Monday, November 24, 2014

“የምክር ቃል”፦ የውጪ አገር ነገር

This article was first posted in 2011. Reposted today. Enjoy.
ባለፈው “በኢትዮጵያ አእምሮ” ያለውን “የአሜሪካ ኑሮበተመለከተ አንዳንድ ሐሳቦች ለማካፈል ከሞከርኩ በኋላ ብዙ አበረታች ሐሳቦች እና መልእክቶች ደርሰውኛል። የበለጠ እንድንወያይበት የሚያደርጉ መነሻዎችም አግኝቻለኹ። በተለይም የኒውዮርኩ ወዳጄ ዶ/ር ታዬ ሁሴን ያደረሰኝ “የምክር ቃል” የምትል የቆየች “ምጥን መጽሐፍ” (ትንሽ መጽሐፍ) ርዕሰ ጉዳዩን እንድመለስበት አድርጋኛለች። ይህ መጣጥፍ በዚህቹ መቶ ዓመት ሊሞላት 14 ዓመት በሞላት መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱትን ነጥቦች ለማስታወስ ይሞክራል።አንድ ቀን ከአንድ ወዳጄ ጋር ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት ሥፍራ እየተጓዝን ነበር። አዲስ መጤው ወዳጄ ከብርዱ ጋር አልተግባባም ኖሮ አፍንጫውን የሰረሰረው ቅዛቃዜ በጣም ሲያስነጥሰው እጁን በአፉ በአፍንጫው ላይ ለማስቀመጥ እንኳን ጊዜ ባለማግኘቱ (እንደ አገር ቤቱ) ድምፁን አሰምቶ ቢያስነጥስ አጠገባችን የነበሩ ነጫጭ የአገሬው ሰዎች ብትን አሉ። አፋቸውን አውጥተው አይናገሩ እንጂ በዓይናቸው አፈር ድሜ አስጋጡን። “እነዚህ ያልሰለጠኑ አፍሪካውያን” ያሉን ይመስለኛል። ወዳጄ ነገሩን ቶሎ አላስተዋለውም። ያ ምክንያት ሆኖን ከተጨዋወትንበት በኋላ ነበር የሰዎቹ መበርገግ በቅጡ የገባው።

ከባህል ባህል፣ ከአገር አገር፣ ከሕዝብ ሕዝብ የሰዎች ጠባይና አመለካከት ይለያያል። በዘመናዊነቱ ገፍቷል የሚባለው የምዕራቡ ዓለም የሚመላለስበት የራሱ ዘመናዊ ባህል ፈጥሯል። ከሌሎች አገሮች ወደ እነርሱ አገር የምንሄድ መጤዎች አስተሳሰባቸውን እና አመካከታቸውን ቀድመን የምናውቅበት አጋጣሚ የተወሰነ በመሆኑ በብዙው እንቸገራለን። ይህ የገባቸው የአገራችን ሰዎች ቀደም ብለው፣ ገና አውሮፕላን እንደዛሬው ዋነኛ መጓጓዣ ሳይሆን በመርከብ እና በባቡር ወደ ውጪ አገር ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጁትን መምሪያ (ማኑዋል) ተመልክቼ በእጅጉ ተገርሜያለኹ። ይህንን በ1916 ዓ.ም የተዘጋጀውን መምሪያ ካነበብኩት በኋላ እኔም ለአንባቢዎቼ ባካፍላቸው መልካም መሆኑን አሰብኩ። መምሪያው አንድ ወደ ውጪ አገር የሚሄድ ኢትዮጵያዊ ከጉዞው ብዙ ሳምንታት አስቀድሞ ጀምሮ ሊያከናውናቸው ስለሚገቡት ጉዳዮች በዝርዝር ያቀርባል። ለጉዞው ከሚያስፈልጉት ወረቀታ-ወረቀቶች ጀምሮ በግል ንጽሕና እና ከሰዎች ጋር በሚደረጉት ግንኙነቶች፣ በተለይም ከውጪ ሰዎች ጋር ባሉ የመገናኛ አጋጣሚዎች ተጓዡ ሊያስተውላቸው ስለሚገባቸው ነገሮች በዝርዝር ያቀርባል። 

