Saturday, April 9, 2011

ጉዞ ወደ ብላቴ …

ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል ሦስት)
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል ሦስተኛ ክፍ ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ክፍል አንድን ሁለትን ማንበብ አይርሱ።
+++
ጉዞ ወደ ብላቴ …
ሽንጣም የክፍለ ሀገር አውቶቡሶች መጥተው ኮሌጁ ግቢ ውስጥ ተገጥግጠዋል። ዕለቱ ሐሙስ ነው። የቀን ቅዱስ። መጋቢት 19/ 1983 ዓ.ም። ቅዱስ ገብርኤል መታሰቢያ። ሻንጣዎቻችንን አሰናድተን በሌሊት ተነሥተናል። የመንቀሳቀሻው ሰዓት ከመድረሱ አስቀድሞ ከተወሰኑ ወንድሞች ጋር ወደ ኮተቤ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሄድን። ጸሎት አድርሰን ከካህናቱ ጋር ተሰነባበትን።

ኮተቤ ቅ/ገብርኤል በየሳምንቱ ቃለ እግዚአብሔር የምንማርበት የኮሌጃችን አጥቢያ ስለሆነ ከአካባቢው ሰውም ከካህናት አገልጋዮችም ጋር ጥሩ ግብብነት አለን። ስለዚህ ከቤት ከቤተሰቡ ለተለየው ሁሉ ሌላ ቤተሰብ ሆነውናል። ዓመታዊ ክብረ በዓላት ሲኖሩ አካባቢውን ከሚያጥለቀልቁት ጅቦች ጋር እየተጋፋን የምናከብረው እዚያ ነው። አቤት የኮተቤ ጅብ ብዛቱ …… አይጣል ነበር። የጅብ ዘር በዓለም የቀረ አይመስልም። ጅብ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርበት ያየኹት ኮተቤ ነው። ያንን ባትሪ ዓይኑን ብልጭ ሲያደርግ ልብ ያስደነብራል። እናም ይህንን ሁሉ ትዝታ የምንጋራበትን መንገድ አልፈን ቤተ ክርስቲያኑ ደርሰን፣ ጸሎት ተቀብለን፣ የተማሪውን ስመ ክርስትና ሰጥተን ተመለስን። ካህናቱ ስመ ክርስትናዎቻችንን ወስደው በጸሎት ሊያስቡን ቃል ገብተውልናል።  ሁላችንም በሰላም ሄደን በሰላም ስንመለስ በርግጥም ቃላቸውን እንደፈፀሙ አውቀናል። ደግ አባቶች።አውቶቡሶቹ የኮሌጁ ኳስ ሜዳ ላይ ተዘርግፈዋል። ተማሪው ሁሉም ተሰናድቷል። ተሳፈርን። ጉዞው ሲቀጥል አንድ አውቶቡስ ውስጥ ያለነው ተማሪዎች ለበዓለ ንግሥ ወደ አንዱ ገዳም እንደምንሄድ ሁሉ መዝሙራችንን ጀመርን። አውቶቡስ እየሞላን በመዝሙር መሔድ የግቢያችን ልማድ ነበር። መንፈሳዊ ጉባዔያትን ለመካፈል ከኮተቤ ተነሥተን ወደሌላ የአዲስ አበባ ጫፍ ወደ ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በወር አንድ ጊዜ እንጓዝ ነበር። አንዳንዴም ወደ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ወይም ወደ ግቢ ገብርኤል (መንበረ መንግሥት) ስንሄድ የተሳፈርንበትን አውቶቡስ ሞልተን እየዘመርን እንጓዛለን። የብላቴውም ከዚያ አልተለየም።

ሁሉም ወጣት ነው። ብዙዎቻችን ገና 20 ዓመት እንኳን አልሞላንም። እኔ የማውቀው አብዛኛው ተማሪ ከቤተሰቡ የተለየው ኮሌጅ ሲገባ ነው። ለኮሌጁም ቢሆን መንግሥት እንደ ቤተሰብ እንደሚንከባከበው ስለሚታሰብ ወላጅ ልቡ ማረፉ እርግጥ ነው። በወላጆቻችን ዘንድ መንግሥት አባት ነው፤ መንግሥት ወላጅ ነው የሚል ጽኑ አስተሳሰብ አለ። ለእነርሱ (ፈረንጆቹ እንደሚሉት) “we are in good hands”። አዬ ቤተሰቦቻችን አለማወቃቸው፣ አንድ ነገር ትንፍሽ ካልን የመንግሥት ፖሊስ ቆመጥ እንደሚያሯሩጠን። ይህንን ደግሞ በየዓመቱ ቀምሰነዋል።

