Thursday, December 29, 2011

የሰው አገሩ - ምግባሩ

ይህ ጽሑፍ ለብፁዕ አቡነ አብርሃም ሽኝት ለተዘጋጀ መጽሔት ተጻፈ እና እዚያም ላይ የወጣ ነው።
(ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ):- አበው ሲተርቱ “የሰው አገሩ - ምግባሩ” ይላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ካስቀመጥነው “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል” (“መጽሐፈ ምሳሌ221) ወይም በሌላ ሥፍራ “መልካም ሽቱ መልካም ስም … ይሻላል” (መጽሐፈ መክብብ 7፤1) ካለው ጋር አንድ ነው። መልካም ስም እና ምግባር የተባሉት ሁለቱ ቃላት በአነጋገር የተለያዩ በመንፈስ ግን አንድነት ያላቸው አገላለጾች ናቸው። ምግባር ከአገር፣ መልካም ስምም ከመልካም ሽቱ እና ከብዙ ባለ ጠግነት እንደሚበልጥ ተገልጿል።
ምግባር ከአገር ይበልጣል ማለት ጥሩ ምግባር ላለው ሰው የሔደበት ሁሉ አገሩ፣ አብሮ የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ ዘመዱ፣ የሚያድርበት ሁሉ ቤቱ ነው። ምክያቱም ተግባሩ ጥሩ ነውና። እንኳን በክርስትና በማንኛውም ኑሮ ውስጥ ሁሉ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ትልቅ ትርጉም አለው። ታሪክ እንደሚነግረን የተለያዩ ምግባረ ሠናይ ለመፈጸም ከአገራቸው ወጥተው በሰው አገር ኖረው ያንን የኖሩበትን አገር አገራቸው፣ ሕዝቡን ሕዝባቸው ያደረጉ ብዙ ሰዎች አሉ። በክርስትና ደግሞ ይህ የበለጠ ትርጉም አለው።
እስክንድርያን ያስተማረው ቅዱስ ማርቆስ የግብጽን ምድር ከመርገጡ በፊት ምንም የሚያውቀው ሰው አልነበረም። በእምነትም ቢሆን ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች አልነበሩበትም። ነገር ግን እግዚአብሔርን ይዞ፣ ለእጁ በትር ለእግሩ ጫማ ሳይሻ የወጣው ሐዋርያ ሀገረ-ምስርን አጥምቆ የታላላቆች አበው መፍለቂያ የበረሃ ገነት አደረጋት። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መንበርም እስከዛሬ “መንበረ ማርቆስ” በመባል ይታወቃል።
ክህነትን እና ምሥጢራትን መፈጸምን ያስተማሩን እና ጵጵስናን ወደ አገራችን ያመጡት ሶርያውያን ወንድማማቾች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ምንም ዘመድ አልነበራቸውም። ኢትዮጵያ በክብር ተቀብላ ካስተናገደቻቸው በኋላ ግን አገሩ አገራቸው፣ ሕዝቡም ሕዝባቸው ሆነ። ከዚያም አልፎ ፍሬምናጦስ ከሳቴ ብርሃን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነ። በኢትዮጵያም የወንጌልን ብርሃን አበራ።
ከእርሱም ቀጥሎ ከተለያዩ አገሮች በተዋሕዶ እምነታቸው ምክንያተ ተሰደው ወደ ኢተዮጵያ የመጡት ታላላቅ አበው ተሰዓቱ ቅዱሳን በዘር ኢትዮጵያውያን ባይሆኑም በተግባር ግን የሃይማኖት አባቶቻችን፣ ብርሃን ፈንጣቂዎቻችን፣ ገዳማዊ ሥርዓትን አስተማሪዎቻችን በመሆናቸው እስከዛሬም ሲከበሩ፣ ሲወደሱ ይኖራሉ። እንዲያውም እንደ አቡነ አረጋዊና አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያሉት አባቶች በዘር ኢትዮጵያዊ አለመሆናቸውን የሚያውቀው ሰው ቁጥር ብዙም ላይሆን ይችላል። የሰው አገሩ ምግባሩ ነውና።
ከእነርሱም በኋላ ቁጥራቸው ከ300 የማያንሱ እና በደምሳሳው “ቅዱሳን” የሚባሉ እና ከተለያዩ አገሮች የመጡ አባቶች በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ኖረው፣ አስተምረው አልፈዋል። ባይወለዱበትም አገራቸው ሆኗል። ሕዝቡም እንደራሱ ተቀብሏቸዋል። የሰው አገሩ ምግባሩ።
ከፍ ብለን እንደጠቀስናቸው አበው ሁሉ ብፁዕ አቡነ አብርሃምም በአሜሪካ አጭር ጊዜ ቆይታቸው አገሩን አገራቸው፣ ሕዝቡንም ሕዝባቸው አድርገው በተለይም ከምእመኑ ፍቅርን፣ መከበርን እና አባትነትን አትርፈዋል። የአበው ተረት በእርግጥም በትክክል ለእርሳቸው ይሠራል - የሰው አገሩ ምግባሩ ያሉት።  ሰው በተግባሩ ይመሰገናል፣ በተግባሩም ይወቀሳል። ከብፁዕነታቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የዲሲ እና አካባቢውን ሀ/ስብከት በሕጋዊ መሠረት ላይ እንዲቀመጥ ማድረጋቸውን በትልቅ ከበሬታ እመለከተዋለኹ። የአገሩ ሕግ እና አስተዳደር በሚፈቅደው መንገድ የሀገረ ስብከቱ አገልግሎት መስመር እንዲይዝ አድርገዋል። ከእርሳቸው በኋላ የሚመጡ አበውም ማረፊያ እንዲኖራቸው ትልቅ መስዋዕትነት ከከፈሉ ምዕመናን ጋር በመሆን እና በማስተባበር መንበረ ጵጵስናውን ግሩም አድርገው መሥርተዋል። ከምእመናን ቤት ወደ ምእመናን ቤት በመንከራተት፣ አንድ ማረፊያ በማጣት የተቸገሩ አበውን ጊዜ መደምደሚያ አበጅተውለታል።
ብፁዕነታቸው በአሜሪካ አገልግሎታቸው ከጀመሩ ወዲህ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር እና አንድነት በማጠናከር በኩል ወደኋላ ሊመለስና ሊቀለበስ የማይችል የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ፈጥረዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአሜሪካ ለተመሠረቱ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በሥርዓት መቋቋም “ክሬዲቱን” ለብፁዕነታቸው እሰጣለኹ። “ሁሉም ያው ነው” የሚለውን ሥርዓት አልበኝነት አስወጥተው በአንዲት እምነት በአንዲት አስተዳደር መሥራትን በተግባር ፈር ቀደዋል። ከዚሀ አንጻር ነው በአሜሪካ የሚኖረው ምእመን በትልቅ አድናቆት የሚመለከታቸው። ሌሎችም ከብፁዕነታቸው ምግባር ብዙ ነገር ሊማሩ ይችላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ። ሰውን ለማስደሰት ሳይሆን እግዚአብሔርን ለማስደሰት፣ የሰውን ቃል ለመፈጸም ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ለማስፈጸም የሚቆሙ በሙሉ እንዲህ ይከበራሉ።
ብፁዕ አባታችን፦ ረዥም ዕድሜ፣ ከጤና እና ከመልካም አገልግሎት ጋር ያድሎት ዘንድ ምኞቴም ጸሎቴም ነው።  


