Friday, May 13, 2011

ይቅርታ፤ "አለኹ"


ሰላም ጤና ይስጥልኝ። የብላቴን ታሪክ አምስተኛ ፎርማታ ላይ ገትሬው በመጥፋቴ ይቅርታ፤ ለጻፋችሁልኝ ኢ-ሜይል በሙሉ አመሰግናለኹ። ያገሬ ሰው “የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ ነው” እንደሚለው የጊዜ እጥረት እና አለመመቻቸት ይዞኝ ነው። ክፍል ስድስትን እቀጥላለኹ፣ ሳልውል ሳላድር። ለዛሬው ደግሞ ትዝታውን እንዲያካፍለኝ ጠይቄው የነበረው የያኔው የጅማ መምህራን ኮሌጅ ተማሪ፣ የዛሬው ቀሲስ፣ ስንታየሁ አባተ ነው። እነሆ።
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የዛሬ ሃያ ዓመት ወቅቱ ዘመነ ፋሲካ ነበር። የጂማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም አስተዳደር ድንገተኛ ትእዛዝ አስተላለፈ። በአዲስ አበባ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ባደረጉት ዉሳኔ መሠረት ዕጩ መምህራኑ ወደ ብላቴ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ መሄድና መሰልጠን አለባችሁ በማለት ከጭራ የቀጠነ ትእዛዝ አስተላለፈ። ለተማሪው የመወያያ ጊዜና ዕድል እንኳን አልተሰጠም።


በዚህ ዉሳኔ መሠረት ወደ 400 የምንሆን ዕጩ መምህራን ከጂማ ወደ ብላቴ ጉዞ ጀመርን። በወቅቱ ከጂማ እስከ አዲስ አበባ የነበረው አስፋልት መንገድ የተበላሸ በመሆኑ 333 ኪ.ሜ  መንገድ ቀኑን ሙሉ መጓዝ ግድ ነበር። በመሆኑም ከጂማ ጠዋት የተነሣን ታጠቅ የጦር ማሰልጠኛ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ገባን።

የታጠቅን ብርድ ወንድሜ ኤፍሬም ቢናገረው ይሻላል፤ ቢያንስ ጠዋት ከሆለታ ወደ አዲስ አበባ ሲመላለስ ቀምሶታልና። ቀኑን ሙሉ በሙቀት ሲቀቀል የዋለውን ሰውነታችንን እንደ ወባ የሚያንቀጠቅጥ ብርድ ያንዘፈዝፈው ጀመር። ብርዱን ለማስረሳትና የተማሪውን አሳብ ለመስረቅ ታስቦ ነው መሰለኝ ልዩ የሙዚቃና የመብል መጠጥ ድግስ ነበር ታጠቅ ላይ የቆየን። እኛ እንደ ገባን የደብረ ብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተማሪዎች ተቀላቀሉን።

ውይ ልጅነት!!! ወደ ጦር ማሰልጠኛ ተቋም መሄዳችንን ስንኳ በውል የተረዳን አይመስለኝም። በዚያ ላይ ከቤተሰብ ወጥተን ርቀን መኖር የጀመርነው ገና በዚያን ዓመት በመሆኑ ሁሉንም ነገር እንደ ብርቅ ነበር የምናየው። ብቻ ሰዓተ ሌሊቱ እየነጎደ ነው። የደከመውም ተኛ፤ ሌላውም ከቀረበለት አልኮሆል እየተጎነጨ ከዘፈኑም እየሞካከረ ሌሊቱን አዋገደው።

ሰማዩ የአህያ ሆድ ሲጀምር ጉዞ ተጀመረ። በርግጥ በዕድሜ ትንሽ በሰል ያሉ ምናልባት የወታደራዊ ሥልጠናን ፍጻሜ የተረዱ   በዚያች ሌሊት በስውር ወደ አዲስ አበባ  የኮበለሉ ጥቂት ወንድሞቻችን ነበሩ። ጠዋት በማለዳ አዲስ አበባን አቋርጠን ጉዞ ወደ ብላቴ። ለእኔ ከደብረ ዘይት በኋላ ያለው የሀገራችን ክፍል እንግዳዬ ነበር፤ እኔም ለሀገሩ ለምድሩ እንግዳዉ ነበርሁ። ተሜ ትዘፍናለች “ ንዳ በለው….” የያኔው ተወዳጅ መኪና “ዐይናፋር” አውቶቡስ የስምጥ ሸለቆን ሜዳዎች እየተምዘገዘገ ወደ ፊት ይገሰግስ ጀመር። “ዐይናፋር” የዛሬው ዋልያ መሆኑ ነው። በዕድሜ ብዛት ተገቢውን ጥገናም ካለ ማግኘቱ የተነሣ በየቦታው ተበላሽቶ ማደር ስለጀመረ “ዱር ቤቴ” ሲባል ሰምቼ ………..
ምሳ የት እንደ በላን እንዲያውም እንብላ አንብላ አላስታውስም። ብቻ አንድ ነገር ሁሌ ትዝ ይለኛል። አንድ ከአቃቂ የመጣ ልጅ በመካከላችን ነበር። እንዳብዛኛዎቻችን ለእርሱም የምንጓዝበት ሀገር እንግዳ ሆኖበታል። መንገዱ ረዝሞበታል። “ ጎበዝ አሁን የተጓዝንበት ሀገር ሁሉ ኢትዮጵያ ናት ወይስ ሰዎቹ ወደ ሌላ ሀገር እየወሰዱን ነው?” አለ።

የሌሊቱና የማለዳው የታጠቅ ብርድ ወደ ኋላችን ቀርቶ የስምጥ ሸለቆ ሙቀት ተቀብሎናል። ርቆ መሄድ ላልለመድን ወጣቶች በሁለት ቀናት ጉዞ ላይ ሙቀት ሲታከልበት ጉልበት ይከዳል። ሰውነትን መሸከም ራሱ ያስጠላል። ሙቀቱ እየከረረና እያመረረ የሄደ ይመስላል። ውኀ ማግኝት አልተቻለም። ሾፌሩ የተማሪውን የውኀ ጥም ጥያቄ ከቁብ አልቆጠበውም። ብቻ ለመኪና ውድድር የሚያሽከረክር እስኪመስል ድረስ ወደ ፊት……

