Tuesday, January 17, 2012

ከተማ እና እሳት

READ IN PDF.
ከሰሞኑ ሪፖርተር ጋዜጣን ሳነብ የአቧሬ ገበያ መቃጠልን የሚያትተውን ዜና አገኘኹ። “ኅሣሥ 9 ቀን 2004 .. ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ስምንት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ መነሻው ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት” የተነሣው እሳት የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን “ዶግ-አመድ እንዳደረጋቸው”፣ እሳት አጥፊዎች እሳቱ በተነሣ በስድስት ደቂቃ ውስጥ መድረሳቸውን ነገር ግን “ውኃ የለንም” ብለው እሳቱ አገሩን ሲያጠፋ አብረው ከሕዝቡ ጋር መታዘባቸውን (እሳቱን መሞቃቸውን?) ዘግቧል። በዚህም በዚያም ብቻ አቧሬ ገበያ የእሳት ራት መሆኗን አርድቶኛል። ‘ዶግ አመድ’ አደረጋቸው ስል በደስታ ልቤ ጥፍት ያለ እንዳይመስልብኝ ፈራኹ። ከሪፖርተር እንደወረደ ለመጥቀስ ነው የወሰድኩት። አይ አማርኛ።

አቧሬን ባልወለድባትም ብዙ ዓመታት ኖሬባታለሁ። ቤት አከራዮቼ ከቤተሰብ የማይተናነስ ፍቅር የሚያሳዩ ግሩም ሰዎች ነበሩ። ወደ ሥራ ስሔድም ሆነ ስመጣ አቧሬ ገበያውን አቋርጣለሁ። ሁል ጊዜም እንደሞቀ ነው። የእግረኛ መተላለፊያ በሌለባት በዚያች ቀጭን መንገድ ከታክሲውም፣ ከሌሎች መኪኖችም፣ ከእንስሳውም ጋር እየተሻሸን እየተዋደድን እንተላለፍባታለን። ከመንገዱ ግራና ቀኝ መኖሪያ ቤቶችም ንግድ ቤቶችም ግጥግጥ ብለው ተሰድረዋል። በዓመት በዓል ሰሞን ሙዚቃውም የምግቡም ሽታ ከግራ ከቀኝ አፍንጫንዬን እየጠለዘ፣ እግሬን ከአልፎ ሒያጅ ታክሲ እየጠበቅሁ፣ አቧሬን እያደነቅሁ ወደ ቤቴ እገባለሁ፣ እወጣለሁ።

አቧሬ የመንገድ መብራት በቅጡ የሌለበት ጨለማ ለበስ መንደር ብትሆንም ከፍ ብሎ መንግሥታችንን እና ወረድ ብሎ ያለውን የጦር ሰፈር የሚጠብቁ ነፍጠኞች (ወታደሮች ለማለት ነው) ስለፈሰሱበት ማጅራት መቺ አስፈርቶኝ አያውቅም ነበር። ከመሐል ከተማው ብዙም ሳትርቅ ለመዝናኛ ቦታዎችም፣ ለሥራዬም፣ ለቤተ ክርስቲያንም፣ ወደ ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎች ለመሔድም አማካይ ስለሆነች ጭርንቁስ መሆኗ ሳይሆን ይህ ነገሯ የበለጠ ልቤን ይገዛው ነበር።

አቧሬ ገበያ መቼ እንደተመሠረተች ያስነበቡን ብርሃኑ ሰሙ ሲሆን መጽሐፋቸው ደግሞ “ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ (ከ1879 እስከ 2000 ዓ.ም)” የተሰኘው በ2003 ዓ.ም የታተመው ጥናት ነው። አቧሬ የተባለው አቧራማ በመሆኑ ነው የሚሉት ፀሐፊው ስለ አመሠራረቱ ሁለት ታሪኮችን አቅርበዋል። የመጀመሪያው “የ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት አገልግሎት መስጠት በጀመረ ማግስት ብዙ መኳንንቶች ከሰፈሩባቸው መንደሮች አንዱ … አቧሬ ስለነበርና የቤተ መንግሥቱም ሠንጋ መደለቢያ እዚያ ይገኝ ስለነበር የንግድ ቦታው በመንደሩ ከሥላሴ ገበያ ጋር በአንድ ዘመን - በ1890ዎቹ” ተመሥርቷል የሚል ነው።