9 comments:

Anonymous said...

Kale Hiwot Yasemalen Wondimachen Dn Ephrem! Le Bitsue Abatachenem behedubet yehen habt yatsenalachew.

Anonymous said...

ቃለሕይወት ያሰማልን ኤፍሬም። አባታችንንም በዕድሜ በጤና ይጠብቅልን፤ ቀሪ አገልግሎታቸውን አብዝቶ ይባርክልን።

Anonymous said...

tikikil

ZERAYAKOB YIHUN said...

"ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ሳውቃቸው :
(http://www.danielkibret.com/)
አናጺ ሆነው መንበር እየሠሩ፤ እንደ ልብስ ሰፊ መጋረጃ እያዘጋጁ፣ እንደ አካውንታት ሂሳብ እየሠሩ፣ እንደ ፕሮግራም መሪ ገንዘብ እንዲዋጣ እያደረጉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፡፡ የአሜሪካ አውሮፕላን ማረፊያዎች ጳጳሳትን ሲፈትሹ ክብር በሚነካ ሁኔታ ነው፡፡ ይህንን የፈታሾች ሥርዓት አልበኛነት ሊታገሡት ባለመቻላቸው የአንድ ቀን መንገድ ያህል በመኪና እየተጓዙ ነው አያሌ ሥራዎችን ያከናወኑት፡፡
ሁሌም የማደንቀው አንድ አመለካከት አላቸው የተሻለ ሃሳብ ያመጣ ያሸንፋቸዋል፡፡
የሚሠራ ሰው ካገኙ ሥልጣናቸውን ጭምር ለዚያ ሰው ለማስረከብ ምንም አይቆጫቸውም፡፡ "
ብሎ ፅፎላቸዋል ዳኒ።

Ameha said...

