Wednesday, January 7, 2015

“ፊደል የቆጠሩ ማይሞች - Functionally Illiterates”

(Originally published on 6/27/11)
ገና ለአሜሪካ አገር ባዳ፣ ለሰዉ እንግዳ በነበርኩበት ዓመት የዋሺንግተን ከተማ ትምህርት ቢሮ ይፋ ባደረገው እና ስለ ነዋሪው ማይምነት ባደረገው ጥናቱ በከተማይቱ ካሉት ነዋሪዎች መካከል በዋነኝነት ስፓኒሾች እና ኢትዮጵያውያንን ጠቅሶ ስመለከት እንደ መደንገጥ አደርጎኝ ነበር። “እንዴ፤ በዲቪ የሚመጣው ይኼ ሁሉ ሕዝብ ቢያንስ 12ኛ ክፍል የጨረሰም አይዶል? ታዲያ በየት በኩል ማይም ሆኖ ተገኘ” ብዬ ትንሽ አርበኝነት ቢጤ ውስጤ ሲንፈራፈር ተሰምቶኝም ነበር።


በ2007 ይፋ የተደረገው ይህ ጥናት በአገር አቀፍ ደረጃ አሜሪካ ያላትን የተማረ የሰው ኃይል እና ሥራ ላይ በተግባር በመዋል ረገድ ያለውን ክፍተት ለማወቅ የተደረገ ሲሆን በተለይም የአገሪቱ ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲ ያለችበትን ሁኔታም ያመላከተ ነበር። ውጤቱ እንደሚያመለክተው ከከተማይቱ ነዋሪ አንድ ሦስተኛው ሕዝብ፣ በእነርሱ አነጋገር፣ “functionally illiterate” (ፊደል የቆጠረ ማይም) ነው።

ይኼ “Functional illiteracy” የተባለውን ነገር በግርድፉ ስተረጉመው “ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ማይም መሆን” ማለት ሲሆን ከምናውቀው “ማንበብ እና መጻፍ አለመቻል” (ወገበ ነጭ ማይም እንዲሉ) የተለየ ነው። ልዩነቱ ማይም ሰዎች ማንበብም፣ መጻፍም ምንም ምን የማይችሉ ሲሆን በአገራችን በጣታቸው የሚፈርሙ ዓይነት ሰዎችን የተመለከተ ነው። Functional illiteracy ግን ፊደል ከቆጠሩ፣ ማንበብ እና መጻፍ ከቻሉ በኋላ ተግባራዊ የሥራ መስክ ላይ ከአንድ የተማረ ሰው የሚገባውን ዓይነት ዕውቀት ይዞ አለመገኘት ነው።

ለምሳሌ “ነጭ-ማይም” የሆነ ሰው የፊደል ገበታ ተዘርግቶ ቢመለከት ፊደሎቹ መልሰው ያዩታል እንጂ አንዷን ከአንዷ ለይቶ አያውቃትም። “ሀ”ን ከ“ለ” በጭራሽ አይለይም። ሁሉም ፊደሎች ግራ ይሆኑበታል። ስሙን መጻፍ አይችልም። በሌላ በኩል ፊደል-ቆጠሩ-ማይም ማንበብም መጻፍም ይችላል። ነገር ግን “የሥራ ማስታወቂያዎችን በቅጡ አንብቦ ምንነታቸውን አይረዳም፣ ማንኛውንም ዓይነት ማስታወቂያ ተመልክቶ ምንነታቸውን አያውቅም፣ ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን ተመልክቶ ጭብጣቸውን ገንዘብ አያደርግም፣ የትራፊክ ምልክቶችን፣ የባንክ ወረቀቶችን እና ፖስተሮችን አይቶ የሚፈለግበትን አይፈጽምም” እንደማለት ነው።

በዲሲው ጥናት ላይ እንደተጠቆመው ከተማይቱ ብዙ ፊደል የቆጠሩ እንደዚህ ዓይነት ማይሞች ሊኖሯት የቻሉት በተለያዩ ምክንያቶች የመጡ እና እንግሊዝኛ የማይናገሩ ስፓኒሾች እና ኢትዮጵያውያን እየበዙ በመሔዳቸው ጭምር ነው። ስፓኒሾች (Hispanics) የተባሉት ከደቡብ አሜሪካ የተለያዩ የእስፓኝ/ ስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ድንበር ጥሰው የሚገቡት እና ጆሯቸውን ቢቆርጧቸው እንኳን እንግሊዝኛ መስማት የማይችሉትን ሕዝቦች ለማለት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያኑ የተጨመርነው ከዚህ ዝርዝር ውስጥ ነው ማለት ነው።  

