Friday, June 24, 2011

ከዋሺንግተን ዲሲ እስከ አትላንታ


በሜይ የመጨረሻ ሰኞ ቀን፣ አሜሪካ “Memorial Day/ ሚሞሪያል ዴይ” ብላ የምታከብረውን በዓል አስታክኬና አጋጣሚውን ተጠቅሜ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ያዘጋጀው 13ኛ ዓመታዊ ጉባኤው ላይ ለመካፈል ወደ አትላንታ ጉዞ ላይ ነበርኩ። “Long Weekend/ ሎንግ ዊክ ኤንድ” ወይንም አርብ እና ሰኞን ሥራ ባለመግባት ከሚከበሩት አሜሪካውያን ከሚወዷቸው በዓላት አንዱ በመሆኑ ሰዉ ሁሉ ወደ መንገድ ይወጣል። በአውሮፕላንም፣ በመኪናም፣ በባቡርም በተገኘው ሁሉ ይቺን አራት የእረፍት ቀን ለመጠቀም ቤተሰብም ሆነ ወንድና ሴት ላጤዎች ከከተማዎች ወደ ውጪ የሚጓዙበት ጊዜ ነው። በየከተማው የሚቀሩትም ቢሆኑ ለመዝናኛነቱ ይወዱታል።


ይኼ “Memorial Day/ ሚሞሪያል ዴይ” የሚባለው በዓላቸው መከበር ከተጀመረ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በጠቅላላው በአሜሪካ ጦርነቶች ለወደቁ እና ለሚወድቁ፣ ሕይወታቸውንም ለሰዉ ወታደሮች መታሰቢያነት የሚከበር ነው። አሜሪካውያን በዚህ የሜይ ወር የመጨረሻ ሰኞ ቀን በጦርነት ያለፉ የሚወዷቸውን ወታደር-ቤተሰቦቻቸውን ለመዘከር ወደ መቃብሮቻው ይሄዳሉ። የአበባ ጕንጕን በመካነ መቃብሮቻቸው ላይ ያስቀምጣሉ። የዕንባ ዘለላቸውን ያፈስሳሉ።

አሜሪካ በቅርብ ዘመን እንኳን በኢራቅና በአፍጋኒስታን ጦርነቶች በመጠመዷ ምክንያት ብዙ ልጆቿ ሕይወታቸውን እየሰጡ አስከሬናቸው ወዳገራቸው ይላካል። አብዛኛዎቹም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ለጋ ወታደሮች ናቸው። ብዙዎቹም ወደ ውትድርናውም ወደ ትዳሩም ለመግባት የማይፈሩ ይመስላሉ። የሚያሳዝነው በወጣትነት የወለዷቸው ሕጻናት ልጆቻቸው በአባቶቻቸው መቃብር ላይ አበባ ሲያስቀምጡ ማየት ነው።

በዚህ የሚሞሪያል ዴይ ቀን በጎብኚዎች ከሚዘወተሩት ቦታዎች አንዱና ታዋቂው እኔ ከምኖርበት ከሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ የአንድ ሰዓት የመኪና ጉዞ እንኳን የማይርቀው “የኧርሊንገተን የወታደሮች መካነ መቃብር/ Arlington National Cemetery” ነው (ፎቶውን ይመልከቱ)። ይህ ባለ 2.3 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የወታደሮች መካነ መቃብር ከአሜሪካ የእርስበእርስ ጦርነት ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናችን የአፍጋኒስታን ውጊያዎች ድረስ የሞቱ ወታደሮች የሚያርፉበት ሥፍራ ነው።

