Sunday, January 9, 2011

የተለበዱ (የተሸፈኑ) መጻሕፍት

ከዕለታት አንድ ቀን ከቤቴ ወደ ትምህርት ቤቴ ስጓዝ ከገጠመኝ ገጠመኝ ልጀምር። ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ውስጥ የሆነ ታሪክ ነው። ሁል ጊዜ ከቤት ተነሥቼ ከምሠራበት ቦታ ለመድረስ ከ45 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ይፈጅብኛል። አንድ አስፓልት- ለአስፓልት የምትሄድ የኤሌክትሪክ ባቡር (Tram)፣ አንድ በምድር ለምድር እና በውጪም ገባ ወጣ እያለች የምትሄድ ባቡር (S-Bahn) እንዲሁም አንድ የምድር ለምድር ባቡር (U-Bahn) እና አንድ አውቶቡስ በየቀኑ እይዛለኹ። ስጓዝባቸው ግን እንዲህ አሁን እንዳልኩት የተንዛዛ እና አሰልቺ አልነበረም።

በጠቅላላው ግን ያለኝን ከ45 ደቂቃዎች ያላነሰ ጊዜ መጻሕፍት ለማንበብ ነበር የማውላቸው። ታዲያ ብዙውን ጊዜ የማነባቸው የአማርኛ መጻሕፍት ናቸው። መጻሕፍቱን በወረቀት እለብዳቸዋለኹ። ሌሎች መጻሕፍት ሲሆኑ ግን መለበዴን አላስታውስም። ይህንን የተመለከተ አንድ ጀርመናዊ ባልደረባዬ “ለምን ትለብዳቸዋለህ?” ሲል ጠየቀኝ። አስቤው አላውቅም ነበር። ከልጅነታችን ጀምሮ ደብተርም ሆነ መጻሕፍት እየለበድን ስንጠቀም ስላደግን አሁን መሸፈኔ ከዚያው ቀጥሎ የመጣ የቆየ ልማድ ነበር። ኋላ ዝግ ብዬ የሌሎቹንም ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼን ጠባይ ስመለከት ይህንን “የመጽሐፍ መለበድ” ጉዳይ አየኹባቸው። ነገሩ ደብተርን ከመለበድ፣ ወይም ለመጽሐፉ ንጽሕና እና ጥንቃቄ ከመጠበቅ የዘለለ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገመትኹ።

እንደማስታውሰው ባደግኹበት አካባቢም ሆነ ከፍ ብዬ ባየኋቸው ሥፍራዎች መጻሕፍትን እንደፈቀዱ እና በፈለጉት ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። መጻሕፍቱ የቀለም ትምህርት የምንማርባቸው እና ለዚያው ጉዳይ የሚያግዙንም ይሁኑ ከትምህርት ርዕሰ ጉዳይ ውጪ (Extra Curricular) ይሁኑ እንዲህ በቀላሉ አይገኙም ነበር። በተለይም የንባብ ጥማታችንን ለማርካት የመጻሕፍት ያለኽ በምንልበት በዚያ ዘመን የትምህርት ቤታችን ቤተ መጻሕፍት ከተወሰኑ አሮጌ መጻሕፍት ውጪ ተውሶ ወደ ቤት ለመውሰድም ሆነ እዚያው ተቀምጦ ለመኮምኮም የሚሆን ምንም ነገር አልነበረውም።

እንዳሁኑ “መጽሐፍ አዟሪ” የሚባል ነገር በከተማችን አይታወቅም። ሎተሪ አዟሪዎች እንደነበሩ ግን ትዝ ይለኛል። ጋዜጣ አዙዋሪነት እንኳን አልተለመደም ነበር። ጋዜጣ ያልኩት አዲስ ዘመን፣ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ እና ዘኢትዮፒያን ሄራልድ (The Ethiopian Herald) መሆናቸው ነው። የግል ጋዜጣ የሚባል በአገሪቱም አልነበረ። “ሰርቶ አደር” ጋዜጣ፣ “መስከረም” መጽሔት፣ “የካቲት” መጽሔት በአጎቴ በኩል የሚገኙ ቢሆኑም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይቆሽሹም ሆነ እንዳይቀደዱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጠን ነበር። ለዚያውስ የሚሉት ርዕሰ-ጉዳይ ሲገባን አይደል? አሁን አሁን “የሥጋ መጠቅለያ ናቸው” ከመባላቸው በፊት አዲስ ዘመን እና የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ዓይናችንን የገለጡልን ባለውለታዎቻችን ነበሩ። ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ በሙቅ እየተላቆጡ ግድግዳ ማሳመሪያ እንዲሆኑ በቤታችን ግድግዳ ላይ ከጥግ እስከ ጥግ ከተለጠፉ በኋላም እንኳን አገልግሎታቸው ብዙ ነበር። የምንባብ ማስተማሪያ መጽሐፍ የሚባል ለማናውቀው ልጆች የንባብ ማስተማሪያችን ግድጋዳ ላይ የተለጠፉት ጋዜጦች ነበሩ። ደግሞም ውድድርም ነበረው።

