Saturday, January 8, 2011

“ቻይና ታውን” እና “ሊትል ኢትዮጵያ”

Chinatown, San Francisco
ቻይናውያን በሄዱባቸው ሀገሮች በሙሉ የሚቆሮቁሯቸው እና ከእስያ እስከ አውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ እስከ ጃፓን በመላው ዓለም የሚገኙ ሰፈሮች “ቻይና ታውን” (Chinatown) ይባላሉ። በምስራቅ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በአሜሪካ (ካናዳን ጨምሮ)፣ በአውስትራሌዢያ (Australasia፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ እስያ ለማለት ነው) እና አውሮፓ ቻይና ታውኖች የተለመዱ ናቸው። የቻይና ባህል እና ንግድ ማዕከላት ሆነው ያገለግላሉ። ጥራታቸውም ከአካባቢ አካባቢ፤ ከሀገር ሀገር ይለያያል። አንዳንዶቹ “ቻይና ታውኖች” በንግድ ተኮር ቱሪዝም ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሥራ ፍለጋ የሚሰባሰቡ ሥራ ፈላጊ እና ለፍቶ አዳሪ ቻይናውያን (ቻይናዎች) መኖሪያዎች ናቸው።

በጀርመን ሀገር በሐምቡርግ ከተማ ያለውን የቻይና ታውን ለመመልከት ዕድል ስላልገጠመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ቻይና ታውን በቅጡ ያየኹት አሜሪካን ሀገር ከመጣሁ በኋላ በዋሺንግተን ዲሲ ነው። የዲሲው ቻይና ታውን እንዲያው ከከተማው አውራ መንገድ መካከል ላይ በትልቅ የጥንት ቤተ መንግሥታዊ ግንብ መሳይ በር፣ በቻይናዎች የድንጋይ ላይ ሥዕል ተንቆጥቁጦ ከሩቁ ይታያል። ከዲሲ ከተማ ባቡሮች አንዱ ፌርማታ ታዋቂው የ“ቻይና ታውን ስቴሽን” ነው።  የጃፓኑ ናጋሳኪና የባንጎክ ታይላንዶቹ  ከ200 ዓመታት በፊት በቻይናውያን ነጋዴዎች የተመሠረቱ ቀዳምያት “ቻይና ታውኖች” ናቸው።

በሰሜን አሜሪካ ደግሞ የሳን ፍራንሲስኮው ጥንታዊ፣ ትልቅ እና ዝነኛ ሲሆን የሳን ዲዬጎውን ጨምሮ ብዙዎቹ ከተሞች እንደያቅማቸው የየራሳቸው፡”ቻይና ታውኖች” አሏቸው። የቫንኩቨር (ካናዳ)፣ ኒውዮርክ ሲቲ፣ ቶሮንቶ፣ ቦስተን፣ ፊላዴልፊያ፣ ቺካጎ፣ ዴትሮይት እና ሞንትሪያል “ቻይና ታውኖች” በ19ኛው መ/ክ/ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የተመሠረቱ ናቸው። “ቻይና ታውኖች” በ20ኛው እና በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም መመስረታቸውን ቀጥለዋል። ከአዳዲሶቹ መካከል በ1995 እ.ኤ.አ የተመሠረተው የላስ ቬጋስ እና በቅርቡ ዕውቅና ያገኘው የሳንቶ ዶሚንጎው “ቻይና ታውን” ከዝርዝሩ መካከል ይገኙበታል።

