Sunday, August 21, 2011

“ንዴት ማረቅ” (Anger Management)


ዓለም እና ሕይወቷ በሙሉ ፈጣሪ እና አስተዳዳሪ አለው። እንኳን ይህቺ የምንኖርባት ዓለም፣ ሕዋው ከነግሳንግሱ፣ ከረቂቁ ፍረት እስከ ግዙፉ አሰስ ገሰሱ፣ በዓይን ሚታየው እስከማይታየው ድረስ ፈጥሮ የሚገዛው፣ ባለቤት አለው። በዘፈቀደ የመጣ፣ በዘፈቀደ የሚከወን ነገር የለም። የኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት የአስኳላው ትምህርት እግሩን አስረዝሞ ከመግባቱ ከሺህ ዓመታት ጀምሮ ይህንን የፍጥረት ዑደት እና ሥርዓት እያራቀቁ እና እያመሰጠሩ ሲያስተምሩ ኖረዋል፣ ያስተምራሉም። አዲሱ ዘመነኛ የአስኳላ ትውልድ ያጣውና እያጣው ያለው ይህ አገርኛ ፍልስፍና እና ሥነ ተፈጥሮ ከመጻሕፍት ልብ ውስጥ ብቻ ወደሚገኝበት፣ ልክ እንደ ሉሲ ከሙዚ ወይም እንደ አክሱም ሐውልት  ለአንክሮ ለተዘክሮ ብቻ የሚደነቀር ለመሆን በሚፍገመገምበት በዚህ ዘመን ከጥንቱ አስተምህሮ ውስጥ ሁሌም የምፈልገው አንድ ቃለ ምሥጢር አለኝ።

Saturday, August 20, 2011

በረከተ ደብረ ታቦር


ጌታዬ
እንደ ሙሴ አንደበተ ጎልዳፋ ብሆን፤ አንተ አንደበት ሆንከኝ።
እንደ ኤልያስ እኔ ብቻ ለአንተ የቆምኩ መስሎኝ ብታበይ ስለ ብዙዎቹ ወዳጆችህ ብለህ ማርከኝ፤
እንደ ጴጥሮስ ቸኩዬ ወድጄህ ቀድሜ ብከዳህ፤ በንስሐ ዕንባ ተቀበልከኝ፤ አብልጠህ አከበርከኝ፤
እንደ ያዕቆብ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ ቢጸናብኝ፤ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ሰጥተህ ፈወስከኝ፤
እንደ ዮሐንስ ብታፈቅረኝ የእናትህን ጣዕም በአንደበቴ ፍቅሯን በልቤ ሳልክልኝ፤ በአማላጅነቷ ጠበቅኸኝ።

ጌታዬ፦ ስለ ቸርነትህ በደብረ ታቦር ክብርህን የገለጥክላቸው የነዚህ ወዳጆችህ ፀጋ በረከት ይድረሰኝ።
አሜን