Friday, January 7, 2011

ሁለቱ ክሪስማሶቻችን

ቴሌቪዥኑም፣ መብራቱም፣ ሰዉም በዓል በዓል ይላል። “ክሪስማስ” ቀደም ብሎ ነው የጀመረው ማለት ይቻላል። በፈረንጆቹ የኖቬምበር ወር መጨረሻ ላይ የሚከበረው ታዋቂው አሜሪካውያን በዓል “Thanksgiving” ወይም “በዓለ አኲቴት” (“የምሥጋና በዓል”) ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት ድረስ  አካባቢያችን  በሙሉ “በዐው’ዳመት” ስሜት ውስጥ ነው።  


Thanksgiving(“የምሥጋና በዓል”) የቤተሰብ በዓል ነው። በዚህ በአሜሪካ ከክሪስማስ (ገና) ቀጥሎ እንደዚህ የሚከበር ታዋቂ በዓል ያ አይመስለኝም። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ዛሬዋ አሜሪካ የመጡ ስደተኞች የጀመሩት ይህ በዓል መነሻውና ታሪኩም ከነዚሁ ስደተኞች ጋር የተያያዘ ነው።

ከአውሮፓ የመጡት ስደተኞቹ በአዲሱ አገራቸው የገጠማቸው ችግር ከፍ ለ ነበር። በተለይም ሰብሉ አልይዝላቸው በማለቱ የመጀመሪውን ዓመት ብዙ መከራ ተቀብለዋል። አንድ መጣጥፍ እንደሚጠቅሰው በ1621 ከአውፓ ከመጡት መካከል አንድ ሦስተኛው በወቅቱ ሕይወታቸውን እስከማጣት ደርሰው ነበር። የተረፉትም ቢሆኑ ከሚቀጥለው ዓመት ለመድረስ የቻሉት በአሜሪካ ጥንታውያን ነዋሪዎች (ቀይ ሕንዶች) ርዳታ ነበር።

በሚቀጥለው ዓመት ግን አዝመራው ያዘላቸው ምርቱም እጅግ ግሩም ሆነ። በዚህ የተደሰቱት ስደተኞች እና ጥንታውያን-አሜሪካውያን (Red Indians) ይህንን ላደረገላቸው ፈጣሪ የሦስት ቀን ምሥጋና አቀረቡ። ይህም መነሻ ሆኖ በዓሉን ማክበር ጀመሩ። ይሁን እንጂ አገራዊ በሆነ መልክ ከመከበሩ በፊት 50 ዓመታት አልፈው ነበር።  ከዚያ በኋላም ቢሆን በዓሉ ጊዜ እንደፈቀደው ሲከበር የቆየ ቢሆንም አሁን ባለው መልኩ የአገሪቱ ዐውደ ዓመት ሆኖ እንዲከበር የተወሰነው በ20ኛው መ/ክ/ዘመን አጋማሽ (በ1941) በፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ጊዜ ነው።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ እነሆ በየዓመቱ ኖቬምበር (November) የመጨረሻው ሐሙስ ላይ የምሥጋና በዓሉ ይከበራል። በዓሉ እምነትና ቋንቋ ሳይለይ በሁሉም አሜሪካውያን ዘንድ የሚከበር በዓል ነው። እኛ ኢትዮጵያውያኑ ምን ያህል እንደምናከብረው ለመናገር ትንሽ ቢከብድም በእርግጠኝነት ግን ከወንደላጤዎቹ ይልቅ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች በዓሉን የበለጠ የማክበር ዕድል ይኖራቸዋል።