ቻይኖች በሄዱበት ሁሉ ባህላዊ አሻራቸውን እንዲህ ባለ መልኩ ይተዋሉ። መንደሮቻቸው የባህላዊ ጥንካሬያቸው እና አሻራ የመተው ብቃታቸው ውጤቶች ናቸው። እንደ አሁኑ ቻይና በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ ይህ ነው የሚባል ድርሻና ሁነኛ ሥፍራ ባልነበራት ጊዜያት “በባህላዊ ኢኮኖሚ” (አባባሉ ለዚህ ጽሑፍ እንዲመቸኝ የፈጠርኩት ነው፤ ከዚህ በኋላ የሚጠቀምበት ቢመጣ ባለቤትነቱ የእኔ መሆኑን እንዳይረሳ) ግን ሀብታም ሆና በመገኘቷ ዜጎቿ በሄዱበት ምልክታቸውን እየተዉ ያልፋሉ። በዚህ ደረጃ፣ ከቻይኖቹ ጋር በሚመሳሰል መልኩ፣ በባህላዊ ሀብት ጥንካሬ፣ በሄዱበት አካባቢ ምልክት የሚተዉ ሌሎች ዜጎች የምናገኘው ግሪኮችን ነው። “ግሪክ ስኩል” የሌለበት የዓለም አካባቢ የለም። በመዲናችን በአዲስ አበባ እንኳን በዚህ ስም የሚጠራ ት/ቤት መኖሩን ልብ ይሏል። ምናልባት ወደፊት አዲስ አበባም ሱማሌ ተራ፣ ቦንብ ተራ፣ ጎጃም በረንዳ፣ ከምንለው ተርታ “ቻይና ታውኗን” አግኝታ ከዝረዝሩ ትገባ ይሆናል። በጥንታዊነት እና በባህላዊ-ኢኮኖሚ ብዙ ሀብት የምንለው እኛ ኢትዮጵያውንስ?

ኢትዮጵያውያን ከሀገራችን ወጥተን የመኖሩ ታሪክ ብዙ የቆየ ባይሆንም ስደት እና ፍልሰት ከተስፋፋባቸው ካለፉት 30 እና 40 ዓመታት ወዲህ አያሌ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም በዝርወት በመኖር ላይ እንገኛለን። ከምንኖርባቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ ብዙ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊ የሚገኘው በሰሜን አሜሪካ በተለይም በዩ.ኤስ አሜሪካ ነው። ቁጥሩና ብዛቱ በትክክል ይህን ያህል ነው ለማለት ቢያስቸግርም ዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢውን በመሳሰሉ ቦታዎች በእግሩ ወዲህ ወዲያ ለሚል ሰው የሀገሩን ሰው ወይም ኢትዮጵያዊ ሬስቶራንቶች፣ ሱቆች እና ሱፐር ማርኬቶች ማየት የተለመደ ነው።

ኢትዮጵያውያን የምንኖርባቸው ብዙ የአሜሪካ ከተሞች ቢኖሩም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያስቀመጥንበት እና የ“ኢትዮጵያ ታውን” መልክ ያለው ነገር ያየኹት በሎስ አንጀለስ “ሊትል ኢትዮጵያ” ነው። እንደስሙ “ሊትል ኢትዮጵያ” የሀገራችን ቁንጽል ጣእም የሚታይ-የሚቀመስባት ጎዳና ናት። ከመንገዱ ዳር ዳር ያሉት ንግዶች፣ የሚመላለሱት ሰዎች፣ የሚሰማው ሙዚቃ ወይም ከሩቅ የሚጣራው የምግብ መዓዛ በሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው። ዓይናችሁን ተጨፍናችሁ በሰፈሩ ብታልፉ “ሊትል ኢትዮጵያ” መድረሳችሁን አፍንጫችሁ ይነግራችኋል።

በተመሳሳይ መልኩ በዋሺንግተን ዲሲ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚሸጡ የሚለውጡበት፣ ኢትዮጵያዊ ምግብ ቤቶችና ሱቆች፣ ሙዚቃ ቤቶችና ሌሎች የንግድ ድርጅቶች የሚገኙበትን አካባቢ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ብሎ ለመሰየም የተደረገው ሙከራ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሳይሳካ ቀርቷል። ተቃውሞው የገጠመው ከአፍሪካውያን-አሜሪካውያን ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ አካባቢው ባለው ሌላ ታሪካዊ ፋይዳ ምክንያት ነው። ከዚያ ውጪ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው እንደ አትላንታ (ጆርጂያ)፣ ዳላስ (ቴክሳስ) ያሉ አካባቢዎች ቻይናዎቹን በመሰለ የባህል አሻራ ማስቀመጡ ብዙም አይታይም።

ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን የባህላዊ ማንነት እጥረት ያለብን ሕዝቦች አይደለንም። ምንም እንኳን አንድን ባህል ከሌላው ይበልጣል ወይም ያንሳል ወይም አንድን ቋንቋ እና ማንነት ከሌላው ያንሳል ወይም ይበልጣል ማለት ስሕተት ቢሆንም ባህልን ለሌላው በማስተዋወቅና በማጋባት፣ ያንንም ለማኅበረሰቡ ጥቅም እንዲውል በማድረግ በኩል ግን ትልቅ እጥረት አለብን። በቁጥር በብዛት በምንኖርባቸው አካባቢዎች ሳይቀር የቁጥራችንን ያህል ከዚያ ልናገኝ የሚገባንን ጥቅም አላገኘንበትም። የዲሲ ኢትዮጵያውያን የቋንቋ መብታቸውን ማስከበራቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው።

በዋሺንግተን ዲሲ እንግሊዝኛ መናገር የማይችል ሰው ቢመጣ አማርኛ አስተርጓሚ እንዲመጣለት መጠየቅ ይችላል። በማንኛውም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት በአማርኛ ተናግሮ ጉዳዩን አስፈጽሞ መውጣት ይችላል። ሐኪም ቤት ቢሄድ ወይም ፍርድ ቤት ቢቀርብ በአማርኛ ብቻ መስተናገድ ይችላል። ከዲሲ 5 ደቂቃ ርቀት ነድተው ወደ ሜሪላንድ (ሀገረ ማርያም እላታለኹ እኔ) ወይም ቨርጂኒያ ግዛቶች ሲገቡ ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በነዚህ ሁለት ግዛቶች ቢኖርም የዲሲን ዓይነት “ባህላዊ አሻር” መጣል አልቻለም። የባህል ማጋባት እጥረት ሳይኖርብን አልቀረም። ቡሩክ ላቀው ከተባሉ አትዮጵያዊ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገች አንዲት ጋዜጠኛ እንደጠቀሰቻቸው “ኢትዮጵያውያን ገና ከሕጻንነት ጀምሮ በቡድንና በሕብረት የመሥራት ልምድ ማነሥ (lack of valuable exposure to the team work, leadership, and organizational activities that many American children are trained to thrive in at an early age)” ስላለብን ከሌሎቹ መጤ ዜጎች እኩል ድምጻችን ሊሰማ አልቻለም። ስለዚህም በግል ከሚደረግ ጥረት በተሻለ በሕብረት ሁነኛ  ሥራ ለምሳሌ የጋራ ንግድ ማቋቋም፣ ወይም ልክ ሌሎቹ እንደሚያደርጉት የኢትዮጵያዊውን ማሕበረሰብ ፍላጎት የሚያስጠብቅ ሹም ያስመረጥንበት ሁኔታ የለም።

ሰፋ አድርገን ከተመለከትነው ደግሞ ጉዳዩ በከተማዎች አንድን ቦታ በስፋት ስለመያዝ ወይም አንድን አካባቢ በስማችን ስለመሰየም እና ስለማሰየም (ስለማስጠራት) ወይም “ሹም ስለማስመረጥ” እና ንግድ በጋራ ስለማቋቋም ብቻም  አይደለም። ባህላዊ አሻራን ማስቀመጡ ከቤተሰብ ይጀምራል። በባዕድ ሀገር የምንወልዳቸው ልጆቻችን የራሳችንን ባህል ተቀብለውና አሳድገው መሄዳቸውን ይመለከታል። ቻይናዎቹንና ግሪኮቹን፣ ወይንም ሕንዶቹንና ላቲን አሜሪካኖቹን ስንመለከት በእንግሊዝኛ ተናጋሪው መካከል እየኖሩ የራሳቸውን ባህላዊ-ማንነት አሳድገውና ለልጆቻቸው አውርሰው መዝለቃቸውን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

አሁን አሁን በዝርወት በዳያስጶራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን በሀገር ቤት የሚገኘውም ባህላዊ እሴቱን በፈቃዱ እየጣለ ለመሆኑ ብዙ እየተባለ ነው። በአንድ ወቅት ለአጭር ጊዜ ቆይታ ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ያጋጠመኝን አስታውሳለኹ። አሁን በቅርቡ ደግሞ በአሜሪካዋ የሎስ አንጀለስ ከተማ ለጉብኝት የመጡ አዲስ አበቤዎች (የአዲስ አበባ ነዋሪ ቤተ ሰቦች) ገጠመኝ ሌላ ሀገር ሳይሆን እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥም የባህል አብዮት ያስፈልጋል አሰኝቶኛል። ከጀርመን ስመለስ ያገኘኹት  የ15 ዓመት ወጣት ልጅ አዲስ አበባ ያደገ አልመሰለኝም ነበር። አነጋገሩም ሆነ አለባበሱ፤ “የአማርኛ እጥረቱም” ሆነ አቋሙ ዛሬ በዲሲ አካባቢ የማያቸውን እምቦቃቅላ አሜሪካ-አደግ ልጆች ነበር የሚመስለው። ነገሩ ግን የዲሲ-አደግ ልጆች “ሶፍትዌር” ተጭኖበት እንጂ እርሱስ (ሐርድዌር Hardware እንበለው?) አሜሪካን አያውቀውም።

