Monday, December 26, 2011

የአገር ናፍቆት

ይህንን ነገር እንድጽፍበት ካሰብኩ ቆይቻለኹ። መቸም ውጪ አገር ያለ ሰው በሙሉ በጋራ አንድ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የአገር ናፍቆት ነው። በቅርቡ ከአገሩ ከወጣው ጀምሮ 30 እና 40 ዘመን በሰው አገር እስከኖረው ሰው ድረስ አገሩን፣ ቀዬውን የማይናፍቅ የለም። እናም ጽሑፍ ጻፍ ሲባል በቶሎ የሚመጣለት ርዕስ ይኸው ነው የሚሆነው። እኔም ብዙ ጊዜ ነሽጦኝ ያውቃል። አሁን እንዳነሳው ያደረጉኝ ግን ሁለት አጋጣሚዎች ናቸው።

የመጀመሪያው አጋጣሚ ሰሞኑን ከኢራቅ ለአንዴም ለመጨረሻው እየተመለሱ ስላሉ ወታደሮች የአሜሪካ ዜና ዘገባ ሲቀርብ በቴሌቪዥን የተመለከትኹት ሲሆን በዜና ዘገባው ላይ አሜሪካውያኑ ወታደሮች ይጠየቁት የነበረው ጥያቄ “ናፍቆቱ እንዴት አረጋችሁ? ምንድነው ይናፍቃችሁ የነበረው?” የሚል ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ከአገሩ በቅርቡ የወጣው “አሸባሪው ወዳጄ” መስፍንነጋሽ “ኧረ አገሬ ናፈቀኝ” እያለ ሲያማርር በመስማቴ ነው። እና እኔም የራሴኑ ናፍቆት እንደ አዲስ እያስታወስኩ እህህህ ከማለቱ ጋር ሰው አገሩ ሲናፍቀው ምን ይሆናል? አገርስ ለምን ይናፍቃል? አገሬ ናፈቀኝ ሲባል ምኑ ነው የሚናፍቀው? የትኛው ነገር?” ለማለት ወደድኹ።

የአገር ናፍቆት ማለት ከአካባቢ ወይም ከቤተሰብ ወይም ከወዳጅ እና ይህንን ከመሳሰሉ ነገሮች በመለየት የሚፈጠር ስሜት ነው። ይህ ናፍቆት በሚሰማበት ጊዜ መንፈሳችን ብቻ ሳይሆን ሰውነታችንም መናፈቁን የሚያሳይባቸው ብዙ ምልክቶች አሉት። ኑሮን እስከ መሰልቸት እና ወደ ሥጋትና ከባድ የስሜት ዝቅጠት ውስጥ (anxiety and depression) እስከ መግባት ሊደርስ ይችላል። መጠኑ ግን ከሰው ሰው ይለያያል። አንዳንዱ ናፍቆት ሊውጠው ሲደርስ ሌላው ደግሞ የሆዱን በሆዱ ቻል አድርጎ ትንፍሽ ላይል ይችላል።  

የአገር ናፍቆት የሚፈጠረው የግድ እንደ እኛ ከሰው ባዳ፣ ከአገር ምድረ በዳ ብለው ሲሰደዱ ብቻ አይደለም። በአንድ አገርም እያሉ ከክፍለ ሀገር ክፍለ ሀገር በመራራቅ ሊሆን ይችላል፣ በሥራ ምክንያት ሌላ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች፣ ለትምህርት ብለው ከቤተሰብ እና ከአካባቢያቸው የሚርቁ ሁሉ መናፈቃቸው አይቀርም። በአንድ አውቶቡስ ብርርር ብለው ሄደው መገናኘት ከሚችሉት ጋር የእኛ ዓይነቱን መደበል ስለማይገባ አሁን የምጽፈው ውቅያኖስ አቋርጠው ርቀው ሲሄዱ ስላለው ስሜት ነው።

