Sunday, August 21, 2011

“ንዴት ማረቅ” (Anger Management)


ዓለም እና ሕይወቷ በሙሉ ፈጣሪ እና አስተዳዳሪ አለው። እንኳን ይህቺ የምንኖርባት ዓለም፣ ሕዋው ከነግሳንግሱ፣ ከረቂቁ ፍረት እስከ ግዙፉ አሰስ ገሰሱ፣ በዓይን ሚታየው እስከማይታየው ድረስ ፈጥሮ የሚገዛው፣ ባለቤት አለው። በዘፈቀደ የመጣ፣ በዘፈቀደ የሚከወን ነገር የለም። የኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት የአስኳላው ትምህርት እግሩን አስረዝሞ ከመግባቱ ከሺህ ዓመታት ጀምሮ ይህንን የፍጥረት ዑደት እና ሥርዓት እያራቀቁ እና እያመሰጠሩ ሲያስተምሩ ኖረዋል፣ ያስተምራሉም። አዲሱ ዘመነኛ የአስኳላ ትውልድ ያጣውና እያጣው ያለው ይህ አገርኛ ፍልስፍና እና ሥነ ተፈጥሮ ከመጻሕፍት ልብ ውስጥ ብቻ ወደሚገኝበት፣ ልክ እንደ ሉሲ ከሙዚ ወይም እንደ አክሱም ሐውልት  ለአንክሮ ለተዘክሮ ብቻ የሚደነቀር ለመሆን በሚፍገመገምበት በዚህ ዘመን ከጥንቱ አስተምህሮ ውስጥ ሁሌም የምፈልገው አንድ ቃለ ምሥጢር አለኝ።


አጠቃላይ ዓለም አስተዳደር ይፈልጋል። ያለ አስተዳደር የተረጋጋ ሕይወት ማግኘት ከባድ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንኳን “ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል (1ኛ. ቆሮንቶስ 14፡40)። የሕዝብ አስተዳደር የሚባለው “መንግሥት” ባይኖር፣ ሰው ሁሉ የሚቀበለው የአካባቢ አስተዳደር ባይገኝ ሌላው ቀርቶ አንድን ቤተሰብ የሚያረጋ/ የሚያረጋጋ የቤተሰብ ሥርዓት ቢጠፋ ሕይወት እንዴት ውጥንቅጧ እንደሚወጣ ለመገመት ከባድ አይሆንም። በሰለጠነው ዓለም ብቻ ሳይሆን ሰዎች በቁጥር በዛ ብለው በሚኖሩባቸው መንደሮችም ቢሆን ከተማውና መንደሩ የሚቀበለው የሰው ሕይወት፣ የመኪኖች አጓጓዝ ሥርዓት ቢጠፋ የዕለት ተዕለት ኑሮ እጅግ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው።

ምዕራባውያኑም በየዘመናቸው እና በየፍልስፍናቸው እንዲሁም ሥልጣኔያቸው የሚራቀቁበት ብዙ የዕውቀት ምጥቀት ቢኖራቸውም አንዳንዱ በመገረም እና በቃለ አድናቆት የሚታለፍ አንዳንዱ ደግሞ አስገርሞ የሚያፈግግ ይሆናል። በሁለተኛው ረድፍ ከምጠቅሳቸው ነገሮች መካከል በአማርኛ “የንዴት ማረቂያ ዘዴ” ብዬ የተረጎምኩት “Anger Managment” አንዱ ነው። “ንዴት ማረቅ(ረ ይጠብቃል) የሚባ ነገር ከሐሳቡ ጀምሮ ግርምት ፈጥሮብኛል።

የዛሬ ስድስት ወር ገደማ እዚህ አሜሪካ ውስጥ ቁንጮ ዜና ሆኖ የቀረበ ክሪስ ብራውን የሚባል የአንድ ኮከብ ዘፋኝ ጉዳይ ነበር። ዘፋኙ የሴት ጓደኛው ላይ አካላዊ ጉዳት በማድረስ የተከሰሰ ሲሆን በመጨረሻ የተቀጣው ቅጣት “ንዴት ማረቂያ” ቦታ እንዲገባ መደረጉ ነበር። ለካስ የዘፋኙ ችግር ብልጭ ሲልበት የሚያደርገውን አለማወቁ ኖሯል። “ንዴቱን ማረቅ/ መግራት” አለመቻል ሊባል ይችላል።  