ስለ ጥናቱ ጋዜጣ ላይ ካነበብኩ በኋላ ለመቀበል ብዙ ተቸግሬያለኹ። ምናልባት “የነዚህ ተንኮለኛ ፈረንጆች ዘረኝነትስ ቢሆን” የሚል ሐሳብም ሳይመጣብኝ አልቀረም። አንድ 12ኛ ክፍል ጨርሾ የመጣ ኢትዮጵያዊ እንዴት ግራና ቀኙን ከማይለይ ስፓኒሽ ጋር ሊደመር ቻለ ብዬ ማውጣቴ ማውረዴም አልቀረም። ወዲያው ግን ራሴንም ሌሎች የማውቃቸው ሰዎችንም ሁኔታ ስመለከት በእርግጥም ችግር እንዳለ ተረዳኹ። በምሳሌ ላስረዳ።

ለምሳሌ እንደ ዲሲ ያለ በአንድ ዘመናዊ ከተማ ውስጥ ያለ አድራሻን ለማግኘት እንሞክር። አድራውን አግኝቶ ከተፈለገው ቦታ ለመድረስ የመንገድ ስሞች በቅጡ ማንበብ፣ ትራንስፖርት በትክክል መጠቀም፣ ካርታ ማንበብ ይጠይቃል። በሰለጠነው ዓለም ያለ ማንኛውም ሰው ይህንን ማድረግ ይችላል። ሕጻናቱ ሳይቀሩ ይህንን ያውቃሉ። ለእኛ ለመጤዎቹ ግን እንዲህ ቀላል አይደለም። የራሴን እማኝነት ላቅርብ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ የሔድኩት ለአንድ ወር ስብሰባ መሰል ዝግጅት ነበር። ከአገሬ ስወጣ የመጀመሪያዬ ነበር። ተቀብለው ያስተናገዱኝ ሰዎች ለራሳቸውም ሥራ መሔድ ስለነበረባቸው ስወጣ ስገባ እንዳልቸገር የከተማውን ካርታ ሰጥተው ሸኙኝ። ካርታውን ባየው ያየኛል። በእርግጥ “ማፕ ሪዲንግ/ ካርታ ማንበብ” የሚባል ትምህርት ዘጠነኛ ክፍል ጂኦግራፊ ላይ ተምሬ ነበር።

ያ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርት እንዲህ ላለው ጊዜ ይጠቅም ነበር? አስተማሪው አክብዶት ይሁን ወይም እኔ ደድቤ፣ ባላውቅም፣ ትምህርቱ ያኔም አልገባኝም ነበር። እዚህ ሕጻናቱ ራሳቸው የሚያውቁትን ተራ ነገር እንደ “ሮኬት ሳይንስ” አርቅቆ ሳያስተምረን አልቀረም ሰውየው። ብቻ ያቺን ካርታ ማንበብ አቃተኝ።

ካርታውን በእጄ ይዤ፣ የተባልኩትን ባቡር ይዤ አንድ ፌርማታ ላይ ወረድኩ እና የምፈልገው ሰፈር ደረስኩ። ከዚህ ወደተባለው ቤት ለመግባት አንድ ምልክት ነገር ካርታው ላይ ተስሏል። ምልክቱ የባቡር መንገድን የሚያመለክት እንጂ እኔ ከፈለግኹት ጋር የሚገናኝ አልነበረም። በወቅቱ ግን ትልቅ ምሥጢር ሆነችብኝ። “ጠርብ ማይም” ሆንኩ ማለትም አይደል? ከዚህ በላይ ማይምነትስ ምን አለ? ብቻ በዚህም በዚያም ብዬ፣ ቦታውን አገኘኹትና ምልክቱ የባቡር መሆኑንም አውቄ በራሴ ሳቅኹ። በዚህ መልክ ስመለከተው ፈረንጅ አገር ለመኖር መጥተን ነገር ግን አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮችን ባለማወቃችን “ማይም” ከሚለው ተርታ ውስጥ ልንገባ ችለናል ማለት ነው ብዬ ወሰድኩት። 

የፈረንጅ አገሩን ትተን ወዳገራችንም ብንመለስ ፊደል መቁጠር ሁሉ “የተማረ” እንደማያደርግ/ እንደማያስብል ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ የትራፊክ ምልክቶችን፣ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ማስታወቂያ ተመልክቶ በተባለው መሠረት አለመፈጸም “ፊደል-ቆጠር-ማይም” መሆን ነው። ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ያለ ምንም ሥርዓት አስከባሪ ሥርዓት ይዞ አለመገኘትም እንዲሁ።