ሁለተኛው ደግሞ “ለቤተ መንግሥቱ በነበረው ቅርበት እንዲሁም በስፋቱና በተገልጋዩም ብዛት ለአዲስ አበባ ትልቅ የነበረው የሥላሴ ገበያ፣ በ1923 ዓ.ም የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ፀድቆ የፓርላማው ሕንጻ ከተሠራ በኋላ የሕግ መምሪያና መወሰኛ ምክር ቤቶች በ1924 ዓ.ም ሥራ ሲጀምሩ፣ ሥላሴ ገበያ ከመጀመሪያ መቆሚያው እንዲነሣ ተደርጎ ወደ ፖሊስ ጋራዥ ሲመራ በገበያው ይነግዱ የነበሩት ከፊል ነጋዴዎች  ወደ አቧሬ አቅንተዋል” የሚለው ይላል።

አቧሬ በወቅቱ የነበሩትን ገበያዎች ማለትም ሥላሴን፣ አራዳንና መርካቶን ያስንቅ እንደነበርም በጨረፍታ ያስገነዘቡን ፀሐፊ ብርሃኑ እንደስሙ ከማደግ ይልቅ ቀጭጮ መቅረቱን አስታውሰውናል። እንዲያውም አቧሬን የሚያሞግስ (ሙገሳነቱ ብዙም ባይታየኝም) ነው ያሉትን ስንኝም አስቀምጠውልናል።

የሥላሴን ገበያ፣ ገበያ ብለሽው፣

የአራዳን ገበያ፣ ገበያ ብለሽው፣

የገረድ መጨንጪያ አቧሬን ባየሽው። (የወሰድኩት ከገጽ 296-297 ነው፤ መጽሐፉ ጠቃሚ በመሆኑ መግዛት ይገባል።) አሁን እሳት እንደበላው ሪፖርተር (http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/4713-2012-01-04-06-38-56.html) ያረዳኝ እንግዲህ ይህንን ገበያ ነው። ምን ይደረጋል፤ እሳት የማይጠፋበት አገር።

አዲስ አበባ በትልቅ ለውጥ ላይ እንደምትገኝ የአደባባይ ምስጢር ነው። አቧሬን ስለበላው ዓይነት እሳት ማውሳት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው። የሚያውቁኝ ወዳጅ ዘመዶቼ እና ከዚህ አዲስ አበባ ደርሰው የሚመጡ ሁሉ ሲያወሩኝ “አሁን ብትሄድ አታውቃትም” ይሉኛል። በእርግጥ ካገር ቤት ስወጣ አንድ ኪሎ ሥጋ በ23 ብር ከጊርጊሮ ወይም ጊዮርጊስ ሰፈር ገዝተን፣ አስጠብሰን በልተን፣ ቁርጡን አወራርደን እንውል ነበር። በአንድ ሺህ ብር የቤት ወጪ እንችላለን። ጤፉን፣ ወጣ ወጡን ሁሉ። አንድ ቀይ ወጥ 10 ባልሞላ ብር እናገኛለን። ለስላሳ ከሁለት ብር ብዙም አይዘልም ነበር። ታክሲ በአንድ ብር ከሳላሳ አምስት ሳንቲም አንከብክቦ የፈለግነው ቦታ ያደርሰናል። በአንድ ሺህ 500 ብር ደሞዝ ተንቀባረን እንኖራለን። አሁን ያ ጊዜ የስብስቴ/ የድንጋይ ዳቦ ዘመን ያህል ርቋል ልበል?

