Saturday, July 30, 2011

እርግና እና እርጅና ….

በዚህ በፈረንጁ አገር በስደት ያለነው ወጣቶቹና ጎልማሶቹ እንዲሁም ልጆቻችን ብቻ አይደሉም። ብዙ ዕድሜ የጠገቡ አረጋውያንና አረጋውያትም ተሰድደዋል። በተለይም እንደ ዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ባለ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ነጠላ ለብሰው ወዲያ ወዲህ የሚሉ እናቶችን፣ ከዘራ ቢጤ ጨብጠው በአባታዊ ግርማ ሞገስ በቀስታ የሚራመዱ ኢትዮጵያዊ አባቶችን ማየት የተለመደ ነው።

እነዚህ አረጋውያን ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ ወደ አሜሪካ ይመጣሉ። ገሚሶቹ በልጆቻቸው ግብዣ፣ ለሰርግ ወይም ለምርቃት፣ እንዲያው ለመጠየቅ ወይም የሚወልዱ ልጆቻቸውን ለማረስ አሊያም ለሕክምና ወደ አሜሪካ ይገባሉ። ታዲያ በአሜሪካ ያለ አረጋዊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲህ ተጋብዞ እና ተጠይቆ የመጣ ነው ማለት አይቻለም። በወጣትነት እና በጎልማስነት ዕድሜያቸው መጥተው፣ 30 እና 40 ዓመታትን ኖረው፣ አሁን ወደ እርግናው የገቡም ብዙ ብዙ ናቸው።

ፈረንጅ አገር ሲያረጁበት ደስ አይልም። በወጣትነት፣ በለጋነት፣ “አስረሽ ምቺው” በሚባልበት ዕድሜ እንጂ አቃፊ ደጋፊ በሚያስፈልግበት፣ ተመልካች ጎብኚ በሚሻበት ወቅት ፈረንጅ አገር አያስመኝም።

በፈረንጁ አገር እርግና እና እርጅና ብዙም አይወደዱም። ማስታወቂያው ሁሉ የሚናገረው እርጅና እንዳያስታውቅ ቆዳን በተለያዩ ቅባቶች ስለመደለል፣ የ50 እና የ60 ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ የ30 ዓመት ወጣት ስለመመምሰል ወዘተ ወዘተ ነው። አሁንማ “ፕላስቲክ ሰርጀሪ/ ቀዶ ጥገና” ስለተስፋፋ በተለይም ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ፊታቸውን እያስወጠሩ አሻንጉሊት መምሰል ጀምረዋል።

ፕላስቲክ ሰርጀሪ ስለተፈጸመላቸው የሆሊ ዉድ አክተሮች/አክትረሶች የሚታየው አንዳንዱ ይዘገንናል። ሲያጌጡ ይመላለጡ አለ ያገሬ ሰው። እርጅናን ሽሽት ብዙ ነገር ይፈጸማል።

እርጅና እንዲህ ቢሸሹትም የማያመልጡት ነው። አሜሪካ ደግሞ ሕጉ ለአረጋውያን ጥብቅና ይቆማል። ሕጉን ሲመለከቱት ደግሞ “ካረጁ አይቀር እዚህ ነው” ያሰኛል። “ሲኒየርስ” ይሏቸዋል። “ታላላቆች፣ አንጋፎች” እንደማለት ነው። እርጅናን ከእርግና፣ ከብስለት፣ ከትልቅነት ጋር ስለሚያያይዙት ደስ ይሉኛል።

እነዚህ “ሲኒየርስ” የተባሉ አረጋውያን በወጣትነት ዘመናቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች ለአገራቸው ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ መሆናቸውን ሕጋቸው ስለተቀበለ አጠቃላይ አገሪቱ እነርሱን ለመንከባከብ የሚያስል ብዙ ተቋም/ ፋሲሊቲ አላት።

አውቶቡስ ውስጥ ስትገቡ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ መቀመጫዎች ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች የተዘጋጁ ናቸው። አረጋዊም ሆነ አካል ጉዳተኛ ያልሆነ ሰው ሊቀመጥባቸው ቢችልም ቅድሚያ መስጠት ያለበት ግን ለእነርሱ ነው። ያለምንም ጥያቄ። አውሮፕላን ውስጥ ለመግባት ሰልፍ ባለበት ቦታ አስተናጋጆች አስቀድመው “አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች ወይም ሕጻናት የያዛችሁ በቅድሚያ ግቡ” ብለው ይጋብዛሉ። እነርሱ ከተስናገዱ በኋላ ነው ሌላው የአዳም ዘር መርመስመስ የሚጀምረው።

