Friday, September 9, 2011

“To Fear or Not To Fear”፤ 9/11

በዚህ ሰሞን ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሚዲያዎችን ሁሉ ያጥለቀለቀ የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በየሚዲያው በመተላለፍ ላይ ናቸው። የመጀመሪያው “ሂዩሪኬን አይሪን”/ “ማዕበል-አይሪን” መጣሁ መጣሁ  ባለችበት ባለፈው ወቅት ሲከናወን የቆየው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰሞኑን አሥረኛ ዓመቱ በደረሰው የ9/11 ጥቃት ዙሪያ ያለው ነው። ብዙ ሰው በእንደዚህ ዓይነቱ “ማስጠንቀቂያ” ላይ ያለው አመለካከት ይህንን ጽሑፍ ጋብዟል።1ኛ.  “ሂዩሪኬን አይሪን”/ “ማዕበል-አይሪን”፦ የዚህች ማዕበል ሰሞን (ለምንድነው ሁል ጊዜ በሴቶች የሚሰይሟቸው ሂዩሪከኖቹን?) በተለይም በኒውዮርክ እና አካባቢው የነበረው “መዓት መጣላችሁ” ብዙውን ሰው አርድ አርበድብድ ሆነውበት አልፈዋል።፡የፈረንጆቹን ባላውቅም የኛ ሰው ግን “እነዚህ ሰዎች አበዙት፤ ዝም ብለው ማስፈራራት ይወዳሉ” ወዘተ የሚል አስተያየት ሲሰጥ ሰንብቷል።

ኒውዮርክ ድምጥማጧ የሚጠፋ የሚመስለውን ያህል ሌላውም የምሥራቅ አሜሪካ ክፍል በዳግም ምጽዓታዊ ቁጣ የሚመታ መስሎ ነበር። በዚያን ሰሞን የነበረው የሰዉ ሽብር ሌላ “ክፉ ቀን አያምጣ” አሰኝቶን አልፏል። ሚዲያዎች በሙሉ “ኤክስፐርቶቻቸውን” አሰልፈው በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ ምን ዓይነት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት፣ ምን ምን ዓይነት ዕቃዎች ገዝቶ መዘጋጀት እንዳለበት፣ የቁርጡ ቀን ከመጣ እንዴት አድርጎ ሕይወቱን ሊያተርፍ እንደሚችል ወዘተ መቸም ያልተባለ እና ያልተተነተነ ነገር የለም።

በዋዜማው ሱፐርማርኬቶች በሙሉ ባዶዋቸውን ነበሩ። የሚበሉ ነገሮች በሙሉ ተሸምተዋል። ሰዉ ያገኘውን ሁሉ አግበስብሷል። የሚጠቅመውንም የማይጠቅመውንም። በተለይ የምግብ ዘር አልቀረም። ችግሩ ዝናቡና ንፋሱ መጥቶ መብራት ድርግምግም ሲል፣ ፍሪጅ ሥራውን ሲያቆም፣ የተገዛው ያ ሁሉ ምግብ ብልሽትሽቱ መውጣቱ ነው። መጽሐፍ “ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም” (2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፥15) እንዳለው የመሰለ ነገር ተደገመ/ ሆነ።

ታዲያ እኛ ጠርጣራዎቹ ብዙ ነገር ስንጠረጥር ሰነበትን። ምናልባት ይህ ሁሉ ማስፈራሪያ ነጋዴዎችን ለመጥቀም ታስቦ የተደረገ ነገር ቢሆንስ ብለን ስንጠረጥር እና ስናስጠረጥር ሰነበትን። ከአበሾቹ ብቻ ሳይሆን ከፈረንጆቹም መንደር እንዲህ ዓይነት ጠርጣሮች አልጠፉም። “ማስጠንቀቂያው” ተገቢ አይደለም፣ ለምሳሌ የኒውዮርክ ነዋሪዎች በማዕበሉ እንዳይመቱ ከቤታቸው ለቀው በየመጠለያው እንዲገቡ መደረጋቸውን በመተቸት ከንቲባ ብሉምበርግ ላይ የትችት ጅራፋቸውን አውርደውባቸዋል። ታዲያ እነዚህ ጠርጣሪዎች እና ተቺዎች ይህንን ያሉት ማዕበሉ ካለፈ እና ብዙም የሰው ጉዳት አለማድረሱን ካረጋገጡ በኋላ ነው። እንግዲህ ጥያቄው ማስጠንቂያውን ፈርቶና ሰምቶ “መጠንቀቅ ወይም አለመጠንቀቅ፣ መፍራት ወይም አለመፍራት” ብለን ትንሽ ፍልስፍና ቢጤ እንሞክር። “To be or not to be” እንዳለው ሼክስፒር።

2ኛ፦ በ9/11 አሥረኛ ዓመት ምክንያት አደጋ ጣይ አሸባሪዎች አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለው ሥጋት፤
አሸባሪዎች በዚህ አሥረኛ ዓመት ሰሞን አደጋ ሊያደርሱ እንደሚችል “የደኅንነት ተቋማት” መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል። ምናልባትም አደጋ ሊያደርሱ ከሚችሉ ሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ አሜሪካውን ሊሆኑ እንደሚችሉ በሚዲያዎች እየገለፁ ነው። እኛ በምንኖርበት በዚህ አካባቢ እንኳን የዋሺንግተን ዲሲ ከንቲባ ማስጠንቀቂያ እና ማሳሰቢያ ሲሰጡ በቲቪ መስኮት አይቻቸዋለኹ። “ለየት ያለ ነገር ካያችሁ ወዲያውኑ ለፖሊስ ደውሉ” ብለዋል። ይኸው ማስጠንቀቂያ በየስቴቱ እና ግዛቱ በሙሉ እንደሚቀጥል እሙን ነው።

