Thursday, June 16, 2011

ሥልጠና:- ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ የዛሬ 20 ዓመት (ክፍል 6)


መቸም ዝም ብዬ ለመጥፋቴ ከልብ ይቅርታ ከመጠየቅ ውጪ ሌላ ምን እላለኹ። ምንም አልሞላልኝ ብሎ ሰነበተ። ይኼ የብላቴ ነገር እንዲህ አስቸጋሪ ይሆናል ብዬ መቼ ገመትኩ። ድሮም ጥይት ያለበት ነገር። የት እንደቆምን ሳትረሱ የምትቀሩ አይመስለኝም። ያለፈውን ክፍል እንድትመለከቱ ከመጋበዝ ውጪ እርሱን በመከለስ ጊዜያችሁን ማጥፋት አልፈልግም። በዚህ ክፍል “ስለ ወታደራዊው ሥልጠናና ገጠመኛችን” ለማንሳት ፍላጎት ነበረኝ። እነሆ።

 ሥልጠና

በብላቴ ሥልጠናው የሚጀምረው ከቲዎሪ ነው።  የቀለም ትምህርት ልትሉት ትችላላችሁ። ሁሉም ነገር ትምህርት አለው። አንዳንዱ ትምህርት እና አቀራረቡ ራሱን ሊቅ አድርጎ ለሚቆጥረው ተማሪ አስቂኝ ነበር። ለምሳሌ የሕክምና ተማሪዎች ባሉበት በእኛ ብርጌድ “የመጀመሪያ የሕክምና ርዳታ” አሰጣጥ ትምህርት ሲሰጥ ብዙው ተማሪ የጉምጉምታ ሳቅ ያሰማ ነበር። በርግጥ ሌሎቻችን ገና ለገና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ስለሆንን በጅምላ ራሳችንን እያስኮፈስን እንጂ መምህራኑ የሚያስተምሩትን ቀድመን ያወቅን ሆነን አልነበረም። እንዲያው ይህ ራስን የማስኮፈስ ነገር ከተነሣ ጥቂት ልበልበት። የሚቀየሙኝ አንባብያን፣ የያን ጊዜ ዘማቾች ካሉ ከወዲሁ ይቅርታቸውን እጠይቃለሁ።


በተማሪው ዘንድ “ወታደር” የሚለው ቃል እና “ማይም/ ያልተማረ” የሚለው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች የነበሩ ይመስለኛል። ውትድርና ያልተማሩ ወይም በሕይወት ምንም አማራጭ ያልነበራቸው ሰዎች መግቢያ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ አለ። ብላቴ ከመግባቴ በፊትም ቢሆን እንዲህ ዓይነት አመለካከት በተማሪውም ሆነ በሌላው ሰው ዘንድ እንዳለ አውቃለኹ። በ1966 ዓ.ም የፈነዳው አብዮት ውጤት ያጣው፣ አብዮቱን የቀሰቀሰው “የተማረው ትውልድ” ሊመራውና ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ ይልቁንም ከተማረው እጅ ወጥቶ “ባልተማሩ ማይም የበታች መኮንኖች እጅ በመውደቁ ነው” ሲባል ሰምቻለሁ፤ አንብቤያለሁም። 

በርግጥ አብዛኛው የበታች መኮንን ሕይወት የትምህርት በሯን ያልከፈተችለት፣ አገራችን ድሃ በመሆኗ የወደቀበት ቀንበር እንጂ እርሱ በተፈጥሮው የአእምሮ ድህነት ስላለበት አልነበረም። አብዛኛውም ከግብርና ሙያው በግድ እየተፈናቀለ ወደ ውትድርና የገባ በመሆኑ የእኛን ኤ.ቢ.ሲ አያውቀው ይሆናል። ዕውቀት ግን በእንግሊዝኛው ብቻ አይለካም። በዚህ ዓይነት ከእንግሊዝኛ ተናጋሪው ዓለም ውጪ ያለውን የራሻውን፣ የጀርመኑን፣ የጃፓኑን እና የቻይናውን ሳይንቲስት ሁሉ ደንቆሮ ልናደርገው ነው ማለት ነው።

እኔ ራሴ የማስታውሳቸው፣ በትምህርታቸው እጅግ በጣም ጎበዞች የነበሩ፣ ነገር ግን ሕይወት በመክበዷ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ውትድርናው የገቡ ብዙዎች ነበሩ።

አንዳንዱ ተማሪ ለወታደሩ ያለው አመለካከት ከዚህ የንቀት አስተሳሰብ የመነጨ ነበር። ብዙ ጊዜ አስተማሪዎቹ የሚያዙንን ለመቀበል እናንገራግራለን። የወታደሮቹም ትዕዛዝ ልመና አከል ጥያቄ እንጂ በእውነቱ ትዕዛዝ ነው ለማለት ይከብዳል። በወታደር ቤት ግን እንዲህ እንዳልሆነ ገና ሳልገባም አውቀዋለሁ። እኛ ግን በኢትዮጵያ የነበረውን የወታደር ሥርዓት አስሽረን አያት እንደ አሳደገችው ሞልቃቃ ልጅ እንደ እንቁላል እንዲንከባከቡን ለማድረግ ችለን ነበር። ስረዳው፣ ከበላይ ለወታደሮቹ የተላለፈ መልእክት ያለ ይመስለኛል። “እንዳታሳዝኗቸው፣ እንዳትነኳቸው፣ ዝም በሏቸው” የሚል ዓይነት።  “በምን አወቅህ?” አትሉም? እንደዚያ ባይሆን ኖሮ እንዲያ ስንንሞላቀቅባቸው ዋጋችንን አይሰጡንም ነበር ታዲያ?

