Tuesday, February 1, 2011

የአሜሪካ ኑሮ - በኢትዮጵያ አእምሮ

“ወፍ እንዳገሯ ትጮኻለች” የሚል የአበው (የእመው) ብሒል አለ። የትም ሄደች የት ጠባዩዋ እና ድምጿ፣ ዜማዋ እና ተፈጥሮዋ ያው እንዳገሯ ነው። ሰውስ ከወፍ ምን ይለያል? በሄደበት ሥፍራ እንዳገሩ ያዜማል፣ እንዳገሩ ይበራል። ይህ “እንደራሱ አገር፣ እንደራሱ ልማድ” መብረር አንዳንዴ የማይፈልጉትን፣ የማይፈቅዱትን መዘዝ ይዞ ይመጣል። “የአሜሪካ ኑሮ -  በኢትዮጵያ አእምሮ” ስለዚህ የምታወራ መጣጥፍ ናት።

ከጥንቱ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ልውውጥ ጉዞ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ግብጽ፣ ቻይና፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ብሎም ዘልቆ ወደተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የመጓዝ የቆየ ልማድ ቢኖረንም ወደ ሌላው ዓለም በብዛት ከመፍለስ አንጻር ያለን ልምድ እና ተሞክሮ ግን ብዙ አይደለም።

ቀደም ብለን ንግሥተ ሳባን ወይም ከእርሷ በፊት ያሉትን ተጓዦች፣ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ባለው ዘመን ደግሞ የኢትዮጵያዊቱን ንግሥት የንግሥት ሕንደኬ የገንዘብ ባለሟል ሚኒስትር የነበረው “ባኮስ”ን፣ ወይም ደግሞ በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲጀመር መሠረት የጣለውን “አባ ጎርጎርዮስን”፣ አልያም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአሜሪካ “ሥነ ኢትዮጵያን፣ Ethiopianism” ያስፋፋውን ሐኪሙ ዶ/ር መላኩ በያንን ወዘተ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

እንዲህ “ራሳችንን ለማጽናናት ያህል” ወደኋላ እየጠቀስን የምንጽናናበት የታሪክ ቁራሽ ባናጣም፣ የእኔ ትውልድ ከአገሩ ሲወጣ እግሩ እንደመራው፣ ዕጣ ፈንታ፣ ጽዋ ተርታው እንዳለው በባሌም በቦሌም፣ ቀደም ብሎ ደግሞ በሱዳንም በሶማሊያም፣ በኬኒያም በጂቡቲም፣ ባገኘው በር ሁሉ ነው። አንዳንዴም መውጣቱን እንጂ መድረሻውን በእርግጥም አልሞና ተልሞ ላይሆን ይችላል። “እደርስበት አገር” ያለውን ሳይደርስበት በበጎም በክፉም በመንገድ ላይ ሌላ መድረሻ፣ ሌላ ሥፍራ ላይ ለምዶ ይቀራል።

አወጣጣችንና አኗኗራችን እንዲህ እንደሌላው (የአውሮፓ ቱሪስት?) አልጋ በአልጋ ባለመሆኑም ተጓዡ ስለሚሄድበት አገር “ሙሉ መረጃ” የሚሰጠው (የኛ ጋዜጠኞች እንደሚሉት) አግኝቶ ወይም አንብቦና ተዘጋጅቶ ላይሆን ይችላል። ከገጠመኝና ካየኹት፣ ከወዳጅ ከዘመድ ከምሰማው፣ በተለይም በአሜሪካ ያለነው፣ ኑሯችንና ሕይወታችን በርዕሱ ላይ እንደተጠቀሰው የአሜሪካ ኑሯችን “በኢትዮጵያ አእምሮ” ሆኖ እናገኘዋለን። አንዳንድ ምሳሌ ላንሣ።

በቅርቡ ወደ አሜሪካ የመጣ አንድ “የዲቪ እድለኛ” ከሥራ በኋላ ባለችው ትርፍ ጊዜ ቁጭ ብሎ ሻይ ቡና ሲል አጠገቡ ያለውን ትርፍ ወንበር የምትጋራ አንዲት አሜሪካዊት ወጣት ትመጣለች። ወንበሩ ባዶ መሆኑን አስፈቅዳ ትቀመጣለች። ወንድማችንም (እርሱ እንደሚለው) ባለችው እንግሊዝኛ፣ በምልክት ጭምር “ጨዋታ ይጀምራል”። እናም ሻይ ቡናዋን ጨርሳ ለመሔድ ስትነሳ እርሱም አብሮ እያካሄዳት፣ የሚሠራበትን ቦታ እየነገራት፣ ስልኩን እየሰጣት ይሰናበታታል።

