Monday, November 21, 2011

የአለንጋ ነገር

 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ OPEN IN PDF)
ቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ አንድ የተከበሩ ዳኛ ሰሞኑን የመገናኛ ብዙሃን ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ ሆነው ሰንብተዋል። ሰውዬው መነጋገሪያ ለመሆን የበቁት በሰጡት ፍርድ ወይም ባሳለፉት ውሳኔ ሳይሆን የ16 ዓመት ልጃቸውን በመግረፋቸው ምክንያት ነበር። ድርጊቱ የተፈጸመው የዛሬ ሰባት ዓመት ቢሆንም በስውር የተቀረጸው ቪዲዮ ግን ዩ-ቲዩብ ላይ የተለቀቀው አሁን በቅርቡ በመሆኑ ርእሰ ጉዳዩ ትኩስ ዜና ለመሆን በቅቷል። ነገሩ እንዲህ ነው። (WATCH THE VIDEO)የተከበሩ ዳኛ ዊሊያም አዳምስ ልጃቸውን በተደጋጋሚ ይገርፉ ኖሯል። ልጅት (ሒላሪ) በአባቷ ድርጊት በመማረሯ ካሜራ ደብቃ ታዘጋጃለች። ከዚያም ለሰባት ደቂቃ ያህል አባቷ እና እናቷ እየተፈራረቁ ሲገርፏት የሚያሳየውን ቪዲዮ ትቀርጻለች። አባቷ ዳኛ ዊሊያም አዳምስ በዚያን ቀን ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጊዜያት ይህን ድርጊት መፈጸማቸውን ልጅቷ ተናግራለች፤ እናም ይህን ቪዲዮ ለሰባት ዓመታት ደብቃ ካቆየች በኋላ ለዕይታ ታበቃዋለች። ቪዲዮው በተለቀቀ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተመልካች ከማግኘቱም በላይ በሕዝቡም ሆነ በሕግ አካላት ዘንድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ፈጥሯል፤ ሚዲያዎቹም እየደጋገሙ አራግበውታል።

ዜናው የደረሳቸው ቲቪዎች አባትን ሲያናግሩ የተሰጣቸው መልስ ልጃቸው ‹አልታዘዝ› በማለቷ፣ እና የእጅ ዓመልም ስላለባት "ልጄን ቀጥቻታለኹ" ሲሉ ልጅ በበኩሏ አባቷ "ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ጤናቸው የተጓደለ ሰው" መሆናቸውን ትናገራለች። አባት ያልተደሰቱበት የልጃቸው ጠባይ (የእጅ ዓመል ያሉት) ከኢንተርኔት ላይ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሙዚቃዎችን "ዳውንሎድ" እያደረገች መጠቀሟን ሲሆን ልጅ ደግሞ ጤንነታቸውን የተጠራጠረችው "የ16 ዓመት ኮረዳ በምን ገንዘቤ ልግዛ፣ ደግሞስ ይኼ ሁሉ አለንጋ ለምን?" በማለት ነው።

ይህን ተከትሎ የአሜሪካው ኅብረተሰብ ልጅን በመቅጣት ዙሪያ ሁልጊዜም የማይስማማበትን አጀንዳ ሲወቅጥ ከርሟል። "ልጅን መግረፍ ይገባል ወይስ አይገባም?" የሚለው የባጀ ውይይት ዳግመኛ ተቀስቅሶ ምልልሱ ቀጥሏል። በአብዛኛው እና በተለመደው አስተያየት "ልጅን መግረፍ ወንጀል ነው" የሚለው አስተያየት ሚዲያውም፣ ት/ቤቱም፣ ወላጁም የሚቀበለው ገዢው ሐሳብ ቢሆንም አንዳንድ ቤተሰቦች ግን "ልጆችን ገርፎ ማሳደግ ይገባል" የሚለውን አሁንም እንደያዙ ናቸው። በተለይም ሃይማኖታዊ ባህላቸውን በሚያጠብቁ የአሜሪካ ግዛቶች ያሉ ነዋሪዎች ልጅን ገርፎ ሥርዓት ማስያዝ ተገቢ ነው ባይ ናቸው።

ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች ታዳጊ አገሮች መጥተን እዚህ አሜሪካ ለምንኖር ሰዎች ልጅን መግረፍ የመሳሰለው ነገር አዲስ አይደለም። እንዲያውም አንዲት ልጅ ተገረፈች ተብሎ አገር በሙሉ ኡ ኡ ሲል ስንሰማ፣ "እነዚህ ሰዎች አሁንስ ቀበጡ" ዐይነት ስሜት ያድርብናል። "ታዲያ ወላጅ ልጁን ላይገርፍ ነው እንዴ?" ብለንም እናማርራለን። አንዳንድ ኢትዮጵያዊ ወላጅ አገር ቤት ባየው መልክ ልጁን ቆንጠጥም፣ ገረፍም ለማድረግ ሞክሮ ችግር የገጠመው መኖሩን ብዙ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለኹ። አባት/እናት ልጃቸውን ለመምታት ቀበቶ ይመዛሉ፤ ልጅ 911 ይደውላል ወይም ለአስተማሪው ይናገራል፤ በነጋታው የቤታቸው በር ሲንኳኳ እና የመንግሥት ጠያቂ ሲመጣባቸው ወላጆች ይኼ አገር ኢትዮጵያ አለመሆኑ ይገለጽላቸዋል።

አንድ አባት ነው አሉ። ልጁ እዚህ አሜሪካ በሚሠራው ነገር አንጀቱ ሲደብን ቆይቷል። እንዳይገርፈው አገሩ አሜሪካ ነው። ከዚያ ለዕረፍት ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ይዞት ይሄዳል። አባት በልቡ "መቼ ኢትዮጵያ በደረስኹና ንዴቴን በተወጣኹ" ብሏል ለካስ። ከዚያም እንዳይደርስ የለም አገር ቤት ሲገቡ ዘመዶቹንም ለመሳም ሳይሽቀዳደም የተጠራቀመ ቂሙን ሊወጣ ቀበቶውን ሳበ አሉ። እዚያ ማን ልጅህን ገረፍክ ብሎ ይከሰዋል።

ታሪኩ ኩሸትም፣ ግነትም ምናልባትም ፈጠራም አለበት። በመሠረተ ሐሳቡ ስናየው ግን ብዙ እውነት አለው። እኛ በቤትም፣ በት/ቤትም፣ በጎረቤትም፣ አንዳንዴ በመንገድ አላፊውም ስንኮረኮም፣ ስንገረፍ፣ ስንንበረከክ ስላደግን (corporal punishment እንዲል) መገረፍን የእንጀራ ያህል ለምደነዋል፤ እዚህ አገር ያለ ሕፃን እንኳን መገረፍ ድምፅን ከፍ አድርገው ሲቆጡት መዐት የወረደበት ይመስለዋል። አዬዬ ... እንዴት እንዳደግን ባወቅህ ከማለት ውጭ ምን ይባላል?

መጽሐፍ ቅዱስ "ሕፃንን ከመቅጣ ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና" (መጽሐፈ ምሳሌ 2313 ) እንዲል ልጅን ለአካላዊ ጉዳት ወይም ለሥነ ልቡናዊ ስብራት በማያበቃ መልክ መቅጣትን ብዙው ሕዝባችን የሚቀበለው እውነታ ነው። መጽናኛችንም "ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል።"(ምሳሌ 2917) የሚለው ቃል ነው።  ቅጣ ሲባል ግን በርበሬና ሚጥሚጣ በማጠን፣ ቢላዋ አግሎ በመጥበስ፣ በጉማሬ አለንጋ ጀርባ እስከሚጎብጥ መግረፍ መቅጣት ሳይሆን መግደል ነው። ልጃቸው ላይ እንዲህ ዓይነት መከራ እያወረዱ "ልጄን እየቀጣኹ ነው" ማለት አይገባም።  በተለይም ራሳቸውን ምንም መከላከል በማይችሉ ሕጻናት ላይ እንዲህ ዓይነቱን ነገር መፈጸም ሰብዓዊነት ማጣት ነው።

ከቤት ይልቅ በጣም ትዝ የሚለኝ የት/ቤት ቅጣታችን ነው። ነገሩ ከአስተማሪ አስተማሪ ቢለያይም መግረፍ፣ መኮርኮም፣ በጣት መካከል እርሳስ ወይም እስክሪብቶ አስገብቶ ጣትን መቀርጠፍ፣ እጅ በጉልበት ሥር አሳልፎ ጆሮ ማስያዝ የማይወድ አስተማሪ አላየኹም። ይህ እንግዲህ አፋቸው እንዳመጣላቸው ከሚሳደቡት ፀያፍ ስድብ ውጪ ማለት ነው።

