Monday, January 17, 2011

ትልልቆቹ ወዴት ሄዱ?

በፈረንጆቹ የ2010 መጨረሻ የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ለ25 ዓመታት የዘለቀ አንድ ታዋቂ ፕሮግራም አጥቷል። ከ1985 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲያቀርብ የነበረው አዘጋጇ ጡረታ ወጥቷል። ሌላዋ ታዋቂ ጋዜጠኛም ከ1986 ጀምሮ ስታስተላልፍ የነበረውን ፕሮግራም አብቅታለች። ላሪ ኪንግ እና ኦፕራ ዊንፍሬይ (Larry King and Oprah Winfrey) ለ25 እና ለ24 ዓመታት የዘለቁ ፕሮግራሞችን ሲያስተላልፉ  የቆዩ ሁለት የአሜሪካ ጋዜጠኝነት ምልክቶች ናቸው።


አረጋዊው ላሪ ኪንግ ለ25 ዓመታት ያዘጋጀው የነበረውን ታዋቂ የሲ.ኤን.ኤን ፕሮግራሙን (Larry King Live) ለማብቃት ሲወስን ጡረታ ለመውጣት ፈልጎ ነው። እኔ በጣም የገረመኝ ግን አሜሪካ ለዚህ ታዋቂ ጋዜጠኛዋ ያደረገችው የመጨረሻ የስንብት መርሐ ግብር እና በሙያው ላበረከተው አስተዋጽዖ ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጀምሮ ያቀረቡለት ምስጋና ነው። በዕለቱ ለጋዜጠኛው ክብር የተዘጋጀውን ዝግጅት ይመሩ እና ያስተባብሩ የነበሩት የሙያ አጋሮቹ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች፣ የንግድ ሰዎች ከነዚህም መካከል ዝነኛ ቢሊዬነሮች እንዲሁም ባለቤቱና ልጆቹ ነበሩ።

በመርሐ ግብሩ መካከል የዕለቱን ዝግጅት ያቀናበረው ኮሜዲያን አንድ እንግዳ እንዳለ ገልጾ፣ እንግዳው ክቡር ፕሬዚዳንቱ መሆናቸውን ሲገልጽ ራሱ ላሪ ኪንግ መገረም ይዞት ነበር። ፕሬዚዳንቱም ለ25 ዓመታት አሜሪካንን ያስተማራትን፣ ያዝናናትን፣ በጥያቄዎቹ እና በዝግጀቶቹ እንዲሁም በባለ ማንገቻ ሱሪው የሚታወቀውን ጋዜጠኛ አመስግነው መልካም ጊዜ እንዲገጥመው ተመኝተውለታል።

ላሪ ኪንግ “ላሪ ኪንግ ላይቭ/ Larry King Live” የሚባለውን በቃለ ምልልስ ላይ የተመሠረተ ዝግጅቱን ማቅረብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በዚያ በጎርናና ድምፁ፣ የተጠያቂውን ልብ ሰርስሮ በሚገባ አስተያየቱ፣ በትልልቅ መነጽሮቹ ውስጥ አጮልቆ ያላየውና ያልጠየቀው ታላቅ ሰው የለም። ፕሬዚዳንቶች፣ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሆሊ ውድ ከዋክብት፣ ዘፋኞች፣ አስደናቂ ሥራ የሠሩ ሰዎች ወዘተ ወዘተ በሙሉ ተጠይቀዋል።

ጥያቄዎቹ ለስላሳ ናቸው እየተባለ ቢታማም ሳይጠይቅ የሚያልፈው ነገር የለም።  አዋዝቶ፣ አጫውቶ፣ በቀልድም አዋሕዶ የነገር ልብ ማውጣት ይችልበታል። በዚህ መልክ 25 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ቃለ ምልልሶች አድርጓል። ሌላዋ የሙያ አጋሩ ኦፕራም እንዲሁ ለ24 ዓመታት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አነጋግራለች፤ አብራቸው ስቃለች፣ አልቅሳለች፣ ሕይወታቸውን ቀይራለች። ልክ እንደ ላሪ ኪንግ።

