Tuesday, January 3, 2012

የሚጽፉ ጣቶች - የሚያነቡ ዓይኖች

(ኤፍሬም እሸቴ/ READ IN PDF):- የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዮሐንስ “የመጽሔቷ አምስተኛ ዓመት እንደሚከበር በኢ-ሜይል ሲያስታውቀኝ እና ምናልባት መልእክት አለኝ እንደሁ ሲጠይቀኝ ወዲያዉኑ ሐሳቤን ሰብስቤ በአጭር አማርኛ ለማስቀመጥ ቀላል ሆኖ አላገኘኹትም ነበር። በደፈናው “አዲስ ጉዳይ - እንኳን አደረሰሽ፣ እኛንም እንኳን አደረሰን” ማለቱ ክሊሼ እየሆነብኝ በመጀመሪያ መላውን የአዲስ ጉዳይ የመጽሔቷን ቤተሰቦች እንኳን አደረሳችሁ ብዬ ጀመርኩና ለሚቀጥሉት ዓመታትም እንዲሁ በሰላም እያደረሰን በተመሳሳይ መልኩ “የመጽሔት በዓል” ለማክበር ያብቃን” ስል አከልኩበት። አዲስ ጉዳይ ለብዙ አንባቢዎቿ ትርጉም ያለው የዕውቀት ብርሃን እየፈነጠቀች እንደሆነ ሙሉ እምነት አለኝና ዕውቀት ፈንጣቂ መጽሔቶች እንደ ልብ በማይገኙበት እንደ ኢትዮጵያ ባለው አገር የአዲስ ጉዳይ አምስት ዓመት መቆየት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ለመግለጽ ሞከርኩ።

