Monday, December 24, 2012

የዛሬ አበባዎች (ኤፍሬም እሸቴ/PDF)፦ ልጅነት የንጽሕና እና የንፁህ ልብ ዕድሜ ዘመን እንደሆነ በሁሉም ሰው፣ በሁሉም ባህልና እምነት ይታመናል። ይህ እውነት መሆኑን ወላጅ የሆነ ሰው ወይም ለሕጻናት ቅርበት ያለው ሰው  ጥናትም ባያደርግ ይረዳዋል። ሁላችንም በልጅነት ዕድሜ ስላለፍን በርግጥም እኛም ምስክሮች ነን። በዚህ የማርነት፣ የጣፋጭነት፣ የረዳት የለሽነት ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ችግር ሲገጥማቸው ታዲያ አንጀት ይበላሉ። ሳቃቸው በለቅሶ፣ ፈገግታቸው በዕንባ ሲተካ ማየት የሰውን አንጀት ይበላል። ሰሞኑን በአሜሪካ የተፈጸመው የሕጻናት የጅምላ ጭፍጨፋ ዓይነት ሲከሰትማ ከኅሊና በላይ ይሆናል። “ምን ባጠፉ፣ በምን በደላቸው?” ያሰኛል። ሌላም ብዙ ጥያቄ እንድንጠይቅ ያደርገናል። ስለራሳችን፣ ስለ አገራችንም እንድናስብ ያደርገናል።

Tuesday, December 18, 2012

አደናቃፊ እና ተደናቃፊ


“መንገድ ስትሄድ፣ ድንጋይ (እንቅፋት) ቢመታህ፤ ምንም አይደል። ድንጋይነቱ አይለወጥም፣ አንተም ሰውነትህ አይለወጥም። ያው ድንጋይ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ቢመታህ ግን፣ ድንጋዩ ማነው? መታሰቢያነቱ - አንድ ስሕተት ደግመው ደግመው ለሚሠሩ በሙሉ፤ ያውም ታሪካዊ ስሕተት።”  ብዬ መፈላሰም አማረኝ!!!!!

የሚያስታርቁ ብፁዓን ከሆኑ - የሚታረቁትስ? (ኤፍሬም እሸቴ - PDF)፦ የተረጋጋ ባሕር። ማዕበል የሌለበት። እንዋኝህ ቢሉበት፣ በጀልባ ቢንሸራሸሩበት፣ አሣ ቢያሰግሩበት፣ ቢዝናኑበት … የሚመች …። እንደ ስምጥ ሸለቆ ኃይቆቻችን ያለ … የሰፋ፣ የሰከነ፣ የተረጋጋ፣ የተንጣለለ ውኃ። የረጋ ሕይወት፣ የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንደዚያ ነው። …

በጥንታውያን ገዳማውያን አበው ታሪክ ከተጻፉ ታዋቂ ምሳሌዎች አንዱ በረጋ ውኃ ተመስሎ ይነገራል። ከዕለታት በአንዱ ቀን፣ አንዱ ወጣኒ ገዳማዊ (ጀማሪና ተማሪ የገዳም ሰው) ምክር ፍለጋ ወደ አንዱ አረጋዊ አባት ዘንድ ሄደ። የተማሪው ጥያቄ “ውስጤ ተረጋግቶ በገዳም መኖር የምችለው፣ በጎውንና ክፉውን መለየት የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ነበር። አረጋዊው መምህር መልሱን በተግባር  ሊያሳዩት ፈለጉ። እናም ውኃ የተቀመጠበት ሰፊ ሳፋ መሳይ ነገር አቅርበው ራሱን ውኃው ውስጥ እንዲመለከት አዘዙት። ነገር ግን ሳፋውን በጃቸው እየናጡ ውኃውን ያነቃንቁት ነበር። ጀማሪው ገዳማዊ በጠራው ውኃ ውስጥ የተሰባበረ የራሱን ፊት ተመለከተ።