ላሪ ኪንግም ሆነ ኦፕራ በታወቁበት የቃለ ምልልስ አቀራረብ ለዚህን ያህል ዓመት የዘለቁት ሙያቸውን አክብረው የያዙ፣ የሚሠሩትን ያወቁ ስለሆኑ ነው። በተለይም “የጋዜጠኝነት ሙያ ዋና አንጓ የሆነውን ቃለ ምልልስ ማድረግን ተክነውበታል። ቃለ ምልልስ የጋዜጠኝነት “ልብ” የሆነ ጋዘየጠኞች ተጠያቂን የሚያንቀጠቅጡበት፣ የስሜትን ጓዳ ኮርኩረው ስቀው የሚያስቁበት ወይም የሚያስለቅሱበት ዘዴ ነው።

LKL with George W.Bush and His wife
ቃለ ምልልስ እንዲሁ በዘፈቀደ ከምላስ ጫፍ በሚወረወር ጥያቄ የተሞላ አይደለም። መዘጋጀት ይፈልጋል። ጥያቄ ስለሚያቀርቡበት ጉዳይ ወይም ስለተጠያቂው ጥሩ ዕውቀት ሊኖር ይገባል።  ጥያቄዎቹ የሚሽከረከሩበትን ዓምድ (Theme) ጥሩ አድርጎ መቅረጽ ይኖራል። “የቤት ሥራውን” ያልሠራ ጋዜጠኛ አራምባና ቆቦ ይረግጣል፤ ጥያቄዎቹ ውሽልሽሎች፣ ምን ለማለት እንደፈለገ የማይገልፁ ይሆናሉ። ወይም በደፈናው “ምን ይሰማዎታል? እንዴት ይታያል? ቢገልፁልን?” ከሚል አሰልቺ ድግግሞሽ አይዘሉም። መላሹንም አእምሮውን አስጨንቆ የሚጠቅም መረጃ እንዲሰጥ አያስገድዱም።

የነላሪ ኪንግ ዓይነቶቹ ጠያቂዎች ተጠያቂዎቹን የሚኮረኩሩ፣ የሚያስደስቱ፣ የሚያስፈግጉ፣ የሚያናድዱ፣ ዘና የሚያደርጉ ወይም የሚያሳፍሩ ወይም ቁስላቸውን ነክተው የሚያቅበጠብጡ ናቸው።

ወደ ቀደመው ነገር ስንመለስ፦ 24 እና 25 ዓመት ማለት የአንድ ራሱን የቻለ ወጣት ዕድሜ መሆኑም አይደል? ለዚህን ያህል ጊዜ የአንድን አገር ልብና ነፍስ ይዞ መዝለቅ እጅግ ከባድም፣ አስገራሚም ነው። ከሁሉ ከሁሉ ልቤን የገዛው ግን አጠያየቃቸው ወይም ያላቸው የተመልካች ቁጥር ብዙ መሆኑ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ዋና የሳበኝ ነገር እርሱ አይደለም። በዕድሜና በሙያ ዕውቀት፣ በብስለት እና በዘላቂነት እንዲህ ዓመታትን የሚሻገር መርሐ ግብር እና ሥራ መሥራታቸው ልቤን ይኮረኩረዋል።

ጀርመን አገር፣ ገና ቋንቋውን በቅጡ መስማት ሳልችል፣ የምከፍታቸው ቻነሎች ዕድሜ በጠገቡ ጋዜጠኞች የተሞሉ ሆነው በማግኘቴ እገረም እንደነበር ትዝ ይለኛል። በተለይም መንግሥታዊዎቹ ታዋቂ ቴሌቪዥኖች “ኧርስተ፣ Das Erste” እና “ZDF” ከጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ባለፉ ቱባ ቱባ ጋዜጠኞች የተሞሉ ነበሩ። ወጣቶቹ አብዛኛው ወደ መዝናኛው እና ስፖርቱ ያደሉ ካልሆነ በስተቀር በሌሎቹ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መሪነቱን የያዙት እንደ ላሪ ኪንግ ያሉት አንጋፎቹ (ሲኒየርስ) ናቸው። ዛሬም ድረስ የሌሎች አገሮችን ቴሌቪዥኖች፣ በተለይም ያደጉትን አገሮች፣ የሚመለከት ሰው ይህንን እውነታ ይረዳል።

