Sunday, May 15, 2011

"የስም ነገር"

አሜሪካ የራሷ የስም አሰጣጥና አጠራር ያላት የምትገርም ሀገር ናት። አሜሪካ ረዥም ስም አትወድም። አሜሪካ ሰዎች ትቀበላለች ይባል እንጂ ስትቀበል የራሷን ስም አውጥታ ነው። በየዘመኑ ወደ አሜሪካ የመጡ ስደተኛ ሕዝቦች በሙሉ የራሳቸውን ማንነት እና ስም አወጣጥ እንደጠበቁ ነገር ግን መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ስማቸውን አሜሪካዊ አድርገዋል። “አሌክሳንደር የነበረው አሌክስ፣ ክሪስቲያን የነበረው ክሪስ ወይም “አል” ብለው የሚጀምሩ የተለያዩ ስሞችን በማሳጠር “አል” የሚለውን ብቻ በመውሰድ የራሳቸውን ስያሜ ይፈጥራሉ። (Al Gore/ አል ጎርን ያስታውሷል)። ታዲያ ለአዲሱ ስም ዳቦ አትቆርስም፣ አታስቆርስም። ረዝሞና ረዛዝሞ የተቀመጠ ስም እንዲያጥር በፍቅሯ ታስገድዳለች። ይህንን ሁሉ ማሻሻያ የሚያደርጉት በአብዛኛው በስመ ተጸውዖ (መጠሪያ) ስማቸው ላይ እንጂ በቤተሰባቸው ስም ላይ አይደለም።


በምንኖርበት በዚህኛው የምዕራቡ ዓለም የሚጠቀሱ ሦስት ስሞች  አሉ። የመጀመሪያው “መጠሪያ ስም” ወይም “ስመ ተጸውዖ” (Personal Name፣ First Name፣ Given name) ነው። መጠሪያ ስም ወይም ስመ ተጸውዖ በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው።  ሁለተኛው ደግሞ በእኛ የስያሜ ባህል የማናገኘው “የመካከል ስም” (Middle Name) የሚባለው ሲሆን እርሱን ተከትሎ የሚመጣው ሦስተኛው ደግሞ “የቤተሰብ ስም” (Family Name፣ surname) ነው። እነዚህ ሁለቱ ማለትም “መካከለኛው” እና ሁል ጊዜም የማይለዋወጠው “የቤተሰብ ስም” የሚባለው በእኛ ባህል ባይኖርም በፈረንጆቹ እና ፈረንጅኛውን ባህል በሚከተሉት ዘንድ ግን ይዘወተራሉ። በባህል ደረጃ ሁለቱ ስሞች የሉንም እንበል እንጂ በጽሑፍ ደረጃ፣ በተለይም ወደ ውጪ አገር ስንሄድ ግን፣ ሁለቱንም ስሞች እንዲኖሩን እየሆንን ነው ማለት ይቻላል። የአባታችን ስም “መካከለኛ ስማችን/ Middle Name”፣ የአያታችን ስም ደግም “የቤተሰብ ስም”/(Family Name፣ surname)  እየሆነ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ፓስፖርት ሳወጣ አሁን ያለው አዲሱ ፓስፖርት ሥራ ላይ አልዋለም ነበር። የበፊቱ “ባለካኪ ወረቀቱ” ፓስፖርት ነው የነበረኝ። የድሮው ፓስፖርት ስማችንን በኢትዮጵኛው በደፈናው ደርድሮ ሲያበቃ የትውልድ ቀንን የሚያክል ትልቅ ቁም ነገር ማስቀመጫ ቦታ አልነበረውም። በሄድኩባቸው ሀገራት ሁል ጊዜ የሚያስቸግረው ይኸው የትውልድ ቀን አለመኖር ጉዳይ እንደነበር ትዝ ይለኛል። አንድ ቀን አዲሱን ፓስፖርት የመመልከት ዕድል ገጥሞኝ ስገልጠው የድሮውን ችግር ቀርፎት ነገር ግን የስም አሰጣጡ የእንግሊዝኛውን/ የፈረንጆቹን ባህል የተከተለ ሆኖ ተቀምጦ አገኘኹት። ስም ከነአባትን “Given name”፤ የአያት ስምን ደግሞ “surname” ብሎ ጠቅሶታል።