በሥልጠና ላይ ጥፋት የሚያጠፋ፣ አልታዘዝ የሚል፣ በጠቅላላው ማድረግ ያለበትን የማያደርግ ምልምል ወታደር ወታደራዊ ቅጣት፣ እስርም ሆነ ሌላ ሰውነቱን የሚያደክም ስፖርት እና ሥራ መታዘዙ አይቀርም። እኛ ግን የጥፋት ዓይነት ሁሉ ብንፈጽምም ተቀጣሁ የሚል ወይም ሲቀጣ ያየሁት ሰው አልነበረም።

•••••••••

ከዕለታት በአንዱ እሑድ ለማሪው ተብሎ የተዘጋጀ የመዝናኛ ፕሮግራም ነበር። ስም ያላቸው ዘፋኞች መጥተው ነበር። ፕሮግራሙ በዚያን ሳምንት ብቻ ሳይሆን በየእሑዱ ይዘጋጅ ነበር። ከደቡብ እዝ እና ከሌሎችም ቦታዎች ቲያትሮች እና ዘፈኖች የሚያቀርቡ አርቲስቶች ይመጡ ነበር። ሒሩት በቀለንና አረጋኸኝ ወራሽን በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት እዚያ ነው።

እናም በአንዱ ቀን፣ ሒሩት በቀለ በመጣችበት እሑድ፣ ድራማም ተዘጋጅቶ ስለነበር ዝግጅቱ ተጓተተ። ተማሪው በዚህም በዚያም መነጫነጭ ጀመረ። ከዚያም ምክንያቱን ባላወቅሁት/በማላስታውሰው ሁኔታ ተማሪው ለጥበቃ በተሰማሩት ወታደሮች ላይ የስድብ ናዳ ያወርድባቸው ጀመር። ከዚያም ወደ ወታደሮቹ ድንጋይ መወርወር ተጀመረ። ወታደሮቹ የሚወረወርባቸውን ስድብ እና ድንጋይ ችለው ለማሳለፍ መሞከር ያዙ። ሒሩት በቀለ ራሷ ወጥታ በማይክራፎኑ ተማሪውን ልመና ገባች። እኛ ግን ማን ይቻለን። ድንጋዩንም ወረወርነው። ስድቡንም አወረድነው። ያ ምስኪን ወታደር ድንጋዩንም ተቀበለ፣ ስድቡንም ተሸከመ። ስሜቴን መቆጣጠር አቃተኝ። ዕንባዬን ማቆም አልቻልኩም። ለዚህ ሁሉ ብልግና ግን ተማሪው የቃላት ተግሳጽ እንኳን አልደረሰበትም። “ለወታደሩ እንባው መጣ ብሎ ደርግ ነው፤ ምናምን ነው” የሚለኝ እንዳይመጣ አደራ። ችግር ነው።
•••••••••
ሌላ ትዝታ ላካፍላችሁ። ለሰልጣኞች ምግብ ማብሰያ እንጨት የሚለቅመው ራሱ ሰልጣኙ ነው። በሁለት ይሁን በሦስት ሳምንት አንድ ጊዜ እንጨት የመልቀም ፕሮግራም አለ። እንደተለመደው አንድ ቀን እንጨት ለቅመን ስንመለስ “አህያ የማይችለው ዝናብ” መጣል ጀመረ። የተሸከምነው እንጨት ውሃውን እየጠጣ በጣም ከባድ ሆነ። ከንፋስ ጋር እየተቀላቀለ የሚወርደው ባለ ወጨፎ ዝናብ መሔጃ መንገዳችንን እስክንስት ድረስ አራወጠን። ተማሪው ታዲያ ምን ግድ አለው፤ እንጨቱን እየጣለ መሮጥ ጀመረ - ወደ መኖሪያው። ሌላ ወታደር ቢሆን ኖሮ እንኳን እንዲህ ሊያደርግ “ዝናብ መጣ” ብሎ መሮጡ በራሱ ያስቀጣው ነበር። አንዱ ሥልጠና ይህንን ዓይነቱን ዝናብ ታግሶ የታዘዙትን ግዳጅ መፈጸም አይደል? ጦርነት ውስጥ ብንገባ ኖሮ ዝናብ መጣ ብለን ወደ እናቶቻችን ቤት ልንመለስ ኖሯል? ተማሪዎች ስለሆንን አደረግነው።

•••••••••

ዝናብ ሲነሣ የብላቴ ዝናብ ትዝ አለኝ። በረሃም ስለሆነ ይሆናል፣ ዝናቡም፣ ሙቀቱም፣ ንፋሱም የተለየ ነው። ዝናብ የሚመጣ ቀን አስቀድሞ ንፋሱ ይነሣል። ከዚያም አፈሩን እና አዋራውን እያነሣ ያለብሰናል። አንዳንድ ጊዜ በከንፈሮቻችን ዳር ዳር ሳይቀር የአሸዋ ዘር ይሰገሰጋል። ጸጉራችን እና ሽፋሽፍቶቻችን በአሸዋው ይሞላሉ። ቤታችን ሳንደርስ ዝናቡ ከቀደመ በቁማችን የጭቃ ሐውልት ያስመስለናል። አፈር ናችሁ የተባልነውን፣ ጭቃ ናችሁ ያሰኘናል። ከሥልጠና መልስ ስንታጠብ ላቡ፣ አፈሩ እና አሸዋው እየተደባለቀ ይወርዳል። በዚህ ዓይነቱ ውሽንፍር ዝናብ መካከል አቅጣጫ መሳት የተለመደ ነው። ደግነቱ ግን ለክፉ አልሰጠንም።