ስለ አውሮፓ መንገድ የምክር ቃል” በሚል “በልዑል  ኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት ታተመ፣ መጋቢት 20 ቀን 1916 ዓመተ ምሕረት። አዲስ አበባ ኢትዮጵያ" እንደተዘጋጀ የሚገልፀው ይህ “የምክር ቃል” ….. “ስለ ይለፍ ወረቀት ፓስፖርት፣ ስለ መርከብ መገኘት፣ በምድር ባቡር ስለመሣፈር፣ ወደ መርከብ ስለመግባት፣ በመርከብም በባቡርም በሆቴልም በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ለማድረግ የማይገባ” ስለሚላቸው ነገሮች በአጭር በአጭሩ ነገር ግን በተገቢው ሁኔታ ያብራራል።

Ras Tafari (Haile Selassie) The Amharic reads: "May you have a good journey and reach your country safely. Written Tikimt 25th 1906." The seal reads: "Fitewrari Gebrey, Megabit 2, 1893." Fitewari is a title like General, the date being about March 10, 1900. (http://www.doig.net/Raitchevitch.html)

“ስለ ይለፍ ወረቀት” ሲያብራራ “የይለፍ ወረቀቱን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከተቀበለ በኋላ የሚሄድበትን አገር አስታውቆ ወደ ሌጋሲዎን ሔዶ የቆንስሉን ፊርማ  በይለፍ ወረቀቱ ላይ ማስፈረም ነው። በየመንግሥቱም የሚሔድ የሆነ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከሚኖሩት ቆንስሎች ማስፈረም ያስፈልጋል” ሲል ያስረዳል። በየመንግሥቱም የሚሔድ የሆነ እንደሆነ ያለው ብዙ አገር ደርሰው ለሚመጡ ተጓዦች መሆኑ ነው። ይህንን ቅድመ ጉዞ ለማከናወን ጊዜ እንዳያጥር “ለመንገዱ መነሣት 15 ቀን ሲቀር” መፈጸም እንደሚገባ ይመክራል።

ስለ መርከብ መገኘት” በሚለው ክፍሉ ወደተለያዩ የአውሮጳ አገሮች የሚሄዱ መርከቦች ከጂቡቲ መቼ እንደሚነሡ “በጂቡቲ ወዳጅና ዘመድ ያለው ሰው በጽሕፈት ወይም በቴሌግራም መጠየቅ ያስፈልጋል።  በጂቡቲ ወዳጅና ዘመድ የሌለው ግን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ቆንስላ ቤት ለመጠየቅ ይችላል። … መርከቡ ከጂቡቲ ከሚነሣበት ከሁለት ቀን በፊት ጂቡቲ መድረስ ያስፈልጋል” ይላል። ይህንን ከዘመናችን አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ብናስተያየው የምናገኝበት ብዙ ቁምነገር አለ። ማንኛውም አገር ለዜጎቹ ደኅንነት ሲል አስቀድሞ መረጃዎችን ማዘጋጀት እና ግንዛቤ መፍጠር እንዳለበት የሚያሳይ ነው።

የባቡር ጉዞ ብዙም ባልተለመደበት በአገራችን ጠባዩን እና መደረግ የሌለበትን የማወቁን አናሳነት የተገነዘበው መመሪያው ብዙዎቹን ነገሮች በዝርዝር ያቀረበበት መንገድ ፈገግ ከማሰኘት ጋር አቀራረቡ ትምህርት ይሰጣል። “በየጣቢያው ባቡሩ በቆመ ጊዜ በባቡሩ ውስጥ ባለው ሠገራ ቤት ገብቶ ሽንት መሽናት ሌላም ጉዳይ ማድረግ አይገባም። ይህን የመሰለውን ጉዳይ ሁሉ መፈጸም ባቡሩ በሚሄድበት ጊዜ ነው” ካለ በኋላ “ባቡሩ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ በመስኮት አንገትን ወይም እጅን ብቅ … ያደረገ እንደሆነ … ከባቡሩ ፍጥነት የተነሣ ከእንጨት ጋር ወይም ከገደል ጋር አጣብቆ ይቆርጠዋል” ብሎ ያስጠነቅቃል። 