ይህ ከቤተሰቡ ተለይቶ ለማያውቀው ለብዙው ተማሪ መጽናኛው ስመ እግዚአብሔር መሆኑ እሙን ነው። የጥንካሬው ምንጩም አንዱ ከአንዱ የሚያገኘው ወንድማዊ እና እህታዊ ምክር ነው። በተለይም ከአዲስ አበባ አካባቢ ለመጡ ተማሪዎች ራቅ ወዳለ የኢትዮጵያ ክፍል ሲጓዙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው የሆኑ ብዙ ነበሩ።

አውቶቡሶቹ እስከ ቃሊቲ እስኪደርሱ ድረስ የሰርገኛ ስሜት አልለቀቃቸውም። ቃሊቲ ላይ ስንደርስ ከግቢው ጀምሮ ሊሸኙን በአንድ መኪና አብረውን የመጡት መምህራኖቻችን ተሰናብተውን ተመለሱ። የእኛ የልጆቹ ብቻ ሳይሆን የትልልቆቹም ልብ አብሮን ጉዞ ጀምሮ ነበር። ምናልባት እነርሱ ሊመጣ ያለውን ነገር የበለጠ አመዛዝነውትም ይሆናል። ወይም ወጣቶቹ መምህራኖቻችን አንድም ለዕድገት በኅብረት (አንድ የቤተ ክህነት ሰው ዕብደት በኅብረት ይለዋል)፣ አንድም ለመንደር ምሥረታ “ዘመቻውን” የቀመሱ ሆነው አዝነውልን ይሆናል። ለተማሪያቸው ለማዘን በርግጥ ከዘመቻ ውለው መከራውን ማየት የለባቸውም። የአስተማሪ አንጀታቸው፣ የወንድምነት አንጀታቸው አልችል ብሎም ይሆናል። አንዳንዶቹ መምህራን የታላላቅ ወንድሞቻችን እኩያዎች የሚሆኑ “ለጋ ምሩቃን” ስለነበሩም የተማሪነቱ መንፈስ ገና ተሟጦ አላለቀባቸውም። እኛም አንድ አራት ዓመት ቆይተን ከአስተማሪነት ትውውቅ ወደ ወዳጅነት ትውውቅ ያደረስናቸው አሉን።
Kotebe College, with Abune Selama and Our Lecturers
መምህራኑ ከተመለሱ በኋላ መንገዱ ሰተት አድርጎ ይወስደን ጀመር። እስከ ዝዋይ ያለውን መስመር ከዚያ በፊትም አውቀዋለኹ። ለመጀመሪያ ጊዜ ራቅ ብዬ የሄድኩት ወደ ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ነው። ኮርስ ለመውሰድ በ1982 ዓ.ም እኔን ከመሰሉ 44 ሌሎች የኮሌጅ ተማሪዎች ጋር እዚያ ነበርን። ከታላቁ አባት ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በዓት። እናም አሁን እስከ ዝዋይ ድረስ ምንም የባዕድነት ስሜት አልተሰማኝም። ዝዋይን አልፈን ስንዘልቅ አየሩም፣ ምድሩም አዲስ እየሆነብኝ ሄደ። በዝና የማውቃቸውን ሻሸመኔን እና አዋሳን (አሁን ሐዋሳ ነው የምትባለው) አልፈን ትንሽ እንደተጓዝን ለምሳ እረፍት ሆነ። ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ ይሆናል። በርግጥ የሁዳዴ ሰሞን እንደመሆኑ እስከ ዘጠኝ ሰዓት አጾሙን ማለት ነው ብዬ ልውሰደው?