የላሪ ኪንግ መሸኛ ላይ ይህ ከዓመታት በፊት ያየሁትና በውስጤ አድሮ የነበረው ሐሳብ በድጋሚ ትዝ አለኝ። አገር ቤት በነበርኩበት ዘመን የማውቃቸው አብዛኞቹ ጋዜጠኞች፣ የየዕውቀት ዘርፉ ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ነጋዴዎች ወዘተ በአብዛኛው ወጣቶች ከዚያም ዘለል ቢል ጎልማሶች ናቸው። ያ አውቀው የነበረው ዕውነታ ተቀይሮ ያየኹት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ ስሄድ ነበር። 


ዛሬም አሜሪካን አገር ተቀምጬ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን ስመለከት፣ ሬዲዮኖቹን ስሰማ፣ ስብሰባ ላይ የተቀመጡ ተሰብሳቢዎችን ሳይ፣ ስለ አገሪቱ ሊገልፁ የሚነሱ አንቱ የተባሉ ሰዎችን ስመለከት ወይም እንደኔው ጽሑፍ የሚያበረክቱ ፀሐፍትን ሳይ አብዛኞቹ እንደ ላሪ ኪንግ ያሉ ጎልማሶችና ከዚያም ሲያልፍ አረጋውያን ሳይሆኑ ዕድሜያቸው በወጣትነት ገፋ ካለም በጎልማስነት ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች ሆነው አያቸዋለኹ። እናም በኅሊናዬ አንድ ጥያቄ ይከሰታል፦ “እንደ ላሪ ኪንግ ዓይነቶች፣ እንደ ኦፕራ ዊንፍሬይ ዓይነት ያሉ ትልልቆቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከአገሪቱ ወዴት ሄዱ?”

ሽማግሌ አያሳጣን” የሚባል ምርቃት አለ። ሽምግልና በዕድሜ መንዛዛት ብቻ አይደለም። በዕውቀት ጥልቀት፣ በሰፈር በቀዬ በመከበር፣ በአስተዋይነት፣ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን፣ ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉትም በማሰብ ይገለጽ ይመስለኛል። ቅዱስ መጽሐፍ  “የሽማግሌዎችንም ማስተዋል እወስድባቸዋለኹ” (ኢዮብ 12፡20) እንዳለው አገር ሲረገም እና በመልካም ዘር ፈንታ አራሞቻ ማብቀል ሲጀምር ማስተዋል “ከትልልቆቹ” ዘንድ ይሰወራል። መሠረት ባለው ሁኔታ ትውልዱን የሚጠብቅ “የታደለ አገር” ደግሞ ሽማግሌዎቹ መልካምና ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ሥራ ሠርተው ያልፋሉ፣ አዲሱም ትውልድ የሚገባቸውን ክብር ሰጥቶ ያሰናብታቸዋል።

ላሪ ኪንግ ሥርጭቱን በጨረሰባት በዚያች ምሽት፣ ከስቱዲዮው ወጥቶ የሄደው ወደተዘጋጀለት የማታ ዝግጅት ነበር። ሲ.ኤን.ኤን ላይ ሥርጭቱን በማቅረብ ላይ የነበረው ታዋቂው “”አንደርሰን ኩፐር” (Anderson Cooper) በበኩሉ ላሪ ኪንግ ወደ ተዘጋጀለት አዳራሽ ሲገባ ያለውን የደመቀ መንፈስ በቀጥታ ያስተላልፍ ነበር። ያ ሁሉ ቱባ ቱባ አሜሪካዊ ባለሙያ ቆሞ በጭብጨባ ሲቀበለው የ25 ዓመት ልፋቱ ፍሬ በይፋ ይታይ ነበር። እናም ልቤ አንድ ነገር ተመኘ።