ታዲያ ሰርቶ አደር ጋዜጣ መለጠፍ ወንጀል ስለነበር ግድግዳ ለማሳመር ሳይታደሉ በሳጥን ታሽገው ይቀመጡ ነበር። አንዱ ሕጻን “አብዮታችን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል የሚለውን ፈልግ” ሲል ሌላው ሕጻን ፍለጋ ይጀምራል። እስከ 10 እስኪቆጠር ማግኘት አለበት። አለበለዚያ ተሸናፊ ነው። “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለውን ፈልግ ይላል አንዱ። ከዚያ “አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ….” እያለ መቁጠር ይጀምራል። ሌላው ፍለጋውን ይቀጥላል። በሰፈራችን ጋዜጣ የሚሸጠው ፖስታ ቤት ውስጥ ነበር። ጋዜጣው የሚመጣው በጠዋት ነው። በተለይ እንደ ዓለም ዋንጫ ባሉ ሰሞኖች ቶሎ ስለሚያልቅ በጠዋት ሄደን እንድንገዛ እንላካለን። ወንድሞቼ የሚገዙት ምናልባት በዋነኝነት ለስፖርቱ ገጽ ይመስለኛል።

 ዕድሜያችን ከፍ ሲል ከጋዜጣ ያለፈ ንባብ ፈለግን። ኩራዝ አሳታሚ ብዙ መጻሕፍት ቢያትምም ለእኛ ማን ሰው ብሎ ይገዛልናል? ደግሞስ “ሆዳችንን” ከቻሉ መች አነሣቸው? በዚያ ላይ ልብስ አለ፣ ደብተር አለ፣ እርሳስ እስክሪብቶ አለ። ለዚያውም ለስንት ልጅ!!! እንኳን ቤተሰቦቻችን ትምህርት ቤታችንም (ለላይብራሪው) መጽሐፍ አስቦ አይገዛም።

በዚህ መካከል ገና በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያለ ንባብ የሚወድ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ወደ ከተማችን መጣ። መጻሕፍት እንደጉድ የሚገዛ። ወንድሞቼ በአንዴ ተዋውቀውት ኖሯል። ከዚያ ከመጻሕፍቱ እየተዋሱ ማምጣት ያዙ። እኔና ጓደኛዬ ግርማ ወ/ሩፋኤል ከዚያ በረከት መካፈል ጀመርን።  ወንድሜ፦ “ይህንን መጽሐፍ በሦስት ቀን ውስጥ አንብባችሁ መልሱ” (እኔንና ግርማን መሆኑ ነው) ይለናል። እኛ፦ “እሺ” እንላለን። ከዚያ አንድ ቀን ከግማሽ ለእኔ፣ አንድ ቀን ከግማሽ ለግርማ እንወስዳለን። ከዚያ ካሳለፍን “የመጽሐፍ ገመዳችን” (“የእንጀራ ገመዳችን” እንደሚባለው) ይበጠሳል። ደግሞም እኛ ብቻ ሳንሆን የሰፈሩ ወጣት ያቺን መጽሐፍ በጉጉት ይጠብቃታል። ስለዚህ በወንድሜ ስም የመጣውን መጽሐፍ እኔና ግርማ ቶሎ አንብበን መመለስ አለብን። ታሪክ በለው፤ ልቦለድ በለው፣ ትርጉም በለው፣ ወጥ ሥራ በለው … “እንደ ጉድ” እናነባለን። የማይነበበው ያልተጻፈና ያልታተመ መጽሐፍ ብቻ ነው።