በዚህ በምንኖርበት ዓለም ማንኛውንም አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ሰዎች ከፊታቸው የቀደመ ሰው ካለ በምንም መልኩ ቢሆን ቀድመው አይሄዱም። በጎን መሹለክ፣ ተራን አለመጠበቅ፣ ከፊት ያለ ሰውን ከመጤፍ አለመቁጠር፣ አንድ መስመር በመያዝ ምትክ እጅብ ብሎ ለአስተናጋጅ ማስቸገር የሚባል ነገር የለም። ይህ ዕውቀት ነው። አለማድረግ ደግሞ ማይምነት።

እኛ ኢትዮጵያውያኑ እዚህ አሜሪካ መጥተንም የማንተወውን ነገር ልንገራችሁ። ብዙ ጊዜ የማዘወትረው አንድ የኢትዮጵያ ቡና መሸጫ ቤት አለ። ቡና ፍለጋ በሄድኩ ቁጥር አስተናጋጆቹ እንደማንኛውም ቦታ ሊያቀርቡት የሚገባውን ነገር የራሳቸው ሰው ከሆነ የመቀነስ ጠባይ አለባቸው። ለምሳሌ ቡናውን የምንጠጣበት ካርቶን መሰል መጠጫ እንዳያቃጥለን አብሮ የሚሰጥ ወፍራም መጨበጫ አለው። እርሱ ከሌለ ትኩሱ ቡና በመያዣው ዘልቆ ያቃጥላል።

እና ይህ የኛው ሰው ንግድ ቤት ቡናውን ይሰጥ እና መያዣውን ይከለክላል። የትም ቦታ አይደረግም። እንዲሰጡን ከፈለግን መጠየቅ አለብን። ያንን ባለመስጠታቸው ምን ያህል ሳንቲም እንደሚያተርፉ እግዜር ይወቅ። ነገር ግን ደንበኛቸው የከፈለው ለዚያች ወረቀትም ጭምር ነው። ፈረንጅ ወይም የውጪ ሰው ከሆነ ሳይጠይቅ ሁሉን ነገር ያደርጉለታል። የራሳቸው ሰው ከሆነ ግን ሊያገኝ የሚገባውንም ነገር ይቀንሱበታል። ሌላ ማይምነት።

ቤተ ክርስቲያን ስትሔዱ፣ ምናልባት መቀመጫ በሚጣበብባቸው እንደ ትንሣኤ እና ገና ባሉ በዓላት ወቅት አንዱ ሰው ሦስት አራት ወንበር ላይ ዕቃውን ያስቀምጥና ገና ከሁለት እና ከሦስት ሰዓት በኋላ ለሚመጣ ወዳጁ ቦታ ይይዛል። ቀድሞ የመጣው ቆሞ ባዶ ወንበር ለሌሎች ይቀመጣል። እንዲህ የሚያደርገው ያ ሰው ሌላ ቦታ ቢሆን ግን እንደዚያ አያደርግም። የራሱ ወገን ላይ ሲሆን መብቱን ከልክሎ፣ ሊያገኝ የሚገባውን ነገር ይነሣዋል። ሌላ ማይምነት።

የሌላውን መብት ማክበር እና የራስንም ቢሆን አለማስነካት ትልቅ ዕውቀት ነው። የራስን መብት እያስገፈፉ ዕድሉ ሲገኝ የሌላውን መብት አለማክበር ትልቅ ማይምነት ነው። በዕለት ተዕለት ኑሯችን አንድኛችን የሌላውን መብት መጋፋት ስለለመድን ባሕር ተሻግረን በሄድንበት አገር ሳይቀር የራሳችንን ሰው የሚጎዳ ነገር እንፈጽማለን። ፊደል የቆጠሩ ማይሞች ብንሆን አይደል?

በየመስኩ እና በየኑሮው ሜዳ ጠለቅ ብለን ብንመለከት ልንታዘባቸው የምንችላቸው ብዙ ጉድፎች አሉ። መማር ማለት መለወጥ ከሆነ፣ ኑሮን ለማሻሻል እና በዕለት ተዕለት ኑሮ የሚጠቅም ነገር ለማግኘት ከሆነ፣ አለመማራችንንና ዕውቀተ ጎዶሎ “ፊደል-ቆጠር-ማይም” መሆናችንን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ።

ይቆየን
6/27/11 6:36 AM
Pacific Standard Time
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ . የተወሰነ የግ. በሚታተመውአዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። ነውር ነው።

14 comments:

Anonymous said...

