋቢት 24/2002 ዓ.ም ስቅለት የዚያን ዓመት፣ የ1983 ዓ.ምሕረቱ በዓለ ስቅለት ደግሞ የዋለው መጋቢት 27 ቀን የመድኃኔ ዓለም ዕለት ነበር። በሃያ ሰባት እንደመዋሉ አንዳንዱ "እንስገድ" ሲል ሌላው ደግሞ “አይ፣ መሰገድ የለበትም፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይከለክላል” ይላል። አንዳንዱ ደግሞ “ግዴለም ከወገባችን ብቻ ጎንበስ ጎንበስ እያልን እናስበው” ይላል። ክርክሩ ቀጠለ። በቦታው ሊቅ የለም። ሊቃውንትም የሉም። ተማሪው ከተገናኘ ገና ሳምንቱ ነው። እርስበርሱ የሚተዋወቀው ጥቂቱ ነው። እናም ክርክሩ ጊዜ ወሰደ። በመጨረሻ ግን መሰገድ እንዳለበት ያብራሩት ወንድሞች ሐሳብ ተቀባይነት ኖሮት ዕለቱን ስንሰግድ ዋልን። 

Friday, April 15, 2011

ሕማማት እና ትንሣኤ በብላቴ

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል አራት)
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል አራተኛ ክፍል ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ሁለትንና ሦስትን ማንበብ አይርሱ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________
ሥልጠናው ከመጀመሩ አስቀድሞ ለዚያ የሚያስፈልጉ ነገሮች ተሟልተው ተሰጥተውናል። አንድ ጫማ፣ ቱታ፣ ካልሲ፣ ካናቴራ፣ አዣክስ ሳሙና፣ “ብሬዢኒቭ” የሚሉት ቁምጣ። ቁምጣውን በቀድሞ የሶቪየት ሕብረት ፕሬዚደንት ስም ለምን እንደተሰየመ አላውቅም። አለ ነገር ግን እንደዚያ አላሉትም። የኛ ሰው እንዲህ ነገሮችን እያገናኙ ስም የመስጠት ልዩ  ሥጦታ አለው። ይቺ ብሬዢኔቭ ቁምጣ ተማሪው በከፍተኛ “የዲያሪያ” (ሸርተቴ) ወረርሽኝ በተቸገረ ጊዜ ብዙ ውለታ ውላልናለች። በቦታው አነሣዋለኹ።

Saturday, April 9, 2011

ጉዞ ወደ ብላቴ …

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል ሦስት)
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል ሦስተኛ ክፍ ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ሁለትን ማንበብ አይርሱ።
+++
ጉዞ ወደ ብላቴ …
ሽንጣም የክፍለ ሀገር አውቶቡሶች መጥተው ኮሌጁ ግቢ ውስጥ ተገጥግጠዋል። ዕለቱ ሐሙስ ነው። የቀን ቅዱስ። መጋቢት 19/ 1983 ዓ.ም። ቅዱስ ገብርኤል መታሰቢያ። ሻንጣዎቻችንን አሰናድተን በሌሊት ተነሥተናል። የመንቀሳቀሻው ሰዓት ከመድረሱ አስቀድሞ ከተወሰኑ ወንድሞች ጋር ወደ ኮተቤ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሄድን። ጸሎት አድርሰን ከካህናቱ ጋር ተሰነባበትን።

Friday, April 8, 2011

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት

ይህ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል ክፍል ሁለት ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ማንበብ አይርሱ

ነገረ ወታደር በልጅነት አእምሮ

መቼም ወታደር የመሆን ትንሽ የለውም። አንድ ጊዜ ካምፕ ከገቡ እና መሣሪያ ከጨበጡ ያው ወታደር ተኮነ ማለትም አይደል? ድንገት አይበለውና ነገር ተገጣጥሞ ጦርነቱ አውድማ ላይ የምንውልበት ሁኔታ ቢፈጠር “ግዴለም እነርሱ የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው፤ ሳይፈልጉ መጥተው ነው” ወዘተ ወዘተ የሚል አይኖርም። ስለዚህም የጦር እና የጦርነት ወሬው እያየለ ሲመጣ ነገሩ ከባድ መሆኑ አይቀርም።

