Monday, November 7, 2011

iPod, iPhone, iPad …. iSad


(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- የስቲቭ ጃብስን (Steve Jobs) መሞት ስሰማ ልክ እንደማውቀው ሰው፣ እንደ ቅርብ ወዳጅ ሁሉ፣ በጣም እዝን አልኩኝ።  ሲ.ኤን.ኤን ስቲቭ ከሞተ “30 ደቂቃ ሆነው” እያለ ነበር ዜናውን የሚያትተው። አከታትሎ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጀምሮ ታላላቅ ሰዎች በሙሉ “የተሰማቸውን ሐዘን” መግለጽ ቀጠሉ። የልጅነት ጓደኛው እና የእርሱ ቢጤ “ጂኒየስ” የሆነው ቢል ጌትስ/ Bill Gates/፣ ወጣቱ የፌስቡክ መሥራች “ዙከርበርግ”/ Zuckerberg/፣ የአፕል ካምፓኒ ቦርድ ወዘተ ዓለም አንድ ታላቅ የፈጠራ ሰው ማጣቷን እየገለጹ መስክረዋል።  በርግጥም ታላቅ የፈጠራ ሰው እንደነበረ ሥራዎቹ ምስክሮች ናቸው።

እንደማስታውሰው፣ ከ10 ዓመት በፊት ስለ ቲቭ ጃብስም ይሁን ስለ “Apple” ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። በአንድ አጋጣሚ አግኝቻቸው የነበሩ አንዲት ፈረንጅ ኮምፒውተራቸው አልሠራላቸው እንዳለ ሲናገሩ “My Mac is not working” ሲሉ ሰማዃቸው። “Mac”? ምን ዓይነት ኮምፒውተር እንደሆነ አልገባኝም። ስሙ ግን ደብሮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።

አውሮፓ ከሄድኩ በኋላ አገር ቤት ሆኜ አይቻቸው የማላውቃቸው ነጫጭ “ላፕ ቶፖች” (ጨኔ ኮምዊፕተር እንዲል ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ) ማየት ጀመርኩ። አሻንጉሊት ይመሳስላሉ እንጂ ቁምነገር ያለባቸው አይመስሉም። ረከስ ያሉ ተጠቅሞ-ወርወር (Use and Throw) የሆኑ ዕቃዎች መስለውኝ ነበር። የሚይዟቸው ሰዎች ግን እንዲህ ገንዘብ ያጥራቸዋል የማይባሉ ፀዳ-ፀዳ ያሉ ሰዎች፣ አብዛኞቹም ፈረንጆች፣ ስለሆኑ ምሥጢሩ ሌላ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገመትኹ። በዚያን ወቅት ለራሴ ምንም ላፕ ቶፕ አልነበረኝም። ለመግዛት ከተፈለገ ደግሞ በትንሹ 1400 ዩሮ ያስፈልጋል።

ቆይቶ፣ እኔም ላፕቶፕ ገዝቼ፣  ከዓለመ ኮምፒውተር ጋር ከተዋወቅኹ በኋላ፣ ያቺ አሻንጉሊት የመሰለች ላፕቶፕ ለካስ የላፕቶች ንግሥት ኖራለች አልኩኝ። በተለይ ወደ አዲሱ ምድር ወደ አሜሪካ ከመጣኹ ጀምሮ “አፕል” እና “አፕል ውጤቶች” በሙሉ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ የሀብት እና ደረጃ (ክላስ) ማሳያዎች፣ የዘመናዊነት ምልክቶች፣ “ቀላል እንዳንመስላችሁ” ለሚሉትም ቢሆን (አዲስ አበባ ሞባል የገባ ሰሞን ያንን ፊሊፕስ ዲዮ የሚያክል ነገር ይዘው ይኮሩብን እንደነበሩት ሰዎች) ጉራ መንፊያዎች መሆናቸውን አወቅኹ።

ከዚያ የነ አይፓድ ዘመን ሲመጣ ደግሞ ስለ አፕል እና አንቀሳቃሹ ስቲቭ ጆብስ የበለጠ አወቅኹ። እነዚያ ሚጢጢ የሙዚቃ ማጫወቻዎች የሙዚቃ ኢንደስትሪውን በሁነኛ መልክ ቀይረውታል ይባልላቸዋል። አፕል አዲሱን ሥሪቱን አይፓድን ከማምጣቱ በፊት የሙዚቃው ኢንዱስትሪ የባለቤትነትን መብት በማያከብሩ ሰዎች ምክንያት እጅግ በጽኑዕ ሁኔታ እየተጎዳ ነበር። አዲስ ሙዚቃ ሲወ ወዲያውኑ ኢንተርኔት ላይ እየተጫነ የለፋበት ምንም ሳያገኝ ሕዝቡ ሁሉን ነገር በነጻ ይኮመኩም ጀመር። መንግሥታትም ሕጎችም የአቅማቸውን ለመዋጋት ቢጥሩም ነገሩ እንዲህ ቀላል አልሆነም። አሁንም ድረስ ችግሩ እንደዘለቀ ነው።