አዲስ አበባ ለውጥ ላይ ናት ያልኩት “ብትሔድ አታውቃትም” የሚሉኝ ሰዎች እንደሚነግሩኝ በፎቅ-ላይ-ፎቅ ስለሆነች እንጂ በሌላ ነገር አይደለም። በእርግጥም በፎቅ-ላይ-ፎቅ ከሆነች ደግሞ ትልቁ ጠላቷ እሳት እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለዚህም ፎቁን ከመገንባቱ ጋር የሚነሱ እሳቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ግድ ይላል። እንዲያው በደፈናው “ውኃ የለኝም” ማለት የሚያዋጣ አይሆንም። አለበለዚያ በብዙ ልፋት እና ገንዘብ የተገነቡት ግንባታዎች በእሳት ላንቃ ሲፈተኑ የደቂቃዎች እና የሰዓታት ዕድሜ ይበቃቸዋል። የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ መውደቅ ሳንቆጥር ማለት ነው።

አዮዲ ኦሉኮጁ የተባሉ ናይጄሪያዊ ፕሮፌሰር በሌጎስ ከተማ ስለሚነሱ/ስለተነሱ እሳት አደጋዎች ሲተነትኑ ያቀረቧቸው ሦስት ምክንያቶች ለአዲስ አበባም ትርጉም ያላቸው ይመስላሉ። ምሁሩ የእሳት አደጋ ምክንያት አንድ ብለው የጠቀሱት በጭርንቁስ መኖሪያ አካባቢዎች (shanty towns) ኤሌትሪክ በማጣት ምክንያት በማገዶና እና በመሳሰሉት ነገሮች የሚነሣ እሳት ሲሆን፤ ምክንያት ሁለት ደግሞ በገበያዎች እና በንግድ ማዕከላት አካባቢ እሳት የሚፈጥሩ ነገሮችን ከሌሎች ባለመለየት የሚፈጠሩ ያሏቸው ናቸው። ምክንያት ሦስት በትልልቅ ሕንጻዎች ላይ የሚከሰቱ አደጋዎች ያሏቸው ናቸው።

ጭርንቁስ መኖሪያዎች እሳት ለመፍጠር እና እሳት ከተነሣ ደግሞ ለመቆጣጠር በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው። ቤቶቹ እርስበርሳቸው ተደጋግፈው የቆሙ ከመሆናቸውም በላይ እሳት የሚከላከሉ ሰዎች (ካሉ ማለት ነው) ሊገቡባቸው የሚችሏቸው መንገዶች ብዙም አይኖሯቸውም። በቅርቡ በብራዚል ጭርንቁስ መንደሮች የተነሣው እሳት ምን ያህል ዘግናኝ እንደነበር  በዜና አይተናል። ለብዙ ዘመን ያፈሩት ጥሪት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሲወድም ከመመልከት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም። አዲስ አበባ “ፎቅ-በፎቅ እየሆነች ነው” ብትባልም ጭርንቁስ ሰፈሮቿ አሁንም አሉ።

የአቧሬው አደጋ በገበያ አካባቢ ይከሰታል ካሉት ጋር ይሄዳል። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ አዲሷ አይደለም። መርካቶ እና ጨርቆስ ገበያዎች ምስክሮች ናቸው። ምናልባትም ሌሎች አካባቢዎች። እነዚህ የገበያ ሥፍራዎች የብዙ ቤተሰብ የዕለት ጉርስ እና የአገር ኢኮኖሚ አካሎች ናቸው። በእሳት ሲጠፉ የብዙ ሰው ቤት እንደተፈታ ለመገንዘብ ብዙም ሊቅነት አይጠይቅም። ንግዶቹ ምንም ኢንሹራንስ የሌላቸው ስለሚሆኑ ባለ ንብረቶቹ ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው ቀርተዋል ማለት ነው።

በብዙ ታዳጊ አገሮች እንደሚታየው አነስተኛ ንግድ ያላቸው የአቧሬ ዓይነት ነጋዴዎች ባንክ የመጠቀም ልምዳቸው አነስተኛ ነው። ብዙዎቹም ገንዘባቸውን እዚያው ንግዳቸው ወይም መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ወሻሽቀው ማስቀመጥን ይመርጣሉ። እሳት ንግዳቸውን ሲያቃጥል አብሮ የሚወድመው ያ በጓዳ-ባንካቸው ያኖሩት ጥሪታቸውም ጭምር ነው። መጦሪያቸውንም፣ ካፒታላቸውንም፣ ቤታቸውንም፣ ዕቃቸውንም በአንድ ጊዜ ያጣሉ ማለት ነው። ከዚያ ይባስ ብሎ ደግሞ ዕለቱን የሚጠለሉበት ድንኳን እንኳን እንዳያገኙ የሚከለክል የየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ዓይነት አስተዳደር ሲመጣ ደግሞ መከራቸውን ያከፋዋል።