Thursday, April 7, 2011

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል አንድ)

ይህ መጣጥፍ ከዚህ እትም ጀምሮ ለተወሰኑ ሳምንታት ይቀጥል ዘንድ የተዘጋጀ ነው። በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል። በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ። 
(ክፍል አንድ)
ብላቴ በቀድሞው የሲዳሞ ክፍለ ሀገር፣ ከሐዋሳ ከተማ ወደ 90 ኪ.ሜትር, ከአዲስ አበባ ደግሞ 395 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ነው። ከባሕር ጠለል በላይ 1000- 1400 ሜትር በበረሃማው የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ሞቃት ቦታ። በበጋ ወቅት እጅግ በጣም ሞቃት እና ደረቅ ሲሆን በክረምት ደግሞ ዝናባማ እና የሚተነፍግ ውሃ አዘል አየር (rainy and humid) ይበዛበታል። 

Saturday, March 26, 2011

ስለ “ግለሰብ እና ሕዝብ፤ ታሪክ እና ያለፈ ጉዳይ” (ካለፈው የቀጠለ)


ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፖለቲካ ውዝግብ የሚፈጥር ነገር የሚመረጥ አይደለም። በመጪ ጉዳዮች ላይ ብንወዛገብ አንድ ጉዳይ ነው፤ አገራችን እንዴት እናልማ፣ በየት አቅጣጫ እንምራ በሚለው ጉዳይ ላይ ብንከራከር ብንወዛገብ አንድ ጉዳይ ነው። በተወሰነ ደረጃ ገንቢ ገጽታ አለው። ተወያይተን ተመካክረን አንድ የጋራ አቋም ልንይዝ እንችላለን። ባለፈ ጉዳይ ላይ ብንነታረክ ግን ይኼን ያህል ገንቢ ጉዳይ የለውም። ያለፈ ጉዳይ ነው። ሲሉ ያስታወሱኝን አስተሳሰብ ደግሞ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ባልኩት መሠረት እነሆ የጫርኩትን።

Sunday, March 20, 2011

ስለ “ግለሰብ እና ሕዝብ፤ ታሪክ እና ያለፈ ጉዳይ” (Part I)

Sunday, March 20, 2011:- ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰፊ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ተመልከቼ ነበር። በተለይም በሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እንዲሁም በጅማ እና አካባቢው ያለውን የሃይማኖት ግጭት በተመለከተ ምን እንዳሉ በስፋት ለመስማት ፈልጌ ነበር። በዩ-ቲዩብ ተቆራረጦ ከተቀመጠው የጠ/ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ ጥያቄና መልስ መካከል ባሰብኩት መልኩ ባይሆንም የ“ቁምነገር” መጽሔት ጋዜጠኛ ያነሣቸው ጥያቄዎች እና አቶ መለስ የሰጧቸው መልሶች ይህንን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት ሆኑኝ።

Monday, March 7, 2011

አባት ለልጅ ምኑ ነው?

ተረቱ “አባት ሳለ አጊጥ፣ ጀንበር ሳለ እሩጥ” ይላል። ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ “ኧረ ባክህ አንተ ልጅ፣ ሴት ያሳደገው አታስብለኝ” ይላሉ። ነፍሳቸውን ይማረውና እማማ አስካለም “ኤዲያ፤ ለመውለድ ለመውለድ እበትም ትል ይወልዳል” ይላሉ የማይረቡ አባቶችን ሲተቹ ወይም “አባትን አባት የሚያደርገው ልጅ ለመውለድ ባለው ተፈጥሯዊ ፀጋ ከሴት ማኅፀን ልጅ እንዲገኝ ማድረጉ ብቻ አይደለም” ለማለት ሲፈልጉ። ሌላም ሌላም የአባትን ምንነት የሚያስታውሱ ሥነ ቃሎችን መጥቀስ ይቻላል። እንዲያው ግን አባት ለልጅ ምኑ ነው?