ይኼ መካከል ያለው “Middle Name” እና “የቤተሰብ ስም” የሚባሉት በእኛ ዘንድ ባይታወቁም አዲስ የወጣው ፓስፖርታችን “በውዴታ ግዴታ” ይህንን ስም ሰጥቶናል። እያንዳንዳችን የአያቶቻችን ስሞች “የቤተሰብ ስም” ሆነው ታድለውናል። በተለይም አሜሪካን በመሳሰለው በውጪው ዓለም ለምንኖረውና “የቤተሰብ ስም” የግድ እንዲኖረን “በውድ ለምንገደደው” የፓስፖርቱ ስም አወጣጥ ለውይይት ይጋብዛል።
በእርግጥ የፈለግነውን ስም ብንይዝ አሜሪካ ግድ የሌላት ትመስላለች። ነገር ግን “የቁርጡ ቀን” ሲመጣ ስም በራሱ መወያያ ሆኖ ቁጭ ይላል። በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰሞን ራሳቸው ሴኔተር ኦባማም ሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው፣ ኮሜዲያን እና የሚዲያ ሰዎች አንዱ የመወያያ ርዕሰ-ጉዳይ አድርገው ይዘውት የነበረው የሴኔተር ባራክ (የቤተሰብ) መጠሪያ የሆነው “ኦባማ” የሚለው ኬኒያዊ ስም ነበር። የስም ነገር ፖለቲከኞቹ በእንደዚህ ዓይነቱ አደባባይ ውሎ የሚያነሡት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሕጻናቱ ደግሞ በየዕለቱ እርስበርሳቸው ሲጫወቱ እና ሲተዋወቁ ስለ ምንነቱ እና ትርጉሙ የሚከራከሩበትም ነው።   

በተለይም በስደት ዓለም ላለን ከተለያዩ አህጉራት ለተሰበሰብን መጻተኞች ስማችን ቀላል አንድምታ የለውም። የራሴን ገጠመኝ ላንሳ። አንድ ቀን ልጄ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ዱብ ዕዳ የሆነ ጥያቄ ይዞ መጣ። “አባባ ስሜ ይቀየር” አለ። ለምን? ማን ልትባል ፈለግህ? እኮ እንዴት?” ብዬ በኢትዮጵያዊ ወኔም፣ በአባትነት ተደፈርኩ ባይነትም፣ በወንድነትም በሉት (ሴቶች እናዳትቀየሙ) ኮምጨጭ ብዬ ጠየቅኹት። ለምን ላልኩት “ስሜን አያውቁትም”፣ ማን ልትባል ትፈልጋለህ ላልኩት “ጄደን፣ ወይም ጆርዳን” ብሎ አጭር መልስ ሰጠኝ።

ከውስጣዊ ስሜቴ ራሴን ቶሎ ገትቼ ማስረዳት ገባኹ። በሆዴ “አዬ አለማወቅህ” እያልኩ የስሙን ትርጉም፣ እኔና እናቱ ለምን እንደዚያ እንዳልነው፣ እንዴት የተከበረ ስም እንደሆነ አብራራሁለት። አበው “እስመ ስሙ ይመርሖ ሀበ ግብሩ፤ ስሙ ወደ ግብሩ [ተግባሩ] ይመራዋል[ና]” ሲሉ ስምና ግብር፤ ስምና ማንነት ያላቸው ተዛምዶ የተሰናሰለ መሆኑን ሲያጠይቁ የተናገሩት መሆኑን በልቤ እያወጣኹ እያወረድኹ በአቅሙ ሊገባው የሚችለውን ነገር ለማስያዝ ሞከርኩ። የገባው መሰለኝ። ዝም ብሎ ተቀብሎኛል። ግን ጥያቄው ለረዥም ጊዜ ከአእምሮዬ አልወጣም።

“ጆርዳን” የሚባለውን ስም አውቀዋለኹ። ታዋቂ ጆርዳኖች አሉ። ግር አልተሰኘኹም። ይኼ “ጄደን/ Jaden/ Jayden” የተባለውን ስም ገና መስማቴ ነበር። እንኳን ትርጉሙን ላውቀው እስከነስምነቱ ያኔ መስማቴ ነው። ቶሎ ወደ ኢንተርኔት ሄጄ ማንነቱን እና ምንነቱን ፍለጋ ጀመርኩ። ባገኘኹት መልስ የበለጠ ተናደድኹ።