ቦታው ሐውልቶቹ ራሳቸው ልክ እንደ ደገኛ የወታደር ሰልፍ ተከሽነው የተደረደሩ የሰንጋ ፈረስ ጥር የሚመስሉበት ያማረ ሥፍራ ነው። እንደኛ አገሮቹ መቃብሮች ለማየት የሚያስጠይፉ፣ ለአፍንጫ የሚከረፉ፣ በአጠገብ ለማለፍ የሚያሰቅቁ የሙታን መንደሮች አይመስሉም። እነዚህ አሜሪካውያን በቁማቸው የሰውን ልጅ ማክበር፣ መብት መጠበቅ እንደሚችሉበት ሁሉ ከሞቱም በኋላ ለሚያርፉበት ቦታ እንዲህ ዓይነት ጽዳት እና እንክብካቤ ያደርጋሉ። ያልታደለው ደግሞ ቆሞ በሕይወት እያለም አይከበር፤ ከሞተም ወዲያ መቃብሩ አይከበር። በቁሙ የገዢዎች ዱላና የኑሮ ቀንበር ሲያንገላታው ኖሮ፣ ከሞተ በኋላ ደግሞ መቃብሩ ላይ ባለጌዎች ይጸዳዱበታል።

እንዳደረገችው የጦርነት ብዛት ቢሆን “ሚሞሪያል ዴይ” የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያ ነበረች። ለሺዎች ዓመታት ድንበሯን ለማስከበር አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ደማቸውን ያፈሰሱ ምርጥ ልጆች ያሏት አገር እንደመሆኗ እነርሱን ለመዘከር አንድ ቅርስ ልታቆም ይገባት ነበር። ትናንት የተወለደችው አሜሪካ በጣት ለሚቆጠሩ ጦርነቶች እንዲህ ዋጋ ሰጥታ ዋጋ የከፈሉ ዜጎቿን ስታከብር የሺዎች ዓመታት ታሪክ ባለ ድልብ የሆነችው ኢትዮጵያ የሚረባ ምልክት አለማቆሟ ግርምት ይፈጥራል። ምናልባትም የእኛ እና የእነርሱ ልዩነት ይህ ሳይሆን አይቀርም። ወርቅ ላበደሩን ወርቅ እስካልመለስን ድረስ ዛሬ ለምንሠራው ማንኛውም ጥሩ ሥራ አክብሮት ያላቸው ተተኪ ልጆች ማግኘት አንችልም።

ይህንን በዓል በኅሊናዬ እያወጣኹ እያወረድኩ ወደ አትላንታ ጉዞን ጀምሬያለኹ። አትላንታ የጆርጂያ ግዛት ዋና ከተማ እና የታዋቂው የኮካ ኩባንያ መናኸሪያ ናት። ወደዚህች ከተማ ስጓዝ የመጀመሪያዬ ባይሆንም ከዚህ በፊት በመኪና ተጉዤ አላውቅም ነበር። በአውሮፕላን ከሁለት ሰዓት በታች የሚርቅ ስለሆነ እንደ ሩቅ አገር አይቼው አላውቅም። በዚህኛው ጉዞዬ ግን በመኪና ነበር የሄድኩት። አገር አቋራጭ የ1030 ኪሎ ሜትር (640 ማይልስ) ጉዞ።

በመኪና ለመሔድ አውቶቡስ መያዝ ቢቻልም እንደፈለግነው በራሳችን ጊዜ ለመጓዝ እንድንችል መኪና ተከራይተናል። የመኪና አከራዮች ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት የሚያከራዩዋቸው መኪናዎች በጣም አዳዲስ እና ዘመናዊ በመሆናቸው በጣም ይደላሉ። የግል መኪናን አገር ለአገር ይዞ ከመንከራተት እና መኪናንም ከመጉዳት የኪራይ መኪናዎችን መጠቀም የተለመደ ነው። መታወቂያችንን አሳይተን፣ ክሬዲት ካርዳችንን አስመዝግበን፣ ለመኪናው የዕለት ወጪ እና አደጋ ቢደርስ መኪናውንም ሆነ በመኪናው የምንጠቀመውን ሰዎች ለመጥቀም የሚያገለግል ሙሉ ኢንሹራንስ ከፍለን መኪናውን ተረከብን። ለረጅም መንገድ የተመቸ ጥቁር ጂፕ መኪና።