መንገድ ስተን ብንጠፋ ምን እንደሚገጥመን አላውቅም። አውሬ የሚባል ነገር በአካባቢው አይቼ አላውቅም። ጭው ካለ በረሃ ላይ ተመሥርቶ ከመንደር ቢጠፋ በውሃ ጥም ወይም በረሀብ የሚሞትበት አካባቢም አይደለም። ከብላቴ ወንዝ ጠጥቶ ከጥም መርካት ይቻላል። ጦሩ እና ካምፑ ተበትኖ በእግራችን ስንወጣ እንዳየኹት አካባቢውም ተሸምጥጦ የሚበላ በቆሎም አይጣውም። የሚያስፈሩት “ካገኙ ገድለው ይሰልባሉ” የሚባሉት የአካባቢው ሰዎች ናቸው። ይሰውረን፤ ይሰውረን፤ … ሰወረን።
•••••••••

የብላቴ ሥልጠና ከመሣሪያ ጋር ከመተዋወቅ ይጀምራል። የነብስ-ወከፍ መሣሪያዎችን ከመገጣጠም እና ከመፍታት ይጀምራል። የነብስ-ወከፍ መሣሪያው ራሺያ ሰራሹ ክላሺንኮቭ ነው። ይህ ጠመንጃ በተለይ በታዳጊ አገሮች ከእናታችን ጡት ያላነሰ የምናውቀው ዝነኛ መሣሪያ ነው። መንግሥት ወታደሮቹን ያስታጠቃቸው እሱን ነው። ወንበዴዎች የሚባሉትም የጣጠቁት እሱኑ ነው። በዚህ ጠመንጃ የአበሻ ደም እንደ ዓባይ ፈሷል። ዛሬም ወታደሩ እሱኑ ታጥቋል።

ይኼንን ክላሽ መፍታት መግጠም ያስተማሩን ሰዎች የሚናገሩትን ነገር በጠራ አማርኛ ማስረዳት ችለዋል። ጥሩ አስተማሪዎች ናቸው። ከማልረሳቸው ቃላት መካከል ክላሹ መካከል ያለውና ጥይቷን መትቶ የሚያስፈነጥራትን ብረት “መሪ ዘንግ” ይሉታል። አስፈንጣሪውን ስፕሪንግ ደግሞ “ተመላላሽ ሽቦ” ብለውታል። በአገርኛ ቋንቋ ክላሽን ክሽን አድርገው ይገልጿታል። በዚያን ጊዜ ግን እኛ የኮሌጅ ተማሪዎች ትምህርታችንን በሙሉ በአንግሊዝኛ ከማስኬድ በቀር አገርኛ ቋንቋ ለዚህ ክብር የሚበቃ አይመስለንም ነበር።

መምህሩ አንድ ክላሽ ይዞ ከፊት ለፊት ምን ምን እንደምናደርግ በጥንቃቄ ያመለክተናል። ሌሎቻችን እሱ የሚያደርገውን እያየን እንደግማለን። እንፈታለን፤ ከዚያ እንገጥማለን። እንደነገሩን ከሆነ በእውነተኛው የጦርነት ወቅት ይህ መግጠምና መፍታት ሁነኛ ጥቅም አለው። መሣሪያውን በቅጡ ማጽዳት የማይችል ወታደር በጦርነት መካከል ክላሹ ነክሶ ሊይዝበት እና ሕይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ከየትኛው ጦርነት በኋላ መሣሪያ በሥነ ሥርዓት መጽዳትና ለሌላ አገልግሎት ዝግጁ መሆን አለበት።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ስለ ቦንብ እና ፈንጂ ዓይነቶች አስተማሩን። በተለይም እንደ ጭቃ የሚቦካው እና ባገኘው ዕቃ ላይ እየተለጠፈ በሚያስፈልግበት ጊዜ እንዲፈነዳ የሚደረገው “ልቁጥ ፈንጂ” በወቅቱ ገርሞኝ ነበር። ሰው ማጥፊያውን እንዲህ ቀላል አድርጎ ሲሰራው ማየት ይደንቃል። የእጅ ቦንብ፤ ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎች የሰው ልጅ እርስ በራሱ ሊጠፋፋበት የሰራቸው ናቸው። እንዴት እንደሚያጠፉ እና እንዴት እንደምንጠቀምባቸው በመጠኑ ብልጭ አድርገውልናል።

ከዚያ ቀጥሎ ወደ ጦር ሜዳ ውሎ እና እንዴትነቱ እንማር ጀመር። ስለ ማጥቃት እና መከላከል። ከዚህ ውስጥ ትዝ የሚለኝን በመጠኑ ላካፍላችሁ።

መቸም ወታደር ወይ ጠላት ያለበትን አካባቢ እያጠቃ ለመያዝ ይሞክራል ወይ ደግሞ በተራው እርሱ ተጠቂ ሆኖ መከላከል ውስጥ ይገባል። በሁለቱም ጊዜ እንዴት ማድረግ እንዳለብን ተምረናል። በማጥቃት ወቅት አንድ ወታደር እየተኮሰም እየሮጠም እንዴት ጠላቱን እንደሚያሸብር፣ ወደ ጠላት ምሽግ እንዴት እንደሚጠጋ፣ ወዘተ ወዘተ ሲነግሩን ነበር። ለምሳሌ ጠላት ከፍታ ቦታ ላይ፣ በወታደራዊ ቋንቋ “ገዢ መሬት” ላይ መሽጎ በሚያደፍጥበት ወቅት ወታደሩ ያንን ሜዳም ሆነ ተራራ በሩጫ እና በፍጥነት መውጣት ይጠበቅበታል። እየሮጠም፤ እየተኮሰም፣ ራሱንም ከጠላት ጥይት ለማትረፍ እየታገለ … አቤት የወታደር ነገር።  ወታደርነት ደስ የሚለው በሆሊዉድ የጦርነት ፊልም ውስጥ ብቻ ነው።

