Thursday, November 27, 2014

Thanksgiving የምሥጋና በዓል፣ በዓለ አኮቴት

 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ TO READ IN PDF)
ዛሬ “Thanksgiving” ላይ ቆሜ ስለዚህ በዓል ለብዙ ጊዜ ልጽፈበት እየፎከርኩ አለማድረጌን እየወቀስኩ ጥቂትም ቢሆን ልልበት ወሰንኩ። ምናልባት የፈረንጅ በዓል ስለሆነና ገና ስላልተዋሐደኝ ባዕድ ሆኖብኝ ይሆን እንጃ በተከታታይ ሦስት ዓመታት ብዕሬን አንስቼ ሳልፈጽመው ቀርቻለኹ። ዘንድሮስ አይሆንም ብያለኹ። በተለይ ለረዥም ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን በሐላፊነት ሲመሩ የነበሩትና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ “እኛ ልመና እንጂ ምስጋና አናውቅም፤ ማመስገን ያስፈልገናል” ይሉት የነበረው አባባላቸው የበለጠ አበረታቶኝ የግል ሐሳቤን ለመጠቆም ደፈርኩ።

“Thanksgiving” ወይም በአማርኛ “የምሥጋና በዓል” ወይም ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “በዓለ አኮቴት” ያሉት በዓል ከእንግሊዝ አገር በ17ኛው መ/ክ/ዘመን በስደት ወደ አሜሪካ የመጡ መጻተኛ እንግሊዞች ማክበር የጀመሩት፣ በፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን ብሔራዊ በዓል ተደርጎ የተደነገገ በኖቬምበር ወር በአራተኛው ሐሙስ ላይ የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ በተለያየ ዘመን በተለያዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ሲከበር ቆይቶ ከ1941 ጀምሮ የአሜሪካ ኮንግረስ የኖቬምበር  በአራተኛው ሐሙስ ብሔራዊ ክብረ በዓል ሆኖ እንዲከበር የወሰነበት በዓል ነው።

በዓሉ የቤተሰብ በዓል ነው። አዳሜ ተሰብስቦ “ተርኪ” የተባለውን ባለ ኩልኩልተ-ረጅም ዶሮ መሳይ ወፍ በማረድና በመጥበስ እንዲሁም በአንድ ገበታ ዙሪያ ተሰብስቦ በመመገብ ይከበራል። በዋዜማ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሁለት ተርኪዎችን ከመጠበስ ነጻ የመልቀቅ ሥርዓት የሚፈጽም ሲሆን ለሕዝቡም ንግግር ያደርጋል። በበነጋውም ሁሉም አሜሪካዊ እምነት ሳይለይ ፈጣሪውን ያመሰግናል። የተለየ የአንድ እምነት በዓል ባለመሆኑም አይሁዱም፣ ክርስቲያኑም፣ እምነት የለሹም፣ ሁሉም ሁሉም በየቤቱ ያከብረዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያኑን በተመለከተ በአዋቂዎቹ ዘንድ ሳይሆን እዚሁ አገር ተወልደው በሚያድጉ ልጆቻችን ዘንድ በዓሉ ትልቅ ትርጉም አለው። ወላጆች ግን ገና ና ፋሲካውን እንጂ እንዲህ ያለውን የፈረንጅ በዓል ከቁብ አንቆጥረውም። በተጨማሪም በዓሉ በአብዛኛው “የገና ጾም” ወይም ጾመ ነቢያት በምንው ጾም ላይ የሚውል በመሆኑ ብዙም ትኩረት አይደረግበትም። በተወሰኑ ዓመታት፣ ልክ እንደ ዘንድሮው ጾሙ ከመግባቱ በፊት ባለው ሐሙስ ላይ ይውላል። ምናልባት ያን ጊዜ የምግቡ ጉዳይ ይነሣ ይሆናል።