እንዲህ አምስተኛ ዓመቷን እንዳከበረች ሁሉ ሐምሳኛ ዓመቷን ለማክበር እንድትበቃ፣ ብቅ ጥፍት፣ እልም ድርግም እንዳሉት እንደብዙዎቹ የሕትመት ውጤቶቻችን ሳትሆን ተከታታይ ትውልዶች እየተቀባበሉ የሚያዘጋጇት ዕድሜ ጠገብ መጽሔት እንድትሆን ተመኘኹላት። የሚቀጥሉት ሁለት አንቀጽ ምክር ቢጤዎችንም ጨመርኩ። 
መጽሔቶች እና ጋዜጦች ሳይቋረጡ ለብዙ ዓመታት በሕትመት ለመቆየት የሚችሉባቸው አገሮች በሌላ አነጋገር መረጋጋት፣ ሰላም፣ ዕድገት፣ ዲሞክራሲ እና የሰለጠነ ኅብረተሰብ ያላቸው አገሮች ሲሆኑ በተቃራኒው መጽሔቶች እና ጋዜጦች ብቅ-እልም የሚሉባቸው ደግሞ አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦት፣ ኋላቀርነት፣ አምባገነንነት እና ያልሰለጠነ ኅብረተሰብ ያለባቸው አገሮች ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለኝም። የመጽሔቶች ዕድገት የአገርን እና የኅብረተሰብን የአዕምሮ ዕድገት ያመጣል። የተሻለ ኅብረተሰብ ይፈጥራል። አዲስ ጉዳይን የመሰሉ መጽሔቶች መታየት ያለባቸው እንደ ማንኛውም ንግድ ሳይሆን እንደ ት/ቤቶች፣ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች በዕውቀት መገብያነታቸው ነው። ስለዚህም ነው “መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል/ ባለድርሻ አካላት ሊረዷቸው” የሚገባው።
የአዲስ ጉዳይ ዝግጅት ክፍልም መጽሔቷ የደረሰችበትን የአምስት ዓመት ዕድገት የሚመጣጠን የአቀራረብ ዕድገት ማምጣት ይጠበቅበታል። በቦታ ጥበት ምክንያት ሊያስተናግዳቸው ያልቻላቸውን የአንባቢዎቹን ድምጽ እና አስተያየት የሚያንሸራሽርበት መድረክ መፍጠር አለበት። ዝግጅቶቹን ለሕዝብ ለማቅረብ በየሁለት ሳምንቱ አንድ መጽሔት እንደሚያዘጋጀው ሁሉ በየቀኑ ደግሞ የአንባብያኑን ምላሽ ለማግኘት እንዲያስችለው ከተቻለ ድረ ገጾች ቢያዘጋጅ፤ እስከዚያው ግን “ሶሻል ኔትወርኮችን” (ለምሳሌ ፌስቡክን) በመጠቀም በመጽሔት ላይ ሊያስተናግዳቸው ያልቻላቸውን የአንባብያን አስተያየቶች ቢያወጣ የመጽሔቷን ተደራሽነት ሰፊ ያደርጋታል። ለዚህም የፌስቡክ ኤዲተር ቢኖረው መልካም ነው። አዲስ ጉዳይ በጽሑፎቿ ዓይነት እና ስብጥር እንዲሁም በፀሐፊዎቹ የተለያየ ሙያዊ ተሞክሮ አበረታች መሆን ጥሩ ደረጃ ላይ የምትገኝ ከመሆኗ አንጻር ይህንኑ አጠናክራ በመዝለቅ የበለጠ ተነባቢ እንድትሆን እመኝላታለሁ።
መቸም አነጋገሬ “ውኃ ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታወቁ ወይም ተጠቆመ” ዓይነት ቢሆንም ኢትዮጵያ ብዙ የሚጽፉ ጣቶች፣ የሚታተሙ መጽሔቶችና ጋዜጦች፣ የሚያነቡ ዓይኖች ያስፈልጓታል። ሕትመቶቹ የውኃውን ያህል አስፈላጊያችን ናቸው። “የሚጽፉ ጣቶች እና የሚያነቡ ዓይኖች” በጣም በጣም ያስፈልጉናል። ግብታዊውን የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ በመጣው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወቅት ከተዘመሩ ቀስቃሽ መዝሙሮች መካከል የፀሐዬ ዮሐንስ “አይኖሩም የማይጽፉ ጣቶች፣ አይኖሩም የማያነቡ ዓይኖች” ትዝ አለችኝ። ክፋቱ የማያነቡ ዓይኖች፣ የማይጽፉ ጣቶች ሞልተዋል። ጣቶች እንዳይጽፉ እና ዓይኖችን እንዳያነብቡ የሚያደርጉም ሞልተዋል።
ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሚጽፉ ጣቶች የሚያስፈሯቸው አያሌ ነበሩ። በብዙ የሥልጣኔ ሒደቶች ውስጥ ማንበብ እና መጻፍ ለላዕላዩ ኅብረተሰብ የተሰጠ ልዩ “ፕሪቪሌጅ” ነበር። ማንም ተርታ ሰው፣ ያውም የዕለት ጉርሱን እና የዓመት ልብሱን የማያሟላ የአዳም-ዘር ሁላ ከማንበብ እና ከመጻፍ ደረጃ ማን ሊያደርሰው? ማንበብ እና መጻፍ ራሱ ቅንጦት ነበር። በእርግጥም ወደ ዓለመ-ዕውቀት ለመግባት መታደል በራሱ ትልቅ ጸጋ ከመሆኑ አንጻር ማንበብ እና መጻፍ ከሀብት መቆጠሩ ተገቢ ነበር።