“ወደ መርከብ ስለመግባት” በሚለው ክፍል ደግሞ “በመርከብ ውስጥ የመኝታ ስፍራ ከመቀበል በኋላ በፍጥነት የሠገራ ቤቱንና የመታጠቢያ ቤቱን፤ ቀጥሎም የምግቡን ቤትና የጽሕፈት ቤቱን፣ የመጻሕፍት ቤቱን ማየትና ማወቅ ያስፈልጋል” ይላል። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ ጽሕፈት ቤት፣ መጻሕፍት ቤት የሚለውን በፍጥነት ማወቁ ለምን እንደሚያስፈልግ አልዘረዘረውም። አስፈላጊነታቸውም ቶሎ ግልጽ አይደለም። መታጠቢያ ቤቱና የመሳሰለው “የተፈጥሮ ግዳጅ” ድንገት ቢከሰት ከችግር ለመዳን የተቀመጠ ማስጠንቀቂያ መሆኑ ነው። ደግሞስ የመርከብ ጉዞ፣ የባሕሩ ሁኔታ፣ መንገደኛነቱ ወይም የምግቡ ሁኔታ የሚፈጥረው አንዳንድ አለመመቸት ቢኖር ራስን ቶሎ ለማስተናገድ እንዲቻል የተሰጠው  ማሳሰቢያ ግሩም ነው።

በመርከብ ውስጥ ባዳራሹ (ሳሎን) ወይም በመናፈሻው ስፍራ፤ በትልልቆች ሰዎችና በወይዛዝር ፊት ነጠላ ጫማ አድርጎና የሌሊት ልብስ ለብሶ መሔድ ትልቅ ነውር ነው” የሚለውና “ወደ ሠገራ ቤት በመግባት ጊዜ መዝጊያውን ከወደ ውስጥ አጠንክሮ መዝጋት ያስፈልጋል። ጉዳዩንም ጉዳዩንም ጨርሶ በመውጣት ጊዜ ባጠገብ በተሰቀለው ውኃ እድፉ እንዲወርድና ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ነው። እድፉን በውኃ ንጹሕ ሳያደርጉ ከሠገራ ቤት መውጣት ትልቅ ነውር ነው” የሚሉት አገላለጾች ፈገግታን ያጭራሉ። 

እድፍ”  እንዲሁም “ጉዳይን መጨረስ” ሲል “ወገብ መፈተሽን” የገለጸበት አማርኛ ከቁጥብነቱና ከጨዋነቱ ጋር ሐሳብን በትክክል መግለፁን ያስተውሏል። ይህንን ሐሳብ በአውሮፕላን ለሚበርር መንገደኛ አድርጎም መተርጎም ይቻላል። ወይም በማንኛውም የሕዝብ መገልገያዎች፣ ማለትም በቲያትር ቤቶች፣ በሆቴሎች፣ በትምህርት ቤቶች ወዘተ “ጉዳያቸውን የሚፈጽሙ” ይህንን ቢያውቁት የሥልጡንነት ምልክት ነው። 

በዚህ በውጪው ዓለም ባሉ አውሮፕላኖች ወይም ባቡሮች መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ በትንሹ የሚጻፈው “የተጠቀሙበትን ንጹሕ አድርገው ለሚቀጥለው ሰው ቢያስተላልፉ ይመሰገናሉ” የሚሉ ዓይነት ሐሳቦች ማንበብ የተለመደ ነው። በዚያ ዘመን የነበሩ የአገራችን ሰዎች ይህንን ለራሳቸው ዜጋ ቀድመው በማሳወቅ ከልምድ ማነሥ ሊከሰት የሚችለውን  አሳፋሪ ሁኔታ ያስቀሩለታል። ትልቅ ውለታ ነው። እኛ የዛሬዎቹ ከሰው ተምረንም፣ ራሳችን ተሳስተንም ያወቅነውን መልካም ነገር እንዲህ ከእኛ ቀጥሎ ለሚመጣው ወገናችን የማስተላለፍ ልምዱ ቢኖረን ምንኛ በተመሰገንን።

ወደ ባዕድ አገር የሚሄድ መንገደኛ ሊያውቃቸው የሚገባቸውን ሌሎች ነጥብ የጠቀሰው ይህ የ1916 ዓ.ም መጽሐፍ በዚያ ርቱዕ በሆነ አማርኛው ስለ ግል ንጽሕና ሲያስረዳ “በመርከብ ውስጥ በየለቱ ወይም በሁለት ቀን ሙሉ አካልን መታጠብ ያስፈልጋል። ለዚሁ የሚያስፈልገውን ሳሙና፣ ፎጣ፣ ሰፍነግ መያዝ ነው። ወደመታጠቢያ ቤት በመግባት ጊዜ ከወደ ውስጥ መዝጊያውን አጠንክሮ መዝጋት ነው። ከ 10 ደቂቃ በለጠ በመታጠቢያ ቤት መቆየት አይገባም።” ይላል።