በነጋታው ጠዋት ከሥራው ቦታ ከመድረሱ እርሱን የሚፈልጉ ፖሊሶች ይመጣሉ። “ትናንት በአንዲት ሴት ላይ ባደረሰው ጾታዊ ትንኮሳ” ፖሊስ እንደሚፈልገው ሲነገረው (እርሱ እንደሚናገረው) ያለችውም እንግሊዝኛው ጠፋችው። መሬት ተከፍታ ብትወጠው ተመኘ። “ለመሆኑ ምን ብለሃት፣ ምን አድርገህ ነው?” ሲባል ለካስ አጅሬው ቆንጂትን ሲሸኝ እጁን አደብ አላስገዛ (አላሳረፈ) ኖሯል። “መቸም የወንድ ወጉ አይደል?” ብሎታል በእርሱ አነጋገር። ይህ “የወንድ ወግ” ያለው አስተሳሰብ ፖሊስ አስጎትቶበታል። መቸም አገሩ አሜሪካን ነውና ጠበቃ ይዞ ለመከራከር ወይም “አዲስ መጤ መሆኑን ተጠቅማ ሌላ ጥቅም በመፈለግ እንደመጣችበት” ጠበቃ አቁሞ ለመከራከር መንገድ ላይ ነው።

ከዚህ አነሥ ያሉ ሌሎች ብዙ ገጠመኞች ይኖራሉ። ለምሳሌ አሁን እንዳለንበት እንደዚህ ዓይነት የብርድ ሰሞን (ዊንተር) ላይ ቀለል ያለ ልብስ፣ ለብርድ የሚያጋልጥ፣ አሊያም በረዶ የማይገፋ ጫማ፣ ወይም አንገት ላይ ምንም ሳያደርግ ልክ አዲስ አበባ ወይም አንዱ ሞቃት ከተማ እንዳለ ያለ አለባበስ የለበሰ ሰው ሳይ “ምናልባት አዲስ የመጣ ይሆን?” ብዬ እጨነቃለኹ። እውነትም ከአንድም ሁለት ሦስቴ ግምቴ ትክክል ሆኖ አግኝቼዋለኹ። ታዲያ ስለምንሄድበት አገር “የአየር ሁኔታ” እንኳን የምናውቅበት መንገድ ሳይኖረን ስለሌላው ነገር በምን እናውቃለን ብዬ አስባለኹ።

መቸም አሜሪካን አገር ያለ ሰው ሥራው አይጠየቅም እየተባለ ይቀለዳል። በተለይ ጠያቂው ኢትዮጵያ ያለ ሰው ከሆነ። ብዙዎቻችን ግን ገና ስንመጣ የምንሠራው በጉልበቱ ሥራ ላይ ተሠማርተን ሱፐር-ማርኬቶች፣ ነዳጅ ማደያዎች ወይም አነሥተኛ ዕቃ መሸጫ ሱቆች ውስጥ ነው። የአገሩን ቋንቋ እና ይትበሐል፣ ዘይቤና ጠባይ ሳንለይ የተቀበሉን ሰዎች ባገኙልን እና በፀደቁብን ሥራ ቦታ እንገባለን። ዕድለኛ የሆነ ሰው ከሆነ የተቀበለው ወዳጅ ዘመድ ወይም አሠሪው ምን ማድረግ እንዳለበት ወይም ምን ማድረግ እንደሌለበት ይነግረዋል። እናም ከብዙ ችግር ያተርፈዋል። ሕይወቱን ጨምሮ።

