Monday, December 5, 2011

ጫፍ እና ጫፍ

(ኤፍሬም እሸቴ/ READ IN PDF):-  Polarization (መወጠር ልበለው? ወይም ጫፍ እና ጫፍ መቆም?) የሚለው ቃል በአሜሪካ ሚዲያ ተደጋግመው ከሚጠሩት ቃላት እና ሐረጎች መካከል ተጠቃሽ ነው። አገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት እየመረመሩ ትርፍና ኪሳራውን ሌት-ተቀን፣ ሰባቱንም ቀን (24/7 እንደሚባለው) የሚያሰሉት ጋዜጠኞች እና ምሑራን ሁለቱንም የአገሪቱን ዐበይት ፓርቲዎች ማለትም ሪፐብሊካኑንም ዲሞክራቶቹንም የሚተቹት ፖለቲካውን ወጥረው ወጥረው ወደ ጫፍ፣ ወዳለመግባባት፣ ወዳለመቀራረብ፣ “ሰጥቶ መቀበል”ን ወደ መግፋት ወሰዱት  እያሉ ነው።

አሜሪካ እያፈራረቀች አንዴ ለሪፐብሊካን ፕሮዚዳንት እና ፓርላማ፣ አንዴም ለዲሞክራት ፕሬዚዳንት እና ፓርላማ፣ ሲፈልጋት ደግሞ ፕሬዚዳንቱን ዲሞክራት ታደርግና የፓርላማውን ወንበር አብዛኛውን ለሪፐብሊካን ስትሰጥ፣ ሲሻት ደግሞ ፕሮዚዳንቱ ሪፐብሊካን ሆኖ ፓርላማው ደግሞ በዲሞክራቶች ቊጥጥር ሥር ሲውል የኖረባት አገር ነች። እንዲህ በተለያዩ ፓርቲዎች የምትዘወር አገር ብትሆንም አገራቸውን በተመለከተ ሁነኛ ጉዳይ ላይ ግን የፓርቲ ማልያዎቻቸውን አውልቀው ለአገራቸው ብቻ እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሠሩባት አገር ናት። በአንዳንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ዳር እና ዳር ቆመው የነገር ድንጋይ ቢወራወሩም፣ በየአራት ዓመቱም “የእኛን ፓርቲ አባል ፕሬዚዳንት አድርጉ የእነርሱ አይረባም” እያሉ በነገር ቢሞሸላለቁም በአሜሪካ ጉዳይ ግን ሁሌም አንድ ናቸው። ምርጫው እና ክርክሩ ባለቀ ማግስት ተጨባብጠው ወንበር መለዋወጥ፣ “ይቅናህ፣ እንኳን ደስ ያለህ” መባባል ልምዳቸው ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ተቀራርቦ የመሥራቱ ልማድ እየደበዘዘ፣ መወጠር እየበዛ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና አስተሳሰቦች መካከል ያለው ሰጥቶ የመቀበል ዘይቤ እየቀረ መጥቷል እየተባለ ይተቻል። (አዬ፤ እኛን አላያችሁ።)

ይህ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ጦርነት በተለይም በወግ አጥባቂዎቹ እና በሊበራሎቹ መካከል ያለውን የልዩነት መስመር እያሰፋው በዚህም ምክንያት አገሪቱ በብዙ ጉዳዮች በመጎዳት ላይ እንዳለች ይተቻል። በወግ አጥባቂዎቹ አመለካከት ሊበራሎቹ “በሚፈጽሙት ባህልን እና አሜሪካዊነትን የመሸርሸር ሥራ አሜሪካዊ ማንነት አደጋ ላይ ወድቋል”፤ በሊበራሎቹ አመለካከት ደግሞ “በወግ አጥባቂዎቹ ወግ ጠራቂነት ምክንያት የአገር ኢኮኖሚ ወድሟል”፣ ለምሳሌነት ኢራቅ ላይ በጀመሩት ጦርነት ሰበብ የጠፋውን የገንዘብ መጠን ይዘረዝራሉ፤ ወግ አጥባቂነት “የአሜሪካ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ አገሮችን አሽሽቶብናል፣ የአናሳዎችን መብት ተጋፍቶብናል” ይላሉ። ሕዝቡ በበኩሉ “ሁለቱም ወገን እንዲህ የራሱን ሐሳብ እየዘረዘረ ከመቀራረብ ይልቅ እየተራራቀ፣ ተስማምቶ ካለመግባባት ይልቅ ላለመግባባት እየተስማማ አገራችንን አጠፏት” ሲል  ያማርራል። ዞሮ ዞሮ “ነገሩ ሁሉ ተወጠረ፣ ጫፍ እና ጫፍ ሆነ፣ ወደ መካከሉ የሚመጣ ጠፋ፣ ማዶ ለማዶ ሆነ” ነው።