ጽሑፌን ለማብራራት ሳስብ ለመሆኑ እነዚህ ፈረንጆች ስለዚህ የአገር ናፍቆት ነገር ምን ብለው ይሆን (መቸም የማይሉት የለም) ብዬ ለማየት ሞከርኩ።  ከሆሜር “ዘ ኦዲሴይ” (The Odyssey) ጀምሮ ስለ አገር ናፍቆት ታሪኮች የጠቃቀሱባቸውን መጣጥፎች አየሁ። ኦዴሲየስ (Odysseus) አገሩ ናፍቆት ድንጋይ ላይ መሬት ላይ እየተንፈራፈረ ማልቀሱን የጠቀሱትን አገኘኹ። ከዚያም በላይ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ዮሐንስ ሆፈር (Johannes Hofer) የተባለ የስዊዝ ሐኪም ለሞት የሚያጣጥር ወጣት በሽተኛ አግኝቶ፣ በሽታውም ሌላ ሳይሆን የአገር ናፍቆት መሆኑን በመረዳቱ ወደ አገሩ እንዲሔድ እንዳደረገውና በሽተኛውም እንደተሻለው መዘገቡንም አነበብኹ።

አሜሪካ ላይ  ለመስፈር ከአውሮፓ የመጡ ስደተኞች ዋነኛ ችግር ይኸው የአገር ናፍቆት ጉዳይ እንደነበር፤ ነጻነት እና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ቢመጡም ልባቸው ወደተወለዱበት ቀዬ እየተመለሰ እንደረበሻቸው፤ ይህንንም በየደብዳቤዎቻቸው እና በግል ማስታወሻዎቻቸው ላይ መዝግበውት ማለፋቸውንም አየኹ። በሌላ ሥፍራ ደግሞ በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅትም ወታደሮች በናፍቆት ይቸገሩ እንደነበር ተጠቅሷል። ጦርነቱ አልፎ በሕይወት የተረፈው ወደ አካባቢው ሲመለስ እንደተሻላቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን ባቡሩንም፣ መኪናውንም፣ አውሮፕላኑንም፣ መርከቡንም መገንባትና ማስፋፋት ስለቻሉ ይህንን የሚያክል ትልቅ አህጉር እንደ አንዲት መንደር አድርገዋት እንደቻሉም ታትቷል።   


