Friday, June 24, 2011

ቅድሚያ ለራስ


የአሜሪካ ሬዲዮኖችና ቴሌቪዥኖች አብዛው ዘገባቸው ስለ አካባቢያቸው ነው። “የአካባቢ” የሚባሉት ሚዲያዎች ቀርቶ “አገር አቀፍ” የሚባሉትም እንኳን ሲጀምሩም ሲጨርሱም ስለ ከተማቸውና መንደራቸው፣ ግፋ ካለም አገራቸው ነው የሚያወሩት። በሌላ አገር ከሚጠፉ የሰው ነፍሶች ይልቅ በመንደራቸው የጠፋች ውሻ ጉዳይ የተሻለ ተደማጭነት ሊኖራት ይችላል። በሌላው ዓለም ከሚጀመር ትልቅ ጦርነት ይልቅ በዚያው በአካባቢው ያለ የወንጀልና ወንጀለኛ ዜና ወይም ታሪክ የበለጠ ተደማጭነት/ታዪነት አለው።


ቲቪ እና ሬዲዮኖቹ ብቻ ሳይሆኑ ጋዜጦቹና መጽሔቶቹም ያው ናቸው። ትልቁ ዜና ሽፋናቸው ስለ አካባቢያቸው ነው። ሌላው ቀርቶ ትልልቅ የሚባሉት ስመ ገናና ሕትመቶችም ቢሆኑ ቀላል የማይባለውን ድርሻ የሚሰጡት ለአካባቢያቸው ጉዳይ ነው።

 ታዲያ እንግሊዞች እና አሜሪካኖች ሲበሻሸቁ እንግሊዞቹ አሜሪካውያኑን ከሚነቅፉባቸው ነገሮች አንዱ “ይኼ ጠባብነታቸው፣ ከራሳቸው አካባቢ ውጪ ሌላ አለማወቃቸው” ነው ሲባል ሰምቻለሁ። ምክንያቱም እንግሊዞች ብዙ የማንበብ፣ ሚዲያ የመከታተል፣ ስለ ሌላው ዓለም የማወቅ ሰፊ ትጋት ያላቸው እንደሆኑ ስለራሳቸው ያደንቃሉ። በጋዜጦቻቸው ብዛት በዓለም ያላቸውን መሪነት እያወሱ “አእምሮ ሰፊ” መሆናቸውን ይሰብካሉ። የበሬ ግንባር የምታክል ትንሽ ደሴት ዓለምን ለዘመናት “በእጇ ጭብጥ፣ በእግሯ እርግጥ” አድርጋ የመግዛቷንም ምስጢር ከዚሁ ጋር አገናኝተው ያወሳሉ።

ሁል ጊዜ ታዲያ “ይኼ የአሜሪካውያን ጠባብነት” ይገርመኝ ነበር። መቸም አሜሪካዊን ታሪክና ጂኦግራፊ አለመጠየቅ ይሻላል። አንድን አገር በዓለም ካርታ ላይ ማግኘት ቀርቶ የትኛው አህጉር እንዳለች ማሳየት ጭንቃቸው ነው። የሰውን ስም ከአገር ስም ለይተው የማያዉቁ ይገጥሟችኋል። እንዴት ይህንን የሚያክል ትልቅ አገር እና ትልቅ ሕዝብ እንደዚህ ይሆናል? የሚል ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም።

አሁን አሁን ስመለከተው ግን አንድ ሰው ስለ አካባቢው ምኑንም ሳያውቅ ጨረቃ ድረስ ቢመጥቅ፣ ስለ ቀበሌው ሳይረዳ አውሮፓ እና አሜሪካ ስላለ አንድ ስፍራ አብጠርጥሮ ቢያውቅ ምን ይጠቅመዋል። ስለ ራሳችን ታሪክ ሳንማር ስለ አውሮፓ ታሪክ አብጠርጥረን የተማርንባቸው የትምህርት ዘመናት ትዝ ይሉኛል።

