Monday, October 24, 2011

እኛ፣ 99 ፐርሰንቶቹ

(ኤፍሬም እሸቴ):- “ግብጻውያን ወደ ታህሪር አደባባይ የወጡበትን እና ከብዙ ደም መፋሰስ በኋላ በፈረጠም አገዛዛቸው ጥንታዊቱን ምስርን አስጨንቀው የገዟትን ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣናቸው አሽቀንጥረው የጣሉበትን ምክንያት ብዙ አሜሪካውን ይረዳሉ፤ በደመ ነፍስም ቢሆንም ይስማሙበታል። የራሳቸው ወገኖች “ዎል ስትሪት”ን ለመቆጣጠር የተነሡበትንምክንያት ግን ሁሉ በአንድ ልብ አልተገነዘቡትም” ይላል የኒውዮርክ-ታይምሱ ጦማሪ (Damon Winter/The New York Times) ዴሞን ዊንተር።


“ታህሪር አደባባይ” የግብጾች ማዕከላዊ እና ታዋቂ አደባባያቸው፣ እንደ አዲስ አበባው “መስቀል አደባባይ” ዓይነት ሲሆን በኒውዮርክ የሚገኘው “ዎል ስትሪት” ደግሞ አሜሪካ የአክሲዮን መሸጫ አሜሪካ የንግድ ማዕከል ነው። ግብጾች ይህንን ታዋቂ አደባባይ ነበር የተቃውሟቸው ምልክት እና “ቤዝ” ያደረጉት። አሜሪካኖቹ ደግሞ የዓለም ኢኮኖሚ መዘውር ያለበትን “ዎል ስትሪት አካባቢን በመቆጣጠር” ነው ተቃውሟቸውን የጀመሩት። የግብጾቹ ችግር በዋነኝነት የፖለቲካ፣ የአሜሪካኖቹ ደግሞ የኢኮኖሚ በመሆኑ የተቃውሞ ማዕከላቸውም እንደዚያ ሆኗል።
Tahrir Square in 1941
በእርግጥ ግን በታህሪር አደባባይ አመጽ እና በኒውዮርክ “ዎል ስትሪትን መቆጣጠር” (http://occupywallst.org/) መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። የኒውዮርክ ፖሊስ በግመል ላይ የተቀመጡ ሰላማዊ-ሰልፍ-በታኝ ባለ አለንጋዎችን አላሰማራም። ወይም ከዚያም በባሰ ሁናቴ በከባድ መኪናዎች የራሱን ዜጋ እያባረረ በጎማው አልጨፈለቃቸውም፣ ወይም ሰሞኑን በካይሮ ወታደራዊው አስተዳደር ሲያደርግ እንዳየነው በታንክ እየጨፈለቀ ሰልፉን ለመበተን አልሞከረም። አሜሪካውያን በአገራቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ እጅጉን ልቡናቸው ቢቆስልም በአሜሪካ ያለው የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ሁኔታ ግብጻውያን ለወደፊቱ ሊደርሱበት የሚመኙት እና በታህሪር አደባባይ ደማቸውን ያፈሰሱለት ትልቅ ግብ ነው። 
ይሁን እንጂ “ዎል ስትሪትን ለመቆጣጠር” ማንሃታን ዙኮቲ ፓርክ (Manhattan’s Zuccotti Park) የተሰበሰቡት አሜሪካውያንም ሆነ በታህሪር አደባባይ የነበሩት ግብጻውያን የምሬታቸው ምላሽ እና መንግሥቶቻቸውን ለመጠየቅ የወጡበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው። የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ጥያቄ በየአገሮቻቸው ያለው ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አብዛኛውን ዜጋ (99%ውን) ሳይሆን አንድ-ከመቶውን (1%) ለማገልገል የቆመ ነው የሚል ነው።  “ዎል ስትሪትን የሚቆጣጠሩትን” በሚደግፉት በ‘አል ጎር’ (Al Gore) አባባል “ለዲሞክራሲ የሚደረግ ኡኡታ፤ primal scream of democracy” ነው።  
Tahrir Square now