መጣጥፎቹ እንደሚያብራሩት ከአገር ናፍቆት ጋር በተገናኘ የሚሰሙ ስሜቶች “ለማየት መጓጓት (nostalgia)፣ ጥልቅ ሐዘን (grief)፣  ጭንቀት (depression)፣ የነፍስ መዛል (anxiety)፣  ሐዘን (sadness)፣ ራስን ማግለል (withdrawal) እና አካባቢን ለመላመድ መቸገር (adjustment disorders)” ናቸው። አገሩ የናፈቀው ሰው የሚወደው ሰው እንደሞተበትና ሐዘን ላይ እንዳለ ሰው ዓይነት ስሜት አለው። በትክክለኛ አማርኛ ተርጉሜያቸው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለኹም።    የሰው ልጅ በሚኖርበት አካባቢ የሚገነባው ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን ስሜትም ጭምር ነው። መንደሬ፣ ሰፈሬ፣ አገሬ በሚለው አካባቢ ያለው የሚታዩትም የማይታዩትም ነገሮች ናቸው በጅምላ እርሱነቱን የሚፈጥሩት። እነዚያን ነገሮች በሚያጣበት ወቅት ማንነቱ እና እርሱነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ርቆ ሄዶም ከሆነ መናፈቅ ይጀምራል። በ1977ቱ የመንደር ምሥረታ ወቅት ከየቀዬው የተፈናቀለው ገበሬ ከሰፈረበት ለም መሬት ይልቅ የጥንቱን ድንጋያማውን መንደሩን እየመረጠ የተመለሰው ወዶ ነውን? ለለምነቱማ አዲሱ አካባቢው ይሻለው አልነበረምን? ዬ ግን መቼ አፈሩ ብቻ ሆነና።አንድ ቀን እንዲሁ እንደሁላችንም በስደት ከሚኖር ኢትዮጵያዊ ጋር ወሬ ጀመርን። አያውቀኝም፣ አላውቀውም። ብቻ ስለአገር ናፍቆት አንስተን ስናወራ “እኔ አገር ቤቱን ብዙም አልናፍቅም” አለኝ። “እኔስ አገሬ በጣም ነው የሚናፍቀኝ” ስል መለስኩለት። “እንዴ፣ ቤተሰቦችህ እዚህ አይደሉም እንዴ?” ሲል በድጋሚ ጠየቀኝ። ወዲያው በኅሊናዬ “ቤተሰቦቼ፣ ዘመዶቼ” እዚህ ቢኖሩ ኖሮ አገሬ አይናፍቀኝም ነበር ማለት ነው ብዬ አሰብኩ። እንደሚናፍቀኝ እርግጠኛ ነበርኩ።አንዳንድ ኢትዮጵያውያን እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ ተሰብስበው በአሜሪካ የሚኖሩ አሉ። አንዱ ከመጣ በኋላ እስከ አያት ድረስ ያለው ዘር-ማንዘር በግብዣም በሌላ መንገድም እየመጡ አብረው ይኖራሉ። ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ አገራቸው እንደሚናፍቃቸው እገምታለዅ። ምክንያቱም አገሬ ናፈቀኝ ማለት እናት አባቴ፣ ዘመድ ወዳጆቼ ናፈቁኝ ማለት ብቻ አይደለምና። በመንገድ ላይ ላገኘኹት ኢትዮጵያዊ የመለስኩለትን አሳጥሬ ላጫውታችሁ።ቤተሰቦቼ ማለትም እናቴ፣ እህት ወንድሞቼ፣ አክስት አጎቶቼ፣ የአክስት አጎቶቼ ልጆችና ዘር  ማንዘራችን ወዘተ ወዘተ እዚህ የሉም። ቢኖሩም ግን አገሬ ይናፍቀኛል። ከአራት ኪሎ አካባቢ ግርግር ጀምሮ፣ የወያላው ድምጽ፣ በጠዋት የዶሮው ጩኸት ይናፍቀኛል። እዚህ አገር ዶሮ ሲጮህ ሰምቼ አላውቅም። ማንቂያ ደወል/ Alarm እና አምቡላንስ ካልሆነ በስተቀር። ድሮ ለማየት እንኳን የምሰቀቀው የሆለታ ጭቃ ሁሉ አሁን ትዝ ይለኛል። ከቤት ውስጥ ጓዳ ጎድጓዳው እስከ ውጪው ይናፍቃል።በተለይ ብዙ ኢትዮጵያዊ በማይኖርባቸው አካባቢዎች የሚኖር ስደተኛ ኢትዮጵያዊ የዘመዶቹ ወዳጆቹ ጎረቤቶቹ  መልክ ራሱ ይናፍቀዋል። ጠይም፣ ቀይ፣ ጥቁር፣ የቀይ ዳማ ፊቶች ማየት፤ በቅቤ ያበደ የሽሮ ሽታ፣ ወይም እጅ የሚያስቆረጥም ዶሮ ወጥ፣ የዶሮ ዓይን የመሰለ ጠላ ወይም ጠረጴዛ ላይ የተደፋ ካቲካላ፣ የተጎዘጎዘ ቄጤማ፣ ከዚያም ከጉዝጓዙ ላይ የሚነሣ የደረቅ ሣር ሽታ ይናፍቃል። በኖቬምበር 16/2001 ድሬስደን በምትባል የጀርመን ከተማ የጻፍኳትን “መልኬ ናፈቀኝ” የምትለዋን ግጥም ስታነቡ በምን ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኜ እንደጻፍኩት ትረዱልኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ። እኔን የመሰሉ ብዙዙዙዙዙ ሰዎች ናፍቀውኝ የጫርኳት ነበረች።ሰው ወደሌላ አገር ሲሔድ የመላመድ ችግር የሚገጥመው ይህ ሁሉ ትዝ እያለው ነው። እናም የአገር ናፍቆት ልክ እንደ በሽታ ናፋቂውን ይጎዳዋል። ወይም እንደእኔ ዓይነቱን ደግሞ የማይችለውን ግጥም ያጽፈዋል። ወይም ሲያስለቅሰው ያስውለዋል። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በየቀኑ አገራችንን ጥለን መኮብለላችንን ስለተያያዝነው በናፍቆት የሚጎሰመው በየቤቱ ሞልቷል። ዛሬ ዛሬ በስም የማናውቃቸው አገሮች ሳይቀር አንድ ኢትዮጵያዊ ማግኘት የተለመደ ሆኗል። ይኼ ኩሩ የነበረ ሕዝብ ዛሬ በየአገሩ እንደ ጨው ዘር ተበትኖ ማየት አንዳንድ ጊዜ ልብ ይሰብራል። … አገርስ ነበረን።ኢትዮጵያውያን በተለይም ከ1966 ዓ.ምሕረቱ አብዮት ወዲህ በብዛት እየፈለስን ነው። አሁንም ብሶበታል። (እንኳን ሕዝቡ የአገሪቱ ገንዘብም ስደት ላይ ያለ ይመስላል። ሰሞኑን ያነበብኩት አንድ ሪፖርት በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የአገሪቱ ገንዘብ በአገር ውስጥ ባንኮች ከመቀመጥ በውጪዎቹ ካዝና መኖርን መርጧል ይላል። ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ገንዘቡም ስደተኛ ሆኗል ማለት ነው።) የብሩን እንጃ እንጂ እኛስ አንድ ቀን እንመለስ ይሆናል። ልባችንማ ሁል ጊዜም ከአገር ቤት ነው። የሁል ጊዜ እንጉርጉሯችንም