አንድ ወደዚህ አገር የመጣ ወገናችን እንደማንኛችንም በአንዱ ዕቃ መሸጫ ቤት ይቀጠራል። ቤቱ ብዙ ሰው የሚስተናገድበት ከመሆኑ አንጻር የእጅ ዓመል ያለባቸው ሰዎችም የሚመጡበት ነው። እናም እነዚህ የእጅ አመል ያለባቸው ሰዎች ወደ ሱቁ ገብተው ዕቃ ሲሰርቁ ቢታዩም ዝም ብሎ መጋፈጥ ከባድ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። በተለይ ምሽት ላይ፣ ሰው በሌለበት ከሆነ እያዩ እንዳላዩ ማሳለፍም አለ። ያ ወዳጃችን ግን እርሱ በሚሰራበት ቦታ ሌላ ሰው መጥቶ ዕቃ ማንሣቱን እንደ ድፍረት፣ እንደ ንቀት ቆጠረው። አንድ ደርዘን ሙሉ ቢራ አንጠልጥሎ የወጣውን ሰው ለማስጣል ያገኘውን ነገር ይዞ ካልተማታኹ ብሎ ይጋበዛል። መስረቅ ልማዱ የሆነ የሚመስለው ያኛው ሰው በድፍረቱ ተገርሞ፣ ነገር ግን ቢራውን ሳይመልስለት ይዞ ይሄዳል።

ኋላ ዘግይት ብሎ የሱቁ ባለቤት ሲመጣ የሆነውን ነገር በሙሉ አጫወተው። ባለ ሱቁ ያ ወዳጃችን ባደረገው ነገር ተደስቶ “ጎበዝ” አላለውም። ሰውየውን ተከትሎ መውጣቱ፣ ግብግብ መግጠሙ ትልቅ ስሕተት መሆኑን ነገሮ፣ ከፈለገ ለፖሊስ መደወል እንጂ የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል በእንደዚህ ዓይነት እሰጥ-አገባ ውስጥ መግባት እንደሌለበት ይመክረዋል።

እውነትም ያ ወዳጃችን ዕድለኛ ነበር። ሽጉጥ ወይም ሴንጢ ቢጤ ሊይዝ በሚችለው በዚያ ዓይን አውጣ ሌባ አደጋ ሊደርስበት ይችል ነበር። ከሌባው ጋር ግብግብ የገጠመው ያው አገር ቤት ባለን አስተሳሰብ ነገሮችን ገምግሞ ለመሆኑ ራሱ አጫውቶኛል። እዚህ ደግሞ ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙበት መንገድ የተለየ መሆኑን ቆይቶ ነው የተረዳው። አሁን አሜሪካንን በአሜሪካ አስተሳሰብ እና አእምሮ መመዘን ጀምሯል። ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት በዚህ አጋጣሚ እንኳን ድረ ገጾች ጃገማ በየነ የተባለ የአንድ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን መገደል የሚዘግብ ዜና እያስነበቡ ነው። ይህ የአትላንታ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ የተገደለው በሚሠራበት ሱፐር-ማርኬት ውስጥ ነው። መገደሉን እንጂ የተገደለበትን ሁኔታ ስላላወቅኹ ብዙ ማተት አልችልም። 

በቅርብ የማውቀው አንድ ሌላ ታሪክ ልጥቀስ። ይህ በቅርብ የማውቀው ሰው የዲቪ ሎተሪ ዕድለኛ ሆኖ ወደ አሜሪካን አገር ሲመጣ ሊቀበሉት ቃል የገቡለት ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ቃላቸውን መጠበቅ በሚገባቸው በመጨረሻዎቹ ቀናት እና ሰዓታት ድምጻቸውን በማጥፋታቸው የቆረጠው ቲኬት ሳይቃጠል ሻንጣውን ሸክፎ ይበራል። ከአውሮፕላኑ ሲወርድ ማንም እንደማይቀበለው ቢያውቅም “ለፖሊሶቹም ቢሆን ብነግራቸው የትም አይጥሉኝም። ቢያንስ ማደሪያ ይሰጡኛል” የሚል የራሱ እምነት ነበረው። ነገር ግን አውሮፕላን ማረፊያ የተቀበለውም ሆነ ማረፊያ የሰጠው ፖሊስ አልነበረም። እንባውን የተመለከቱ ኢትዮጵያውን “ቢያንስ ቤተ ክርስቲያን እናድርስህና ለነፍስ ያለ ያስጠጋህ” ብለው ወሰዱት። በዚያ በመድረክ ሲያስተምር ከኢትዮጵያ ጀምሮ የሚያውቀው ሰው አገኘ። እግሩ ላይ ወድቆ “ካልወሰድከኝ አልለቅህም” አለ። ያ ለጋ ወጣት ከዚያ መምህር ጋር ለአንድ ዓመት አብሮ ቆይቶ፤ ቤተዘመድ ሆኖ፣ ለትምህርት ከተማውን ሲቀይር በእንባ ተለየ።