“አሁን ብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ደርሳችኋል ውረዱ” ተባልን። ሙቀትና ጉዞ እንዲሁም የውኀ ጥም ያዛለውን ሰውነት የመጎተት ያህል ይዘን ከመኪናው ስንወርድ የገና ዳቦ የሚደፋበት ምጣድ ውስጥ የገባሁ ነበር የመሰለኝ፤ ላዩ ታቹ እሳት። ከእኛ ቀድመው የዘመቱ የአዲስ አበባ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከበብ አደረጉን። የሁሉም የጋራ ጥያቄ ከዬትኛው ተቋም እንደ ሄድን ነው? እግዚአብሔር ይስጣቸውና ዕቃችንን ተቀበሉን። ከመድከሜ የተነሣ በወቅቱ ምን ዓይነት ምዝገባ እንደ ተደረገልን አላስታውስም።ምግብ መብላት አለ መብላታችንንም አላስታውስም። ብቻ የሆነ መድኃኒት መዋጤን አስታውሳለሁ።

ብቻ አንድ የማልረሳት ነገር ትዝ ትለኛለች። የውኀ ነገር። ከውኀ ጥሙ የተነሣ ምላሳችን ደርቋል። አፋችን ዱቄት የቃመ ሰው መስሏል። “ውኀ ውኀ” ማለት ጀመርን። አንድ በውል የማላስታውሰው ሰው ከኬስፓኑ በስተ ቀኝ ወዳለው የውኀ ቧንባ አመለከተን። ያቺ ቧንቧ ጌዴዎን ሠራዊቱን በውኀ አጠጣጥ እንደ ፈተነ የተፈተንባት ትመስለኛለች።በአቧራ የተከደነ ፊታችንን ስንኳ እንታጠብ አላልንም።አፋችንን ቧንቧው  ላይ ገጥመን ከፈትነው። ወደ ጉሮሯችን የወረደው ውኀ ግን ጥም የሚቆርጥ ሳይሆን አንጀት የሚመልጥ ፍል ውኀ ነበር። ጠላታችሁ ይሳቀቅና በጣም ተሳቀቅን። የውኀ ጥሙም ጠፋ። ሰማያዊ ቱታ፣ሸራ፣ ለሙቀት የሚሆኑ የውስጥ ሱሪዎች ተሰጡን። ብርጌድ አንድ የሚል መጠርያችን እንደ ሆነም ተነገረን።

አንደኛ ብርጌድ ልዩ መገለጫዎች ነበሩት። የብርጌዱ አባላት እስትጕቡእ ነን። የምንበዛው የተለያዩ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ብንሆንም በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ይማሩ የነበሩ ነገር ግን ዘመቱ ሲባል በቤተ ሰብ ተፅዕኖ፣ በፍርሃት፣ በፖለቲካ አቋም ልዩነት….አንዘምትም ብለው ቀርተው የነበሩና በኋላ ደግሞ መንግሥት ርምጃ ሊወስድባችሁ ይችላል ሲባሉ ዘግይተው የመጡ ዘማቾች ግራ የተጋቡ ግራ የሚያጋቡ መሃል ሠፋሪዎች……የነበሩበት ብርጌድ ነበር። ይህ ብርጌድ “ ሽነድ” የሚል ምሕፃረ ቃላዊ ስያሜ ተሰጥቶትም ነበር።

“ሽነድ” ሽብር ነዢ ድርጅት ማለት ነው። በዘማች ተማሪዎች አካባቢ የሚነገሩ መረጃዎች እውነትም ይሁኑ የተፈበረኩ መነሻቸው ሽነድ ነበር። አንዱ የነሣና ዛሬ ወደ ጦር ግንበር ሊያዘምቱን ነው ይላል፤ ሌላኛው ደግሞ ትናንት ማታ የወያኔ ታጣቂ ሰላዮች ቦንብ እንደ ታጠቁ ትምባሆ ሞኖፖል ተያዙ ይላል፤ ሌላኛው ድግሞ ለጥቆ ከዘማች ተማሪዎች መካከል ለወያኔ በመገናኛ ሬድዮ መልእክት ሲያስተላልፉ ተያዙ ይላል። አንዳንዱ ደግሞ ከመተኛታችሁ በፊት መኝታችሁን ፈትሹ የወያኔ ደጋፊዎች ፈንጂ ሊያኖሩባችሁ ይችላሉና ይላል። ይህ ከሽነድ የመነጨው የሽብር ወሬ በቀላሉ ወደ ሌሎቹ ብርጌዶች ቀንድና ጭራ ተበጅቶለት ይናኛል።

የፎለን ሜዳው ሥርዓት፣ሆ እያላችሁ  ለምን በሞራል አትሄዱም የሚለው የአሰልጣኞቹ ጭቅጭቅ፣ የጦሩና የተማሪው ግጭት……የሻለቃ አረጋ ቁጣ፣ የመቶ አለቃ አሰበ ፈገግታ እንዳልተርክላችሁ ጊዜ ያጥረኛል። (አባባሉ የቅዱስ ጳውሎስ ነው)። ነገር ግን ተኩስ ወረዳ ወርደን ዒላማ ስንለማመድ የሆነውን ላውጋችሁ።

ተኝቶ መተኮስን እየተለማመድን ነበር። በሁለት ተማሪዎች መካከል አንድ አሰልጣኝ ይቆማል። በሁለቱ ተማሪዎች መካከል ያለው ርቀት ምናልባት ሜትር ከግማሽ የሚሆን ይመስለኛል። ልምምዱ በእውነተኛ ጥይት ነበር። ከፊት ለፊታችን በቅርብ ርቀት የተተከሉ እንጨቶች ላይ የተሰኩ ካርቶኖች ነበሩ። ልምምዱ እነዚያን ካርቶኖች ዓልሞ መምታት ነበር። አሰልጣኙ “ተዘጋጅ ጀምር” ብሏል፤ ተኩሱ ተጀመረ። ሁሉም እንደየችሎታው እያለመ ይተኩሳል። በእኔና በሌላኛው ጓደኛዬ መካከል አንድ ተካ የሚባል የግቢያችን ተማሪ  ነበረ። እርሱ ገና እያነጣጠረ ሳለ ከጎኑ ያለው ዒላማው እንደገባለት ምላጭ ይስባል። የጥይት እርሳስ ወደ ተላከችበት ስትስፈነጠር ቀለኽ ትፈናጠርና ከተካ አፍንጫ ታርፋለች። ትኩስም ስለነበረች ትንሽ አፍንጫውን እንደማድማት ትላለች። ተካ ጥይት የመታው ይመስለውና ደንግጦ “ተሠዋሁ እኮ” እያለ ወደሚተኮስበት ሊገባ ሲል ቆሞ የነበረው አስተኳሽ ይዞ አስቀረው። በብዙዎች ተማሪዎች ዘንድም ስሙ “ተሠዋሁ” ሆኖ ነበር።