በአሜሪካ ያሉትን ለሰላማዊ ሰልፍ ያስወጣቸው ከፖለቲካው ጥያቄ ይልቅ የኢኮኖሚው ጥያቄ ነው። ይህም በአጭር አባባል “የኢኮኖሚ እኩልነት መጥፋት/ economic inequity” ነው። የአሜሪካ የደኅንነት ኤጀንሲ (C.I.A.) “የኢኮኖሚ ፍርደ ገምድልነት” ስለሚበዛባቸው አገሮች ያወጣው ደረጃ እንደሚያመለክተው አሜሪካ ልክ እንደ ቱኒዚያ እና ግብጽ ሁሉ ይኸው የኢኮኖሚ አለመጣጣም የሰፈነባት አገር ናት። ይህንን ኢ-እኩልነት ጦማሪው ዴሞን ዊንተር በሦስት ምሳሌዎች እንደሚከተለው ይተነትነዋል፦
140ዎቹ ዲታ አሜሪካውያን ያላቸው ሀብት ሲደመር ቀሪዎቹ 150 ሚሊዮን አሜሪካውያን ካላቸው ይበልጣል፤ 
  • አንድ በመቶ አሜሪካውያን ከቀሪዎቹ 90 በመቶዎች የበለጠ ሀብት አላቸው፤
  • በጆርጅ ቡሽ የ2002-2007 የአገዛዝ ዘመን አሜሪካ ካፈራችው አጠቃላይ ሀብት 65 በመቶው ወደ ዲታዎቹ አንድ ፐርሰንቶች ኪስ የገባ ነው።
ከዚህ በላይ የኢኮኖሚ ፍርደ ገምድለነት ከየት ይመጣል? የኮርኔል ዩኒቨርሲቲው “የዳርዊን ኢኮኖሚ/ The Darwin Economy” መጽሐፍ ደራሲ ሮበርት ፍራንክ (Robert H. Frank) እንደሚያትቱት በኢኮኖሚ ከተራመዱ 65 አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ፍርደ ገምድልነት ያለባቸው አገሮች የማደግ ብቃታቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ የሄደ ሲሆን የሀብት ክፍፍላቸው ሚዛናዊ እና “ፍትሐዊ” የሆነባቸው ደግሞ የበለጠ ለማደግ ችለዋል።
በአሜሪካ ያለውም ይህንኑ ይመስላል። በአገሪቱ የሀብት ስርጭት ሚዛናዊ በነበረባቸው ከ1940-1970ዎቹ ዓመታት የአገሪቱ የዕድገት እመርታ እንደዚያው ፈጣን እንደነበር መጽሐፉ አውስቶ ሀብት ወደ ጥቂቶች ካዝና ብቻ መሰብሰቡ በፈጠነባቸው ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን ኢኮኖሚው ማሽቆልቆል መጀመሩን ይጠቅሳል።
አሜሪካ ወደ ቬየትናም ለጦርነት መግባቷን ተቃውሞ ከቆመው ከዚያን ዘመን ወጣት ሥር ነቀል እንቅስቃሴ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም በሚባለው በአሁኑ ሕዝባዊ ንቅናቄ አሜሪካውያን የባንኮችን እና የባለፀጎችን (ዎል ስትሪት) ቅጥ ያጣ ብዝበዛ፣ ሥራ አጥነትን እና የኑሮ አለመሻሻልን በምሬት መቃወም ጀምረዋል። ሁለቱ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንን ሕዝባዊ ንቅናቄ በሚመስላቸው ለራሳቸው ፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ለመጠቀም በመጣር ላይ ናቸው። ፕሬዚዳንት ኦባማን ጨምሮ ብዙ ዴሞክራቶች በየንግግሮቻቸው ንቅናቄውን በመደገፍ እየተናገሩ ሲሆን ሪፐብሊካኖቹ እና የነርሱ ደጋፊ ሚዲያዎች ደግሞ “የሶሻሊዝም ናፋቂዎች” ናቸው በሚል ዓይነት ይጎንጧቸው ይዘዋል። ሕዝቡ ግን የአደባባይ ተቃውሞውን አጽንቶ ከመቀጠሉም በላይ በመላው አገሪቱ እና በመላው ዓለም እንደ ሰደድ እሳት በመቀጣጠል ላይ ይገኛል። ከጣሊያኑ የተቃውሞ ሰልፍ በስተቀር ሁሉም ሰላማዊ እና የአደባባይ ሕዝባዊ በዓልና የፌሽታ ስሜት የያዘ ነው።