ነገሩ ምሳ ይሁን እንጂ ምሳ ነው ለማለት ይከብዳል። በቆርቆሮ የታሸገ እንዲሁም ኮቾሮ መሰል ኩኪስ ነገር አደሉን። የጠጣነውን አላስታውሰም። ጠጥተን ይሆን? መቸም ባንጠጣ ውሃ ጥሙ ይገድለን ነበር። ከአዲስ አበባ ስወጣ ሁሌም ጭንቅ የሚለኝ የዝዋይ-ማዶ ውሃ ነው። ውሃው ከጉሮሮዬ አይወርድም። ይቅርታ የዝዋይ ማዶ ሰዎች። ሰው በተለይ የኮተቤ ኮሌጅን (የሆለታን) ውሃ ለምዶ የዝዋይን፣ የሐዋሳን ውሃ ልጠጣህ ሲሉት …። መቸም ሰው እንደ ልማዱ ነው። ሙቀት አገር የመኖር ልማዱ ስለሌለን መሰለኝ። አለበለዚያ ከቅንጦት መቆጠሩ አይቀርም። በተለይ ነገር ተበላሽቶ አገር ከፈረሰ በኋላ ከብላቴ ስንበተን የጠጣነውን ውሃ ሳስታውሰው የዝዋይ ግፍ ነው እላለኹ።

ንግባዕኬ …. ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ። ምሳችንን በልተን መጠነኛ ዕረፍት ከተደረገ ዘንዳ ጉዞ ተጀመረ። ከሐዋሳም ከወጣን በኋላ ዋናውን መንገድ ይዘን ጥቂት እንደተጓዝን ትንሿን የሞሪቾን ሰፈር እናገኛለን። እዚያ ላይ ወደ ቀኝ ታጥፈን አቧራማውን የብላቴን መንገድ ተያያዝነው። ከዚያ ጀምሮ ቢያንስ 60 ኪሎ ሜትር የተጓዝን ይመስለኛል። ለእኔ ፍፁም አዲስ አገር ነው። የጎጆዎቹ አሠራር፣ የግቢዎቹ ሁኔታ ወዘተ ወዘተ እኔ ከማውቀው ገጠራማ አካባቢ የተለየ ነው። ለገጠሩ ለገጠሩ ሴት አያቴን እና ሌሎች ዘመዶቼን ለማየት ከሆለታ ወደ ዱፋ (ወደ ሜታ ሮቢ፣ ሙገር መስመር) የሦስት እና የአራት ሰዓት የእግር መንገድ ስንጓዝ አውቀዋለኹ። ጎጆ ቤቶቹ፣ ማሳዎቹ፣ በመንገድ ላይ ለማረፍም፣ ውሃ ለመጠጣትም የምንጠጋባቸው “ምንጭ” ያላቸው ተረተሮቹ በሙሉ ትዝ ይሉኛል። ብላቴ መስመር ላይ ያሉት የተለዩ ሆነውብኛል። አውቶቡሶቹ ያንን ሞቃታማ አየር እየሰነጠቁ፣ የትንባሆውን ተክል አልፈው፣ ተአምረኛውን የጨሪቾ ሚካኤልን አልፈው ከብላቴ ግቢ ደረሱ። ተአምረኛ ያልኩበትን ምክንያት በሌላ ጊዜ እመለስበታለኹ።

ብላቴ የገባነው ከመሸ ነው። እንደደረስን አንድ አዳራሽ መሰል ግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ባለው የብረት መጋዘን ወይም ኬስፓን ውስጥ ሰልፍ ይዘን ቆምን። ገና ስንመጣ ጀምሮ የሰማነው ነገር ነበር። በተለይም መጽሐፍ ቅዱስ እና የጸሎት መጽሐፍ ፈትሸው ይጥላሉ ስለተባለ ጭንቅ ብሎኛል። እንደወትሮው ቢሆንማ ለወታደራዊ ሥልጠና የሚገባ እጩ ወታደር በሙሉ ምንም ሃይማኖታዊ ምልክት እንዲኖረው አይፈቀድለትም ሲባል ሰምቻለኹ። ማተቡን ክሩን በጥሰው ይጥሉበታል፤ የጸሎት መጽሐፉንም ይወስዱበታል። ይወረውሩበታል ይባላል። እንደዚያ ቢያደርጉብኝ ምን እንደምል ከራሴ ጋር እየተሟገትሁ ተራዬ ደረሰ። የሚመዘግበን ሰው አንዲት ክኒን እና ውሃ ሰጠኝ። የወባ መከላከያ ናት። ዋጥኩ። ዋጥን። መዋጥ ነው። ይህ የጦር ካምፕ ነው እንጂ ከተማ አይደለም። ገዳይ ቢጫ ወባ ያለበት በረሃ እንጂ አዲስ አበባ አይደለም። እኛም ወታደሮች እንጂ “ምሁራን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሊቃውንት” አይደለንም። ከክኒናው ጋር የሚያስፈልገን ነገር ተሰጠን። ሰዓቱ የራት ሰዓት ስለሆነ ወደ “ሜንስ ሜት” (መመገቢያ ቤት) ሄድን።

