Friday, February 11, 2011

አዬ አሜሪካ!

(ተስፋዬ)
በቅርቡ ነው የመጣሁት፡፡ እንደ መታደል ሆኖ አበባ ይዞ የሚቀበል ቤተሰብ ስለተቀበለኝ ዱላስ አውሮፕላን ማረፊያ ኧረ ውሃ በላኝ ብዬ አልጮሁኩም፡፡ ተመስገን ልበላ፤ ለካ ይህም አለ፡፡ እርግጥ በአሜሪካ ፍቅር ጥንብዝ ብዬ የሠከርኩ አልነበርኩም፡፡ ሰው ሆኖ ሆድ የማይብሰው የለምና አንዳንድ ቀን ሆድ ሲብሰኝ የነበርኩበትን ከተማ ብቻ ሳይሆን የምር የማልጨክንባትን እንደ ስዕለት ልጅ የምሳሳላትን ኢትዮጵያን ሳይቀር ጥዬ መውጣት እመኛለሁ፡፡

የምለምነው ነገር ደረሰ፡፡ ባሥራ አንደኛው ሰዓት የሞላሁት ዲቪ መጣ፡፡ ሲያመጣው አንዳንድ ጊዜ … እንዳለው መሆኑ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ቪዛ ለማግኘት መረጃ ማዘጋጀት የጀመርኩት ቀጠሮው ሊያበቃ 10 ቀን ብቻ ሲቀረው ነበር፤ ግን ተሳካ፤ ቪዛው ለ6 ወር እንደሚያገለግል ተነገረኝና ረዥም ጊዜ ተሰጠኝ፤ ደስ አለኝ አገሬ ለመቆየት፡፡ የጊዜ ባቡር አይቆምምና ቪዛው ሊቃጠል 17 ቀን ሲቀረው በስንት ውትወታ በዕለተ ቅዳሜ አገሬን ለቅቄ ዋሽንግተን ዱላስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን አረፍኩ፡፡
እንደ እድል ሆኖ ኢትዮጵያ እያለሁ፤ ከረዥም ልፋትና ጥረት በኋላ ከጓደኞቼ ጋር የጀመርናት አነስተኛ የአገልግሎት ሰጪ ንግድ ቡቃያ ላይ ደርሳ ለፍሬ በቃሁ እያለች ነበርና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የድርሻችሁን ማለቷ የሚቀር አልነበረም፡፡
እንደ እድል ሆኖ አሜሪካ የገባሁት ደግሞ የኢኮኖሚው ቅራሪ ላይ መሆኑ ነው የሚገርመኝ፡፡ ይቺ የዓለም ቁጥር አንድ ሃብታም አሜሪካ በበጀት ጉድለት ተዘፍቃ፣ በሥራ አጥ ቁጥር ተጥለቅልቃ፣ ዲሞክራቶቹ የሚሉት እውነት እየሆነ ከመጣ ደግሞ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው የሚባለው የመካከለኛ ገቢ ክፍል (middleclass) እየጫጨ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ እዚያ ሆነን እገሌ ዶላር ላከ፣ ከአሜሪካ መጣ፣ የአቶ/ወ.ሮ እገሌ ልጅ ለቤተክርስቲያን ማሠሪያ በዶላር ይህን ያህል ላካች ተብሎ ለዶላሩ ይሁን ለስዕለቱ ግልጽ ባልሆነ መልኩ ዶላር በእልልታ ስም ስንቱን ኢትዮጵያዊ ልቡን አሸፍቶታል መሰላችሁ፡፡ ዛሬ ግን ዶላር በዓለም አቀፍ ግብይት ከዩሮ እና ፓውንድ ለጥቆ በ3ኛ ደረጃ ተሰልፎ ይገኛል፡፡


በእርግጥ አሜሪካ ጥሩ አገር አይደለችም ማለት አይቻልም፡፡ ቢቻልም የሚያምን ሰው የለም፤ የሚያሳምን ማስረጃም ማቅረብ ያስቸግራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ቀን መጻፍ ይቻል ይሆናል ምክንያቱም አሜሪካንን ስላየናት፣ ስለኖርንባት ብቻ እናውቃታለን ማለት አይሆንምና፡፡


በዚሀ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያውን ዲቪ አመልካቾች ቁጥራቸው ከ500ሺህ በላይ ሆኖ የአሜሪካንን መንግሥት በማስገረሙ ይመስላል የወርኃ ኅዳር የአፍ ማሟሻ ዜና እርሱው ነበር፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቅ ግን መልሱ ሁለት ይመስለኛል፤ 