ወደ ሌላኛው ገጠመኝ ልውሰዳችሁ። እነ ኤፍሬም ግንቦት 16 ወይም 17 ይመስለኛል ከብላቴ የወጡት። ከሽነድ ብርጌድ ለነበርን ግን ይህን ዕድል ያገኙት ጥቂቶች ናቸው። ግንቦት 18/1983 ዓ.ም ያ ማሰልጠኛ የኀዘን ድባብ አጥሎበት ነበር። የሚወራው ነገር ሁሉ መያዣ መጨበጫ የሌለው ነበር። እኔ በራሴ የማደርገውን አላውቅም። የሽነድ አባላት በዚያች ቀውጢ ሰዓት ስንኳ ቀድመው ስለወጡት ተማሪዎች ብዙ ይሉ ነበር።አንዱ በሰላም አዲስ አበባ ገብተዋል ሲል ሌላኛው ወያኔ መንገድ ላይ ይዞአቸው ወደ እስር ቤት አስገብቷቸዋል ይላል። አዋሳ እየጠበቁን ነው የሚል የመኖሩን ያህል ኬንያ ገብተዋል የሚልም ነበር። ሌላው ደግሞ ከደቡብ ዕዝ ጋር ተቀላቅለው ወያኔን ሊወጉ እየተዘጋጁ ነው ይላል። እነዚህን ምንጭ አልባ ዜናዎች እየሰማን ቁርስና ምሳ በላን።

ከምሳ በኋላ አጭር ስብሰባ ተደረገና ወዲያዉኑ መውጣት እንዳለብን ተስማማን። ወዴት መሄድ እንዳለብን ግን በውል የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ብቻ አዲስ ወደ ተሠራው አውሮፕላን ማረፍያ ሄድን። አንድ ነግር ግን እንዳትረሱ ፤ በዚያች ግቢ ከ17 ጀምሮ ተጠያቂነት ያለው አካል አልነበረም። አንዲት ሄሊኮፕተር እንደምትመጣና ወደ ድሬዳዋ እንደምትወስደን አሁን በማላስታውሰው ሰው አማካይነት ተነገረን። እርሷን ጥበቃ በአዲሱ አውሮፕላን ማረፍያ ላይ ታች ማለት ጀመርን። ወይ የመከራ ጊዜ ሰዓት ርዝመቱ!!! ለስልጠና ብላቴ ከቆየሁት ጊዜ ይልቅ ያቺን ሄሊከኮፕተር ጥበቃ እዚያ አየር ማረፍያ የቆምሁት እንደሚበልጥ ይታሰበኛል።  ሽነድ አሁንም ይሸንዳል።

ከብዙ ጥበቃ በኋላ ሄሊኮፕተሯ በአቧራ ተከባ ዐረፈች። ተማሪው እንደ እናት ንብ ከበባት። በውስጧ ካሉት ሰዎች መካከል አንዱ መሣርያ የያዛችሁ ተማሪዎች መሣርያችሁን ጣሉ፤ ያለበለዚያ መሣርያ ይዛችሁ ልናሳፍራችሁ አንችልም” ሲል መመርያ ሰጠ። ተሜ ለሁለት ተከፈለ። መሣርያ የያዘው አንጥልም፤ ያልያዘው ጣሉ። ስምምነት ጠፋ። ጩኸት ብቻ ሆነ ልክ እንደ ጲላጦስ አደባባይ። “ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ………” እንደ ተባለው አብራሪውም ተማሪዎቹ እንዳልተስማማን ባየ ጊዜ እየኮበኮበ ጥሎን ሄደ።

ቀኑ መሸ፤ ፀሐይም ጠለቀች። አሁን ወያኔ ዙርያውን ከብባለች  ተባለ፤ ሽነድ። ሁላችንም በፍርሃት ወደ ኬስፓናችን ተመለስን። ግን ምን ተበልቶ ሊታደር? ማሠሰልጠኛው አሁን ተፈትቷል። እስቲ ምግብ ቢገኝ ብለን ወደ መመገቢያ ክፍል ገባን። ባልተከደነ ጎላ ድስት ውስጥ ከምሳ የተረፈ ማካሮኒ  በነፍሳት ተወሮ አገኘን። ጎበዝ ሳይንስ አሁን አይሠራም፤ ሰባ ሰባት ሆነን ያችን ምግብ እንደ ነገሩ ተቃመስናት።
ሌላው ሥጋት ተረኛ ዘብ የለ፤ ማን ይጠብቅ? ለካ የሽብር ሌሊት ይረዝማል የሚባለው እውነት ነው። ከአሁን አሁን ወያኔ መጥታ አፈነችን በሚል ስጋት ስንባንን አደርን። ጠዋት ሁሉም ከየኬስፓኑ ወጥቶ ከፎለን ሜዳ ሳንደርስ ዝቅ ብሎ ካለው አዳራሽ መሳይ ትልቅ ቤት አጠገብ ተገናኘን። በእግር ወደ አዋሳ መሄድ እንዳለብን ተወያየን።