በተጨማሪም “ጧት ጧት ራስን ፊትን ሳይታጠቡ ወደ ውጭ መውጣት አይገባም። ደግሞ በጥርስ ቡርሽና በሳሙና ጥርስን አፍን መታጠብ ነው። ደግሞ በጥፍር ውስጥ እድፍ እንዳይታይ በየጊዜው ማውጣት ያስፈልጋል። በትልልቅ ሰዎች ፊት ይልቁንም በወይዛዝር ፊት ጥርስን መፋቅ፣ ከጥፍር ውስጥ እድፍ ማውጣት አይገባም” ይላል።

ከሰዎች ጋር የመነጋገሩ አጋጣሚ ሲኖር በምን ዓይነት መልክ ማስተናገድ እንደሚገባ ሲያስረዳ ደግሞ “አክብሮ ተቀብሎ በብሩህ ገጽ በደስታ መነጋገር ነው እንጂ ፊትን አጥቁሮ፣ ተከፍቶ ማነጋገር አይገባም” ሲል ፈገግታ አስፈላጊ መሆኑን ካብራራ በኋላ “በመነጋገር ጊዜ ፊት ለፊት ሆኖ ዓይን ላይን እየተያዩ መነጋገር ነው እንጂ ፊትን አዙሮ ወይም በዓይን ሌላ ነገር እያዩ መነጋገር አይገባም” ይላል።

እንደ ባሕልም እንደ ልማድም ሆኖ ብዙዎቻችን የሰው ዓይን እያየን፣ ድምጻችንን በሚሰማ መልኩ ከፍ አድርገን መናገር አልለመድንም። የማውቃቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ሴቶቹ፣ በዚህ በምዕራቡ ዓለም በትምህርትም ሆነ በሥራ ገበታቸው ላይ በትጋት የሚሠሩ ቢሆኑም ሲናገሩ ድምጻቸውን አሰምተው ስለማይናገሩ ወይም ሰውን ትክ ብለው እያዩ መናገርን እንደ “ዓይን አውጣነት” በመቁጠር ወደሌላ አቅጣጫ በመመልከት ወይም አንገታቸውን ሰበር ስለሚያደርጉ በራሳቸው እንደማይተማመኑ ሰዎች የመታየት ችግር ይገጥማቸዋል። ከዚህ አንጻር  ይህ የ1916 ዓ.ም ማስገንዘቢያ ዛሬም ወደ ውጭ አገር ለሚሄዱ ወገኖች  አስፈላጊ ነው ማለት ነው።  

ዛሬም ቢሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ስለሚያጋጥም ነገር ግን “ፀያፍ” ስለሆነ አንዳንድ ጠባይ ደግሞ እንዲህ ይላል። “በሰውም ፊት ቢሆን ለብቻም ቢሆን አክ ብሎ አክታ ወደ ምድር መትፋት አይገባምና በቀስታ አክ ብሎ በመሐርም መቀበል ነው። በመናፈጥም  ጊዜ አፍንጫን በመሐርም አጥብቆ ይዞ በቀስታ መናፈጥ ነው እንጂ ድምጡን አሰምቶ በኃይል መናፈጥና ወደ ምድር መጣል አይገባም።” ይላል።

የውሎውን የአዳሩን እንዲህ ሲያትት ቆይቶ ከምግብ ጋር በተገናኘ ስለ ገበታ ላይ ሥርዓትም “ቡን ወይም ሾርባ በመጠጣት ጊዜ ሙቀቱ ሲበርድ በቀስታ ሳብ አድርጎ መጠጣት ነው እንጂ ትንፋሽን አሰምቶ ፉት ማድረግ አይገባም” እንዲሁም “በምግብ ጊዜ አፍን ገጥሞ በቀስታ ማላመጥ ነው እንጂ አፍን ከፍቶ መመገብና አፍን እያጮኹ ማላመጥ አይገባም” በማለት የገለጻቸው ሐሳቦች ግሩም ምልከታዎች ናቸው። 