ማንበብ ብቻ አይደለም። ከየመጽሐፉ ያገኘነውን ቁም ነገር እንጽፋለን። ይኼንን ያሳየን ተስፉ ከበደ ነው። ግሩም የእጅ ጽሑፍ ነበረው። “በእሑድ ሬዲዮ” ላይ እንደሚቀርቡት ዓይነት “አጫጭር ቁም-ነገሮች” መርጦ ማውጣት ይችልበታል። “ሕይወት እና ሽንኩርት ያስለቅሳሉ” የሚሉ ዓይነት አባባሎች እኛ አንብበን የዘለልነውን እርሱ አያልፋቸውም። ፈልፍሎ ያወጣቸዋል። እኔም በኋላ ላይ የእርሱን “ደብተር/ ማስታወሻ” በእጄ ገለበጥኩት። ታዲያ በክረምቱ (ትምህርት ቤት ሲዘጋ) ወይ እንጨት መልቀም ወይም አንደኛውኑ እንዲህ የሰው ደብተር መገልበጥ ካልሆነ ሌላ ምን ይሠራል?

እንዲህ እንዲህ እያልን 12ኛ ክፍል ጨረስን። ከዚያ በኋላ ለወራት ቁጭ የምንልበት “የሥራ ፈትነት ጊዜ” ተጀመረ። የወንድሜ የመጽሐፍ ጓደኛ ያሉትን መጻሕፍት በሙሉ ልቅም አድርገን ያነበብነው ያን ጊዜ ነበር። ማንበብ ብቻ ሳይሆን ዝርዝራቸውንም በአንድ ትንሽ ደብተር ላይ በተርታ መዝግበን ይዘናቸው ነበር። የምናገኘው ዕውቀት ብቻ ሳይሆን እነዚያ መጻሕፍት ባይኖሩ ጊዜውስ እንዴት ይገፋ ነበር? ታዲያ መጽሐፍ መለበድ ይነሰን?

ዛሬ ከአገሬ ወጥቼ በምዕራቡ ዓለም ስኖር አንዱ መዝናኛዬ የመጽሐፍ መሸጫዎች ናቸው። የዚህ ሀገር መጽሐፍ መሸጫዎች (ለምሳሌ ቦርደርስ እና ባርነስ ኤንድ ኖብልስ) መዝናኛዎች ናቸው ማለት ይቻላል። አንድ ሰው መግዛት የሚፈልገውን መጽሐፍ ለመምረጥ ሲሄድ እዚያው ሻይ ቡናውንም ፉት እያለ ለቅምሻ ያህል ደግሞ የፈቀደውን መጽሐፍ ከመደርደሪያ ላይ ላጥ አድርጎ ማንበብ ይችላል። የምገዛው መጽሐፍ ባይኖረኝም እንኳን እዚያ ሁሉ መጽሐፍ መካከል ዞር ዞር ማለት ደስ ይለኛል። ሳስበው በልጅነት ለመጻሕፍት የነበረኝ ጉጉት “አልወጣልህ ብሎኛል” ብዬ አስባለኹ።

በዓይኔ ርዕሳቸውን ብቻ እያየኹ እየተደነቅኩ፣ እየተደመምኹ የምሔድበት ጊዜ አለ። መጽሐፎቹ ከብዛታቸው የርዕሰ ጉዳያቸው ዓይነት መበርከት ሁሌም ይገርመኛል። መጽሐፍ የማይጻፍበት ርዕስ የለም ማለት ይቻላል። ሰውን የተመለከተ ማንኛውም ነገር መጽሐፍ አለው። ልቦለድ፣ ኮምፒውተር ነክ ጉዳዮች፣ ኢኮኖሚ፣ ታሪክ በየዓይነቱ፣ ባልትና፣ ስፖርት፣ ሃይማኖት በየዓይነቱ ወዘተ ወዘተ በየመልካቸው ተሰድረዋል። የሕጻናት ክፍል ለብቻው ነው። ከሕጻናቱም በላይ ገና በለጋ ወጣትነት ደረጃ ላሉ ልጆች (ቲንኤጀርስ) የሚሆኑ መጻሕፍት ለብቻቸው ሥፍራ አላቸው። መጽሔቶች እና ጆርናሎች ለብቻ ናቸው። አቤት አበዛዛቸው።