እኛ ኢትዮጵያውያኑ የምናመሰግንባቸው ብዙ በዓላት ቢኖሩንም በተለየ መልኩ “የምስጋና በዓል” የምንለው የተለየ በዓል የለንም። “ድሮስ በዓል ያለ ምስጋና ይከበራል ወይ?” ብሎ የሚጠይቅ ቢመጣ “አዎ በየበዓሎቻችን ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን” እላለኹ። በኦሪቱም ሕዝበ እስራኤል በዓለ ሠዊት (ዘኁ. 28፤26፣ ዘጸ. 34፤22) በሚባለው በዓል ሰብላቸውን ሰብስበው፣ አሥራቱን በኲራቱን ካስገቡ በኋላ ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ በዓለ መጸለት ወይም የዳስ በዓል (ዘሌ.23፤39-44) በሚባለው ደግሞ በየሰባት ዓመቱ አንድ ጊዜ ዳስ በመሥራት እና በዳስ ውስጥ በማደር ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበት እና በየመንገዱ ያደሩበትን እያከበሩ አምላካቸውን ያመሰግኑ ነበር በዚያ እኛም እንመስላቸዋለን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጸሎት ምሥጋና ዐቢይ ክፍል ነው። ወደ ቅዳሴ ከመግባቱ በፊት ካህኑ በሚያደርሰው “ወካዕበ ናስተበቊዕ ለንግሥተ ኲልነ” ብሎ ለእመቤታችን፣ ብሎም በጸሎተ ኪዳኑ “ለከ እግዚኦ ለገባሬ ኲሉ ለዘኢታስተርኢ አምላክ ንሰፍሕ ነፍሰነ። ወስብሐተ ዘነግህ ንፌኑ ለከ እግዚኦ ለጥበበ ኲሉ ሣህል አምላክ ሣራሪሃ ለነፍስ። ንሴብሐከ ለዘእምቅድመ ዓለም ተወልደ እምአብ፣ ቃል ዘበሐቲቱ በቅዱሳኒሁ ዕሩፍ፣ ኪያከ ዘትሴባሕ ስብሓታት ዘኢያረምም ወእምሠራዊተ ሊቃነ መላእክት። አቤቱ ሁሉን ለፈጠርህ ለማትመረመር አምላክ ለአንተ ሰውነታችንን እናስገዛለን፣ አቤቱ የነግህ ምስጋናንም እናቀርብልሃለን። የሁሉ ዕውቀት ኃያል የምትሆን፣ ይቅርታህ የበዛ አምላክ ነፍስን የፈጠርሃት፣ ከዓለም አስቀድሞ ከአብ የተወለድህ አንተን እናመሰግንሃለን” (ጸሎተ ኪዳን) እያለ ለጌታ ምሥጋናውን ያቀርባል። በቅዳሴውም “አእኲትዎ ለአምላክነ፣ አምላካችንን አመስግኑት” ሲል ሕዝቡ “ርቱዕ ይደሉ፤ እውነት ነው ይገባዋል” እያ በጋራ አምላካቸውን ያመሰግናሉ። ምሥጋና የእግዚአብሔር ሀብቱ ነውና እንኳን አስተዋይ አእምሮ ያለው ፍጥረት ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት ሳይቀሩ ያመሰግኑታል።

