Monday, January 10, 2011

የጠፋ አእምሮ ፍለጋ

 ስቲፈን ኮልቤ (Stephen Colbert) እና ጆን ስቱዋርት (Jon Stewart) 
ይህንን መጣጥፍ በማዘጋጅበት ቀን በአሜሪካ “የአማካይ ዘመን ምርጫ” (Mid Term election) የሚባለው ምርጫ ዋዜማ ነው። ቴሌቪዥኑም፣ ሬዲዮውም፣ ጋዜጣና መጽሔቱም ሆነ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የላቸውም የሚባሉ የኮሜዲ ዝግጅቶች ሳይቀሩ ርእሰ ጉዳያቸው ይኸው የአማካይ ዘመን ምርጫ ነው። ፖለቲከኞቹ አንዱ ከአንዱ በልጦ እና ልቆ ለመገኘት የማያደርገው ጥረት የለም።
በብዙ ቦታዎች ሕዝቡም ስለ ምርጫው እንዲያስብ የሚያደርጉ ብዙ ዝግጅቶች በከተማ መካከሎች (ዳውን ታውን) ይዘጋጃሉ። ሕዝቡ እየዘፈነም፣ እየተዝናናም ይመርጣል፣ ያስመርጣል።


በዚህ በአሁኑ የምርጫ ሰሞን ዋዜማ ሁለት ስሞች ጎልተው እየተሰሙ ነው። ታዋቂዎቹ ኮሜዲያን ጆን ስቱዋርት (Jon Stewart) እና ስቲፈን ኮልቤ (Stephen Colbert) እንዲሁም ዝግጅቶቻቸው “The Daily Show” እና “The Colbert Report”።  እነዚህን ሁለት ሰዎች በተለይም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ስመለከታቸው የሰጠኝን ትርጉም ላካፍላችሁ ወደድኹ።


ሁለቱ ኮሜዲያን በየቀኑ ከሰኞ እስከ አርብ ለ30 ደቂቃዎች የሚያዘጋጁ፤ በአሜሪካ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እጅግ በጣም ብዙ ተመልካች ያላቸው ሰዎች ናቸው። በስላቅ እና ውስጠ-ዘ ቀልዶቻቸውና ዘገባዎቻቸው አሜሪካውያንን ወደፈቀዱት መንገድ መምራት እንደሚቻላቸሰው ፖለቲከኞቹም በቅጡ ስለሚረዱ ፕሮግራሞቻቸውን እንደ ዋዛ-ፈዛዛ የሚመለከት ፖለቲከኛ የለም። ስለዚህም መጽሐፍ ያሳተመ ሰው ቢሆን፣ ፊልም ያወጣ ቢሆን፣ አክተር ቢሆን ዳይሬክተር፣ ተመራጭ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነ ተርታ ባለሙያ የእነርሱን መድረክ እጅግ በጣም ይፈልጋል። በቅርቡ ራሳቸው ፕሬዚዳንት ኦባማ የፕሮግራሙ እንግዳ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ከሳምንት በፊት ደግሞ አዲስ መጽሐፍ ያሳተሙት የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ተረኛ ነበሩ።

በተለይም ከቶኒ ብሌየር ጋር የነበረው ቃለ ምልልስ የሚገርምም፤ የሚደንቅም ነበር። በሳቁና በቀልዱ መካከል በተለይም የኢራቅና የሕዝብ ጨራሽ መሣሪያዎች ጉዳይ ላይ ሲደረስ ኮሚዲያኑም ቀልዱን ወደ ጎን ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላብ-ላብ እስኪላቸው ፈጥርቆ ሲይዛቸው “እንዴ፣ ይኼ የኮሜዲ ፕሮግራም ነው ወይስ ሐርድ ቶክ?” አሰኝቶኛል። ስቴፋን ኮልቤ በበኩሉ የአሜሪካ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነውን ፈቃድ የሌላቸው “ሕገ ወጥ” ሠራተኞች ጉዳይ እና “እነርሱ በመምጣታቸው የምንሠራው ሥራ ሁሉ ተወሰደብን” የሚሉትን አሜሪካውያን ሐሳብ ተቀብሎ ይህንን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ቀልድ አዘል ጉዞ እንመለከታለን። ኮልቤ ብዙ የውጪ ሰዎች የሚሠሩትን እጅግ ከባድ የእርሻ ሥራ ለመሥራት ወደ እርሻ ይኼዳል። በእርሻ ቦታው ያሉ ሠራተኞችን፣ ቀጣሪዎችን ያነጋግራል። ራሱም ሥራውን ይችለው እንደሆነ ይሞክራል። ነገር ግን እንኳን በቅጡ ሊሠራው ሰውነቱን እንኳን መሸከም ሲያቅተውና በየመንገዱ ሲቀር ያሳየናል። ቀልድ የተቀላቀለበት ማጋነን ቢሆንም ጉዳዩ ኮንግሬስ ድረስ የሚያስጠራ እና ሐሳቡን እንዲገልጽ የሚያስደርግ ሆኖ በኮንግረሱ ተገኝቶ ቃሉን ሰጥቷል። በዚያም “የውጪ ሰዎች ሥራችንን ወሰዱብን” የሚለውን ክፍል በተሳልቆ እና በቀልድ አመክንዮዋቸውን ባዶ አስቀርቶታል።