ልክ እንደ መጻሕፍቱ በየርዕሰ ጉዳዩ መጽሔቶች አሉ። ሌላው ቀርቶ ስለ ንቅሳት (ታቱ) ብቻ እንኳን ራሱን የቻለ መጽሔት አለ። ስፖርት በየዓይነቱ አለው። እግር ኳስ ለብቻ፣ የአሜሪካ ፉትቦል ለብቻ፣ መኪና እሽቅድድም፣ ቦክስ ወዘተ በየራሳቸው ብዙ ብዙ መጽሔቶች አሏቸው። እንዲህም ሆኖ ከሌሎቹ ያደጉ የአውሮፓ አገሮች ጋር ሲነጻጸር አሜሪካ የአንባቢዎች አገር ነው ለማለት ይከብዳል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ከንባብ ይልቅ ወደ ማዳመጥ እና በቪዲዮ ወደ መመልከት ያደላል። ከጠንካራ ርዕሰ ጉዳይ ይልቅ ወደ ሙዚቃ፣ ኢንተርቴይንመንት እና “አስረሽ-ምቺው” ያደላል እየተባለ ይወቀሳል።  ይኼ “የአይ-ፓድ ትውልድ” እንደ ድሮ የአራዳ ልጆች “ጭንቅ አይችልም”። ንባብ ጭንቅ መሆኑ ነው። የማያነብ ትውልድ ለዕውቀት ሩቅ የሆነ ትውልድ ነው።

ይህ ሁሉ የመጽሐፍ ዓይነት ተደርድሮለት ማንበብ ሞቱ ነው።  ቅዳሜ እና እሑድ ከልጄ ጋር ወደ መጻሕፍት ቤቶች የመሔድ ልማድ አለን። እርሱን ይዤ ወደ ሕጻናት መጻሕፍት ተርታ በምንሄድበት ወቅት አንዱን መጽሐፍ ያነሣል ሌላውን ይጥላል። ለእርሱ ምኑ ነው? ሁሉም ልጆች እንደዚያ ናቸው። እነርሱ ዛሬ እያነሱ የሚጥሏቸው መጻሕፍት በልጅነታችን ልናገኛቸው አለመቻላችንን ለመንገር ደግሞ ገና ለጋ ናቸው። እንኳን ሕጻናቱ ያደጉትም ቢነገራቸው አይገባቸውም። ወደ መጀመሪያውና ወደ ተነሣንበት ታሪክ ስንመለስ “ለምን ትለብዳለህ መጽሐፍ?” ብሎ የጠየቀኝን ሰው ላስታውሳችሁ። መጽሐፍ ያልተለበደ፣ መጽሐፍ ያልተሸፈነ፤ መጽሐፍ ያልተሸለመ ምን ሊሸለም፣ ምን ሊሸፈን፣ ምን ሊለበድ ነው? አለማወቁ!!! 
ቸር ያሰንብተን

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።

12 comments:

hiwot said...

Ewnet new metsahitin menkebakeb alebin.
Astemariwochachin nachewna.
Joro lesetachew bizu yemilun alachew.
Yemayaneb sew benegegeru addis neger ayegegnim.

Thanks ephrem,Blogeh yegena setota honalenalech,bertalin!

Anonymous said...

ya
"books are real friends". btw haw to teach our children and make them ethical and good readers?? It worried me as a father. Please suggest on this.
tks for writing
May God and his mother be with all of us.

Anonymous said...

Dn epherm ,

I had the same coincidence, when I was in elementary school. But yours case was the worst. In my village primary school we had an excellent small laibary.. the Libarain was my best freind, I think I read all books there Abet....

Anonymous said...

Thank you Dn. Ephrem. You took me back to my childhood memories. That was how we grew up, always longing for something that we were not able to find easily. What amazing me a lot is not the economic obstacles we had then but the adults were ignorant of the need of the kids around them. We could have become better readers if they had helped us a bit more than letting us listen to their "YeBuna WeRe"! Any ways, it is better to learn from our childhood and take care of our kids-trying to understand their needs. Thanks for sharing this interesting story!