በአሜሪካ ያሉ አረጋውያን የሚጦሩባቸው ሁለት መንገዶች አሉ። አንደኛው የሲኒየሮች መኖሪያዎች/ የአረጋውያን መኖሪያዎች ውስጥ መኖር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በየቤታቸው ተቀምጠው የሚንከባከባቸው ሰው መቅጠር ናቸው። ከመጀመሪያው ጀምሬ በመጠኑ ለማብራራት ልሞክር።

አረጋውያን ዜጎች ወደ እርጅናው ዓለም በሚገቡበት ወቅት ብዙው የቤተሰባቸው አባል ራሱን ችሎ ይወጣል። የራሱን ጎጆ ይቀልሳል። ስለዚህ ብዙዎቹ ብቻቸውን ይቀራሉ። የፈረንጅ አገር ልጅ ቤተሰቡን የሚያየው በዓመት ያውም ለ “ታንክስ ጊቪንግ/ በዓለ አኮቴት” እና ለክሪስማስ/ ገና ነው። እርሱም ጎበዝ ልጅ ከሆነ። አለበለዚያ ወላጆች በቅርብ ርዳታ ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ የለም። ስለዚህ ቤት ንብረት ያላቸውም ቢሆኑ ገንዘባቸውን ቋጥረው ሌሎች አረጋውያን ካሉባቸው ማንኛውንም ዓይነት ርዳታ ከሚያገኙበት “የአረጋውያን መኖሪያዎች” (senior house) ይገባሉ።

እነዚህን የአረጋውያን መኖሪያዎች እና ጥራታቸውን ለማወቅ በሕሊናችን “አንድ ንፁሕ ሆቴል” ብንስል ትክክል ይሆናል። ልዩነቱ ነዋሪዎቹ በሙሉ አረጋውያን መሆናቸው ነው። እነዚህ የአረጋውያን መኖሪያዎች ሁሉም ነገር አላቸው። በየቤታቸው ተከርችመው በብቸኝነት እና በጠያቂ ማጣት ሊንገላቱ ይችሉ የነበሩ አረጋውያንን በአንድ  ሥፍራ በማሰባሰብ በስፖርትም፣ በመዝናኛም፣ እርስ በእርስ በመጨዋወትም ሕይወትን እንዲያጣጥሙት ያግዛል። አስፈላጊ በሆነው ጊዜ ሁሉ የሚረዷቸው 24 ሰዓት አብረዋቸው የሚቆዩ ባለሙያዎችም አሉ።

ኢትዮጵያን ከመሳሰሉ አገሮች የምንመጣ ሰዎች ከምንሰማራባቸው እና በአጭር ጊዜ ስልጠና ወደ ሥራ መስክ ለመሰማራት ከምንችልባቸው ዘርፎች አንዱ አረጋውያንን መንከባከብ ነው። በጥቂት ወራት ስልጠና “ሰርተፊኬት” በማግኘት ወደ ሥራው መሰማራት ይቻላል። በዚህ በኩል በተለይ ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች የሚመጡ ሰዎች ተክነውበታል። በዚህ የሥ መስክ የተሰማሩ ወዳጆቼ ኢትዮጵያውያን እንደሚነግሩኝ ከሆነ በአሜሪካ አገር ማርጀት ግዴታ ከሆነ ትልቁ ጥቅሙ ይህንን የመሰለው ነገር ነው።