ወላጅ “ደግሞ ይሄ የምን በዓል ነው?” ብሎ ናቅ-ናቅ፣ ተወት-ተወት ላድርገው ቢል እንኳን ልጆቹ መቆሚያ መቀመጫ ስለሚያሳጡት ለእነርሱ ብሎ ማክበሩ አይቀርም። በዓሉ ትልቅ የወፍ ዘር “Turkey” (“የቱርክ ዶሮ?”) በመብላት የሚከበር ሲሆን አሠራሩ መቸም ለእኛ ለኢትዮጵያውያኑ ባዕድ ነው። እንኳን መሥራቱ መብላቱም ላይ ቢሆን ብዙዎቻችን አንደፍረውም። ብዙ ወዳጆቼ “ደግሞ ብለን ብለን አሞራ እንብላ እንዴ?” ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ። እኔም ብሆን ቀምሼው አላውቅም። በዓሉ በእኛ “የጾመ ነቢያት/ የገና ጾም” ወቅት ስለሚሆን ለመሞከር እንኳን ዕድሉን አላገኘኹም።  ልጄም ገና ሕጻን ስለሆነ “ካላመጣችሁ” ለማለት አልደረሰም።

ይህ በዓል አከባበሩ ብቻ ሳይሆን የሚከበርበት ምክንያቱ ደስ ይለኛል። “የምስጋና በዓል” ሐሳቡ ራሱ ደስ አይልም? የሰው ልጅ ላመስግን ካለ የሚያመሰግንበት ብዙ ምክንያት አለው። የሚመሰገኑም ብዙ ሰዎች ይኖራሉ። የፈጣሪን ምስጋና ሳንነካ ማለቴ ነው። ፈረንጆቹ የማመስገን “እጥረት” የሌለባቸው ለዚህ ይሆን?

ብዙ ጊዜ በየሱቁም፣ በየመንገዱም “ታንኪው፣ ታንኪው” መባባል የተለመደ ነው። እንደ “ታንኪው” እና “ኤክስኪውዝ ሚ” በብዛት የሚጠራ ቃል ያለ አይመስለኝም። ለትንሹም ለትልቁም ታንኪው ነው። ታዲያ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ “ውሸታቸውን ነው፤ ዝም ብለው ነው ታንኪው የሚያበዙት” ሲሉ ይተቿቸዋል። ነገር ግን እነርሱን እንተች እንጂ ራሳችን “ታንኪው” ለማለት፣ ስለተደረገልን ነገር ለማመስገን ጎሮሯችንን ያንቀናል። ምናልባትም የምስጋና እጥረት ያለብን አይመስላችሁም?

ታዋቂው ደራሲ፣ ገጣሚና የሥነ ጽሑፍ መምህር ደበበ ሰይፉ በአንድ ወቅት እንዲህ አደረገ። በክፍሉ ውስጥ ካሉት ተማሪዎች አንዲት ቆንጆ ልጅ አስነስቶ “እስቲ ይቺን ልጅ መርቋት፣ አመስግኗት” አለ አሉ። ተማሪዎቹ መጠነኛ የምስጋናና የሙገሳ ቃላት ጣል ጣል አደረጉባት።

መምህሩ ቀጥሎ ያቺኑ ልጅ “እስቲ ትንሽ ስደቧት” አለ አሉ። የነገሩኝ ጓደኞቼ በትክክል ነግረውኝ ከሆነ ተማሪው ስድቡን በግድ ነበር ያቆመው። አንዱ በአንዱ ላይ እየተነሣ የሽርደዳውን መዓት አወረዱባት። መምህሩ የፈለገው “ለምስጋና ቃላት የሚያጥሩን፣ ለሽርደዳ እና ለስድብ ግን የምንበረታ” መሆናችንን በተግባር ማሳየት ነው። ተሳክቶለታል።

ነፍሳቸውን በአፀደ ቅዱሳን ያስድርልን እና ሊቁ የቤተ ክህነት ሰው ሊቀ ጉባዔ አባ አበራ በቀለ ስለ “የምስጋና ቀን” አድንቀው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እርሳቸው የአውሮፓውን፣ የአሜሪካውንም፣ የኢትዮጵያውንም ዓለም በትምህርት እና በኑሮ ደህና አድርገው ስለሚያውቁት የ“ምስጋና በዓል” ምስጢሩም ትርጉሙም ያስደንቃቸው ነበር። እናመስግን ብለን ካሰብን ፈጣሪንም፣ እንደየደረጃቸው ሌሎችንም የምናመሰግንበት ብዙ ብዙ ጉዳይ አለን።


በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ታሪክ አለ (የሉቃስ ወንጌል 17፡11-19)። የአስር ድውያን (በሽተኞች ታሪክ)። ሁሉም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው እንዲፈውሳቸው ለመኑት። ይፈወሱ ዘንድ ሄደው ራሳቸውን ለካህን እንዲያሳዩ አዘዛቸው። ሲሄዱም ተፈወሱ። ነገር ግን ከተፈወሱት መካከል ተመልሶ ስላደረገለት ነገር ያመሰገነው አንዱ ብቻ ነበር። የቀሩት ዘጠኙ ግን የያዙትን ይዘው፣ በዚያው እንደወጡ ቀሩ። ለልመና ቸኩለው፣ ለምስጋናው ጊዜ ጠፉ።

የምስጋናውን በዓል ተከትሎ የሚመጣው ደግሞ በዓለ ገና (ክሪስማስ) ነው። በዓመተ እግዚእ (Anno DomineAD or A.D) የሚቆጥሩት ምዕራባውያን እና በዓመተ ምሕረት የምንቆጥረው የምሥራቅ ክርስቲያኖች በተለያየ ጊዜ እናከብራለን። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ “ዕድለኞች ስለሆንን” ሁለቱንም እናከብራለን፤ በዚህ በፈረንጁ አገር።

የምዕራብ ክርስቲያኖች የሚባሉት ካቶሊኮች እና ፕሮቴስታንቶች ለልደት (ክሪስማስ) ከፍ ያለ ሥፍራ ስለሚሰጡ የበዓላት በኵርና አውራ አድርገው ያከብሩታል። ከእምነትም ባለፈ በባህላዊ አከባበሩም ቢሆን እንደ ገና “ክሪስማስ” የሚሆን የለም። በእኛ በምሥራቅ ሀገሮች ክርስቲያኖች (በምሥራቅ እና በኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች) በኩል ደግሞ ትንሣኤ (ፋሲካ) ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል። ይህ ማለት ግን ገና (“ክሪስማስ”) ምንም ቦታ የለውም ማለት አይደለም።

የኢትዮጵያ ሊቃውንት እንደሚናገሩት ከሆነ ከገና ይልቅ ለፋሲካ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጡበት ምክንያቱ በቤተ ልሔም የተወለደው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኋላ በመስቀል እንደተሰቀለ በዚያው ቢቀር ኖሮ፤ ሞትንና በመቃብር መበስበሰን አጥፍቶ ባይነሣ ኖሮ ዛሬ ክርስትና የሚባል እምነት ባልኖረ ነበር ስለሚሉ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በቀራንዮ ተሰቅሎ፣ ሞትን ድል ነሥቶ የተነሣው ጌታ ከሁሉ ይልቅ ኃይሉን ለገለጠበት ለትንሣኤው የበለጠ ሥፍራ ይሰጣሉ። በጠቅላላው ግን ልደትና ጥምቀትን የመሳሰሉት በዓላት ዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ተብለው በታላቅ ሁኔታ ይከበራሉ።

“ክሪስማስ” የሥጦታ በዓል ነው። ሥጦታ የማያገኝም ሆነ ሥጦታ የማይሰጥ ሰው የለም። በተለይ ልጆች በጉጉት ነው የሚጠብቁት። ሥጦታውን የሚያመጣላቸው ደግሞ ባለ ጺመ ነጩ አረጋዊ “ሳንታ” ነው። ሳንታ በገና ዋዜማ ሌሊት ወደቤት ገብቶ ሥጦታቸውን ከክሪስማስ ዛፉ ሥር ያስቀምጥላቸዋል ተብሎ ይነገራቸዋል። ወላጆች ደግሞ የገዙትን የተለያየ ሥጦታ ጥሩ አድርገው ሸፍነው ማታዉኑ ዛፉ ሥር ማስቀመጥ አለባቸው።