ይህ ስም አሜሪካ-ወለድ የሆነ፣ ትርጉሙ በትክክል ይህ ነው ተብሎ ያልተበየነ፣ ነገር ግን ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በመጠሪያነት በጥቅም ላይ መዋል የጀመረ፣ ታዋቂው የፊልም አክተር “ዊል ስሚዝ” ለልጁ ያወጣለት መሆኑ በአብነት የተጠቀሰ ስም መሆኑን “የሕጻናት ስሞች” ዝርዝር እና ትርጉም ውስጥ አገኘዅ።  “ጉድ በል እንትን” የተባለው ደረሰ ማለት አይደለም? ገና አምስት ዓመት ለሞላው ልጅ ይህንን መንገሩ ማደናገር እንጂ ማሳወቅ/ መጥቀም ስለማይሆን ለአቅመ-ዕውቀት እስኪደርስ በአዳር ይዤዋለኹ። ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ቢያድለኝ ያኔ እነግረዋለኹ። ከገባውና ከተስማማ የራሱን ስም ይጠብቃል፣ ለልጁና ለልጅ ልጁ ያስተላልፋል።  የስም-ነገር ቀላል አይደለም።

እኛ ኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳንሆን ሌላውም ዓለም ወደ አሜሪካም ሆነ የራሱ ባህል ወዳልሆነ ቦታ ሲሄድ ተመሳሳይ ችግር ላይ መውደቁ አይቀርም። ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጻፈውና ቆይቶም ለፊልምነት የበቃው የሕንዳዊ-አሜሪካዊቱ ደራሲ የ“Jhumpa Lahiriየሕንዳዊ ቤተሰብ ታሪክን የሚያሳየው “ሞክሼ/Namesakeየተሰኘው ድርሰት ጥሩ አብነት ይሆነናል። (ማንበብ ለሚወዱ መጽሐፉን እጠቁማለኹ። ፊልሙም (http://www.imdb.com/title/tt0433416/) ግሩም ሆኖ ተሠርቷል።)   

በርግጥ እንኳን ባህር ተሻግረን ሰው አገር ሄደን፣ እዚያው አገራችን ውስጥ ተቀምጠንም ቢሆን የስም አወጣጣችን መስመሩ እየተለየ መሔዱን ለመረዳት ብዙም ምርምር አይፈልግም። ወላጆች የልጃቸው ስም አጠር ብሎ፣ ሲጠሩት አፍ ላይ ደስ-ደስ የሚል፣ ዜማ ያለው፣ ሲያሞካሹት የሚጥም፣ ልክ እንደሚበላ ምግብ፣ እንደሚጠጣ መጠጥ እርካታን የሚፈጥር ዓይነት፣ ከተቻለ ብዙ ሰዎች ያላወጡት እና አዲስነት ያለው እንዲሆን ይጥራሉ። ለዚህ ጥሩ መፍትሔ የሆነው እንደየቤተ እምነቱ ወደሚቀበሉት “ቅዱስ መጽሐፍ” ማተኮር ነው።

የጥንት የኢትዮጵያውያንን ስም አወጣጥ ስንመለከት ሃይማኖት ትልቅ ድርሻ እንደነበረው የታሪክን ሀሁ የሚያውቅ ማንም ሰው ሊገነዘበው ይችላል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በሃይማኖት የመጣላትን ሁሉ በጅምላ አልተጫነችም። የተቀበለችውን ነገር “ኢትዮጵያዊ” (ethiopianize) አድርጋ፣ አገርኛ ጸጋ አላብሳ፣ የራሷን አሻራ ትታ፣ አገራዊውን ባህል መንግላ ሳትጥል አስማምታ ነው። ከእስልምናውም ይሁን ከክርስትናው ዓለም ያገኘችውን በራሷ መሰለቂያ አጥርታ ነው ያሳለፈችው። በዚህም ምክንያት በቤተ እምነቶች ምክንያት አገራዊ ባህል ከሥሩ ተነቅሎ ሳይጠፋ ዘመናትን ተሻግሮ ለእኛ ሊደርስ ችሏል።

ይህ ትውልድም ይህንን የቆየ ኢትዮጵያዊ አሠራር ቢጠቀምበት ባህሉን፣ ማንነቱን እንደጠበቀ ለልጆቹም የሚያስተላልፍ ይሆናል። እንዲያው “ከዚህ መጽሐፍ ነው ያገኘኹት፣ ከዚያ እምነት ነው የወሰድኹት” እያለ የራሱን ባህል፣ ያውም ከእምነቱ ጋር በምንም መልኩ የማይጋጨውን፣ እያጠፋ ቢሄድ በጦር ሜዳ ያላጣውን ነጻነት በሰላሙ ዘመን በባዶ ሜዳ ሊያጣው ይችላል።