Thursday, March 3, 2011

Mr. Limbaugh, what does an Ethiopian Look Like?

Let us start by this quotation:
On his radio show today Rush Limbaugh attacked First Lady Michelle Obama for not looking skinny enough. Limbaugh said, “The point is. If you are going to do this, if you are going to tell everyone to eat twigs and berries and gravel and all this other stuff, you’d better look like an Ethiopian.”

Tuesday, March 1, 2011

ሥጋዬ

ዕዳህ ለእኔ ዕዳ፣
ዕዳህ ለእኔ ፍዳ፣
ደስታህም ሀዘን፣
ሀዘንህም ሀዘን፤

ሲደላህ ስትርቀኝ፣
ስታጣ ስትቀርበኝ፣
ያንተ ባጣ ቆየኝ፣

ውኃ አጣጭ

ድካም እንጂ ግጣም ፍለጋ፣
ከማይገጥመኝ ከማልገጥመው የምቆለፍ የምዛጋ።
ግራ እንጂ ቢሆን ነው ያለ ቁልፍ  መኖሬ፣
ያለ ቤቴ ያለ በሬ የሌላ ደጅ መቆርቆሬ።

Monday, February 28, 2011

የኢንተርኔቱ ዓለም እና ጣጣው

የዚህን እትም የሮዝ፣ ይቅርታ የ“አዲስ ጉዳይ”፣ ጽሑፌን በሌላ ርዕስ ላይ እያዘጋጀኹ ነበር። በመካከሉ የአሜሪካ ድምጽ ለመስማት ከፍቼ መስማት ጀምሬ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የአንድ ወዳጄ  ስልክ አንቃጨለ። ሳነሳው የአሜሪካ ድምጽን ለመስማት ሞክሮ እንዳልተከፈተለት ነገረኝ። “ኧረ እየሰማኹ ነው፤ እስቲ ድጋሚ ሞክረው” አልኩት። ሞከረው። አይሰራም። እኔም እሰማው የነበረውን ትቼ ድጋሚ ሌላ ስከፍት እውነትም ሌላ ሆኗል። ድረ ገፁ ግን ራሱ የአሜሪካ ድምጽ ነው። የሚታየው ግን የተለመደው የቪ.ኦ.ኤ ዓርማ ሳይሆን በአረብኛ ያሸበረቀ “እኛም እንደምንችል አሳየናችሁ” የሚል ፉከራ ቢጤ ነው።

Saturday, February 26, 2011

ጥያቄና መልስ

ሲሉኝ ሲጠይቁኝ፤
ከወዴት አገር ነህ ከየትኛው ሥፍራ፣
ከየትኛው መንደር ከየትኛው ጋራ፣
እስቲ ስላገርህ፣
ንገረን እባክህ?

የትኛውን ልጥቀስ የትኛውን ብዬ፣
የትኛውን ላንሣ የትኛውን ጥዬ፣
የትኛው ይሻላል ከየቱ ልነሣ፣
የቱን ላስታውሳቸው የትኛው ይረሣ?

Friday, February 25, 2011

አሜሪካዊ ከሆንክ መንግሥትህ ይደርስልሃል፣ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ...

ሊቢያ ሰሞኑን እንዲህ መዓት ሲነድባት የሌሎች አገራት መንግሥታት ደግሞ በዚያ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን ለመታደግ መርከቦቻቸውን እና ጀልባዎቻቸውን አሰልፈዋል። ቱርክ እና ቻይና መርከቦቻቸውን ሲሞሉ ተመልክቻለኹ። አሜሪካ ገና ዜጎቿን ጠቅልላ አላወጣችም። ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ትናንት ተናገሩ እንደተባለው ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጡት “የዜጎቻቸው ደኅንነት” ነው። እንግዲህ የሊቢያውን የሰሞኑን ሁኔታ በመሰለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስትወድቅ አሜሪካዊ ከሆንክ መንግሥትህ ያወጣሃል፣ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ ደግሞ ፈጣሪ ብቻ ይደርስልሃል።