እንደዚህ ወጣ “የአሜሪካ መንግሥት ሁሉን ነገር አመቻችቶ ይቀበለናል” የሚል የተሣሣተ መረጃ ይዘው ንግዳቸውን ዘግተው፣ ቤታቸውን ሰጠው፣ ቤታቸውን፣ መሬታቸውን ወይም ሌላ ያላቸውን ጥሪታቸውን “እንደፈረሰ ትዳር” ወዲያ ወዲህ ብለው የሚመጡ ሰዎች እንዳሉ ብዙ ጊዜ ሲነገር ይሰማል። አሜሪካ ቢመጡ፣ ዲቪ ቢሞሉም ሆነ ቢሰደዱ በአብዛኛው ዓላማው ኋላ ተመልሶ ተሻለ ኑሮ ለመኖር ይሆናል። ኋላ ተመልሶ የማይገኝና በብዙ ዘመን የተገነባ ጥሪት በትኖ መምጣት ግን የሚያሳየው ነገር ቢኖር ስለ አሜሪካ የምናስበውና የምንወስነው ከእውነታው በራቀ መረጃ ላይ መሆኑን ነው

ኢትዮጵያ ውስጥ ባላቸው እውቀት በገቡ በበነጋው “አሜሪካ እጃቸውን ስማ የምትቀበላቸው” የሚመስላቸው ብዙ ምሁራን፣ አገር ቤት ያላቸውን ንግድ ወዲያው የሚስፋፋ የንግድ ሥራ የሚጀምሩ የሚመስላቸው የንግድ ሰዎች፣ ለራሳቸው መጦሪያ ከመንግሥት አግኝተው ለልጅ ልጆቻቸው ነጻ ትምህርት የሚያገኙ የሚመስላቸው ወላጆች፣ በቲቪ እና በፊልም እንደሚያዩዋቸው ወጣቶች እነርሱም በአንድ ጀንበር ከታዋቂነት ሰገነት፣ ከሆሊዉድ ምንጣፍ የሚወጡ የሚመስላቸው ለጋዎች ወዘተ ማየት የተለመደ ነው። እውነታው ግን ከዚህ በፍፁም የሚለይ ሆኖ ሲያገኙት ከሰውነት የክብር ደረጃ ተሽቀንጥረው የሚወድቁ፣ የአእምሮ መታወክ ወይም የትዳር መናጋት የሚያጋጥማቸው ብዙ ወገኖች ይኖራሉ።

ነገሩና ችግሩ “አሜሪካንን በኢትዮጵያ አስተሳብ መመዘን” ይመስለኛል። ከተቻለ “በአሜሪካ አስተሳሰብ እና አእምሮ በኢትዮጵያ መኖርን” እመለስበት ይሆናል። 


ለዛሬ በዚህ ይቆየኝ። 


© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ. ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይቻልም።


   

21 comments:

ጌታሁን said...

ጠቃሚ ምክር ነው፣ ቃለሕይወት ያሰማልን፡፡

Anonymous said...

በጣም ደስ የሚል መጣጥፍ ነው::ቀጥልበት አንድ ቀን ብዙ አንባቢና ሃሳብ ሰጭ ይኖራል ብዬ ተስፍ አደርጋለሁ:: በርታ::

Anonymous said...

ሰው ለሰው መድኃኒቱ የተባለው በዚህ ምክንያት መሰለኝ። እግዚአብሔር ይስጠው ቤቱ ቢወስደው የቀን ጅብ ሳይበላው አመለጠ። ቢመክሩት ህይወቱን ለአደጋ ከማጋለጥ ተረፈ። የምትጽፈው ሁሉ ደስ ይለኛል አትጥፋ እጅህ ይባረክ!!

Anonymous said...

True that Dn.Epherem,even for those with good understanding i can say it is a big institution everyone will gonna lern PAICENCE and if then NEVER GAVE UP.......

Anonymous said...

ዲን. ኤፍሬም,
ጥሩ መልእክት ነው!
አንዱ ታሪክ እኔም በራሴ ያደረግሁት ነው። ሰው እንደሌለ በመቁጠር እቃውን አነጠልጥለው እየተንገማለሉ ሲሄዱ ብታይ ምን ይሰማሃል። አሁንም ችግሩን ባውቅም የማደርገው ይመስለኛል። “የአሜሪካንኑሮበኢትዮጵያአእምሮ”!!!

