Sunday, January 30, 2011

ድብርት

ምንድር ነው?
ደርሶ ልቤን ያከበደው፣
ጠይም ፊቴን ያከሰለው፣
ጥርሴን ከሣቅ የከለለው።

የዕንባ እናቴን ጠርቶ፣
ዓይኔን ደም ቀብቶ፣
ጉሮሮዬን በሳግ ሞልቶ፣
አንጀቴን በእጥፋት ቀንቶ፣
ደስታዬን በሐዘን የወጋው፣
ቀኔን ከጎዳና የጣለው፣
ምንድር ነው?
(ታኅሣሥ 17/93 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ) 

Saturday, January 29, 2011

“ጭንቅ አንችልም”

በዚህ ባለፈው ሰሞን በፍጥነት የጣለ የበረዶ መዓት የምኖርበትን አካባቢ አሽመድምዶት ነበር። ለነገሩ ይኼንን ያህል ብዙ ጫማ በረዶ ጥሎ ሳይሆን ከሜትሮሎጂው ግምት ውጪ  እና ከጠበቁት ፍጥነት በላይ ለአንድ ሙሉ ቀን በመጣሉ፣ በረዶ በመጥረግ እና በተመሳሳይ ሥራ ላይ ሊሠማሩ የሚገባቸው ሰዎች በመዘናጋታቸው ነው ተብሏል።  የመጀመሪያውን ቀን የምኖርበት አፓርታማ መብራት ሳይቋረጥበት ለመቆየት የበቃ ቢሆንም በሁለተኛው ቀን ግን መብራት ማግኘት አልቻልንም። እናም መብራት ሲጠፋ ቀስ በቀስ እያለ ቤታችን መቀዝቀዝ ጀመረ። ሻይ እንዳናፈላ ምድጃው አይሠራም። ወደ ውጪ እንዳንወጣ በረዶው እና የአየሩ ጠባይ በጣም አስቸጋሪ ነው።

Tuesday, January 25, 2011

ስንብት

ስንብት ጥሩ ነው።
ካልተሰናበቱ
ካልሄዱ ካልራቁ፣
ሌላ አገር ሌላ ሰው ካላጠያየቁ፣
ሌላ ካል’ለመዱ፣
ባዩት ተደስቶ
ለዚያው ተጣጥሮ በዚያው መወሰኑ፣
አይናፋርነት ነው ለሕይወት መቅለስለስ፣
ያው በሻ ጉራ በባዶ መኮፈስ።

ልጅነት … ትዝታ

ትዝ አለኝ ትናንቴ፣
ድኼ ያደግሑበት ቤቴ።

ያሣለፍኩት ጊዜ …
ውኃ ተራጭቼ፣
ወርጄ ወጥቼ፣
ኳስ አንከባልዬ፣
አባሯ መስዬ፣
አቧራ አክዬ።

Monday, January 17, 2011

ትልልቆቹ ወዴት ሄዱ?

በፈረንጆቹ የ2010 መጨረሻ የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ለ25 ዓመታት የዘለቀ አንድ ታዋቂ ፕሮግራም አጥቷል። ከ1985 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲያቀርብ የነበረው አዘጋጇ ጡረታ ወጥቷል። ሌላዋ ታዋቂ ጋዜጠኛም ከ1986 ጀምሮ ስታስተላልፍ የነበረውን ፕሮግራም አብቅታለች። ላሪ ኪንግ እና ኦፕራ ዊንፍሬይ (Larry King and Oprah Winfrey) ለ25 እና ለ24 ዓመታት የዘለቁ ፕሮግራሞችን ሲያስተላልፉ  የቆዩ ሁለት የአሜሪካ ጋዜጠኝነት ምልክቶች ናቸው።