የተወሰንን ልጆች ምናልባት ከመንገድ የሚያገኘንን ስለማናውቅ ጠብ መንጃ መያዝ እንዳለብን ተስማማንና ወደ መሣርያ ግምጃ ቤት ተጓዝን። ግምጃ ቤቱ ለሴቶች ብርጌድ አቅራቢያ ምናልባትም የግንቦት ልደታን ካከበርንበት አቅራቢያ ያለ ይመስለኛል። ወደዚያ ከመጓዛችን በፊት  መጋዘኑ መሰበሩን ሽነድ አብስሮናል። መሣርያ ለመውሰድ እንሂድ እንጂ ፍርሃት ግን በልቡናችን መልቶ ነበር። መጋዘኑ የተለያዩ የጦር መሣርያዎች ማስቀመጫ ነው። ምናልባት የተለያዩ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ ሌሎች እኛ የማናውቃቸውና አደጋ ሊየደርሱ የሚችሉ መሣርያዎች ቢኖሩስ? ወታደሩ መጋዘኑን ከሰበረ በኋላ ፈንጂ አጥምዶበት ከሆነስ? እነዚህ ናቸው የፍርሃታችን ምንጮች። ብቻ ስንፈራ ስንቸር ከመጋዘኑ ገብተን አንዳንድ  ነፍስ ወከፍ መሣርያ (ኤስ ኬ ኤስ?) ወሰድን።  የጥይቱን ቁጥር አላስታውሰውም።
 
ከመጋዘኑ አፍኣ ተቀምጠን የወሰድነው መሣርያ መሥራት አለ መሥራቱን መፈተሽ ጀመርን። አንድ በአካል ድክም ያለ ተማሪ ከአጠገቤ ተቀምጦ ጠብ መንጃውን ይጎረጉራል። አያያዙ ካለዚያን ቀን መሣርያ በእጁ ነክቶ የማያውቅ ይመስላል። በዚያ ላይ መሣርያውን የሚጎረጉረው አፈ ሙዙን ወደ እኔ አዙሮ ነው። ሁኔታው አላማረኝም። መላልሼ አያያዙን እንዲያስተካክል አፈ ሙዙንም ወደ ላይ ወይም ወደ መሬት እንዲያደርግ ብነግረውም የሰማኝ አልመሰለኝም። የመረጥሁትን መሣርያ መሥራቱን ካረጋገጥሁ በኋላ ተቀምጬ ጥይት በካርታው (?) እየጨመርሁ ነበር። ጎኔ የነበረው  ልጅ ሳያውቀው የጠብ መንጃውን ምላጭ በመሳቡ የተተኮሰችዋ ጥይት ከጭኖቼ መሃል ከመሬት አርፋ አፈር አለበሰችኝ። እንደዚያች ቀን የደነገጥሁበት ቀን ትዝ አይለኝም።
ከእኔ ጋር የነበሩ ጓደኞቼ የተመታሁ መስሏቸው ያን ተማሪ ሊመቱ ነበር። ደኅንነቴን ሲያውቁ ግን መለስ አሉ። ያ ተማሪ ለካስ ብላቴ እንደ ደረሰ በመታመሙ ይሰጡ የነበሩ ሥልጠናዎችን አልወሰደም። የብርጌዱ ተማሪዎች ሲወጡም ተለይቶ የቀረው በዚሁ በጤና ጉዳይ ነበር። አሁን ግን የጭንቅ ቀን በመምጣቱ ነው ከአልጋው ተነሥቶ ወደ መጋዘኑ የመጣው።
ጠብ መንጃው ከነ ጥይቱ ተስተካክሎ ተያዘ። የቀረው መጓዝ ብቻ ነው፤ ስለሆነም ጉዞ በአየር ማረፍያው በኩል አቋራጭ ነው ስለ ተባለ በዚያ አቅጣጫ ተጀመረ። አንድ ኪ.ሜ እንደ ተጓዝን ጓዝ መቀነስ እንዳለብን ተነጋገርን። ስለዚህ  ቅያሪ ልብስ ብቻ አስቀርተን ሻንጣዎቻችንን ሁሉ ከሜዳው ላይ ወረወርናቸው። ቻዎ ብላቴ!!! ጉዞ ወደ አዋሳ።