ታዲያ እነዚህ ሁለት ሰዎች በዋሺንግተን የጠሩትና እጅግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የወጣላቸው በደፈናው ቀልደኞች ስለሆኑ ሳይሆን በውስጡ የመረረ ይሕዝብን እና የሀገርን ችግር የሚመለከት አንድምታ ያለው በመሆኑም ነበር። የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ መሪ ቃል የነበረው “To Restore Sanity” (አእምሮን ወይም አቅልን ስለመመለስ) ነበር። በሌላ አነጋገር ብንመለከተው አሜሪካ የአእምሮ ሕመም እናደለበት ሰው “አእምሮዋን ስታለችና አእምሮዋን እንመልስላት፣ ልቧ ጠፍቷል እንፈልግላት” የሚል ይመስላል። በተለያየ ልዩነት መካከል ተወጥራ የምትገኘውን አሜሪካንን ከገባችበት የመለያየት እና የመሳሳብ ጽንፈኝነት እንድትወጣ ለማሳሰብ የተዘጋጀ ዝግጅት ነው። ሀገሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በአክራሪዎች አደጋ ተወጥራለች ብትባልም “ሚዲያው እንደሚያራግበው አእምሯችንን እስክንስት ድረስ በፍርሃት መሸማቀቅ” የለብንም፤ “ዋነኛውን የአሜሪካ ሀብት እርሱም ነጻነትን” ማጣት የለብንም፣ እርስ በርሳችንም እንዲህ መበላላት የለብንም” በሚል ለሕዝብ የቀረበ ተማጽኖ ነበር። አሜሪካውያን በርግጥም ዕድለኞች ናቸው። ፖለቲከኞች ቢያጠፉ ሚዲያው፣ ሚዲያው ቢያጠፋ ኮሜዲያኑ፤ ሁሉም ቢያጠፋ ደግሞ ሕዝብ-በቀል (grass root movement) እንቅስቃሴዎች “ኧረ ተዉ!!” ይላሉ። “አእምሯችንን መሣት የለብንም፤ ይህ ጊዜ ያልፋል፤ ዘላቂውን ነገር አንርሳ” ሲሉ ያሳስባሉ።

የ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ይህ “ቼክ ኤንድ ባላንስ” እጥረት አለባት። ሌላው ቀርቶ በቤተ እምነቶች የሚነሡ መለያየቶች እንኳን በጥንታዊው ሃይማኖታዊ ሕግ መፈታት እንዳቃታቸው ስንመለከት፤ ፖለቲካዊ መስመሮች በሚለያዩባቸው እየተለያዩ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ አብረው መሥራት እንደ ሰማይ ርቆ፣ እንደ ጨለማ እና ብርሃን ተለያይቶ ስናገኝ፤ በማኅበረሰባዊ ተራክቦዎች የሚፈጠሩ መጠነኛ ልዩነቶች የሚፈቱበት አግባብ በቀላል መንገድ የማይደረስበት ሆኖ ሲታይ “የሣትነው አቅል/አእምሮ እንዲመለስ የሚያሳስብ” ሰው፣ ፈላስፋ፣ ፀሐፊ፣ ሰባኪ፣ ፖለቲከኛ፣ መምህር፣ የሃይማኖት መሪ ወይም ጋዜጠኛ እንደሚያስፈልገን ያመለክተናል።  ኢትዮጵያ ትንሣኤ ልቡና ወይም የጠፋ አእምሮ ለመፈለግ የሚወጣ ሰው ያስፈልጋታል።