የሎስ አንጀለሶቹ አዲስ አበቤዎች ደግሞ በአዲስ አበባ አማርኛ የማይናገር ልጅ እያሳደጉ መሆናቸውን በኩራት የሚናገሩ ናቸው። ያስተናገዳቸው ወዳጃችን በጉዳዩ ከማዘኑ የተነሣ ከእንግዶቹ ጋር ሊጋጭ ጥቂት ነበር የቀረው። ምናልባት ቻይናዎቹ አዲስ አበባ ላይ “ቻይና ታውን” ሲሰሩ እኛ የራሳችንን “ሊትል ኢትዮጵያ” እንዳናጣ ሰጋሁ። የትምህርት ጥራታቸው እንግሊዝኛ በመናገር ብቻ የሚለካ ሕጻናት መዋያዎችና አንደኛ ደረጃዎች ከበረከቱ ችግሩ ልንመልሰው በማንችለው መልኩ ስር ሊሰድ ይችላል። “የትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ከእንግሊዝኛ በስተቀር አማርኛም ሆነ ሌላ ቋንቋ መናገር እንከለከላለን” ያለኝ ልጅ አማርኛ በቅጡ አያነብም። ማንበብ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቡናዊ ማንነቱ ከሚኖርበት ማኅበረሰብ ማንነት የተራራቀ ስብዕና ይዞ እንዲያድግ እየተደረገ ነው። “ሥጋው ኢትዮጵያዊ፣ ነፍሱ የሌላ ሀገር ” ሆኖ ወደ ወጣትነት ብሎም ወደ ጉልምስና ሲሸጋገር ሀገራዊውን ቋንቋ እና ማንነት እንዳያውቅ መደረጉ የሚፈጥረውን ቀውስ በትክክል መመልከት እንጀምራለን። በዳያስጶራው የሚገኘው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ልጆቹ የዚህ ሰለባ የሚሆኑበት ብዙ አጋጣሚ መኖሩ ጥሩ ማሳያም ማስተማሪያም ሊሆን ይገባል።

ቸር ያሰንብተን።

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።

7 comments:

Anonymous said...

thanks for sharing us it is to much impressive metatif

Anonymous said...

good view

Ze-Nazareth said...

It is nice view. But what must be done? Most of us are unable to differentiate between Civilization and loosing once identity. We are thinking as if modernization and civilization is behaving like westerns.
Am waiting for the solution as well. Try to indicate us some ways of overcoming this problem. At least we can print and distribute for those who don't have Internet Access.
God bless U.

Anonymous said...

ጥሩ ምልከታ ነው በተለይ እኛ የልጆች ሃላፍንት ያለብን እንዴት መሆን እዳለብን ግራ ገብቶናል ልጆች የት ይማሩ

Anonymous said...

Thank You Ephrem

Wubshet Yilak said...

Dear Brother Efrem,
realy thank you for sharing your great and ext-important Visionary thoghts about this Title and all the others. Egziabher Abzito Yibarkih.
You know it is my everyday task to worry about such things ,i don`t know why but i feel it so hard. And now i am so surprised to read my thoghts from you.
Nice to get to know you.
Bis nachtesmal.
Wubshet aus Deut.

Anonymous said...

lastemarken libel woyis legeletskilin yechelemebinin guday enameseginalen wondimachin keep it up God bless you. "lijoch yet yimaru" lalkew/shew melsu ye lijoch ye mejemeriya ena tiliku timhirt bet beteseb new enga lijochachinin be kuankuachin ena be bahilachin kalasadegnachew beteley bet be kuankuachin kalaworanachew mecheresachew bahilachewun ena hayimanotachewun yafrubetal kezihs yisewuren amen.

Blog Archive