የሚጠብቀን ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ነው። ከመቐለ እስከ ሐዋሳ እንደማለት ነው። መንገድ አመልካቿ “ጂ.ፒ.ኤስ” መንገዱ ሊፈጅብን የሚችለው ጊዜ 10 ሰዓት ሊሆን እንደሚችል ስንነሣ ጠቆመችን። በእርግጥ መንገድ ላይ መኪና ቢበዛ፣ መንገዱ ቢዘጋጋ፣ ለእረፍት ብንቆም ወይም ሌላ የሚያዘገየን ሁኔታ ቢፈጠር ስላለው ብክነት አታውቅም። ብቻ ለቀሪዎቹ አስር ሰዓት መንገድ ላይ እንደምንሆን አውቀን ተዘጋጅተናል።

ምንም እንኳን ውጪው በበጋው አየር የሚቃጠል ቢሆንም የመኪናዋ ማቀዝቀዣ ሙቀ እስከመኖሩም እንዳናውቅ አድርጎናል። ውሃችንን እየተጎነጨን፣ ጨዋታችንን እያቀለጥን ጉዟችንን ተያያዝነው። አሜሪካ መቼም ትልቁ ሀብቷ መንገዷ ነው። ከሰሜን ደቡብ፤ ከምዕራብ ምስራቅ በአስፓልት መንገድ ግሩም ሆና ተሰናስላላለች።

በዚህ በተመቸ መንገድ ላይ እንደውሃ እየፈሰስን ወዳጄ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ “ዘ ግሪን ኮሪደር” የሚለው በደን የተገጠገጠ ጎዳና ውስጥ ገባን። ወደ ጎን በግራም በቀኝም ያለው ደን ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ የታየው የተንጣለለ አስፋልት እና ሰማይ ነው።  ዶ/ር ጌታቸው የዛሬ አስር ዓመት ገደማ በዚሁ ጎዳና እንደተጓዘ ነግሮኝ ሲያበቃ ዛሬም ድረስ ንክችም ሳይደረግ መቆየቱን ለማድነቅ ከመኪና ውስጥ ሆኜ ካነሳሁት አንዱ ፎቶ ግርጌ ሥር “እኔ ይህንን green corridor ካየኹት አስር ዓመት ሊሆነው ነው። … (አቤት) እኛ አገር ቢሆን …. በማገዶ …” ብሎ ጽፎበታልአቤት እኛ አገር ቢሆን ኖሮ፣ “ቆርጠን ቆርጠን እንገነዳድሰው ነበር” ማለቱ መሰለኝ። (በዚያ መንገድ ላይ ያነሳዃቸውን ፎቶዎች ማየት ለሚፈልግ ወደ ፌስቡክ ገጼ ብቅ ማለት ይበቃዋል)።

ድሮ በልጅነቴ የማውቀው ዓይነት በሀረጎች የተጠቀለለ ደን ያየኹት እዚህ መንገድ ላይ ነው። ደኑ በሀረጎች መጠቅለሉ ብዙም እግረኛ እንዳልጎበኘው ምስክር ነው። አገር ቤት እንዲህ ዓይነት ደን ካየሁ ዓመታት አልፈዋል። ልጆች ሆነን እንቦርቅበት የነበረው አካባቢ ዛሬ ተመንጥሮ “ደን” የሚለውን መጻሕፍት ላይ ካልሆነ በአካል የማናገኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የልጅነት መዝናኛችን አንዱ በነዚህ ዛፎች መካከል እየተመላለሱ የችቦ እንጨት መልቀም፣ የማገዶ ጥራጊ መሰብሰብ፣ ከፍ ስንል ደግሞ “Open Air Library/ ነፋሻ ቤተ መጻሕፍት” ሆኖን ማጥኛ ቦታችንም ነበር። አንደበት ኖሮት ባይናገርም ያ ደን ባለውለታችን ነው።