ምናልባት ይህ እንደ መነሻ እና እንደ ማሳያ ሆኖ በተለያዩ ዓለማት ለመኖር ለሚሄዱ ያገራችን ሰዎች መርጃ የሚሆኑ መጻሕፍትን ለመጻፍ በቂ ዕውቀት ያላቸው ፀሐፊዎች የራሳቸውን ድርሻ ለማበርከት ቢያስቡበት ጥሩ ነው። አውሮፓ እና አሜሪካ በአብዛኛው የመመሳሰል ጠባይ ስላለው ለእነርሱ የሚሆን አንድ መጽሐፍ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ወደ አረብ አገሮች ለመሔድ ለሚያስቡ ሊሆን የሚችል፣ በዚያ ያለውን መልካም የሥራ አጋጣሚ እንዲሁም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሊገጥም የሚችለውን አደጋ የሚያመለክት አንድ መጽሐፍ፣ በንግዱም በሥራውም ወደ ቻይና እና ሕንድ ሊሄዱ ለሚፈልጉ ሠራተኞች ወይም የንግድ ሰዎች ሊሆን የሚችል ደጋፊ መጽሐፍ እንዲሁ፣ በሩቅ ምስራቅ ከቻይና እና ከሕንድ በተጨማሪ ወደ ኢኮኖሚ ተዓምረኞች ማሌዢያ፣ ታይላንድና ጃፓን ሊሄዱ ለሚችሉ ሰዎችም ሊሆኑ የሚችሉ መጻሕፍት ማዘጋጀት ቢችሉ ደራስያኑ ለልፋታቸው የሚሆን ጥቅም ሳያገኙበት የሚቀሩ አይመስለኝም።   

እስከዚያው ማለትም እንዲህ ዓይነት መርጃ ነገሮች እስክናገኝ ግን ወደየትኛውም የዓለም ክፍል ለመሔድ ከመነሣታችን በፊት ስለምንሔድበት አገር ጠንቅቀን ለማወቅ መሞከር ያስፈልጋል። አለበለዚያ የቤት ሥራችንን ባለመሥራታችን ብቻ ጥቅሙ ሊቀርብን፣ የማያስፈልግ ጉዳትም ሊገጥመን ይችላል። 

ለዚህ ጽሑፍና መወያያ እንዲሆን ያቺን “የምክር ቃል” ያዘጋጁትን አበው በማመስገን ላብቃ። መልካም ጊዜ።
--------------------------------------------------------------------------------
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “ሮዝ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 
(ሮዝ ቅጽ 5 ቁጥር  83፤ የካቲት 2003 ዓ.ም)
6 comments:

Getachew said...

Berata wendimachin des yemil tshub new sefa bla be kis metshaf melk bitizegaj tru neber mechem ke hager mewtatachin alkere.

Anonymous said...

Thanks for the inspiring article. Huwalegnoch binhonim kedami endeneberin yasayal.

Anonymous said...

ጎበዝ ፋራውና አራዳው አልለይ አለእኮ!
በእውነቱ ይህ የጉዞ መመሪያ በጉዞ ወቅት ያለውን ከማስተማሩም በላይ በእያንዳንዳችን ቤትና ግላዊ ልማድ ውስጥ ያለውን አካሄድ ከማኅበረሰብ ፍላጎት ጋር በማጣጣም እንድንፈጽመው በጥሩ መንገድ የሚመክር ነው፡፡ የጉዞ መመሪያው በቤታችን ውስጥ ያለውንም የሚመክር ነው፡፡ የፊት መታጠቢያ፣ የገላ መታጠቢያ፣ የመጸዳጃ ሲንኮችን አጠቃቀምና አያያዝ፤የመኝታ ክፍልን ስንዱነት፣የአመጋገብ ሥርዓትን ስለመግራት የሚያስተምር የጉዞ ብቻ ሳይሆን የማጀት መምሪያም ጭምር ነው፤ ካስተዋልነው፡፡

እኔን የገረመኝ በምግብ ጊዜ የሚሰማው ችክችካ፣ በትኩስ መጠጥ ጊዜ የሚሰማው ፉጨት፣ በአብሮነት ጊዜ በዓይን አፋርነትም ይሁን በመሰላቸት የሚደረገው እይታ መቀየርና ጥፍርን ማሽሞንሞን ዛሬም ሊወገድ ያልቻለ ሥርዓታቸን ነው፡፡ ጉዳዩ ግን ከ90 ዓመት በፊት ጀምሮ የተነሳ ነው፡፡ አይ አራዳ አሉ፤ ለመሆኑ ፋራው ማነው አራዳውስ የትኛው ትውልድ ነው? ዘይገርም ይሏል ይኼ ነው፡፡

gebremariam said...

dn efrem kale hiwot yasemalin berta bizu neger kante entebikalen beteleyim sile dirsanat ena gedlat(hagiography)

God bless u

Anonymous said...