እርጅና አካል እንደ ወጣትነቱ ዘመን በቀላሉ እንዳይታዘዝ የሚያደርግ የተፈጥሮ አስደናቂ ጊዜ ነው። የታላቁ ደራሲ የመንግሥቱ ለማ አባት አለቃ ለማ ኃይሉ እንዲህ ሲሉ እንዳጫወቱን ማለት ነው። ሰውየው አረጀ። ቁጭ ብሎ ሳለ ሰውነቱ፤ እጁ እግሩ ይጠያየቁ ጀመረ። ‘
ዓይን፣ አንድምን ነህ?’ አሉት እጅና እግር። ‘
አሄሄ፣ ሌሊት በጨለማ ምንገዱን ለይቼ እሄድ የነበረ፣ ዛሬ ፀሐይ መለስ ሲል አልታየኝ አለ’፤
‘እግር እንደምን ነህ?’
‘አዬ! የኔ ነገር ቀርቷል። አቀበቱን ስወጣው ቁልቁለቱን ስወርደውስብር ስብር ስብር እል የነበረ፤ ወንዙን ዘልየ ስሻገር እንደ ቆቅ እሽከረከር የነበረ፤ ዛሬ የቤቴን መድረኩን መሻገር ተሣነኝ -  እወጣለሁ ስል ሰናክለኛል’ አለ እግር።
‘እጅ እንደም ነህ?’
‘አዬ! ወንዙን አሻግሬ እመታ የነበረ፤ ወደፊት እወረውርሃለሁ ያልሁት ወደ ኋላዬ ይወድቅ ጀመረ’ አለ።
‘ጥርስ እንደምን ነህ?’
‘አዬ! ባቄላውን አተሩን ቆሎ ጥሬውን ስበላው፣ ሳደቃቅቀው አጥንቱን የነበረ፤ አሁን ፍትፍቱን ለመብላት ተሣነኝ።
‘ልብሣ እንደምን ነህ?’ አሉት።
‘ኧኸኸ! ወትሮ ከነበርኩበት እድር ከፍ ብዬ ወደ አንገት ጠጋ ብዬ ተቀምጫለሁ’ አለ።
‘ሁሉም አባይ ነው’ አለ ሰውየው። ‘እውነተኛ ልብ ብቻ ነው’። ‘እማያረጅ እማይደክም ልብ ብቻ’’። (መጽሐፈ ትዝታ፤ ገጽ 205)

አረጋዊነት አካል የሚደክምበት፣ ልብ ግን አሁንም በተስፋ እና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሚቆምበት፤ ኑሮ በአዲስ ጣዕም እና በአዲስ ለዛ የሚቀጥልበት ጊዜ ነው። በሰለጠነው ዓለም አረጋዊነት ማለት “ሸክም መሆን” ተደርጎ ስለማይቆጠር ሰው በማርጀቱ ምክንያት ብቻ ከዓለም ተገፍቶ የኑሮ ሸክም ሊጫነውና በመጨረሻ ዘመኑ እያለቀሰ ወደ መቃብር እንዲወርድ አይፈረድበትም። እንዲያውም አረጋውያን በሁሉም በኩል ባላቸው ጥቅም እና በሚደረግላቸው ርዳታ ምክንያት ብዙዎች ጡረታ የሚወጡበትን ጊዜ በጉጉት እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል።

በተለያየ ምክንያት ወደ አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያውያን አረጋውያንም ከዚሁ የአረጋውያን ጥቅም ሲካፈሉ አግኝቻቸዋለሁ። የተሟላ ሕክምና፣ ንፁህ መኖሪያ እና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ የሚደግፋቸው ባለሙያ ባለበት ይኖራሉ። አንዳንዶቹም ልጆቻቸው በአሜሪካ ያሉ በመሆናቸው በየተወሰነው ጊዜ እየሄዱ ይጎበኟቸዋል።

ይሁን እንጂ በተለይ በአረጋዊነት የሚናፈቀው አገር ቤት ይመስለኛል። ቤተ ክርስቲያን መሳለሙ፣ የታመመ መጠየቁ፣ በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ አረጋውያን ጋር ያለፈውን እያነሱ መጨዋወቱ፣ የልጅ ልጆች ሲያድጉ እና ለቁም ነገር ሲበቁ ማየቱ የሚገኘው እዚያው አገር ቤት ነው። ድህነቱ ባይኖር ኖሮ።

