Friday, June 24, 2011

ቅድሚያ ለራስ


የአሜሪካ ሬዲዮኖችና ቴሌቪዥኖች አብዛው ዘገባቸው ስለ አካባቢያቸው ነው። “የአካባቢ” የሚባሉት ሚዲያዎች ቀርቶ “አገር አቀፍ” የሚባሉትም እንኳን ሲጀምሩም ሲጨርሱም ስለ ከተማቸውና መንደራቸው፣ ግፋ ካለም አገራቸው ነው የሚያወሩት። በሌላ አገር ከሚጠፉ የሰው ነፍሶች ይልቅ በመንደራቸው የጠፋች ውሻ ጉዳይ የተሻለ ተደማጭነት ሊኖራት ይችላል። በሌላው ዓለም ከሚጀመር ትልቅ ጦርነት ይልቅ በዚያው በአካባቢው ያለ የወንጀልና ወንጀለኛ ዜና ወይም ታሪክ የበለጠ ተደማጭነት/ታዪነት አለው።

ከዋሺንግተን ዲሲ እስከ አትላንታ


በሜይ የመጨረሻ ሰኞ ቀን፣ አሜሪካ “Memorial Day/ ሚሞሪያል ዴይ” ብላ የምታከብረውን በዓል አስታክኬና አጋጣሚውን ተጠቅሜ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ያዘጋጀው 13ኛ ዓመታዊ ጉባኤው ላይ ለመካፈል ወደ አትላንታ ጉዞ ላይ ነበርኩ። “Long Weekend/ ሎንግ ዊክ ኤንድ” ወይንም አርብ እና ሰኞን ሥራ ባለመግባት ከሚከበሩት አሜሪካውያን ከሚወዷቸው በዓላት አንዱ በመሆኑ ሰዉ ሁሉ ወደ መንገድ ይወጣል። በአውሮፕላንም፣ በመኪናም፣ በባቡርም በተገኘው ሁሉ ይቺን አራት የእረፍት ቀን ለመጠቀም ቤተሰብም ሆነ ወንድና ሴት ላጤዎች ከከተማዎች ወደ ውጪ የሚጓዙበት ጊዜ ነው። በየከተማው የሚቀሩትም ቢሆኑ ለመዝናኛነቱ ይወዱታል።

Thursday, June 16, 2011

ሥልጠና:- ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል 6)


መቸም ዝም ብዬ ለመጥፋቴ ከልብ ይቅርታ ከመጠየቅ ውጪ ሌላ ምን እላለኹ። ምንም አልሞላልኝ ብሎ ሰነበተ። ይኼ የብላቴ ነገር እንዲህ አስቸጋሪ ይሆናል ብዬ መቼ ገመትኩ። ድሮም ጥይት ያለበት ነገር። የት እንደቆምን ሳትረሱ የምትቀሩ አይመስለኝም። ያለፈውን ክፍል እንድትመለከቱ ከመጋበዝ ውጪ እርሱን በመከለስ ጊዜያችሁን ማጥፋት አልፈልግም። በዚህ ክፍል “ስለ ወታደራዊው ሥልጠናና ገጠመኛችን” ለማንሳት ፍላጎት ነበረኝ። እነሆ።

 ሥልጠና

በብላቴ ሥልጠናው የሚጀምረው ከቲዎሪ ነው።  የቀለም ትምህርት ልትሉት ትችላላችሁ። ሁሉም ነገር ትምህርት አለው። አንዳንዱ ትምህርት እና አቀራረቡ ራሱን ሊቅ አድርጎ ለሚቆጥረው ተማሪ አስቂኝ ነበር። ለምሳሌ የሕክምና ተማሪዎች ባሉበት በእኛ ብርጌድ “የመጀመሪያ የሕክምና ርዳታ” አሰጣጥ ትምህርት ሲሰጥ ብዙው ተማሪ የጉምጉምታ ሳቅ ያሰማ ነበር። በርግጥ ሌሎቻችን ገና ለገና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ስለሆንን በጅምላ ራሳችንን እያስኮፈስን እንጂ መምህራኑ የሚያስተምሩትን ቀድመን ያወቅን ሆነን አልነበረም። እንዲያው ይህ ራስን የማስኮፈስ ነገር ከተነሣ ጥቂት ልበልበት። የሚቀየሙኝ አንባብያን፣ የያን ጊዜ ዘማቾች ካሉ ከወዲሁ ይቅርታቸውን እጠይቃለሁ።