I'm not fun of buying & read those magazines,like Rose but due to my work,I have to visit hair dresser once a week or if i make it @ home once in two weeks. first thing I'm gonna do when arrive at the salon is collecting 3 or 4 latest edition of those magazines & read most of interesting topics ( for me) through out the time I spend there. about health ,social issues,etc mostly I & my husband read Dn. Daniel's articles.this was my first time to read ur"s & I liked it It was interesting & funny. u know wa days after i read ur article i met a guy in DC whom i used to know in ETH long time ago.he bought me a dinner @ one of Abesha's restaurant. when we ate he was making noise, while he chew & talking with his mouth full. OMG i wish i could have a word to write the sound. politely I told him not to do so but He continued to do it. he's not new for foreign life style.may be he didn consider it how atseyafi ( disgusting) it was.
pls keep it up to write on those & other many ideas. might help us (miskin Ethiopian).
by the way I love the details on z old books.
u known wa, betam kemiyanadidugn negeroch andu (in Addis)....dabo lemegzat yeteselefen sew alfew lemegzat yemimokru. people whom don give a dam about the elderly & mother with infant @ bus & taxi station.
hope will write u the short one next time. lol
take care,God bless U!

Anonymous said...

ኤፍሬም ጥሩ ነገር ነው የነገርከን ጥርስን በመፋቅ ላይ ላልከው የሚገርመኝና በመንገድ ላይ ሲፍቅ ሳይ ባለውቀውም አግባብ አይደለብ ወንድሜ ስለው የሰደበኝ ሠው ሁሌም አልረሳውም በተለይ ጠዋት በምትወጣበት ጊዜ የእነጨት መፋቂያ ይዞ የማይታይ ወንድና ሴት የለም እኔ የወንዶቹ ብዙም የይገርመኝም የሴቱ ነው ፣ ሌላው መስተንግዶን በተመለከተ ጐንበስ ቀና ብለህ የምታስተናግደው ሰው ተጠራጥሮ ከማየት ውጪ ብዙም ሲደሰት አታየውም እኔ ሆቴል ውስጥ ስለምሰራ ይመስለኛል አሁን አሁንማ ፈገግ ብለህ ስታየው የሚመስለው የሆነ ነገር ፈልገህ እንጂ እሱ የሚፈልገውን ለማስተናገድና ለመጠየቅ የቆም የማይመስለው ሠው ከትልቅ እስከ ትንሽ ምኑን እነግርሃለሁ አበዛዙ መከባበር የሚባለው ባህሉ ሁሉ የጠፋ እስኪመስለኝ ድረስ ነው የምታዘበው ስልጣኔ ነው እንዳልለው ከምታይበት ነገር ትረዳለህ አላዋቄነው እንዳይባል እራሱን ኮፍሶ ነው የሚያወራህ ስለዚህ ከአሁን በፊት በፃፍከው ነገር ላይ ሳነብና ስረዳ አሁን ይሄንን ሳነብ ለዘመናችን ጥሩ የኔታዎች ያስፈልጉናል ባህሉንም መከባበሩንም ነውሩንም በተለይ የአበላል ስርአት ላይ ያለውን ምን አይነት አሳዳጌ እንዳሳደጋቸው በራሱ ይገርመኛል ይኔን ሳስብ እንዳሁኑ ያለው "ሚኒተሪ" ሳይሆን የድሮዎቹን ከአቆራረስ ጀምሮ እስከ ማላመጥና መዋጥ ድረስ ያለው ሂደት ሳይ ለኒ በደንብ ያስደስተኛል ለዚህ ነው ለዚህ ትውልድ የኒታዎች በደንብ ያስፈልጉታል የምልህ ባህሉን ፣አኗኗሩን ፣አበላሉን ፣አለባበሱን ፣ አሁን ቢከፍቱት ተልባ ብቻ ነው ያለው ኬጂ እና ኘሪኘ ምንም አልጠቀመውም

Blog Archive