እኔም ይህንኑ የውጠራ ነገር (Polarization) በኢትዮጵያዊኛና በኢትዮጵያዊነት አሰብኩት። ነገራችን ሁሉ የተወጠረ/polarized ሆኖ ተሰማኝ። ወዲያው መለስ ብዬ “ማሕበረሰባችን ከማንኛውም አፍሪካዊ እና ምናልባትም ከማንኛውም ድሀ አገር የተለየ ምን ውጥረት እና መወጠሪያ ይኖረዋልና ነው?” ብዬ ከራሴ ጋር ተሟገትኩ። ምናልባት በፖለቲካው ውስጥ በግራ እና በቀኝ ከቆሙት ነገር ወጣሪ ፖለቲከኞቻችን ውጪ ሌላው ሕዝብ ጥሩ ነው ብዬ የዋህ አስተያየት ለራሴ ሰጥቼ፣ በንግግሬ ተደስቼ ላቆም አልኩና ራሴን እየዋሸኹ እንደሆነ ስለታወቀኝ ከምር ይቺን ነገር አንድ ልበልባት ብዬ ገባሁበት።

በአገራችን አብዛኛው ወጣሪው በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት ፖለቲካውን የያዘው አንድ ትውልድ ብቻ የሚመስለው ብዙ ሰው አለ። ይኼ የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ የሞላው የወጣሪው ትውልድ ፖለቲካ አንድ ጊዜ የራሺያ፣ አንድ ጊዜ የአልባኒያ፣ አንድ ጊዜ የቻይና … ብቻ አገር እየቀያየረ “አይዲዮሎጂ” እየኮረጀ የአገሪቱን ሚዛናዊ የመቻቻል ባህል ሰብሮ ጫፍ እና ጫፍ ያስቆመ ነው፤ (ባለፈው በአንድ ጽሑፌ እንዳልኩት) “አቸነፈ እና አሸነፈ” የሚለውን ቃል አንዱ በ“ቸ” አንዱ በ“ሸ” መጻፉን ከቁም ነገር ቆጥሮት ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ያህል ሲጠፋፋ የኖረ ትውልድ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው። ያ ወጣሪ ትውልድ አሁንም በስተርጅናው መቀራረብን ሞቱ አድርጎት፣ እርሱን ያጠፋውን አይዲኦሎጂ በተሻለ መልኩ ለአዲስ ትውልድ አባላት የውጠራ ዘሩን እየዘራ ነው ተብሎ ይታማል።

እናም በፖለቲካችን ውስጥ ያለው ጫፍ እና ጫፍ የመቀመጥ ጉዳይ ከጊዜ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት እና እየተበላሸ መጥቷል። በሁሉም ወገን ያለው ወጣሪ የሚወደውን ክፍል መልአክ፣ የሚጠላውን ደግሞ ሰይጣን ዲያብሎስ አድርጎ ከመሳል ውጪ “የተለያየ ሐሳብ ያለን አንድ የአገር ዜጎች ነን” የሚል ጠብታ አስተያየትም አይሰማበትም። አንዱ ሌላውን በከሐዲነት፣ በአሸባሪነት፣ በከፋፋይነት (ሌሎች ብዙ መጥፎ ቃላትን አስቡ) እየከሰሰ መቀራረቢያ በሌለው መልክ ድልድዩን እያፈረሰው ነው። ሌላውም ዜጋ እንደየ አቅሙ አንዱን ወይም ሌላውን ደግፎ ለሚወደው የምስጋና ዘፈን (ቅንድቡ ያምራል እንዲል)፣ ለሚጠላው ደግሞ “አንገቱን በለው” ዓይነት ነጠላ ዜማ ይለቃል።

