Tuesday, October 11, 2011

ጋብቻ - ኢትዮጵያ፤ ፍቺ - አሜሪካ

(ኤፍሬም እሸቴ):- እዚህ አሜሪካን ውስጥ ከሚታተሙት እና እኔም ከምወዳቸው ጋዜጦች መካከል አንዱ “USA Today/ ዩ.ኤስ.ኤ ቱዴይ” የተባለው (እና የድሮውን “የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ”ን የሚያስታውሰኝ) ጋዜጣ አንዱ ነው። ፖለቲካም፣ ማሕበራዊ ሕይወትም፣ ቴክኖሎጂም፣ ስፖርትም፣ ቢዝነስም … ሁሉም ሁሉም በአጭር-በአጭሩ እና ቅልብጭ ባለ እንግሊዝኛ የሚታተምበት ጋዜጣ ነው። (የዛሬዪቱ ኢትዮጵያም እንደዚህ ነበረ ማለቴ አይደለም)።

ጋዜጣው በቅርቡ ይፋ የሚሆን ስለ ትዳር እና ፍቺ እንዲሁም ስለ ልጆች ሁኔታ የተደረገ አንድ ጥናታዊ ውጤት ዘገባ ባስነበበት ክፍሉ ለፍቺ ምክንያት ናቸው የተባሉ 18 ነጥቦችን በዝርዝር አቅርቧል።  ይህ የምወደው ጋዜጣ ያስነበበው ዘገባ በአሜሪካ ያለነው ኢትዮጵያውያን ያሉብንን የትዳር ተግዳሮቶች እና ፍቺዎች ጉዳይ እንዳሰላስለው እና የሚሰማኝን በግርድፉም ቢሆን  እንዳካፍላችሁ ገፋፋኝ። ቦታ ከበቃኝ።


ጥናቱ እንደሚያመለክተው የፍቺዎች ትልቁና ዋነኛ መንስዔ ተደርጎ የተቀመጠው “የትዳር አጋሮች በተለያየ መንገድ ማደግ” (Growing Apart) የሚሉት ነጥብ ነው። በአጭሩ ምንነቱን ለመበየን ያህል “መራራቅ፣ በጊዜም ይሁን በሌላ ምክንያት የተቀራረበ ግንኙነት አለመኖር፣ የፍላጎት፣ የስሜት መራራቅ” ማለት ነው። በዘመነ ቢን ክሊንተን የአሜሪካ ም/ፕሬዚደንት እና ኋላም በአካባቢ ጥበቃ ጠበቃነታቸው “የ2007 የኖቤል የሰላም ሽልማት” አሸናፊ የነበሩት አል ጎር (Al Gore) ትዳራቸው መፍረሱን  ለማስታወቅ ወደ መድረክ ሲወጡ በምክንያትነት የተናገሩት ቃል ይኸው “Growing Apart” ነው።

ተፋቺዎቹ አል ጎርና ባለቤታቸው “አድገናል፣ ነገር ግን ዕድገታችን የመጣው በአንድ አቅጣጫ እና በተመሳሳይ መልኩ ሳይሆን ሁለታችንም በየፊናችን ስለሄድን አብረን መኖር አንችልም፤ ስለዚህ እንፋታለን” ሲሉም ሰምተናቸዋል። ቃሉ አዎንታዊ በሆነ መልክ የተቀረፀ፣ መጨረሻው የትዳር መፍረስ ሆኖ እንኳን ሰዉ በበጎ እንዲቀበለው የሚያደርግ ነው።

እውነቱን መረር ብሎ ለሚመለከተው ግን በተለያየ አቅጣጫ ማደግ ሳይሆን በተለያየ አቅጣጫ የትዳርን ማገር መሳብና በኋላም ማፍረስ መስሎ ነው የተሰማኝ። ጥቂት በጥቂት እያለ በመካከል የሚገባ መነቃቀፍ፣ ራስን ለመከላከል ሌላኛው የትዳር አጋር የሚያቀርበውን ሐሳብ አለመቀበል፤ የጠላትነት ስሜትን ማዳበር፣ በዚህም መቀራረብን ማራቅ እና መለያየት “በየግል በተለያየ አቅጣጫ ማደግ” ተብሎ አምሮ ተከሽኖ ቀርቧል። አለመቀራረቡ እና በአንድ ቤት ጣራ ሥር እየኖሩ ደባልነት ሲመጣ ደግሞ ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ጥናት በሁለተኛ ፀረ-ትዳርነት ያነሣው “መወያየት አለመቻል፣ መነጋገር አለመቻል” ("Unable to talk together") የሚለው ነጥብ ይከተላል። እርሱም በተራው ለሌሎች ብዙ ችግሮች በሩን ወለል አድርጎ ይከፍታል።