Anonymous said...

እውነት ብለሃል እረ ብዙ ገተመኞች በርታ ጠንክርልን

Anonymous said...

በጣም ጥሩ ትምህርት ነው::

Anonymous said...

dn ephrem በጣም ጥሩ ጡሁፍ ነው የማስበውን ነገር ነው
ሌላ ምን ይታየጋል መሰለሀ በዚህ አሜሪካ ላለነው
ስለ ቤት
ስለ መኪና
ስለ ጥቃቅን ንግድ ያለን መረጃ አናሳ ነውና
ሁሉም ያለውን ህሳብ ቢሰጥ

Sam ze Calgary said...

Dn Efrem, Thank you. You remind us what we did. It gives good information for our youth. I am eager to see the next topic.

Mine said...

wendimacin berta mechem yehulachinim lib surgery bisera yalewu kegna gar aydelem malete ezih Ethiopia aydelem yalewu American newu ena zim belen bechifin endanasib ena endanemegn teru milketa newu Ene bebekule temire lememtat kalhone lelela Sidet kebad endehone temirebetalehu wey mesededem kehone beki mereja sayizu meguaz yehiwot adega newu.

betam tiru tsehuf newu berta besedet yalutin wegenochaachinin amlake kidusan kehatiyat besteker melkamun hulu adergo le hagere Ethiopia beselam yabkachewu.

Ameha said...

ወንድማችን ዲያቆን ኤፍሬም በቅድሚያ የከበረ ሠላምታዬ ይድረስህ። የተነሳው ርዕስ አዲስ ለመጡትም ሆነ ገና ወደ አሜሪካ ለመምጣት ላሰቡ ወገኖቻችን በጣም ጠቃሚ እንደሚሆን አምናለሁ። ምንም እንኳ ብዙዎች ወገኖቻችን የውጭ ሀገር ኑሮ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ ቢገለጽላቸውም፣ ያለ መታደል ሆኖ እውነታውን ላለመቀበል "እሱ ሀብታም እየሆነ እያየሁት እሱን እንዳልጋፋው፣ እሱን እንዳላስቸግረው፣ ሊረዳኝ ስላልፈለገ ብቻ ክፉ ክፉውን ያወራልኛል" በማለት ራሳቸውን ስለሚደልሉ ወይም ስለሚያሞኙ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ለአደጋ ሲጋለጡ ይስተዋላል። አንተም ወንድሜ በተለያዩ ምሣሌዎች ችግሮቹን ለማሳየት የበኩልህን ጥረት አድርገሃል።
እንደ እኔ፣ እንደ እኔ የሚታየኝ፣ ማንም ሰው አገር፣ ግዛት ወይም አካባቢ ሲቀይር ኑሮ ከመጀመሩ ወይም ሥራ ከመያዙ አስቀድሞ ስለዚያ አገር ወይም አካባቢ ሕግና ደንብ፣ ህብረተሰቡ ቦታ (value) ስለሚሰጣቸው ጉዳዮች፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያላቸው ጠባያት (በኛ ባህልና እምነት ያልለመድናቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት)፣ የአየሩ ሁኔታ፣ አመጋገባቸው፣ አለባበሳቸው፣...ወዘተ መጠየቅ ወይም ማንበብ ይኖርበታል። ይህንንም ማድረግ የሚችለው ደግሞ ወይ ጥሩ ዘመድ ሲኖረው (ለዛውም እሱን ቁጭ ብሎ የሚያስረዳ ሲገኝ) ወይም እንግሊዝኛ አንብቦ መረዳት የሚችል ሲሆን ብቻ ነው። አለበለዚያ ግን "ጨረቃ ላይ ወደቀ" ማለት ነው።
ወንድሜ ዲያቆን ኤፍሬም! እንደምገምተው ለሀገሩ ባዳ ባለመሆንህ የኛ ከሙኒቲ ቢሮ ውስጥ አዲስ ለመጡ ወገኖች በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት ካለ አይተህ፣ የራስህን ሀሳብ ጨምረህ ከቤተሰብህና ከሥራህ ጊዜ ትንሽ ቀንሰህ ብታዘጋጅ ምን ይመስልሃል? እኔ ብዙ ባላውቅም በዚህ ጉዳይ ሊተባበሩህ የሚችሉ ወገኖችንም ድጋፍ ብትጠይቅ የሚያስከፋ አይመስለኝም። ከዚያ በተረፈ ተጨማሪ መረጃ ለሚፈልግ የሚከተለውን ድህረ ገጽ መመልከት ይችላል። www.welcometousa.gov ወይም ደግሞ ይህንን ፒ.ዲ.ኤፍ. ዶኩመንት download ማድረግ ይችላል። http://www.uscis.gov/files/nativedocuments/M-618.pdf
በተረፈ ዲያቆን ኤፍሬም አገልግሎትህን እግዚአብሔር ይባርክልህ!

