Saturday, March 26, 2011

ስለ “ግለሰብ እና ሕዝብ፤ ታሪክ እና ያለፈ ጉዳይ” (ካለፈው የቀጠለ)


ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፖለቲካ ውዝግብ የሚፈጥር ነገር የሚመረጥ አይደለም። በመጪ ጉዳዮች ላይ ብንወዛገብ አንድ ጉዳይ ነው፤ አገራችን እንዴት እናልማ፣ በየት አቅጣጫ እንምራ በሚለው ጉዳይ ላይ ብንከራከር ብንወዛገብ አንድ ጉዳይ ነው። በተወሰነ ደረጃ ገንቢ ገጽታ አለው። ተወያይተን ተመካክረን አንድ የጋራ አቋም ልንይዝ እንችላለን። ባለፈ ጉዳይ ላይ ብንነታረክ ግን ይኼን ያህል ገንቢ ጉዳይ የለውም። ያለፈ ጉዳይ ነው። ሲሉ ያስታወሱኝን አስተሳሰብ ደግሞ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ባልኩት መሠረት እነሆ የጫርኩትን።

አቶ መለስ “ያለፈ ጉዳይ” ያሉት ስለ አጼ ኃ/ሥላሴ ከመንበረ ሥልጣን መውረድ፣ አሟሟት እና አቀባበር እና ተያያዥ ጉዳዮች መሆኑ ነው።
እርሳቸው ለአንድ ታሪካዊ እውነታ እና ታሪካዊ ሰው የጠቀሷት ትንሽ መልስ ብዙ ጓዝ አስታወሰችኝ። አቶ መለስ “ያለፈ ጉዳይ” ያሉት ምንድር ልበለው ብዬ ሳስብ “ታሪክ” ከሚለው ቃል ውጪ ሌላ መልስ ላገኝለት አልቻልኩም። በዚህ ዘመን እና ሁኔታ በተለይም ኢትዮጵያ ልትታረቅበት እና ልታስታርቀው ሚገባት ጉዳይ “መጪው” ብቻ ሳይሆን “ያለፈውም ጉዳይ” ይመስለኛል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከራሳችንም እርስበርሳችንም አላግባባን ያለው የትናንቱ፣ የትናንት በስቲያው ጉዳያችን ነው። በያንዳንዱ የታሪክ አንጓ ላይ የምንሰጠው የታሪክ ትርጉም እና አንድምታ አራምባ እና ቆቦ በመሆኑ ምክንያት እንደ አገር እና ዜጋ፤ እንደ “ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች”፤ እርስበርሳችን ያለን መተማመን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ማንኛውም ጤናማ አገር ጤናማነቱ “ስላለፈው ጉዳይ” ባለው “ጤናማ” ብሔራዊ መግባባት (National Consensus?) ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ጤናማ ብሔራዊ መግባባት ደንቃራ ከገጠመው  ያ አገር ምን ያህል የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረው፣ ምን ያህል የተማረ ዜጋ ቢኖረው፣ ምን ያህል ሰፊ አገር ቢኖረው፣ እንዲሁም ምን ያህል ጠንካራ መንግሥት ቢኖረው ከችግሩ እና ከችጋሩ ይላቀቃል ብዬ አልገምትም። ያም አገር እና የዕድገት አቅጣጫው አደጋ ላይ ይወድቃል ብዬ አስባለኹ።

በተፈጥሮ ሀብቷ እዚህ ግቢ የማትባለው ጃፓን የሥልጣኔ ጫፍ ደርሳ ሁሉ የሞላቸው ኮንጎዎች ለምን የዕለት እንጀራ ናፋቂዎች ሆኑ? የበሬ ግንባር የሚያክሉ የአውሮፓ አገሮች ለሰው ክብር የሚገባውን ኑሮ ሲኖሩ እና ለሰው ልጅ የሚገባውን ኑሮ ሲኖሩ ለምን አረቦቹ ነዳጅ ላይ ተቀምጠው ያክካሉ፣ አፍሪካውያንስ ከአልማዝና ዕንቁ እስከ ተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ይዘው ለምን ለስደት ሲወጡ የባሕር ራት ይሆናሉ?