Wednesday, February 23, 2011

ዘመናዊ የሴቶች ባርነት በዱባይ - የኢትዮጵያውያቱ ሕይወት

ይህ የኢትዮጵያውያት እህቶቻችንን የዱባይ (የአረብ አገሮች) ሕይወት የሚያሳይ ዝግጅት ነው። ፕሮግራሙን ያቀረበው የጀርመን ቴሌቪዥን ሲሆን፣ አንዱ የበረታ ወገናችን በእንግሊዝኛ ወይም በአማርኛ ተርጉሞ እስኪያሳየን ድረስ ለጊዜው ጀርመንኛ የሚሞክሩ ብቻ የሚያዩት ነው።
Nightmare in Wonderland, Albtraum im Märchenland - Moderne Arbeitssklavinnen in Dubai
Albtraum im Märchenland - Moderne Arbeitssklavinnen in Dubai

Monday, February 21, 2011

Did I witness VOA being Hacked?

A while ago (7pm Eastern Time), I tried to open Voice of America website (http://www.voanews.com/) and amazingly come up with the picture I attached below. It looks like the website was hacked. It also says that following websites are also hacked by Iranians. 

Friday, February 11, 2011

አዬ አሜሪካ!

(ተስፋዬ)
በቅርቡ ነው የመጣሁት፡፡ እንደ መታደል ሆኖ አበባ ይዞ የሚቀበል ቤተሰብ ስለተቀበለኝ ዱላስ አውሮፕላን ማረፊያ ኧረ ውሃ በላኝ ብዬ አልጮሁኩም፡፡ ተመስገን ልበላ፤ ለካ ይህም አለ፡፡ እርግጥ በአሜሪካ ፍቅር ጥንብዝ ብዬ የሠከርኩ አልነበርኩም፡፡ ሰው ሆኖ ሆድ የማይብሰው የለምና አንዳንድ ቀን ሆድ ሲብሰኝ የነበርኩበትን ከተማ ብቻ ሳይሆን የምር የማልጨክንባትን እንደ ስዕለት ልጅ የምሳሳላትን ኢትዮጵያን ሳይቀር ጥዬ መውጣት እመኛለሁ፡፡

Wednesday, February 2, 2011

የአንባብያን አስተያየት

ወንድማችን ዲያቆን ኤፍሬም በቅድሚያ የከበረ ሠላምታዬ ይድረስህ። የተነሳው ርዕስ አዲስ ለመጡትም ሆነ ገና ወደ አሜሪካ ለመምጣት ላሰቡ ወገኖቻችን በጣም ጠቃሚ እንደሚሆን አምናለሁ። ምንም እንኳ ብዙዎች ወገኖቻችን የውጭ ሀገር ኑሮ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ ቢገለጽላቸውም፣ ያለ መታደል ሆኖ እውነታውን ላለመቀበል "እሱ ሀብታም እየሆነ እያየሁት እሱን እንዳልጋፋው፣ እሱን እንዳላስቸግረው፣ ሊረዳኝ ስላልፈለገ ብቻ ክፉ ክፉውን ያወራልኛል" በማለት ራሳቸውን ስለሚደልሉ ወይም ስለሚያሞኙ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ለአደጋ ሲጋለጡ ይስተዋላል። አንተም ወንድሜ በተለያዩ ምሣሌዎች ችግሮቹን ለማሳየት የበኩልህን ጥረት አድርገሃል። 