Anonymous said...

አዬ አሜሪካ!
በቅርቡ ነው የመጣሁት፡፡ እንደ መታደል ሆኖ አበባ ይዞ የሚቀበል ቤተሰብ ስለተቀበለኝ ዱላስ አውሮፕላን ማረፊያ ኧረ ውሃ በላኝ ብዬ አልጮሁኩም፡፡ ተመስገን ልበላ፤ ለካ ይህም አለ፡፡ እርግጥ በአሜሪካ ፍቅር ጥንብዝ ብዬ የሠከርኩ አልነበርኩም፡፡ ሰው ሆኖ ሆድ የማይብሰው የለምና አንዳንድ ቀን ሆድ ሲብሰኝ የነበርኩበትን ከተማ ብቻ ሳይሆን የምር የማልጨክንባትን እንደ ስዕለት ልጅ የምሳሳላትን ኢትዮጵያን ሳይቀር ጥዬ መውጣት እመኛለሁ፡፡
የምለምነው ነገር ደረሰ፡፡ ባሥራ አንደኛው ሰዓት የሞላሁት ዲቪ መጣ፡፡ ሲያመጣው አንዳንድ ጊዜ … እንዳለው መሆኑ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ቪዛ ለማግኘት መረጃ ማዘጋጀት የጀመርኩት ቀጠሮው ሊያበቃ 10 ቀን ብቻ ሲቀረው ነበር፤ ግን ተሳካ፤ ቪዛው ለ6 ወር እንደሚያገለግል ተነገረኝና ረዥም ጊዜ ተሰጠኝ፤ ደስ አለኝ አገሬ ለመቆየት፡፡ የጊዜ ባቡር አይቆምምና ቪዛው ሊቃጠል 17 ቀን ሲቀረው በስንት ውትወታ በዕለተ ቅዳሜ አገሬን ለቅቄ ዋሽንግተን ዱላስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን አረፍኩ፡፡
እንደ እድል ሆኖ ኢትዮጵያ እያለሁ፤ ከረዥም ልፋትና ጥረት በኋላ ከጓደኞቼ ጋር የጀመርናት አነስተኛ የአገልግሎት ሰጪ ንግድ ቡቃያ ላይ ደርሳ ለፍሬ በቃሁ እያለች ነበርና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የድርሻችሁን ማለቷ የሚቀር አልነበረም፡፡
እንደ እድል ሆኖ አሜሪካ የገባሁት ደግሞ የኢኮኖሚው ቅራሪ ላይ መሆኑ ነው የሚገርመኝ፡፡ ይቺ የዓለም ቁጥር አንድ ሃብታም አሜሪካ በበጀት ጉድለት ተዘፍቃ፣ በሥራ አጥ ቁጥር ተጥለቅልቃ፣ ዲሞክራቶቹ የሚሉት እውነት እየሆነ ከመጣ ደግሞ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው የሚባለው የመካከለኛ ገቢ ክፍል (middleclass) እየጫጨ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ እዚያ ሆነን እገሌ ዶላር ላከ፣ ከአሜሪካ መጣ፣ የአቶ/ወ.ሮ እገሌ ልጅ ለቤተክርስቲያን ማሠሪያ በዶላር ይህን ያህል ላካች ተብሎ ለዶላሩ ይሁን ለስዕለቱ ግልጽ ባልሆነ መልኩ ዶላር በእልልታ ስም ስንቱን ኢትዮጵያዊ ልቡን አሸፍቶታል መሰላችሁ፡፡ ዛሬ ግን ዶላር በዓለም አቀፍ ግብይት ከዩሮ እና ፓውንድ ለጥቆ በ3ኛ ደረጃ ተሰልፎ ይገኛል፡፡
በእርግጥ አሜሪካ ጥሩ አገር አይደለችም ማለት አይቻልም፡፡ ቢቻልም የሚያምን ሰው የለም፤ የሚያሳምን ማስረጃም ማቅረብ ያስቸግራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ቀን መጻፍ ይቻል ይሆናል ምክንያቱም አሜሪካንን ስላየናት፣ ስለኖርንባት ብቻ እናውቃታለን ማለት አይሆንምና፡፡