Anonymous said...

Dn. u remind me how I was stealing books (most of the time fictions) from my bro. I was living with him and he won't allow me to read fictions in education seasons. so what I was doing is that I will take the books and read few pages each day and put it where it was before he come home.I can say I have read lots of books in this way;good old days... oh I forget to tell him what I did. I think I have to tell him now after all it is a past story.
Thanks Dn.

Anonymous said...

ዲ/ኤፍሬም እንድትጀምር የረዳህ አምላክ በጉዞህ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሁን ያበርታህ ያጽናህ በዚህ የፈተና ዘመን ዘርፈ ብዙ ሆኖ መገኘት መታደል ነው ለኛም ተስፋ ሆንከን እግዚአብሄር ይመስገን በተለይ ለኔ በዚች ሰዓት ሃገሬን መንደሬን ስማቸውን የጠቀስካቸውን ጓደኞችህን ቤተሰባቸውን ስንቱን አስታወስከኝ የቅዱሳን አምላክ ጥበቃውን አብዝቶ ፍሬችሁ ያማረ እንዲሆን ይርዳን በርታ በርቱ ወላዲተ አምላክ ከጉናችሁ ትሁን

ከአቡዳቢ

Ze-Nazareth said...

በተለይም ወጣቱ ትውልድ ከንባብ ይልቅ ወደ ማዳመጥ እና በቪዲዮ ወደ መመልከት ያደላል። ከጠንካራ ርዕሰ ጉዳይ ይልቅ ወደ ሙዚቃ፣ ኢንተርቴይንመንት እና “አስረሽ-ምቺው” ያደላል እየተባለ ይወቀሳል። ይኼ “የአይ-ፓድ ትውልድ” እንደ ድሮ የአራዳ ልጆች “ጭንቅ አይችልም”።
You r really correct. This is what am worrying about. The same is true in Ethiopia. Shall we translate all "Birana" Books of our church and history to Video? or ...

Anonymous said...

የእኔ ብቻ የይመስለኝ ነበር ለካ ሁሉም ይለብዳል!!! ዲ/ን ጥሩ ጽሁፍ ነው::

Anonymous said...

I am glad to see many blogers like you, Dani, and others because you guys are double edged sword. You are educated in modern as well as Our Orhtodox religion education. Keep writing.

Samuel From Chicago

Anonymous said...

Dn Efrem thanks for sharing your experiance. My point is different . . . the title that you chose is not the right word (Amharic) - 'melebed' is not the proper word as it has no root word like 'lebede' . This word 'lebede' can't be further enumerated or 'ayibezam' . Please refer to the people of the language cause my teacher told me that the proper term for covering books like you mentioned is 'ledebe', which can be enumerated as 'meledeb' 'aledadeb', 'lideba', 'ledabi' ... etc. Please check; Thank you for reading my comment. Your little brother

Anonymous said...

hi adebabaye am i radio journalist what do u think broadcasts ur essay my experimentalism radio program.
thank u!
ayele

ፍሬ said...

ማንበብ ስትል ብዙ ነገርን ያስታወሰኛል ሁል ጊዜ ት/ቤት ከተዘጋ በሃላ ያሉትን ጊዜቶች የቺ ሁለት ወር ክረምት አንድ ልቦለድ መፀሃፍ ሲመጣ ለጊቢው ልጆች ሁሉ ነበር የሚዳረሳው አንዳንዴም እንጣላ ነበር መጀመሪያ ክላነበብኩኝ ተባብለን አንዴ ትዝ የለኛል ፍቅር እሰከ መቃብር ሳነብ በጣም አለቅስ ነበር እና አባቴ በጣም ስለተናደደብኝ እንዳለነብ ከልልኮኝ ነበር
መፀሃፍ መለበድ አለበት ስትል አባቴን አስታወስከኝ ትዝ ይለኛል መፀሀፋችሁ ተለብዳል እስቲ አሳዩኝ ይል ነበር የአመቱ መጀመሪያ መስከርም ላይ ት/ቤት ሲከፈት ሁሉንም ደብተሮቻችንን ለብደን ትምህርት እንጀምራለን ከዛ በሃል ግን አንድ ሴሚስተርም አይቆይም .....

Blog Archive