አንደኛ ደረጃ በነበርንበት ጊዜ አስተማሪዎቻችን ከሚቀጡን ቅጣት ሁሉ በጣም የማልረሳው እጅ በእግሮች መካከል አሳልፎ ጆሮ ማስያዝን ነው። እንደዚያ የሚቀጣ ተማሪ ቅጣቱን ጨርሶ ሲነሣ ፊቱ በላብ ተደፍቆ፣ ወገቡ እና እግሮቹ፣ መላው አካሉ እየተንቀጠቀጠ ወደ ቦታው ሲመለስ በልጅነት አእምሯችን አሥቂኝ፣ አሁን ሳስበው ደግሞ አናዳጅ ነው። ብዙ ጊዜ ቀምሻታለኹ። በራሳችን እርሳስና እስክሪብቶ ጣታችንን እየጨፈለቁ የሚያስጮኹንም መምህራን አይረሱኝም።

ቅጣቱ አንደኛ ደረጃን አልፈን፣ መለስተኛውንም፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃውንም ስንዘልቀው አልለቀቀንም። እንደማስታውሰው የ9 ክፍል ተማሪ ሆነን፣ ለራሳችን ትልልቅ ሰዎች ሆነናል ብለን በምንጀነንበት ጊዜ እንኳን፣ ክፍል ሙሉ ተማሪ አስወጥተው በንብርክክ ክፍላችንን በጉልበታችን የሚያስዞሩ "ዩኒት ሊደሮች" ነበሩን። ብዙኀኑ የክፍል ተማሪ ፊት መመታት፣ መንጓጠጥ እና መሰደብ የተለመደ ክሥተት ነበር። እንዲህ ዐይነቱ ክብረ ነክ ነገር ዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆችም ድረስ ባሉ አስተማሪዎች የሚዘወተር ጠባይ ነበር። ተማሪውን በመልኩ፣ በአለባበሱ፣ በስሕተቱ ብሎም በአነጋገሩ መተቸት የተለመደ ነገር እንደነበር ትዝ ይለኛል። አስተማሪዎቹ ለምን እንደዚህ "መብት ገፋፊ" እንደሆኑ እግዜር ይወቀው።   

በጥንታዊው የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዐት ተማሪው መምህሩን እንደ ንጉሥ ብሎም እንደ አባት ሲያከብረው መምህሩ በፈንታው ተማሪውን እንደ ባሪያው ሳይሆን እንደ ልጁ ይመለከተው ነበር። ተማሪው "በዬኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር፣ በእኔ ጉሮሮ አጥንት ይሰንቀር፤ አንድ ቀለም የነገርህን እንደ አባትህ፣ ሁለት ቀለም የነገርህን እንደ ፈጣሪህ" እያለ እያሞካሸ ለመምህሩ ያለውን ፍቅር ሲገልጽ መምህሩም እንደ ተማሪው አብሮ የልመና ቁራሽ እየተካፈለ፣ ድህነቱን አብሮ እየገፋ ዕውቀቱን ሲመግበው ኖሯል።

ቅጣት ቢኖርም የሥራ ነበር እንጅ እንዲህ ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። ተማሪው ለመምህሩ ካለው ፍቅር የተነሣም ብዙዎች ትምህርታቸውን ፈጽመው ሲመረቁ በቀለም አባቶቻቸው ስም እስከ መጠራት ይደርሳሉ። በዘመናዊው መምህር ዘንድ ግን ተማሪውና አስተማሪው ዐይንና ናጫ፣ እሳትና ጭድ ሆነው ነው የማውቃቸው። ዘመናዊው ትውልድ ትኩረት ከማይሰጠው ጥንታዊ የትምህርት ዘይቤያችን ይህን መከባበሩን፣ መዋደዱን እንኳን ብንማር እንዴት ግሩም ነበረ።

ንግባአኬ ኀበ ጥንተ ነገር እንዲል ወደ ተማሪ እና አስተማሪ ግንኙነት የሳበን በቴክሳሱ ዳኛ የተነሣው የግርፊያ ጉዳይ በልጅነት የቀመስናትን ኩርኩም እና ግርፋት ትዝታ ጎትታ፣ በአሜሪካ "ደሞ በልጄ፣ ወልጄዋለኹ፣ ልጄ ነው፣ ማን ሊከለክለኝ" ብሎ አለንጋ ማንሣት ያለውን መዘዝ በመጠኑ ጠቅሰናል። በተለይም በአሜሪካ የሚኖረው የአገራችን ሰው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ከቀላል እየቆጠረው ብዙ ችግር እንደገጠመው ማወቁ ተገቢ ነው። የልጅቱ ግርፋት በኢንተርኔት እንደተለቀቀ ብዙ ሕዝብ የተመለከተው እና ለቴክሳስ መንግሥት የስልክ፣ የኢሜይል እና የሌሎች አቤቱታ ማቅረቢያ መንገዶችን ሁሉ የተጠቀመውን ያህል በእኛ ዐይነቱ ባህል ለኖረው ግን ብዙም የሚደንቅ ነገር አልነበረም።