አውሮፓውያን ፈረንጆች ቅኝ ግዛቶቻቸውን ከነፈጓቸው መብቶች መካከል እንደ ገል ቀጥቅጠው፣ እንደ ሰም አቅልጠው የሚገዟቸውን ሕዝቦች የዕውቀት ብርሃን እንዳያዩ ማድረጋቸው ዋነኛው ነበር። ፋሺስት ጣሊያኖች የኤርትራ ወንድሞቻችን ከ4ኛ ክፍል የበለጠ እንዳይማሩ በሕግ መከልከላቸውን በየታሪኩ ስናነብ ኖረናል። ለአምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ያንኑ ለመድገም ሞክረዋል። እንደ ቅኝ ገዢዎቹ አውሮፓውያን ሁሉ የጥንቶቹም ቢሆኑ የሚጽፉ ጣቶችንም ሆነ የሚያነቡ ዓይኖችን ሲፈሩ ኖረዋል። ከቻሉ ወዳጆቻቸው እና አገልጋዮቻቸው ያደርጓቸዋል፣ ካልሆነ ግን እንዳይኖሩ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
ታሪክ እንደሚነግረን የሮማ ገዢዎች ግሪኮችን ሳይቀር ያስተዳድሩ በነበረበት ዘመን ፈላስፎቹን፣ ፀሐፊዎቹን፣ ንግግር አዋቂዎቹን በእንክብካቤ ይዘው ደጋፊዎቻቸው ለማድረግ ችለው ነበር። በውድቀታቸው ወቅት ደግሞ ከነዚሁ የዕውቀት ቀንዶች ጋር ተለያይተዋል። በመካከለኛው ዘመን-አውሮፓ ማንበብ እና መጻፍ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዋቂዎች እጅ ውስጥ ብቻ በነበረበት ዘመን፣ አብዛኛው ተራ ሕዝብ ከመ-እንስሳት ከዕውቀት ተለይቶ ይኖር ነበር። ይህም ለገዢዎች ትልቅ እረፍትን ሲሰጣቸው ኖሯል። ይሁን እንጂ የሕትመት እና የማተሚያ ሥልጣኔ እየተስፋፋ ሲመጣ የማንበብ እና የመጻፍ ቁልፍ ከጥቂቶች ሀብትነት ወደ ሕዝቡ ሲሸጋገር የዕውቀት ብርሃን የብዙዎችን ዓይን መክፈት ጀመረ። አውሮፓም እንደ ከዚያ በፊቱ ሕዝቡን “ከፍ ሲሉ አንገቱን-ዝቅ ሲሉ ባቱን” እየቆረጡ የሚገዙት አልሆን አለ። ከነተረቱ “ያወቀ-ፀደቀ”፣ እንዲሁም “ያላወቁ አለቁ” ነው።
በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ለውጦች የሚጀመሩት በዕውቀት-ቀንዶች፣ በሚያነቡ ዓይኖች-በሚጽፉ ጣቶች ነው። በረሃብ ውስጥ ያሉ ረሃብተኞች ሠርተው ከገቡበት የድህነት እና የችጋር አረንቋ ለመውጣት እንቅስቃሴ የሚጀመረው በሚቆፍሩ እጆች ሳይሆን በሚጽፉ ጣቶች ነው። ለነጻነት የተደረጉ የትኞቹም ተጋድሎዎች የተጀመሩት በሚተኩሱ አነጣጣሪ - ቅልጥም ሰባሪ በሆኑ ፋኖዎች ሳይሆን የዕውቀት-ቀንድ በሆኑ ምሁራን ነው።
የዕውቀት ቀንድ የሆኑ የብዕር ሰዎች፣ ማለትም በደፈናው የሚጽፉ ጣቶች ያልናቸው፣ ችግር ነቃሾች እና የጎደለ ነገር ተመልካቾች እንዲሁም የወደፊቱን በትኩረት ለማየት የሚደፍሩ ናቸው። ሌላው ሕዝብ ያላየውን በንስር ዓይናቸው ተንትነው ይመለከታሉ። ሌላው ያልተረዳውን ይረዳሉ። ላልተረዳው ለማስረዳትም ይጥራሉ። በተባ ብዕራቸው፣ በሰላ አንደበታቸው አጣፍጠው ይጽፋሉ-ይናገራሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ ሌላው ሕዝብ ተቀብሎት የሚኖረውን፣ ነገር ግን የማይበጀውን ነገር አይቀበሉም። ሌላውም እንዳይቀበለው ያደርጋሉ። ቀጥሎም በኅብረተሰቡ ኑሮ ውስጥ የጎደለውን ነገር በማሳየት ሕዝቡ አዲስ ነገር እንዲፈልግ ያደርጉታል። ልቡናውን ያነሣሱታል። ሕዝቡ የሚያነግባቸውን “መፈክሮች” ይፈጥሩለታል። የቀረው የሌላው ሕዝብ እንቅስቃሴ ይሆናል።  ለውጥ ይከተላል። ገዢዎች ይህንን ጉዳይ ቶሎ ይረዳሉ። ከቦልሸቪኮች እስከ ናዚዎች ድረስ ጨካኝ እና ጨቋኝ መንግሥታት ብረት ካነገበው ባልተናነሰ ብዕር የያዙ ጣቶችን ይፈሩ ነበር። የሚፈሩበትም በቂ ምክንያት አላቸው። ራሳቸውም በአብዛኛው ከዚሁ ከሚጽፈው ወገን ስለሚሆኑ የሚጽፉ ጣቶችን ጥቅም እና ጉዳት ያውቃሉ። ስለዚህም በቻሉት መጠን የእነርሱ አገልጋይ ያደርጓቸዋል። የማይታዘዙላቸው ከሆነ ግን ከሥራቸው ነቅለው ለማጥፋት ወደኋላ አይሉም።