በእኔ አመለካከት፤
1. የውጪው ዓለም አኗኗር የአእምሮ ሰለባ መሆናቸን ነው፡፡ ፊልሙ፣መኪናው፣አለባበሱ፣ ሙዚቃው፣ ስታዲየሙ፣ ማስታወቂያው፣በፊልም ውስጥ የሚታዩት የረቀቁ የመሠረተ ልማት ጥልፍልፎች፣ ኮምፒውተርና የሞባይል ቴክኖሎጂ፣ ወደ አገር ቤት ብቅ የሚለው ጅንኑ ኢትዮጵያዊ ተደማምረው ገነትማ ያለችው አሜሪካ ነው ብለን እንድንደመድም አድርጎናል፡፡


2. ኢትዮጵያ አምራች ለሆኑት ዜጎቿ በሚያመረቃ ደረጃ የሥራ መስክ መክፈት ያለመቻሏ ናቸው፡፡


ቶሎ አልሞቅም፤ እንኳን በማይክሮ ዌቭ፣ በጋዝም ያው ነኝ፡፡ አዲስ አካባቢን፣ አዲስ ሰውን ለመለማመድ ጊዜ የሚያስፈልገኝ ነኝና ቨርጂኒያ፣ዲሲ፣ ሃገረ ማርያም ግጥግጥ ያሉትን ከተሞች እንዲህ በቀላሉ የሚሞከር አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ለእንግሊዝኛ ሩቅ አይደለሁም ያልኩት ሰው የአነጋገሩ ዘይቤ ተለወጠና የወፍ ቋንቋ ሆነብኝ አንድ ደንበኛ ሃንድከርቺቨ (handkerchief) ስትለኝ አቤት ያልኩት እስኪበቃኝ በሳቅ አንፈቅፍቆኛል፡፡ በራስ መተማመን የሚባለው ነገር በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ጭራስ አብሮኝ የተፈጠረ አልመስልህ እስኪለኝ ሸሸኝ፡፡ አሁን አሁን በጥቂቱ ልቅረብህ እያለኝ መሆኑ ደግሞ መልካም ዜና ነው፡፡ ለእኔ ሁሉም ነገር አዲስ ነው፡፡ ባንክ ቤቱ ኤሌክትሮኒክስ ነው፤ አውቶቡሱ ኤሌክትሮኒክስ ነው፣ ሰው ራሱ ኤሌክትሮኒክስ ነው (ሞባይል፣ ኮምፖውተር፣ ሪደር ላይ ቸክሎ) እንኳን እኔን እጥፍቶ ጠፊውንም ከቁብ አይቆጥርም፡፡ በዚያ ላይ የፖሊስና የሜትሮ አክሰስ የሚባሉት፣ የእሳት አደጋ መኪኖች ጩኸት ልቤን ያርዱታል፤ አደጋ ሳይሆን የጥፋት ቀን ያስመስሉታል፡፡ በሩ ደስ ሲለው ተሽቀንጥሮ ይከፈታል፣ ሲለው ደግሞ ለመክፈት መታገል ነው ወደ ውስጥ ይሁን ወደ ውጪ ወደየትኛው እንደሚሳብ ያደናግራል፡፡
አሜሪካ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በማስታወሻ ተመዝግቦ ሊያዝና ሊጠና የሚችል መረጃ ጥቅም ላይ የሚውልበት አገር መሆኑን እየዋልኩ እያደርኩ መገንዘብ ችያለሁ፤ ስመጣማ ወንድሞቼ ከአኔ ባይርቁም ቅሉ ብቻዬን ሳስበው ለእኛ መረጃ የሚሰጥና የአገር ልጅ የሚያለማምድ፣ ሆድ ሲብሰን፣ በቡና የሚያብሰን ተቋም እንኳን በቅጡ አለመኖሩ ገርሞኛል፡፡


አይ እግሊዘኛ! እንግሊዝኛማ ተጉመጥምጣ ተፋችኝ አለቅልቃ ደፋችን ማለቱ ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ አይ እግሊዝኛ አለ አንዱ ዘፋኝ ሽፍታ ሲያዘፍነው፡፡
ቸር ያቆየንና፤ አደባባይ አዲስ ቤት ነውና ኤፍሬም ከፈቀደ አንድ ሁለት ዙር ካቆምኩበት ቀጥዬ የታዘብኩትን ጨምሬ እነሆ እላለሁ፡፡
ምስጋና ይሁን ለአዶናይ አምላክ
ተስፋዬ

9 comments:

Yonas said...