“የሦስቱ ልጆች መዝሙር” በሚለው ቅ/ገብርኤል ከእሳት ባዳናቸው ሕጻናት ጸሎት ላይ ዕጽዋት እና እንስሳት እንዲሁም ሌሎች ፍጥረታት በሙሉ እግዚአብሔር እንደሚመሰግኑ ተጽፏል። “እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ የተመሰገነ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ ያለ ነው” ካለ በኋላ ፍጥረታቱን ይዘረዝራል። እነርሱም፦
  • ፀሐይ ጨረቃ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣  
  • በሰማይ ያሉ ኮከቦች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
  • የበጎ ጠል የበጎ ዝናም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
  • ነፋሶች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል
  • እሳት ዋዕይ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     መዓልትና ሌሊት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣  
·                     የክፉ ጠል የክፉ ጤዛ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     ብርድ ውርጭ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     ብርሃን ጨለማ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣  
·                     ደጋ ቆላ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     በረድ ጉም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     መብረቅ ደመና እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     ምድር እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች
·                     ተራሮች ኮረብቶች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     በዚህ ዓለም የሚበቅሉ አትክልት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     ጥልቆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     ባሕር ፈሳሾች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     በውኃ ውስጥ የሚመላለስ ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     በሰማይ የሚበሩ ወፎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     አራዊት እንስሳት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     የአዳም ልጆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     እስራኤል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     እግዚአብሔር የሾማቸው ካህናት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     የእግዚአብሔር ባሪያዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     የጻድቃን ሰውነታቸውና ልናቸው እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
·                     የቀና ልቡና ያላቸው ጻድቃን … እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣ እርሱ የተመሰገነ ነው ለዘላለምም ከፍ ከፍ ያለ ነው ይላል (የሦስቱ ልጆች መዝሙር ቁጥር 27-83)በዚህ ዝርዝር ውስጥ ፀሐፊው ብዙ ነገሮችን እያነጻጸረ አቅርቧል። መዓልትን ከሌሊት፣ ደጋን ከቆላ ወዘተ ወዘተ። እያንዳንዳቸው ቢዘረዘሩ ብዙ ነገር ይወጣቸዋል። የተጋ አንባቢ “ሥነ ፍጥረት” የሚለው የሊቁን የሞገስ ዕቊበ ጊዮርጊስን መጽሐፍ ያንብብ።

እግዚአብሔርን ስለ መግቦቱ እና ጠብቆቱ ሁሉ እንዲህ እያመሰገንነው በጎ ያደረጉልንን ባለውለታዎቻችንንም ማመስገን ብንለምድ እንዴት መልካም ነበር። ከልጅነት ጀምሮ እስከ ዕውቀት በየሕይወታችን እርከን አሻራቸውን ጥለው ያለፉ ብዙ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች አሉ። በብዙው ሰው ዘንድ ወላጆችን ማመስገን፣ በተለይም እናትን ማመስገን፣ የተለመደ እና በየዘፈኑም በየእንጉርጉሮውም “እናቴ” እየተባለ የተነሣ ስለሆነ እዚህ መድገሙ መደረት ይሆናል። ከወላጆቻችን፣ እና ከቤት ቤተሰቦቻችን በተጨማሪ “እናመሰግናለን” ልንላቸው የሚገቡም ብዙ ናቸው። እንደ ባህል ሆኖ “እናመሰግናለን፣ አመሰግናለሁ” ማለትን አፋችን አልተለማመደውም። ውጪ አገር ከመጣን በኋላ በትንሹም በትልቁም “ቴንኪኪኪኪኪው” (ወንድ)፣ “ቴንኪውውውዉዉዉዉ” (ሴት) የሚሉንን እንደ “ፉገራ” የምንቆጥርበት አጋጣሚም እንዳለ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹን በአማርኛ አምተናቸዋል። ምክንያታችን “ለምዶባቸው እንጂ ከልባቸው አይደለም” የሚለው ነው። ቢሆንም አመሰግናለኹ ማለት ባይጠቅምም አይጎዳምና በጎ የሠሩልንን እናመስግን።

ወደ በዓሉ ስንመለስ፣ ይኼ በዓል በየዓመቱ መምጣቱ ካልቀረ፣ እኛም እዚህ መኖራችን ካልቀረ (ዕድሜ ይስጠንና)፣ እንዲህ ዝም ብለን ባናልፈው ጥሩ ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊ አድርገንም ቢሆን ማክበር ብንችል ጥሩ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ “የምስጋና” ቀን በመሆኑ በቤተሰብ በዓልነቱ ብንቀበለው እና ከቤተሰባችንና ከወዳጆቻችን ጋር ተደስተን ብናሳልፈው ግሩም ይሆናል። በተለይም በዚህ አገር ቤተሰብ የመሠረትን ሰዎች የልጆቻችንን ልብ እንገዛበት ይመስለኛል፣ እነርሱም በጓደኞቻቸው መካከል በኩራት የሚናገሩት የበዓል አከባበር ይሆንላቸዋል፣ በት/ቤትም “በዓሉን እንዴት አከበራችሁ?” ሲባሉ የሚመልሱት አይቸገሩም ብዬ አስባለሁ።