እንደ ሰዉ ሀገር ቢሆን ኖሮ ለነዚህ ዜጎች መጠለያ እና ማቋቋሚያ መፈለግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ታዲያ መንግሥትን መንግሥት አድርገነው ስናበቃ በችግራችን ካልደረሰልን ምን ያደርግልናል? መንግሥት መሆን ማለት እነርሱ ከቦሌ ወደ ቤተ መንግሥታቸው ሲገቡ እንዳናያቸው በፖሊሶቻቸው ማባረር ብቻ ነው እንዴ? ወይንስ ዓመታዊ በዓሎቻቸውን ሲያከብሩ አደባባይ ወጥተን እንድናደምቅላቸው ብቻ ነው የሚፈልጉን? መንግሥት ማለት በሕዝቡ ችግር ወቅት የሚደርስ ተቋም ማለት መስሎኝ። ከነዚያ ጭርንቁስ የገበያ አካባቢዎች ቀረጥ ሲሰበስብ ቆይቶ በእሳት ሲጋዩ ካልደረሰላቸው፣ የዕለት ማረፊያ ካልሰጣቸው፣ ራሳቸውን በድጋሚ ችለው ወደ ንግዱ እንዲመለሱ ካልረዳቸው ምን ዋጋ አለው? ልማት ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ገንዘባቸውን ማበደር ካለባቸው ለእነዚህ ልምድ ላላቸው ነገር ግን ገንዘብ ላጠራቸው ዜጎች መድረስ ይኖርበታል።

በሌላ በኩል በከተሞች አካባቢ ከሚነሱ እሳቶች መካከል በሦስተኛነት የተጠቀሰው የትልልቅ ሕንጻዎች እሳት ነው። በምዕራቡ ዓለም የተለመደ የዕለት ተዕለት ዜና አካል ነው። ከጭርንቁስነት ወደ ፎቅነት በመለወጥ ላይ ላሉ አዲስ አበባን እና የክፍለ ሀገር ከተሞችን (ባሕር ዳር፣ ጅማ፣ መቐለ፣ አዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ደሴ፣ ጎንደር ወዘተ ወዘተ) በይበልጥ ይመለከታል። የከተሞች ፎቅነት የሚከተሏቸውን አደጋዎች ከመቆጣጠር ጋር አብሮ ማደግ አለበት። የአደጋ ጊዜ መውጫዎች፣ እሳት ሲነሳ በቶሎ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች አብረው መታሰብ አለባቸው። ከተሞቹን የሚያስተዳድሩት አካላትም የከተማ ውስጥ አደጋ መከላከልን በተመለከተ ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል።