Tuesday, February 1, 2011

የአሜሪካ ኑሮ - በኢትዮጵያ አእምሮ

“ወፍ እንዳገሯ ትጮኻለች” የሚል የአበው (የእመው) ብሒል አለ። የትም ሄደች የት ጠባዩዋ እና ድምጿ፣ ዜማዋ እና ተፈጥሮዋ ያው እንዳገሯ ነው። ሰውስ ከወፍ ምን ይለያል? በሄደበት ሥፍራ እንዳገሩ ያዜማል፣ እንዳገሩ ይበራል። ይህ “እንደራሱ አገር፣ እንደራሱ ልማድ” መብረር አንዳንዴ የማይፈልጉትን፣ የማይፈቅዱትን መዘዝ ይዞ ይመጣል። “የአሜሪካ ኑሮ -  በኢትዮጵያ አእምሮ” ስለዚህ የምታወራ መጣጥፍ ናት።

Sunday, January 30, 2011

ድብርት

ምንድር ነው?
ደርሶ ልቤን ያከበደው፣
ጠይም ፊቴን ያከሰለው፣
ጥርሴን ከሣቅ የከለለው።

የዕንባ እናቴን ጠርቶ፣
ዓይኔን ደም ቀብቶ፣
ጉሮሮዬን በሳግ ሞልቶ፣
አንጀቴን በእጥፋት ቀንቶ፣
ደስታዬን በሐዘን የወጋው፣
ቀኔን ከጎዳና የጣለው፣
ምንድር ነው?
(ታኅሣሥ 17/93 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ) 

Saturday, January 29, 2011

“ጭንቅ አንችልም”

በዚህ ባለፈው ሰሞን በፍጥነት የጣለ የበረዶ መዓት የምኖርበትን አካባቢ አሽመድምዶት ነበር። ለነገሩ ይኼንን ያህል ብዙ ጫማ በረዶ ጥሎ ሳይሆን ከሜትሮሎጂው ግምት ውጪ  እና ከጠበቁት ፍጥነት በላይ ለአንድ ሙሉ ቀን በመጣሉ፣ በረዶ በመጥረግ እና በተመሳሳይ ሥራ ላይ ሊሠማሩ የሚገባቸው ሰዎች በመዘናጋታቸው ነው ተብሏል።  የመጀመሪያውን ቀን የምኖርበት አፓርታማ መብራት ሳይቋረጥበት ለመቆየት የበቃ ቢሆንም በሁለተኛው ቀን ግን መብራት ማግኘት አልቻልንም። እናም መብራት ሲጠፋ ቀስ በቀስ እያለ ቤታችን መቀዝቀዝ ጀመረ። ሻይ እንዳናፈላ ምድጃው አይሠራም። ወደ ውጪ እንዳንወጣ በረዶው እና የአየሩ ጠባይ በጣም አስቸጋሪ ነው።

Tuesday, January 25, 2011

ስንብት

ስንብት ጥሩ ነው።
ካልተሰናበቱ
ካልሄዱ ካልራቁ፣
ሌላ አገር ሌላ ሰው ካላጠያየቁ፣
ሌላ ካል’ለመዱ፣
ባዩት ተደስቶ
ለዚያው ተጣጥሮ በዚያው መወሰኑ፣
አይናፋርነት ነው ለሕይወት መቅለስለስ፣
ያው በሻ ጉራ በባዶ መኮፈስ።

ልጅነት … ትዝታ

ትዝ አለኝ ትናንቴ፣
ድኼ ያደግሑበት ቤቴ።

ያሣለፍኩት ጊዜ …
ውኃ ተራጭቼ፣
ወርጄ ወጥቼ፣
ኳስ አንከባልዬ፣
አባሯ መስዬ፣
አቧራ አክዬ።

Monday, January 17, 2011

ትልልቆቹ ወዴት ሄዱ?