 "Country Road Take me Home"

ያገሬ ጎዳና ውሰደኝ አርቀህ፤

እኔ በተጓዝኩት አንተ ምን ቸገረህ”

ዓይነት ነው፤ ወደ ቀዬያችን፣ ወደ አገራችን።

  

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።መልኬ ናፈቀኝ

እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው፤

መልኬ ነው ናፍቆቴ ጥቁሩን የቀይ ዳማን፣

ጠይም አሳ መሳይ ብስሉ ቀይ በርበሬን፣

ቸኮሌት መልክ ያለው የበሰለ ወይን፣

እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው።ክርድድ ያለ ፀጉር ልስልስ ያለ ሉጫ፣

ወተት መሳይ ጥርሶች፣

ቅልስልስ አንገቶች፣

የሚስቁ ዓይኖች፣

እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው።ደርባባ ቁመና ደርባባ አረማመድ፣

ደርዝ ያለው ፈገግታ ጥዑም አነጋገር፣

አፋራም እህቶች፣

ጎምላላ ወንድሞች፣

ቁምነገር አዋቂ የጨዋታ አባቶች፣

ቤተ መቅደስ ሳሚ ቆራቢ እናቶች፣

እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው።ነጭ የሕዝብ ባሕር ከሰለጠነበት፣

ካጥለቀለቀበት፣

የነፍስ ብቸኝነት ግዘፍ ከነሣበት፣

ከዚህኛው ሕይወት፣

እኔስ የናፈቀኝ ያነኛው ድህነት፣

የነፍሴ ጓዶቼ የሚፏልሉበት፣

እኔስ የናፈቀኝ መልኬ ነው መልኬ ነው።ሰው ነፍስና ሥጋ ሰው ውኃ ሰው አየር፣

ሰው እሳት ሰው አፈር፣

ሆኖ የሚኖርበት፣

መልክ ገጽ አካሌ የተቀረጸበት፣

ያኛው ቀዬ መንደር፣

ያኛው አገር ሰፈር፣

እሱኛው ሕይወቴ፣

እሱ ነው ናፍቆቴ። (ኖቬምበር 16/2001፤ ድሬስደን፤ ጀርመን)


11 comments:

Anonymous said...

