Friday, January 7, 2011

ኢንተርኔት አውሮፕላን ውስጥ

በዓለም ታዋቂው የኢንተርኔት መፈለጊያ ድርጅት ጉግል ሰሞኑን ባወጣው  ማስታወቂያ ላይ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ የሚመጡትን በዓላት አስመልክቶ በየትኛው የአየር በረራ ላይ ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ቃል ገብቷል። በዓላት ያላቸው በኖቬምበር ወር መጨረሻ ያለውን የ“ታንክስ ጊቪንግ” በዓል እና “ክሪስማስ”ን (በዓለ አኲቴት እና ገና) መሆኑ ነው። በነዚህ በዓላት ሰሞን ወገን ከወገኑ፤ ቤተሰብ ከቤተሰቡ ለመገናኘት በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በመንገድ ትራንስፖርቶች በሙሉ የሚነቃነቅበት ጊዜ ነው።


በሌላው ጊዜም ቢሆን አሜሪካውያን በአውሮፕላን የመጠቀም ባህላቸው እግ ከፍተኛ ነው። እንደሚነገረው ከሆነ በአንድ የአዘቦት ቀን ከቦታ ቦታ በአውሮፕላን ከሚጓጓዙ ሰዎች መካከል 60 ሺህ የሚሆኑ አሜሪካውያን በአየር ላይ ይገኛሉ። 60 ሺህ ሰው በስንት አውሮፕላን ሊበር ይችላል?” ብለን ለማካፈል አንዱ አውሮፕላን በአማካይ 100 ሰው ይይዛል ብለን ብንመድብ የሀገሪቱ ሰማይ ከ6,000 ያላነሰ የአውሮፕላን ቁጥር በአንድ ጊዜ በሰማይ ላይ ይርመሰመስበታል ማለት ነው። በእርግጥ አብዛኞቹ አውሮፕላኖች ከ100 ሰው በላይ የመጫን አቅም ያላቸው ሲሆኑ ከዚያ በታች የሚጭኑና ለአጭር በረራ የሚወጡም መኖራቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባናል። ጉግል ለነዚህ ሁሉ በነጻ ኢንተርኔት ሊያድል ነው ማለት ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርኔት በሰማይ ላይ (አውሮፕላን ውስጥ) የተጠቀምኩት “ኤየር-ትራን” (Airtran) አውሮፕላን ውስጥ ባለፈው ዓመት ነበር። ጀርመን የሚገኘው ወዳጄ አብርሃም በለጠ ከዚያ ላይ “ቻት” የማድረጊያ መልእክት ስልክለት እና የት እንዳለኹ ስነግረው የምቀልድበት መስሎት ነበር። በርግጥ ለእኔም የሚገርም ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ሰሞኑን ወደ ኦውስቲን፣ ቴክሳስ በ“አሜሪካን ኤር ላይንስ” ስጓዝ ተጠቅሜያለሁ። በሁለቱም በረራዎች ለአንድ ጊዜ ዙር ከ$10 እስከ 13 ዶላር አስከፍለውኛል። በ3 ሰዓቱ በረራ ወቅት ሊሠራበት ከሚችለው ሥራ አንጻር ግን የገንዘቡ መጠን አያንስበትም አሰኝቶኛል።

በዚህ በምዕራቡ ዓለም ኢንተርኔት የሀገሮቹ የጀርባ አጥንት ነው። መንግሥታትና ድርጅቶች ከሚገለገሉበት መሠረታዊ አገልግሎት በተጨማሪ ለእያንዳንዳችን የሕይወታችን አካል ከመሆኑ አንጻር ያለ እርሱ መኖር የማይቻል ከሚመስልበት ደረጃ የተደረሰ ይመስላል። ይህንን ምናልባት በምሳሌ ለማብራራት ልሞክር።