በፈረንጆቹ የ2010 መጨረሻ የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ለ25 ዓመታት የዘለቀ አንድ ታዋቂ ፕሮግራም አጥቷል። ከ1985 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲያቀርብ የነበረው አዘጋጇ ጡረታ ወጥቷል። ሌላዋ ታዋቂ ጋዜጠኛም ከ1986 ጀምሮ ስታስተላልፍ የነበረውን ፕሮግራም አብቅታለች። ላሪ ኪንግ እና ኦፕራ ዊንፍሬይ (Larry King and Oprah Winfrey) ለ25 እና ለ24 ዓመታት የዘለቁ ፕሮግራሞችን ሲያስተላልፉ  የቆዩ ሁለት የአሜሪካ ጋዜጠኝነት ምልክቶች ናቸው።

Monday, January 10, 2011

የጠፋ አእምሮ ፍለጋ

 ስቲፈን ኮልቤ (Stephen Colbert) እና ጆን ስቱዋርት (Jon Stewart) 
ይህንን መጣጥፍ በማዘጋጅበት ቀን በአሜሪካ “የአማካይ ዘመን ምርጫ” (Mid Term election) የሚባለው ምርጫ ዋዜማ ነው። ቴሌቪዥኑም፣ ሬዲዮውም፣ ጋዜጣና መጽሔቱም ሆነ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የላቸውም የሚባሉ የኮሜዲ ዝግጅቶች ሳይቀሩ ርእሰ ጉዳያቸው ይኸው የአማካይ ዘመን ምርጫ ነው። ፖለቲከኞቹ አንዱ ከአንዱ በልጦ እና ልቆ ለመገኘት የማያደርገው ጥረት የለም።

Ethiopian Orthodox Tewahedo Christian Kid in Austin USA Praying in Geez,

Sunday, January 9, 2011

የገና (የልደት) በዓል አከባበር (Part 2)

የተለበዱ (የተሸፈኑ) መጻሕፍት

ከዕለታት አንድ ቀን ከቤቴ ወደ ትምህርት ቤቴ ስጓዝ ከገጠመኝ ገጠመኝ ልጀምር። ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ውስጥ የሆነ ታሪክ ነው። ሁል ጊዜ ከቤት ተነሥቼ ከምሠራበት ቦታ ለመድረስ ከ45 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ይፈጅብኛል። አንድ አስፓልት- ለአስፓልት የምትሄድ የኤሌክትሪክ ባቡር (Tram)፣ አንድ በምድር ለምድር እና በውጪም ገባ ወጣ እያለች የምትሄድ ባቡር (S-Bahn) እንዲሁም አንድ የምድር ለምድር ባቡር (U-Bahn) እና አንድ አውቶቡስ በየቀኑ እይዛለኹ። ስጓዝባቸው ግን እንዲህ አሁን እንዳልኩት የተንዛዛ እና አሰልቺ አልነበረም።

የገና (የልደት) በዓል አከባበር (Part I)

የቃላት ጨዋታ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ ኅዳር 11/93 ዓ.ም)

የቃላት ጨዋታ፤
ከልብ መራቂያ ቱማታ፤
ስንተዋወቅ፣
ልንተናነቅ፣

Saturday, January 8, 2011

“ቻይና ታውን” እና “ሊትል ኢትዮጵያ”

Chinatown, San Francisco
ቻይናውያን በሄዱባቸው ሀገሮች በሙሉ የሚቆሮቁሯቸው እና ከእስያ እስከ አውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ እስከ ጃፓን በመላው ዓለም የሚገኙ ሰፈሮች “ቻይና ታውን” (Chinatown) ይባላሉ። በምስራቅ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በአሜሪካ (ካናዳን ጨምሮ)፣ በአውስትራሌዢያ (Australasia፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ እስያ ለማለት ነው) እና አውሮፓ ቻይና ታውኖች የተለመዱ ናቸው። የቻይና ባህል እና ንግድ ማዕከላት ሆነው ያገለግላሉ። ጥራታቸውም ከአካባቢ አካባቢ፤ ከሀገር ሀገር ይለያያል። አንዳንዶቹ “ቻይና ታውኖች” በንግድ ተኮር ቱሪዝም ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሥራ ፍለጋ የሚሰባሰቡ ሥራ ፈላጊ እና ለፍቶ አዳሪ ቻይናውያን (ቻይናዎች) መኖሪያዎች ናቸው።