‎''ጉድ አልኩ ይህን ካየሁ ዎዲህ ነዉ ያለዉ ፀሐይዬ ''
''እኔም ጉድ አልኩ ይህንን ከሰማሁ ዎዲህ ''
መቸም ኢንተርኔት የተራራቀን ያወራርባል ና እኔ ኑሮየ ከ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ በረጅም እርቀት ላይ ቢሆንም ከ ኢትዮጵያ ኤፍኤሞች አንዱ የሆነዉን በሸገር ኤፍም 102 1 ን ዓርብ ዓርብ የሚተላለፈዉን ዜናና ሸገር ሸለፍ እከታተላለሁ እደተለመደዉ ትናንት ዓርብ የመጀመሪያዉን ምእራፍ ዜና እየሰማሁ ነዉ ኮየት የቤት ሰራተኛ ከ ኢትዮጵያ ይብቃኘ እያለች እደሆነ ምክንያቱም ኢትዮጵያዉያኑ ከ 87 በላይ በሆኑ ዎጀሎች ዉስጥ እደገቡ እዳስቸገሮት እዲሁም ባለፈዉን 1 ኢትዮጵያዊ አሰረዋን አደገደለች
ከዚያም በማስከተል 2 ነህምያ እና አድሮስ የተባሉ (ሰዉ ነጋዴ)ኤጀንሲዎች ፍቃዳቸዉ በ ሰራተኛ ጉዳዮች ሚንስቲር እደተሰረዘ ምክንያቱም አድሮስ ህገዎት ሥራ እደሰራ መረጃ እደተገኘበት
ነህምያ ግን በ 1 ዓመት ጊዜ ዉስት ምንም ሰዉ ስላልላከ ፈቃዳቸዉ እደተሰረዘ
1 ኤጀንሲ አለ ዜናዉ በመቀጠል በ 1 ወር ከ 50 -60 ሰዉ መልአከ አለበት አለ ጉድ አልኩኝ ባለፈዉ አመተ 46 እደነበሩ አሁን 180 አደደረሰ ኤጀንሲዉን በዛት ገለጹ እስኪርብቶ አስቸ ማባዛት ጀመርኩ በ 1 አመተ የሚሄደዉን ሰዉ ብዛት አባዝቸ ስጭርስ ማመን አቃተኝ ዜናዉን አየደጋገምኩ 5 ገዜ ሰማሁት ያዉ ነዉ (የምሰማዉ በ አእንተርኔት ነዉ በያቸሆለሁ )
ጉድ አልኩኝ 1 ኤጀንሲ ባመት ከ 50 _ 60 ሰዉ መላክ ካለበት ባለፈዉ ዓመት ብቻ 45 ኤጀንሲዎች 27000 -32400 ሰዉ ልከዋል ማለት ነዉ በትንሹ
(የ ኤጀንሲዎቹን ብዛት 45 ያልኩት ነህምያ ምንም ስላልላከ ነዉ ) አሁንም ጉድ አልኩ
የባሰ አታምጣ !!! ለነገሩ ይቸ አገር ሰዉ አያስፈልጋትም እንዴ ? ብየ ሳልጨርስ ለካ የባሰ መጥቶል ከዚህም የባሰ አይመጣ አንጂ የ ኤጀንሲዎቹ (የሰዉ ነጋዴዎቹ )ብዛት በዚህ ዓመት ከ 100% በላይ አድጎ 180 ደርሶል ጉድ በል አግዲህ !!! ይህ ማለት በትንሹ በዚህ ዓመት ከ 108000 - 129600 በ ህጋዊ ተብየዎቹ ሰዉ ነጋዴ በኩል በቻ ይህንን ያክል አበሻ ይሰደዳል ማለት ነዉ ኤጀንሲዎቹ ደሞ በብዛት ዎደአረብ አገር ነዉ የሚልኩት ጉድ ጉድ ጉድ ጉድ ሰማሁ ዘድሮ
እራሳችአሁን አዳያማቸሁ ቀስ በላቸሁ አስኪ አስቡት በድቭ በ ፖለቲካ በትምህርት ለሰራ ለስብሰባ ሄዶ የሚከዳዉ በ እግር በመኪና በየ አቅጣቻዉ የሚተመዉ ቢደመር ስንት ሊደርስ ነዉ ከ ጉድም ጉድ ያሰኛል
ኧረ እዲዉ ለነገሩ የችን አገር ብቻዉን ሊቀመትባት አስቦ ይሄንን የሚሰራ ሰዉ(ቡድን :ድርጅት)ይኖር እንዴ ??? አላዉቅም ብቻ ግን ጉድ ነዉ ።
ምን ይሻል ይሆን ነብሩ አረንጎዴ ሰምያዊ ዎይነጠጅ ሳይሆን እደዛዉ እደተጉረዘረዘ እዚህ ደርሶል እኛ ስንት ጊዜ ተገለባበጥን ታመስን ምነዉ ሳንገላበት እዛዉ እርር ብለን ቀርተን ቢሆን
ይሻለን ነበር በኔ አስተያየት 1956 - 1966 ያለዉ ያ የተረገመ ዘመን ኢትዮጵያን በካሰር በማይድን በሸታ ላትድል የተለከፈችበት ዓመት የተረገ ይሁን !
ካመት አቆጣጠር የዎገድ መታሰብያለሁ አይኑረዉ ::
sofani19@gmail.com

keeme99@fastmail.fm said...

ያለሁት ሀገር ቤት ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሰደድ የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መውጣት ይፈልጋል፡፡ እንዴት ይህ ሁሉ ህዝብ ሀገሩ ላይ ተስፋ ይቆርጣል፤ ይገረማል፡፡ በአንድ IMRDበሚባል scholarship ካመለከቱት ውስጥ 34% የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ የጎሮቤታችን የኬንያ አመልካቾች ግን 3% ብቻ ናቸው፡፡ (http://www.imrd.ugent.be/userfiles/IMRD/files/20-12-2011.pdf )ታድያ ይህ እርግማን አይደለም ትላላችሁ… ሳስበው አንድ ቀን ይህቺ ሀገር ባዶዋን የምትቀር ይመስለኛል፡፡

Anonymous said...

awo enem yenafekeg hagre new ene yenafekeg Meleke new !!! wendem Eferem uuuuuu beye endalekes new yaderekeg enem yalut hulu keminafekebet """ Dresden Geremen """ selehone

ahuen ene yalubet semet tesemetok eziw Dresden endetafekew new yetesemag

AWO MELEKE HAGERE NAFEKEG !!!!!!!!!!