በአገራችን ስንት ቋንቋ እንዳለ ምንም ሳይነገረን ስለ ጣሊያን ታሪክ፣ ስለ አውሮፓ ፍልስፍና፣ ስለራሺያ  ቀይ ጦር፣ ስለ ቻይና እና ቬትናም አብዮት፣ ስለ አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ ስለ እንግሊዝ ነገስታት፣ ስለ እስራኤል ምርጥነት ስለ አረቦች ተዋጊነት … ያልተጫንነው ጭነት አልነበረም። ስለ እነርሱ ስንማር ማረሻችንን መቀየር ሳንችል፤ ጥብቆ አሰፋፍ ሳናውቅ፣ መርፌ ሳንሰራ እነሆ ሺህ ዘመናት አለፉን።

አሜሪካ እውነት አላት። ጨረቃ ለመድረስ አካባቢን ማወቅ ይቀድማል። የቻይናን ግንብ ለመጎብት ከመብረራችን በፊት ላሊበላን ማየት አለብን። ውቂያኖስ ከመሻገራችን በፊት ጣና ላይ መንሳፈፍ ብናስቀድም ይበልጣል። የካናዳን ናያግራ ፏፏቴ ከማየታችን በፊት የአገራችንን የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ብናውቅ አዋቂዎች ነን። 

አሜሪካ እውነት አላት። ቅድሚያ ለራስ። ቅድሚያ የራስ። ሌላው ቀስ ብሎ ይደርሳል። መናገርም፣ መጻፍም፣ ማስተማርም የሚሻለው ቶሎ ጥቅም ላይ የሚውለውን ነው። ስለ አየር ንብረት ሲናገሩ “በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በደቡብ አንዳንድ አካባቢዎች ይዘንባል” የሚል ዓይነት እጅ እግሩ የማይታወቅ ትንበያ አያቀርቡም። ስለ አዲስ አበባ ለመናገር ስለ መላው ሸዋ አያነሱም። ስለ አዋሳ ለማስረዳት የደቡብ ሕዘቦችን ክልል በሙሉ አያካልሉም። ጥቅም የሚሰጠውን በአጭሩ እና በሚረዳ ቋንቋ መልክ ያቀርባሉ።

ግን ሁሉ አሜሪካዊ እንዲህ “ጠባብ” መስሎን እንዳንሳሳት። አሮጊቷ እንግሊዝ ስታረጅ ዓለምን የመግዛት በትረ ሙሴውን የተረከቡት በቀላሉ አይደለም። የዓለም ጭንቅላትና ልብ ያለው አሜሪካ ነው። ከሊቃውንቱም ቁንጮዎቹ ያሉባት አገር ናት። እነርሱ የብዙውን ሰው ዕውቀት አብረው ያወቁለት እስኪመስል ድረስ በዓለም ላይ ያለችውን ሰባራዋን ሰንጣራዋን ነገር ሁሉ የሚያውቁ ሞልተውባቸዋል።

ነገር ግን ሁሉንም ሳይንቲስት፣ ሁሉንም ፈላስፋ፣ ሁሉንም ምሁር ማድረግ አላስፈለጋቸውም። ያገራችን ገጣሚ 
“ሁሉ ከሆነ ቃልቻ፤
ማን ሊሸከም ስልቻ” እንዳለው ዜጋቸው ሁሉ በመላው ዓለም ስላለው ነገር እንዲጨነቅ ማድረግ አልፈለጉም። ስለ አካባቢው እና ስለ ራሱ ሕይወት ግን በቅጡ እንዲያውቅ፣ የሚጠቅመውን እና የሚጎዳወን በደንብ እንዲረዳ አድርገውታል።

አራት ኪሎ የሚፈጠረውን ስድስት ኪሎ በማይሰማበት አገር የምንኖረው ስለ አካባቢያችን ትተን የሩቁን እንድንመለከት ስለሆንን ይመስላል። “ከሩቅ መልአክ የቅርብ …” እያልን ብናድግም የቅርቡን በቅጡ አልተመለከትነውም። የተገላቢጦሽ ሆኖ የቅርቡ ሩቅ ሆኖብናል።

እዚህ የማገኛቸው ወዳጆቼ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ቦታዎችን ያዩት ውጪ አገር ከወጡ በኋላ ነው። ድሮ ገንዘብ ስላልነበራችሁ ይሆናል ማለቴ አልቀረም። “ኖ” ነው መልሳቸው። ትዝም አላላቸውም ነበር። የቅኝት ጉዳይ ነው። እኛ የተቃኘነውን የሩቁን ዘፈን በመዝፈን እንጂ የቅርባችንን በማንጎራጎር አልነበረም። አንዴ ወደ ምሥራቁ ጎራ፣ አንዴ ወደ ምእራቡ ጎራ እና ፍልስፍና ስንላጋ ኖርን እንጂ የራሳችንን መስመር በራሳችን ዕይታ ፈልጎ ለማግኘት አልቻልንም ነበር።ዛሬም ያው ነው። ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው የአስተሳሰባችን እና የአመለካከታችን ቅኝት ኢትዮጵያዊ እና አገራዊ በሆነ ነጥብ ላይ የተመረኮዘ አይደለም።