Monday, December 10, 2012

ሦስቱ ባዶ ወንበሮች (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ወንበር እና ዙፋን ብዙ መገለጫ አለው። ወንበር ሲባል ሁላችን ራሳችንን የምናሳርፍበት ማንኛውም መቀመጫ ማለት መሆኑ እንዳለ ሆኖ “ወንበር” ብዙ አንድምታ እንዳለው እናውቃለን።

ለምሳሌ ፍርድ ቤት ገብተን “የግራ ወንበር፤ የቀኝ ወንበር” ሲባል ብንሰማ ትርጉሙ “የግራ ዳኛ፣ የቀኝ ዳኛ” መሆኑ ይከሰትልናል። ምናልባት ወደ አብነት ት/ቤት (ቆሎ ት/ቤት) ጎራ ብለን “ወንበር ተዘርግቷል፤ ወንበር ታጥፏል” ሲባል ብንሰማ “ትምህርት ተጀምሯል፣ ትምህርቱ ተጠናቋል” ማለት ነው። “እገሌ ወንበር ተከለ” ከተባለ ደግሞ “መምህር ሆነ፣ አንድ የትምህርት ዘረፍ ለማስተማር ጀመረ” ማለት ይሆናል። ሥልጣን ባለበት አካባቢ “እገሌ የእገሌን ወንበር ይፈልጋል” ከተባለ …. ያው … ሥልጣንም ከሆነች፣ ኃላፊነትም ከሆነች … ሊቀማ የተዘጋጀ አለ ማለት ነው።

Monday, November 26, 2012

ከአብዮት ፍንዳታ እስከ ዘመነ “ፍንዳታ”(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ በንጉሠ ነገሥት የምትመራዋ ኢትዮጵያ ዘውዷን አፍርሳ፣ አልጋ አስገልብጣ፣ ንጉሥ አስገድላ፣ ሚኒስትር አስረሽና፣ ወጣት አሰድዳ ከምሥራቁ ካምፕ ከገባች እነሆ 40 ‘ዘበን’ ሆናት። የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ ማለት ነው። በነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ ያለፉ፣ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደየማንነታቸው አንዱን ዘመን ከአንዱ እያነጻጸሩ እንደሚያመሰግኑትና እንደሚረግሙት ሁሉ አንዱን ትውልድም ከአንዱ እያነጻጸሩና እያወዳደሩ አንዱን ያሞግሳሉ ሌላውን ያኮስሳሉ። አንዱን በትጋቱ፣ ሌላውን በሥራ-ፈትነቱ፤ አንዱን ለአገር በመሞቱ፣ ሌላውን በራስ-ወዳድነቱ ያነሱታል። እንዲህ መነጻጸሩ ካልቀረ መጠነኛ ሐሳብ ብናክልበትስ?

የጋዜጠኛ ዋጋው ስንት ነው?

  • መታሰቢያነቱ፦ ለታላቁ ጋዜጠኛ ለደምሴ ዳምጤ

(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ሬዲዮ የብዙ ኢትዮጵያውያን ባለውለታ ነው። ምንም ይሰማበት ምን፣ የትኛውም ጣቢያ ይሰማበት የትኛው፣ ከየትንንሽ መንደሮቻችን እና ከተሞቻችን፣ ጎጆዎቻችን እና ሕንጻዎቻችን አውጥተው ወዳላየነው እና ወደማናውቀው አዲስ ዓለም እና አዲስ ሐሳብ በምናብ የሚያደርሱን የልቡናዎቻችን አክናፋት ሬዲዮኖች ናቸው። በዚያም ውስጥ ዕውቀታቸውን በዘባነ-ድምጽ (በድምጽ ትከሻ) ጭነው፣ በሬዲዮ ቧንቧ የሚያንቆረቁሩልን እና በድምጻቸው ብዕር ዕውቀት በልቡናችን የሚጽፉት ጋዜጠኞችም እንዲሁ ትልቅ ባለውለታዎቻችን ናቸው። ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲል ተረታችን፣ “ኮከብ እምኮከብ ይኼይስ ክብሩ፤ ከአንዱ ኮከብ ክብር የአንዱ ኮከብ ክብር ይበልጣል” እንዳለው ቅዱስ መጽሐፍ ከአንዱ የሬዲዮ ጣቢያ ሌላኛው፣ ከአንዱ ጋዜጠኛም ሌላኛው ጋዜጠኛ፣ ከአንዱ ደራሲም ሌላኛው በማይረሳ መልኩ ተለይቶና ልቆ ይወጣል።