የከተማ ውስጥ አደጋ አንድም እሳት፣ አንድም ወንጀል ነው። የወንጀሉ ጉዳይ የዚህ ጽሑፍ ርዕስ አይደለም (የኮከብ አሳየን ጽሑፎች በ“ወንጀል” ዓምድ ይመልከቱ)። እሳቱን በተመለከተ ግን በከተሞች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክፍለ ከተማ እና በቀበሌዎች ደረጃ ዝግጅት ያስፈልገዋል። በገንዘብ እና በካፒታል እጦት የሚመካኝም አይደለም። እንዲህ ዓይነት ተግባራት በአብዛኛው በበጎ ፈቃድ የሚሠሩ ከመሆናቸው አንጻር ወጣቶችን፣ ተማሪዎችን፣ ሌሎች ነዋሪዎችን በማስተባበር፣ ሥልጠና በመስጠት የክፉ ጊዜ ደራሾች ማድረግ ይቻላል። ልክ እንደ ፀረ ኤድስ ማኅበራት ማለት ነው። በሰለጠነውም ዓለም ቢሆን ግማሹ እሳት አደጋ ሠራተኛ በበጎ ፈቃድ የሚሠራ፣ ሰባራ ሳንቲም የማይከፈለው ነው። ለአብነትም በዚህ በአሜሪካ ታዋቂ ከሆኑት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነውንና በእሳት ማጥፋት ሥራ በበጎ ፈቃድ ሲያገለግል የቆየውን ብራያን ዊሊያምስ (Brian Williams) የተባለ ጋዜጠኛ መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ዕድሜው በወጣትነት ደረጃ ያለው ዜጋ ትልቁን ቁጥር የያዘባት አገር ከመሆኗ አንጻር በፖለቲካ ታማኝነት እንዲደራጁ ለማድረግ የምንተጋውን ያህል ለዚህ ዓይነቱም አገራዊ አገልግሎት ለማደራጀት መጣር ይገባናል። በየቀበሌው እና ክፍለ ከተማው ያሉ የወጣት ማኅበራትን ለዚህ አገልግሎት ማሰልጠን፣ ገና ራሱን ያልቻለውን እና ከየቤተሰቡ ጋር የሚኖረውን ብቻ ሳይሆን በፈቃደኝነት ሊሰለፍ የሚችለውን “ራሴን ችያለሁ” የሚለውን ሌላውን ሠራተኛ ማሰባሰብ ይቻል ይመስለኛል።

ይኼ የእሳት ነገር ብዙ ሊባልበት ይቻላል። በከተሞች ብቻ ሳይሆን በቤተ እምነቶችም እንኳን ብንመለከት ታላላቅ አገር ቅርሶች የሆኑ በየገዳማቱ ያሉ ንብረቶች እና ንዋየ ቅድሳት በዕለት እሳት ሲጠፉ እየተመለከትን ነው። የካቲት 5 ቀን 2002 . ከቀኑ 1200 ሰዓት ጀምሮ የአደጋዉ ምክንያት ባልታወቀ እሳት የወደመው በጣና ሐይቅ ዙሪያ ከሚገኙት የዘጌ ገዳማት መካከል አንዱ የሆነው የመሐል ዘጌ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለአብነት ሊጠቀስ ይቻላል።  በአደጋው ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ከዚያ አስቀድሞ የደብረ ዳሞ ገዳም ዕቃ ቤት፣ አዲስ ዓለም ማርያም ሙዚየም፣ የተለያዩ ገዳማት ደኖች በየጊዜው መቃጠላቸውን ከየዜናውም ተረድቻለሁ። እንዲህ ዓይነቱን እሳት ለመከላከል የየእምነቶቹ ተከታዮች ግዴታ ቢኖርባቸውም መንግሥትም ኃላፊነት አለበት። እንዴት አድርገው እሳቱን መከላከል እንዳለባቸው የሚያስተምራቸው፣ የሚያሰባስባቸው ከሌለ ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ከፍላጎትነት አይዘልም።

እኛ አገር እሳት ማዳፈን፣ እሳት መጫር፣ እሳት መዋስ እንጂ የተነሣ እሳት እንዴት እንደሚጠፋ ዝግጅት የለንም። አሁን ግን “እያደግን ነው፤ እየበለጸግን ነው” ካልን የማደግና የመበልጸግ እንዲሁም ከተሜነትን የማስፋፋት አንዱ መገለጫ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እየካቡ ፎቅ መሥራት ብቻ ሳይሆን ፎቆቹን ከነሰዎቻቸው ከአደጋ መከላከልም ነው። ኮንዶሚኒየሞች መስፋፋታቸው ጥሩ ነው። ነገር ግን በኮንዶሚኒየም ውስጥ የሚኖር ሰውም መፍጠር አለብን። የሽንት ቤት አጠቃቀሙ፣ ልብስ ማስጣቱ፣ የዓመት በዓል እርድ መፈፀሙ፣ ቡና መውቀጡ ወዘተ እንዴት መሆን እንዳለበት ከመግባባቱ ጋር ሕይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር ሲገጥም እንዴት መከላከል እንደሚገባም መመካከር ይፈልጋል። ሰዉን ሁሉ ከየቤቱ አውጥተን ፎቅ ላይ አጠራቅመነው ስናበቃ ችግር ሲመጣ መውጫውንም ካላመለከትን ሥራችን ሙሉ አይሆንም። ስለዚህ ከነዚህ ቤቶች አቅራቢያ፣ ቢያንስ በየክፍለ ከተማው እና በየቀበሌው እሳት መከላከያ ክፍሎች ማደራጀት መጀመር ይኖርበታል።           