የግንቦት 19/1983 ዓ.ም ፀሐይ ከወትሮዋ ይልቅ የደመቀችና የፈካች መስላለች። እዚህ ካይሮ ያሉ ኢትዮጵያውን ፀሐይዋ ስትከርባቸው “ዛሬስ ፀሐይዋ ከነ ልጆቿ ነው የወጣችው” እንደሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው። ላብ እንደ ጅረት በመላው ሰውነታችን ይጎርፍ ጀመር። እርሱም ቢሆን ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ነበር። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ፊታችን ላይ ላብ ሳይሆን ደቃቅ የጨው እንክብሎች መታየት ጀመሩ። የሚጠጣ ውኃ ማግኘት እንደ ሰማይ ርቋል። ከአንዲት ደሳሳ ጎጆ  ውኃ ብንለምን ጎርፍ የመሰለ ድፍርስ ውኀ ሰጡን።  ምን ያድርጉ ያላቸውን ነው። ወንድሜ አሁን ሳይንስ አይታሰብም። ስለ ጤና ማሰብም አይቻልም።ብቻ ጉረሮ የሚያርስ “ውኃ” ይገኝ። ያን ውኃ ከጥሩ ምንጭ ወይም ከቧንቧ እንደ ተገኘ ውኃ ተሻምተን ጠጣነው። ቁርስ አልተበላ። ሕሊናችን ወደ ፊት ቢያስብም እግሮቻችን ግን ወደ ኋላ የሚራመዱ እስኪመስሉን ድረስ ጉዟችን በድካም የተመላ ነበር። በዚያ ሀሩር ሃያ አምስት ኪ.ሜትሮች ተጉዘን ዲምቱ ከምትባለው መንደር ደረስን።  
ዲምቱ የገጠር ከተማ ብትሆንም ስደተኛውን ተማሪ ለመቀበል ግን አቅም ነበራት። በየ ደሳሳ ቤቶች ውስጥ የመብልና የመጠጥ ንግድ የሚጧጧፍባት መንደር ናት። የበረሃው ሀሩር፣ ረሃብና ውኃ ጥም ያደከመውን ሰውነት የጣር ያህል እየጎተትን እህል ውኃ ፈልገን ቀመስን። ቅዱስ ዳዊት ነው “ እክል ያጸንዕ ኀይለ ሰብእ፤ እህል የሰውን ጉልበት ያጸናዋል” ያለው? አሁን ትንሽ በርትተናል። ከሰውም ተቀላቅለናል።
ቀጣዩን ጉዞ ከመጀመራችን በፊት ከፊት ለፊታችን  ስላለው ነገር መረጃ ማግኘት ግድ ነው። ስለሆነም የከተማዋን ሰዎች ስለ ወቅታዊው ሁኔታ ጠየቅናቸው። የሚያውቁትን ያህል ነገሩን። እግዚአብሔር ይስጣቸው። ከብላቴ የመጡ ጥቂት የአየር ወለድ አባላት ከድልድዩ አጠገብ ሆነው ማንኛውንም ዓይነት መሣርያ ከያዘ ሰው ቀምተው እንደሚወስዱ አረዱን። ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ? ጓዛችንን ሁሉ ጥለን የያዝነውን መሣርያ፣ ከሃያ አምስት ኪ.ሜትሮች በላይ በዚያ በረሃ በመሸከም የደከምንበትን መሣርያ እንዴት ይቀሙናል? አሁን ምን እናድርግ? ሌላ ጭንቀት። ጦርነት ልንከፍት? ጊዜው የከፈተብንን ጦርነት መች ተወጣነውና?
በኋላ መሣርያዎቻችንን መሸጥ እንዳለብን ተስማማን። ይህም ቢሆን ከሐሳብና ከጭንቀት የሚያድነን መፍትሔ አልነበረም። ሰዎቹ መሣርያዎቹን ከገዙን በኋላ ብራችንን አምጡ ብለው ቢቃወሙንስ? ቢገድሉንስ? ማን ነበር “ተመንደብኩ በኵለሄ” ያለው? ከብዙ የሐሳብ ውጣ ውረድ በኋላ መሣርያዎቹ ተሸጡ። አንድ ጠብ መንጃ በ250 ብር፣ አንዲት ጥይት በ0.40 ሣንቲም ተሽጠ። አሁን ከውትድርና ጋር የሚያይዘን ምናልባት ለታሪክ የያዝኳት ቱታ(ሰማያዊዋ) ብቻ ካልሆነ እኔ ዘንድ አንዳች ነገር የለም። ብቻ በመንገድ የመቁሰል አደጋ ቢደርስብን ለመጀመርያ ርዳታ መስጫ ይሆናል ብየ የያዝኩት አንድ ጠርሙስ አዮዲን እጄ ላይ ነበር። አሁን ሳስበው ጠርሙስ ሙሉ አዮዲን ተሸክሜ ያን ሁሉ መንገድ መጓዜ ይገርመኛል። ጠብ መንጃችንን ሸጠን ብራችን ቋጥረን ፀሐይ ማዘቅዘቅ እንደ ጀመረች ለቀጣዩ ጉዞ ተነሣን። አሁን ሸክማችን ቀሏል። ጉልበታችንም በቀማመስነው ምግብ ትንሽ ጸንቷል። እየዘመርንም እያወጋንም መጓዛችንን ቀጠልን። እኛ በተራመድን ቁጥር ፀሐዪቱም ለመጥለቅ የምትሮጥ ትመስላለች። እረኞች ከብቶቻቸውን እየነዱ ወደየቀዬያቸው እየተመለሱ ነው። ከቁመታቸው በላይ ዘለግ ያለና ሰፋፊ ጦር የያዙ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ ልዩ ፍጥረት ተገርመው ያዩናል። ይህ ደግሞ ሌላ ፍርሀት ፈጠረብን።
ቀደም ሲል ከሞሪቾ እስከ ብላቴ ባለው መንገድ ከሚኖሩ  ሰዎች መካከል ከባህል የተነሣ ወንድ ገድለው ይሰልባሉ የሚል ዜና ሰምተን ነበር። ይህን ዜና በሚያጠናክር መልኩ ያን አስፈሪ ጦር ያዘው በልዩ ትኩረት ሲያዩን ደግሞ በውስጣችን ከፍርሃት የላቀ ፍርሃት ተሰማን። ቅዱስ ጳውሎስ “…ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን  እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር” እንዳለው ሞት እንደቀረበን ያህል ተሰምቶን ነበር። መሣርያዎቻችን ተሸጠዋል፤ በምን ልንከላከል ነው? ልቡናችን በሐዘን ቢከብድብንም እግሮቻችን ግን ሥራቸውን አላቋረጡም፤ ይራመዳሉ። ፀሐይዋ ከእኛ ጋር ውድድር የያዘች ትመስላለች። እርሷም ወደ ማደርያዋ ለመግባት ትቻኮላለች። ዓይኖቻችን በጨለማው መያዝ ጀምረዋል። የምናየው ከአጠገባችን ያለውን ብቻ ነው። እነዚያ ባለ ጦሮች ይጠራሩ ጀመር። ምን እንደሚነጋገሩ አናውቅም። ብቻ ፍርሃት የነገሠበት ልባናችን እኛን ሊገድሉ እየተነጋገሩ እንደሆነ አድርጎ ነገረን። ሁሉም እንደየእምነቱ ጥንካሬ ጸሎት እያደረሰ ነው በልቡናው። ፀሐዪቷ አሁን ፈጽማ ጠልቃለች። እኛም ተስፋችን ተሟጧል። የሰዎቹም የጥሪ ድምፅ እያየለ እንደሆነ ተሰማን። “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰብቅታኒ!!”
በክርስትና እምነት አስተምህሮ መሠረት መጥፎው ነገር እግዚአብሔርን ሥራውንና ኀይሉን በዘመንና በቦታ ወስኖ እንደ ታሪክ መናገር ነው። እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ የምናነባቸውን ታላላቅ ሥራዎቹን ጥንት እንደ ሠራው ሁሉ አሁንም ይሠራል። ተስፋችን ተሟጥጦ የእነዚያ ሰዎች አስፈሪ ጦሮች ካሁን አሁን ተወርውረው ከሰውነታችን ላይ ተተከሉ እያልን በምንሸማቀቅበት ሰዓት የቀይ መስቀል ድርጅት ተሳቢ ካላብረስ መኪና ከመቅጽበት ከፊታችን ድቅን አለ። ሾፌሩ በዚያ ጨለማና ወጣ ገብ የገጠር ማሳ ውስጥ እንዴት እንዳዞረው አላውቅም። ብቻ  “ቶሎ ቶሎ በሉና ከላይ ውጡ “’ ሲለን  የፍርሃት ካባዬ ከላዬ ሲወድቅ ታወቀኝ። ሁለተኛው መኪና ከኋላ ያሉትን ተማሪዎች ሊሰበስብ ከነፈ። ሾፌሩ ከካርቶን ውስጥ ያለውን “ጋሌጣ” ወይም “ኮቸሮ” እንድንበላውም አዘዘን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ሕዝቡን ከመከራ ሁሉ ይታደጋቸው እንደ ነበር ያስረዳናል። በተመሳሳይ መልኩ እኛንም ቀይ መስቀልን ልኮ ታደገን። አሁን ፊታችን በርቷል። አፋችንም ለምስጋና ተከፍቷል። የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ እየተጫወትን ሞሪቾ ከተማ ደረስን። መኪናው ወደ አንድ የቀበሌ ጽ/ቤት ቅጽር ግቢ ገባና” ውረዱ” ተባልን። እኛ ወርደን እንዳበቃን መኪናው ለሌላ ተልእኮው ሄደ፤ ተጓዘ።
የሞሪቾን የአየር ንብረት ሁኔታ ባለውቅም የዚያን ሌሊት ግን ሊዩ የሆነ ብርድ ነበር ያደረባት። ለተማሪው የሚበቃ ክፍል ባለ መኖሩ ያደርነው ሜዳ ላይ ነው። እንኳን ያቺን የሞት ቀጣና አለፍናት እንጂ ብርዱስ ምንም እንደማይለን ተረድተናል። ደግሞም በመንገድ የዛለ ሰውነት በቀላሉ በእንቅልፍ ስለሚሸነፍ ስጋት አልገባንም። ሁላችንም “ሿ” ብለን ተኛን።

እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ አንድ ኀይለኛ ድምፅ ቀስቀስን። አንድ ተማሪ ነው፤ ያለቅሳል፤ ይጮኻል፤ ይስቃል፤ በሀገሪቷ ላይ፤በተማሪው ላይ፤ በራሱ ላይ ስለሆነው ነገር ይናገራል።መጀመርያ ላይ እንቅልፍ እምቢ ብሎት መስሎን ነበር። በኋላ ግን የአእምሮ ጭንቀት አግኝቶት እንደ ሆነ ተረዳን። ያለቅሳል፤ ያንጎራጉራል። የሚናገረው ቃል ሕሊናን ይረብሻል። በዚህ ጉዳይ የምናደርገው ነገር ጠፍቶን ግራ እንደ ተጋባን ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ሲሆን ሁላችንም ወደ አዋሳ ጉዞ ጀመርን።
ከሞሪቾ አዋሳ በትክክል ባላውቀውም 35 ኪ.ሜትሮች ያህል የምትርቅ ይመስለኛል። ትክክለኛ ርቀቱን የሚያውቁ ያርሙኛል። በጧቱ ብዙ ገሰገስን። ፀሐይ ወጥታ ሰማይ ምድሩን ስናይ አዋሳ እጅግ ቅርብ ሆና ስለ ታየችን በተስፋና በሞራል ብንራመድም እርሷ ግን እንዳንደርስባት የምትሸሽ ይመስል በቀላሉ ልትደረስ አልቻለችም። እኛም ጉልበታችን መዛል ጀምሯል። መቼም የተጀመረ መንገድ ሳይፈጸም ከመሃል መቅረት የለ ጥርሳችንን ነክሰን ተጉዘን አዋሳ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት ገባን። ግንቦት ሃያ 1983 ዓ.ም።
አዋሳ ጭር ብላለች። ምግብ ቤቶቿ ተግባራቸውን ያቆሙ ይመስላሉ። ሻይ ለመጠጣት ብንፈልግ እንኳ ዬት ተገኝቶ? ቡና ቤቶችና ሆቴሎች በፍርሃት ስለ ተዘጉ መኝታ ማግኘት አልተቻለም። ስለዚህ ማረፍያ ቢገኝ ብለን ወደ አዋሳ እርሻ ኮሌጅ አቀናን። ኮሌጁ ከብላቴ የተመለሱ ተማሪዎችን ለመቀበል በሩን ክፍት አድርጓል። ያ ግቢ ላለፉት ሁለት ወራት ግን ዝግ መሆኑን ልብ ይበሉ። አሁን የሚታየኝ ምግብ ውኃ አይደለም፤ ብቻ ጎኔን የማሳርፍበት ቦታ። እግሮቼ ተላልጠዋል። ከዚህን በላይ እንኳን መራመድ መቆም ከማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። ውስጥ እግሬ አብጧል።ከኮሌጁ ግቢ እንደ ገባሁ እንደ ምንም ወደ አንድ የተማሪዎች ማደርያ ክፍል አመራሁና ካገኘሁት ተደራራቢ አልጋ ከላይኛው ቆጥ ላይ “ዧ” ብዬ ወደቅሁ።
እንደ ሞት የከበደ እንቅልፍ ወሰደኝ። ምን ያህል ሰዓት ወይም ደቂቃ እንደ ተኛሁ አላስታውስም። ብቻ ከዚያ ጣፋጭ እንቅልፍ ከታችኛው ተደራቢ ተኝቶ የነበረው ጓደኛዬ (ሲሳይ ለማ) ሲገላበጥ ባንኜ ተነሣሁ። “ለምን ቀሰቅስኸኝ?” ብዬም ጮኹበት። እስቲ ጎንህን እየው? አለኝ። ልብሴን ገልጬ ጎኔን ባየው ጤፍ ላይ ተኝቼ ገላዬ ላይ የተደመደመ ይመስል ትኋኑ እላዬ ላይ ተደምድሟል። የመጨረሻ አዘንሁ። መንገዱን አልፌ ብመጣ ትኋኑ እዚህ ደገሞ ሌላ መሰናክል ይሁንብኝ? ያንን ክፍል እንኳን ልቆይበት በዓይኖቼ ላፍታ ላየው አልወደድሁም። አይደል ክፍሉን ግቢውን ጠላሁት። በልብሴ ውስጥ የተሰገሰጉት ትኋኖች እንደ ረመጥ ይለበልቡኝ ጀመር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ትኋኖችን ይዤ ከዚያ ግቢ ወጣን።
የት እንሂድ?የት እንግባ? ማን ያስጠጋናል? ከተማዋ ውስጥ መንከራተት ጀመርን። ከብዙ ድካም በኋላ አንድ የአኢሴማ ጽ/ቤት (03?) አገኘንና እንዲያሰጠጉን ለመናቸው። የጽ/ቤቱ ወለል ሊሾ የሚባለው ነው። ምንጣፍ ወይም ሰሌን ነገር አልነበረውም። ሴቶቹም በዚያ ሊሾ መሬት ላይ ገብታችሁ ተኙ ማለቱ ከብዷቸዋል። ግን የሊሾው ቅዝቃዜ ከድካማችን ስለማይብስ እሽ እንዲሉን ተማጸናቸው። ሲፈቅዱልን ገብተን  አቧራዋን እፍ ብለን ተኛን። ግንቦት 20፣21። ደስታ ከረሜላ የምታክል ዳቦ በ0.25 ገዝተን ረሃባችንን ማስታገስ ጀመርን።
ግንቦት 21 ጠዋት  ከመኝታችን ተነሥተን በር ላይ ቆመን የዕለቱን እንቅስቃሴ እየተመለከትን ነው።ከእኛ በፊት ከብላቴ የወጡት ተማሪዎች በሰላም ኬንያ መግባታቸው ተወራ። አንድ የአየር መቃወሚያ መሣርያ ያለበት መኪና ካለንበት በር አጠገብ ሆኖ ወደ ኬንያ መሄድ የሚፈልግ እንዳለ ይጠራ ጀመር። ጓደኛዬ የኔወንድም እንየው ካልሄድን ብሎ ሞገተን። ብቻ እንደ ምንም አሸነፍነውና አስቀረነው። ግንቦት 22፣ 23። ወያኔ ሀገሪቱን መቆጣጠሯ እውን መሆኑ እየታመነ መጣ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ እስካሁን ደቡብ ዕዝ እጁን አልሰጠም፤ ተማሪውም ወደ ኬንያ አልገባም፤ነገር ግን ከደቡብ ዕዝ ጋር ተቀላቅሏል ብለው ያወሩ ጀመር። ለእኔ የሁሉም ነገር አልታይህ ብሎኛል። የምፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ መኪና አግኝቼ አዲስ አበባ ከቤተሰቤ ዘንድ መድረስ።
ግንቦት 23/1983 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 አካባቢ የአንዲት አይሱዙ መኪና ረዳት ሻሻመኔ የሚሄድ ሰው እንዳለ ጠየቀን። ጎበዝ ትንሽም ብትሆን መቅረቡ ይሻላል በሚል አሳብ ሦስት ሦስት ብር ከፍለን ወደ ሻሻመኔ ተጓዝን። ሻሻመኔ የደረስነው 8፡00 አካባቢ ይመስለኛል። ገና ከመኪናው ሳንወርድ አንዲት ሚኒባስ ታክሲ አዲስ አበባ ልትሄድ ረዳቷ ሲጣራ ሰማንና ሃያ ሆነን ተሳፈርን።  በአርባ  አርባ ብር ከፍለን ጉዞ ወደ አዲስ አበባ። አሁንም ግን ፍርሃት በውስጤ ነበር። ወያኔ በመንገድ ብትይዘንስ? እርሷን ልንወጋ እንደ ዘመትን አይደል የምታውቀው? ብታስረንስ? ብትገርፈንስ? ዘማች ተማሪዎች መሆናችንን እንዴት ታውቃለች? ቢያንስ ለማስታወሻ ብለዬ የያዝኩት ሰማያዊ ቱታ ከእኔ ጋር አለ። ደግሞ ያ ጠርሙስ ሙሉ አዮዲንም አልተጣለ። ሌሎቹም እንዲሁ አንድ ነገር አያጡ። ብቻ መንገዳችን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥን መጓዝ ጀመርን።