በጾሙ ወራትም ቢሆን ግሩም ግሩም “በየዓይነቱ” ምግቦቻችንን ከሽነን ኢትዮጵያዊ “ቬጂቴሪያን” (vegan thanksgiving) በዓል ብናደርገው ባህላቸው ላይ አንድ ቅመም ጨመርንላቸው ማለት አይደለም? እንደዚህ ዓመቱ ዓይነት ፍስክ ወቅት ሲሆን ምርጥ ዶሮ ወጥ፣ ወይም ቀይ ወጥ፣ ጥብሳ ጥብሱን፣ ድፎ ዳቦውን ወዘተ ወዘተውን አድርገን ልክ እንደ አገራችን ማንኛውም በዓል ብናከብረው “ኢትዮጵያዊ ታንክስጊቪንግ/ Ethiopian Thanksgiving” ተብሎ ይጠራልናል። አስቴር በቀለ (2010) የተባሉ ፀሐፊ “Ethiopian American Thanksgiving” ሽልማት ያስገኘ ጽሑፍ ነው ያሉትን ማንበብ ችዬ ነበር። እርሳቸው የምግቡን ዝርዝርም አቅርበዋል። ግሩም ነው። እንግዲህ እንዲህ እንዲህ እያልን ባህላችንንም ለሌሎቹ ማስተዋወቅ ብንችል መልካም ነው።

መልካም የምስጋና በዓል ይሁንላችሁ!
እግዚአብሔር ይመስገን
   

Originally posted on:
Date: 11/23/11 
Time: 9:37 PM
Pacific Standard Time

23 comments:

Anonymous said...

Kale hiwot yasemaln.Well said, we need to give dignity for our icons.As Daniel says earlier"eski enmesgagen".

Anonymous said...

http://www.danielkibret.com/2011/06/blog-post_707.html እና http://www.danielkibret.com/2011/06/blog-post.html

በጣም ደስ የሚል ሃሳብ ነው፡፡

getnet said...

arife hasabe gen endet ensu makebere endejemru bengern tiru nebre!!!

Anonymous said...

Thanks Dn/Efrem for sharing your information!!!!

Anonymous said...

አድናቂህና አክባሪህ ነኝ ስለዚሁ በዓል እንደው በኛ ምን ተጽፎል ብዬ ስፈልግ ነው ያንተን ብሎግ ላይ ጠቃሚ ሃሳቦችን ያገኘውት። ጥሩ ትመጣና ሰፋ አድረግህ አላቀረብከውም ለምሳሌ የበአሉ አከባበር ምን እንደሚመስል መቼና ለምን መከበር እንደተጀመረ ብትጽፍልን ጥሩ ነበር። በዓሉን ኢትዮጵያዊና ሐይማኖታዊ ልብስ ለማልበስ ያደረከው ጥረት አደንቃለሁ። ለማናናቸውም የክርስትና ሃይማኖት ከማልካም ባህሎች ጋር አይጋጭምና በጥሩ አቀማመጥ ስላስቀመጥከው አመሰግናለሁ። የጽሁፍ አድናቂ ከሃገረ አሜሪካ ጆርጅያ

Anonymous said...