በማጥቃት ወቅት ወታደሩ የያዘውን ቀላል መሣሪያ ሳያቋርጥ እየተኮሰ ወደ ጠላቱ ምሽግ መሮጥ ይጠበቅበታል። ጠላቱ ጭንቅላቱን ቀና እንዳያደርግ ጥይቱን እያዘነበ ቀረብ ሲል ደግሞ የእጅ ቦንብ ወርውሮ ዘሎ ከጠላቱ ምሽግ ይገባል። ከዚያ ጠመንጃ የማያስፈልግበት ደረጃ ይደርስና “ጨበጣ” የሚሉትን በሳንጃ መሞሻለቅ ላይ ይደርሳል። እጅ በእጅ ከጠላቱ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ይተናነቃል። ይጥላል፤ ይወድቃል። ይኼው ነው። መግደል እና መሞት።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ስለ መከላከል አስተማሩን። መከላከል “ገዢ” መሬት ላይ ቦታ በመያዝ የሚከናወን ነው። ያንን ለማሳየት ሁላችንንም በአካባቢው ወዳለች ከፍታ ቦታ ወሰዱን። ቡቄሳ ተራራ/ ኮረብታ ትባላለች። ማታ ማታ እነሻንበል ደቤና ሠራዊቱ “ሞራል ያወጡበታል” ያልኳችሁ ተራራ ናት። እናም መከላከል እንዴት እንደሆነ እንድነረዳ በአንድ በኩል ሆነን አሰልጣኞቻችን እውነተኛ ጥይት በመጠቀም ያሳዩን ገቡ። መአቸም ያ ቀን በሕይወቴ ከማልረሳቸው ቀናት አንዱ ኢሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር።

የነበረውን ሁኔት በተቻለን አቅም ልገልጽላችሁ እሞክራለሁ። መከላከል ሲፈጸም፣ የጠላት ከፍተኛ የሆነ የጥይት ውርጅብኝ አለ ማለት ነው። ያንን ለማሳየት አሰልጣኞቻችን የእጅ ቦንብ በመወርወር እያፈነዱ ያሳዩን ጀመሩ። አንድ ወታደር ጦርነት ሲከፈትበት ሰማዩ እና ምድሩ በምን ዓይነት መልክ እንደሚደበላለቅ በመጠኑ እንዲገባን ፈልገው ነው። በሚተኮሰው የከባድ መሣሪያ ምትክ የእጅ ቦንቦችን እየተጠቀሙ ያስተምሩን ነበር። በመካከሉ ግን አስደንጋጭ ነገር ተፈጠረ።

አሰልጣኛችን ቦንቡን የሚወረውረው ምሽግ ውስጥ ሆኖ ነው። የሚፈነዳው ወረድ ብሎ ከሜዳው ላይ ነበር። ድንገት ግን ቦንቡ አሰልጣኙ ካለበት ምሽግ ውስጥ ፈነዳ። ወዲያው የታየኝ አንድ የብረት ቆብ አየር ላይ ተስፈንጥሮ መሬት ላይ ሲወድቅ ነበር። ምን እንደሆነ አልገባኝም። ሌላውም ተማሪ የገባው አይመስለኝም። ለጥቂት ሰከንዶች ጸጥታ ሆነ። ከዚያ ኃይለኛ የጣር እና የሕመም ጩኸት ተሰማ። ማቃሰት ተከተለ።

ለካስ አሰልጣኛችን ወጣቱ አየር ወለድ ቦንቡን መወርወር ሲገባው እጁ ላይ አቆይቶት ኖሮ ቦንቡ እጁ ላይ ፈንድቷል። ያንን የነገረን ሌላው አሰልጣኛችን ቆይቶ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ወጣቱ አየር ወለድ እጁን እና ሁለት ዓይኖቹን አጣ። ሕይወቱ ግን ተረፈ። ወታደሮቹ ተባርበው አነስተው ወደ ሕክምና ይዘውት ሄዱ። ባለንበት ደርቀን ቀረን። ሞት እንዲህ ቅርብ ኖሯል ለካስ።

ያ ወጣት ኢትዮጵያዊ ማን ነበር? ስሙን እንኳን አላውቀውም። አላስታውሰውም፡፤ አጭር ሰውነተ ደንዳና፣ አቋሙ ያማረ አየር ወለድ እንደነበር ትዝ ይለኛል። የፍቼ ልጅ ነው አሉ። መንግሥት ከተለወጠ በኋላ ቤተሶቹ ጋር መግባቱን ሰማኹ። ምናልባትም ይኼን ጊዜ የሰው እርጥባን የሚለምን “የኔ ቢጤ” ሆኖም ይሆናል። እንኳን ለእርሱን መሰል አካል ጉዳተኛ ለባለ ሙሉ አካሉም የምትመች አገር አይደለችም።

የሚገርመው ይህ አደጋ ደርሶ ገና ከድንጋጤያችን ሳንወጣ አሰልጣኞቻችን ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ተማሪው “አልማርም” አለ። እንዲህ የሚባል ነገር የለም በወታደር ቤት። ወታደር ይሞታል፤ ወታደር ይተካል። ኑሮም፤ ጦርነትም ይቀጥላል። ሕይወት እንዲህ ርካሽ ናት? ደግሞስ ይህ ነፍስን ማጣት ለማን? የሚሞተውስ ለማን? በውስጤ የሚመላለሰው በግጥም ቢገለጥ እንዲህ ይሆን ነበር።

የሞቴን ምክንያት እኮ ማን ይንገረኝ?
አጥንቴን ተክዬ፣
በደሜ አብቅዬ፣
እኔ ተገድዬ፤
እኔ ተዋግቼ፣
ስንት ዘመን ሞቼ?