ወያኔን በቴሌቪዥን መስኮት ከማየት በስተቀር በአካል አይቼ አላውቅም ነበር። በደርግ መገናኛ ብዙኃን የሚነገረንም ነገር ወያኔን ልዩ ፍጥረት እንደ ሆነች አድርጎ የሚያቀርብ ነበር። እንኳን ሌላ “አንቺ” የሚለውን ቅጽል እንኳን ውስጤ እንዴት ገብቶ እንደ ቀረ አላውቀውም። ያችን ልዩ ፍጥረት አድርጌ የሳልኋትን ጉድ ወያኔን ለመጀመርያ ጊዜ ያየኋት በዚያች ሚኒባስ ሃያ ሆንን ወደ አዲስ አበባ እየመጣን ሳለ ሞጆን አልፈን ደብረ ዘይት አየር ኀይል ሳንደርስ በመካከል ካለው ስፍራ ነበር። ልክ ስናያት ከእኛ የምትለይበትን ነገር ለማወቅ ነበር የጓጓሁት። ግን ከጠጉራቸው መንጨባረር ውጪ የኔው አምሳያዎች ነበሩ። ፊታቸው እንደኔው ፊት የማይፈታ ፈገግታ የተለያቸው የዓመታት ጦርነት ያንገላታቸው ሰዎች ነበሩ። ቃል የለም። ሚኒባሷ ከአቅሟ በላይ እስቲ መስል ድረስ በሃያ ሰው ታጭቃ ትከንፋለች። አዲስ አበባ ጭል ጭል የምትል መብራቷን እያበራች በቅርብ ርቀት መታየት ጀመራለች። “ ጓድ መሪ?” አለ አንዱ። ሌላኛው ተቀብሎ “ቀጥል ይሰማኛል” ሲል መለሰ። የመጀመርየው “አዲስ አበባ መብራቷን እያበራች በቅርብ ርቀት ትታያለች” አለ። ተቀባዩ ምን ነበር ያለው? ጠፍቶብኛል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ግንቦት 23/1983 ዓ.ም እስታዲየም አጠገብ ሃያ ሰዎች ከአንዲት ሚኒባስ ተራገፍን።
ታክሲ ወደ ቸርችል ጎዳና እንዴት እንደ ያዝኩ አላውቅም። ብቻ ወደ ቀኝ ወደ ግራ ገልመጥ ሳልል ተረስ ሰፈር ቀበሌ 16 ካሉት ቤተሰቦቼ በሰላም መድረሴን ብቻ ነው የማውቀው።
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን።
ቀሲስ ስንታየሁ አባተ
ካይሮ፣ ግብፅ፤
ግንቦት 3/2003  ዓ.ም።              

11 comments:

Anonymous said...