አንድ ቀን ብዙ ሕጻናት ከተሰበሰቡበት፣ የአንዲቱ ልጅ ልደት ከሚከበርበት ቦታ ተገኝቼ ነበር። የልጅቱ ስም “ፍራኦል” ነው። ተሰብሳቢዎቹ የስሙን ትርጉም አላወቁም። አጠገቤ ከተቀመጡት ሰዎች መካከል አንደኛዋ ሌላዋን ትጠይቃለች። “ምን ማለት ነው?”። የምትመልሰው ደግሞ “አይ-ዶን’ኖ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙት መሰለኝ” ትላለች። አንዳንዱ ሰው ምንጩን የማያውቀው ስም ሲያገኝ “መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለ ሳይሆን አይቀርም” ማለት ጀምሯል ማለት ነው።

ሴት አያቴ “ወ/ሮ ፊሮ/ፍሮ ሮቢ” (ዘመድ፣ ዘመድነሽ፣ ዘመዴ ለማለት ነው) መሆናቸው የዚህኛውንም ስም መነሻ ቶሎ ለመገመት አስችሎኛል። “በእርግጠኝነት ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም ምንጩ። ኦሮምኛ መሰለኝ” ብዬ የአያቴን ስም በእማኝነት ከነገርኳቸው በኋላ እርግጠኛ ለመሆን የልጅቱ እናት ከጓዳ ስትወጣ ጠብቀው ጠየቋት። “ፍራኦል/ ፊራኦል ማለት ኦሮምኛ እንደሆነ፤ ከዘመድ በላይ” ወይም ማን-እንዳንቺ-ዘመድ ለማለት ፈልገው እንዳወጡት ነገሩን። ጠያቂዎቹም “ደስ አይልም? ውይ ደስ ሲል” ምናምን ተባብለ አጀንዳን ቀየርን በእርግጠኝነት ግን ለፈረንጅ አፍ ቀለል ያለ ስም ማውጣት የተለመደ ነው። በሥራ ቦታ የሚያጋጥመንን ላንሣ።

ሥራ ቦታ ላይ ስማችን ወሳኝ ነው። ግልጽ ነው። በተለይም እኛ አዲስ መጤዎቹ በምንሠራቸው አነስተኛ ሥራዎች ላይ ከደንበኛም፣ ከሌሎች ሠራተኞችም ጋር አብሮ ለመሥራት ነገሩን ቀለል እንዲያደርገው “አጠር ያለ ስም” መኖሩ አስፈላጊ ነው። ረዥም ስም አሜሪካ ይደብራታል። “አጠር አርገው አቦ” ምናምን ማለቷ አይቀርም። ሙሉነህ፣ ሙሉነሽ፣ ሙሉጌታ፣ ወዘተ ዓይነት ስሞቻችን በሙሉ በአጭሩ “ሙለር” ብለን ደረታችን ላይ እንለጥፋቸዋለን። ዓለማየሁ “አል” ወይም አሌክስ ይሆናል። መሐመድ የሚባሉ ሰዎች “ሞ/ Mo ተብለው ያጥራሉ። አሜሪካ ስገባ የቀጠሩኝ ኢራናዊ ሰውዬ ለረዥም ጊዜ “ሞ” ሲባሉ ስማቸው መሀመድ መሆኑን ያወቅኹት ዘግይቼ ነው። ከዚያ ወዲህ ብዙ “ሞ”ዎች በየሚዲያው አይቻለኹ። አንዳንድ ስሞች ለማጠር ምንም አማራጭ የማይገኝላቸው ሲሆን ለሥራ ቦታ እንደ ቅጽል ስም ዓይነት (ኩኩ፣ ባቢ ወዘተ ዓይነት) ሲጠቀሙ አይቻለኹ። የመዝገብ ስማቸው ግን ከዚያ ፍፁም የተለየነው። አንዳንድ ጊዜ በሥራ ላይ የምናውቃቸው ሰዎች ትክክለኛ ስመ-ተጸውዖ ወይም መጠሪያ ስማቸው ሌላ ጊዜ ከምናውቀው ፍፁም የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን።

ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ለፈረንጅ አፍ የቀለለ ስም ማለት ብዙ ጊዜ ባህላችንን ያልተከተለ ይሆናል። እንዲህ በቀላሉ ኢትዮጵያዊ ስማችንን እየጣልን ይመስላል። ለምን እንደዚህ እንደሚያደርጉ ወላጆች ምክንያትም ለማቅረብ ይሞክራሉ። “ልጃችን የተለየ ስም ካወጣንለት ነገ ችግር ሊገጥመው ይችላል” የሚል አንድምታ አላቸው። ማስረጃ ግን የላቸውም። “የራሳቸው ሳይንሳዊ ትንታኔ” ነው። “አማርኛ ብናናግረው ልጃችን ወደፊት እንግሊዝኛ ለማወቅ ይቸገራል” እንደሚለው ዓይነት ምንም ዕውቀትን ያልተመረኮዘ አባባል ማለት ነው።

ባህል እና ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። ነገር ግን የባህላችንን እና የታሪካችንን ድልብ እና ያለውን ጥቅም በቅጡ መረዳት ስላልቻልን ልክ ታሪክ እንደሌላቸው ሕዝቦች የራሳችንን እየጣልን የሩቁን ለማግኘት መከራችንን እንበላለን። ምናልባት እንደ ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የራሳችንን ሀብት ሙሉ በሙሉ ካላጣን ምናልባት የነበረንን አንረዳው ይሆን?

ሁል ጊዜ የሴት አፍሪካ-አሜሪካውያት ስሞች ሁል ጊዜ ይደንቀኛል። እነዚህ ጥቁር አሜሪካውያት ስማቸውን ከነጮቹ ሴቶች በመለየት የራሳቸው የስያሜ ይትበሃል ዘዴ ይከተላሉ። “ኒኪሻ፣ ኒኪታ፣ ናታሻ፣ አይሻ፣ ነኪያ፣ ለታሻ፣ ሳሻ፣ አዚያ፣ ” ወዘተ የሚሉ የምዕራቡን ዓለም ተለምዷዊ ስም አወጣጥ ያልተከተሉ፣ ከሒንዱ እና ከአፍሪካ እንዲሁም ከአረብኛ ስሞች የሚወስዷቸው ብዙ ስሞች አሏቸው። ከቻሉ ሙሉ ስም ከሌላ ቋንቋ ይዋሳሉ። አሊያም ከሁለት ነገር አዳቅለው አንድ ስም ይፈጥራሉ። ትርጉም ኖረው አልኖረው ደንታቸው አይደለም።

እኛም ወደዚያው እያመራን ይሆን ያሰኘኛል። ዛሬ ዛሬ ትርጉማቸውን ወዲያው ሰምቼ የማላውቃቸው ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ስሞች እሰማለኹ። ምናልባት ይህ “ትርጉሙ በቀላሉ የማይገኝ ስም” ማግኘት ራሱ ይሆናል ምስጢሩ። የድሮዎቹ ስሞችማ ከዚህ በኋላ “የጥንት ስሞች ሙዚየም” ውስጥ ካልሆነ በሕያው ሕጻን ስምነት ጥቅም ላይ ሲውሉ አንመለከታቸው ይሆናል። ከዓመታት በፊት የሰማኹት አንድ ቀልድ ትዝ አለኝ። ሕጻናት መዋያ ውስጥ፣ ከልጆቹ መካከል አንደኛው ልጅ ስሙ “ኢትዮጵያዊ” ነው። እንደ ሌሎቹ ሕጻናት ዓይነት ‘ዘመናዊ ስም’ አይደለም። እናም ሌሎቹ ልጆች ሲቀልዱበት “የትልቅ ሰው ስም፣ የትልቅ ሰው ስም” አሉት ሲባል፣ ሲቀለድ ሰምቻለኹ። አገርኛው ስም እንዲህ “አድልዎ እና መገለል” እየተፈጸመበት በራሱ ጊዜ ከጨዋታው ሜዳ ውጪ ሊሆን ነው ማለት ነው? ታሪክ ሲለወጥ …