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 2012 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ልክ እንደ ዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ “ልብ አንጠልጣይ” ሆኖ አለፈ። ከአንድ ዓመት በላይ ሲካሄድ የነበረው “የምረጡኝ ዘመቻ”ም ዕልባት አገኘ። ግማሽ አሜሪካ (50%) ፕሬዚዳንት ኦባማን በድጋሚ መረጠች። ግማሽ አሜሪካ (48%) ደግሞ ሚት ራምኒ እንዲመራት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። በቃላት ሲጠዛጠዙ የከረሙት ተወዳዳሪዎችም በመጨረሻ ተመሰጋገኑ። ራምኒም ለኦባማ መልካም ዕድል ተመኙ። እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ሊጸልዩም ቃል ገቡ።

የእርቅና የሰላም አየር - በሰሜን አሜሪካ(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሕይወት ውስጥ የተለየ ሥፍራ ይዞ የመጣ ዓመት ነው። ላለፉት 20 ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቱን በፓትርያርክነት ሲመሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አርፈው መንበሩ ባዶ መሆኑን ተከትሎ ብዙ ጥያቄዎች መነሣት ጀምረዋል። ከነዚህ ጥያቄዎች አንዱ ደግሞ በተለይም በዚህ በምኖርበት በሰሜን አሜሪካ ያሉትን አራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን የጨመረ “እርቅ እና ሰላም” የሚደረግበት ሁኔታ ነው። ይህ ጽሑፍ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያጠነጥን ስለሆነ “ቤተ ክርስቲያን” የሚለው በዚህ ማዕቀፍ ብቻ እንዲታይ በማስታወስ ልቀጥል።

እናት ተፈጥሮ ስትቆጣ(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ “ሒዩሪኬን/Hurricane ሳንዲ” ጉዳችንን አፈላችው እኮ ጃል ሦስት ቀን በቤታችን ተዘግተን ከረምን። መውጣት የለ፤ መግባት የለ። ጥርቅምቅም ሆነ ነገሩ ሁሉ። በመስኮታችን ወደ ውጪ ስንመለከት ያለው የንፋስ ሽውታ እና የዝናብ ውሽንፍር ወደ ሲዖል መሔጃ መንገድ እንጂ የሰፈራችን ደጃፍ አይመስልም።

Wednesday, November 7, 2012

አንድ ማስታወሻ ለጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ (መስፍን ነጋሽ/ለ - adebabay.com/ PDF)፦ በእኔ እድሜ የደምሴን ያህል አገራዊ የስፖርት ስሜትን፣ በተለይ እግር ኳስን ወደ ልባችን ያቀረበ ጋዜጠኛ አልነበረም። እንደዛሬው ኢንተርኔት መገልበጥ ማእረግ በማያሰጥበት ዘመን። በሳምንት ሁለትና ሦስት ቀን ስታዲየም በምገባበት፣ ሁለቱን ሙሉጌታዎች፣ እነሚሊዮን በጋሻውን፣ እነቸርኬን (ጊዮርጊስ) እነሙሉዓለም እጅጉን (ጦሩ) እነአብዲን (ድን) እነአፈወርቅን (እርሻ) ደሞ የአየር ኀይሉ አጥቂ ማን ነበር? ... ረሳሁት ማለት ነው? (ይልቅ ተከላካያቸው መሰለ፣ ጆን ቴሪን ቁጭ ነበር) ከዛ ደሞ ... ይህ ሁሉ ሲሆን ብቸኛው የስፖርት መረጃ ምንጫችን ደምሴ ነበር፤ እርግጥ ሌሎችም ጋዜጠኞች ነበሩ በተለይ እነ ... ማነው ... ይንበርበሩ መሰለኝ። ቢሆንም ደምሴ የተለየ መስህብ ነበረው።