Thank you

Anonymous said...

በጣም ነው የሚመች ፤ በደንብ ጨማምርበት። ዲ. ኤፍሬምም በጅ የሚል ይመስለኛል።
እግዚአብሔር ይስጥልን ወንድም ተስፋዬ።

Anonymous said...

You remind me my first year experience. Thanks

Anonymous said...

Loved it Tesfish.

ZERAYAKOB YIHUN said...

It is a good perspective about country of OBAMA tesfaye please continue for a good explanation I thanks again & again ok.
D/Ephrame I read your messages from "ADEBABAY" "ROSE" it is untouchable area to write because some case AMERICA is always GOOOOOOOOOOOOOOOOOOOOOD for all ETHIOPIAN.
There is miss understand beyond the FILMS,TV programs and Magazines all are show the beauty of USA.
The back of America is more & more complex please write detail. Like tesfaye and oters contribute for ADEBABAY.
THANKS FOR ALL THING.

John Architect said...

እግዜር ይስጥልን፡፡ እፎይ!!! ለ አሥራ ምናምንኛ ጊዜ ዲቪ ከመሙላት አዳንከን፡፡ መጥኔ ለናንተ! እኛማ የልቅሶአችንንም ሆነ የሳቃችንን ዜማ ከሚለይልን (የምንወደው እና የሚወደን) ህዝባችን መሃል ነን! ብንፈልግ የሽልንግ ቆሎ አልያም አሹቅ ከእማማ ተዋቡ ገዝተን ለሦሰት (ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል) ተካፍለን ከከካን በኋላ ከጎረቤታችን ወይራ ታጠነ ማሰሮ የቀዳነውን ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰን ስንፈልግ እጅ ለእጅ ሲየሻን አንገት ላንገት ተቃቅፈን ወጋችንን እየጠረቅን አንነጉዳለን! መንገዱንም እድሜውንም፡፡

እዚህ ፖሊስ ዘንድ የምንደውልበት ስልክም ልማድም የለንም፡፡ የተቀያየመ ቢኖር መሪጌታ ደምሰውን የመሰለ ሽማግሌ ማን ነው እምቢኝ ብሎ ሸንጎ የሚውል! ብቻ መጥኔ ለናንተው!

mela said...

ወይ ተስፋዬ ምንድነው የጻፍከው አሜሪካ በመኖርክ እግዚአብሔር አመስግን ፡፡

ኢትዮጵያን ውስጥ መኖር ማለት ምን ማለትእንደሆነ ታውቃለህ የሰቀቀን ኖሩ የምንኖርበት አገር ናት እኔ ያለሁበት መስራቤት ከአሁን አሁን ከስራ ተባረርን እያልን እንሰጋለን ኖሮ በቀን በቀን እየጨመረ ነው የልጅ ትምህርት ቤት አለ እረ ምኑ ቅጡ ደግሞ ኢትዮጵያ ይሻላል ከተሻለ ለምን አትመጣም ለምን እውነት አንነጋገርም እኔ አሜሪካ ሙሉ ለሙሉ ምንም ችግር አይኖርም አልልም ግን ከኢትዮጵያ ይሻላል ኢትዮጵያ አገር ውስጥ እንኳን ጥሩ መስራቤት የሚባል ሥራ የሚያገኝ እንኳን እንዴት ያስቀናል፡፡ እዴ የእግዚአብሔር ውሃን ለማግኝት እንኳን የምንቸገርበት አገር አገር ይባልልናል አቶ ተስፋዬ አሜሪካ መነኩሴ ሁሉ የሚሰደድባት አገር የተባረከች አገር ናት፡፡ ምክንያቱም መጸሐፍ ቅድስ ላይ ጻድቅ ሲራብ ዘሩም ሲለም አላየሁም ይላል ስለዚህ እኛ አገር ችግር አለ እውነትን አትሸፋፍኑ ችግር አለ፡፡

Anonymous said...

Endiiiiiiii lemin yiwashal??????????? Ethiopia wust chigr silale newu eyetesededachihu yalachihut. so lemin yiwashal??????? abo arfachihu nuru

Anonymous said...

Ayeeeeeee Lemin Tadiya Lemehed Enji Lememeles eko kelal new..Bakih Begna malagetun Tewewna Eski lib kaleh temeles? Keza wuch gin Bado were anfeligm wendim

Blog Archive