በዚሀ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያውን ዲቪ አመልካቾች ቁጥራቸው ከ500ሺህ በላይ ሆኖ የአሜሪካንን መንግሥት በማስገረሙ ይመስላል የወርኃ ኅዳር የአፍ ማሟሻ ዜና እርሱው ነበር፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቅ ግን መልሱ ሁለት ይመስለኛል፤ በእኔ አመለካከት፤
1. የውጪው ዓለም አኗኗር የአእምሮ ሰለባ መሆናቸን ነው፡፡ ፊልሙ፣መኪናው፣አለባበሱ፣ ሙዚቃው፣ ስታዲየሙ፣ ማስታወቂያው፣በፊልም ውስጥ የሚታዩት የረቀቁ የመሠረተ ልማት ጥልፍልፎች፣ ኮምፒውተርና የሞባይል ቴክኖሎጂ፣ ወደ አገር ቤት ብቅ የሚለው ጅንኑ ኢትዮጵያዊ ተደማምረው ገነትማ ያለችው አሜሪካ ነው ብለን እንድንደመድም አድርጎናል፡፡
2. ኢትዮጵያ አምራች ለሆኑት ዜጎቿ በሚያመረቃ ደረጃ የሥራ መስክ መክፈት ያለመቻሏ ናቸው፡፡
ቶሎ አልሞቅም፤ እንኳን በማይክሮ ዌቭ፣ በጋዝም ያው ነኝ፡፡ አዲስ አካባቢን፣ አዲስ ሰውን ለመለማመድ ጊዜ የሚያስፈልገኝ ነኝና ቨርጂኒያ፣ዲሲ፣ ሃገረ ማርያም ግጥግጥ ያሉትን ከተሞች እንዲህ በቀላሉ የሚሞከር አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ለእንግሊዝኛ ሩቅ አይደለሁም ያልኩት ሰው የአነጋገሩ ዘይቤ ተለወጠና የወፍ ቋንቋ ሆነብኝ አንድ ደንበኛ ሃንድከርቺቨ (handkerchief) ስትለኝ አቤት ያልኩት እስኪበቃኝ በሳቅ አንፈቅፍቆኛል፡፡ በራስ መተማመን የሚባለው ነገር በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ጭራስ አብሮኝ የተፈጠረ አልመስልህ እስኪለኝ ሸሸኝ፡፡ አሁን አሁን በጥቂቱ ልቅረብህ እያለኝ መሆኑ ደግሞ መልካም ዜና ነው፡፡ ለእኔ ሁሉም ነገር አዲስ ነው፡፡ ባንክ ቤቱ ኤሌክትሮኒክስ ነው፤ አውቶቡሱ ኤሌክትሮኒክስ ነው፣ ሰው ራሱ ኤሌክትሮኒክስ ነው (ሞባይል፣ ኮምፖውተር፣ ሪደር ላይ ቸክሎ) እንኳን እኔን እጥፍቶ ጠፊውንም ከቁብ አይቆጥርም፡፡ በዚያ ላይ የፖሊስና የሜትሮ አክሰስ የሚባሉት፣ የእሳት አደጋ መኪኖች ጩኸት ልቤን ያርዱታል፤ አደጋ ሳይሆን የጥፋት ቀን ያስመስሉታል፡፡ በሩ ደስ ሲለው ተሽቀንጥሮ ይከፈታል፣ ሲለው ደግሞ ለመክፈት መታገል ነው ወደ ውስጥ ይሁን ወደ ውጪ ወደየትኛው እንደሚሳብ ያደናግራል፡፡
አሜሪካ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በማስታወሻ ተመዝግቦ ሊያዝና ሊጠና የሚችል መረጃ ጥቅም ላይ የሚውልበት አገር መሆኑን እየዋልኩ እያደርኩ መገንዘብ ችያለሁ፤ ስመጣማ ወንድሞቼ ከአኔ ባይርቁም ቅሉ ብቻዬን ሳስበው ለእኛ መረጃ የሚሰጥና የአገር ልጅ የሚያለማምድ፣ ሆድ ሲብሰን፣ በቡና የሚያብሰን ተቋም እንኳን በቅጡ አለመኖሩ ገርሞኛል፡፡
አይ እግሊዘኛ! እንግሊዝኛማ ተጉመጥምጣ ተፋችኝ አለቅልቃ ደፋችን ማለቱ ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ አይ እግሊዝኛ አለ አንዱ ዘፋኝ ሽፍታ ሲያዘፍነው፡፡
ቸር ያቆየንና፤ አደባባይ አዲስ ቤት ነውና ኤፍሬም ከፈቀደ አንድ ሁለት ዙር ካቆምኩበት ቀጥዬ የታዘብኩትን ጨምሬ እነሆ እላለሁ፡፡
ምስጋና ይሁን ለአዶናይ አምላክ
ተስፋዬ