ሜንሲ ቤት የምን ቋንቋ ነው። በአማርኛችን ውስጥ የተሰባበሩ አረብኛዎች፣ ጣሊያንኛዎች፣ ስፓኒሽኛዎች፣ አራማይኩም፣ ቅብጡም፣ ግሪኩም፣ ሱርስቱም፣ አረብኛውም፣ ስለሞላበት አንዳንዱን ቃል ፍቺ ለማወቅ ወይ ሊቅ መጠየቅ ወይ መዝገበ ቃላት ማማከር ይጠይቃል። ይቺ “ኬስፓን” እና “ሜንሲ ቤት” የምትለው ከየት እንደተገኘች አሁን አላወቅዃትም። ሆለታም ሆኜ ወታደሮቹ ምግብ ቤታቸውን “ሜንስ ቤት” እንደሚሉ አውቃለኹ። ከሌሎቹ ተማሪዎች በዚህ በዚህ “እልቃለኹ” ማለት ነው (ለፈገግታ)።

ወራቱ ወርሃ ጾም ያውም ዐቢይ ጾም በመሆኑ የምግባችን ነገር ጭንቅ ሆነ። ደግሞም ጾሙ ሊፈታ አንድ ሳምንት ነው የቀረው። ዓይጥ ወልዳወልዳ … እንዳይሆን። ያንን ማታ እንጀራ በሻይ እና በውሃ እያማግን በላን። ፍርሃታችን “የምን ጾም ነው? ቀበጦች!! ትበላ እንደሆን ብላ!!!” የሚል ወፍራም የወታደር ድምጽ እና ቁጣ ጠብቀን ነበር። አልመጣም። ስለዚህ እንጀራ በውሃ እያማግን መብላታችንን እንደ ትልቅ ሥጦታ ቆጠርነው። ተመስገን። 


ከዚያ ወደየተመደብንበት ማደሪያ ቦታ ተጓዝን። የደረሰኝ አልጋ ከታች ነው። ከላይ አንድ ልጅ ይተኛል። በኬስፓኑ ውስጥ ብዙ ተማሪ ነው ያለው። መኝታ ክፍል ሳይሆን የአልጋ አነጣጠፍ ማስተማሪያ ወርክ ሾፕ ይመስላል። ኮተቤ እንደገባኹ ከመኝታ እጥረት የተነሣ ብዙ ተማሪ ካለበት ሰፊ ክፍል ውስጥ ማደር ስለለመድኹ አሁን አዲስ አልሆነብኝም። እናም ጥቅልል ብዬ ተኛዅ። “እንዴ በር የለውም እንዴ ቤቱ? በዚህ በረሃ?” ጉድ ፈላ። ደግነቱ ለመመራመር ድካሙ ጊዜ አልሰጠኝም። እንቅልፉ ይዞኝ ጭልጥ አለ። ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የፊሽካ እና እንደ ብራቅ የሚጮኽ ሰው ድምጽ ነው። ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ። ሥልጠው ተጀመረ በቃ?

ወይኔ እንቅልፌ ….

(ይቀጥላል) ...

29 comments:

Anonymous said...

d. ef betam girum new

Anonymous said...

+++
የሞርቾ ሸንኮራ አገዳ እና ሙዝ ባለውለታ ነበር:: የተቀቀለ ዛቡጤ መኮረኒ እና ትንንሽ ፓስታ የተቀላቀለበት ሌሎችም በጅምላ የተሰሩበት ሚኒስትሮን ተብየ ለጾም ተብሎ ለብርጌድ አምስት እተዘጋጀ የዛሬን አያድርገው እና ከትልልቅ ዳቦ እና ከትልቅ ማንኪያ ጋር ይሰጡ ነበር አትረሳህዉም አይደል? ደግሞ ብሉ! ካልበላችሁ ውባ ትታመማላችሁ እስፖርቱን አትችሉትም ይሉን ነበር እኮ:: በል ወንድሜ በርታልኝ እየተከተልኩህ ነው::

ከተጠንቀቅ

Anonymous said...

interesting!

Anonymous said...

berta tenkir we are eager to hear the next history. Bezia zemn sileneberew terikachin yetewesene ginizabe yeminagegnibet melkam agatami new

Emuye said...