የሞቴን ምክንያት እኮ ማን ይንገረኝ?
እኔ በበላሁት - እነርሱ ሲጠግቡ፣
የኔኑ ኮረዶች እነርሱ ሲያገቡ፣
እኔ በጠጣኹት - እነርሱ ሲረኩ፣
የገዛ ቆሎዬን - እነርሱ ሲከኩ፣
ሳቄን ሲስቁብኝ - ለቅሶዋቸውን አልቅሼ፣
እዝናቸውን ስበላ - ጥቁር ከላቸውን ለብሼ፣
ነጭ ልብሴን ተጎናጽፈው - ብር አምባሬን አጥልቀው፣
በሰርግ በመልሴ ሊዝናኑ - መደገሱን ለኔ ጥለው
የሞቴን ምክንያት እኮ ማን ይንገረኝ? …..

ያ ወታደር አደጋ የደረሰበት ቀን እጅግ የሚያስጠላ ቀን ሆኖ አለፈ። ነገር ግን ሕይወትም ቀጠለ።  ልጠናውም ቀጠለ። ያ ወጣት አየር ወለድ ደፋር እና ልበ ሙሉ ነበር አሉ። ነገር ግን ጥቂት ወራት ቢቆይ ኖረ እስከነሙሉ አካሉ ወደቤተሰቦቹ መሔድ ይችል ነበር። አልሆነም።

 ሥልጠናችን ካካተታቸው መካከል በሌሊት መዋጋት አንዱ ነው። ከዚህ ሥልጠና ውስጥ ዛሬም ድረስ የማስታውሰው “አብሪ ጥይት” እና “ስብጥር ተኩስ” የሚሉትን ቃላት ነው። አብሪ ጥይት ስሙ እንደሚያመለክተው ብርሃን ያለው ጥይት መሆኑ ነው። የሌሊቱን ውጊያ ያስተማሩን በእርሱ ነው። ስብጥር ተኩስ ደግሞ ምንም በማይታይበት ጭለማ ጠላት ቢመጣ የሚደረገውን የተኩስ ዓይነት ነው። አሁን አሜሪካኖቹ ሲያደርጉ የማየው በሌሊት ጥርት አድርጎ የሚያሳይ መነጽር የለም ማለት ነው። እናም ስብጥር ተኩስ በዘፈቀደ አደጎን እና ወደ ጎን የሚደረግ “የአቦ ሰጡኝ” ተኩስ ነው። በዚያ በሌሊት አሰልጣኞቻችን በአብሪ ጥይት እየተጠቀሙ እንዴት እንደምንተኩስ ሲያሳዩን የጥይቶቹ አበራረር የራሱ ስልት እና ውበት ነበረው። ከነገር ሁሉ የሌሊት ጦርነት በጣም የሚያስጠላ ይመስለኛል። ሰው የእውር ድንብሩን ከጠላቱ ጋር ሲታኮስ …።

የሌሊት ውጊያ ብቻ ሳይሆን በሌሊት የሚደረግ ጉዞም ራሱ አስገራሚ ነገር ነው። ወታደር በዘፈቀደ አይሁድም። አንድ መስመር ይዞ ነው። ያውም በጸጥታ። ተማሪ ደግሞ ጸጥታ አይወድም። አስቸጋሪዎች ነበርን። ያ ሥልጠና ሕይወታችንን ሊያተርፍ የሚችል ቁምነገር እንዳለው አልተገነዘብንም ነበር። በጦርነት ወቅት ቢሆን የሌሊት ጉዞ ገደልም፣ ፈንጂም፣ የጠላት ጥይትም ያለበት ስለሚሆን እጅግ የከፋ፣ አስቸጋሪ፣ ቀጭንነቱም “የገነት መንገድ” ዓይነት፣ በግራ እሳት በቀኝ እሳት ነው።

ተማሪ መቼም ቀልደኛ ነው። አንድ ቀን ሌሊት ለሥልጠና ወጥተን ስንሔድ ጨረቃዋ ቦግ ብላ ጥሬ ታስለቅማለች። አንዱ ጫካ መካከል ውሃ የመሰለ ነጭ የንጣፍ ድንጋይ በቀጭኑ አለ። ከሩቅ ሲያዩት ውሃ ኢመስላል። ተማሪው በሙሉ ከፊቱ አለው ሰው ኢሰለው እያየ ባለ በሌለ አቅሙ ይዘላል። አንድ ተንኮለኛ ተማሪ ወጣ ብሎ ይስቃል። ለካስ ውሃ እንዳልሆነ አውቆ ሲያበቃ ማዘለል የጀመረው እርሱ ነው። ሁላችን ወገባችን እስኪንቋቋ እየለልን ስንሸገር ቆይተን መሸወዳችንን ቆይቶ አወቅን። ስቆ ማለፍ እንጂ ምን ይደረጋል።