Anonymous said...

ሃይ! ተስፋዬ ጥሩ ዘግበሃል:: ቀሪዉን ደግሞ ባስቸኳይ ጻፍልን::

John Architect said...

እግዜር ይስጥልን፡፡ እፎይ!!! ለ አሥራ ምናምንኛ ጊዜ ዲቪ ከመሙላት አዳንከን፡፡ መጥኔ ለናንተ! እኛማ የልቅሶአችንንም ሆነ የሳቃችንን ዜማ ከሚለይልን (የምንወደው እና የሚወደን) ህዝባችን መሃል ነን! ብንፈልግ የሽልንግ ቆሎ አልያም አሹቅ ከእማማ ተዋቡ ገዝተን ለሦሰት (ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል) ተካፍለን ከከካን በኋላ ከጎረቤታችን ወይራ ታጠነ ማሰሮ የቀዳነውን ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰን ስንፈልግ እጅ ለእጅ ሲየሻን አንገት ላንገት ተቃቅፈን ወጋችንን እየጠረቅን አንነጉዳለን! መንገዱንም እድሜውንም፡፡ እዚህ ፖሊስ ዘንድ የምንደውልበት ስልክም ልማድም የለንም፡፡ የተቀያየመ ቢኖር መሪጌታ ደምሰውን የመሰለ ሽማግሌ ማን ነው እምቢኝ ብሎ ሸንጎ የሚውል! ብቻ መጥኔ ለናንተው!
ኑሮን እኖር ብዬ
ለመኖር መኖሬ
ነገን አገኝ ብዬ
ዛሬዬን መቅበሬ
መች ያልቃል ብሶቴ
መች ያልቃል ጉጉቴ
ዘንድሮዬን ሰዋሁት
ለከርሞ ምኞቴ

tewodros said...

TESFISH TIRU AYTEHAL AKELIBET..

Anonymous said...

Hey too late for hundreds.......

Anonymous said...

I like this Diakon Ephrem Egziabher agelgilotihin yibark. let's share on various issues... I think there will be many of them.
Sharing is not only happiness but also God's word.

Anonymous said...

I realy appreciate the article, please we expect more... I have a lot to say too...

Anonymous said...

It is a good start, there are plenty things that the Ethiopian people should be aware of them.

Anonymous said...

አነበብኩ፡፡ ግርምም አለኝ፡፡ ወጣን፡፡ ወረድን፡፡ ሄድን ፡፡ተሰደድን፡፡ የአንድ ነገርን ጭራ ለመያዝ፡፡ የደስታን፡፡ ደስታን የምናባርርበት ምጽአት ናፈቀኝ፡፡ እርግጥ ደስታ ከደጅ ነበረች፡፡ ግን አናስተውላትም፡፡ በረከትም በር ላይ ነበረች፡፡ ማንም ከቁብ አልቆጠራት፡፡ ፍቅርም ከኛ ዘንድ ነበረች፡፡ ቸል አልናት፡፡ ወገኖቼ አብዝተን ባከንን፡፡ ግና ምንም አላተረፍንም- ልክ እንደ ባለዲናሩ ሰውዬ፡፡ ምናልባት ለባእዳን ያፈሰስነውን ጉልበታችንን እዚህ በቅድስቲቱ አገር ብናፈሰው የት በደረስን ነበር፡፡ እንጃ፡፡ ብቻ ፈጣሪ ያስበን! በቃ ይበለን!

Anonymous said...

waw... Tesfaye ,,, you're nice guy and genuine . and have a skill of writing. keep it up.!!!!!!

Blog Archive