የተዘመረላቸው እና ያልተዘመረላቸው ጀግኖች

አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት። ባለሥልጣን አይደሉም ወይም ታዋቂ እና ዝነኛም አይደሉም። አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ተርታ ዜጋ (ተራ ዜጋ ላለማለት ነው) ነዎት እንበል። እናም በሕዝብ ትራንስፖርት ሊጠቀሙ አውቶብስ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ወይም ባቡር ውስጥ ገብተዋል እንበል። መምጣትዎን በለበሱት የሥራ ልብስ ወይም በመታወቂያዎ ያወቁት አስተናጋጆች ለሀገርዎ ስለሚሰጡት አገልግሎት ከበሬታ በመስጠት ጠብ-እርግፍ ብለው ቢያስተናግዱዎት፣ ቢያመሰግኑዎት ምን ይሰማዎታል? ይህንን ይያዙልኝ እና ወደ አንድ ገጠመኜ ልውሰድዎት።

ጫማዪቱ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ ጥቅምት 7/1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)
ብቅ ቢል አውራ ጣቱ፣
ባይሸፈን ንቃቃቱ፣
ከእግሩ ግን አለች ጫማዪቱ።
ሶሏ እጅግ ቢሳሳ፣
ተረከዟ ቢበሳ፣
ጣቱን ባትሸፍን፣
ካቧራ ባታድን፣
ዉሃ እንኳን ባታግድ ቀለምም ባያምራት፣
ጣቶቹን ባታተርፍ ከመንገድ እንቅፋት፣
ማሠሪያ ባይኖራት፣
ሊስትሮ ባያውቃት፣
መጫሚያ መሆኗን እኮ ማን ሊነፍጋት?

Friday, January 7, 2011

ስብሰባ

(ኤፍሬም እሸቴ)
የነገር ፀጉር መሰንጠቅ የነገር ዝተት ዘትቶ፤
የነገር ዘባተሎ መቅደድ የነገር ዘባተሎ ሰፍቶ፤
የነገር ብልት ማወራረድ የነገር ጭቅና አውጥቶ፤
ጠቢብና ሊቅ መሆንህ በዚህ ከሆነ የሚለካ፤
ያልተዘራውን መኸር አጭደህ ያልተፈጨውን ዱቄት አቡካ።
(ኅዳር 3/93 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)

ምን ዓይነት “ኦርቶዶክስ” ነን?

A picture I took from St.Emmanuel Church
in Berlin Germany
“ፌስቡክ”ን መጠቀም ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሰዎች “ሃይማኖት” የሚለው ቦታ ላይ የሚያስቀምጡትን ስመለከት እንዲሁም አንዳንድ የማላውቃቸው ሰዎች ወይም “የፌስቡክ ጓደኝነት” የሚጠይቁኝ ወዳጆቼ እነማን መሆናቸውን ለማወቅ የግል ማኅደራቸውን እና ማንነታቸውን ወደሚያሳየው ቦታ ስገባ እና ስለ ሃይማኖታቸው ሳነብ የሚገርም ነገር አይቻለኹ። ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ደግሞ ተደጋጋሚነቱ ነው። እና እነዚህ ወዳጆቼ ሃይማኖት የሚለው ሥፍራ ላይ ሲጽፉ “ግሪክ ኦርቶዶክስ” ይላሉ። ሰዎቹ ግሪካውያን እንነዳልሆኑ ይታወቃል።

ምክንያተ ጡመራ Why Blogging?