እዚህ አሜሪካን አገር ትልቁ ሰይጣን ባለትዳሮቹ እንዳይነጋገሩ እና ችግራቸውን እንዳይፈቱ የሚያደርገው ጋግርታም አጋንንት ነው። ሳይነጋገሩ ያለውን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል? ደግሞ መነጋገሩ እንዲህ መቼ ቀላል ሆነ? በአሜሪካኖቹ ጥናት ላይ “ለትዳር መፍረስ ምክንያት ነው” ብለው መልስ ከሰጡት መካከል 52% የተስማሙበት ይኸው ጉዳይ ("Unable to talk together") በሌሎች አገሮች እና ባህሎችም ውስጥም አይኖርም ማለት አይቻልም። አንድ ጣራ ሥር፣ አንድ አልጋ ላይ እያደሩ ነገር ግን ጀርባ ለጀርባ ተሰጣጥተው የሚኖሩ ሰዎችን ቤት ይቁጠራቸው።

በመነጋገር ሊቀልሉ የሚችሉ ተያያዥ ችግሮች አሉ። “እስቲ እንነጋገር፤ አለ ብዙ ነገር” እንዲል። ለእኛ ለኢትዮጵያውያኑም ሆነ ለሌሎቹ “ሮጦ-አደር” ዜጎች (ለኑሯቸው ተሯሩጠው፣ ወጥተው ወርደው የሚኖሩትን ለማለት የፈጠርኩት ነው፤ አትሌቶችን ማለቴ አይደለም) ፈተና የሚሆነው “ብዙ ሰዓት በሥራ ላይ ማሳለፍ” እና በዚህም ምክንያት ጊዜ ማጣት፣ እንዲሁም “ለትዳር አጋር በቂውን ትኩረት አለመስጠት” (Not enough Attention) የትዳሮቻችን ፀሮች ሆነዋል።

የኛ ሰው ገቡ እስኪጎብጥ የሚሠራለት ብዙ ሐሳብ/ ጉዳይ በልቡ አለ። አገር ቤት የጀመረው ቤት ይኖረዋል፤ በየወሩ ዶላሩን የሚጠብቁ ዘመዶች፣ የአሜሪካ ቤት የወር ክፍያመኪና እና የቤት ወጪ ዓይኑን አፍጥጦ ይጠብቀዋል። አንዳንዴም አሜሪካ መኖሩን ዶላር እንደ መዛቅ የሚመለከት ዘመድ ከአገር ቤት መግቢያ መውጫ ሊያሳጣው ይችላል። እናም ባል ለሚስት፣ ሚስት ለባል ሊሰጡት የሚገባው ትኩረት ይረ እና አእምሮ በብዙ ሐሳብ ይወጠራል። ሚስት “ተረሳሁ፣ ዞር ብሎም አያየኝ” ልትል ትችላለች። ባልም “እርሷ ጭንቀቷ መቼ ስለ እኔ ሆነ?” ይላል። ከዚያ የሚከተለውን ውጤት ማወቅ ምን ይከብዳል።