Monday, January 10, 2011

የጠፋ አእምሮ ፍለጋ

 ስቲፈን ኮልቤ (Stephen Colbert) እና ጆን ስቱዋርት (Jon Stewart) 
ይህንን መጣጥፍ በማዘጋጅበት ቀን በአሜሪካ “የአማካይ ዘመን ምርጫ” (Mid Term election) የሚባለው ምርጫ ዋዜማ ነው። ቴሌቪዥኑም፣ ሬዲዮውም፣ ጋዜጣና መጽሔቱም ሆነ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የላቸውም የሚባሉ የኮሜዲ ዝግጅቶች ሳይቀሩ ርእሰ ጉዳያቸው ይኸው የአማካይ ዘመን ምርጫ ነው። ፖለቲከኞቹ አንዱ ከአንዱ በልጦ እና ልቆ ለመገኘት የማያደርገው ጥረት የለም።

Ethiopian Orthodox Tewahedo Christian Kid in Austin USA Praying in Geez,

Sunday, January 9, 2011

የገና (የልደት) በዓል አከባበር (Part 2)

የተለበዱ (የተሸፈኑ) መጻሕፍት

ከዕለታት አንድ ቀን ከቤቴ ወደ ትምህርት ቤቴ ስጓዝ ከገጠመኝ ገጠመኝ ልጀምር። ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ውስጥ የሆነ ታሪክ ነው። ሁል ጊዜ ከቤት ተነሥቼ ከምሠራበት ቦታ ለመድረስ ከ45 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ይፈጅብኛል። አንድ አስፓልት- ለአስፓልት የምትሄድ የኤሌክትሪክ ባቡር (Tram)፣ አንድ በምድር ለምድር እና በውጪም ገባ ወጣ እያለች የምትሄድ ባቡር (S-Bahn) እንዲሁም አንድ የምድር ለምድር ባቡር (U-Bahn) እና አንድ አውቶቡስ በየቀኑ እይዛለኹ። ስጓዝባቸው ግን እንዲህ አሁን እንዳልኩት የተንዛዛ እና አሰልቺ አልነበረም።

የገና (የልደት) በዓል አከባበር (Part I)

የቃላት ጨዋታ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ ኅዳር 11/93 ዓ.ም)

የቃላት ጨዋታ፤
ከልብ መራቂያ ቱማታ፤
ስንተዋወቅ፣
ልንተናነቅ፣

Saturday, January 8, 2011

“ቻይና ታውን” እና “ሊትል ኢትዮጵያ”

Chinatown, San Francisco
ቻይናውያን በሄዱባቸው ሀገሮች በሙሉ የሚቆሮቁሯቸው እና ከእስያ እስከ አውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ እስከ ጃፓን በመላው ዓለም የሚገኙ ሰፈሮች “ቻይና ታውን” (Chinatown) ይባላሉ። በምስራቅ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በአሜሪካ (ካናዳን ጨምሮ)፣ በአውስትራሌዢያ (Australasia፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ እስያ ለማለት ነው) እና አውሮፓ ቻይና ታውኖች የተለመዱ ናቸው። የቻይና ባህል እና ንግድ ማዕከላት ሆነው ያገለግላሉ። ጥራታቸውም ከአካባቢ አካባቢ፤ ከሀገር ሀገር ይለያያል። አንዳንዶቹ “ቻይና ታውኖች” በንግድ ተኮር ቱሪዝም ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሥራ ፍለጋ የሚሰባሰቡ ሥራ ፈላጊ እና ለፍቶ አዳሪ ቻይናውያን (ቻይናዎች) መኖሪያዎች ናቸው።