ዲ. ኤፍሬም በጣም አስተማሪ ምልከታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡ መቼም በጽሑፍህ መዝጊያ ላይ ያለችው “ይቆየን” ቀጣይ ክፍል ዕንድንጠብቅ አመላካጭ ከሆነች እሰየው ብያለሁ፡፡ የጽሑፍህን መጠናቀቅ የምታረዳን ከሆነች ግን በጽኑ እቃዎም ዘንድ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ብዙ ምሳሌዎችና አስተማሪ ገጠመገኖች ልትጨምርልን ትችላለህና፡፡ እናም ቀጣዩን ክፍል በጉጉት እጠባበቃለሁ፡፡

Anonymous said...

nice!!

Anonymous said...

አግዚአብሔር ይስጥልን ዲ/ን ኤፍሬም። ብዙ ማለት የቻላል በዚ ጉዳይ ላይ ። አኔን የገጠመኝን ልንገርህ ካገር ቤት አንደመጣሁ አገር ቤት ያው ከሰው ጋር አንደከብት አየተገፋፉ መሄድ ለምጄ አዚም አንደመጣሁ በመንገዱ መሃል ላይ ነበር የምሄደው። የተቀበለኝ የዚህ ሀገር ዜጋ ነበር አና ቀስ ብሎ ይህ ሕዝብ በብዛት የሚሄድበት ቦታ ስለሆነ ቀኝሽን ይዘሽ ሕጂ አለኝ። ወይ ጉድ በጣም ቀላል የሆነን ነገር ካለማድረግ የሚመጣውን ትርምስ አሰብኩኝ ከሰባት ዓመት በውሃላ አንደገና አገርቤት ስሄድ ነገሩ ሁሉ ብሶበት አየው።
ዲ/ን በዚ ጉዳይ ብዙ ነገር ማስተማር ትችላለህ። አናንተን የመሰለ መካሪ የሰጠን አምላክ ይመስገን!

Anonymous said...

አይይይ ይቆየን!!!!!!! እስከመቸ ይሆን ?

Anonymous said...

እና ኤፍሬም አሜሪካ ማሀይሞች አለቻችሁ ነው የምትለን? ወይ ነዶ!!! እስኪ ጐበዝ ከሆነች በአማርኛ ትሞክረን!!!

Anonymous said...

መቸም እንግሊዘኛ አለመናገር መሀይምነት አይደለም ችግሩ በህግ አለመመራት እንጅ ብዙ ትምህርቶችን እጠብቃለሁ

ኃ/ገብርኤል ከአራት ኪሎ said...

ዲ/ን ኤፍሬም በጣም ጥሩ ምልከታ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ፀጋውን ያብዛልህ። አንዳንዴ እንደው ስመለከተው በተለይ ለህግ መገዛትን እንደ አላዋቂነት የምንወስድ ሰዎች ቁጥራችን ለቁጥር አዳጋች ነው። አታድርጉ ስንባል ፈጥኖ የሚታየን ባለማድረጋችን የሚመጣውን መልካም ነገር ሳይሆን ትዕዛዙን በመፈፀማችን ከሰው በታች የሆንን በመሆኑ ትዕዛዙን ላለመፈፀም እልህ የሚይዘን ይመስለኛል። እዚህ ሀገር ቤት አንድ ሰሞን እግረኞች በእግረኛ ማቋረጫ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚያሰገድድ እንቅስቃሴ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በፖሊሶች እና በፌደራል ወታደሮች ጭምር ቁጥጥር ተጀምሮ ነበር። ለአንድ ሳምንት ያህል ጥሩ ነገር መታየት ጀመረልህና ወዲያውኑ የኛ ሰው ወታደርቹ ሲኖሩ በዜብራው ላይ ይሻገራል ከሌሉ ግን እደፈለገው ማድረጉን ጀመረ። በተለይ አሁን አሁንማ በጣም አሪፍ እየሆነ ነው እንዴት አትለኝም ሰዉ በመሐል አስፋልት ላይ መኪኖቹ ደግሞ በዜብራ ላይ መሻገር ጀምረዋላ!!!!!
ዲ/ን ኤፍሬም በተለይ አንተ ባለህበት አካባቢ ህፃናቱ ጭምር አቀላጥፈው የሚያደርጉትን እኛ እንቸገርበታለን ብለሃል ግን እንዴት? እውቀቱን ከየት አገኙት? መቼም ከፍጥረታቸው ነው እንዳትለኝ። ከትምህርት ቤት ነው ወይስ በወላጆቻቸው? ዋናው ነገር ይሔ ይመስለኛል ምክንያቱም ጎዶሏችን ምንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናልና።
ቸር ያሰማን።

Anonymous said...