ኢትዮጵያ እርስ በእርሷ የተለያየችው፣ አንዱን ከአንዱ የሚያናቁረው፣ እርስ በርሳችን የሚያናጨን “ላለፈ ጉዳይ” የምንሰጠው መልስ አይደለምን? ባለፉት 40 ዓመታት የተነሡት አብዮታውያን የኢትዮጵያ ልጆች ሊመልሱት የሞከሩትና አሁንም የሚሞክሩት “ያለፈ ጉዳያችን” አይደለምን? ላለፈው ጉዳያችን የሰጡትና በመስጠት ላይ የሚገኙት መልስ ከብሔር ፖለቲካ እስከ ሊበራሊዝም፣ ከ “ትገንጠል፣ አትገንጠል” እስከ “የራስን ዕድል በራስ እስከመወሰን”፣ የራስን ቋንቋ ከመጠቀም እስከ የላቲን ፊደል መጠቀም ጓዝ ይዞ አልመጣምን?

አቶ መለስ የሚመሩት አብዮት የሚታወቀው “ላለፈ ጉዳያችን” በሚሰጣቸው ደፋር መልሶች ነው። በዚህ በኩል ደግሞ ግንባር ቀደሙ ራሳቸው አቶ መለስ ናቸው። እርሳቸውና የእርሳቸው ትውልድ ለአገርኛው ታሪክ፣ ትምህርት እና ዕውቀት ያለው እና የነበረው ግንዛቤ እና ቅርበት ምን ያህል ጥልቀት እንደነበረው ሁል ጊዜም ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ነበር፣ ነውም። በዚህም ምክንያት “ላለፉ ጉዳዮቻችን” የሰጧቸውና የሚሰጧቸው መልሶች አሁን ላለንበት ጥሩም ሆነ መጥፎ ደረጃ አድርሰውናል። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ገሚሶቻችን ኢትዮጵያውያን “መንግሥተ ሰማይ ነው” ስንለው፣ ሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ደግሞ “ዋነኛው ሲዖል ከዚህ በምን ይበልጣል” ብለን እንከራከራለን።

እነአቶ መለስ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ጉዳይ በራሳቸው ታሪካዊ ትንታኔ ፈቱት እንጂ “ያለፈ ጉዳይ” ብለው አልተዉትም። ግማሹ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊውን ፊደል ሳያውቅ እያደገ ያለውና መሠረቱን ላቲን ባደረገው በአውሮፓዊው ፊደል እየተጠቀመ ያለው ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት ሳይሆን “ኢትዮጵያዊው ፊደል በግድ የተጫነብን ነው” በሚለው “ታሪክን ያጣቀሰ ላለፈ ጉዳይ” በተሰጠ መልስ አይደለምን? ሌላው ቢቀር ከኤርትራ ጋር ጦርነት ገጥመን 70 እና 80 ሺህ ወጣቶቻችንን የገበርነው “ድንበራችን እዚህ ነው፣ እዚያ ነው” እያልን ታሪክ እየጠቀስን አይደለምን?

ላለፉት ከ40 ላላነሡ ዓመታት አብዮተኛ ኢትዮጵያውን ሲያንከባልሉት የነበረው የኢትዮጵያን ታሪክ የመከለስ እና ድጋሚ የመጻፍ ጉዳይ አሁን ወደ ቤተ ሃይማኖቶች እና ወደ ምዕመኖቻቸው በመዝለቁ በዋነኞቹ ቤተ እምነቶች ማለትም በክርስትና እና በእስልምና መካከል ሁነኛ መጓተትን እና መቆራቆስን በመፍጠር እየተገለጠ አይደለምን? ችግሩ ከቤተ-ፖለቲካ እየወጣ ወደ ቤተ-እምነት እየዘለቀ እና መሠረቱን እያጸና ነው ማለትስ አይደለምን?