“ካረጁ አይበጁ” እንዲሉ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ማርጀት ዋስትና የለውም። ጧሪ ቀባሪ ልጅ ከሌለ በስተቀር። ባለፈ ሕይወታቸው ታፍረውና ተከብረው የኖሩ ሰዎች እርጅና ሲመጣ ያንን ክብራቸው ገፍፎ ወደ ጎዳና ያስወጣቸዋል። የሰው እጅ ያሳያቸዋል። ‘ያዙኝ ደግፉኝ’ ያሰኛቸዋል። አለቃ ለማ እንዲህ አሉ “ከደዌ ሁሉ እሱ ይከፋል፣ እርጅና”።
እርጅና ብቻህን ና፤
ያንተ ተከታዮች ብዙ ናቸውና።”
በእርግጥም የእርጅና ተከታዮቹ ብዙ ናቸው። የበሽታውን ዓይነት ማለታቸው ነው። ነገር ግን በዚህ በምዕራቡ ዓለም ለአረጋውያን የሚያስፈልገውን ነገር በጥንቃቄ ስላዘጋጁ፣ ሕጎቻቸውም ለአረጋውያኑ በሚመቹ መልኩ ስለተሰናዱ ማርጀትን ከበሽተኛነት የሚቆጥረው የለም። እንዲያውም ብዙዎች ጥሩ ጥሩ የሚለብሱት እና በብዛት የሚዝናኑት በዚህ ጊዜ ነው።

እውነቱን ለመናገር በኢትዮጵያ ሕዝቡ አረጋውያንን የሚገፋ ሳይሆን የሚያቅፍ፣ የሚጸየፍ ሳይሆን የሚራራ ከመሆኑም በላይ ልጆች አረጋውያን ወላጆቻቸውን የመጦር ባሕላዊ ግዴታ ስላለባቸውም አረጋዊነት በክብር እንደተያዘ ነው። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ አይሆንም። በሕጎች እና ዘመኑ በሚጠይቃቸው ነገሮችም መደራጀት ያስፈልገዋል። ብዙ ገንዘብ ሳናወጣባቸው ባሉን ነገሮች እነርሱን ልንረዳ እንደምንችል ታውቆ ቢያንስ “ቅድሚያ በመስጠት” እንኳን በዕድሜያቸው ላበረከቱት አስተዋጽ በጎ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

ያለፈውን የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዐቢይ ርእስ “ወደፊት እንዴት እንጦራለን?” የሚለውን ጽሑፍ ሳነብ አንዱም ትዝ ያለኝ ጉዳይ ይህ ነው። ሀብታም ብንሆን ደሃ፣ መልከ መልካሞች ብንሆን አስቀያሚዎች፣ ዘርና ቋንቋ ሳይለይ በሁላችን የሚመጣ እርጅና ነውና ለአረጋውያን የምናደርገውን ነገም ሌሎች ለእኛ እንደሚያደርጉት ማሰብ ያሻዋል። ያደገው የምዕራቡ ዓለም በቴክኖሎጂ ካላደግነው እኛን ከመሰለው አገር የሚለየው አንዱም በዚህ የአረጋውያኑ አያያዝ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። መሠረት ያለው አገር እና ሕዝብ ሕጻናቱን እና አረጋውያኑን በጥንቃቄ ይንከባከባል። “አእምሮ የሌለው ሕዝብ” (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ እንደሚለው) ደግሞ ለአረጋውያኑ ክብር አይሰጥም። እኛስ?

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 

11 comments:

Anonymous said...

efe betam des yilal tebarek

Anonymous said...

dn. Efrem Egziabher yibarkih. Metsihafus yemilew "edmeh bemidr lay endirezmlh Enat ena Abathin akibr " aydel ! yibarkih. Metsihafus yemilew "edmeh bemidr lay endirezmlh Enat ena Abathin akibr " aydel !

Tesfaye G said...

Diacon Eprem,

It is very nice article. God Bless you.

Tesfaye

Anonymous said...

Berta wendeme tiru eyeta new Egziabher yibarke

Anonymous said...

ኤፍሬም ዛሬ ሁሌም ልቤ ውስጥ ያለ ሃሳቤን ገለጽክልኝ፡፡ እኛ ሀገር በየመንገዱ ቁጭ ብለው የሚለምኑ አረጋውያንን ባየሁ ቁጥር አንገቴም ልቤም በሀዘን ይሰበራል፡፡ መቸ ይሆን ……….. እግዚአብሔር ሆይ ባክህን ……………..

Anonymous said...

Nice Article! Keep on writing please!God Bless You!

ዘቢለን ጊዮርጊስ said...