Betam yigermal yihen neger lemesmat endet yaguagua? yih bedemsirachin wust yegebawu yamahiberachin tarik silehone meselegn.

Anonymous said...

Abezahew! Why don't you make it a littel longer????????

You reminded me of an old show called "Cosby 49" it's hilarious. Please try to see it and may be you'll find something similar to your experience in Belate. It will make you laugh non stop.

Beterefe, I like your blog ...your sense of humor...so much. Please try to apdate it every ...(as fast as you can)

ድርሻዬ። said...

ኤፍሬም ለምን ኣንድ ግዜ ኣትነግረንም ሆዴን ስለቆረጠኝ ነው። ጥሩ ታሪክ ነው። በል ኣራተኛውን ክፍል ረዘም ኣድርገህ ፃፈው።

Anonymous said...

ተናግረህ ልታናግረን ነው። እስቲ እናዋጣ።ካየነውም ቢሉ ከሰማነው ከኖርነውም(ጦርነታማ ችግር የለብንም ወይ በልጃችን ወይ በራሳችን ወይ በአባታችን በጎረቤት በወንድም ኖረነዋልና)
በቆርቆሮ የታሸገ=ዝግኒ፣እስቃጥላ (ተብሎ ይነበብ)
ኩኪስ=ጋሌጣ
ሰዓቱ=ሰሰዓቱ(ተብሎ ይነበብ)
አንድ ልጅ?አንድ ጓድ በል አልተባልክም።መረሳትማ የለበትም።
ፍሬንድ ጦርሜዳ ላይ ስለበርና መስኮት ይታሰባል እንዴ ስለጣራውም ፈጣሪን አመስግን።ባይሆን በየተራ እየወጣችሁ ዋርድያ ቁሙ።ዛንዜራና ቱታ ተቀበላችሁ ወይስ ገና ነው።
ለማንኛውም ጸጉር ተላጩ ይኼ ብላቴ ነው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ማሰልጠኛ አደልም።ምስጢር ላይ ሲደረስ ለምዕመናን የማይገባ ካለ ይዘለል። ተመችቶኛል።
በነገራችን ላይ ጭርቾ-ጭርሲል አልወድም ነች የሚሉ አሉ።ወደ ግራ ወደ ቀኝ ቢዞሩ ኬስባን ብቻ በሚያዩበት ዓለም አንድ ሰው ራሱን ጠፈር ላይ ያለ ነው እንዴ ያለሁት ብሎ ቢጠራጠር ኩሸት እንጂ ውሸት አይሆንም።
እሺ ቀጥለ ፎሌን ሜዳ ።እንቅልፌ ይላል እንዴ?እንቅልፍ ደህና ሰንብት።ቀጭታ ውሰደና ቀጥልልን።

Adane Fekadu said...

I am reading it as an autobiography. The story is wonderfully constructed and the way it is expressed has a good texture to be read! D/n Ephrem, please keep the good work up. And I am not gonna leave you when you finish this article – because you gave us your word that you will tell us about “ተአምረኛውን የጨሪቾ ሚካኤል” God bless you. (Adane; http://bit.ly/gSgcJj)

Anonymous said...

ስንገባ የተሰጡን ብሬዥኔብ ቁምጣ፤ ከነቴራ፤ ሰማያዊ ቱታ፤ ሸራ ጫማ፤ ኮፊያ፤ የወታደር ብርድልብስ፤ አንሶላ....

Lake sheto said...

ኣራተኛውን ክፍል ረዘም ኣድርገህ ፃፈው።

Anonymous said...

ኤፍሬም ስለ ታሪኩ የሚያውቁት፣ የኖሩበት እንኳን እንዴት እየተንገበገቡ እያነበቡ እንደሆነ እያየሁ ነው፡፡ እኛማ በወሬ የምናውቀው እንዴት እንሁን! አባክህ ፈጠን አድርገው፣ ግን አንድም ሳታስቀር ንገረን ሁሉንም አደራ፡፡
እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን

Anonymous said...

setiyewa tizita be posta yalechiw wedda aydelem

Anonymous said...