ከሥልጠናዎች ሁሉ እውነተኝነቱ የበለጠ ጎልቶ የሚሰማኝ ለመጀመሪያ ዘጊ ጥይት የተኮስንበት ቀን ነው። ኢላማ ወረዳ። እያንዳንዱ ተማሪ ሰባት ሰባት ጥይት ተሰጥቶት ዒላማውን እንዲመታ ተነግሮታል። በደረታችን ቧ ብለን ተኝተናል። ክላሳችንን ትከሻችን ላይ ግጥም አድርገን ይዘን በአንድ ዓይናችን የሰው ቅር ያለው ዒላማ ላይ እናነጣጥራለን። አሰልጣኞቻችን ከበላያችን ቆመው እንዴት እንደምንይዝ ያሳዩናል። ክላሹ ሲተኮስ ስለሚራገጥ በደንብ ጠበቅ ድርጎ መያዝ ያስፈልጋል።

ጥይት ስተኩስ የመጀመሪያ ቀኔ ስለሆነ መሸበሬ አልቀረም። አንዳንድ ተማሪዎች ግን ጠመንጃ ልክ እንደ እስክሪብቶ አብሯቸው ያደገም ነበሩ። ከተሰጣቸው ሰባት ጥይት ሰባቱንም ሳያባክኑ ዒላማቸውን መምታት ችለዋል።፡እኛ ከተሜዎቹ ጥይቶቹን ወዴት ወዴት እንደላክናቸው እግዜር ይወቀው። አንዱን ወደ ባሌ አንዱን ወደ ቦሌ ሳንተኩሳቸው አልቀረንም።

ከከተሜ ጓደኞቼ መካከል አንደኛው የሆነውን ልንገራችሁ። ቧ ብሎ ከተኛበት ቦታ አጠገቡ ያለው ተማሪ ሲተኩስ ቀለሃው ወደ ጎን ሲፈናጠር ጭንላቱን ይመታዋል። የቀለሃው ምት ማለት የስድስት ወር ሕጻን ልጅ በድንጋይ ቢመታችሁ ካለው ሰሜት ጋር እኩል ነው። ያ ወዳጄ ለካስ ጥይት የመታውና የሞተ መስሎታል። ዓይኑን ጨፍኖ ሰው ከሞተ በኋላ የሚሆነውን ይጠብቃል። ሰው ሲሞት ምን እንደሚሆን ስለማያውቅ መተንፈሱንም ቀጥ አድርጎ ይጠብቃል። (“ከዚህ በፊት ሞቶ አያውቅም አይደለ?” አለ ቀልደኛው ተስፋዬ -  ነፍሱን ይውና።) ያ ወዳጄም “ከዚህ በፊት ሞቶ ስለማያውቅ” ደንግጦ ቢጠብቅ ምንም አልመጣም። ዓይኑን ከፍቶ ቢመለከት ሁሉም ሰላም ነው። ጭንቅላቱን ቢዳብስ ደም የለውም። ማታ ከሥልጠና መልስ ይህንን ታሪክ ሲነግረን መሬት ላይ እየተንፈራፈርን ሳቅንበት። ደግነቱ በራሱ መቀለድ የሚችል ሰው ስለነበረ አልተቀየመንም። ሌላው “ፈሪ ወዳጄ” ደግሞ ዓይኑን ጨፍኖ ሰባቱንም ጥይት በአንድ ትንፋሽ አርከፍክፎ ጨርሷቸዋል። አይፈረድበትም። እስክሪብቶ እንጂ ጥይት አናውቅም።

(ይቀጥላል)

17 comments:

ibew said...

wel come back.. a nice interesting story....where have u been...disappeared like dinosaur.

Anonymous said...

የብላቴ ነገር ....የብላቴ ነገር ምን ነበር? ............ እናፈቃለሁ ብለህ ተረስተሃል አያቴ!!

Anonymous said...

እንኳን በሰላም መጣህ! እነ ሂሩት በቀለ የመጡበት ቀን ለግርግሩ መነሻ ሆነው አንድ ሰልጣኝ ተማሪ ዘፋኞቹን ሊሸልም ወይም ሊጨፍር ወደ መዽረክ ሲወጣ ወታደሩ ሆዱ ላይ በቦክስ ስለመታው ተማሪ ሁሉ ድንጋይ አንስቶ እንደ ግሪሳ ወፍ በአንዴ ወደ መድረክ የለቀቀው ተእይንትና እሱን ተከትለው ወታደሮቹ ዙሪያውን የለቀቁት ተኩስ ዬማየረሳ ትዝታ ነው፡፡ ሂሩት በቀለና የፖሊስ ኦረኬሰተራ ሙዚቀኛ ሽማግሌ ልመና ተማሪዎችን አረጋግቶ ፐሮግራሙ ቀጠለ።
እኔ ይህንን ሁሉ ትእይንት እዚው ገዢ መሬት ላይ ሆኜ እከታተል ነበረ።
ታዬ ከማይጨው

Mengistu Assebe said...

በናፍቆት ነበረ የምጠብቀው ። ጊዜ እንደሌለህ ወይም እንደሚያንስህ፤ አውቃለሁ። እኔም ለማነበብ እንኳን ጊዜ ያጥረኛል። ምን ይደረግ የኑሮ ነገር!
የአፃፃፍ ችሎታህን ና ያሳለፍከውን ትውስታህን ስእላዊ አድርገህ ማቅረብህ እኔም በወቅቱ እዚያ ከናንተው ጋራ ብላቴ እንደነበርሁ ያደርገኛል።አቤት ያገሬ ልጅ፣ ወገኔ ያሳለፈው፣ የሞተው ... መድሐኔዓለም በቃ ብሎ ለሚቀጥለው ትውልድ ሠላም፣እድገትና ፍቅርን ያውርስልን። ሁላችንም እስቲ በዘወትር ፀሎታችን እንለምነው። እድለኛም የሆንነውን ለማየት ያብቃን። አንተም ወንድሜ በርታ። ታሪክ እያስቀመጥህ ነውና እመቤታችን የቃልኪዳን ልጄ ለብርታትህ ትማለድህ። ለሚቀጥለው በሰላም ያድርሰን

መ አ
ከሐገረ ማርያም

Anonymous said...

welcome back eph..
we have been longing for u
berta

Anonymous said...

