Saturday, January 8, 2011

የተዘመረላቸው እና ያልተዘመረላቸው ጀግኖች

አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት። ባለሥልጣን አይደሉም ወይም ታዋቂ እና ዝነኛም አይደሉም። አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ተርታ ዜጋ (ተራ ዜጋ ላለማለት ነው) ነዎት እንበል። እናም በሕዝብ ትራንስፖርት ሊጠቀሙ አውቶብስ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ወይም ባቡር ውስጥ ገብተዋል እንበል። መምጣትዎን በለበሱት የሥራ ልብስ ወይም በመታወቂያዎ ያወቁት አስተናጋጆች ለሀገርዎ ስለሚሰጡት አገልግሎት ከበሬታ በመስጠት ጠብ-እርግፍ ብለው ቢያስተናግዱዎት፣ ቢያመሰግኑዎት ምን ይሰማዎታል? ይህንን ይያዙልኝ እና ወደ አንድ ገጠመኜ ልውሰድዎት።

ከሰሞኑ በአንዱ ቀን እኔ እና ወዳጄ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ወደምትገኘውና የክልሉ መንግሥታዊ መቀመጫ ከተማ ወደ አውስቲን (Austin) በአሜሪካ አየር መንገድ ለመጓዝ ቦታችንን ይዘናል። እንደ አውርፕላን ልማድ አስተናጋጆቹ  ስለ አንዳንድ ነገር ገለጻ ሲያደርጉልን  “ወገባችሁን እሰሩ፣ አደጋ ቢመጣ በዚህ በዚህ አድርጋችሁ፣ እንዲህ እንዲህ እንዲህ ሆናችሁ አምልጡ” ሲሉን ቆዩ እና ሌላ አንድ ማሳሰቢያ እናዳለቸው ተናገሩ። “ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ ሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማሪፊያ ወደ አውስቲን ቴክሳስ በምናደርገው በረራ ላይ አንድ እንግዳ አለን። እንግዳችን የኔቪ (ባሕር ኃይል) አባል የሆኑና ለተልዕኮ ከተሰማሩበት ከአፍጋኒስታን ወደ ቤተሰባቸው ለእረፍት በመመለስ ላይ የሚገኙ ናቸው” ስትል አውሮፕላኑ በጭብጨባ ድምቅ አለ። “Welcome Home. ዌል ካም ሆም፤ እንኳን ደህና ወደ ሀገሮ (ወደ ቤትዎ) ተመለሱ” የሚለው የአስተናጋጇ የተጠና ድምጽ ሲስረቀረቅ ሁላችንም እያጨበጨብን አዳመጥናት።

እኔና ዶ/ር መስፍን በአውሮፕላኑ 33ኛ መቀመጫ ላይ ከኋላ ስለተቀመጥን በዓይናችን ወታደሯን ፍለጋ አንጋጠጥን። አትታይም። ከአውሮፕላኑ አጋማሽ መቀመጧን ያወቅነው መውረጃቸን ቦታ ደርሰን እርሷ እስክትወርድ ሌላው ሕዝብ ቁጭ ብሎ በጭብጨባ ሲሸኛት ነው። እንደ አውሮፕላን ሥርዓት ቢሆን “ቢዝነስ ክላስ” የተቀመጡት ከወረዱ በኋላ ከመጀመሪያው ወንበር ወደ ኋላ በየተራችን መውረድ ነበረብን። ነገር ግን ነፍሷን ለሀገሯ ለመስጠት በጦር ግንባር የነበረችው ያቺ ክብርት ሴት እያለች ማንም ከቦታው አልተነቃነቀም። ሁለት ቅጠልያ ዝንጉርጉር የወታደር ሻንጣዎቿን ተሸክማ ከወረደች በኋላ ነበር ሌላው ከየተቀመጠበት የተነሣው። አሜሪካውያን “ጀግኖቻቸውን ማክበር ሲችሉበት” ተባባልን ከዶ/ር መስፍን ጋር።

እግር ጥሏችሁ በትላልቅ አሜሪካ አየር ማረፊያዎች ተገኛችሁ ሰዎች በየድምጽ ማያዎች “people of the military” የሚል ማስታወቂያ በጆሯችሁ ሽው ብሎ ያውቃል ብዬ እገምታለኹ። ለእነርሱ ቅድሚያ ለመስጠት፣ እነርሱን ለማስተናገድ፣  የሚፈልጉት ማንኛውም ነገር ካለ ርዳታ መጠየቅ እንደሚችሉ ለማሳሰብ ብቻ በየምክንያቱ ስማቸውን ያነሣሉ። ይህንን ሲሰማና ሲመለከት ወዳጅ ዘመዱ በሚሊቴሪው ውስጥ የሚያገለግል ሰው ወይም ራሱም በጦሩ ውስጥ ያለ አንድ ዜጋ ምን ሊሰማው እንደሚችል ለመገመት ሞከርኩ።