አይ ኤፍሬም፥

የወባ ኪኒን ብቻ አይደለም እኮ የተሰጠን፡፡ የወጉን ነገር ነበረ፡፡ የጸረ 6 ይሁን የጸረ "ወንበዴ" እስከ አሁን ሊገለጥልኝ አልቻለም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ሲላላጡ ማጀዘቢያ ማምከኛ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡

ከ20ዓመታት በፊት ምርጥ የነበሩት የጀርመን ስሪቶቹ ዓይናፋር የአንበሳ ሽንጣም አውቶቡሶች እንደወሰዱን አይዘነጋም፤ አይ ምቾች የዛሬው ስካይ ባስ ማለት ነውኮ፡፡

ጋሌጣን አለማወቅህ ገርሞኛል፡፡ ያደጉበትን መርሳት የበሉበትን ወጭት... ሊያስብል ምን ይቀረዋል? ጋሌጣ፣ጋቤጣ፣ኮቾሮ፣ኮዳ፣... የሜንስ ቤት ነገር ግን ለኔም እለተገለጠልኝም፡፡

ሜንስ ቤትን ስትነግረን ሜንስ ቤቱ ላይ ለረዥም ዘመናት ተጽፎ የቆየውን እጅግ አስገራሚ ቃለ ኃይል (መፈክር) አለመጻፍህ ገርሞኛል፤ ከ20 ዓመታት በላይ ዛሬም በኅሊናዬ እያቃጨለ ከመስመር (lane)እንዳልወጣ የሚያግዘኝ ወንጌል ነውና፡፡ እንዲህ ይላል፣

"ማየት ማመን ነው በምሳሌነት መታየትን የመሰለ ዋናና የማስተማር ዘዴ የለም"
ጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም

በእርግጥ ይህን ቃል ከምሥራቅ ጀርመን ጉዞአቸው ቀሽበው እንዳመጡት ይገነራል፤ ሆኖም ማቴ፣ 5፥14-16 ያለውን የሚገልጥ ዛሬ የምናየውን ድብልቅልቅ በትንቢት መልክ የሚናገር ሳይሆን ይቀራል?

ለማንኛው እርፍ ይዞ ወደኋላ አይሉምና እኛ እግር እግር እየተከተለን ቃርሚያ መልቀማችንን አንተውም፡፡ ቀጥጥጥጥጥ...ል

Anonymous said...

"Gash Debe" Endayihonu Fishkawun yenefut.

Anonymous said...

kifil 4 eko zegeye D/N.

Anonymous said...

Please .............. continue to the next part and this time Dn. it should be a little bit longer .....u have to promise that pleaseeeeeeeeeeeee.......

Anonymous said...

ክፍል 4 ናፈቀን እኮ እፍሬም፣

The Architect said...

ጡር አይሆንብህም !!! የወሬ ያለህ ያስብልህ!

KE MIDRE NORWAY said...

Sidst kilowoch 6gna brged.EGNA Komersoch DEGMO 5gna brged nebern. MEMESASEL....SHNED....etc endatresachew.Ephi Blate sleneberku bzu tizita alegn. Ketilibet.

kE MIDRE NORWAY

Anonymous said...

ere ye kifl 4 yaleh deacon

Anonymous said...

እረ አባባዬ እባክህ እየጠበቅን ነው

Hiwot

Anonymous said...

እኔ ሁሉንም ነገር አውቄዋለው!!! ሸውዳችኹ ዘዋይ ገባችኹ አይደል!! ግምቴ ልክ ከሆንኩ•••••
የሚቀጥለውን ጽሑፍ ስትጀምር አዎ ብለህ ጀምር።

MelkameKene said...

As far as I know the word "ሜንሲ ቤት" come from the Italian word of 'Mensa'. Its has two meaning mass eating room or table.

Anonymous said...

sile mahbere kidusan tarik 20 amet tenegeren minwagalew ye kidusan na ye semaetat gedl btnegrun tiru neber ras wedadoch nachihu

asbet dngl said...

የደንግል ልጅ ይባርክህ:: ለአንባቢ ግሩም መንፈስ አዳሽ ታሪክ ነው::

Anonymous said...

Mensa is a German word which offers low-cost meals for students

Jofe Amoraw said...

I'm thinking the "Mens" had its origins from the "mess" (further, Old French and Latin). The phrase "mess hall" (aka Chow hall) is in common usage in western military institutions. መመገብያ አዳራሽ። Officers and enlisted men sometimes don't dine in the same mess halls.

Jofe Amoraw said...

I'm thinking the "Mens" had its origins from the "mess" (further, Old French and Latin). The phrase "mess hall" (aka Chow hall) is in common usage in western military institutions. መመገብያ አዳራሽ። Officers and enlisted men sometimes don't dine in the same mess halls. Very good post. Thank you