Anonymous said...

wndme dn efrem yhn thufn sanb betam new yegeremgn mikneyatum semonun betam agere nafkogn neber enam bizu zemedoch aluachew kemibalut wust negn agbche ena hulet lijoch welge ante bemtnorbet ager 10 amet norealehu endihum ke 30 amet befit yemetu zemedoch alugn gn man endeager amlak fekdo andken yeagerachn tnsa lemayet yabkan ena end esraealoch egnanm amalak yisebsben amlak betegana behaymanon yitebkh wndime dnk thuf new

Bisrat said...

Minim enkuan tsihufu des bilm hod yababal.
Ahun antes ketsafikew behuala min tesemah? Dn. Efrem

Anonymous said...

thank u ya egnas enemelesan. Agrachinen amelake kejibochi yetebekat

Anonymous said...

ለዚች አገር ህዝቦች ስደት ምክኒያት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ገዢዎቻቺን ናቸው ብየ አምናለሁ። እግዚኣብሄር ይይላችሁ።

Anonymous said...

ሰላም ኤፍሬሜ ... በጣም ልብ የሚመስጥ መጣጥፍ ነው። እኔማ ሀገሬ ሰላድር የቀረውበት ግዜ ትንሽ ነው። እንደው ለጥ ስል አይ እንደው እልም ወደ ኢትዮጵያ። አይ ሀገር!!! እንጃ መቼ እንደሚለቀኝ። ይኸው ከአገሬ ከወጣው አስራ አምስት ዓመት ነገ ይሆነኛል ---ያስደነግጣል አይደል?! አይዞን ትደርስበታለህ። የእነዚህ የነጮች ቀን ሲሄድ አይጣል ነው --- እንደ ባቡራቸው። ኧረ እንደው ይቅር። ናፍቆት ትዝታ በጣም ነው የሚረብሸው --- በተለይ ደግሞ ደግ ወሬ መጥፋቱ። እንደው እንኳ ለማጽናኛ።
በል እስኪ በጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ ግጥም ልሰነባበት፦
"ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ፤
ሀገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ?
አዎን ይናፍቃል ሀገርም እንደሰው፤
ትዝታው በዓይን ላይ የሚመላለሰው።"

እርሱ መህሪ አምላክ ሀገራችንን ከምናየውና ከምንሰማው ክፉ ነገር ይጥብቅልን። አሜን።

Anonymous said...

EPHRI TNX TO WRITE THIS ..I EXPECT IT IS ONLY FOR ME ..I GET STRESSED..BUT NOW IT IS OKAY...I HAVE TO COMPLETE MY MISSION THAT IS EDUCATION HERE IN FINLAND

yibeltal said...

ኢትዮጵያውያን በተለይም ከ1966 ዓ.ምሕረቱ አብዮት ወዲህ በብዛት እየፈለስን ነው። አሁንም ብሶበታል። (እንኳን ሕዝቡ የአገሪቱ ገንዘብም ስደት ላይ ያለ ይመስላል። ሰሞኑን ያነበብኩት አንድ ሪፖርት በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የአገሪቱ ገንዘብ በአገር ውስጥ ባንኮች ከመቀመጥ በውጪዎቹ ካዝና መኖርን መርጧል ይላል። ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ገንዘቡም ስደተኛ ሆኗል ማለት ነው።) የብሩን እንጃ እንጂ እኛስ አንድ ቀን እንመለስ ይሆናል። ልባችንማ ሁል ጊዜም ከአገር ቤት ነው። Egziabher yibarkeh Tiru argeh geletsehwal Hezbuanem habetuanem Eyasededut new Egzabeher yifaredachew!!! Ethiopia lezelalem tinur

lily said...

ababaye ye ewnet nafkot yasamimal ene erasu bekirbu new yagegemikut gin ahunm alekekegnim. be..ta..m new yeminafkew kakimh belay yihonal alikiseh ayiwetalh bereh mehed atichil mekera new eko endew.ewnet ewnet yamal lezawm betam