Wednesday, October 12, 2011

ቃላት እና ቋንቋ እንደየዘመኑ፣ እንደየመንደሩ፣ እንደየመንግሥቱ

(ኤፍሬም እሸቴ):- ሁል ጊዜም አዲስ ዘመን አዲስ ቃል እና አገላለጽ ይዞ ይመጣል። አዲሱ ቃል መምጣቱ ሳይታወቅ የሚረሳውን ያህል አንዳንድ አገሮችና ባሕሎች ግን እነዚህን አዳዲስ ቃላት የመመዝገብ እና የማጥናት ልምድ አላቸው። የዓመቱን አዲስ አባባልና ቃል መርጠውም ያስታውቃሉ። አዲስ በሚታተም መዝገበ ቃላት ውስጥም ያስገባሉ። ለምሳሌ በ2010 በዚህ መልክ መነጋገሪያ ከነበሩት መካከል ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት የጆን ማኬይን ምክትል ወይዘሮ ሣራ ፔሊን አንዷ ናቸው።  ሴቲዮዋ በንግግር መካከል ተሳስተው የተናገሩት ቃል የ2010 ምርጥ አዲስ ቃል (“New Oxford American Dictionary 2010's Word of the Year”) ተብሎ አዲስ የ“American lexicon” ለመሆን በቅቷል።


ወይዘሮዋ የተጠቀሙበት  “ሪፉዲዬት/Refudiate” የሚለው ቃል ሲሆን ከዚያ በፊት የማይታወቅ ቃል አልነበረም። እርሳቸው “refute እና repudiate” የሚሉትን ሁለት ቃላት አዋድደው የፈጠሩት፣ የጻፉትና የተናገሩት ቃል ነው። ቃሉን መጻፋቸው እንደታወቀ ከኮሜዲያን እስከ ፖለቲካ ተንታኞች ድረስ በዚያ ሁሉ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ጣቢያ ሲብጠለጠሉ ሰንብተዋል። እርሳቸውም ቃሉን የተጠቀሙበትን ጸሑፍ (የትዊተር ገጽ) ወዲያውኑ ቢያነሱም “ሞኝ እና ወረቀት የያዘው” ሆነና የተሳሳቷት ቃል ተመዝግባ ለመቆየት በቃች። በመጨረሻም ክብር አግኝታ የዓመቱ ምርጥ አዲስ ቃል ለመባል በቅታለች። ከዚህ ጀምሮ “ሪፉዲዬት/Refudiate ማለት to reject with denial” ማለት ሆኗል።

በአገራችንም በየጊዜው ብቅ ብለው ከዚያ የሚከስሙ ብዙ አዳዲስ ቃላት አሉ። ብዙዎቹም በ “አራዳ ቋንቋነት” ስለሚወሰዱ ማንም ከቁምነገር ሳይጥፋቸው የሚቀሩ ናቸው። ሚዛን ደፍተው ለመዝለቅ የሚችሉት ከመንግሥታዊ ሥራዎች ጋር ተገናኝተው የሚፈጠሩና የሚነገሩት ናቸው። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከየሚኖሩበት አገር ጋር የሚጣጣም ዳጳስጶራዊ አማርኛ ፈጥረው ይግባባሉ።

ጀርመን አገር እግር ጥሏችሁ ብትሔዱ፣ ግብዣ ቢጤ ቢገጥማችሁ፣ የሚጋብዟችሁ ሰዎች የሚጠቀሟት አንዲት ቃል “ይጣፍጥህ፣ ይጣፍጣችሁ” የምትል ናት። “መልካም ምግብ ይሁንልህ” እንደማለት ስትሆን ቀጥተኛ የጀርመን ትርጉም ናት። በዚህ በአሜሪካ ደግሞ እንግሊዝኛውን በቀጥታ ወደ አማርኛ በመመለስ የምንግባባቸው ብዙ አባባሎች አሉ።

አንድን ሰው “እየተማርክ ነው ወይ?” ለማለት ሲፈልጉ “ኮሌጅ ትሄዳለህ?” ይሉታል። ወይም “እማራለሁ” ለማለት የፈለገ እንደሆነ “ት/ቤት እሄዳለሁ” ይላል። (Do you go to school/ college? ማለት መሆኑ ነው)። ብዙው የአገራችን ሰው ግማሹን እየሠራ ግማሹን የሚማር በመሆኑ ቃሏን ብዙ ጊዜ መስማት የተለመደ ነው። መጀመሪያ ሰሞን ግር ይሎትና እርስዎም ጥቂት ቆይተው “የሚቀጥለው ዓመት ኮሌጅ መሔድ እፈልጋለሁ” ብለው ሲያቅዱ ይገኛሉ።