የእኛ የኢትዮጵያውያኑ ልጆች ይህንን ታሪክ ሰምተው የሚመጡት ከትምህርት ቤት ወይም ከቴሌቪዥን ነው። እኛ እንኳን ልንነግራቸው ብዙዎቻችን ታሪኩን በቅጡ አናውቀውም። ታሪኩን የሰማው ልጅ እቤት ሲገባ ወላጆቹን መጠየቅ ይጀምራል። ስለዚህ ወላጅ ሳይወድ በግዱ ያላደገበትን “የሳንታ ታሪክ” እያጠና ሥጦታውን በገና ዛፍ ሥር ይደረድራል። ልጅ በጠዋት ይነሣና ሥጦታውን ከገና ዛፍ ስር አንስቶ በደስታ ወደ መኝታ ቤት ገብቶ ለወላጆቹ ለማሳየት ይሮጣል።

በዓላቱ በዚህ በፈረንጁ ዓለም የሚደምቁት አንድም “ቢዝነስነታቸው” የበረታ ስለሆነ ነው። በዚህ ሰሞን ሸማቹ ሕዝብ ገንዘቡን አውጥቶ እንዲገዛ በየማስታወቂያው ይወተወታል። በርግጥም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለግብይት ስለሚውል ኢኮኖሚውን ያንቀሳቅሰዋል። ከጥቃቅን አሻንጉሊት እስከ መኪና ገበያ፣ በየሱቆቹ ከሚደረግ ግብይት እስከ ኦን-ላይን ሽያጭ ድረስ በቀንም በሌሊትም ገበያው ይደራል። እኛም ለወዳጅም ለዘመድም የሚሆን ነገር ወይም ወደ አገር ቤት የምንልከው ነገር ፍለጋ ገበያዎቹን እናስሳለን። ካልቻልንም ከኢንተርኔቱ እንሸምታለን። ከዚያም ሁለት ገናችንን እናከብራለን።

ቸር ያሰንብተን።


© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።

8 comments:

Anonymous said...

So magnificent ........

Anonymous said...

Dn Epherem Enquank Le Berhane Le detue Adresehe. I was so exicited when i got your blog hope we are gonne read a lot . keep sharing us .

Anonymous said...