ፖለቲካውን ስመለከተው፣ ፖለቲከኞቻችን ጦርነትን መዋጋት እንጂ ሰላምን መኖር እንደማይችሉ ለራሴ ደምድሜያለኹ።  ፖለቲካችን “የጠላት ያለህ” ዓይነት ነው። ባህላችንም ጦርነትን ጥሩ አድርጎ ለሚዋጋው እንጂ ሰላሙን ጥሩ አድርጎ ለሚኖረው ክብር የለውም ይሆን?
“ገዳይ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል፣
ገዳይ ገዳይ ያልሽው ወንድምሽ አይገድል፣
አርሶ ያብላሽ እንጂ ከርስሽ እንዳይጎድል” ማለት ምን ማለት ነው? ገዳይነት (አንበሳም ይሁን አውራሪስ፣ ነብርም ይሁን ወራሪ ጠላት) ከእርሻና ከአራሽነት ይሻላል ማለት ነው? ወይስ መስሎኝ ነው? ለመግደልና ለመጋደልስ ቢሆን ከርስ ሲሞላ አይደል? ከአራሽነት ይልቅ ወታደርነት፣ ሞፈር ከመሸከም ይልቅ ጠመንዣ መሸከም፣ ነጋዴ ገንዘብ አገላባጭ፣ ቀጥቃጭ እንጨት ጠራቢ ከመሆን ይልቅ ሹመኛ ባለሥልጣን መሆን የበለጠ ሊያስከብር ይገባዋልን?

ደግሜ ደጋግሜ አንብቤ በማልጠግበው በ“መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ” መጽሐፍ (ገጽ 50) ውስጥ የተጠቀሰ ባሻ ወልደ ማርያም የሚባል አንድ ወታደር አለ። ያ ወታደር ስሙ “ወልደ ማርያም” በመሆኑ ይበሳጭ ነበር። የመበሳጨቱ ምክንያት ደግሞ “ጀግና ወታደር፣ ገዳይ ተጋዳይ ሆኜ ሳለ እናቴ የቄስ ስም፣ የ{ቆሎ} ተማሪ ስም ሰጠኝ፣ ነፍሷን አይማረው” ባይ ነው። ስሙ “ምታው፣ በላቸው፣ ሽናባቸው” ወዘተ ወዘተ የሚሉት ኃይልን ጉልበትን ወኔን እና ተዋጊነት የሚያሳዩ አለመሆናቸው በጣሙን አሳዝኖት ኖሯል።
የዘመናችንም ፖለቲካ በዚሁ በባሻ መንፈስ የተቃኘ አይመስላችሁም? ሰላም ሳይሆን ጦርነት የሚቀናቸው፣ ጦርነቶችን ጥሩ አድርገው የሚመሩ ሰላሙን ግን በአፍጢሙ የሚደፉ። ጦርነት ላይ በጽንዓት ቆመው ሰላምን ግን መቋቋም የሚያቅታቸው። የጦርነት ጀግኖች የሰላም ፈሪዎች። ጦርነት ከሌለ እረፍት የሚነሣቸው፣ እንደዚያ ጥጋበኛ ንጉሥ “ጦር አምጣ” እያሉ መሬት በአለንጋ የሚደበድቡ፤ ከዚህ ዓይነቱ ውጠራ የተገላገለና የራቀ አስተሳሰብ፣ ዳር እና ዳር ቆሞ መጓተት የሌለበት ለአገር የሚጠቅም አገራዊ ፖለቲካ በቅርብ ዘመን ለማየት የማይጓጓ ማን አለ? በቃ፣ ጫፍ እና ጫፍ/ ውጠራ የሌለበት።

ፖለቲካው እንዲህ ሳያምርበት (ከዚህ በፊት በአንድ ጽሑፍ ለማቅረብ እንደሞከርኩት) የሀብት ሚዛም እጅግ ከተወጠረ፣ የድሃውና የሀብታሙ ብዛት እየተራራቀ ከሄደ፣ ድልድይ የሚሆን መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ ቁጥር ካነሠ ሌላ “ውጠራ” መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በአዲስ አበባ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ችግር፣ ፈታኝ ከሚባሉ የከተማዋ ችግሮች መካከል” ነው ብለው አጠይመው የተናገሩትን ያጤኗል። በቀን አንድ ጊዜ መብላት በሚቸግርበት አገር የእንጀራ ጠርዝ እጃችንን ይቆርጠናል የሚሉ ዜጎች መብዛት ችግር ነው። የጥቂት ሰዎች ብቻ አለመጠን ባለጸጋ መሆን የአገር ዕድገት ምልክት ሳይሆን ያልተስተካከለ፣ ያልተመጣጠነ እና ሚዛናዊነት የጎደለው የሀብት ክፍፍል ምልክት በመሆኑ ዞሮ ዞሮ ማዕከላዊነት የሌለው እና ጫፍ እና ጫፍ የቆመ/ የተወጠረ ሕብረተሰብ ይፈጥራል።