በየቀኑ የባንክ አካውንቴን እና የገንዘብ ሁኔታዬን እመለከታሉ። ምናልባት እኔ ሳላውቀው የወጣ ገንዘብ መኖር አለመኖሩን ለመከታተል ብቻ ሳይሆን ቡና ስጠጣም ይሁን “ሱፐር ማርኬት” ስገዛ የከፈልኩት መጠን በትክክል መወሰዱን እመለከታሉ። አንዳንድ ወርሃዊ ወጪዎቼን የምከፍለው በኢንርኔት ነው። ለምሳሌ ቤቴ ውስጥ ያለኝን የቴሌቪዥን ወርሃዊ ክፍያ ወይም ለቤት ውስ ኢንተርኔት የምጠቀምበትን ገንዘብ በዚያው በኢንተርኔት እከፍላለሁ። በሆነ ምክንያት በተለይም እዚሁ አሜሪካ ውስጥ ወይም ሌላ ሀገር ሰው ገንዘብ መላክ ቢኖርብኝ ከቤቴ ሳልወጣ በኢንተርኔ አዛለኹ። በአካል ወደ መሸጫ ቦታዎች ሄጄ ከምገዛው ነገር ውጪ በኢንተርኔት የምገዛው ዕቃ ሲኖር የማዘው፣ የምከፍለው፣ ደረሰኝ የምቀበለውም ሆነ ዕቃው ከተላከበት ቀን ጀምሮ እኔ ጋር እስኪደርስ ድረስ በሚሰጠኝ መከታተያ ቁጥር የምከታተለው በዚያው በኢንተርኔት ነው። 

ከዚህ ሁሉ ባሻገር ከኢንተርኔት ዋነኛ ሥጦታዎች መካከል አንዱ የሆነውን ኢ-ሜይል ለመጠቀም የግድ ኢንተርኔት ያስፈልገናል። ገና በጠዋቱ ከሌላው ሥራ በፊት የተላከልኝ ኢ-ሜይል መኖር አለመኖሩን ሳላረጋግጥ ወደሌላው ሥራዬ አልገባም። ሌላውም ሰው እንደዚያው ነው። ያውም ኢንተርኔት ያለው ስልክ የሌለው ሲሆን ነው። አሁን ደግሞ ፌስቡክን እና ኦርኩትን (Facebook and Orkut) የመሳሰሉት ዝነኛ “የአዳም ዘር መገናኛ”/ “ሶሻል-ኔትዎርክ” (Social Network) ከመጡ ወዲህ ወዳጅ ጓደኛችንን ፍለጋ መንገዳችን ኢንተርኔት ሆኗል። 

የአውሮፕላኑን አነሣኹ እንጂ በሌሎችም የሕዝብ መጠቀሚያ ሥፍራዎች  ለተጠቃሚው ከሚቀርቡት አስፈላጊ ነገሮች መካከል “ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት” (WIFI) አንዱና ዋነኛው ነው። አገር አቋራጭ አውቶቡሶች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና ቡና ቤቶች በተለይ ቡና በማፍላታቸው ብቻ ተኩራርተው አይቀመጡም። ደንበኛቸው ቡናውን እየጠጣ ኢንተርኔቱን እንዲጠቀም ነገሮቹን ያመቻቹለታል። ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው አደባባዮች እና ማዕከለ-ከተማዎች (ዳውን ታውንስ) በተወሰነ መጠን ርቀት “ነጻ ኢንተርኔት አገልግሎት” ይኖራቸዋል። በተለይም አየሩ ውጪ ለመቀመጥ የተመቸ በሚሆንበት በበጋው ወራት “ጨኔ-ኮምፒውተሩን” (ዶ/ር ፈቃደ ጭን ላይ የሚቀመጥ ኮምፒውተር ለማለት እንደሚጠቀምበት) ወይም ላፕ-ቶፑን ይዞ የፈለገውንና የፈቀደውን ይሠራል።

ዛሬ ጊዜ ኢንተርኔቱ እንዲህ ከቅንጦትነት አልፎ የማንኛውም አገልግሎት ጀርባ አጥንት ሆኗል። እንግዲህ አንድ ሰው ይህንን ለምዶ ሲያበቃ የዚህ አገልግሎት ወደሌለበት ሥፍራ ቢሄድ እንዴት ሊቸገር እንደሚችል ማሰብ አይከብድም።