ዲ/ን ኤፍሬም
እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሰህ!!!
አንባብያን ካለን የመማር እድላችንን ከጊዜ ጊዜ እየሰፋልን ነው፡፡ ካሉት መደረኮች የአንተ ሲጨመር ደግሞ እድሉን የላቀ ደርገዋል፡፡ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተቀምጣችሁ ያስተዋላችሁትን፣ያነበባችሁትን፣የምታውቁትን ወዘተ በማጠናቀር እኛ ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ በአንድ ቦታ ተቀምጠን በመረጃ መረብ ታግዘን በኮምፑተር መስኮት እንድናነበው እና የግንዛቤ ለውጥ እንድናገኝ ስላደረገልን እግዚአብሔር አማላካችን የተመሰገነ ይሁን፡ ለእናንተም ባደረጋችሁት መጠን ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ በቀረበው ትንታኔ በከፊል ብስማማም ፤እኛ ኢትዮጵያውያን እና ምዕራባውያን በዓላትን የምናከብርበት ላህይ ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያውን ዘንድ የገና በዓል ሲከበር ምንም በዓድ አምልኮ ያልተቀላቀለበት፤ የጌታችንን ልደት በትክክል በማስብ የሚደረግ ከመሆኑም በላይ ብእርግጥም የሚንጸባርቅ ነው፡፡ይህን ስል ግን ፈፅሞ የተዛባ አከባበር የለም ማለቴ አይደለም ነገር ግን በአብዛኛው እንጂ፡፡ የገና ዛፍ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ምናችንም አይደለም እሰከገባኝ ድረስ፡፡ ምን አልባት ጽሁፍህ የሚቀጥል ሆኖ የምትለው ነግር ካለ እንጂ በዚህ ክፍል የተንፀባረቀው ግን እኛ ኢትዮጵያውያን በምዕራቡ ዓለም የአከባበር ስርዓት ብንሄድም ያለውን ችግር ለይቶ የሚያስቀምጥ አልመሰለኝም፡፡ እንዲህ የምለው የሁላችሁም የጡመራ መነሻ ለእና ለወገኖቻቸሁ መልካሙን እና የማይገባውን በመለየት እንድንጠቀም ማስገንዘብ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ስለዚህ የራሳችን እንቁ የሆኑ ሰማያዊም ጭምር ሃይማኖታው፣ባህላዊ እና ሀገራዊ ትውፊታችንን እና ስርዓቶቻችንን ገንዘባችን እንድናደርግ ከሌሎች ሀገራት እያነፃፀራቸሁ ብታስገንዝቡን መልካም ነው እላለሁ፡፡ በእርግጥ የሚጠቅሙን ከሆነ የሌሎች ሀገራት ልምድ አታካፍሉን የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ የራሳችንን ባህል ፣ሃይማኖትናትውፊት እየጣልን የምዕራባውያንን ናፋቂ በሆነበት በዚህ ሰዓት ክፍት( ማሰሪያ የሌለው የመሰለኝ) አደጋው የከፋ ይመስለኛል፡፡ በተረፋ ዲ/ን ሌሎች ጽሁፎችህን ወድጄልሀለሁ፡፡ አምላክ በስራህ ሁሉ አይለይህ!!!
ኃይለ ሚካኤል

Anonymous said...

Dear Dn.Ephrem, I agree with your story for the most part, but there are many Ethiopians who do know the true story behind "santa claus". the name Santa claus "children friend" came from St.Nicholas who was a Greek saint and bishop. Please google the rest of the story and let your reader know in your way( BTW I like your word choices). Thanks

Anonymous said...

Nice to see u here Dn Ephrem
@ኃይለ ሚካኤል

መልካም ብለሃል ነገር ግን ልዩነቱን ማወቅ ክፋት ባይኖረውም ልዩነቱን አውቆ አተቃውሞ፣ የእኛ ብቻ ትክክል ነው ለማለት ከሆነ ግን አደጋ አለው። ስለዚህ ለእውቀት ብቻ ያታወቅ ባይ ነኝ

ዲሜጥሮስ

Anonymous said...

Dear Dn Ephrem,

Happy to get your blog!

It is good but ...Is it logical to follow western culture(Santa claues) and give presents to our kids? Where you boy grows are you celebrating Dec.25 as a Christmas day? Or are you celebrating both? It would better to tell the meaning of Santa and its relevance according to EOTC teaching than blaming us.

John said...

እድሜ ለንስሃ ዘመን ለፍስሐ የምትሰጠን አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ ወደ ልቡናችን ትመልሰን ዘንድ አንድ የመማርያ ዕድል ስለጨመርክልን እናመሰግንሃለን፡፡ የሚጽፉና የሚያስተምሩ ወንድሞቻችንንም በጸጋ እና በጤና ጠብቅልን! ተ መ ስ ገ ን !

Anonymous said...

Dn. Ephrem I am happy about the opening of this blog.
But I don't get the message of this article. I don't expect u to emphasize on the White's Christmas while most of us know it is originated from idolatry worship. I don't understand why u want to write this article in a way to support the celebration of two Christmases while only one is heavenly and the other is worldly.
I expect u to discourage those Ethiopians who celebrate the worldly Christmas and ignore the heavenly one.

Blog Archive