የነዚህን ኮሜዲያን ሀሳብ ብንወስደው በቅርቡ በየመገናኛ ብዙኃን የተመለከትነው የአርቲስቶቹ የዘሪቱ ከበደ እና የሚካኤል በላይነህ ዓይነት ማንንም የማይጠብቅ፣ ከማንም የማይፈልግ ለሀገር መደረግ ያለበትን ለማድረግ የሚጀመር እንቅስቃሴን በብርቱው እንደግፋለን። ትናንት ከትናንት ወዲያ “ጋሽ አበራ ሞላ” የጀመረው፤ ወይም ወ/ሮ አበበች ጎበና ያሳዩት ዓይነት እንቅስቃሴ በሌላውም የሕይወታችን ዘርፍ እንዲታይ ለማድረግ እንጥራለን። ሀገራችን እና ማኅበረሰባችን ያሉበትን የተለያየ ችግር እና ክፍተት ለመሙላት ማኅበር እና ስብስብ፣ ድርጅት እና ትልቅ ካፒታል ሳንፈልግ “የጠፋ አእምሮ” ለመፈለግ (የጥንት ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት “ትንሣኤ ልቡና” ለማግኘት) እንወጣለን።  በሰከነ አእምሮ ለመነጋገር፣ ለማቀድ፣ ለመወያየት፣ እንችላለን።

ታሪክ እንደሚነግረን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሀገር እንዳለ አቅሏን ስታ አቅጣጫዋን የምታጣበት ዘመንና ጊዜ አለ። በሒትለራዊት ጀርመን ዘመን አንድ መሪዋ ብቻ ሳይሆን አያሌ አያሌ ሰዎች አብረው አቅላቸውን ስተው ነበር። የሞሶሎኒ ጣሊያንም እንደዚያው አብራ ሰክራ ነበር። የዓለማችን ግማሹ ክፍል ከ1917 የራሺያ አብዮት ጀምሮ ለ70 ዘመን በኮሙኒዝም አስተሳሰብ አቅሉን ስቶ ነበር። አፍሪካዊቱ ሩዋንዳ በዘር ማጥፋት መስመር የነጎደችው እንዲህ ልቧን አጥታ በነበረበት ወቅት ነው። እኛም በተለያዩ ዘመኖች ልባችን እየጠፋ በደም አበላ የታጠብንበት የተለያየ የታሪክ ክፍልና ዘመን አለን። በቃል ሳይሆን በጥይት ብቻ የተነጋገርንበት፣ በቅን ልቡና ሳይሆን በጠቆረ ልብን የተያየንበት፣ ለሀገር ይበጃል አይበጅም ሳይሆን እኔንና ወገኔን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም በሚል ጠባብ አስተያየት የተያየንበት ብዙ ዘመን አለ። ይህ ሁሉ ልብ ማጣት፣ የአእምሮ መነሣት ነው። ዛሬም ከዚያ አዙሪት አልወጣንም። እናም “የጠፋ አእምሮ ፍለጋ” እንውጣ።
ቸር ያሰንብተን


© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።

8 comments:

kelem. said...

Ephrem you raise awonderful issues its grate.

Anonymous said...

መጀመሪያ ሳልናገር የማላፈው ነገር የዚህ የጡመራ መድረክ መከፈት በጣም መደሰቴን ሲሆን ኤፍሬም እሸቴ እግዚሐብሔር ማስተዋል እና ጥበቡን እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ሰጥቶ ያለህን አብዝቶልህ ብዙ ፅሁፎችን እንደምትፅፍልን ተስፋ በማድረግ ነው
“የጠፋ አእምሮ ፍለጋ” ን በጥሩ እይታ ስለጻፍክልን እጅግ እናመሰግናለን
ላሜዳ …ከአ.አ

Anonymous said...

wonderful outlook !!!

Anonymous said...

Dn Ephrem, thank you very much for sharing your ideas. let me say one thing, having differnt website is very good idea. But if you add one thing , that is having one big blog manged by kes Yared, kes deje, dn Danieal, dn Ephrem...and others. You know nothing subsitite unity. I feel bad when every one move its own, is there a possibility to see blog by kes YYY and Dn XX or ....
Finally I know how much effort as you need to up date ur blog... let God Help you

Anonymous said...

Great Job Dn. Ephrem! A thoughtful analysis!!!

Anonymous said...

it is marvelous article keep it

frew said...

thank you. agreed!

Anonymous said...

dear dn efrem
you raised current and a very good point.
I have heared while dn.daniel preaching as"do we have alzimr or a problem to forget things?"
we ethiopians are like a dim light where we get on when someone triggers us and off when we lose the agent to trigger be in religion,politics,culture and our social value.
we should back to our former self and follow our forefathers integrity.
God bless you and your work

Blog Archive