ይኼ ለትዳር አጋር “ትኩረት አለመስጠት” (Not enough Attention) የሚባለው ነገር ቀላል ነገር ሆኖ አልተገኘም። ከፍ ብለን በጠቀስነው ጥናት ላይ “34.1%” የሚሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ያነሡት ጉዳይ ነው። ሚስት ጠዋት ሽክ ብላ ስትለብስ “አምሮብሻል” ካልተባለች፣ ባል ደግሞ ማታ ደክሞት ሲመጣ “እንዴት ነበር ውሎ ዛሬ” ካልተባለ፣ “ምን በላህ/ሽ፣ እንዴት ዋልክ/ሽ” ካልተባለ ጉድ ፈላ። እዚህ አገር "How was your day?" የሚሏት አባባል አለች። የዕለት “ሪፖርት ማቅረቢያ” ናት። ልጆችም፣ ወላጆችም ስለ ዕለት ውሏቸው የሚነጋገሩበት የማዕድ ዙሪያ “ስብሰባ/ ግምገማ” "How was your day?" ነው። እኛ ደግሞ ይህንን በቴሌቪዥኑም፣ በፊልሙም፣ በሥራ ቦታም እንሰማ እና የትዳር አጋሮቻችን እንደዚያ አለማለታቸውን ከንቀት እና ካለመሰልጠን ልንቆጥረው እንችላለን።

እንደ ባህልም እንደ ልማድም ሆኖብን የትዳር አጋሮቻችን ጥሩ ቢለብሱም፣ ጥሩ ቢሠሩም ቶሎ ብሎ በጣፋጭ (ጮሌ?) አነጋገር “ዋዉ! አሪፍ ልብስ፤ አሪፍ ምግብ” ምናምን ማለትን እንደሽርደዳም፣ እንደሽወዳም እንቆጥረዋለን መሰል፣ አይሆንልንም። ደፈር ብለን ለማድነቅ ብንሞክርም “ኡኡቴ፣ አልቀረብህም” ብንባልስ ብለን እንሰጋለን፤ አጋጥሞንስ ቢሆን? እንዲያውም ከአድናቆቱ ይልቅ ውረፋው ይስማማናል። “ምነው ዛሬ ደግሞ አያትሽን መስለሻል?” ይላል እንደነገሩ-እንደነገሩ የለበሰችውን ሚስቱን በነገር ለመንካት። “ልብስ የሚገዛልኝ፣ ልጅ የሚያስመስለኝ ባል ስላጣሁ ይሆናላ” ብላ በነገር ትመልስለታለች። ከዚያ ተጀመረ ማለት ነው። የገንዘቡም፣ የወር ወጪውም የምኑም የምኑም ነገር ይነሣና ጭቅጭቅ ይጀመራል።

እንኳን ሌላ ነገር ተጨምሮበት የገንዘብ ጉዳይ ብቻውንም ጦርነት ለመፍጠር በቂ አቅም አለው። በአሜሪካውያኑም ዘንድ ለፍቺ ምክንያት ከሆኑት ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ ("How Spouse Handles Money") ነው። የእኛም ሰዎች ጭምር። አሜሪካ እንደ አገር ቤት አይደለም። በለመድነው ታሪክ፣ ከቤተሰብ መካከል ብዙ ጊዜ አባወራዎች ብቻ ሠርተው መላውን ቤተሰብ የሚያስተዳድሩበት ዘመን ነበር። ሚስቶች “የቤት እመቤቶች” (ቃሉ ደስ ሲል) ብቻ ሆነው ልጆቻቸውን በሥርዓት አሳድገው፣ ባሎቻቸውን መርተው ይኖራሉ።

አሜሪካ ባልም ሚስትም ይሠራሉ። እሰየው ነው። ሁለቱም የየራሳቸው ገቢ አላቸው። ባል ገንዘብ አመጣም አላመጣም ሚስት እንደ ጥንቱ ዘመን “የወር አስቤዛ” ብላ “ላትጨቃጨቅ” ትችላለች። ሁለት ገቢ መኖሩ መልካም ሆኖ ሳለ “ራሴን በራሴ ማስተዳደር እችላለሁ፣ ራሴን የቻልኩ ነኝ” የሚለው ስሜት በሁለቱም ላይ የማይሆን መመካት እያሳደረ ትዳሮች ፈተና ላይ ይወድቃሉ። እንዲያውም ለኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ትዳር መናጋት ዋነኛው ችግር ይኼ ሳይሆን ይቀራል?