በተጨማሪም በዓሉ በአብዛኛው “የገና ጾም” ወይም ጾመ ነቢያት በምንለው ጾም ላይ የሚውል በመሆኑ ብዙም ትኩረት አይደረግበትም። በተወሰኑ ዓመታት፣ ልክ እንደ ዘንድሮው ጾሙ ከመግባቱ በፊት ባለው ሐሙስ ላይ ይውላል። ምናልባት ያን ጊዜ የምግቡ ጉዳይ ይነሣ ይሆናል።በተጨማሪም በዓሉ በአብዛኛው “የገና ጾም” ወይም ጾመ ነቢያት በምንለው ጾም ላይ የሚውል በመሆኑ ብዙም ትኩረት አይደረግበትም። በተወሰኑ ዓመታት፣ ልክ እንደ ዘንድሮው ጾሙ ከመግባቱ በፊት ባለው ሐሙስ ላይ ይውላል። ምናልባት ያን ጊዜ የምግቡ ጉዳይ ይነሣ ይሆናል። ብለሃል በአንድ ቤተ ክርስቲያን ዕሁድ እለት ተገኝቼ ነበረ ይህ በዚህ በታንክስ ግቪንግ ቀን ጾም እንደሆነ ተናገሩና ቅዳሴም የአቡነ አረጋዊ ወርሃዊ ቀን በመሆኑ ከሰዓት እንደሚቀደስ በማስታወቂያ ተናገሩ አንተ ደግሞ ይህ ቀን ጾሙ ከመግባቱ በፊት ያለ ቀን መሆኑን ጻፍክ ታዲያ ወንድም ኤፍሬም ትክክሉ የቱ ነው። ጾሙ የሚገባው ሐሙስ ነው ወይስ አርብ እንደው ብዙዎቻችን እየተነጋገርንበት ያለ ጉዳይ ነው ስለበዓሉ ምንነትና አከባበር በሰጠህው ማብራሪያ አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው።ከዳላስ

Anonymous said...

እንዴ እነሱ ያንን እብድ እብድ የሚያሀል ዶሮ መሰል በግ ሲባሉ ምድረ ኢትዮጵያዊ የበይ ተመልካች ነው ነው የምትለን? አይመስለኝም። እነሱም ቢሆኑ የምስጋና ቀን ብለው ሆድ እስኪያብጥ ስበሉበት ነው የሚውሉ። በእውነት ጌታ በዚህ ይከብራል ተብሎ ይታሰባል? እንጃ። እኛ እናመስግን ካልን ያለን የባዓል ቀናት ከበቂ በላይ ነው። ይልቁን ሌላ ከመጨማመር ያለንን ብቅጡ ብንይዝ ይሻላል ባይ ነኝ።

በመጨረሻ ያልገባኝ ልጥቀስ ፦ "“ድሮስ በዓል ያለ ምስጋና ይከበራል ወይ?” ብሎ የሚጠይቅ ቢመጣ “አዎ በየበዓሎቻችን ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን” እላለኹ።"
አዎን በዓል ያለ ምስጋና ይከበራል ነው። ወይንስ አዎን በዓል ያለምስጋና አይከበርም ነው?

በርታ ቸር ይቆየን

Anonymous said...

"አይሁዱም፣ ክርስቲያኑም፣ እምነት የለሹም፣ ሁሉም ሁሉም በየቤቱ ያከብረዋል"
እስልምና ለምሳሌነት አይበቃም? or USA is the land of christians and jewish only.
pleas try to be fair and balance.

ማህደረ said...

I strongly disagree with you. The early colonists of New England regularly celebrated "Thanksgivings" after a military victory, end to a drought, or other "favorable" event. The Christian group known as the Separatists (later called Pilgrims) generally shunned holidays, but periodically proclaimed a Day of Thanksgiving and Praise in response to evidence of God's favor or a Day of Humiliation and Fasting in response to God's perceived displeasure. we /you should teach our children about the essence of being Ethiopian not about the feast of the then colonist power. To think like that , for me as a proud Ethiopian, is absurd."...እነርሱም በጓደኞቻቸው መካከል በኩራት የሚናገሩት የበዓል አከባበር ይሆንላቸዋል፣ በት/ቤትም “በዓሉን እንዴት አከበራችሁ?” ሲባሉ የሚመልሱት አይቸገሩም ብዬ አስባለሁ።" this statement really gave me a headache. if you want your children to dictate what is not theirs and loose what they have, then I have indeed overestimated you. If i am not mistaken, its you who preach us about being a proud Ethiopian. I am really confused and disappointed.
If you truly examine the meaning of this holiday, I am sure you wouldn't come to this conclusion. But then of course, much of the diaspora is going out of the lain. White America (I am not being racist) embraced Thanksgiving because a majority of that population glories in the fruits, if not the unpleasant details, of genocide and slavery and feels, on the whole, good about their heritage: a cornucopia of privilege and national power. Children are taught to identify with the good fortune of the Pilgrims. It does not much matter that the Native American and African holocausts that flowed from the feast at Plymouth are hidden from the children’s version of the story – kids learn soon enough that Indians were made scarce and Africans became enslaved. Is this what you are planing to teach your children? sorry for my harsh words.