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::  

      

  

12 comments:

Ameha said...

ወንድሜ ዲ/ን ኤፍሬም እግዜር ይባርክህ! አቧሬን እኔም አውቃታለሁ፤ ብዙም ተመላልሼባታላሁ። ከአዲስ አበባ ከሚናፍቁኝ ሠፈሮች በዋናነት የምትጠቀሰው እሷው ናት። ገበያዋ በመቃጠሉ እጅግ አዝኛለሁ። ለባለ ንብረቶቹ እግዚአብሔር መጽናናቱን ይላክላቸው። የጻፍከውን አስተያየት ዘጠና ዘጠኝ በመቶ እጋራዋለሁ። ለእሳቱ መንስዔ ግን የራሴ ጥርጣሬ አለኝ፤ ሆን ተብሎ በመንግሥት አካለት የተቀነባበረ ይመስለኛል። "ዘመናዊ የንግድ ማዕከል ለመገንባት፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ ለሰጠ ባለ ሃብት አሳልፎ ለመስጠት፣ የአካባቢው ነጋዴዎች ሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት የማይመቹ በመሆኑ ... ወዘተ" ሆን ተብሎ (intentionally) የተፈጸመ ድርጊት ይመስለኛል። ከዚህ ቀደም ጨርቆስንም ያቃጠሉት በተመሳሳይ መልኩ ነበር። ምሥጢሩን ጊዜ ይፈታዋል። ወንድሜ፣ ከዓለማዊ ከመንግሥት ምንም አትጠብቅ፤ እርሱ እንደሆነ የምንወደውንና የምንኮራበትን ነገር ሁሉ ሊያዳክም የተነሳ ኃይል ነው። እርሱ ፍርዱን ከእግዚአብሔር ያገኛል። ከወገናዊነት በመነጨ ስሜት ስላቀረብክልን ጽሑፍ እግዚአብሔር ይስጥልን።

Anonymous said...

እሳት አጥፊዎች እሳቱ በተነሣ በስድስት ደቂቃ ውስጥ መድረሳቸውን ነገር ግን “ውኃ የለንም” ብለው እሳቱ አገሩን ሲያጠፋ አብረው ከሕዝቡ ጋር መታዘባቸውን (እሳቱን መሞቃቸውን?) ዘግቧል።
It is sad news. I share your concern. At this moment, I am designing water supply scheme for a real estate project (not in Eth). The fire demand per capita is more than (>2x) that of domestic consumption requirement. Despite her 'development', Addis Ababa has not yet satisfied the domestic water demand let alone to provide water for fire. Not only our infrastructures are very below the standard, their planning is not well organized.
... But I have a dream one day..........

Ephrem Eshete G. said...

@ Ameha,
According to the articles I read in writing this up, some governments start fires of shanty towns deliberately to force people out of those areas. I am not sure if that of Abuware is the same. I remember the same speculations during the previous government of Col. Mengistu as well. If true, this will be a crime committed against poor citizens of our country.

Anonymous said...

Good answer Ephrem.

Anonymous said...

Dear Eph.

Thank You for sharing your reading from the Reporter and even from your in-depth knowing of Awbuware.

Contrary to the causes explicitly jotted down from the book of Professor AYODEJI OLUKOJU, the Historian; there are, in my understanding, some more causes that come out from arson traits.

In this regard The Government is taking the role of arsonists. With the pretext of development and redevelopment of Addis the poor are getting rid of from their land as garbage and litter is collected for dumping.