በአጠቃላይ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ የዘለለ፣ አገራችንን በትክክል የሚገልጽ፣ እኛነታችንን የሚረዳና የሚያስረዳ፣ “ያለፈ ጉዳያችንን” የሚተነትን መግባባት ያስፈልገናል። እንደ አገርም እንደ ሕዝብም ወደፊት መራመድ ያቃተን ያልቋጨነው የኋላ ጉዳይ፣ ያለፈ ጉዳይ ስላለን ነው። ከየት እንደመጣን ሳንግባባ ወደየት እንደምንሄድ በምን እንግባባለን። ኋላችንን አላወቅን፣ ወደፊታችንን በምን እንተልመዋለን? ግማሾቻችን አንድ ሕዝብ እና አንድ አገር ነን እያልን፣ ሌሎቻችን ምንም አንድ የሚያደርገን ነገር የለም እያልን፣ ገሚሶችም አንድ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጠላቶች ነን እያልን እንዴት “ያለፈው ጉዳይ” አያስፈልገንም? በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጉዳያችንን እና ዕዳችንን ማወራረድ፣ ወደፊታችንን መተለም ይኖርብናል። አለበለዚያ “አባቱን አያውቅ፣ልጅ ልጁን ይናፍቅ” ያስብለናል።  

10 comments:

The Architect said...

በእርግጥ ያለፈውን ማንሳት ማንን ይጠቅማል? አሁን የደርግ ባለስልጣናትን 30 ዓመታት ባለፈው የቀይ ሽብር እና የነጭ ሽብረ ጉዳይ አጥፍተዋል አላጠፉም እያለ የሚወቅስ እና የሚከስ የሚያስር እና የሚያንገላታ ሰው አለ?

ኮረኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን 20 ዓመታት በላይ በሆነው ጉዳይ ወንጀለኛ ናቸው ብሎ የሚያስብ አለ?

ከምርጫ 97 ጋርስ በተያያዘ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ስድስት ዓመት ባለፈው ጉዳይ ለፍርድ ለማቅረብ የሚፈልግ አለ?

ባለፈው በሰው አገር እንህ እና እነዲያ ብላችሁ ተናግራችሁ ነበር በሎ ባለፈ ጉዳይ ሰው የሚያስር አለ?

አረ የለም!!! ያለፈ ነገር እኮ ነው !!! ቂቂቂቂቂቂቂ

Anonymous said...

Interesting observation. let me share a marvelous saying for all Ethiopians who are longing for its bright future. I got the excerpt from the debate between the liberals and the conservatives in USA. It reads:

"We are pygmies mounted on the shoulders
of giants, able to see further that our
ancestors only because of their
support, and liable to tumble into the
abyss if, presumptuously, we sneer at
the wisdom of our ancestors."
Russell Kirk

We are now sneering at the wisdom of our ancestors. Officials were/are writing history to serve their own purpose. NOW, Where is the level of development during the axumite period? Where is the advancement of the Lalibela Roch-hewn churches. NOW, Where is the democratic culture of gada system and other cultures? What is the contribution of Gebrehiwt Bayikedagn, Yoftahe Nigussie, Mersie- Hazen, Atse Menilik, Atse Hailesellassie, and Others for the present status of the Nation in the International Arena? At Meles and fellows will not give credit. That is why we lack policies, laws and institutions that reflects our identity. But, history will not. Ato Meles Why do you dare to sneer at Atse Hailesellasie. Do you forget what you said while Gadaffi threatens Addis not to be the seat of AU? You were making use of the past history that you now consider it as if it is irrelevant for country's development. If you didn't understand the value of the past, or at lest consider it
as useless, the party that you are heading will not attempt to rewrite history and taught it to the University Professors at AAU
We are now getting into the abyss because we are sneering at the wisdom of our ancestors. Meles and others may claim that the country is growing recording two digits economic performance. But, most of the community did not witness tangible reform in the way and standard of life.

"WRONG WAY, GO BACK" it is important advice. lets have consensus on the past. lets learn from Japan, India and North Korea. their developmental efforts are accelerated primarily due to the value they attached to their past, their identity and their homeland. Still this is what you will adhere to follow if we give credit for the past.

Habtamu from Addis

Anonymous said...