እንደ ኢትዮጵያ ያለው አገር አብዛኛው ሕዝብ ወጣት ከመሆኑ አንጻር ሙያዎችም በአብዛኛው በወጣት የተገነቡ ናቸው። ነገር ግን አገሪቱ ገና ወጣት አይደለችም። በየሙያው አረጋውያንን እና አንጋፎችን ያፈራች ናት። በሙያቸው አንቱ የተባሉ፣ በሥራቸው የተከበሩ፣ ለትውልድ ሊወረስ የሚችል ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብት ያላቸው ጎምቱዎች አገር ናት። እነዚህን የአገር ቅርስ ጎምቱዎች በመብራት መፈለግ ግን ይገባል።

ኢትዮጵያ በተለይም “የለውጥ ማዕበሎች” አገሪቱን መናጥ ከጀመሩበት ካለፈው አርባ ዓመታት ወዲህ ብዙ የያኔ ወጣቶችና ጎልማሶች፣ የዛሬ አረጋውያንና ትልልቆች ለአገራቸው ማበርከት የሚችሉትን ሳያበረክቱ ተገፍተው ተቀምጠዋል። እነርሱም ከነገሩ ጦም እደሩ ብለው፣ አስታዋሽም ሳያገኙ፣ እነርሱም ለመታወስ ሳይሞክሩ በሁሉም በኩል ኢትዮጵያ ከሳሪ ሆና “የትልልቆች ያለህ” ትላለች።

“ትልልቆቹ” አንዱ ለአንዱ በአክብሮት የሚቆም ወይም የሚያጨበጭብ እና ለሠራው ሥራ ከበሬታን የሚሰጥ ሳይሆን ዛሬም እንደትናንት የወጣትነታቸው ዘመን (ጉልበትና ዕድሜ ባይፈቅድላቸውም) የመጠፋፋት መንፈስ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ይታያል። ከቤተ እምነቱ እስከ ቤተ ፖለቲካው፣ ቤተ ዩኒቨርሲቲው እስከ ቤተ ማኅበረሰብ ድረስ “ትልልቆቻችን” እንደ ላሪ ኪንግ ለረዥም ዘመን ወደናቸው፣ ሰምተናቸው፣ ተከትለናቸው፣ በኋላም የሚሰጡንን ወርሰናቸው በፍቅር የምናሰናብታቸው አልሆኑም። ይልቁንም የምንጠላቸው፣ የምንወረውርባቸው፣ የምንጸየፋቸው፣ የእኛ አይደሉም የምንላቸው ሆነን ተገኝነተናል።

ይህች ግሩም አገራችን ሁሌ ጀማሪ፣ ሁሌም በወጣት፣ ሁሌም ወጣት መሆን አይገባትም። በአስኳላውም፣ በአገረኛው ዕውቀትም የበለፀጉ፣ ያረጁ (አረጋውያን የሆኑ) ለወጣቱ ሀብታቸውን አስረክበው የሚሄዱ “ትልልቆች” ያስፈልጉናል። ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ ኮሌጆቻችን፣ የምርምር ተቋሞቻችን፣ ማኅበረሰቦቻችን ትልልቆችን ይሻሉ። የት ናችሁ?

ቸር ያሰንብተን።


© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።
12 comments:

Anonymous said...

Kale hiwotin yasemalin wendimachin.

Awon Ewunet newu Yihichi Hager ewunetim telelekochun Teshalech Ahun lalenewu wetatochim Ke 15 amet ena keza belay yeneberu sewochin Tililikoch honewu enafekachewalen kenesum beso enesum yelum yet hedu??? "SIDET" Beteley Betecherstiyan norewu bezu liyagelegelwuat yemichelu sewochin Besedet eyatach newu negem yiketelal.Sidet Sidet Sidet......

esti Anten chemiro sint nachehu Yejemerachehutin satekuwachu weyim norachehu satastemirun satmekrun wede baed hager yetesedededachehut ???? eshi "nuron lemashenef" yibalal hulum yilal gin endiyawum yihen kanesah turu Yetesededachehut hulu meche newu memeles ena angafawochun abren yeminefeligachewu??????? newu beka lememeles atasebum ?????? tadya yet hedu belen lemeteyek kerasachin enenesa.

Lezih tiyake mels etebekalehu??????

tiru hasab newu amlak agelgilotehin yikebeleleh bedme tebeko wedehagereh beselam yimeleseh.