ይኼ ሞገደኛ ዘፋኝ ቃለ ምልልስ ሊሰጥበት ከገባበት ከኤ.ቢ.ሲ ቴሌቪዥን (ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ ፕሮግራም) በንዴት ጨርቁን ጥሎ ሲወጣ የቴሌቪዥን ጣቢያውን አብረቅራቂ የመስተዋት ግድግዳ አርግፎት ሄዷል። በዚህም ምክንያት በፊት ተጥሎበት የነበረው “የንዴት ማረቅ” ቅጣት ተጨምሮበታል። ከቴሌቪዥኑ ፕሮግራም እንዲያ ጨርቁን ያስጣለው የጋዜጠኛ ጥያቄ ነበር። (እንዲህ ጨርቅ የሚያስጥል አፋጣጭ ጥያቄ የሚጠይቅ ጋዜጠኛ ይስጠን ቢባል ምርቃት ነው እርግማን?)

ምንም እንኳን የአንድ ዘፋ ነገር እንዲህ ሲጋነን ማየቱ ቀልቤን የሚስበው ባይሆንም፤ ለእኔ ትልቁ ቁምነገር የአንድ ሰው መናደድ እና መስተዋት መስበር ሳይሆን የተጣለበት ቅጣት ነበርና ነገሩን ትንሽ በውስጤ አመላለስኩት። በአገራችን እንዲህ  ዓይነት ፍርድ እና ብይን የመስጠት ብዙ ልምድ ቢኖረን “ንዴት ማረቂያ ግባ” የሚባለው (‘ከርቸሌ ውረድ’ እንዲሉ) ስንት ይሆን? አልኩኝ ለራሴ።

በተለይ በዚህ በአሜሪካ ደግሞ ይብሳል። ሰዉ ትዕግሥት የሚባል ነገር አልፈጠረበትም። ፀባዩ አፍንጫው ላይ ነው። በጥቂቱ ቅይም፣ ቁጥት፣ ብስጭት፣ ንድድ ብሎ ከዚያም ድንገት ፍንድት ይላል። አበሻውም ሌላውም ዜጋ። ተፋቀሩ ከማለት ይልቅ ተጣሉ፣ ተዋሐዱ ከማለት ይልቅ ተለያዩ፣ አብረው በስኬት አደጉ ከማለት ከስረው ተለያዩ የሚለው የሁል ጊዜ የእኛ ሰው ዜና ነው።

ወደ ሚዲያ አውጥቶ ለመናገር ሰዉ ይፈራ ካልሆነ በስተቀር (ፖለቲካል-ኮሬክትነስን ያስታውሷል) በቁጣቸው እና በቶሎ- ፈንጂነታቸው መቼም አፍሪካ-አሜሪካውያኑን (ጥቁር አሜሪካውያንን) የሚያህላቸው እንደሌለ እኛ ሐበሾቹ ሁልጊዜ እያነሣን እናማቸዋለን። ወንዶቹ አፍንጫቸውን ነፍተው፣ በጋ ከሆነ በንቅሳት የተዥጎረጎረ (ታቱ) ክንዳቸውን፣ ጡንቻቸውን እና ደረታቸውን ገልብጠው፣ ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው፤ በዓይናቸው እንትን እና በቅንድባቸው እያዩ ሲራመዱ ላየ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” የሚለው ተረት ትዝ ይለዋል።

ትራንስፖርት ላይ፣ ወይንም ዕቃ መሸጫ መለወጫ ቦታዎች፣ አስተናጋጅ እና ተስተናጋጅ ሆኖ ግንኙነት ሲፈጠር በሚደረጉ የቃላት ልውውጦች ላይ አነጋገራቸው እና አኳሗናቸው ሁሉ ኃይለ-ቃል የተቀላቀለበት ነው። ሁል ጊዜም የተናደዱ ይመስላሉ። ለጊዜው አልፎ በሚሄድ የቃላት ልውውጥ ራሳቸውን መግታት እየተሳናቸው ክፉ ወንጀሎች ይፈጽማሉ። አንዳንዴ ለአገሬው ‘ጥቁር ሕዝብ’ ንዴት እና ቁጣ በስሪንጅ የተሰጠው ይመስላል። እንዴት ከልጅ እስከ አረጋዊ ቁጡ ይሆናል? ብዬ አስባለሁ። ነገሩ ግን ወዲህ ነው።