በድህነት አረንቋ በሰጠመ ሕብረተሰብ መካከል በወርቅ በአልማዝ የተንቆጠቆጡ ጥቂት ሰዎች መኖር  የወርቅን ጥሩነት ከማሳየት ይልቅ የድህነትን አስከፊነት ያጎላዋል። በወርቁ ለመድመቅ፣ በገንዘቡ በቅንጦት ለመኖር፣ ብዙሃኑ ድሃ ሕዝብ ቢያንስ ቢያንስ በልቶ ማደር አለበት። አለበለዚያ ወርቁም አያደምቅ፣ ገንዘቡም አያቀናጣ። ስለዚህ ለድሃው-ለጉልበት የለሹ ተብሎም ባይሆን (ድሮስ ድሃ ማን ያዝንለታል) ለሀብታሙ- ሥልጣን ላለው ጉልበተኛ ሲባል (ሁሉን በእጁ ይዟልና) ለድሃው ወገን የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን መስጠት ይገባል።

ይቆየን።

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው  አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም። 


10 comments:

Anonymous said...

nice.good point.keep the good job.

Anonymous said...

some times you write as you know nothing, but this one has a point

Anonymous said...

ኤፍሬም ተው ሆድ አታስብሰን፡፡ እኛ እየኖርንበት እምምም እያኗኗርን...... ኧረ አሁንስ ከዚያም አልፋል እንኑር አንኑር አይታወቅም........ እውነቴን ነው እኮ፡፡ በአስማት መኖር ጀምረናል መሰለኝ፡፡

Anonymous said...

በቀን አንድ ጊዜ መብላት በሚቸግርበት አገር የእንጀራ ጠርዝ እጃችንን ይቆርጠናል የሚሉ ዜጎች መብዛት ችግር ነው።

Anonymous said...

POLETICA POLETICA MENE YESHALENAL YET NEW YEMENAREFEW?????????

kesis Sintayehu said...

Dn. Ephrem, thank you for the article. By the way could you say few points that have leading us to polarization? Does it have any relation with our upbringing? If we mention the political and social problems and find out the people who have created the problems, I doubt whether the problem will solved. But let us find good meanses that safeguard our generation from polarization. To do so, we, the church servants have great responsibilities. We have to start to think how we creat good citizens, who could work for humanity, but not for those whom the consider as "their" party.
Blessings.

Anonymous said...

በሀገራችን እንደ ዜጋ ሳይፈሩ ሀሳብን የመግለጵና በፖለቲካው አለም የመሳተፍ መብት የአንድ ጎሳ ብቻ በመሆኑ ያሳዝናል :: እኛ የትግራይ ተወላጅ ካልሆን ሁለተኛ ዜጋ እንጅ እንደ ዜጋ/በኢትዮጵያዊነታችን/ መብት የሚባል ነገር የለም እውነታው ይሄው ነው ቢሆንም ግን የትግራይን ህዝብ የማያካትት ኢትዮጵያዊነት የለም :: እንኳን የትግራይ ህዝብ የኤርትራም ህዝብ ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ እነሱም ያውቁታል እኛም እናውቀዋለን :: ዋናው ነጥብ ዘረኝነት እና ጎጠኝነት በቤተ ክህነት ውስጥ ሆነ በቤተ መንግስት ሊበቃ ይገባል ይሄ አስተሳሰብ ሀገራችንን ከፋፈላት ህዝብንም በጣም በጣም ለያየን ለዚህ ነው ነገራችን ሁሉ የተወጠረ/polarized ሆኖ የተሰማህ ::
ወንድሜ ኤፍሬም ይህንን የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መራራቅ ለመፍታት እንደዚህ አይነት የውይይት መደረኮች መፈጠራቸው ለመፍትሄው አንድ እርምጃ ጀምረናል እላለሁ በረታ ቀጥልበት ::
አምላከ እስራኤል ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይጠብቅልን በቃችሁ ይበለን
እግዚአብሄር ከሁላችን ጋር ይሁን !

Anonymous said...

Ephrem it is brillian, but where is your point on church polarization?
Could you think of few groups who are polarizing our EOC?
Thanks

Anonymous said...

Dkn Epherm menew sebket alko wode poletica? woynes menalebet poletikegna dkn behon? leante yetesetehn agelgelot atzenga. aydel ende? sele nefse madan ende dkn Estifanos tefaten. keholu yebeltalenna

Ephrem Eshete G. said...

Selam,
Sebketum alalke, poletikawem alteneka. "Yetesetehen atezenga" selalugn amesegenalehu. Leza meslogn metsafe ahun. yalechegn yechiw nat.