በውጪ ያለነው ሰዎች ይኼ “ሚድል ኔም” የተባለውንም ነገር መጠቀማችን ካልቀረ ትርጉም ባለው መልክ ለማድረግ ብንሞክር ጥሩ ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖቹ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው በባዕድ አገር አድገው ነገር ግን እምነታቸውን የሚያስታውሳቸው አንድ ቋሚ ነገር ለማስቀመጥ የክርስትና ስማቸውን “ሚድል ኔማቸው” ቢያደርጉት ጥሩ ይመስለኛል። (ለውይይት ክፍት ነው፤ ሐሳብ ስጡበት)

ለምሳሌ፤ የልጁ ስም አበበ ቢሆን እና የአባቱ ስም ከበደ ዓለማየሁ ቢሆን፤ ልጁን አበበ ከበደ ዓለማየሁ ከማድረግ እና የአባቱን ስም (ከበደን) ሚድል ኔም አድርጎ በአያቱ ከመጥራት የክርስትና ስሙን መካከል በማስገባት አንድ ቋሚ ነገር ማኖር የሚቻል ይመስለኛል። ልጁ ስመ ክርስትናው ወልደ-ኢየሱስ ቢሆን፤ ስሙ ሲጠራ አበበ ወልደ-ኢየሱስ ከበደ፤ ወይም ሲያጥር አበበ ከበደ ይሆናል ማለት ነው። ልጁም ሲያድግ ስመ ክርስትናውን ለማስታወስ ሳይቸገር ሊዘልቅ ይችላል። በአያቱ ከሚጠራ በአባቱ እንዲጠራ ይሆናል። በሌላው እምነት ያለውን ስለማላውቅ ሐሳብ መስጠት ይከብደኛል።

ለማጠቃለል፦ ብርሃኑ ብሥራት (መልአከ ብርሃን ቀሲስ) እንዳዘጋጁትና “የመጠሪያ ስሞች መዝገብ” እንደተባለው መጽሐፍ ዓይነት በብዛት በማይገኝበት በእኛ ዓይነቱ ባህል ውስጥ ለልጅ ስም ማውጣቱ ቀላል ስለማይሆን በዘመኑ ታዋቂ ወደሆነው ማድላቱ የግድ ይሆናል። ትክክለኛውን መርጦ ለማውጣት እኮ የሚናገርና የሚያስተምር አገርኛ ምሑር ማግኘቱም እንዲህ ቀላል አይደለም። አለበለዚያ ወላጆች ከፊልሞች፣ ከድራማዎች፣ ከልቦለዶች፣ ከቴሌቪዥን እና ሬዲዮኖች ያገኙትን ስም ቀለብ ማድረጋቸው አይቀርም። ምዕራባውያኑ በዚህ በኩል ለሕዝባቸው ጥሩ ነገር አስቀምጠዋል። የሕጻናት ስሞችን ዝርዝር እና ትርጉም የሚያትቱ መጻሕፍት እና ድረ ገጾች አሏቸው። ወላጅ የሚፈልገውን ስም ትርጉም በየዓይነቱ መርጦ መመልከት ይችላል። የእኛዎቹም ስሞች በመጽሐፍነት ለመጠረዝ፣ በድረ-ገጽነት በዝርዝር ለመቅረብ “ክብር” ቢበቁ ወላጆች ምርጫ እንዲኖረን በር ይከፍትልናል። ቢያንስ ቢያንስ ሳናውቅ ከመሳሳት ያድነናል።

….  የስም ነገር ለዛሬ ከዚህ ላይ ይቆየን።

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “
አዲስ ጉዳይ 
መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 

18 comments:

Anonymous said...

Good suggestion brother but what if we follow our own system. No obligation to have middle name. I think its optional. correct me if i am wrong. cos i didn't give middle name to my new born baby girl. Anyways Edme Kenjera Yestelign!
MZZ

Ameha said...

ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ ጥሩ ምልከታ አድርገሃል። እኔ ከሁሉም ያሳሰበኝ ፈረንጆቹን ለማስደሰት ሲባል ኢትዮጵያዊውን የስም አጠራር ወይም አሰያየም ቀይሮ ፓስፖርት ላይ እንዲሰፍር መደረጉ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ድርጊት ሲፈጽም የሚመለከታቸውን አካላት (stake holders) አማክሮ ወይም የፍትሐ ብሔር ሕጉን አገናዝቦ ነው የሠራው ለማለት ያዳግተኛል። ምክንያቱም ሌላው ቢቀር የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከሚያዘው ወይም ከሚፈቅደው አሰያየም/ አጠራር ያፈነገጠ በመሆኑ ነው። እንደተለመደው ለዚህ ሲባል በ24 ሰዓት ውስጥ አዲስ ሕግ ካልወጣ በስተቀር! አዲሱን ሲስተም ለኢሚግሬሽን ያቀረቡት፣ ያሰለጠኑት፣ መሣሪያውንም የሰጡት ጀርመኖች እንደሆኑ ሰምቻለሁ። ከዲ/ን ኤፍሬም አፃፃፍ እንደተረዳሁትም የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው የጀርመኖቹን አሠራር ነው። ጀርመን አገር middle name የሚባል ነገር የለም። ያለው መጠሪያ ስም (given name) እና የቤተሰብ ስም (family name or surname) ብቻ ነው። middle name የሚጠየቀው አሜሪካን አገር ነው። እሱም አብዛኛውን ጊዜ እንዳለ አይጻፍም፤ የመጀመሪያዋ ፊደል ብቻ ትጻፋለች። ለምሣሌ ስሙ፡- Abebe Besso Bela ቢሆን የመሐለኛው ስም B. ብቻ ተጽፎ ይታለፋል። አንዳንዴም በውስጠ ታዋቂነት ሳይጻፍ ይዘለላል።

Anonymous said...

ኤፍርም በጣም ጥሩ እይታ ነው

Anonymous said...

ልጅ በአባቱ የማይጠራበት ሀገር አሜሪካን አየሁ

Anonymous said...

አይይ ኤፍሬም ክፉ አስለምዶን ጠፋ አይደል!!

Anonymous said...

'...የራሱን ባህል፣ ያውም ከእምነቱ ጋር በምንም መልኩ የማይጋጨውን፣ እያጠፋ ቢሄድ በጦር ሜዳ ያላጣውን ነጻነት በሰላሙ ዘመን በባዶ ሜዳ ሊያጣው ይችላል።' Well stated.

Anonymous said...

ጥሩ አይተኸናል፡፡

Anonymous said...

That is a good Idea, look our name is truly indicates biological father, grand father, etc... names clearly, and also any one can easily see how he relates with his close relatives until 7th generation. It has its own biological value other wise we do not have clear ancestry data for various purpose (at least a common way in the US and Ethiopia). So I agree this must be kept as it is and as you suggested that instead of simply ignoring the father name let us do "Our Christian Name" as a family name and continue.

You raise a good issue, I have one daughter, I and my friend argued a lot about her naming. I followed the normal Ethiopian naming system but in school and other offices they shorten my name and she called by her grand father name. My friend has one boy and he registered his boy's name as first name and father name as last name and his grand father name as middle name, why the boy is born in America and I am the head of the family and my name should be a family name. This was issue debating us a lot so let us at least keep our Identity let us do something on the naming.

ርብቃ ከጀርመን said...

ሰላም ዲያቆን ኤፍሬም እንደምን ከረምክ ስምንበተመለከተ ጥሩእይታህን አስነብበህናል ልጆት ቀጥታያባታቸውን ስምለመስጠት ከተፈለገግን ከቤተሰቦቻቸው አንደኛው አባት (እናት) በሀገራቸው ፓስፖርትየሚኖሩ ከሆነ ከእንባሲ በሀገራችን ደንብመሰረት ልጅበቀጥታያባቱን ስም እንደሚወስድ ማለትም የልጁስም አበበ ከሆነ ያባቱስም ደግሞ ተሰማ ከሆነ አበበተሰማ እንዲሆን ለማድረግ ከእንባሲው ባህላችን እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ በማጻፍ ማስደረግ እንደሚቻል በራሴ ሞክሬ ሆኖልኝ አይቸዋለሁ እና ቤተሰብ የመጠየቅመብቱ መጠቀም ያለበት ይመስለኛል ይሄን ያረኩት ከ3 አመት በፊት ነው ህጉ ካልተቀየረ ለማንኛውም እንዳልከው ባህላችን የጠበቀ ስምለማውጣት ወላጆች ማስተዋሉን ይስጠን!

Anonymous said...

Dear Ephreme,
I got your concern, about naming and identity. Your proposal and way forward is good. However, the ability to sustain once own identity as well as culture are fore sure under the control of the economic status of a given community or country. Any one who has a real concern for Ethiopia's future generation need to investigate how to help the economic issue of our people. This investigation can be done in group discussion, in the form of association or in any form.
Yours

Anonymous said...