ለ500 ዓመታት በባርነት ቀንበር መከራቸውን ያዩት ወንድሞቻችን/ እህቶቻችን የአፍሪካ ግዞተኞች አሜሪካውያን በውስጣቸው በእርግጥም የተጠራቀመ ንዴት አለ። ለ500 ዘመን ከሰውነት ክብር በታች አዋርዷቸው የኖረ የዘረኛ ነጮች አስተዳደር ላይ ያነጣጠረ ቁጣ አለ። ገና ገንፍሎ ወጥቶ አልረጋም። ጥቁር አሜሪካውያን (አፍሪካውያን አሜሪካውያን) እኩልነታቸው ከተረጋገጠ ገና የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ ብቻ በመሆኑ ያ የፀረ ጭቆና እና የፀረ ዘረኝነት ቁጣ እና ንዴት አሁንም ተንጠፍጥፎ አልወጣም። ዛሬም የዘረኝነት ጉዳይ የአሜሪካ ትኩሳት ነው።

ቁጡ ጥቁር አሜሪካውያን ተናዳጅነታቸው የእንቢተኝነት እና የአንገዛም ባይነት ምልክት የነበረባቸው የ1960ዎቹ ዓመታት ቅርብ እንደመሆናቸው ዛሬም እምቢተኝነትን እንደ “ወንድነት”፣ ቁጣን እንደ አሸናፊነት የመመልከቱ ባህል እና ልማድ ሰልጥኖ ቀርቷል። ወንዶቹ ብቻ ሳይሆኑ (ሴቶቹም) ኃይለኛና ቁጡ መሆናቸውን “ከጠንካራ ሴትነት” የሚቆጥሩ አፍሪካውያት-አሜሪካውያት ቁጥርም ብዙ መሆኑን ሚዲያዎች ሁሌም ያብራራሉ። የተቆጣ ሕዝብ!!!

በእኛም አገር ቢሆን “ቁጡነትና አትንኩኝ” ባይነት እንደ ጀግንነት የመታየቱ ሁኔታ በስፋት ያለ ይመስለኛል። በተለይም “የባህል ገበያ” በሆኑ እንደ ኮሌጅ ሕይወት ባሉ ቦታዎች “የጠባይ ዓይነት”፣ የሰው ነጩ በሚታይበት፣ ሁሉንም ዓይነት ሰውና ጠባይ ማየት የተለመደ በሆነበት “ንዴትን እንደ ላከያ የሚወስዱ ብዙ ተማሪዎች አይ ነበር። አኩራፊዎች፣ በትንሽ በትልቁ ተናዳጆች፣ ብቸኞች፣ ተግባቢዎች፣ ቀልደኞች፣ አልቃሾች … ሁሉም ዓይነት ጠባይ በሞላበት ውስጥ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ባይ ብዙ “የተጠመዱ ቦንቦች” ነበሩ።

አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ጠብ ያለሽ በዳቦዎች ድንገት ይፈነዱና ከቃላት ውርወራ እስከ ግብ-ግብ ድረስ ይገጥማሉ። ነገር ግን “ንዴት ማረቂያ” ፍርድ ስላልነበረ ውሎ ሲያድር ራሱ “ንዴቱን ማረቂያውን” ከኑሮ እያገኘው ተናዳጁ ትዕግስተኛ፣ አኩራፊው ተጫዋች፣ ዝጋታሙ ሳቂታ ሆኖ ይወጣል። የእኛ “አንገር ማኔጅመንት” ቦታዎች “ኮሌጆቻችን” ነበሩ ማለት ነው። ያልተከፈላቸው የጠባይ ሐኪም እና መካሪ ተማሪዎች የብዙውን ተማሪ ሕይወት አርቀው እና አሻሽለው እንዳወጡት አስታውሳለሁ።