የአረቦቹን ዓለም ባጥለቀለቀው የ2011 እንቅስቃሴ ደረታቸውን ለጦር-ግንባራቸውን ለጥይት የሰጡ ወጣቶች በየአደባባዩ ከመውጣታቸው አስቀድሞ ብዙ ፀሐፊዎች ለረዥም ጊዜ ለፍተዋል። ሕዝቡን ከእንቅልፉ ቀስቅሰዋል። የተሸከመው ከባድ ቀንበር እንዳጎበጠው አስታውሰውታል። ከዚያ የተሻለ ኑሮ መኖር እንደሚገባው በመምከር የነጻነት ጥማት አሳድረውበታል። የተጠማውን ነጻነት እንዲያገኝም ባሳዩት መንገድ በመትመም አምባገነኖቹን ከመንበራቸው ለመፈንቀል ችሏል።
ሌላው ሕዝብ እንደከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ እነዚህ የብዕር ሰዎችም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል፣ ከአገር ተሰድደዋል። በቱኒዚያ፣ በግብጽ እና በቻይና ያሉ መንግሥታት ዓይነቶች አሁንም የሚጽፉ ጣቶችን የመቁረጥ ተግባራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው። የእነርሱ አገልጋይ ለሆኑት የዕውቀት ሰዎች ፈረሱም ያው፣ ሜዳውም ያው የሚሉትን ያህል የሚቃወሟቸውን ከዋሉበት አናስውል፣ ካደሩበት አናሳድር ይሏቸዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህን ጥቂት የቀለም-ቀንድ የሆኑ ሰዎች በማሰር እና በማንገላታት፣ በማጋዝ እና በመግደል የያዙትን እና ያነሡትን እውነት ማጥፋት እንደማይቻል ታሪክ ምስክር ነው። ሊመጣ ያለውን ለውጥ ማዘግየት ካልሆነ በስተቀር ማስቀረት አይቻልም። መፍትሔው ችግሩን ያመለከተውን ማጥፋት ሳይሆን ችግሩን ማጥፋት ነው። ነቢዩን በመግደል የነቢዩን ላኪ መግደል አይቻልም። የነቢዩ ተግባር ያየውን እና የሚያውቀውን መናገር እንደሆነ ሁሉ የሚናገረው ቁም ነገር ላይ እንጂ ተናጋሪው ላይ ማተኮር ምንም እርባና አይኖረውም።
እንግሊዞች በሕንድ የነበራቸው የበላይነት እንዳይነቃነቅ ለማድረግ ከጠሩበት ሙከራ መካከል ደረጃቸው የወረደ እና የእነርሱን የበላይነት የተቀበለ “የተማረ” ሰው ለመፍጠር መሞከራቸው አንዱ ነው። የራሺያ አብዮተኞችም ሆኑ የጀርመን ናዚዎችም ክፋታቸውን የሚሸፍንላቸው የብዕር ሠራዊት አሰማርተው የሰዉን ዓይን ለመሸበብ ሞክረዋል።  በአገራችንም ቢሆን በየዘመናቱ ለተነሡ ገዢዎች አፋሽ-አጎንባሽ ሆነው የሚያገለግሉ የዕውቀት ሰዎች ነበሩ፣ አሉም። በዚያ ዘመን መጠቀም የሚችሉትን ያህል ለግላቸው ለመጠቀም ነቢያተ ሐሰት ሆነው ጨለማውን ብርሃን፣ እሬቱን ማር ብለው ይጽፋሉ፤ ይዘምራሉ፤ የሕዝቡንም የኑሮ ቀንበር ያከብዳሉ። እነርሱም ቢሆኑ ግን የሚመጣውን ለውጥ መግታት አይቻላቸውም።
 እንግዲህ አዲስ ጉዳይ አምስት ዓመት ብቻ ሳይሆን ሐምሳ ዓመት ከዚያም በላይ እንዲሞላት የምመኘው በዚህ መንፈስ ነው። ዕውቀት እና አዋቂዎች ያሉት አገር አይወድቅም። የአገር ጥንካሬ በገንዘብ ብዛት ብቻ ሳይሆን በአእምሮ ንቃትም ነው። ቢራ ፋብሪካ እንጂ ወረቀት ፋብሪካ የሌለበት አገር፤ ድራፍት ቤት እንጂ ላይብራሪ የሌለበት ሰፈር፣ የጦር ካምፕ እንጂ ኳስ ሜዳ የሌለበት አካባቢ፣ የአካባቢ እስር ቤት እንጂ የአካባቢ መጽሔት/ጋዜጣ የሌለበት አገር  … ወዘተ ….. ወደ ግራ ሲሉት ወደ ቀኝ በሚታጠፍ ኅብረተሰብ መካከል ለውጥም ሆነ ዕድገት ማምጣት ዘበት ነው። የሚቆፍሩ እና የሚገድቡ እጆች መኖራቸው አስፈላጊ ቢሆንም የሚያስቡ ጭንቅላቶች፣ የሚጽፉ እጆች፣ የሚያነቡ ዓይኖች ከሌሉ ያ አገር ጤናማ አገር ነው ለማለት አይቻልም።
በመጨረሻ “አዲስ ጉዳይ ዕደጊ ተመንደጊ፣ ጋዜጣ ሁኚ፣ ኢንተርኔት ሁኚ፣ ድረ ገጾች ፍጠሪ፣ ሌሎች ወዳጆችም አፍሪ፣ አንባቢ አያሳጣሽ” ብሎ የሚመርቅ ሽማግሌ/ አንባቢ አያሳጣሽ።
© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም16 comments:

Anonymous said...

LONG LIVE YOU TYPE OF WRITERS! GOD BLESS YOU!

afi said...

"ቢራ ፋብሪካ እንጂ ወረቀት ፋብሪካ የሌለበት አገር፤ ድራፍት ቤት እንጂ ላይብራሪ የሌለበት ሰፈር፣ የጦር ካምፕ እንጂ ኳስ ሜዳ የሌለበት አካባቢ፣ የአካባቢ እስር ቤት እንጂ የአካባቢ መጽሔት/ጋዜጣ የሌለበት አገር … ወዘተ …."all are true, all are real in the country in addition to this i am wondering that many/millions/ police stations has been constructing with in small villages and they are stuffed with numbers of man power,so you the people what is going on in the country? what the ground reason and result to this atmosphere? what if all this police stations would be libraries? or what if all "chat" renders would be book stores and so and so...

Anonymous said...

ዲ/ን እግዚአብሄር ፀጋዉን ያብዛልህ። እንዳንተ አይነት ሰዎችንም እግዚአብሄር ለኢትዮጵያ ያብዛላት። ኣይዞህ በርታ ጠንክር። “ውኃ ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታወቁ ወይም ተጠቆመ”...ድንቅ ገላጭ ነዉ።...ኢቲቪ ላቆሰለን ሁሉ ፈዉስ የሚሆን ኣባባል...

YENEALEM said...

BERTALN WONDM ESHETE

Anonymous said...

yap yap yap,u said what must be to said,u wrote that must be write,u advised what must be advice!God blesses ur work!ur hand!ur family!ur religion!ur country!

keep on ur writing till to see the sun rise!

Anonymous said...

thank u interesting comment, bizu bizu anbabi ethiopiachen teshaleche.

tensae said...

በአገራችንም ቢሆን በየዘመናቱ ለተነሡ ገዢዎች አፋሽ-አጎንባሽ ሆነው የሚያገለግሉ የዕውቀት ሰዎች ነበሩ፣ አሉም። በዚያ ዘመን መጠቀም የሚችሉትን ያህል ለግላቸው ለመጠቀም ነቢያተ ሐሰት ሆነው ጨለማውን ብርሃን፣ እሬቱን ማር ብለው ይጽፋሉ፤ ይዘምራሉ፤ የሕዝቡንም የኑሮ ቀንበር ያከብዳሉ። እነርሱም ቢሆኑ ግን የሚመጣውን ለውጥ መግታት አይቻላቸውም።/

ለጥቅም ብለው ጥቁሩን ነጭ ብለው ከሚመሰክሩ ጸሀፊያን ይሰውረን!!

tensae said...

ለጥቅም ብለው ጥቁሩን ነጭ ብለው ከሚመሰክሩ ጸሀፊያን ይሰውረን!!

Anonymous said...

10Q!

lily said...

wow Ababaye eyandanduwan sentence anidm eyaliku bamesetirew minegna des balegni betam perfect biyewalehu

Anonymous said...

D.Ephrem,you need to write more.Don't be silent.It's time for you to send your message like Abune Gorgorios,your father.Thanks a lot for your posting about our country.There is more to say and to write.Yikoyen.

Mehari said...

ወረቀት ፋብሪካ ምን ይሠራልናል!? ማይምነትን በጠፍ ጨረቃ ጠፍቶ እንዲሔድ ያደረገ የትምህርት ፖሊሲ የተከልን ሰዎች አይደለን እንዴ! እኛ አሁን የምንፈልገው ሆቴል የምንገነባበት ሲሚንቶ እና ሆቴሉ ውስጥ ገብተን የምንጠጣው ቢራ፡፡

hani said...

“ውኃ ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታወቁ” .......በእንደነዚህ ዓይነት ፁሁፎች እና ወሬዎች እኮ.... ደንዝዘናል

Anonymous said...

fana wegi new Egiziabher yistilin

Anonymous said...

ዲያቆን ኤፍሬም
እግዚአብሔር ይባርክህ።
ዕውቀትን ያብዛልህ።
እኛንም የሚጽፉ ጣቶችንም ሆነ
የሚያነቡ ዐይኖችን አያሳጣን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Anonymous said...

“ውኃ ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታወቁ” በረከት ሰምኦን መሆን አለበት የተናገረው!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!1