ከከተሜ ጓደኞቼ መካከል አንደኛው የሆነውን ልንገራችሁ። ቧ ብሎ ከተኛበት ቦታ አጠገቡ ያለው ተማሪ ሲተኩስ ቀለሃው ወደ ጎን ሲፈናጠር ጭንላቱን ይመታዋል። የቀለሃው ምት ማለት የስድስት ወር ሕጻን ልጅ በድንጋይ ቢመታችሁ ካለው ሰሜት ጋር እኩል ነው። ያ ወዳጄ ለካስ ጥይት የመታውና የሞተ መስሎታል። ዓይኑን ጨፍኖ ሰው ከሞተ በኋላ የሚሆነውን ይጠብቃል። ሰው ሲሞት ምን እንደሚሆን ስለማያውቅ መተንፈሱንም ቀጥ አድርጎ ይጠብቃል። (“ከዚህ በፊት ሞቶ አያውቅም አይደለ?” አለ ቀልደኛው ተስፋዬ - ነፍሱን ይማረውና።) ያ ወዳጄም “ከዚህ በፊት ሞቶ ስለማያውቅ” ደንግጦ ቢጠብቅ ምንም አልመጣም። ዓይኑን ከፍቶ ቢመለከት ሁሉም ሰላም ነው። ጭንቅላቱን ቢዳብስ ደም የለውም። ማታ ከሥልጠና መልስ ይህንን ታሪክ ሲነግረን መሬት ላይ እየተንፈራፈርን ሳቅንበት። ደግነቱ በራሱ መቀለድ የሚችል ሰው ስለነበረ አልተቀየመንም። ሌላው “ፈሪ ወዳጄ” ደግሞ ዓይኑን ጨፍኖ ሰባቱንም ጥይት በአንድ ትንፋሽ አርከፍክፎ ጨርሷቸዋል። አይፈረድበትም። እስክሪብቶ እንጂ ጥይት አናውቅም።

Gecho said...

Ephi, be siltenaw lay be Ethiopia politica zurya wede 2 gize wiyiyit neber.Ye Ene Mesfine nigigir ayresagnim.
ke 5 gna brged
Gecho

Anonymous said...

ስለ ጥፋት እና ቅጣት-እንደተባለው እንደመደበኛ ወታደር ባንቀጣም አልፎ አልፎ ትንሽ ደንገጥ የሚያደርጉ ቅጣቶች ነበሩ ለምሳሌ በተማሪ ፊት ፑሻፕ ለማሰራት መሬት ያዝ ይባል ነበር፡ ተራ ወታደሮች እና የበታቾቹ ተማሪውን አሳቻ ቦታ ካገኙትም እልሃቸውን ይወጡበት ነበር በተለይ እነሂሩት ባሉበት ፀብ ከተጫረ በኃላ። እስርም የቀመሱ ነበሩ። አንድ የአራት ኪሎ ተማሪ ጫት ይዞ ተገኝቶ ታስሮ አደረና በወታደር ትምህርት ወረዳ እንዲመጣ ተደረገ። ትምህርት ካበቃ በኃላ መቶ አለቃው እስኪ ለምን እንደታሰርክ ንገራቸው አለው። ራሱን እያከከ ጫት ይዤ አግኝተውኝ ነው ብሎ መለሰ። መቶ አለቃውም ሁለተኛ ትቅማለህ ቢለው ሀገር ሰላም ይሁን እንጂ እንቅማለን ብሎ ሁላችንንም መኮንኑን ጨምሮ አሳቀን።