ለትምህርትም ለኑሮም አገሬን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት፣ አዲስ አበባ ላይ፣ ከጓደኞቼ ጋር የምናስበውንም የምንጭረውንም ነገር የምናስቀምጥበት አንዳንድ ደብተር (Journal) ነበረን። ግጥምም፣ መጣጥፍም፣ ፖለቲካም፣ መዝናኛም … የሆነውን ሁሉ የምንጭርበት ነበር። ነገር ግን ልጫረው እንጂ ለጋዜጣም፣ ለመጽሔትም፣ ለሬዲዮም ሆኖ አያውቅም ነበር። በየወሩ ግድም ባለን የጓደኞች የሥነ ጽሑፍ ጉባዔ እዛው እቤታችን የምናነባቸውን ነገሮች የምናዘጋጅበትም ነበረን። አንድ ቀን ሰብስበን መድበል እናደርጋቸዋለን የሚል ሐሳብ ነበረ። እንዲያውም ኃላፊነቱን ለእህታችን ለጽላት (የዳንኤል ምሽት ይላል የገጠር ሰው) የሰጠናት ይመስለኛል። ከዚያ ኑሮ ሲበታትነን - እኔም አውሮፓዬ ሔድኹ። ዳንኤል ክብረትም፣ አሥራት ከበደም፣ መስፍን ነጋሽም፣ ተስፋዬ ሽብሩም፣ መርሻ አለኸኝም፣ አሉላ ጥላሁንም፣ ያሬድ ገ/መድኅንም ግርማ ወ/ሩፋኤልም፣   ሸዋደግ ሞላም፣ ታምሩ ለጋም፣ ትዕግስት ዳኜም፣ ጽላት ጌታቸውም፣ ምስራቅ ግዛው ሁሉም ሁሉም በኑሮ ጣጣ ሲጠመድ መድበላችንን ውሃ በላው ወይም መድበላችን ውሃ ጠጣ። 

ዕንባ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ ኅዳር 6/1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)

የደሜ አረቄ፣
ያወጣኹሽ ከልቡናዬ መቅደስ አፍልቄ፤
ተስፋ ሕይወቴን ጨምቄ፣
በሕይወት መጅ አድቅቄ፣
በሕይወት ወፍጮ ሰልቄ፣
በኑሮ እሳት አቃጥዬ፣
በ“ነገ ያልፍልሻል” አባብዬ፣
ዕንባዬ።

ኢንተርኔት አውሮፕላን ውስጥ

በዓለም ታዋቂው የኢንተርኔት መፈለጊያ ድርጅት ጉግል ሰሞኑን ባወጣው  ማስታወቂያ ላይ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ የሚመጡትን በዓላት አስመልክቶ በየትኛው የአየር በረራ ላይ ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ቃል ገብቷል። በዓላት ያላቸው በኖቬምበር ወር መጨረሻ ያለውን የ“ታንክስ ጊቪንግ” በዓል እና “ክሪስማስ”ን (በዓለ አኲቴት እና ገና) መሆኑ ነው። በነዚህ በዓላት ሰሞን ወገን ከወገኑ፤ ቤተሰብ ከቤተሰቡ ለመገናኘት በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በመንገድ ትራንስፖርቶች በሙሉ የሚነቃነቅበት ጊዜ ነው።

ወፍ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ መስከረም 29/1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)
የትኛው ቀበሌ የትኛው ወረዳ፣
ከየትኛው ቤት ነሽ ከየትኛው ጓዳ፣
አድራሻሽስ የት ነው መኖሪያ መንደርሽ?
አንቺን የሚፈልግ የት ነው የሚያገኝሽ?
ወጉ እንዳይቀርብሽ ቤትም ትሰሪያለሽ፣
ስንጥሮች ለቃቅመሽ አበባ ሰብስበሽ።
ወረዳ ባያውቅሽ ቀበሌ ቢረሳሽ፣
መዝገብ ባያሰፍርሽ ቁጥር ቢዘነጋሽ፤

ሁለቱ ክሪስማሶቻችን

ቴሌቪዥኑም፣ መብራቱም፣ ሰዉም በዓል በዓል ይላል። “ክሪስማስ” ቀደም ብሎ ነው የጀመረው ማለት ይቻላል። በፈረንጆቹ የኖቬምበር ወር መጨረሻ ላይ የሚከበረው ታዋቂው አሜሪካውያን በዓል “Thanksgiving” ወይም “በዓለ አኲቴት” (“የምሥጋና በዓል”) ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት ድረስ  አካባቢያችን  በሙሉ “በዐው’ዳመት” ስሜት ውስጥ ነው።  

Blog Archive