Thursday, April 21, 2011

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል አምስት)

ቢጫ ወባ፣ “ሻምበል ደቤ” እና ዱካክ 
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል አምስተኛ ክፍል ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ከክፍል አንድ እስከ አራት ያሉትን ማንበብ አይርሱ። 
-----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ዘንግቼ አልፌው የነበረ እና አንድ ወንድሜ ያስታወሰኝን የ1983 ዓ.ም የስቅለት በዓል ጉዳይ ላካፍላችሁ።  ልክ እንደ 1984 ዓ.ምሕረቱ የሚያዚያ 16 ዕለተ ኪ/ምህረት ስቅለት፤ እንደ 1997 ዓ.ም ሚያዚያ 21፣ እንደ 1999 ዓ.ም መጋቢት 28 የአማኑኤል ቀን፣ እንዲሁም በጻድቁ አቡነ ተ/ሃይማኖት ቀን እንደዋለው የመጋቢት 24/2002 ዓ.ም ስቅለት የዚያን ዓመት፣ የ1983 ዓ.ምሕረቱ በዓለ ስቅለት ደግሞ የዋለው መጋቢት 27 ቀን የመድኃኔ ዓለም ዕለት ነበር። በሃያ ሰባት እንደመዋሉ አንዳንዱ "እንስገድ" ሲል ሌላው ደግሞ “አይ፣ መሰገድ የለበትም፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይከለክላል” ይላል። አንዳንዱ ደግሞ “ግዴለም ከወገባችን ብቻ ጎንበስ ጎንበስ እያልን እናስበው” ይላል። ክርክሩ ቀጠለ። በቦታው ሊቅ የለም። ሊቃውንትም የሉም። ተማሪው ከተገናኘ ገና ሳምንቱ ነው። እርስበርሱ የሚተዋወቀው ጥቂቱ ነው። እናም ክርክሩ ጊዜ ወሰደ። በመጨረሻ ግን መሰገድ እንዳለበት ያብራሩት ወንድሞች ሐሳብ ተቀባይነት ኖሮት ዕለቱን ስንሰግድ ዋልን። 

Friday, April 15, 2011

ሕማማት እና ትንሣኤ በብላቴ

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል አራት)
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል አራተኛ ክፍል ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ሁለትንና ሦስትን ማንበብ አይርሱ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________
ሥልጠናው ከመጀመሩ አስቀድሞ ለዚያ የሚያስፈልጉ ነገሮች ተሟልተው ተሰጥተውናል። አንድ ጫማ፣ ቱታ፣ ካልሲ፣ ካናቴራ፣ አዣክስ ሳሙና፣ “ብሬዢኒቭ” የሚሉት ቁምጣ። ቁምጣውን በቀድሞ የሶቪየት ሕብረት ፕሬዚደንት ስም ለምን እንደተሰየመ አላውቅም። አለ ነገር ግን እንደዚያ አላሉትም። የኛ ሰው እንዲህ ነገሮችን እያገናኙ ስም የመስጠት ልዩ  ሥጦታ አለው። ይቺ ብሬዢኔቭ ቁምጣ ተማሪው በከፍተኛ “የዲያሪያ” (ሸርተቴ) ወረርሽኝ በተቸገረ ጊዜ ብዙ ውለታ ውላልናለች። በቦታው አነሣዋለኹ።

Saturday, April 9, 2011

ጉዞ ወደ ብላቴ …

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል ሦስት)
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል ሦስተኛ ክፍ ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ሁለትን ማንበብ አይርሱ።
+++
ጉዞ ወደ ብላቴ …
ሽንጣም የክፍለ ሀገር አውቶቡሶች መጥተው ኮሌጁ ግቢ ውስጥ ተገጥግጠዋል። ዕለቱ ሐሙስ ነው። የቀን ቅዱስ። መጋቢት 19/ 1983 ዓ.ም። ቅዱስ ገብርኤል መታሰቢያ። ሻንጣዎቻችንን አሰናድተን በሌሊት ተነሥተናል። የመንቀሳቀሻው ሰዓት ከመድረሱ አስቀድሞ ከተወሰኑ ወንድሞች ጋር ወደ ኮተቤ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሄድን። ጸሎት አድርሰን ከካህናቱ ጋር ተሰነባበትን።

Friday, April 8, 2011

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት

ይህ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል ክፍል ሁለት ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ማንበብ አይርሱ

ነገረ ወታደር በልጅነት አእምሮ

መቼም ወታደር የመሆን ትንሽ የለውም። አንድ ጊዜ ካምፕ ከገቡ እና መሣሪያ ከጨበጡ ያው ወታደር ተኮነ ማለትም አይደል? ድንገት አይበለውና ነገር ተገጣጥሞ ጦርነቱ አውድማ ላይ የምንውልበት ሁኔታ ቢፈጠር “ግዴለም እነርሱ የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው፤ ሳይፈልጉ መጥተው ነው” ወዘተ ወዘተ የሚል አይኖርም። ስለዚህም የጦር እና የጦርነት ወሬው እያየለ ሲመጣ ነገሩ ከባድ መሆኑ አይቀርም።

Thursday, April 7, 2011

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል አንድ)

ይህ መጣጥፍ ከዚህ እትም ጀምሮ ለተወሰኑ ሳምንታት ይቀጥል ዘንድ የተዘጋጀ ነው። በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል። በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ። 
(ክፍል አንድ)
ብላቴ በቀድሞው የሲዳሞ ክፍለ ሀገር፣ ከሐዋሳ ከተማ ወደ 90 ኪ.ሜትር, ከአዲስ አበባ ደግሞ 395 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ነው። ከባሕር ጠለል በላይ 1000- 1400 ሜትር በበረሃማው የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ሞቃት ቦታ። በበጋ ወቅት እጅግ በጣም ሞቃት እና ደረቅ ሲሆን በክረምት ደግሞ ዝናባማ እና የሚተነፍግ ውሃ አዘል አየር (rainy and humid) ይበዛበታል።