TPLF is still masterminding the skill of Koreta (as in Guerrilla) as it had done in the wilderness. On the one hand it articulated the advantage of the New Lease decree which is really treated as a mask for highway robbery acts and on the other hand using Koreta it has now moved to a platform that enable it setting fire to get more land for grabbing so as to get quenched the thirst of hard currency.

I wonder if Abuware is not burnt by TPLF. But it is TPLF who made it happen and no wonder for that for TPLF has an excellent track record of fallacy and lie. To mention a few:

1. Seyoum Mesfin had proudly (to me arrogantly) told us as if Bademe
was ours as per the court decision. (to me deficiency syndrome for
Language proficiency)
2. Plotted bomb attack against innocent civilians to allegedly accuse OLF
of the crime but exposed to public by Wikileaks through US Cable
report.
3. It repudiated the act of giving Ethiopia's land to Sudan but really
evidenced by member of the borders committee as seen on ESAT TV
4. Committed genocide on more than 400 Anuak tribe but the
investigation group under the strict command of the PM had issued
report of fairness
5. The massacre of more than 200 Addis Ababans had been reported as
fair and balanced to the SO CALLED PARLIAMENT. But the Heroes of
the Investigation group denied the report and let themselves for
exile.
6. Terrorize the nation with anti-terrorism law that aimed at silencing
the dissidents from free speech and the nation from claiming the
right to live.

AND SO MANY EVIDENCES

Anonymous said...

Ato meles looks like General Teto of Rome how burnt His countery to blame chrstians the same time meles and His party will burn Addis ababa and its peopels phsicaly even if we are exprianced mentaly.Gobez befor 2 years He was one burn villeg aroun 6 kiloo, Merkato,shola Etc you will see addis the next.....
"Besentu lekatel alech beret metad"
from seattel

Anonymous said...

ጭርንቁስ ኑሮ የሚኖሩ አብዛኛው ያገሬ ሰዎችም እሳት ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ የሚገባም ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ጽሑፍ ነው፡፡ ቀጥልበት ጌታዬ!ጭርንቁስ ኑሮ የሚኖሩ አብዛኛው ያገሬ ሰዎችም እሳት ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ የሚገባም ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ጽሑፍ ነው፡፡ ቀጥልበት ጌታዬ!

Anonymous said...

ኤፍሬም አሪፍ ነገር ነው ያስነበብከን፤ ለመሆኑ እኛስ የብዕራችንን ትሩፋት ዕኖሆ በረከት ማለት የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን በዚህ ድረ ገጽ?

ኤፍሬም እሸቴ said...

Bedesta. Ebakwo Tsefuh kalewot yelakulegn, awetawalehu.

Anonymous said...

zenaw ENDEWEREDE KEHONE isn't it too early to blam the govremment?


Tazabiw washington dc

Anonymous said...

ኤፍሬም ምን ጥግ ጥጉን መሄድ ያስፈልጋል? እኛ እኮ ተሳቅቀን ነው እየኖርን ያለነው፡፡ በቤታችን ዙሪያ ፎቆች በተሰሩ ቁጥር ባለሀብቱ በባለመስታውት መስኮቱ የምንበላውን አሹቅ እና ኮቾሮ አይቶ እንዳያስመልሰው፣ የቤታችን ጣሪያም ሰላሙን እንዳይነሳው እየጸለይን ነው የምንኖር፡፡ ለነገሩ የት ይቀርልናል አንድ ቀን “ እስኪ እነዚህን ጭርንቁሶች ወደዛ በሉልኝ” ማለቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ደግሞ ወይ እሳት ይለቁብናል ወይ............፡፡

Anonymous said...

I am so sad to read such bad news but not surprised!
I guess this is the 3rd or 4th one to happen,,,I wont forget what happened in Merkato and Cherkos gebeya.
Yemigermew tiru wore mesmat newe,,,,Yaltadelech ager!
Like U mentioned,we need to worry more about the people who could not afford to live! Hintsa biqatel Hintsa yitekal,,,,Ye sew lij kibur hiwot gin betam yasazinal! FM from VA