የተዘመረላቸው እና ያልተዘመረላቸው ጀግኖች

አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት። ባለሥልጣን አይደሉም ወይም ታዋቂ እና ዝነኛም አይደሉም። አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ተርታ ዜጋ (ተራ ዜጋ ላለማለት ነው) ነዎት እንበል። እናም በሕዝብ ትራንስፖርት ሊጠቀሙ አውቶብስ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ወይም ባቡር ውስጥ ገብተዋል እንበል። መምጣትዎን በለበሱት የሥራ ልብስ ወይም በመታወቂያዎ ያወቁት አስተናጋጆች ለሀገርዎ ስለሚሰጡት አገልግሎት ከበሬታ በመስጠት ጠብ-እርግፍ ብለው ቢያስተናግዱዎት፣ ቢያመሰግኑዎት ምን ይሰማዎታል? ይህንን ይያዙልኝ እና ወደ አንድ ገጠመኜ ልውሰድዎት።

ጫማዪቱ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ ጥቅምት 7/1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)
ብቅ ቢል አውራ ጣቱ፣
ባይሸፈን ንቃቃቱ፣
ከእግሩ ግን አለች ጫማዪቱ።
ሶሏ እጅግ ቢሳሳ፣
ተረከዟ ቢበሳ፣
ጣቱን ባትሸፍን፣
ካቧራ ባታድን፣
ዉሃ እንኳን ባታግድ ቀለምም ባያምራት፣
ጣቶቹን ባታተርፍ ከመንገድ እንቅፋት፣
ማሠሪያ ባይኖራት፣
ሊስትሮ ባያውቃት፣
መጫሚያ መሆኗን እኮ ማን ሊነፍጋት?

Friday, January 7, 2011

ስብሰባ

(ኤፍሬም እሸቴ)
የነገር ፀጉር መሰንጠቅ የነገር ዝተት ዘትቶ፤
የነገር ዘባተሎ መቅደድ የነገር ዘባተሎ ሰፍቶ፤
የነገር ብልት ማወራረድ የነገር ጭቅና አውጥቶ፤
ጠቢብና ሊቅ መሆንህ በዚህ ከሆነ የሚለካ፤
ያልተዘራውን መኸር አጭደህ ያልተፈጨውን ዱቄት አቡካ።
(ኅዳር 3/93 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)

ምን ዓይነት “ኦርቶዶክስ” ነን?

A picture I took from St.Emmanuel Church
in Berlin Germany
“ፌስቡክ”ን መጠቀም ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሰዎች “ሃይማኖት” የሚለው ቦታ ላይ የሚያስቀምጡትን ስመለከት እንዲሁም አንዳንድ የማላውቃቸው ሰዎች ወይም “የፌስቡክ ጓደኝነት” የሚጠይቁኝ ወዳጆቼ እነማን መሆናቸውን ለማወቅ የግል ማኅደራቸውን እና ማንነታቸውን ወደሚያሳየው ቦታ ስገባ እና ስለ ሃይማኖታቸው ሳነብ የሚገርም ነገር አይቻለኹ። ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ደግሞ ተደጋጋሚነቱ ነው። እና እነዚህ ወዳጆቼ ሃይማኖት የሚለው ሥፍራ ላይ ሲጽፉ “ግሪክ ኦርቶዶክስ” ይላሉ። ሰዎቹ ግሪካውያን እንነዳልሆኑ ይታወቃል።

ምክንያተ ጡመራ Why Blogging?