ከግለሰብዕ ደረጃ አልፈን ከተመለከትነው በአገር ደረጃም ብዙ ብዙ መተንፈሻ ያጡ ቁጣዎች እና ንዴቶች አሉ። ያለፈ ማንነት እና ‘አገር ግንባታ’ ውስጥ በተፈፀሙ ጉዳዮች ዙሪያ ንዴታቸው ያልበረደላቸው ብዙዎች እንዳሉ እንመለከታለን። ሰው ከታሪክ ጋር ተስማምቶ፣ ያለፈን ነገር ባለፈ ታሪክነቱ ካልተቀበለው እና ከዚያ ተምሮ ወደፊት መመልከት ካልቻለ “ንዴቱ ባለመታረቁ” እና ጉዳት በማያደርስ መልኩ መፍትሔ ባለማግኘቱ ሰውየው “ዝም ባለ የፀጥታ ንዴት ውስጥ” ይኖራል ማለት ነው። ጋዜጦቻችን እና መጽሔቶቻችን፣ ሬዲዮ ቴሌቪዥኖቻችን እንዲሁም ፖለቲከኞቻችን በአንድ ወይም ስለ አንድ የታሪክ ወቅት የተሰማቸው እና የሚሰማቸው “ንዴት እንዳልለቀቃቸው ከጽሑፎቻቸው እና ከንግግሮቻቸው ላይ በግልጽ እናያለን።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሰለባ የሆኑት አይሁድ እና በመንግሥታቸው ደረጃም ቢሆን የዘር ማጥፋቱን የፈጸሙት ጀርመኖች ወደ ኋላ ተመልው የፈሰሰውን ውሃ ለማፈስ ባይችሉም ከነገሩ ጋር ታርቀው እና ንዴታቸውን አብርደዋል። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ድጋሚ እንዳይከሰት ትክክለኛውን ትምህርት ወስደው ቀጥለዋል። ከዚህ ውጪ ዛሬም እንደ ትናንቱ እያለቃቀሱ የዛሬ ኑሯቸውን ሲዖል አላደረጉትም።

ለዚህ ማሳያ የሆኑኝ ለንደን የጎበኘኹት “የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሙዚየም”፣ ዕድል ገጥሞኝ ያየዃቸው የተለያዩ የጀርመን ሙዚየሞች፣ እንዲሁም ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው “የሆሎኮስት ሙዚየም” ናቸው። ከዚያም አልፎ ት/ቤቶች ስለዚህ ዓይነቱ የዘር ማጥፋት ክፋት ያስተምራሉ። በዚህም ንዴታቸውን ያርቁታል፣ በሚገባው መልክ ያስተነፍሱታል፣ ይማሩበታል።

ኢትዮጵያም ካለፈው ማንነቷ ጋር በመታረቅ፣ የጠፋውን በጥፋቱ፣ የለማውን በልማቱና በበጎነቱ ካልወሰደች፣ መንግሥትም ሕዝቡ ካለፈ ማንነቱ ጋር ተዋውቆ እና ታርቆ እንዲሄድ ካልረ፣ ፖለቲከኞች በአለፍ ገደም የታሪክ ቁስል እየጫሩ ንዴት የሚቀሰቅሱ ከሆነ፣ አገራችን አገር አሆንም። በትናንቱ እየተናደድን፣ የንዴት አራራችንን ለማካካስ እኛም ሌላ ወንጀል ስንፈጽም እኛም አገራችንም ከጥፋት አዙሪት የመውጣታችን ነገር ሕልም ይሆናል። ብሔራዊ “አንገር ማኔጅመንት” ያስፈልገን ይመስለኛል። ሁል ጊዜም ‘እህህ’ እና “እነ እንትና ድሮ የሰሩን ነገር” እያሉ ንዴትን በቁጣ እያጀቡ ማዜም ለአገር አንድነትም ሆነ ለሕዝቦች ዘላቂ ወዳጅነት ምንም አይፈይድም። የተናደደ ሰው ንዴቱን ያርቃል/ ያስተካክላል ማለት የተጎዳውን ይረሳል ማለት አይደለም። ይቅር ማለት እና መርሣት (Forgive, not forget) ይለያያል። እስከነተረቱ “የወጋ ቢረሣ፣ የተወጋ አይረሣ” እንል የለ? አገራዊም ሆነ ግለሰባዊ ንዴቶቻችን ይታረቁ፣ ይተንፍሱ፣ መስመር ይያዙ፣ ትምህርት ይወሰድባቸው፣ እንለፋቸው።

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 

5 comments:

Anonymous said...