Monday, October 29, 2012

እውነታ - ማንጠር (Fact Checking)(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ አሜሪካ አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ደፋ ቀና እያለች ነው። ሁለቱ እጩዎች ማለትም ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የማሳቹሴትስ ገዢ የነበሩት ሚት ራምኒ እረፍት የላቸውም። ከደጋፊዎቻቸው ያሰባሰቡት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በተለይም ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች ከፍ ላለ የማስታወቂያ ክፍያ በዋል ላይ ይገኛሉ። ከማስታወቂያውም ባሻገር ራሳቸው ተወዳዳሪዎቹም በመላው አገሪቱ በመዞር የምረጡኝ ዘመቻ በማካሔድ ላይ ናቸው።

Monday, October 15, 2012

ሰው በ200 ሺህ ዶላር ብቻ አይኖርም፣ በታማኝነትም እንጂ A TRIBUTE TO AN HONEST ETHIOPIAN

 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ከዚህ ቀደም በሦስት ተከታታይ ርዕሶች (በቅጽ 6 ቁጥር 114፣ 115 እና 116/2004 ዓ.ም) “ስለ ላስ ቬጋስ” መጠነኛ ዘገባ ማቅረቤን ታስታውሱ ይሆናል በኔቫዳ በረሃ ውስጥ ስለምትገኘው የበረሃ ውስጥ ገነት። ከነስሟ “የኃጢአት ከተማ” (Sin City) ስለምትባለው። በቅጽ 114 ስለ ከተማዋ፣ በ115 በአካባቢው በበረሃ ውስጥ ስላለ ገዳም፣ በ116 ደግሞ ስለ ታላቁ የሑቨር ግድብ። ይህ ጽሑፍ ድጋሚ ስለ ቬጋስ እና ታማኝነት እንዳነሣ የሚያደርግ ግሩም ዜና ላካፍላችሁ። ዘገባውን በኦክቶበር 8/2012 ያወጣው የላስ ቬጋስ መጽሔት “Las Vegas Review-Journal” ሲሆን ከዚያ በኋላ ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ተመላልሰውበታል።

Wednesday, October 10, 2012

Honest Ethiopian cabdriver returned over $ 200,000 Dollar

(BY TOM RAGAN, LAS VEGAS REVIEW-JOURNAL):- Here's one of those stories that could only really happen in a gambling town like Las Vegas. And as the cliché goes, "What happens in Vegas, stays in Vegas." Or maybe for this story it ought to be, "What happens in the cab, Stays in the cab." But that's not how it works for Adam Woldemarim, a big and honest teddy bear of an Ethiopian cabdriver. Back on Sept. 2 he was cleaning out the back seat of his van just before the start of his 2 p.m. shift when he spotted something between the seats. It was a black soft laptop case. It was stuffed with $221,510. In cash.

Monday, October 8, 2012

ይህ ሁሉ ለአንድ ሰው(ኤፍሬም እሸቴ/ ARTICLE IN PDF)፦ ባለፈው ዓመት በአንዱ እሑድ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኔ አንድ የክርስትና ዝግጅት ነበር። በአካባቢያችን ከሚኖሩት ክርስቲያኖች አንዷ ልጃውን ለማስጠመቅ መጥተው ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ካህናቱ ከቅዳሴው አስቀድመው ለሕጻኑ መደረግ ያለበትን ሥርዓተ ጸሎት ያደርሱ ገቡ። ሙሉ ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ ካህኑ ሕጻኑን በውኃው ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረጉ “አጠምቀከ በስመ አብ፣ አጠምቀከ በስመ ወልድ፣ አጠምቀከ በስመ መንፈስ ቅዱስ ይን ስምከ …፤ በአብ ስም አጠምቅኻለኹ፣ በወልድ ስም አጠምቅኻለኹ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅኻለኹ፣ ስምህ … ይሁን” እያሉ የክርስትና ስሙን እየሰየሙና እየተናገሩ ያጠምቁታል።