ይህንን ሁሉ ያተትኩት እንዴት ባለ “የቴክኖሎጂ ዘመንና አገር” እንዳለን “ለማብሰር” በዚያም ላይ “አመለጣችሁ፤ እንቁልልጭ” ለማለት አይደለም። ማንኛውም በውጪ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ እንደሚሰማው ሁሉ “ምነው ይኼንን አገሬ ባገኘኹት” ከሚል ቁጭት ነው። ከአዲስ አበባ ወደየትኛው አቅጣጫ ተጉዤ ብሔድ፣ በፈለግኹት ሥፍራ የፈቀድኩትን ነገር ባገኘው፣ ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚያግዝ ስንት እውቀት ባገኙበት፣ የኪነ ጥበቡ ዓለም ምን ያህል በተጠቀመበት፣ ነጋዴው ምን ያህል ባተረፈበት፣ ገበሬው ምን ያህል ከዓለም በተገናኘበት የሚል ስሜት ያጭራል። የዻያስጶራው ኢትዮጵያዊ ልብማ እንዲህ የሚል ይመስለኛል፦

ተደርጎ ያውቃል ወይ እንዲህ ያል ሥርዓት፣
እግር ባሕር ማዶ ልቤ አገር ቤት
ግጥሟ ሙሉ በሙሉ የራሴ እንዳትመስላችሁ። የታዋቂው ደራሲ የአብዬ መንግሥቱ ለማ አባት ሊቁ የኔታ ለማ ኃይሉ (ወልደ ታሪክ) ስለራሳቸው የከሸኗትን ትዝታ አዘል ግጥም ለራሴው እንድትስማማ አድርጌ ቀይሬያት ነው። እርሳቸው ከትውልድ አገራቸው ወጥተው ሳይመለሱ ቢቀሩ የናፍቆታቸውን የገጠሟት ግጥም ነበረቻቸው። አዲስ አበባ እየኖሩ አገራቸው መቄት ውል ቢልባቸው የቀረጿት ትመስላለች።
ተደርጎ ያውቃል ወይ እንዲህ ያል ሥርዓት፣
እግር አዲሳባ ልቡና መቄት

ኢንተርኔቱ እንደ “መቄት” የራቀንን አገር ሁሉ እያቀረበ፣ የረሳነውን እያስታወሰ፣ የልጅነት ጓደኞቻችንን እያገናኘ ጥሩ ዘመድ ይፈጥርልን ይዟል። ዕድሜ ለ“ዲጂታል ካሜራ” እንጨት ለቅመን፣ ውሃ ተራጭተን፣ ኳስ ተጫውተን ያደግንባቸውን ሰፈሮች ፎቶዎች እያየን እንደሰታለን። ናፍቆቱ ሲበዛብን ደግሞ “ጉግል ሳተላይት ማፕ” ውስጥ ገብተን የሠፈራችንን “የሳተላይት ፎቶ” ለመመልከት እንጥራለን። ይኼንን ጽሑፍ የሚያነቡ ሰዎች “አዲስ አበባ”ን በጉግል ማፕ ቢመለከቷት በየአገሩ የተበተነው የሸገር ልጅ ሰፈሩን ሁሉ ምልክት አድርጎ፣ አቅልሞ፣ አቅልሞ ያገኘዋል። ናፍቆት የወለደው ይመስለኛል። ዕድሜ ለኢንተርኔት ናፍቆታችንን በአቋራጭ እንወጣዋለን።
ጨረስኩ።


አሁን ይኼንን ጽሑፍ ራሱን የምልከው በዚያው በኢንተርኔቱ አይደል?

ቸር ያሰንብተን።


© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።

5 comments:

hailemichael zedallas said...

I am so glad to see this blog.shows me that we have a lot of brothers who can reach reach us easily.we have kesis yared,melakeselam dejene,dn daniel,now you(ABABA) keep it up.MAY God bless our church.