I think bad behaviors such as rudeness, short-temperedness, being criminal correlate with poverty and lack of education rather than being black. Unfortunately most blacks are poor. So it seems like blacks culturally have these bad behaviors.

We should also be tolerant of things that look bad but not actually really bad. There is nothing wrong with tattoos. Even some tribes in Ethiopia wear tattoos. Wearing pants low shouldn't necessarily be a bad thing. It is just a style.

Anonymous said...

ግሩም ጉዳይ ነው ያነሳኸው፡፡ ትርጓሜው አና ስለ አሜሪካው አንገር የሰጠው ታሪካዊ ትንተና ጥሩ ነው፡፡ የኛን ሃገር በቀል "አንገር ማኔጂመንት" በጣም ነው ያሳቀኝ፡፡ ጥሩ አድርገህ ካፕቸር አድርገኽዋል፡፡ "ሶሻል ላይፍ አያሉ በሶየን ጨረሱት" ብሎ ደብዳቤ ለቤተሰቦቹ ላከ የተባለውን ልጂ አስታወስከኝ፡፡

ወደ ፖለቲካው ስንመጣ ግን ለይት የሚል ነገር አለ፡፡ ጭራጭ ቁጣ የማያውቅ ሰው በይሉኝታ መናገር የማይፈልገውን ነገር አንዲናገር የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ የሰሞኑ የፕሮፌሰር መስፍን ጽሁፍ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህኛውም ጽሁፋቸው ቁጡ አልሆነም፡፡ አንዳንዴ ግን የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ ተብሎ የተተው ነገር በወጊው ይብስና አንደገና አንደወጋ ያለውንም ረስቶ ልክ አንደተወጋ ብዙ ማውራት የሚፈልግ ሰው አና ቡድን ይኖራል፡፡ አንደዚህ ያሉትን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ የሚለው በፖለቲካ ውስጥ ትንሽ ችግር አስከትሎኣል፡፡ አንዳልተወጋ አና አንደወጋ መነገር ያለበት ሃይል አለ፡፡ አሁንም አየወጋ መሆኑን ማስታወስ የሚያስፈልግበት ሁኔታ አለ፡፡ በሃገር ጉዳይ ላይ ያሳየነው ለዘብተኝነት ሃገሪቱን ጠቅሞኣል ማለት ያስቸግረኛል፡፡ በማለባበስም የትም አይደረሰም፡፡ ቢያንስ ፖለቲካዊ ማንነቱን ማወቅ አለበት፡፡

Anonymous said...

Damay

ጋዜጦቻችን እና መጽሔቶቻችን፣ ሬዲዮ ቴሌቪዥኖቻችን እንዲሁም ፖለቲከኞቻችን በአንድ ወይም ስለ አንድ የታሪክ ወቅት የተሰማቸው እና የሚሰማቸው “ንዴት” እንዳልለቀቃቸው ከጽሑፎቻቸው እና ከንግግሮቻቸው ላይ በግልጽ እናያለን።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሰለባ የሆኑት አይሁድ እና በመንግሥታቸው ደረጃም ቢሆን የዘር ማጥፋቱን የፈጸሙት ጀርመኖች ወደ ኋላ ተመልው የፈሰሰውን ውሃ ለማፈስ ባይችሉም ከነገሩ ጋር ታርቀው እና ንዴታቸውን አብርደዋል። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ድጋሚ እንዳይከሰት ትክክለኛውን ትምህርት ወስደው ቀጥለዋል። ከዚህ ውጪ ዛሬም እንደ ትናንቱ እያለቃቀሱ የዛሬ ኑሯቸውን ሲዖል አላደረጉትም።

Anonymous said...

ጥሩ ኮርስ ነው የሰጠኸን እግዚአብሄር ይስጥልን

Anonymous said...

ቆንጆ ፅሁፍ ነዉ ::በእጅጉ ያስተምራል ::ልብ ያለዉ ልብ ይበል::ያለፈን በደል መረሳት ከቂመኛነትና በቀልተኛነት መፅዳት ታላቅነት ነዉ:: ለፀሐፊዉ ምስጋናዬ ከልብ ነዉ:: ዘላለም-ከጎጃም::