Anonymous said...

Well done!

ኤፍሬም እሸቴ said...

ሁላችሁንም አመሰግናለሁ ስለ አስተያየታችሁ፤
ማህደረ ያሉት ላይ የተወሰኑ ሐሳቦች ላንሣ፦
1. ትክክል ነው ታሪኩ የተጀመረው እርስዎ ባሉት መልክ መሆኑን አንብቤያለሁ። ጅማሬው እርሱ ይሁን እንጂ መልኩን ቀይሮ አሁን ያለበት ደረጃ እና ዘይቤ ግን የተለየ እንደሆነ እረዳለሁ። ለዚህም ነው ብናከብረው እና የራሳችን መልክ ብንሰጠው ጥሩ ነው ያልኩት። ሕጻናቱ ጥሩ ጥሩውን ብቻ እየተማሩ “ቅኝ ገዢዎች በነባሩ ሕዝብ “ቀየ ሕንዶች” ላይ ያደረሱትን ሳይማሩ የሚያልፉ አይመስለኝም። አንደኛ ክፍል የሚማረው ልጄ በሕበረተሰብ ሳይንስ የሚማሩት ሲነገርኝ ሁሌም እገረማለሁ። ለ1ኛ ክፍል ጠጣር ታሪክ እንደሚነግሯቸው የተረዳኹት ከእርሱ ነው። “Children are taught to identify with the good fortune of the Pilgrims. It does not much matter that the Native American and African holocausts that flowed from the feast at Plymouth are hidden from the children’s version of the story – kids learn soon enough that Indians were made scarce and Africans became enslaved” ያሉትን ነጥብ መልሰው ይመልከቱት። ወይም ሰፋ አድርገው ያብራሩልን እና ሁላችንም እንማርበታለን።
2. ይህንን በዓል ማክበር “ኢትዮጵያዊነት”ን እና “ኩሩ ኢትዮጵያዊነትን” ይጋፋዋል ብዬ አላስብም። በዚሁ ግን ትልቅ ጥያቄ አነሱ። እዚህ አገር ለምናሳደጋቸው ልጆች የምናስተምራቸው “ማንነት” በእርግጥ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ልጅ ከሚማረው ጋር አንድ መሆን የለበትም። እዚህ በስደት ተወልደው የሚያድጉት ልጆች አሜሪካ ያለፈችበትን ማወቅ ግዴታቸው ነው። ዞሮ ዞሮ “ቁጥራቸው ከጥቁር” የሆነውን ኢትዮጵያውያን በዚሁ አገር የሚገጥማቸውን ፈተና የሚቋቋሙበት የዕውቀት መሣሪያ ካላስታጠቅናቸው ፈተናውን ለማለፍ እንደሚቸገሩ አያጠራጥርም።
3. "...እነርሱም በጓደኞቻቸው መካከል በኩራት የሚናገሩት የበዓል አከባበር ይሆንላቸዋል፣ በት/ቤትም “በዓሉን እንዴት አከበራችሁ?” ሲባሉ የሚመልሱት አይቸገሩም ብዬ አስባለሁ።" this statement really gave me a headache. ራስዎትን ሳይታመሙ እንወያይበት። እንማማርበት።
4. “sorry for my harsh words.” ችግር የለም። ውይይቱ ላይ ያተኩሩ።

ኤፍሬም እሸቴ said...

ከዳላስ ለጻፉት፦
ይህ የነቢያት ጾም/ ጾመ ስብከት መጀመሪያ ሁልጊዜም የኅዳር እኩሌታ(በ 15) ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ የኅዳር እኩሌታ ዛሬ አርብ ነው።

ኤፍሬም እሸቴ said...