የሰው ልጅ መቸም ምን ቢያገኝ ጠገብኩ አያውቅም። የምዕራቡ ኮርፖሬት-ስግብግብነት ምንም የማይጠረቃ፣ ከኑሮው እና ከሥራው በሚፈናቀለው ሕዝብ የሚከብር አስቀያሚ ሥርዓት ነው። ደግነቱ ግን ፖለቲካው ሙሉ በሙሉ በነዚህ ባለሀብቶች የተያዘ ባለመሆኑ ሕዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣት ምሬቱን፣ ለውጥ መሻቱንም እየገለጸ ነው። ጥቂት ሰው ብቻ ጠግቦ የሚኖርባት፣ ሌላው ግን ተርቦ የሚያድርባት አገር ምንም ዋስትና ሊኖራት አይችልም።
ምናልባት እንዲህ ባለው የኢኮኖሚ አለመመጣጠን መካከል ሰው በሰላም ወጥቶ የሚገባባት አገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም። የተንደላቀቀ ኑሮ በሚኖሩ ሰዎች የግንብ አጥር ሥር ተቀምጦ በሥርዓት የሚለምን ነዳይ፣ በኤሌክትሪክ ሽቦ ባልታጠሩ የንግድ ሱቆች ፊት ለፊት እርጥባን የሚለምን አጀንቱ በረሃብ የታጠፈ ሰው፣ ወርቅና ሌሎች የከበሩ ጌጣጌጦች ያለምንም የብረት አጥር ከሚሸጥባቸው ጥቂት ደሃ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ካልሆነች ሌላ ማን ሊሆን ይችላል?
አሜሪካን በመሳሰሉ አገሮች ያሉ ሕዝቦች እንዲህ ዓይነቱን፣ ምንም ዓይነት፣ ፍርደ-ገምድልነት የሚሸከሙበት ጫንቃ የላቸውም። እነርሱ እየተራቡ እና ከሰውነት በታች በተጣለ ኑሮ እየኖሩ ሌላው ግን ብቻውን በገነት እንዲኖር አይፈቅዱም። በጭራሽ። በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ የሰው ልጅ ጥቅም የማይጠበቅበትን  ሥርዓት አይቀበሉም። አሁን ያሉት መንግሥቶቻቸው የዚህ እምቢተኝነታቸው እና ክብራችን ይጠበቅ ባይነታቸው ውጤት ይመስለኛል። ፈረንሳዊው ፈላስፋ (Joseph de Maistre፣ (1753-1821)”) እንዳለው “ሁሉም ሕዝብ ሊያገኘው {የሚገባውን} መንግሥት ያገኛል፤ Every nation has the government it deserves/ “Toute nation a le gouvernement qu’elle mérite”  ያለው ያግዘኝ ይሆናል።
የዜጎች ቁጣ የመጥፎ አስተዳደር ማስተካከያ፣ የተበላሹ አሠራሮች መጠገኛ ፍቱን መድኃኒት ነው። በሥልጣን ወንበር የሚቀመጡ ሰዎች ይህንን ሕዝባዊ ቁጣ እስካልፈሩ ድረስ “ፈጣሪን ፈርተው” ሕዝባቸውን ያገለግላሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ምድራዊ ባለሥልጣኖች የሚፈሩት የፈጣሪን ቁጣ ሳይሆን የሕዝባቸውን ቁጣ ነው። እንደ ግብፁ ሆስኒ ሙባረክ፣ እንደ ቱኒዚያው ቤን አሊ (ከነሚስታቸው) ዓይነቶቹ መሪዎች መቀመቃት የሚያወርዳቸው የሕዝባቸው ቁጣ ካልመጣባቸው በስተቀር ፍርደ ገምድልነታቸው መጨረሻ የለውም፤ የሕዝባቸውም ከሰብዓዊ ፍጡር በታች የወደቀ የዕለት ተዕለት ኑሮ ትርጉም አይሰጣቸውም።  
ከሰውነት በታች የወረደ ኑሮ ተቀብሎ የሚኖር ሕዝብ ካለ በራሱ ፈረደ፡፡ ለጊዜው አሜሪካኖችም ሆኑ የእነርሱ ዓይነት አመለካከት የያዙ ሕዝቦች አሁን በየአገሮቻቸው ያለውን የኢኮኖሚ ፍርደ ገምድልነት አንሸከምም ብለዋል። “99 ፐርሰንት ሆነን ሳለ አንድ ፐርሰንቶቹ ብቻ እየኖሩ እኛ የኑሮ አዘቅት ውስጥ አንኖርም” ብለው ድምጻቸውን አሰምተዋል። የምዕራቡን የኢኮኖሚ መዘውር የያዙት እና ቢያተርፉም ቢከስሩም ገንዘባቸው ምንም የማይቀንስባቸውን ባንኮችን የመሳሰሉ ተቋማትን (በደፈናው ዎል ስትሪት) ተቃውመው የወጡት ዜጎች ምን ለውጥ እንደሚያመጡ ወደፊት እናየዋለን። “እምቢኝ” ማለታቸው ግን ያስደስታል።
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።7 comments:

Anonymous said...

እኛ ሀገርም በልቶ የሚያድረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ግን ምን ማድረግ ይቻላል እውነት እንነጋገር ከተባለ እኮ ከሙባረክም ሆነ ከጋዳፊ የባሰ መንግስት ነው ያለን፡፡ ራበን ብለን ሰልፍ ብንወጣ /ለዛውም የምንወጣበት የማርያም መንገድ ካገኘን/ ያለምንም ጥርጥር በታንክም ሆነ ባዳፍኔ ይፈጀናል፡፡ ራበኝ ብሎ የወጣ ሰላማዊ ሰልፈኛ ሳይሆን አሸባሪ፣ ባንክ ዘራፊ፣ ፀረ-ዲሞክራሲ........... በሚል ሽፋን ................ ይኸው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስንት ቅጽል ስም እየወጣላቸው ራሳቸውን አይደለም ቤተሰብ እና ዘመድ አዝማዳቸው መቆሚያ መቀመጫ እስኪያጡ ድረስ አይደል እንዲ የሚሳደዱት፡፡ የት ይኬዳል ይህች አገር ግን የማናት? የእኛ ወይስ በየመ/ቤቱ ተሰግስገው በድሀ ሀገር ስም /በተለያየ ኘሮጀክት ስም/ የሚመጣውን ርጥባን ያለምንም ይሉኝታ እየተከፋፈሉ ሀገሪቱን መቀመቅ የሚያወርዱአት ካድሬ ነን ባዮች ናት? ደግሞ አለማፈራቸው አንገታችንን ደፍተን የቻልነውን እንስራ የምንለውን ሷያሸማቅቁን........ ኡኡኡኡኡኡ ኧረ ተወኝ ኤፍሬም ሆድ ይፍጀው ነበር ድሮ የሚባል አሁን ግን ሆዳችንን ፈጀው አቃጠለው......... የት ሄደን እንፈንዳ???????????????????

Anonymous said...

ጽሁፎችን ሳነብ ብዙ እማራከሁ የአጻጻፍህ ስልት ከሌላው ስለሚለይና
ለመረዳትም ስላማያስቸግር

ከሆለታ ገነት አርባአራት ከተማ

Anonymous said...

ጤና ይስጥልኝ ኤፍሬሜ።

አይይ...እንደው ባያሌው ግሩም ምልከታ ነው። በርታ እግዚአብሔር ይጠብቅህ። በነገራችን ላይ እኛም እኮ "ታህሪር አደባባይም" ሆነ "ዎል ስትሪት" ያልወጣንበት ቀንንና ጊዜ ያለም። ልዮነቱ እኛን ሰሚ ስለሌለ፤ በየእምነት ቤታችን ወደ አንድዬ አቤት ማለታችን ብቻ ነው። እንደው ብቅ ብለን ቢያዩንማ የመጀመሪያው አስተያያት ሰጭ እንዳሉት እንደው ያበጥሩን ነበር። እርሱ ጌታ ለጥያቄያችን መልስ የሰጠ ዕለት "ዕዳው ገብስ ነው" የሚሆነው... እንጃ ብቻ !

ቸር ያሰማን... አቦ በጣም ትዘገያለህ።

Tsegaye Girma said...

Well written dear Efrem. Those who have the guts to say "no" to unjust deeds are lucky ones. But... what is it that makes us, Ethiopians, do nothing about such inequalities?

ርብቃ ከጀርመን said...

መልካም ብለሀል ዲየቆን ኤፍሬም እንዳልከውም በኛሀገርብቻ ይሆናል እንዲህአይነት የዋህነት ያለው ክፉአይስማብንእና እንዲህ በርሀብ እየማቀቀ ከሚሰርቅ የሰውፊት ቢጠብሰው እርሀብና እርዛት ቢያስጨንቀው ይሻለዋል ግን እስከመቸ ነው ጥያቄው መንግስት ይሄን ለማረጋትና በነፍስወከፍ በቀን አንድየ እንኩዋን ጠግቦ ካልበላ ይሄህዝብ አንድቀን የገነፈለእለተ አያድርስነው እና የሚመለከተው ክፍል ቢያስተውለው ጥሩ ይመስለኛል እግዚያብሄር ሀገራችንን ከእልቂት ይጠብቅልን ላስተዳዳሪዎችም ማስተዋልን ይስጥልን !

eleni said...

እኛ ኢትዮጵያውያን እርሀብ ስለምንችል ነው አፋችንን ዘግተን ቁጭ ያልነው፡፡

Anonymous said...

An Interesting Article. I like the links u put too which makes even better than the text only