ቢጫ ወባ፣ “ሻምበል ደቤ” እና ዱካክ
ይህ መጣጥፍ በአንድ የታሪክ ወቅት በነበርን ተማሪዎች ገጠመኝ ዙሪያ በማጠንጠን የዛሬ 20 ዓመት ወደ ብላቴ የጦር ካምፕ ያደረግነውን ጉዞ፣ የገጠመንን ገጠመኝ፣ እግዚአብሔር ያደረግልንን ውለታ የምንዘክርበት ይሆናል፤ በወቅቱ በዚያ የጦር ካምፕ የነበሩ ተማሪዎችን ትዝታ ከራሴው ጋር ጨምሬ ለማቅረብ እሞክራለኹ ባልኩት መሠረት የሚከተል አምስተኛ ክፍል ዝግጅት ነው። አስቀድመው ግን ከክፍል አንድ እስከ አራት ያሉትን ማንበብ አይርሱ።
-----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ዘንግቼ አልፌው የነበረ እና አንድ ወንድሜ ያስታወሰኝን የ1983 ዓ.ም የስቅለት በዓል ጉዳይ ላካፍላችሁ። ልክ እንደ 1984 ዓ.ምሕረቱ የሚያዚያ 16 ዕለተ ኪ/ምህረት ስቅለት፤ እንደ 1997 ዓ.ም ሚያዚያ 21፣ እንደ 1999 ዓ.ም መጋቢት 28 የአማኑኤል ቀን፣ እንዲሁም በጻድቁ አቡነ ተ/ሃይማኖት ቀን እንደዋለው የመጋቢት 24/2002 ዓ.ም ስቅለት የዚያን ዓመት፣ የ1983 ዓ.ምሕረቱ በዓለ ስቅለት ደግሞ የዋለው መጋቢት 27 ቀን የመድኃኔ ዓለም ዕለት ነበር። በሃያ ሰባት እንደመዋሉ አንዳንዱ "እንስገድ" ሲል ሌላው ደግሞ “አይ፣ መሰገድ የለበትም፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይከለክላል” ይላል። አንዳንዱ ደግሞ “ግዴለም ከወገባችን ብቻ ጎንበስ ጎንበስ እያልን እናስበው” ይላል። ክርክሩ ቀጠለ። በቦታው ሊቅ የለም። ሊቃውንትም የሉም። ተማሪው ከተገናኘ ገና ሳምንቱ ነው። እርስበርሱ የሚተዋወቀው ጥቂቱ ነው። እናም ክርክሩ ጊዜ ወሰደ። በመጨረሻ ግን መሰገድ እንዳለበት ያብራሩት ወንድሞች ሐሳብ ተቀባይነት ኖሮት ዕለቱን ስንሰግድ ዋልን።