Ahunem yemeleh benor Yenenem Lib Surgery serteh Betayewu ayichalim enji Lebe yalehu "SIDET" newu keman limar tadya.

Anonymous said...

ጽሁፉን ሳነብ እኛም ነበሩን የሚለው ሃሳብ አቃጨለብኝ ድምጻቸው የሚያጉረመርመውን እነ ልዑል ሰገድ ኩምሳን የእንግሊዘኛ ዜና አቅራቢውን እነ ዜናነህ መኮንን ግሳስበው ነበሩ ብቻ ሆነብኝና ተውኩት

Anonymous said...

እንደው ድንቅ ነው ባያሌው። በርታ። የኛ ነገር እንደወ ዝም ነው። በነገራችን ላይ የሃይማኖቱ አምድ ያት ገባ? መልካም በዓል።

Anonymous said...

Great article. Keep it up.

hailemichael zedallas said...

“ትልልቆቹ” አንዱ ለአንዱ በአክብሮት የሚቆም ወይም የሚያጨበጭብ እና ለሠራው ሥራ ከበሬታን የሚሰጥ ሳይሆን ዛሬም እንደትናንት የወጣትነታቸው ዘመን (ጉልበትና ዕድሜ ባይፈቅድላቸውም) የመጠፋፋት መንፈስ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ይታያል።

Anonymous said...

YE KEDUSAN AMLAK EGZABHAR REJIM EDMA YESTELEN !!!KHY!!!

Dawit said...

ትልቁን አባባ ተስፋዬን እድሜውን ሙሉ ያገለገሉት ኢቴቪ በምን መልክ እንዳሰናበታቸው አስታወስከኝ።

Anonymous said...

ብዙውን ግዜ …ትልልቆች እየተረሱ አዲስ ሲመጣ እጹብ እጹብ የሚባልበት ሀገራችን እውነት ነው በጣም ያሳዝናል። ከስተያየት ስጽሁፎቹ ውስጥ ቀልቤን የሳበው “ አባባ ተስፋዬ” ብሎ የተጠቀሰው የኔንም ትውስታ አነሳውና ብዕሬን አነሳሁ። አባባ ተስፋዬ ሥራቸውን ካቆሙ በኋላ መርካቶ መሀል ካሴታቸውን እያዞሩ እኔ ከነበርኩበት ሱቅ ብቅ ሲሉ ውስጤ እንዴት እንደተሰበረ አምላክ ያውቃል።አንጋፋዎች አቅም ባነሳቸው ግዜ መውደቂያቸው ይህ መሆኑ እና አሁን አንተ ባነሳኸው የሊሪ ኪንግ የስንብት ፕሮግራም ሳነጻጽረው ውስጤ ቆዘመ፡፡

Anonymous said...

Correct!
Let me tell u what Dr. Abera Deressa (The previous minister of Agriculture) said at Aba Geda Assembly Hall for Graduates of different Ethiopian Universities this summer.
"Yihe Astesasebun alilewutim yal ena bediro astesaseb yallewun sew bota endititeku naw enante yetemeretachihut. Ahun enante befitnet masters doctrate tiyizuna yihenin lemengist policy aligezam billo bareje astesaseb yalewun temarku bay hullu taswegidutalachihu".

Samson said...

I think our church was successful in this regard in the past decades. She is a good example for the country. But I do not know our generation. Thank you Dn Efrem.

Selam said...

I just finished watching the Canadian National TV news. They were talking about the current Egypt historic demonstrations. The current commodity price hike and poverty of the young generation is the main cause of its population anger and frustration. The average age of the population of Egypt is 21 with 10% of unemployment rate. It is very amazing to see this in comparison to other developed countries like Canada whose average population age is 40. Unfortunately it is the same story in our country.

Anonymous said...

"ትልቁን አባባ ተስፋዬን እድሜውን ሙሉ ያገለገሉት ኢቴቪ በምን መልክ እንዳሰናበታቸው አስታወስከኝ።"
Hulim Ersachewun sasib betam azinalehu,"Lijochiye denanachihu? kuchi belu.. kuchi belu" Ohhhhhh Ethiopia Hageri meche yihon..........

Blog Archive