የዚህ ድውይ አስተሳሰብ ውጤት ደግሞ በአዲሱ ትውልድ ላይ አፍርቶ እና ጎምርቶ ልናየው እንችላለን። ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና የእነርሱ ልጆች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ቆዳቸው እና ቀለማቸው፣ ቁመናቸው እና ስያሜያቸው የእና የሆነ አእምሮ እና አስተሳሰባቸው ግን ከእኛ ባህል እና ልምድ በብዙ የራቀ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነው።

እንደማንኛውም የአሜሪካ ወጣት፣ በተለይም ጥቁር ወጣት፣ ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው፣ ቀበቶ ሊይዘው ይገባ የነበረውን ሱሪ እንዳይወድቅ በእግሮቻቸው ወጥረው፣ ሰንሰለት የመሰለ ዘለበት እያንቀጫቀጩ ሲሄዱ ማየት የተለመደ ነው። ራሴም እንዲህ ዓይነቱ የውስጥ ሱሪን እያሳዩ መሔድ ምን ይሉታል እያልኩ እገረም ነበር። አንዱ ጉዳዩን እና ትርጉሙን አውቃለሁ የሚል ሰው ሱሪያቸውን እንደዚያ ዝቅ አድርገው የሚሄዱበት ምክንያቱ በባርነቱ ዘመን ጥቁሮች ሰንሰለት በእጅ በእግራቸው እየገባ ለመራመድ ይቸገሩበት የነበረውን የጨለማ ዘመን ለማስታወስ ያደረጉት መሆኑን አጫወተኝ።

በእርግጥ ይህ ሱሪ ዝቅ ማድረግ ትርጉሙ ይህ ከሆነ የእኛዎቹ ልጆች በራሳቸው ላይ ሰንሰለት አጥልቀው የሚያስታውሱት የትኛዎን ባርነት ይሆን እያልኩ አሰብኩ። እዚያው አሜሪካ ተወልደው ያደጉት ልጆች እንኳን ይህንን ቢያድረጉ እሺ፣ ከኢትዮጵያ የመጣው፣ ያውም ነፍሰ ካወቀ በኋላ የመጣው ጎልማሳ እንደዚያ አድርጎ ሲሄድ ማየት ግን አስቂኝም አናዳጅም ስሜት ይፈጥራል። ከዚያም አልፎ ገና ከአገራቸው ሳይወጡ ይህንኑ “ሰንሰለት አጥላቂነት” የሚለማመዱ ወጣቶችን ማየትም እንደዚያው

የሰንሰለቱ ብቻ ሳይሆን የመኪና አነዳዱንም፣ ሙዚቃ እያንባረቁ መሔዱንም ኮፒ አድርገናቸዋል። አፍሪካዊ-አሜሪካውያኑ መኪናዎቻቸው በሚያወጡት አካባቢ የሚያናውጥ ሙዚቃ ይታወቃሉ። የእኛዎቹም እንደዚያው ያደርጋሉ። በተለይ አርብ ማታ ጀምሮ ባሉት የሳምንት መጨረሻ ቀናት። ልዩነታቸው እነዚያ እንግሊዝኛ፣ እኛዎቹ ደግሞ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ ወይም አንዱን ኢትዮጵያዊ ዘፈን መክፈታቸው ነው። የሚገርመው ወደዚህ የባህል መንሸራተት የምንሔደው እኛ ኢትዮጵያውያኑ እና ኤርትራውያኑ ነን እንጂ ጎረቤቶቻችን ሱዳኖች እና ሶማሌዎች እንደዚያ አያደርጉም። ባህላቸውን ይጠብቃሉ።