ምነው ኤፍሬምን የበላ ጅብ አልጮህ አለ።እኔም ኤፍምን የበላ ጅብ ይጮህ ዘንድ ለባለ ወልድ ሁለት ጡዋፍ ተሳልኩ;።

Anonymous said...

የኤፍሬምን ነገር በሳተላይት ያሳየኝ፡፡ ይኸው እሱን ለመጠበቅ ስንት ቀን ሙሉ መስመር ላይ ተገትሬ ቢያየኝ ቴሌ ኔትወርክ ሊዘረጋብኝ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡

Anonymous said...

where is my comment!

Anonymous said...

ኤፍሬም ስራ ይበዛብሃል ። ስለቱን ለባለወልድ አስገብቻለሁ አንተም ሰላም ሁን ። በጣም ጠፋህ ሰላም እንደሆንክ ልቦናየ ነግሮኛል ።ዝምታህ ምንድን ነው ?መጽሓፍህ ሊወጣ ማተሚያ፡ ቤት መግባቱን ምንጮቻችን ገልጸዋል እኛም፡እንደ አምላክ ፍቃድ እንጠብቃለን ። አክባሪህ ከምእራብ ካናዳ

Anonymous said...

today is June 12
u posted this article on May 15
it means a month ago
most website viewers at least check all their favorite websites at least per 3 days
so when they try to see again and again there is no change at all. they will not see it again hoping that ephrem is busy and he post an article evrer month
so my suggestion is that
1- why donnot u share the blog to some one whom u know very well and write an article by both of u if u are busy

2- i know u have so many articles u wrote on simatsidk and Hammer even in the 1980's why don't u post it again when u are busy

i am not saying i am an advisor of u but just to get an updated information from your solid experience
Thankyou

ፍሬ said...

ዲ/ን ኤፍሬም በጣም ጥሩ ነገር ነው የታዘብከው አኔ አሁን በአባቴ ስም ነው መጠራት የምፈልገው ግን በአያቴ ስም ነው የምጠራው ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ሄጄ ምን ገጠመኝ መሰለህ አባቴ አንድ ቀን ላናግርሸ እፈልጋለሁኝ አለኝ እኔ ደግሞ አገር ሰላም ብዬ አቤት አልኩት በጣም እየተናደደ አዝናለሁኝ አለኝ ምነው ምን አጠፈሁ አልኩት ምነው ገና ሳልሞት ስሜን አጠፋሸው አለኝ ለካ ስሜ ከተፃፈ በሃል የአባቴ ስም አንድ ፊደል ብቻ ነው ከዛ የአያቴ ስም አለ ለካ እሱን አንብቦ ነው አሜሪካኖቹ እንደዚህ ነው የሚጽፉት ብለው ሊረዳኝ ነው በሃላ እናቴ መጥታ ገላገለችኝ ኢና እሰከ አሁን ድረስ ደስተኛ አየደለም... እና በጣም ችግር ነው....

Anonymous said...

Dear Dn Ephrem
Last name, Middle Name and Family name. I'm suffering because of the confusion. No one clearly tells me the difference but now I got it from your article (Thank you).
By the way I'm here in US for the last one month and I have seen one thing. Most Ethiopian who lives here in US prefer to talk to much than listening. I have discussed the problem with four people and they told me that it is correct. But I asked them the problem and they replied to me " it is ok....". Please observe

Anonymous said...

የብዙ ሺ ስሞች ፍቺ ላይ ጥናት ያደረገውንና ጥቂቱን በአንድ ወቅት በዕንቁ መጽሔት ያሰፈረውን ጋዜጠኛና ደራሲ ጌታቸው ወልዩ ጠይቀው አስቲ? ከእብራይስጥ፣ ዐረብኛ፣ ግእዝ፣ እንግሊዝኛ፣ …የተወሰዱና ሀገርኛ ሆነው ከሁነት፣ ከወንዝ፣ ተራራ፣ ሃይማኖት፣ተስፋ፣ ኖሮ፣ ድርጊት ወዘተ የተገኙ ስሞችን ባስገራሚ ሁኔታ አጥንቱዋቸዋል። የተወሰኑት በርዕዮት የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቴዎድሮስ ጸጋዬ አቅርቦአቸዋል። ዓይነ ስውሩን ቴዲን ጠይቁት። ዶክተር ታደሰ ነኝ።