የአይፓድ (iPod) አስተዋጽዖ እዚህ ላይ ነው። አፕል እና መሥራቹ አቶ ስቲቭ ጆብስ ትንሿን ሙዚቃ መጫወቻ ከፈጠሩ በኋላ ሰዎች በጥቂት ክፍያ ሙዚቃዎችን እንዲገዙ፣ እነርሱም ሳይጎዱ፣ የሙዚቃ ኢንደስትሪውም ሳይጎዳ፣ አፕልም ተጠቅሞ ሁሉም ጥቂት ጥቂት የሚያተርፍበትን ቴክኖሎጂ አስገኘ። እናም ተንታኞቹ እንደሚናገሩት ትልቅ እመርታ አስመዘገበ። ሰዉ ሁሉ በየጆሮው ላይ ባለነጭ የጆሮ ማዳመጫዋን ሰክቶ በየመንገዱ ላይ፣ በየባቡሩ እና አውቶቡስ ውስጥ እንዲሁም በሕዝብ መገበያያዎች ላይ መታየቱ የተለመደ ሆነ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ በተለይም በምዕራቡ ዓለም፣ ሙዚቃን ከቤት ውጪ ለማዳመጥ ትልቅ ቴፕ ጎረምሶች ትከሻቸው ላይ ተሸክመው አላፊ አግዳሚውን እየረበሹ ይሄዱ ነበር። ሶኒ የትንሽ ካሴት ማጫወቻ ሲያመጣ፣ ያንን በማዳመጫ መስማት ተጀመረ።፡ከዚያ ሲዲ ማጫወቻ እና ሲዲ ሲመጣ ነገሩ ተለወጠ። ከዚያማ ዘመነ-አይፓድ መጣና ቤት ሙሉ ሙዚቃ በሚጢጢ ዕቃ መሸከፍ ተቻለ። ይህ ሁሉ የአቶ ስቲቭ ጆብስ አእምሮ ውጤት ነው።

ስቲቭ ጃብስ አፕልን ገና በወጣትነቱ ከመሠረተና ካምፓኒው ስም ማግኘት ከጀመረ በኋላ ከቦርዱ ጋር በተፈጠረ አለመስማማት የራሱን የአእምሮ ውጤት ትቶ ለመውጣት ተገድዶ ነበር። ድጋሚ የተመለሰው እና “አፕል”ን አሁን ባለው መልኩ ድጋሚ እስከ ግርማ ሞገሱ ከገባበት አዘቅት ያወጣው ከዓመታት በኋላ ነው። ይሁን እንጂ ከአፕል ቢወጣም ሥራ አልፈታም። በ1986 ሊከስር የደረሰውን “Pixar Animation Studios”ን በመግዛት ወደ ፊልም ቢዝነስ ገባ። ተንቀሳቃሽ ፊልሞችን በመሥራት ከዲዝኒ ወርልድ ጋር ማሠራጨት ጀመረ። የመጀመሪያ ፊልሙ “ቶይ ስቶሪ/ Toy Story” (1995 እ.ኤ.አ.) ትልቅ ተቀባይነት አገኘ።

ፒክሳርን ለዲዝኒ ወርልድ እስከሸጠበት ጊዜ ድረስም ትልቅ ዝና፣ ገንዘብ እና ሽልማት ያስገኙለትን 12 የካርቶን ፊልሞች ማለትም Bug's Life (1998)፣ Toy Story 2 (1999)፣ Monsters, Inc. (2001)፣ Finding Nemo (2003)፣ The Incredibles (2004)፣ Cars (2006)፣ Ratatouille (2007)፣ WALL-E (2008)፣ Up (2009) እና Toy Story 3 (2010) ሠርቷል። በተለይም “Toy Story 3” በካርቶን ፊልሞች ታሪክ በገቢው ወደር ያልተገኘለት ሲሆን እስካሁንም ከ$1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል። ከእርሱ ወዲህ የተሠራው የዚህ ካምፓኒ ፊልም “Cars 2” ሲሆን እርሱም በ2011 ለዕይታ የበቃ ነው። በጠቅላላው እነዚህ ፊልሞች $602 ቢሊዮን ዶላር በማስገባት ፒክሳርን የኢንደስትሪው መሪ ለመሆን እንዳበቁት በብዙ ተጽፏል። የስቲቭ ጆብስ ጭንቅላት።