ዲን ኤፍሬም በጣም አመሰግናለሁ በጠቅላይ ሚስትራችን በተሰጠው ውስጠ ወይራ አረፍተ ነገር ላይ ሰፊ ትንታኔ መስጠትህ። ችግራችን ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ የማየትና በሃሳቡ ዙሪያ በቂ መረጃ ይዞ የሃሳብ ፍጭት ካደረግን በዃላ ቋጭቶ ያለማለፍ ይመስለኛል። አሁን አሁን ማንም እየተነሳ እየጎተተን ነው። በተለይ እኛ ወጣቶቹ በግ ሆነናል። ያለፈ ጉዳይ እኮ ጥሩም መጥፎም ይኖረዋል። ጥሩውን ይዘን መጥፎውን እንዳንደግመው ከውሸት በጸዳ መልኩ ተተንትኖ መቅረብ አለበት። ያለፈ ጉዳይ ብሎ ትንታኔ እንዳይሰጥበትና ማህበረሰባችን እውነቱን እንዳያውቅ ማድረጉ እየጠቀመ ያለ እራሳቸውን ነው። አስፈላጊ ሲሆን አንዷን ጉዳይ መዘው በራሳቸው ማብራሪያ ሰጠው ለለመዷት ፍጆታ ያዉሏታል። ለዚህ ነው በትግራይ፤ባህርዳር፤ናዝሬትና ሌሎች ከተማ የ'ሰማዕታት ሐውልት' ብለው የሚያቆሙልን!!! ለእኔ እጅግ ሁሌም የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው። ያ 'ሰማዕት' ብለው ሐውልት ያቆሙለት እኮ የገደለው የእኔን አጎትና አባት ነው፤የገደለው የኔን ኢትዮጵያዊ ወንድም እኮ ነው። የሐሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል ግን ያ ልዩነት እንደዛ መሆን ነበረበት ወይ? ያለፈ ጉዳይ ነው ብለው ቢተውት ኖሮማ እንዲህ 50 ሚሊዮን ባላይ ብር አውጥተው ሐውልት አይሰሩም ነበር። ለእኔ መርዝ ነው እየተከሉ ያሉት። ይህ መርዝ ለራሳቸውም የሚጎዳ ይመስለኛል።

@The Architect -የምትጽፈውን ብታውቅ ጥሩ ነው። ያለፈ ጉዳይ ማለት አንተ በጠባቧ ጭንቅላትህ ወይም ነገሩን ለማስቀየስ ይረፋል ብለህ በወረወርሃቸው ጥያቄዎች የሚገደብ አይደለም።

አስተውሎ የሚራመድ ሰው ያድርገን!

Anonymous said...

ያለፈው ጉዳይ መተው ካለብንም እሳቸውም መተው የሚገባቸው ይመስለኛል። በተግባር ግን አልተውትም፡ለምሳሌ
1. ብሔር ተብየ ስጠየቅ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ለምን ታዲያ እሱ የነፍጠኞች አስተሳሰብ ነው ይሉኛል?
2. በኢትዮጵያ ስም ስደራጅና ሳደራጅ ለምን ታዲያ ያፄው ስርዓት ናፋቂ ይሉኛል?
ተነጋግረን ና ተግባብተን እልባት ስላልሰጠንባቸው አይደለም? ይሄው የማድበስበስ አባዜው ካለቀቀን ነገ ደግሞ በብሔር ተደራጅተው የሚመጡትን የመለስ ስርዓት ናፋቂ ተብለው ላለመፈረጃቸው ምን ማረጋገጫ ይኖራል? መቼም እሳቸውም ሰው ናቸውና አፈሯን መቅመሳቸው አይቀርም። ስለዚህ ከመቃብር በላይ ተሻጋሪ የሆነ ስራ ቢሰሩ ባያድበሳብሱት ለእሳቸውም ለሃገራችንም መልካም ነው እላለሁ። ጥሩም ሆኑ መጥፎ አገሪቱን እየመሩ ስለሆነ ከታሪክ ተወቃሽነት ቢወጡ ጥሩ ነው። ደግሞስ ኢትዮጵያዊ አይደሉምን? እኛ የምናውቃቸው አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ወደዱም ጠሉም ዘመን ተሻጋሪ ጥሩ ስራ ሰርተው ማለፋቸውን ነው። በዛም ልክ መጥፎ አሻራ ጥለው ያለፉ ጥቂቶችም ነበሩ!! እናም ምርጫቸውን ከወዲሁ ቢያስተካክሉ መልካም ነው። ከጥሩዎቹ ለለመደብ!