Anonymous said...

ዲ. ኤፍሬም ጥሩ ተመልክተሃል እኔም ገጠመኜን ልበል፡፡

በዩኒቨርሲቲ ሳለሁ በትርፍ ጊዜዬ ልጆችን አስጠና ነበር፡፡ አንዱ ተማሪዬ ሳንፎርድ ተማሪ ነበረ። ሳስጠናው አማርኛ ይከብደዋል ብዬ አስቤ አለውቅም ነበርና አንድ ቀን ፈተና ከጨረሰ በኋላ የትምህርተ መጽሐፉን ምንባብ እንዲያነብልኝ ጠየኩት ለማንበብ ልማድ በእረፍቱ ጊዜ እንዲያዳብር በማለት መጽሐፉ ተገለጠ አርእስቱ ልብስ ነበር የሚለው ጀመረ ል ብቻዋን ብ ብቻዋን ስ ብቻዋን በመጥራት ልብስ በመለት ጀመር ደነገጥኩ ምናልብት ይሄንን ብቻ ይሆናል በማለት ወደታች እንዲቀጥል አደረኩ አሁንም አንድ አንድ ፊደል ይቆጥርና ክፍት ቦታ ሲያገኝ ቃላቶቹን ለማገጣጠም ይሞክራል። እንዴት እንደዚህ ይሆናል በማለት ተቆጣሁና እስተማሪህ ምን ይልሃል ብዬ ጠየኩት እንዴ ሰር(እሱ ያወጣልኝ ስሜ ነው) እኔ እኮ በአማርኛ ከክፍላችን ሁለተኛ ነኝ መምህሩም ይወደኛል ብሎኝ እርፍ። ከዚያን ቀን ጀምሮ ብዙ ዘዴዎችን በመጠቀም ቢያንስ ማንበብ በደምብ እንዲችል አድርጌዋለሁ። ልጁ ግን ፍላጉቱ ቢኖረውም የተረዳው እንዳልነበረ ግልጽ ነው ቤቱ ውስጥ ያሉት መጽሐፎች ሁላ እንግሊዘኛ ነበሩና። እኔም የአቅሜን የምችለውን አድርጌአለሁ ግን ምን ይህሉ ቤተሰቦች ይሄንን አስተውለዋል? በፍጹም አላስተዋሉም "መሬቱ የሚቀበለውን ሳይሆን ገበሬው የሚፈልገው ዘራ" እነዳለ ዲ. ዳንኤል ነገራችንን እረስተናል ብዙ ወጣቶች Identity crises ውስጥ ናቸው በሂፕ ሆፕ፣በፕሪሜር ሊግ፣በፋሽን ሽፋንነት ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሃገራቸው ከሆነች ቆይቷል ከእርሱ ዘመድ መሰድብ ይልቅ የሩኒ መሰደብ የፋብሪጋስ መሰደብ ይከፋዋል ስለዚህ በሰፊው ሊታሰብበት ይገባል።
በክረምት የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎት ማለትም በማስተማር አገለግላለሁ ሁሌም የምገነዘበው ይህንን ነው። መፍቴሄውም ደግሞ የትምህርት ቤት ባለቤቶችና መምህራን ላይ እንዳለ አምናሁ። ቤትን ከመገንባት ሰውን መገርባት ይበልጣልና ዲ. ኤፍሬም ከቻልክ ይህንን እርእስ መወያያና ብዙ ሰው ማንበብ እንዲችል ብታደር መልካም ነው። የኔን በዚህ አበቃሁ።

ኪዳነማርያም ዘደብረ ይድራስ

Anonymous said...

Keep it up Dn Ephrem ... we need more technological literature that can show being used in western ...this helps us (living in home) to be aware of to do something good ....Stay blessed!!

Anonymous said...

Wat is wrong on ur pic? Ayitayim eko.

Anonymous said...

Pls Efrim do anything wat u can on it. Maninetachin atirfilen.

Blog Archive