November 24, 2011 3:14 PM ላይ ለጻፉት “አኖኒመስ”
በዚህ ጽሑፍ ላይ የጠቀስኩት በንባብ ያገኘኹትን እና እርግጠኛ የሆንኩበትን ነው። የእስልምና ተከታዮች ይህንን በዓል ያክብሩ አያክብሩ አላወቅኹም። እንዳሉት ትንሽ መቆፈር ይኖርብኝ ይሆናል። እርስዎም ከአስተያየትዎ ጋር በእምነታችሁ ታከብሩ አታከብሩ እንደሆነ ቢነግሩን ጥሩ ነበር። ይህንን አለመጥቀሴ ግን “እስልምና ለምሳሌነት አይበቃም? or USA is the land of christians and jewish only. pleas try to be fair and balance” ወዳሉት የሚያደርስዎት መሆን አይገባውም። እኔ ስለማውቀው ከጻፍኩ፣ እርስዎ የሚያውቁትን ከጨመሩበት፣ ብዙ ትምህርት አገኘን ማለት አይደለም? በዚያ ይረዱኝ።

Anonymous said...

i like your positve response.You are good intellectual

Anonymous said...

I am to late to read and comment, But, to early to give opinion and remind about how to celebrate next year.

That day I Questioned myself that This is really a very good culture in that all the children of God regardless of religious, social and political backgrounds, gather and Praise and give Adoration to The Almighty and enjoy themselves eating and drinking. Why We Ethiopians fail to do so. This is the only way we can get together and show up our oneness in diversity.

I wish if we are gonna celebrate Thanksgiving day without segregation next year? Is there any one who willingly take the initiative?

Thank you Ephrem

Anonymous said...

ኑሮ፣ መከራ፣ ስቃይ፣ ሌላም ተናግሬው የማልጨርሰው ምን የምንለው ነገር አለን ቅዱስ ጊዮርጊስ በዕለተ ቀኑ እሳት ያዝንብባቸው እባካችሁ ፀልዩ ኦ አምላኬ ሆይ አንተ ምህረቱን አውርድልን ይቅርበለን፣ እንደኛ ጥፋት ሳይሆን እንዳንተ ቸርነት ጠብቀን!!

w/micael said...

dear ephrem nice to meet you! I'm sami...you comment on comments of adebabay readers ..this makes your blog unique and clear according to others ..It is good, memihir dani kibret and others great blogers use your style!..specially D.dani must use it! most of the time i read un balanced and truthless coments on his blog,he must write aginest those bad coments!..i think you transfer my massage to beloved bloger dani..and others!
AMESEGINIHALEHU!!!!!!

Yohannes Mengistu said...

አቤቱ ሁሉን ለፈጠርህ ለማትመረመር አምላክ ለአንተ ሰውነታችንን እናስገዛለን፣ አቤቱ የነግህ ምስጋናንም እናቀርብልሃለን። የሁሉ ዕውቀት ኃያል የምትሆን፣ ይቅርታህ የበዛ አምላክ ነፍስን የፈጠርሃት፣ ከዓለም አስቀድሞ ከአብ የተወለድህ አንተን እናመሰግንሃለን” (ጸሎተ ኪዳን) እያለ ለጌታ ምሥጋናውን ያቀርባል።

Fayisa said...

Nice view. But if I am not mistaken we have already started the fasting period on Monday.

mieraf said...

ጥሩ መልዕክት ነው

mieraf said...

ጥሩ መልዕክት ነው

Anonymous said...

“እኛ ልመና እንጂ ምስጋና አናውቅም፤ ማመስገን ያስፈልገናል” እንዲህ እንዲህ እያደረግህ ልባችንን ወደ ተራራ ላይ አውጥተህ መልካም እንድናስብ ብታደርገን ጥሩ ልመናውም ቢሆን እንኳ ቅጥ ያለው ቢሆን ጥሩ ነበር ፡፡

Anonymous said...

Kalehywet yasmaln. Teru eyta new.

Blog Archive