ዲ/ን ኤፍሬም! ይቅርታ፡ይደረግልኝና፡ስለ፡አቡነ፡አብርሃም፡የምትሰጡት፡አስተያየ፡ሁሉ፡በጣም፡የተጋነነ፡ነው። ከዲሲ፡እና፡አካባቢው፡እሳቸው፡የሚያስተዳድሩት፡ቤተ፡ ክርስትያን፡ውስጥ፡ይገለገል፡የነበረው፡ምእመን፡ከ100፡አይበልጥም፡ነበር።

Anonymous said...

ዲ/ን ኤፍሬም! ይቅርታ፡ይደረግልኝና፡ስለ፡አቡነ፡አብርሃም፡የምትሰጡት፡አስተያየ፡ሁሉ፡በጣም፡የተጋነነ፡ነው። ከዲሲ፡እና፡አካባቢው፡እሳቸው፡የሚያስተዳድሩት፡ቤተ፡ ክርስትያን፡ውስጥ፡ይገለገል፡የነበረው፡ምእመን፡ከ100፡አይበልጥም፡ነበር።
I agree with this bilachihu bilachihu Ende Abune Paulos Hawult litakomulachew Yimeslal.
Yilik Tseliyulachew!!!!!!!!!!!!!!!!!!

Anonymous said...

እኛ ሐረሮች ታድለናል!!ፈቃዱ ቢሆን…..

Anonymous said...

የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ!!!
"ከፍ ብለን እንደጠቀስናቸው አበው ሁሉ ብፁዕ አቡነ አብርሃምም በአሜሪካ አጭር ጊዜ ቆይታቸው አገሩን አገራቸው፣ ሕዝቡንም ሕዝባቸው አድርገው በተለይም ከምእመኑ ፍቅርን፣ መከበርን እና አባትነትን አትርፈዋል። የአበው ተረት በእርግጥም በትክክል ለእርሳቸው ይሠራል - የሰው አገሩ ምግባሩ ያሉት።"
የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ ይላል ያገሬ ሰው
በመጀመሪያ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ ያውም ጥንት የነበረውን ቤተክርስቲያን በመክፈል ለሾሟቸው ፖትሪያሪክ ዳይናስቲ ከማስፋፋት በስተቀር አገሩን አገራቸው፣ ሕዝቡንም ሕዝባቸው አድርገው ከኢትዮጵያውያን ውጭ ላሉ ዜጎች ተዋህዶን ሲያስፋፉ አልታዩም ስደተኛውን ከማሳደድ ያለፈ ነገር የለም ታዲያ ለምን ከነ አቡነ አረጋይ እና ከነ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ጋር ማመሳሰል ለምን አስፈለገ???ከንቱ ውዳሴ ከመባል ያለፈ ምንም ማለት አይቻልም
ብፁዕ አቡነ አብርሃም እንደ አቡነ ይስሀቅ ዘምእራብ ጃማይካወችንና አሜሪካኖችን አስተምረው አጥምቀው ቢሆን እንኳ መልካም ነበር እንዲሁ አላስፈላጊ ገድለ አቡነ አብርሃም መደለዝ ክርስቲያንዊ ስነምግባር አይደለም በተለይ ከአንተ አልጠብቀውም ::
"ብፁዕነታቸው በአሜሪካ አገልግሎታቸው ከጀመሩ ወዲህ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር እና አንድነት በማጠናከር በኩል ወደኋላ ሊመለስና ሊቀለበስ የማይችል የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ፈጥረዋል።"
ይሄ ደግሞ በጣም ይገርማል የቤተክርስቲያናችንን ትምህርት ያላወቁ ወይንም የራሳቸው የፖለቲካ አዥንዳ ያላቸው የሚያደርጉትን ከማደረግ ውጭ ስለቤተክርስቲያን አንድነት ሰሩ ከምትለኝ ወደኋላ ሊመለስና ሊቀለበስ የማይችል ልዩነት ፈጥረው ሂደዋል ብትለኝ ለንግባባ እንችላለን በቀረውስ ወንድሜ ዲ/ን ኤፍሬም የዘመናችን አባቶቻችንን ከጳድቃንና ከሰማእታቶች ጋር ማወዳደሩ አግባብ አይደለም ለወደፊቱም ቢሆን አይደገም ውዳሴ ከንቱ ያጠፋል እንጅ አያድንም ገድልም የሚጳፈው ካረፉ በኌላ እንጅ በህይወት እያሉ እንዳለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምራናለችና ዲ/ን ኤፍሬም በፈጠረሁ አምላክ ከህሊናዎት ጋር ይነጋገሩና ያስተካክሉ እላለሁ ::

yenealem said...

"ሁሌም የማደንቀው አንድ አመለካከት አላቸው የተሻለ ሃሳብ ያመጣ ያሸንፋቸዋል፡፡
የሚሠራ ሰው ካገኙ ሥልጣናቸውን ጭምር ለዚያ ሰው ለማስረከብ ምንም አይቆጫቸውም፡፡ "