አሜሪካ ለሚመጣ ስደተኛ፣ እጅግ በጣም የተማረውም፣ ምንም የተለየ ሙያ ያልነበረውም፣ የመጀመሪያ ጊዜ ሥራዎች ተመሳሳይ ናቸው። ባልም ሚስትም አንድ ዓይነት ሥራ፣ አንድ ዓይነት ገቢ ሊኖራቸው ይችላል። ይኸው ነገር ሊኖር የሚገባውን መከባበር እና መቻቻል ለመናድ እንደመነሻ እየሆነ ይቀርባል። ለረዥም ዘመን የዘለቁ ትዳሮች አሜሪካ ሲመጡ ስብርብራቸው ይወጣል። ልጆቻቸውን ለወግ ለማዕረግ ያበቁት እንኳን ሳይቀሩ እዚህ ሲመጡ ትዳራቸውን በቀላሉ ይንዳሉ።

እንደ አገር ቤቱ ያለ ትዳር መኖርን እንደ ኋላ ቀርነት መቁጠር ይበዛል። ሌላው ቀርቶ ኩሽና ጉድ ጉድ ብሎ ሽሮ መሥራትን እንደበታችነት በመቁጠር “እርሱ ኢትዮጵያ ቀረ፤ ከፈለገ ገብቶ ራሱ ይቀቅል” መባባል እንደ ቁምነገር ይቆጠራል። “ሴት ለኩሽና፣ ወንድ ለአደባባይ” የሚባለው ግብዝነት የለብኝም። እንዲያውም ከሴት የሚያስንቅ የኩሽና ሙያ ያላቸው ብዙ ወንዶች አውቃለሁ። እኔም ብሆን “ክሽን ያለች ሽሮ” ለመሥራት አላንስም። ነገር ግን “ለብዙ ዘመን ወንዶች ሲጨቁኑን ኖረዋል፣ ይኼ አሜሪካ ነው” ዓይነት አካሄድ ደግሞ በጎ አልመሰለኝም። (‘ያለፈው፣ የወንድ-የበላይነት-ዘመን ናፋቂ’ … እንዳልባል እንጂ።)

ወንዶቹም እንዲህ በቀላሉ የምንቀየር አይደለንም። “የአበሻን ወንድ ከመቀየር፣ አሎሎ ብረት በድስት ጥዶ መቀቀል ይሻላል” እያሉ ይቀልዱብናል። ዛሬም፣ አሜሪካ መጥተንም፣ ጥንን እያልን፣ እጃችንን ኪሳችን ውስጥ ከትተን እየተጀነንን መኖር ያምረናል። የአገሩ ሕግ አላወላዳ አለን እንጂ፣ እንደ ጥንቱ፣ ሴቶቹን ‘በእጃችን ጭብጥ፣ በእግራችን እርግጥ’ አድርገን ብንገዛቸው እንወድ ይሆናል።

የቤት ውስጥ ተግባራትን ባለማከናወንም እንወቀሳለን - ወንዶቹ። ከቤት ማጽዳት ጀምሮ፣ ልጆች ማስተኛትን ጨምሮ፣ ልብስ ማጠብን (በማሺንም ቢሆን) አካቶ ያለው የቤት ውስጥ ጉዳይ ዋነኛ የአሜሪካ ትዳር የሰላምም/ የጦርነትም ምክንያት ነው። በጠቀስነው ጥናት ላይም ("household responsibilities") ተብሎ ሰፍሯል።

አሜሪካ ያለ ሰው የማያገኘው፣ አገር ቤት ያለ ሰው ግን እንደ ቀላል ነገር የሚቆጥረው የዘመድ ወዳጅ ርዳታ ነው። የሚስት ወዳጅ ዘመድ፤ የባል ወዳጅ ዘመድ ለመልካም ትዳሮች የሚያበረክቱት ብዙ በጎ ድርሻ አለ። እንኳን ወዳጅ ዘመድ፣ ጥሩ ጎረቤት እና ጥሩ ሠራተኛ የሚናፈቅበት አገር አሜሪካ ነው።

ለምሳሌ አንድ ቀን ባልም ሚስትም ሥራ እንዲቆዩ የሚገደዱበት ሁኔታ ቢፈጠር ልጆችን ማን ይይዛቸዋል። ወይ ያላቸውን ገንዘብ ከፍለው በቅጡም ለማያውቋቸው ሕጻናት ጠባቂዎች መስጠት ወይም ያለ ፍላጎታቸው ከሁለቱ አንደኛቸው ቤት ለመቆየት ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ የሁል ጊዜ ሁኔታ ስለሆነ ውሎ አድሮ በባለትዳሮቹ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም። በተለይም ከሁለቱ አንደኛቸው ልጆችን በመንከባበከቡ ላይ ዳተኛ ከሆኑ ነገር ተበላሸ ማለት ነው። እንኳን ለብቻ ለሁለትም ከባድ ነው።