አንድ የአገርዎን ሰው ወይም ወዳጆን መንገድ አግኝተው ሲያዋሩት ይቆዩና ስትለያዩ የሚናገሮት እንድ አባባል አለች። ከተሰነባበታችሁ በኋላ “በል እስቲ፣ ሌላ ጊዜ አይሃለው” ይልዎታል። “ሌላ ጊዜ አይሃለሁ” ማለት “ምናባክ ትሆናለህ” የሚል ዛቻ ሳይሆን “ዳግም እንገኛኛለን/ ያገናኘን” የምትል መልካም አነጋገር ናት። የእንግሊዝኛው “I'll see you later. and (See you) later. Good-bye until I see you again” የአማርኛ ቅጂ ነው። “ሰሞኑን እንገናኛለን፣ መጥቼ እጠይቅኻለኹ” እንደማለት ዓይነት።

ከእንግሊዝኛው ወስደን በአሜሪካዊው አማርኛ ብዙ ጊዜ የሚባል ሌላው አባባል ደግሞ በየንግግሩ መካከል “እውነት ነው እውነት ነው” እያሉ ደጋግሞ መመለስ ነው። እርስዎ አንድ ነገር ሲያጫውቷቸው እነርሱ “እውነት ነው” እያሉ በመደጋገም ከመለሱልዎት “የሚናገሩት ነገር ትክክል ነው” ለማለት፣ “ተስማምቻለሁ” ለማለት ጥቅም ላይ የዋለች ማጀቢያ ናት። እንዲህ ዓይነቱ “ደጊመ ቃል/ ቃላትን መድገም” ቀደም ብሎ የማውቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ዓላማውም “አጽንዖተ ነገር” ነበር። ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ የማውቃቸው አንዳንድ ወዳጆቼም “እውነት ነው፣ እውነት ነው” እያሉ ማውራት መጀመራቸውን ታዝቤያለኹ።

የዳያስጶራው ሰው ሲታመም “ሐኪም አይተኻል? ሐኪምማ ማየት አለብህ” ሊሉት ይችላሉ። ሒድና ታከም፣ ተመርመር እንደማለት ነው። ቶሎ ሐኪም ቤት መሔድ ጥቅም አለው ምናምን ብለው ምክር ቢጤ ሲጀምሩ በሚናገሩት ነገር መስማማቱን ለመግለጽ “አይ ኖውውውውው” እያለ ከንፈሩን ሞጥሞጥ አድርጎ “ዉ” ላይ ረዘም አድርጎ ይመልስሎታል (በተለይ ሴቶቹ)።  “ገብቶኛል፣ ተረድቻለኹ” ዓይነት ነገር ቢሆንም በሚገባበትም በማይገባበትም ቦታ “አይ ኖዉ” የሚለው ስለሚበዛ ሊሰለቾት ይችላል።

በአገር ቤትም ቢሆን እንደዚህ ዓይነት አዳዲስ ቃላት እና “ክሊሼዎች” የተለመዱ ናቸው። አንዳንዶቹም በየመገናኛ ብዙሃኑ በቱባ ቱባ ባለሥልጣናት ሳይቀር ተደጋግመው የሚባሉ ናቸው። በተለይም ከአገሩ ርቆ ነገሮችን ለሚመለከት እና ለሚያዳምጥ ሰው የቃላትና አባባሎች አካሔድ እያስፈገገውም፣ እያስገረመውም በጥሙና እንዲመለከታቸው ያደርጉታል።

“የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚለውን አባባል ስሰማ በመጀመሪያ ግርታ ከዚያም ፈገግታ አጭሮብኝ ነበር። ሁሉም ዐ.ነገር በዚህ እንዲያልቅ አዋጅ የወጣ እስኪመስል ድረስ ብዙ ሰው፣ በተለይም መድረክ ላይ የምትደረግ ንግግር ቢጤ ከሆነች፣ ማጠቃለያው “የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚል ነው። ስምህ ማነው ሲባል “ስሜ እገሌ እገሌ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው” መባል ብቻ ነው የቀረው።

በአገራችን የመንግሥት ለውጥ እና የቋንቋ ለውጥ አብሮ ስለሚሔድ አዲስ መንግሥት ሲመጣ አዳዲስ አባባሎችን መፍጠሩ የተለመደ ነው። ቃላትና አባባሎች የአንድን ሰው ፖለቲካዊ አቋም የሚገልጹ መታወቂያዎች ሆነው የሚቀመጡበት “ሁኔታ ነው ያለው”።