እነሂሩት ባሉበት ስለተንሳው ግርግር-ታዬ ከማይጨው ምክንያቱን በከፊል ገልጾታል። አዎ መድረክ ላይ እየወጣችሁ ዘፋኞቹን እንሳም አትበሉ ሸልማችሁ ብቻ ውረዱ ተባለ። አንዱ ተማሪ ግን ልሰልም ነው ብሎ ወቶ ለምሳም እየደነሰ ሲሄድ አስር አለቃው ይጎትተዋል ተማሪው አፀያፊ ነገር ሳይናገረው አልቀረም ወታደሩ ተማሪውን ይመታዋል። መድረኩ ታች ሜዳ ላይ ሲሆን እኛ ደግሞ የተቀመጥነው ተራራማ ቀይ አሸዋ የፈሰሰበት ነው። ለመድረኩ ቀረብ ያለውና ደልዳላው ቦታ ለከፍተኛ መኮንኖች ሲሆን እኛ ከፍ ብለን ነበር የተቀመጥነው። ተማሪው መድረክ ላይ ሲመታ ከተራራው ወደታች አንኩአር አንኩአር ቀይ አሸዋ ተወረወረ መድረኩ ላይ ለማድረስ ነበር ሆኖም ድንጋዩ የመታቸው መኮንኖቹን ነበር። በዚህ ጊዜ አንዱ መኮንን ሽጉጡን አውጥቶ ወደላይ ተኮሰ፤ ከዛም አካባቢው በጥይት ጩኸት ቀለጠ። እኛም እንደውም አናይም ብለን ወደኬዝፓናችን ጉዞ ስንጀምር ሂሩት ልጆቼ እባካችሁ እኛ ከአዲስ አበባ ድረስ የመጣነው ለናንተ ብለን ነው ብላ ስትማፀን እሺ እኛ እራሳችን የመድረኩን ጥበቃ እንሰራለን ወታደር አንፈልግም ተብሎ እራሳቸውን የሾሙ ተማሪዎች ጠባቂ ሆነው በሰላም አይተን ተመለስን። በዚህ ቂም የቕጠሩት ወታደሮች በሳምንታት ዘግየት ብለው ገብተው የነበሩትን የመምህራን ማሰልጠኛ ተማሪዎች አንዳንድ የትምህርት ክፍለጊዜዎች በሰጡአቸው አጋጣሚ ጎሽመዋቸዋል። አንደኛው አቅጣጫ መለየት የተባለው ትምህርት ነው። በምሽት (ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ) ራቅ ወዳለ ቦታ ተወስደን በመቶ በመቶ ሆነን ይመስለኛል ወደብርጌዳችሁ ድረሱ ነው። አቅጣጫ ከሳትን ኬላ ጠባቂዎች አብሪ ጥይት እንሚተኩሱብን ተነግሮናል። ኣኛ ይህን ትምህርት የተማርነው ከግርግሩ በፊት ስለነበር በሰላም አልፈነዋል ዘግይተው የገቡት የመምህራን ማሰልጠኛ ተማሪዎች ግን ከዛ በኃላ ስለተማሩት ለብቻው ሲደናበር ያገኙትን ተማሪ ወታደሮቹ ጎሻሽመውታል። ሌላው መረጃ ማድረስ ነው። እዚህም ራቅ ወዳለ ስፍራ ሄደን በግል ወይ በቡድን ሊሆን ይችላል ኬላ ላይ ያሉትን ጠባቂዎች አሳማኝ ምክንያት ሰቶ አልፎ መልክቱን ብርጌድ ማድረስ ነበር። አንዳንዱ ልብሱን አውልቆ እብድ ነኝ ብሎ አልፎአል፤ ሌሎች በቡድን አንዱን እንደሬሳ ተሸክመው ቀብር እየሄድን ነው ብለው ያለፉም ነበሩ። አንዱ ተማሪ ምክንያቱ አሳማኝ ስላልነበረ የጠላት ሰላይ ነህ ተብሎ አጋድመው አብሪ ጥይት አጮሁበት እንደመግደል ማለት ነው። ከዛ በኃላ ቀጥ ብሎ ዋናውን መንገድ ይዞ ሲሄድ የሚቀጥለው ኬላ ላይ ሲያዝ እንዴት እንዲህ ቀጥ ብለህ ትመጣለህ ስባል የለም እዛኛው ኬላ ላይ ተገድያለሁ ብሎ አስቆአቸዋል። አሁንም የመምህራን ማሰልጠኛ ተማሪዎች ከግርግሩ በኃላ ስለተማሩት በዚህ አጋጣሚም የተጎሸሙ ነበሩ።

ሌላ ወንድም ኤፍሬም ያላነሳው ነገር ተፈሪ ዓለሙ በመሪ ተዋናይነት የሚሳተፍበት 1929 ትያትር ነው። እንደዚሁ አንድ እሁድ 1929ን ሊያሳዩን ከአዲስ አበባ መተው ነበር። የሚታየው ሜዳ ላይ የተሰራ መድረክ ላይ ስለነበር የመድረክ መብራቶች እንዲኖሩ ተብሎ በምሽት ነበር ያየነው። እናም አንዳንድ ተማሪዎች ከትያትሩ ይልቅ ጊዜውን ያሳለፉት ከሴት ተማሪዎች ጋር ነበር፡ አስነዋሪ ነገሮች ሁሉ ያደረጉ እንደጀብድ ሲያወሩ ሰምተናል ከትያትሩ በኃላም ሴቶች ብርጌድ አብረን ካልገባን ብለው ያስቸገሩም ገብተውም አድረው የወጡ እንደነበሩ ሲወራ ነበር።

ስለንጨት ለቀማ-ወንድም ኤፍሬም እና እኔ በርግጥ የተለያየ ብርጌድ ነበርን ሆኖም እኛ እንጨት አለቀምንም። ሌላ የሚያስታወስ ይኖር ይሆን?

እስቲ ወንድም ኤፍሬምን እየተከታተልኩኝ የረሳው ላይ ለመጨመር እሞክራለሁኝ።

Anonymous said...

ወይ ኤፍሬም ኧረ እንኳን ደህና መጣህ፡፡ አኛ የአንተን ጽሁፍ እንድናነብ አንድ ቀን 24 ሰዓት መሆኑ ቀርቶ ለአንተ ብቻ 32 ቢሆን አሪፍ ነበር፡፡

Anonymous said...

Hi! its really nice to here from you again. I'm glad to know you're okay and at the same time angry at you. Remember one day we might never come back and check you site again. Take care!!!!!

ኤፍሬም እሸቴ said...

Hi Last Anonym,

You deserve to be angry at me my friend. I apologize.

Take care too.

Solomon Wondimu said...

Dear Brother
You took me two decades back and enabled me to visualze what happened there. Please try show us all events.

Anonymous said...

minew yihn neger eresahew d/n ephrem? eyetebeqn new ketayun kifl.

Anonymous said...

selam d/n ephrem,how r u ?
i think blate part 6 has a continution, so where is part 7 ? but u post alot oters. what about it (part 7)? efi would u plzzzzzzzzzzz

Anonymous said...

Efrem I am sure you had a diary then otherwise remembering all this! May be you have a good memory. thanks fos sharing. I was also there you took me back. Do you remember the poem "Shertetie Shebelaw" I think Daniel wrote it.

Anonymous said...

please finish the lesson am waiting still

Anonymous said...

deacon please finish.......it is interesting and memorable