ባህላችንን እና ማንነታችንን የመውደዳችን ያህል ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት አናሳ ስለሆነ ይመስላል ልጆቻችን በፍጥነት እየጣሉት ነው። በቁጥር በርካታ በሆንባቸው አካባቢዎች ሳይቀር የመሰማታችን ደረጃ በቁጥር ከእኛ ከሚያንሱት ጋር ሲነጻጸር በጣም አናሳ ሆኖ እናገኘዋለን። በመነሻዬ እንዳልኩት “አካባቢን” ያለማወቅ እና ያለመጠቀም ችግር ያመጣብን ተባብሮ፣ ተከባብሮ፣ ለአንድ ግብ የመሥራት እጥረት ነው። በግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠር የኛ ሰው ኢኖርበታል በሚባለው “ዲሲ እና አካባቢው እስካሁን ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ለመንግሥት የሥልጣን ወንበር ሲወዳደር አላየኹም፣ ወይም አልሰማኹም። በብዛት ኢትዮጵያዊው የተረባረበበት የፖለቲካ ጉዳይ የኦባማ ምርጫ የሚሆን ይመስለኛል። ጥሩ ውጤትም አግኝተውበታል።

ሲጠቃለል፤ ከሩቅ አጀንዳ ይልቅ የቅርቡን፤ ከውጪው ጉዳይ ይልቅ የራሳችንን፣ ከሩቁ ዕውቀት በፊት የቅርባችንን፣ ከነዚያ በፊት የእኛን የምንይዝበት መንገድ መቀየስ ያስፈልገናል። ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ሳንሆን፣ መጀመሪያ የመቀመጫዬን እንዳለችዋ የራሳችንን ሕይወት የሚለውጠውን ነገር አውቀን፣ የጎደለውን ብንጠይቅ በእርግጥም የአሜሪካዎቹ የአካባቢ ሬዲዮና ቲቪዎች ትኩረት ያገኙበትን ምክንያት በቅጡ እንረዳዋለን።

 © ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ . የተወሰነ የግ. በሚታተመውአዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። ነውር ነው።

5 comments:

Anonymous said...

Very true Ayate......ቅድሚያ ለራስ.........መጀመሪያ ለራሱ የሆነ ሰው ለሌላው ይተርፋል፡፡

Anonymous said...

masetawale yesetane

Anonymous said...

Dn ephereme even if you are away from your blog for weeks but it is ok now i am satisfied by this reading, you touch me and thanks God your talent show us most of ethiopians personality which is very hurt and we always think about what is gonne be the next generation?

Anonymous said...

አዎ ቅዲሚያ ለራስ! እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። የራሴን ትግርታዊ የሆኑ መጽሐፍት ነገር ግን የተጻፉበትን ቋንቋ ምንም በማላውቀው ምክንያት እንዳላውቅ ተደርጌ የተለየዃቸውን ማንበብ ስጀምር ያኔ ብዙ ምስጢር ይገለጽልኛል። ማንነቴንም አውቄ ራሴን ለስራ እንዳዘጋጅ ይረዱኛል። ጊዜዬን በሙሉ በእነሱ ቅኝት ያጠፋሁበትን ምክንያት የማወቅ እድሉም ይኖረኛል። በእኔ የደረሰ በሌሎች እንዳይደርስ ስልት ለመቀየስም የሚያስችል እውቀት አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ። እናም ቅድሚያ ለራስ፣ቅድሚያ ወደራስ--ያኔ የተደበቀብን ቁልፍ ከፍቶ ቢቀዱት የማያልቀው እውቀት በትውልዱ አእምሮ ለመሙላት የሚያስችል ነገር ይቀዳ ይሆናል። ማን ያውቃል!!!!

Anonymous said...

betam zegyet biye banebewm bzu endasib reditognal. Ahun ahun enem yemichenekibachew negeroch bemehonachew yeliben yenegerkegn yahil new yetesemagn,

Efrem kehager wuchi lemiweledu lijochachin ahun egnaw yalawekinewn man yasawikachew bileh tasibaleh? Israelawiyan be Gibts midr eyalu hulum yerasachewn silemiyawku lelijochachew yastemru neber, egna gin yanewnum yewuchiwn enji yerasachinin alitechaninm ena ahun lelijochachin min enadrig? eski asibibet? biyanse yetarik mahider aynet blog akim yalew bikefitilin ena lijochachinin binastemiribet.Ahun betikitu be teleyayu electronics media keminagegnachew techemari malet new.
lantem Egz. yirdah.