አንድ ቀን፣ እዚሁ ከምኖርበት ከሀገረ ማርያም ጠቅላይ ግዛት፣ ሲልቨር ስፕሪንግ አውራጃ፣ አንዲት የስልክ መጠገኛ እና መሸጫ የሆነች የአገራችን ሰው ሱቅ ውስጥ ነበርኩ። ሁለት ቆነጃጅት “አይፎን ሊገዙ” መጡ። መግዛት ብቻ ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ “ለማስከፈት/Unlock ለማስደረግ” ነው አመጣጣቸው። አዲሱ “ኤይፎን 3” እንደወጣ ነበር። በትክክል ካስታወስኩ $ 600 ዶላር ያላቸው ይመስለኛል ሻጩ። ቆነጃጅቱ ተነጫነጩ። ግን አዲስ አበባ ቃል የገቡለት ሰው ሁነኛ ሰው ሳይሆንባቸው አልቀረም፣ እየተነጫነጩም ቢሆን ገዙት። ለራሳቸው የያዟት ግን ምስኪን ሳምሰንግ ነገር የደከመች ስልክ ናት። አዲስ አበባ ያለው ሰው ያንን ተቀብሎ ሲጠቀምባት፣ ከጉራው ባለፈ፣ የላኩለት ልጆች እነርሱም “አይፎን 3” የሚይዙ ይመስለው ይሆናል። አለማወቅ።

ያ አይፎን 3 ሲያስደንቀን ሲያስደምመን ቆይቶ፣ አይፎን 4፣ እርሱን ሳንጨርስ ደግሞ አይፎን 4S (iPhone 4S) መጣ። እንዲህ በየዓመቱ የሚያስደንቁ እና የዓለምን ሕዝብ የአኗኗር ዘዬ ቀይረዋል የተባሉ ግኝቶችን ያመረተው የስቲቭ ጆብስ ጭንቅላት ነበር። ስለ አይፎን ከተነሣ የፋርማሲ ተማሪ የሆኑ ወዳጆቼ የነገሩኝን ልንገራችሁ። የፋርማሲው የፒ.ኤች.ዲ ተማሪ እንደነገረኝ ከሆነ ለትምህርታቸው አስፈላጊ ናቸው ተብለው በዩኒቨርሲቲው ከተነገራቸው ነገር አንዱ አይፎን ነው። በስልክነቱ ሳይሆን ለሳይንሱ በመረጃ መዝገብነት በመጥቀሙ። ጥንት የመድኃኒት ዓይነት፣ ጥቅም እና ጉዳታቸውን በቶሎ ለማወቅ የኪስ መጽሐፍ ይዞ ይዞር የነበረ ዶክተርና ፋርማሲስት አሁን አይፎን ነው የሚይዘው። ያውም ጥቅሙ ከዚያ የኪስ መጽሐፍ በብዙ እጥፍ የሚበልጠውን አይፎንን። 


ለሰጠኝ ትልቅ ሰው እግዜር ይስጠውና ከአፕል ምርቶች በቅጡ ለመጠቀም ዕድል ያገኘኹት አይፓድን (iPad) ነው። በመጠኑ “አዲስ ጉዳይ መጽሔትን” ያክላል። ወይም ትንሽ ቢያንስ ነው። የሚገርም ግኝት ነው። ሲመጣ ባዶውን ነው። ተጠቃሚው እንደፈለገው ሊጠቀምበት የሚችል ድንቅ ፈጠራ ነው። እንዳበጁት የሚሆን፣ ዶክተሩ ለሕክምናው፣ መሐንዲሱ ለምህንድስናው፣ ሁሉም ሁሉም እንደሙያው ሌላው ቀርቶ ሕጻናቱ ለ“ጌም” እና ለደረጃቸው ለሚጠቅም ትምህርት የሚጠቀሙበት ሆኖ ነው ያገኘኹት። አንድ ችግር ያየሁበት አማርኛ መጻፍ ላይ እንደማንኛውም ኮምፒውተር ቀላል አለመሆኑ ነው።