ኤፍሬም መልካም ብለሀል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አረጋውያንን የመጦር ሃላፊነት አለበት ብየ አምናለሁ ምክንያቱ ግልጽ ነው እኛ የነሱ ውጤት ነንና

Anonymous said...

እንዴት ሰነበትክ ዲ. ኤፍሬም?
"ሕጎቻቸውም ለአረጋውያኑ በሚመቹ መልኩ ስለተሰናዱ ማርጀትን ከበሽተኛነት
የሚቆጥረው የለም። እንዲያውም ብዙዎች ጥሩ ጥሩ የሚለብሱት እና በብዛት
የሚዝናኑት በዚህ ጊዜ ነው።" እንዴታ እንጂ። ጡረታቸው እኮ እንኳን እነሱን ሌላውንም ያንቀባርራል። አሁን ተጨመረ እንጂ ብታምኑን ባታምኑም ወንድ አያቴ ሲያርፉ ሴት አያቴ 10 ብር ነበር የምታገኘው። በዚያ ዕድሯን ትከፍል ነበር። እርግጥ ሲገኝ የነበረው የደሞዝ መጠን ንጽጽር ነው ጡራታው። እንደው ልጀ ባይኖራት ኖሮ እንዴት ትኖር ነበር?! አሁን እንኳን መቶ ቤት በገባበት ጊዜ እንዴት ትዘልቅው ነበር ብዬ ሳስብ ይሰቀጥጠኛል። ምክንያቱ አንድ ዳቦ እኮ ዛሬ 1 ብር ነው።
እኛ እኮ የግድ እንደ አሜሪካ መሆን የለብንም። ዲ.ኤፍሬም እንዳለው በነገሮች ሁሉ ለእነርሱ " ቅድሚያ በመስጠት" ልናከብራችው እንችላለን። በመጓጓዛ በኩል የሚታያው ግፊያ እንዴት እንደሚዘገንን ለአዲስ አበቤ መንገር አያሻም። መንግስት ግን በሕግ ለአረጋዊያ ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረግ ይችላል። ምን ዋጋ አለው! የዛሬዎቹ እንኳን ይህንን የመሰለ ሕግ ሊያወጡ በየተገኙበት ትንሽ ትልቁን በማዋረድ ነው የተጠመዱት። ባለፈው 20 ዓመት በዚህ በኩል እንኳን የተናደው ታላላቆቻችንን ያለማከበርና የማዋረድ ባህል በስንት ዓመት እንደምንፈታው እርሱ ነው የሚያውቀው።
በነገራችን ላይ አያቴ "እንኳን መሞት ማርጀት አለ" ትላለች። ከሞት እርጀና ከፍቶ!!!
እስኪ አንድዬ ዕድሜ ከጤና ጋር ሰጥቶ አረጋዊን እንደ ደንብ የሚጦሩበት ሀገር ያሳየን።
ወንድሜ ሰላመ እግዚአብሔር አይለይህ።

Anonymous said...

saydegs ayitalam yibal yele? egna hager yalew lijoch lebetesebachew yalachewn fikr ena meredadat ezi hager yetekaw yaw mengist new malet yichalal. egna balen yebeteseb fikr lay hulunm aregawiyan yemakber ena yemenkebakeb gdeta endalebn biseman tru new.
Egzia bher yistlin D/n Ephrem.

ደቂቀ ጸሃፍት ዘሳን ሆዜ said...

ጤና ይስጥልኝ ዲ/ን ኤፍሬም ግሩም የአግራሞት ቅኝት ነው። የሚገርመው ባገራችን አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ህጻናቱም የዚሁ ችግር ሰለባዎች ናቸው። መንከባብ የሚገባንን የነገ አገር ተረካቢዎች እና ያለፉ አገር አቅኝዎችን አለመንከባከቡ በጎልማሳነት እድሜ ያለውንም ትውልድ ወደፊት የችግሩ ገፈት ቀማሽ አንዲሆን ያደርገዋል። ስለዚህ በዚህ በጎልማሳነት እድሜያችን ያለፍንበትን የህጻንነት፤ መጭውን የእርጅናችንን ጊዜ በማሰብ ሁሉን እድሜ ያማከል የእንክብካቤ ስርአት ልንፈጥር ይገባል። አንድም በረከት አንድም አግባብነት ያለው ፍትሃዊ አሰራር ይሆናል።

Anonymous said...

thank you, our brother