ለትምህርትም ለኑሮም አገሬን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት፣ አዲስ አበባ ላይ፣ ከጓደኞቼ ጋር የምናስበውንም የምንጭረውንም ነገር የምናስቀምጥበት አንዳንድ ደብተር (Journal) ነበረን። ግጥምም፣ መጣጥፍም፣ ፖለቲካም፣ መዝናኛም … የሆነውን ሁሉ የምንጭርበት ነበር። ነገር ግን ልጫረው እንጂ ለጋዜጣም፣ ለመጽሔትም፣ ለሬዲዮም ሆኖ አያውቅም ነበር። በየወሩ ግድም ባለን የጓደኞች የሥነ ጽሑፍ ጉባዔ እዛው እቤታችን የምናነባቸውን ነገሮች የምናዘጋጅበትም ነበረን። አንድ ቀን ሰብስበን መድበል እናደርጋቸዋለን የሚል ሐሳብ ነበረ። እንዲያውም ኃላፊነቱን ለእህታችን ለጽላት (የዳንኤል ምሽት ይላል የገጠር ሰው) የሰጠናት ይመስለኛል። ከዚያ ኑሮ ሲበታትነን - እኔም አውሮፓዬ ሔድኹ። ዳንኤል ክብረትም፣ አሥራት ከበደም፣ መስፍን ነጋሽም፣ ተስፋዬ ሽብሩም፣ መርሻ አለኸኝም፣ አሉላ ጥላሁንም፣ ያሬድ ገ/መድኅንም ግርማ ወ/ሩፋኤልም፣   ሸዋደግ ሞላም፣ ታምሩ ለጋም፣ ትዕግስት ዳኜም፣ ጽላት ጌታቸውም፣ ምስራቅ ግዛው ሁሉም ሁሉም በኑሮ ጣጣ ሲጠመድ መድበላችንን ውሃ በላው ወይም መድበላችን ውሃ ጠጣ። 

ዕንባ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ ኅዳር 6/1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)

የደሜ አረቄ፣
ያወጣኹሽ ከልቡናዬ መቅደስ አፍልቄ፤
ተስፋ ሕይወቴን ጨምቄ፣
በሕይወት መጅ አድቅቄ፣
በሕይወት ወፍጮ ሰልቄ፣
በኑሮ እሳት አቃጥዬ፣
በ“ነገ ያልፍልሻል” አባብዬ፣
ዕንባዬ።

ኢንተርኔት አውሮፕላን ውስጥ

በዓለም ታዋቂው የኢንተርኔት መፈለጊያ ድርጅት ጉግል ሰሞኑን ባወጣው  ማስታወቂያ ላይ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ የሚመጡትን በዓላት አስመልክቶ በየትኛው የአየር በረራ ላይ ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ቃል ገብቷል። በዓላት ያላቸው በኖቬምበር ወር መጨረሻ ያለውን የ“ታንክስ ጊቪንግ” በዓል እና “ክሪስማስ”ን (በዓለ አኲቴት እና ገና) መሆኑ ነው። በነዚህ በዓላት ሰሞን ወገን ከወገኑ፤ ቤተሰብ ከቤተሰቡ ለመገናኘት በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በመንገድ ትራንስፖርቶች በሙሉ የሚነቃነቅበት ጊዜ ነው።

ወፍ

(ኤፍሬም እሸቴ፤ መስከረም 29/1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ)
የትኛው ቀበሌ የትኛው ወረዳ፣
ከየትኛው ቤት ነሽ ከየትኛው ጓዳ፣
አድራሻሽስ የት ነው መኖሪያ መንደርሽ?
አንቺን የሚፈልግ የት ነው የሚያገኝሽ?
ወጉ እንዳይቀርብሽ ቤትም ትሰሪያለሽ፣
ስንጥሮች ለቃቅመሽ አበባ ሰብስበሽ።
ወረዳ ባያውቅሽ ቀበሌ ቢረሳሽ፣
መዝገብ ባያሰፍርሽ ቁጥር ቢዘነጋሽ፤

ሁለቱ ክሪስማሶቻችን

ቴሌቪዥኑም፣ መብራቱም፣ ሰዉም በዓል በዓል ይላል። “ክሪስማስ” ቀደም ብሎ ነው የጀመረው ማለት ይቻላል። በፈረንጆቹ የኖቬምበር ወር መጨረሻ ላይ የሚከበረው ታዋቂው አሜሪካውያን በዓል “Thanksgiving” ወይም “በዓለ አኲቴት” (“የምሥጋና በዓል”) ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት ድረስ  አካባቢያችን  በሙሉ “በዐው’ዳመት” ስሜት ውስጥ ነው።  

Blog Archive