ኤፍሬም የታዘብካቸው ነግሮችን እኔም በጣም እጋራሃለሁ:: ከሃበሻ እርር ድብን ከሚያደርጉኝ ፀባዮች ውስጥ እነዚሁ ይገኙበታል:: እንዳዴ ታውቃለህ ምነው እዚህ መጥተው እንኳ ነጮቹ ከሚያደርጉት ነገር የሚጠቅመውን መማር ቢጀምሩ እላለሁ:: በአንፃሩ እኮ ደግሞ ሌሎችን የማይረቡ ነገሮች ለመማር ቁጥር አንድ ሃበሻ ነው:: ወደ ጥናቱ ስመለስ ተዋቸው እነዚህ ነጫጭባዎች እኛን ዝቅ ማድረግ ስለሚወዱ ነው:: ከአፍሪካ የመጣ ሁሉ ምንም የሚያውቅ አይመስላቸውም:: የእኛን ማወቅ እና አለማወቅ የሚመዝኑት በእነሱ ባህልና ነባራዊ እውነታዎች ነው:: እነሱ የሚያውቁት ነገር እኮ ከአካባቢያቸው ያገኙትን በተደጋጋሚ የሚያዩትን የሚጠቀሙበትን በመገናኛ ብዙሃን የሚሰሙትንና የሚማሩት ከልምድ ከተገኘ እውቀት እንጂ ጅኒዬስ ሆነው አይደልም:: በርግጥ የተወሰኑ በጣም ጎበዝ አሉ:: ያም ቢሆን ግን ከአደገ አገር ማደጋቸው ብዙ ነገር ለማወቃቸው ከፍተኛ ሚና አለው:: ሌላው ቀርቶ collage algebra ለማለፍ ሶስት ጊዜ ደጋግመው የሚማሩ ሰዎች እኛን ማህይም ቢሉ አመድ በዱቄት ነው የሚሆነው::
ደግሞ የአንተ ካርታ ለማንበብ ግራ መጋባትም ቢሆን መሃይምነት አይደለም:: እኛ እኮ ኢትዮዽያ ካርታ አንጠቀምም:: እንደዚህ አይነቶችን በሂደት ስንኖርበት የምንማራቸው ናቸው:: አንተ ወዲያዉኑ እንደተማርከው ማለት ነው:: እዚህ ያሉትን ነጮችን "functionally illiterate" ያልተባሉትን እንኳ ብትጠይቅ ካርታ ማንበብ የማያውቅ አለ:: እኛ ምነው የእግርና የታክሲ መንገዱን ኢትዮዽያ ውስጥ አሳምረን እንነግራቸዋለን አይደል::

Anonymous said...

ግሩም ነዉ ኤፍርም
የኔ ማህበርተኛ ካልሆንክ ቡዳ ነህ የሚለዉን ምን
ትለዋለህ ??????

Anonymous said...

Ye America habesha mikir yasfelgewalna, endante ayte makeri asfelagi newu. berta

Alem Tessema said...

Ephi, endet new yenegeriken! Ewinetim mayimenet!...

Anonymous said...

A great view Dn. Ephrem. Thank you for sharing us your views. I hope we will behave our selves.

Anonymous said...

ህዝቦች በእድገት ወደፊት ሊሄዱ የሚችሉት ተመሳሳይ ግብ ሲኖራቸው ነው፡፡ለዚህ ደግሞ በጋራ የሚስማሙበትን ስርዓት ማክበር ለጋራ ብልፅግና መስራት ሲችሉ ነው፡፡
እኛ ጋ ከ ኢትዮጵያዊ ዘር ተለይቶ ፣ጓደኛ ተመርጦ፣ መንደር ተመሳስሎ ፣ ቤተሰብ ይህ ካልሆነም በግል በእጅመንሻ ህግም የመስሪያ ቤት ህግ ይደፈራል ፣ የሀገር ህግ ይጣሳል፣ እያንዳንዱ በግሉ በአቐራጭ ያድጋል ፣ ይህም በቤተሰቡ አባላት በአካባቢው ህብረተሰብ ይወደሳል፡፡ ንቁ ፣ ቀልጣፋ ተብሎ ሌብነቱ ይሸፋፈንል፡፡ ይህ መንገድ አዋጭ መሆኑ ስለታመነበት ትውልዱ ሁሉ ወደ አቐራጭ ተሟል፡፡

Anonymous said...

አውነት ነው፤ መምህር እግዚአብሄር ይጠብቅህ..