አንድ ነገር እውነት ነው። ካለመጠንቀቅ መጠንቀቅ ይሻላል። እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ቦታዎች ራስን መጠበቅም ይገባል። ነገሮን አቃሎ ከመመልከት ከሚመጣ ጉዳት ራስንም ቤተሰብንም መጠበቅ ያስፈልጋል። በተለይም ቅዳሜ እና እሑድ ተከትሎ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች፤ ገበያ ቦታዎች (ሞሎች)፣ ትራንስፖርቶች፣ ፊልም ቤቶች፣ ስቴዲየሞች ወዘተ ለመገኘት ዕቅድ ያላቸው ሰዎች አስፈላጊውን የጥንቃቄ መመሪያዎች መስማት እና ተግባራዊ ለማድረግም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

እንዲህ ዓይነቱ የጥንቃቄ ነገር በሚነሣበት ወቅት ነገሮችን የሚያጣጥሉ ሰዎች የሚያቀርቡትን አንድ አመክንዮ ልጥቀስ፡፤ እርሱም “እግዚአብሔር ያውቃል” በሚል የሚቀርብ ሃይማኖተኝነት የተላበሰ ነገር ግን ነገረ-ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ ካለመረዳት የሚሰዘነር የስንፍና አገላለጽ ነው። “ራስን ከመቅደስ ጫፍ ወርውር” ለሚለው ጥያቄ “እግዚአብሔርን አትፈታተን”  የሚለው የጌታችን መልስ ጥሩ ማስረጃ ነው። አንድ የወሎ ገበሬ በጎቹ ጠፍተውበት፣ ተኩላም እንዳይበላበት ተጨንቆ በየፈፋው ሲፈልጋቸው ያየው አንድ እረኛ “አይህ፣ እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፣ አንተ ወደቤትህ ግባ፣ እግዚአብሔርን አታምንም እንዴ?” ቢለው  “አይ ወዳጄ፣ ፈጣሪንም አምናለኹ፣ በጎቼንም እጠብቃለኹ” ሲል መልሶለታል። የሰውን ሥራ መሥራት ለሰው፣ የፈጣሪን ሥራ ለፈጣሪ መተው ይገባል። የራስን ተግባር ሳይሰሩ እግዚአብሔር ያውቃል” ማለት ግን ስንፍና ብቻ ነው።

በጠቅላላው ካለመጠንቀቅ መጠንቀቅ ይሻላል። በመጠንቀቅ የሚመጣ ጉዳት የለም። መጠንቀቅ ማለት መፍራት፣ እምነት ማጣት፣ በእግዚአብሔር አለመታመን አይደለም። ሳይጠነቀቁ ተዘልሎ መቀመጥ ደግሞ የእምነት እና በእግዚአብሔር የመታመን ምልክት ሊሆን አይችልም። ስለዚህ በዚህ የዕንቁጣጣሻችን ሰሞን (በዚህ አገር የሰፕቴምበር 11 ሰሞን) ራስን ከመጠበቅ ጋር በዓላችንን በደስታ ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ ከዘመድ ጋር እናክብረው።

መልካም አዲስ ዓመት።
  

4 comments:

Anonymous said...

Very true.....ካለመጠንቀቅ መጠንቀቅ ይሻላል

Anonymous said...

ዲ/ን ኤፍሬም ግልጽና ለማንም ሰው በጣም ጥሩ አስተማሪ ጽሁፍ ነው። ሁል ጊዜ ወቅታዊና ተጨባጭ የሆኑ ጽሁፎችን በአደባባይ ላይ በመሰማታችን ላመሰግንህ እወዳለው።
የወሎው እረኛ ብሂል የሚያስተምር ነው። አንዳንዴ በራሳቸው ፍልስፍና ተጉዘው በዚህ አገር እንደዚህ አይነት ብሂል አለ ብለው የራሳቸውን ወይም ፍላጎት ለማሞላ የሚጥሩ ሰዎችን እየሰማን ነው። በቅርቡ የአንድ ዐፍሪካዊ አገር ያለ ነው በሚል ወንድምህን እገድላለው ሲለው ሰምቶ እራሱ ወንድሙ ገደለው ማለት ምን አይነት ብሂል ነው በቃ ለራሳችን ስሜትና ፍላጎት ማርካት ሕዝቡ ገና ለገና የዛን አገር ታሪክ አያውቀውም ብሎ መናገር ራሱን የቻለ ድፍረት ነው።

Anonymous said...

“ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም” (2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፥15)

Anonymous said...

ዲ/ን እንኳን አደረሰህ።

“ለየት ያለ ነገር ካያችሁ ወዲያውኑ ለፖሊስ ደውሉ” በአበሻ ተጠራጣሪነት በአካባቢህ ፖሊስ ስንቴ ተጠርቶ ይሆን?!

ዓመቱን የጤና የሠላም ያድርግላን። አሜን።