ይህንን ያህል መንገድ ለሚነዳ ሰው ትልቁ ፈተናው የሰውነት ድካም አሸንፎ ሳያሸል መንዳት ነው። አለበለዚያ እንደ ውሃ ፍስስስስስስሰ በሚያደርግ ጎዳና ላይ ዓይንም መተኛቱን ሳያውቅ ድንገት ክድን ይልና የሚዘገንን አደጋ ይፈጠራል። ሰዉ ደግሞ ሲነዳ ዕብድ ነው። የመኪና ዓይነት ጭው ጭው ይላል። እጅ ከመሪ፣ ዓይን ከጎዳናው ሳይነቀል መንዳት ያስፈልጋል። ያቺን ጂፕ ያሽከረክራት የነበረው ወዳጃችን ፍሬሰው ከበደ ጠንቃቃ ዘዋሪ ነው። ድካም የሚባል አያውቀውም። ይልቁንስ ይደክመን የነበረው ሌሎቻችን ነበርን። በእርሱ እያሳበብን በየቦታው እየወረድን እረፍት እናደርግ ነበር።

አሜሪካ ጎዳናዎች ለእረፍት እንዲሆኑ በተዘጋጁ ማረፊያዎች የተሰናዱ ናቸው። እነዚህ highway rest areas/ ማረፊያ ሥፍራዎች” የሚባሉት እና በየተወሰነው ፍራ የሚገኙት የመኪና ማቆሚያዎች መጸዳጃ ቤቶች እና ቀዝቃዛ የማሺን መጠጦችን የያዙ ራስን ማስተናገጃ ቦታዎች ናቸው። ባለቤታቸው መንግሥት ነው። ከእነርሱም ውጪ የተለያዩ ሬስቶራንቶች እና ሆቴሎች ያሉባቸው ማረፊያ ቦታዎች እልም ባለው ገጠር መካከል አልፈው አልፈው ይገኛሉ።

የገረመኝ ግን መንግሥት የሚያዘጋጃቸው የማረፊያ ቦታዎች ናቸው። በተለይ መጸዳጃ ቤቶቹ ከንጽሕናቸው ሁሉንም ነገር ያሟሉ መሆናቸው፣ ደግሞም እልም ባለው ገጠር መካከልም ቢሆን መገኘታቸው። አገር ቤት እያለሁ የማውቃቸውን ትልልቅ ተቋም እየገነቡ ሽንት ቤትን ያህል ነገር ለሰዉ የማይሰሩትን ቤተ እምነቶች፣ መዝናኛዎች፣ ስቴዲየሞች፣ ወይም ትምህርት ቤቶች አስታወሰኝ። አንዳንዱ ቦታ የሚበላ የሚጠጣ ነገር አዘጋጅቶ ሽንት ቤቱን በትልቅ ቁልፍ ይከረችመው እንደነበር ትዝ ይለኛል። “አስገባ ግን አታስወጣ” ዓይነት የደንቆሮ ብልሃት።

ይህንን በሚያክል ረዥም ርቀት፣ ያ ሁሉ መኪና በሚርመሰመስበት፣ “ችግር ቢፈጠርስ” የሚል ስሜት መምጣቱ አይቀርም። በየተወሰኑ ኪሎሜትሮች ርቀት የፖሊስ መኪናዎች የጎዳናውን ጥግ ይዘው ቆመው ማየት የተለመደ ነው። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ከአንዱ ጥግ ወጥተው በአጠገባችን እንደ ጥይት ተተኩሰው ያልፉና አንዱን መኪና አስቁመውት እንደርሳለን። ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የፖሊስ ተግባሩ በጣም የተሰናሰለ ነው። በየመንገዱ ላይ የገጠሟቸው ካሜራዎች በሚሰጧቸው መረጃዎች ከሚፈቀደው በላይ ፍጥነት የሚያሽከረክረውን በአንድ ጊዜ ቀጥ ያደርጉታል።