Monday, October 1, 2012

የኢንተርኔት አጠቃቀማችን “ነጻነት” ጉዳይ(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ የኢንተርኔት መብት አያያዝ ጉዳይለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁናቴ በተመለከተ በየዓመቱ ጥናት የሚያደርገው “ፍሪደም ሐውስ” የሚባለው ታዋቂው አሜሪካ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የ2012 ዘገባውን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት እንዳላቸው እና ዓመታዊ ሪፖርታቸው በጉጉት እንደሚጠበቀው “ሒዩማን ራይትስ ዎች”ን እንደመሳሰሉት ድርጅቶች ሁሉ “Freedom House”ም ሚዛን የሚደፋ ሪፖርት በማቅረብ የሚታወቅ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የተቋቋመ የአሜሪካ ድርጅት ነው።

Friday, September 14, 2012

በመስከረም ትዝ ከሚሉኝ ነገሮች


እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ


(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ READ IN PDF)፦ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓመታት አልፈው፣ አገር ቤቱም እንደ ጨረቃ ርቆ፣ ትዝታም የሕልም ያህል ቀጥኖ፣ ልቡና ዛሬን ሳይሆን ትናንትን፣ የዛሬን አዋቂነት ሳይሆን የትናንትን ልጅነት ሲናፍቅ … መስከረም እና አዲስ ዘመን በትዝታ መስኮት መምጣቱ አይቀርም። ያው አዲስ ዓመት። እንቁጣጣሽ። ሰማይ ምድሩ የሚለወጥበት። ገና ከቤታችን ወጣ ስንል ኳስ የምንጫወትባቸው ሜዳዎች፣ የትምህርት ቤታችን ግቢ፣ በሩቁ የሚታየን የተራራ ገመገም ሳይቀር ቢጫ ይለብሳል። በአደይ አበባ ይሸፈናል። የት/ቤታችን ሣር የእኛን ቁመት በልጦ፣ በውስጡ እየተሽሎከሎኩን ስንሮጥ፣ ስንወድቅ ስንነሳ፣ አዲስ ዓመትን ከአዲስ የትምህርት ዘመንም ከፍንደቃም ጋር እናያይዘዋለን።

Tuesday, September 11, 2012

ኢዮሐገብረ ክርስቶስ ደስታ (ገጣሚና ሰዓሊ)

ረቡዕ መስከረም 1/1955 ዓ.ም (READ IN PDF)

++++++

ኢዮሐ!

አበባ ፈነዳ፣

ፀሐይ ወጣ ጮራ፣

ዝናም

ዘንቦ

አባራ።

ዛፍ

አብቦ

አፈራ።

Friday, August 31, 2012

ስለ “ግለሰብ እና ሕዝብ፤ ታሪክ እና ያለፈ ጉዳይ”ከዚህ በታች ያለው ጽሑፍ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሰጥተውት በነበረ ቃለ ምልልስ ላይ ተመርኩዞ  Sunday, March 20, 2011 (Part 1) Saturday, March 26, 2011 (Part 2) ላይ በዚሁ የጡመራ መድረክ ላይ የወጣ ነበር። ያላነበቡ ወዳጆቼ እንዲያዩት በሚል በድጋሚ በአንድ ላይ ተዘጋጅቷል። (READ IN PDF)
(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com Sunday, March 20, 2011 Saturday, March 26, 2011):- ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰፊ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ተመልከቼ ነበር። በተለይም በሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እንዲሁም በጅማ እና አካባቢው ያለውን የሃይማኖት ግጭት በተመለከተ ምን እንዳሉ በስፋት ለመስማት ፈልጌ ነበር። በዩ-ቲዩብ ተቆራረጦ ከተቀመጠው የጠ/ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ ጥያቄና መልስ መካከል ባሰብኩት መልኩ ባይሆንም የ“ቁምነገር” መጽሔት ጋዜጠኛ ያነሣቸው ጥያቄዎች እና አቶ መለስ የሰጧቸው መልሶች ይህንን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት ሆኑኝ።

Blog Archive