እንግዲህ የስቲቭ ጃብስን ሞት የሰማኹት ለፈጠራቸው ግኝቶች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ይዤ ነው። በርግጥም ዓለማችን እንደ ጋሊሊዮ፣ እንደ ፎርድ፣ እንደ Thomas Alva Edison ወዘተ ወዘተ የሚቆጠር አንድ ትልቅ ሰው ማጣቷን የመገናኛ ብዙሃን እያነጻጸሩ ሲተነትኑ ነበር። በዕለቱ ማዘኔን የተመለከተው ወዳጄ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ “iSad” ሲል የውስጤን ገልጸታል። ቃሏ ፈገግም አድርጋኝ፣ ስሜቴንም ገልጻልኛለችና ርዕስ አድርጌያታለኹ።

ስቲቭ ጆብስ በወጣትነቷ ያረገዘችው እናቱ ማሳደግ ባለመቻሏ ለአሳዳጊ ሰጥታው በጉዲፈቻ ያደገ ልጅ ነበር። ነገር ግን አስተዳደጉ እዚህ ትልቅ ደረጃ ከመድረስ አላገደውም። ራሱ ከመሠረተው ኩባንያ ተባርሮ ነበር። በኋላ ግን ተመልሶ ከቀደመው የተሻለ ግኝት፣ የተሻለ ሥራ ለመሥራትና ስሙን ከመቃብር በላይ ለማድረግ አላገደውም። እጅግ በጣም ተቀናቃኝ ከሆኑት ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ማይክሮሶፍት ቢሆንም አብሮ ለመሥራት እና ወዳጅነት ለመመሥረት አላደገደውም። እንዲያውም ከተባረረበት በድጋሚ ወደ አፕል ሲመለስ የማይክሮሶፍት መሥራች እና የልጅነት ጓደኛው ቢል ጌትስን “አፕል” ላይ “ኢንቨስት” እንዲያደርግ በማሳመንና በማግባባት ተፎካካሪዎች ግን ወዳጆች መሆናቸውን፣ ተፎካካሪነት ጠላትነት አለመሆኑን አስመስክሯል። እንዲህ ላለው ሰው አንድ ጽሑፍ ማስታወሻም መታሰቢያም እንዲሆንለት ቢጻፍለት አያንስበትም። እንዲህ ዓይነት ሰው ገና በጎልማሳነቱ ሲሞት ደግሞ በርግጥም ያሳዝናል- iSad

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 
    

13 comments:

ርብቃ ከጀርመን said...

ነፍስይማር ብያለሁኝ በተረፈግን ብዙየማላውቀውን ነገር በደንብ አብራርተህ ስለገለጽከውና ለጠቅላላ እውቀት የሚሆን ነገር ስላካፈልከን እናመሰግናለን አንተንም እግዚያብሄርያጽናህ ጽሁፎችህ ወቅታዊና አለማችንን የሚዳስሱ ስለሆነ ደስይሉኛል በርታ!

Anonymous said...

ከጠቅላላ እውቀቴ ጭማሪ አግኝታለሁ፡፡ አንተንም እግዚአብሔር ያጽናህ እሱንም ነፍሱን ይማረው ፡፡

Anonymous said...

Nefs Yimar biyalehu, Ya it was very sad to loose this kind of person. Thank you for sharing this.

Anonymous said...

iSad too man

Anonymous said...

i sad too efrem nice one

Anonymous said...

Lol on your i Sad. Ababa

Anonymous said...

I like I sad'ን ababaye I like "i sad too"ንም and isad too guys. He already showed the worled everything is possible. and he did his job.

Anonymous said...

Selam Dn Ephrem,

Pls attache the Pdf format. We can't read it from anywhere.

Best regards

Yewudasse Abat said...

ስንት ሰው በቁሙ እየሞተ ሰርቶ ላለፈው ያን ያህል አትዘን፡፡

ባይሆን ነፍስ ይማር ነው የሚባለው፡፡ ነው ወይስ አሜሪካ ነፍስ ይማር አይባልም ?

Anonymous said...

You lamented for the Great. You knew well how he transformed the world dynamically.

I really like the lexicon "iSad". I wish if APPLE is gonna market a product in this word in memory of The Great Steve Jobs.

Why don't you contact APPLE for the idea if only it is yours.

Sincerely,

Anonymous said...

isad!

Anonymous said...

endazenku selazenk hazenh yegebagnal...beqerebu nebr sele esu tensh yemaqew negereochun sesema keleb azenku degageme face book lay eletef nebr ye esun negger ...yetredugn gin aymeslegnem nebr ...enem betam azegnalehu antem berta esu endalew..."Dont wory about me just continu fight my legacy..."....RIP steav jobs esty yehn semaw eferemhttp://www.youtube.com/watch?v=5-sV8tQPNxU ty

Anonymous said...

mazenes aygebahem Dn Ephrem