ከልጅነቴ ጀምሮ ያደግኹት ከወታደሮች ጋር ነው። ብዙ የወታደር ታሪኮችን ሰምቻለኹ። ነፍስ ካወቅኹም ብዙ ታሪኮችን አንብቤያለኹ። ወታደሮች ሲሰጥኑ፣ ሲወድቁ ሲነሱ በልጅነቴ ከጓደኞቼ ጋር ከኋላቸው እየሮጥን ስንመለከታቸው አድገናል። የኑሮን ጣዕም በማላውቅበት በዚያ ዘመን “ምን ለመሆን ትመኛለህ?” ስባል ያለምንም ጥርጥር “ወታደር” ብዬ እመልስ ነበር። የዕድሜ ታላቆቻችን ወደ ሚሊቴሪው ገብተው ያንን ሽቅርቅር ልብስ ለብሰው ሲመጡ፤ በተለይም የአየር ወለድ ነብርማ ልብስ ለብሰው፤ እግሩ ፍራም የሆነውን ስፖንጅ ቡትስ አድርገው ሲመጡ በልጅነታችን እንቀናባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ጦር ሜዳ ውለው፤ አካላቸውን አጥተው፣ ወደ ሕዝቡ ዕለት ተዕለት ኑሮ ሲቀላለቀሉ ግን ዋጋ እንሰጣቸው ነበር? ለከፈሉት ዋጋ ምን መልሰንላቸው ይሆን? ሶማሊያ እና ሩዋንዳ፣ ባድመ እና ጾረና ውለው ሲመጡ ለከፈሉት ውድ ነገር ምን መልሰንላቸው ይሆን እያልኩ ራሴን እጠይቃለኹ።

“መለዮ ለባሾች” ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም የሥራ መስኮች ብዙ ጀግኖች ነበሩን። አሉንም። በግሌ እንኳን የዓለምን የጥበብ በር የከፈቱልኝ ብዙ “ጀግኖች” አሉኝ። በግእዙ የትምህርት ዓለም የሚባለው አጭር አባባል የበለጠ ይገልጸዋል። “አሐደ ቀለመ ዘነገረከ ይሁን ከመ አቡከ። ክልዔተ ቀለመ ዘነገረከ ይሁን ከመ አምላክከ” (አንድ ቀለም የነገረኽ/ያስተማረኽ እንደ አባትህ ይሁንልህ። ሁለት ቀለም የነገረህ/ያስተማረህ እንደ አምላክህ ይሁንልህ) ይላሉ። ከአንድም፣ ከሁለትም ቀለም በላይ የነገሩን/ያስተማሩን ነገር ግን እንኳን እንደ አባትና እንደ አምላክ ቀርቶ እንደ ጓደኛም የማንቆጥራቸው፤ እስከ ስማቸውም እንኳን የረሳናቸው ብዙ ናቸው። “ሀ … ሁ” የሚለውን የፊደል ዘር ያስቆጠሩን የኔታ አስናቀ፤ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እጃችን ፊደል መጫር እንዲችል በአባታዊ ቁጣም፣ በቁንጥጫም ያስተዋወቁን የኔታ ክፍሌ  ከእንግሊዝኛው ጋር በግሩም ሰዋስው ያስተዋወቁን ቲቸር መዝገበ፣ የመንደራችንን ሕጻናትን የሚያክሙት ነጭ የሚለብሱ “ድሬሰሮች” በትንሿ ከተማችን ለነበሩት እኩያዎቼ ጀግኖቻችን ነበሩ።

አንድ ሀገር ትልቅ ሀገር የሚባለው ከመንግሥት እስከ ተርታው ሕዝብ የራሱን ጀግኖች ሲያውቅ እና ሲያከብር ይመስለኛል። በሁሉም መስክ ጀግና የሌለው ሀገር የለም። በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያ “ያልተዘመረላቸው ብዙ ጀግኖች” (Unsung Heroes) ያሏት ሀገር መሆኗ ብዙ ጊዜ ይሰማኛል። ችግሩ ጀግና ፈልጎ ማግኘቱ ላይ ነው። “ማን ይፈልግ?” ለሚለው መልሱ የግድ መንግሥት ብቻ አይደለም። ከላይ ያቀረብኩት የአሜሪካውያኑ ታሪክ አንድ ሕዝብ ራሱ እንዴት ጀግናውን እንደሚያከብር የሚያሳይ እንደሆነው ሁሉ የእኛም ሕዝብ ጀግኖቹን የመፈለግ ልምድ እንዲኖረው የሚያመለክት ነው። በዚህ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ ልምድ እየታየ ነው። በኪነ ጥበቡና በስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ታሪክ የሠሩ ሰዎች የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ አጥተው ከሚቸገሩበት ኑሮ በተለያዩ ሰዎች ርዳታ የተሻለ ዕድል እንደገጠማቸው እንሰማለን።

ራቅ ብለን ወደ ታሪክ መዝገብ የገባን እንደሆነም ለእኛነታችን ኢትዮጵያዊ ማንነት አሻራቸውን ያስቀመጡ ጀግኖቻችንም ከተረሱበት ጉድጓድ የሚያወጣቸው እያገኙ ነው። ለአብነት “ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” የሚባለው እና በወጣት ኢትዮጵያውያን የሥራው ክቡርነት ዋጋ እያገኘ የመጣው “አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ”ን መጥቀስ ይገባል። አባ ጊዮርጊስ በግለሰብ ደረጃ ትዝ ይበለን እንጂ “ግእዝ ቋንቋ”ን ራሱን እንደ አንድ አካል (ሰው) ብንመለከተው አዲሱ ትውልድ “አንረሳህም” በሚል ዋጋ እየሰጠው ነው። “የግእዝ ቤተሰብ” የሚል የወጣቶች ስብስብ አባላት በዚህ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቋንቋ ሲነጋገሩ፣ ድራማ ሲሰሩ መመልከት በእጅጉ ያስደስታል። ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠትን፣ የራስን ማንነት ቆፍሮ ማውጣትን ያወቀና የተረዳ አዲስ ትውልድ ለመምጣቱ ምልክት በመሆኑ ለልቡና ሐሴትን ያጎናጽፋል።
ቸር ያሰንብተን


© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።

1 comment:

Anonymous said...

i am the river who falls to it's source. i know that u some some information about Dr Esayas who is a writer of "እንደ ቸርነትህ" pls have something to say
kidanemariam Ze Debere Yederas
thanks Dn Epherem

Blog Archive