በ“ግብታዊው አብዮታችን” ዘመን “አቸነፈ” እና “አሸነፈ” የተለያዩ የሁለት አብዮታዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መገለጫዎች ሆነው ይታወቁ እንደነበር ታላላቆቻችን ይነግሩናል። ወታደራዊው መንግሥት “ሠርቶ አደር” ያለውን አሁን “ላብ አደር” ይባላል። ገበሬው እና የከብት ጭራ ተከትሎ የሚኖረው ‘ዘላን’ በረኸኛ “አርብቶ አደር፣ አርሶ አደር” ይባላሉ። “ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ” ሲባል የነበረው አሁን ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች” ተብለዋል። በነጠላው “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ማለት ብቻውን ሌላ መዘዝ ሊኖረው ይችላል፤ “የአንድ ብሔር የበላይነትን ናፋቂ ወይም ብዙነትን አለመቀበል” ተደርጎ ሊያስቆጥር ይችላል።

ጉቦኝነት፣ በሌላው ሰው ገንዘብ መበልጸግ እና ሥልጣንን ጥቅም ለማግኛ ማዋል “ሙስና” እንደተባሉ ተቀብለን ከተግባባንባቸው ቆይተናል። አሁን ደግሞ “ኪራይ ሰብሳቢነት” መጥታለች። እንዲህ ሲባል የሰማ ውጪ አገር ያለ ኢትዮጵያዊ “እንዴ፣ ታዲያ ሰው ቤቱን አከራይቶ ኪራይ ላይሰበስብ ነው እንዴ? በነጻ አከራይ ማለታቸው ነው?” ብሎ ግር ቢሰኝ እንዳይደንቆት። “ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት አለብን” የሚል ሹም ሲገጥመው እንዴት ክው እንደሚልም ያስቡት።

በአብዮቱ ዘመን መንግሥትን ተቃውመው በከተማ ግብ ግብ የገጠሙ የተለያዩ ፓርቲዎች በቀይ ሽብር በሚሳደዱበት ዘመን እነርሱም በፈንታቸው በነጭ ሽብር የመንግሥት ባለሥልጣኖችን፣ ከቀበሌ ሹሞች ጀምረው፣ ይገድሉ ነበር። በዚህ መልክ ግድያ የሚፈጽሙትን ቡድኖች ወታደራዊው መንግሥት ‘አናርኪስቶች’ ሲላቸው፤ ይህንኑ የሰማ፣ የቃሉ ትርጉም በቅጡ ያልተረዳው ሰው፣ ለራሱ በሚገባው አባባል ‘አሪቲዎች’ ይላቸው ኖሯል። ታሪኩን ያጫወተኝ ዘመዴ እንደነገረኝ እነዚሁ “አናርኪስቶች” አንድ የቀበሌ ሹም ገድለው ቀብሩ ላይ ዘመዱ “ወይኔ ወይኔ፣ አሪቲ መኮንንን ገደለች” እያለ አለቀሰ አሉ።

እግዚአብሔርን ማመን ተራማጅ አለመሆን፣ የኮሚኒስትነት እጥረት ብሎም አድሃሪነት ተደርጎ ስለሚወሰድ ካኪ ለባሹ ሁሉ ሀልዎተ እግዚአብሔርን ክዶ ጭልጥ ብሎ ጠፍቶ ነበር። በዚያን ጊዜ ሃይማኖትን ሊያመለክቱ የሚችሉ አገላለጾች ለምሳሌ “እግዚአብሔር ያማርህ፣ እግዚአብሔር ያውቃል፣ እንኳን ማርያም ማረችሽ” ዓይነት አገላለጾች ችግር ገጥሟቸው ነበር። እናም ሰውዬው አልጋ ላይ የዋለ ወዳጁን ሊጠይቅ ሄዶ ምን ይበለው? “እግዚአብሔር ይማርህ” እንዳይለው ችግር ሊገጥመው ሆነ። እናም በአጭሩ “ለመዳን ሞክር” ብሎት ወጣ አሉ።

በዚህ መልክ ሲባሉና ሲገለጹ የነበሩ ብዙ አባባሎች ዛሬ በቀልድነት ካልሆነ የሚያስታውሳቸው የለም። ዛሬም የሚነገሩት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተዘንግተው እንደሚቀሩ ምንም ጥርጥር የለውም። የታሪካችን አንድ አካል እንደመሆናቸው መዝግቦ የሚያስቀምጣቸው ባለሙያ ቢገኝ ግሩም ነበር። የየዓመቱን አዲስ ቃል ብቻ ሳይሆን የየመንግሥታቱን “አዳዲስ ቋንቋዎች” እንዲሁ መዝግቦ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል።

“የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው”ን የመሳሰሉ አገላለጾች ብቅ እንደማለታቸው መጠን መዘንጋታቸውም እንደዚያው ፈጣን ነው። ልክ እንደ “ሪፉዲዬት”። ለምሳሌ “ማታ ወይም ከምሽቱ … ሰዓት” ለማለት “ምሽት … ሰዓት” የሚለው ዓይነት እንግዳ አማርኛም እንዲሁ። “አብሮነት፣ አብሮነታችን” ወዘተ የሚሉት የሬዲዮ አማርኛዎችም ድንገት ብቅ ብለው በአዲሱ ትውልድ በመለመዳቸው እንዴትና በምን ሁኔታ እንደተፈጠሩ ሳናውቅ የቋንቋችን አካላት ሆነው ይዘልቃሉ።

መቸም መገናኛ ብዙሃን ቃላት እና አባባሎች የመፍጠር ትልቅ ብቃት እንዳላቸው የምንገነዘበው በጥሙና ስንከታተቸው ነው። ብዙ ጊዜ በምሰማው ‘የሸገር ሬዲዮ’ ላይ “መረጃዎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን” እያሉ ደጋግመው ሲናገሩ እሰማለኹ። ልብ ብዬ ስመለከት ለካስ ቴሌቪዥኑና ሌሎች ሬዲዮዎችም እንደዚያው ይላሉ። የስፖርት ጋዜጠኛው “የዚህን ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውጤቶችን ወደ እናንተ እናደርሳለን” ይላል። “እንዘግብላችኋለን” ለማለት ፈልጎ ነው። አንዱ “መረጃዎችን ወደናንተ እናደርሳለን” ሲል፤ ዘፈን መራጩ ደግሞ “አዳዲስ ዜማዎችን ወደናንተ እናደርሳለን” ይላል። ቃሉ እንደኔ አዲስ ለሚሆንበት ሰው መደጋገሙ ያሰለቻል። ቢሆንም በአዲስ ቃልነቱ ተቀብሎ ከመያዝ ውጪ ግን አማራጭ የለውም፤ ይገባልም።

እንደዚህ አዋጅ ሳናውጅላቸው ነገር ግን ቀስ በቀስ ጥቅም ላይ ማዋል ከጀመርናቸው ቃላት መካከል “ብሎግ” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተፈጠረው “ጡመራ” የሚለው ቃል አንዱ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በአማርኛ “ብሎግ ለከፈቱ” ፀሀፊዎች (ብሎገሮች) ቃሉ ተመራጭ ትርጉም ሆኗል። ፀሐፊዎቹ (“ብሎገሮቹ”) ደግሞ “ጦማሪዎች” ተብለዋል። (ለምሳሌ፦ “እኔ http://www.adebabay.com/ በሚለው የጡመራ መድረኬ ላይ እጦምራኹ” ብዬ ራሴ “ጦማሪ” መሆኔን ባስተዋውቅ ግሱንም ገሰስኩት፣ ቃሉንም በምሳሌ አስረዳኹት ማለትም አይዶል?)። ጡመራ፣ ጦማሪ ሲባል “” ጠብቆ ይነበባል።

እዚህ አሜሪካ ቢሆን ከላይ የጠቀስናቸው ቃላት እና ሐረጎች በሙሉ ተመዝግበው አስተያየት ሲሰጥባቸው እንሰማ ነበር። ይህንን በቤት ሥራ ወስደው የሚመዘግቡ፣ የሚተነትኑ፣ የሕብረተሰቡን ሁናቴ የሚያጠኑ ተቋማት ነጥረው እስኪወጡ ድረስ አዲስ ጉዳይ መጽሔትን የመሳሰሉ የመገናኛ ብዙሃን ይህንን ኃላፊነት ቢወስዱ ያስመሰግናቸዋል። አንባብያንም በአለፍ ገደም የሚያገኟቸውን በማበርከት ሊረዷቸው ይችላሉ። እንግዲህ በመግቢያዬ ቋንቋ እንደየዘመኑ፣ እንደየአገሩ፣ እንደየመንግሥቱ ነው ያልኩት ይህንን ለማብራራት ለመሞከር ነበር።    
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።

11 comments:

Anonymous said...

efti selam neh wey ? wedijewalehu ! please asses all words which are spoken by politicians , there are many many amazing words .

Anonymous said...