ልጅነቴን እንደማስታውሰው ከቤተሰባችን ባልተናነሰ ዘመድም፣ ጎረቤትም ነው ያሳደገን ማለት እችላለሁ። እናቶቻችን “እትዬ እንትና፤ እስቲ እነዚህን ልጆች እዪልኝ፤ አንድ ቦታ ደርሼ ልምጣ” ብለው ጥለውን ብርር ነው። እነ እትዬ እንትናም ካስፈለገ ተቆጥተው፣ ካስፈለገ ቆንጥጠው፣ ካስፈለገ ሱቅ ልከው፣ እንደፈቀዳቸው አድርገው “ቢዚ” ያደርጉናል። ከእናት/አባቶቻችን እኩል የሰፈሩን እናቶች/አባቶች እንፈራለን። አሜሪካ ላለ ትዳር “እነ እትዬ እንትና፣ ጎረቤቶች” ሊኖራቸው የሚችለው ቦታ ክፍት ይሆንና ከቁምነገር የማንቆጥረው የነበረው ያ የአገር ቤቱ ማሕበራዊ ድግግፎሽ ጉድለቱ ይታያል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ሳይንቲስቶች አሜሪካኖቹ ስለ ራሳቸው እንዳደረጉት፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ያተኮሩ ተመሳሳይ ጥናቶች ሲያደርጉ ብዙ የምናውቀው ነገር ይኖራል። እስከዚያው ግን በኢትዮጵያ እየተመሠረቱ አሜሪካ የሚፈርሱ ትዳሮች ምክንያታቸውን በቅጡም ሳንረዳው፣ መፍትሔም ሳንፈልግላቸው መዝለቃቸው ግድ ይሆናል።
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።


Cartoon: Courtesy of http://qsaltlake.s3.amazonaws.com/wp-content/uploads/2011/08/Divorce_by_sailor_midnightstar.jpg8 comments:

Anonymous said...

beselam new yetefahew??????????????

igzabher yistilign....betam astemari new

gin yihe chigir hager betim sir iyesedede yale neger new...
bizu malet yichalal....

በፍቃዱ ኃይሉ said...

ግሩም ነው:: ርዕሱን መጀመሪያ ሳየው ለአሜሪካ ተጋብተው አሜሪካ የሚፋቱትን ጥንዶች ልታወራ መስሎኝ ነበር:: ስለዚህም ጉዳይ ትጥፋለህ ብዬ ወደፊት እጠብቃለሁ

Anonymous said...

ጥሩ ምልከታ ነው ወንድም ኤፍሬም ፡፡ ግን የአሜሪካን የማኅበራዊ ሳይንስ ሳይንቲስቶች የሚሉንን ከመጠበቅ የአገራችን ባለሞያዎች ብዙ ሊሉን ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ ነው የሚባለው?
አዜብ ዘሚኒሶታ

Anonymous said...

One day you blog will attract more attention when we open our eyes as a good reader.

Anonymous said...

ወንድም ኤፍሬም ይልመድብህ ብያለሁ፡፡ ዳተኛነትህን ያቅርልህ፡፡

The Architect said...

እንዴት ያለ ግሩም ጽሑፍ አስኮመኮምከን ጃል! ነጮቹ ችግሮቻቸውን በጥናት እና ምርምር ላይ በተመሠረተ መንገድ እየተነተኑ መፍትሄ ስለሚሹለት ይመስለኛል የእድገታውም የስልጣኔያቸውም ምሥጢር፡፡ እኛ እንደሆንን ይኸው አንደዬ ጥንት እነዳስቀመጠን አለን፡፡ ሳንሰማም ሳንለማም…

Anonymous said...

'እኛ እንደሆንን ይኸው አንደዬ ጥንት እነዳስቀመጠን አለን፡፡ ሳንሰማም ሳንለማም… 'wedijatalehu

Anonymous said...

kala heiwat yasamahe
ename yamesemamabate gezaa yalamasatatate nawe.