Egziabher Yestlen Kesis. Bezuwochachen kemanaweqew yetarik baher bemiTafit Qnqwa yagarun tarik gerum new. Yeh tewled kezeh men yemar yehon?

Ameha said...

ድንቅ የታሪክ ማስታወሻ! ከወንድሜ ከቀሲስ ስንታየሁ ጋር አብሬ እይተጨነቅሁ አዲስ አበባ ደረስኩ። ዲ/ን ኤፍሬም፡- አንተም ሆንክ ሌሎቹ ወገኖች የምትጽፏቸውን ገጠመኞች በአንድ መድብል እየሰበሰብክ አስቀምጣቸው። አንድ ቀን ትልቅ መጽሐፍ ይወጣውና የታሪክ ማጣቀሻ ይሆናል። ካንተም ሆነ ከሌሎቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ገና ብዙ ትውስታዎችን/ትዝታዎችን እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ፤ ረጅም ዕድሜ ይስጣችሁ!

Desalew said...

tarek newna letarek terakabie nigerun!! great story kesiss!!!

Anonymous said...

dinik tarik new egziabher yistilin yresanewin wendim efrem tastawisenaleh ke jemerik ayker benekakaw ejih oda,walda tika, kakuma,efo belina,hagere maryam temeles

Anonymous said...

ማነህ ባለ ሳምንት እኔ ነኝ የምትል የብላቴ ወዳጅ??!!!……..ዲ/ን ዶ/ር ንዋይ ገሠሠ ካለህበት ሆነህ ጽዋውን ከቀሲስ ስንታየሁ ተቀብለህ በባለ ሙሴው ዲ/ን ኤፍሬም አደባባይ ጠበል ቅመሱ በለን ፡

Anonymous said...

+++
ታሪኩ ሙሉ እንዲሆን ቀጣይ ባለታሪኮች

1) ዝዋይ ገዳም የገባ ግሩፕ ዲ/ን ሙሉጌታ ወይም አንተው ተርከው
2) ከነቀሲስ ስንታየሁ ግሩፕ በፊት ቀድሞ የገባ አለ የሰማ ባለታሪክ አንድይበሉን
3) የህቶች ጉዞ ደግሞ እህቶ ቢዘግቡበት በቦታው የነበሩ
4) ግንቦት 18 በፎሌ ሜዳ ስንሳፈረ ዶ/ር ነዋይ መኪና ላይ ወቶ የቅ/ሚካኤልን ዝክር እንዳትረሱ እያለ ከነሙሉ ልብሳችን ሁነን እስክ ሞያሌ ዋልዳ ድረስ ዶ/ር ነዋይ እና ሌላው ቢቀጥል::
በጉጉት እንጠብቃለን::
ከባለታሪክ

Anonymous said...

ከቀሲስ ስንታየሁ ጋር ሆኜ ውጣ ውረዱን በማለፍ ፡ ሲሞቃቸው ሞቆኝ ፡ ሲበርዳቸው በርዶኝ ፡ ሲርባቸው ርቦኝ ፡ ሲፈሩ ፈርቼ ፡ እዛች አዲስ አበባ ላይ በሰላም መግባቴ በጣም አስደስቶኛል፡፡ እንደነ ቀሲስ እና ዲያቆን ቢዚያ ዘመን ከስድስት ኪሎ ዩኒበርሲቲ የመጨረሻ አመት ተማሪ ሳለ ወደ ብላቴ ያቀና አጎት ስለነበረኝ በልጅነት አእምሮዬ የማስታውሰው ብዙ ነገር አለኝ፡፡ ከሁሉም በላይ የአያቴን እምነት፡፡ እስኪ አባቶቻችንም ሆናችሁ ወንድሞቻችን እያዋጣችሁ የእናንተ ታሪክ ለኛ ትምህርት ይሁነን፡፡

ሰላም

Anonymous said...

ቃለ ሕይወት ያሰማዎት። እስከ ሻሸመኔ አብረን ነበርን። እኔ ወደ ኮፈሌ እርስዎ ወደ አዲስ። በአንድ ነገር ዛሬ የሆነ ያህል ቀናሁብዎት። እኔ ከብላቴ እስከ ሞሮቾ በእግሬ ስደርስ እርስዎ በቀይ መስቀል መኪና። አዋሳ ላይ እርስዎ በትኃን ሲበሉ እኔ አልጋ አግኝቼ ነበር። የአዋሳ ነዋሪ መስተንግዶም መረሳት የለበትምና የመጻፍ ተሰጥ ኦ ያላችሁ ብታስነብቡን።
እስከ ዛሬ አቆይቶ ይህንን ታሪክ ለመጻፍም ለማንበብም ላበቃን ልኡል እግዚአብሄር ዛሬም ዘወትርም ምስጋና ይድረሰው አሜን።
ታዬ ነኝ ከማይጨው

The Architect said...

thank you all for sharing God's history manifested on you!!by the way what about those brothers and sisters went to Kenya??? please !

Anonymous said...

"ጠብ መንጃ" ...ሃሃሃሃሃ በጣም አሳከኝ፡፡ ዲ. ኤፍሬም በዕውነቱ ከፍ ያለ እንጀራ ይስጥህ፤ ቃሉን በዚህ መልኩ ተረድቸው አላውቅም ነበረ፡፡ አማርኛ እንዴት ውብ ነው አስባልከኝ ፡፡

Anonymous said...

"ክፍል ስድስትን እቀጥላለኹ፣ ሳልውል ሳላድር"
ኧረ ከመዋል ከማደር አልፈህ ከራረምክ ዲ/ን በሰላም ነው?