ከእኛ ዐይነቱ ባህል ማለቴ በትንሹም በትልቁም እንኳን ሕፃኑ ዐዋቂው ጭምር የሚጎሸምበት ኅብረተሰብ ውስጥ የኖረ ሰው የ16 ዓመት ልጅ መገረፏን ከቁብ አይቆጥረውም። ጠዋት ነግቶ ከቤት ወጥተን ማታ መሽቶ ወደ ቤታችን እስክንከተት ድረስ ባለው አንድ ቀን ውስጥ በአካል ጉሸማም ይሁን በመጥፎ ቃላት ጉነጣ ስንገረፍ ስለምንውል እንዲህ ዓይነቱን የቤተሰብ ጉዳይ ብዙም አናስተውለውም። መብታቸው ሳይሸራረፍ በሚጠበቅላቸው ሕዝቦች መካከል ግን የአንዲት ኮረዳ መገረፍ አገራዊ ዜና ሆኖ ባለ ሥልጣናቱን ያነጋግራል።

የሌላው ሰው ክብር መደፈርን የራሱ መደፈር አድርጎ የሚቆጥር ሕዝብ "ነግበኔ" (ነገም በእኔ) ስለሚል "ምን አገባኝ፣ ከነገሩ ጦም እደሩ፣ ነገርን እና ቅምዝምዝን አጎንብሶ ነው" ብሎ ትከሻውን ለሸክም እና ጀርባውን ለግርፋት አያዘጋጅም። ምናልባት መደፈርን እና መገፋትን ብዙ ስለተለማመድነው ይመስለኛል ቆዳችን ደንድኖ "ትዕግሥተኛ መሳይ" ገባሮች የሆንነው። ከታክሲ ወያላ ጀምሮ፣ የሆስፒታልና መሰል ተቋማት ጥበቃዎችን ጨምሮ፣ የመንገድ ላይ ፖሊሶችን ይዞ በደረጃው እስከ ላይ ድረስ የሚገፉን ሰዎች መብዛት ተፈጥሯዊ እና ሰብአዊ መብት እና ክብር የሚለውን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋና ስጦታ እንድንረሳው አድርጎን ይሆናል እንጉርጉሯችን ጎመን በጤና የሆነው። በሌለ ጎመን።         

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 

8 comments:

Anonymous said...

Wow, I always say a little bit of girifat is fine but this one is too much. I can't hit my daughter like this. This is cruel. I couldn't even finish looking at this one. Thanks for sharing

Anonymous said...

በእውነት እኔ ግን እንደ ዱላ የሚያናድደኝ ነገር የለም፡፡ ሰው እኮ ሰው ነው ፡፡ እንስሳት እንኳ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ አላ
ቸው፡፡

Anonymous said...