እዚህ አሜሪካ ትራፊክ ፖሊስ እና ሌባ የሚያባርረው ፖሊስ የተለያ አለመሆናቸው ጠቅሟቸዋል። መኪና ሥርዓት የሚያሲዘውም፣ ሌባውን ለቀም የሚያደርገውም ያው አንዱ ፖሊስ ነው። የመኪናውን ወንጀለኛ የሚይዘውን ለአንዱ፣ የእግረኛውን ወንጀለኛ የሚይዘውን ለአንዱ የሚሰጠው ዓይነት አሠራር የላቸውም። ደግሞ ሥርዓታቸው።

እንዲህ እንዲህ እያልን አትላንታ ከመሸ ገባን። አትላንታ ኮካ ኮላ ፋብሪካው እና ሙዚየሙ አለ። ከአጀማመሩ ጀምሮ አንድን የኮካ ምርት የአመራረት ሒደት የሚያሳዩበት፣ በሁሉም አገር ቋንቋዎች የተጻፉ (አማርኛን ጨምሮ) ፖሰተሮች ያሉበት የጉብኝት ሥፍራ ነው። ቦታውን ጎብኝተን ስንጨርስ እዚያው የተመረተ “ትኩስ ኮካ” አበርክተውልን እሷን እየተጎነጨን እንወጣለን።

ከኮካም ውጪ የታላቁን የሰብዓዊ መብት ታጋይ የማርቲን ሉተር ኪንግን ማዕከል (Martin Luther King, Jr., National Historic Site) መጎብኘት ይቻላል። ጊዜ በቅቶኝ፣ የሄድኩበትን ጉዳይ ፈጥሜ ለማየት ባለመቻሌ አዝኛለኹ። የሚቀጥለው የአትላንታ ጉብኝቴ ይህንን ማዕከል መጎብኘት ይሆናል ብዬ በልቤ ቀጠሮ ይዣለሁ። ዛሬ “እኛ ጥቁሮቹ” ከነጮቹ እኩል በአሜሪካ የምንወጣው የምንገባው እነ ኪንግ በከፈሉት ትልቅ መስዋዕትነት ነው። “ደግሞ እኔ ኢትዮጵያዊው ምን ሆንኩኝና” ለሚል አሜሪካ መጥተህ እየው እለዋለሁ። በተለይ በዚህ በሰው አገር ለምናሳድጋቸው “ጥቁር” ልጆቻችን፣ የነኪንግ ውለታ ትልቅ ነው። ኦባማ ዛሬ ፕሬዚደንት የሆኑት ቀድሞ ማርቲን ሉተር ኪንግ በሠራው የቤት ሥራ ላይ ተመርኩዘው አይደለምን?

ይቆየን!© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ . የተወሰነ የግ. በሚታተመውአዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። ነውር ነው።
  

4 comments:

Anonymous said...

ኤፍሬም ደግሞ ካለ ክፋ ነገርህ ሰው ማጓጓት ትወዳለህ፡፡ አንዴ አትላንታ ….. አንዴ ይቆየን …. እንደገና ደግሞ ብላቴ ኡኡኡ…… ምነው ሸዋ!!!!! ልባችንን ከስንቱ ልታደርገው ፈለክ?

እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን

gammachiis said...

KIDMIA LE ABINET TIMIHIRT BET!" BE'INTE SIMA LE MARIAM!!!"

Anonymous said...

de efrem ayeh esey silete semere le bale welid negirew nebere ke mirab canada

Anonymous said...

http://debelo.org/

http://www.zeorthodox.org/

http://www.melakuezezew.info/

http://www.kesisyaredgebremedhin.com/

http://www.adebabay.com/

http://www.betedejene.org/

http://www.aleqayalewtamiru.org/

http://www.mahletzesolomon.com/

http://degusamrawi.blogspot.com


http://www.tewahedomedia.org

http://www.eotc-mkidusan.org/site/

http://suscopts.org/

http://www.dejeselam.org/

http://mosc.in/