Anonymous said...

The archtecht yesetweu hasab eko melkam new. yemiyasedibew almeselgnm....ye silak tiyakewoch endehonu new yegebagn ene.....gobez ere rega bilen yehulunm hasab enastewul...hule yegna bicha lik new yetm aladeresenm....

Anonymous said...

የግለሰቡ እሳቤ ግንባሩን ሳይቀር እየጎዳው ይመስለኛል፡፡ ግለሰቡ በታሪክ ሂደት ውስጥ የመሪነት ሚና እየተጫወቱ ቢሆንም ኳሷ እግራቸው ሥር ስላለች ብቻ ከጨዋታ ሕግ ውጪ እንደፈለጉ የሚለጉ (የሚጠልዙ) ይመስለኛል፡፡

ያለፉትን 20ዓመታት ንግግሮቻቸውን በቅጡ የሚከታተል መቸም ጊዜ ቢሆን በተመሰከረለት አስተምህሮ ላይ ረግጠው ማስረጃ በማቅረብ ሕዝባቸውን ሲያሳምኑ አይታይም፡፡

በብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋም ከንቀት የመነጨ እንጂ እርሳቸው እንደሚሉት እንኳን የመቶ እና የ200 ዓመት ታሪክ እንዲህ ዓይነቱን ያለፈ ጉዳይ አንስቶ በዘመናት ሂደት ውስጥ የቆሰለውን ኢትዮጵያዊነት ለማከም ከበቂ በላይ ነው፡፡

እኒሁ መሪ በሚለኒየሙ ዋዜማ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ከአክሱም ሥልጣኔም በማሻገር ምስል ለመከሰት ሞክረዋል፡፡ መቶን በአስራዎች አባዝተው የኢትዮጵያን ታሪክ ሺህ ውስጥ አስገብተዋል፡፡

ባለፈ ጉዳይ ላይ መግባባት ካልተደረሰ የነገው መሠረት ማን ሊሆን ነው? ነገ በዛሬ መሠረት ላይ መቆሙንስ አጥተውት ነው? ኢሕአዴግ ዛሬ የሆነው በትናንትናው የታጋዮቹ መሠረት ላይ አይደለም ማለት ነው?

ባለፈ ጉዳይ ካሉ፥ የደርግን የግፍ አገዛዝ በይቅርታ አልፈውታል? የደርግ ባለሥልጣናት የፍርድ ጉዳይ ጉንጭ ማልፋት ያህል ነው ማለትዎ ይሆን? የኤርትራ የመገንጠል ተልዕኮ ከኦሮሞ ወይም ከኦጋዴን የነጻነት ጥያቄ ጋር አይናበብም ማለትዎ ይሆን?

Anonymous said...

ዌል እንግዲህ አለ ኃይሌ...... እስቲ.... የቃላት ጨዋታን ትተን.... መሬት የረገጠ ነገር ላይ እንወያይ......

Anonymous said...

"ዌል እንግዲህ አለ ኃይሌ......" funny በጣም የምትመች ቋንቋ ነች፡፡ ከአሁን በሁላ ብጠቀምባት ቃላት ሰረቅሽ እንደማልባል አምናለሁ፡፡ በተጨማሪ እኔም ወንድሜ በተናገረው ላይ ለማከል ያህል ማንም ሰው የተሰማውን አስተያየት የመስጠት መብት እንዳለው አውቀን እኛም አግባብ ባለው ሁኔታ ሃሳባችንን ማቅረቡ የውይይት አድማሳችንን ስለሚያሰፋ በተቻለ አስተያየቶቻችን ስሜታዊ አይሁኑ፡፡ ዲ. ኤፍሬም ምልከታህ ጥሩ ነው በርታ
አዜብ ዘሚኒሶታ

Anonymous said...

ki ki ki ki ki.............

Anonymous said...

Is it only for kikikikiki???!!! So!yor are also same as meles!you don't want to see your past mistakes!have you realy see it? God Knows!