" አስተማሪዎቹ ለምን እንደዚህ "መብት ገፋፊ" እንደሆኑ እግዜር ይወቀው።"
እንዴ ኤፍሬሜ ግልጽ እኮ ነው። ያልተዘራ ይብቅላል? እነሱም እንደ ጌሾ እየተወቀጡ፣ እንደ ተልባ ታምሰውና እንደ አህያ ተገጥበው ስላደጉ መልካም አድርገው ስለያዙት ነው። እኔማ የመጀመሪያ ትምህርቴን የተማርኩበት ት/ቤት የነበረው ስርዓት በዘር እንኳን ባይሆን በዱላ የአፓርታይድ ነበር ብል ማጋነን አይሆንም። እጅ በጆሮ ይዞ ቀመጫን መጠብጠብ፣ ግቢውን በእንብርክክ ማዳረስ፣ መንበርከክ፣ ዴስክ ላይ ለጥ ብሎ ተኝቶ ቀመጫንና ጀርባን ማስለብለብ፣ በማስመሪ ጠርዝ የእጅን አንጓ ቃ እያደረጉ መቀጣት እንደ እስፖርት ሆኖ ነበር። በጣም የሚገርመኝ የነበረው ግን መውገሪያውን ችንጋ ከየት እንደሚያመጡት ነበር። ከምር ይህን የሚያስታጥቃችው ተማሪን የማይወድ አካል ሳይኖር እንደማይቀ እጠረጥራለው (ምን አልባት ቅጥቀጣን በሚመለከት ከማዕከላዊም የሞያ አማካሪ ሳይኖራቸው አይቀርም)። አንዳንዱ ችንጋ ወይንም ጎማ እኮ ማጠሩ እንጂ ውፍረቱና ጥንካሬው መኪና ይጎትታል። ታዲያ ይህው እነሱ ወገቤን ቆርጠው የዘመኑን ኑሮ መሸከሚያ አሳጡኝ። ከምር የጀርባ መልኩ ያለመታየቱ እንጂ በቦንብ የተደበደበ ከተማ አስመስለውታል። ደግሞ ገራፊ ከገራፊ፣ ዱለኛ ከዱለኛ፣ ተደባዳቢ ከተደባዳቢ አስተማሪ መወዳደራችው ይግርማል። በድብደባ ተፈሪና ተከባሪ ለመሆን! አንዳንዴ ሳስበው ት/ቤት ሳይሆን የጣር አካዳሚ እንኳን እንዲህ አርጎ የሚቀጣበት አይመስለኝም። ደግሞ እኮ አንዱ ባጠፋ የክፍሉ ተማሪ ሁሉ እዳውን መብላቱ ነው። ከተለቀሰማ በቃ አለቀ! ምን ሆነህ ነው? ተብሎ የሚጨመረው ከዋናው ቅጣት ይባልጣል።.......... አቦ ሆድ አስባስከኝ

እስኪ ቸር አሰንብቶ ቸር ያሰማን።

Anonymous said...

Tinitawewu yehagerachin memihiranina temariwoch meseretumekebaber newu minalibatih man yawukal eniyan chekila yekolo temariwochimeko yewushawun nikishana erehab enidihum wererishignun enidichiluna enidiberetu yaderegachewu yeyeneta fitsim fikir newuna kezih bizu temirenal egnam lelijochachin letananashochachin fikirin binisetachewu enikuwan libelashu kegna yeteshale yemihon zega yemafirat enidil enagegnalen.....

Anonymous said...

I watched the video and read your article.

I am against improper punishment and agree with your opinion.

But I've never seen horrific beating by the Judge. He and his spouse repeatedly warned their daughter of rolling on and give her back and butt. This is a clear indication that how much they do care, love and have sympathy to the beloved daughter. What really astonished me is that they supposed to stem from very good religious background.

Nothing odd!! as the saying goes "no pain no gain" How can she be make turnaround from he wrong doings without proper advice and punishment before totally she reach the level of addiction.

For me this is a good lesson and awakening bell to those Ethiopians who are negligent and those who ignorantly blame child punishment as totally devastating and uncivilized.

A good Story

Thank you Ephrem

I apologize for commenting in English for I don't have compatible Amharic keyboarding for MAC.

Anonymous said...

እኛ ስንት ሸንበቆ ላያችን ላይ እንዳለቀ አላወቁም

Anonymous said...

Demissie
Ayeee Shenbeko Abayen yalaye minchi yadenkale ale yagere sewe.Anonymous dula ayewkume malete new. Enkuan beshenbko alefelote!!!!

Anonymous said...

Thank you for posting this video,

Most of us (Ethiopians) we passed through such kind of spanking, I would say in the past, it was the right thing to do, but now the way we teach our children is so different than then. The technology,knowledge, life style, culture, understanding, value of judgement... were helped us to understand in a better way.
I had been raised severe than the one seen in the above video, when I think of those days, I say my families had done for my good to disciplined me. I am thankful of them even if it was the challenging path. I would boldly say that is what it shaped me for my success in life.
If you ask me today, I will never and ever punish my two beautiful boys like this, instead we discuss what went wrong and establish boundary, and different techniques of teaching methods (with the help of God).
Up to now everything looks good. For the future God knows, I will pray every day for my children.
One last thing, the bible says to raise our children according to the word of God, so that when the grow up they will never walk away from it, so dear brothers please teach ur children the word of God.
Thank you all, I am sincerely apologize for using plain English, my computer doesn't have Amharic software.
Thank you all