“እግዚአብሔር ያማርህ፣ እግዚአብሔር ያውቃል፣ እንኳን ማርያም ማረችሽ” ዓይነት አገላለጾች ችግር ገጥሟቸው ነበር።" ከምርም ነገሩ በጣም ዘልቆ ገብቶ ነበር። እውነት መሆኑን ድንጋይ ነክሼ መማል ባልችልም፤ በቀድሞ ህፃናት አንባ ልጆች "እንደምን አደራችሁ?፣ እንደምን ዎላችሁ?" ወ.ዘ.ተ. ተብለው ሲጠየቁ "እግዚአብሔር ይመስገን" በማለት ፈንታ "እናች(ሸ)ንፋለን" በማለት ይመልሱ እንደነበር ሰምቻለሁ።
ኤፍሬሜ ምነው "እንድምታን" ተራሳ? ወይንስ እኔ ልብ አላልኩት።
ማለፊያ ጽሁፍ ነው። አትዘግይ።
ቸር ወሬ ያሰማን።

Anonymous said...

የሚመች ጽሁፍ ነው ለኔ ተመችቶኛል

yirg said...

A Great article. Go on!
You are passing what you have to the next genertion.

Anonymous said...

it is really great thought.

Anonymous said...

lol...on "እውነት ነው", I am one of a kind Ababa.

Anonymous said...

among those current words of our coutry 'beharawi megbabat, hedase, ......

Anonymous said...

እንደው የእዚህ አዲስ ቃላት ጉዳይ ከተነሳ
ከፖለቲከኞች “ማሳለጫ”
ከሚዲያው “ጆሮ ገብ” (የመረጥንላችሁ ሙዚቃ ጥሩ ነው ለማለት)

Anonymous said...

ዲ. ኤፍሬም ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ “ የሚመች ጽሁፍ ነው ለኔ ተመችቶኛል” ተመችቶኛል፤ ይመችህ፡፡
ይሄ ቃል ራሱ ከአዳዲሲ ቃለቶች አንዱ እኮ ነው፡፡
አዳዲስ ቃላቶች የምትመዘግቡ ካላችሁ ይህችንም እንዳትረሷት ለማስታወስ ነው
አቦ ይመቻቸሁ
አዜብ ዘሚኒሶታ

Adane Fekadu said...

Nice observation. I just wanted to give two simple examples on your profound discussion.
[1. From Politics] – this year (I am talking with respect to Ethiopian calendar) was a year on which we have heard the word “” a lot on Ethiopian media (especially on ETV & Et. Radio). Most of the talks by the journalists (better to say ‘reporters’) were using the word with almost everything – e.g. ልማታዊ መንግስት፣ ልማታዊ አመራር፣ ልማታዊ ባለሀብት፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ…etc. Thus, I believe the word “” can be considered as one of the arising word in the current Ethiopian regime. Don’t you think? Recently, following the death of the late PM Meles Zenawi (RIP), I happened to read a short paragraph saying “ኢትዮዽያ ታላቅ ልማታዊ መሪዋን አጣች።” on one of Ethiopian blogs. Oh, by the way, how about the ‘word’ “RIP” itself (even if it didn’t arise from in Ethiopia) … ልማታዊ አርቲስቶች፣ ልማታዊ ነጋዴዎች ልማታዊ፣ ወላጆች ልማታዊ ተቃዋሚዎች፣ ልማታዊ ኮሜድያኖች… [እናም በመጨረሻ ልማታዊ አልቃሾችና አስለቃሾች

[2. In Ethiopians social life] I had the chance to visit HOME (Ethiopia) after half a dozen years. As anybody can realize, there are so many social, cultural, economical (and, of course, political) changes in the country. What I wanted to write is one thing I faced during my communication with my family members and friends. Let me write the first event. I was talking to my brother (a teenage) about a shoe I bought for him. He said to me “አይነፋም!”. I didn’t understand him, so I said “what?/ ምን?” He said again with strong sound “አይነፋም!” I still didn’t understand what he meant by “አይነፋም!” Fortunately my other brother was listening to our conversation and he said “አይነፋም ማለቱ አልወደድኩትም፣ አልተስማማኝም ማለቱ ነው።” I was very surprised by this word which was “invented” by this generation. In the past, if we wanted to use “ያራዳ ቋንቋ” for something like this, we used to say “አይመችም” if we don’t like it or “ይመቻል” otherwise. Now these two words “ይመቻል” and “አይመችም” are substituted by “ይነፋል” and “አይነፋም” respectively. Since, it is a bit long since I left home, I have no idea when this “” was created; but it was a bit surprise for me.

To conclude my point, ዲያቆን ኤፅሁፍህ ይነፋል። እሺ? ቢሆንም ግን ልማታዊ ፅሁፍ ነው ብለን ለመፈረጅ የማይቻል የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው።”

@AdaneFekadu

Anonymous said...

ሽብርተኝነትስ?