Tuesday, February 7, 2012

መሪ ቃሎች - መፈክሮች

READ IN PDF. አሜሪካ በምርጫ እና የአንድ ፓርቲ ቅድመ ምርጫ ውድድር ተወጥራለች። የሪፐብሊካን ፓርቲ በዚሁ የፈረንጆች ዓመት በሚደረገው ፕረዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ፓርቲውን ወክሎ የሚቀርበውን እጩ ለመምረጥ እየተፎካከሩ ነው። በዚሁ አካሄድ የመረጡት አንድ የፓርቲያቸው ተወካይ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ይፎካከራል ማለት ነው። ለውድድሩ ከገቡት ተፎካካሪዎች መካከል እስካሁን መዝለቅ የቻሉት አራት ሲሆኑ በሚቀጥሉት ቀናት በሚደረጉ ድምጽ አሰጣጦች የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ይቀራሉ ተብሎ ይጠበቃል።


አሜሪካ በርግጥም የዲሞክራሲ አገር ናትና አንድን ፓርቲ የሚወክልን ሰው ለመለየት የሚሄዱበት እልህ አስጨራሽ መንገድ እና የመስፈርታቸው ጠንካራነት በእጅጉ ያስቀናል። በፓርቲው ለመመረጥ የሚደረገው ፉክክር ብቻውን አንድ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ካለው ምንም አይተናነስም። ተመራጮቹም ከግል ገመናቸው እስከ ፖለቲካ አቋማቸው በሚንጠረጠሩበት በዚህ ውድድር የአቅማቸውን ሁ ሉ በማድረግ ላይ ናቸው። በየሳምንቱ በሚደረገው የቀጥታ የቴሌቪዥን ክርክር አንደኛቸው ከሌላኛቸው የሚሻሉበትን ነጥብ ለማቅረብ ይጥራሉ። የሚጠየቁትን ጥያቄ አሳማኝ በሆነ መልኩ ለመመለስ ይሞክራሉ። በዚህ መልኩ እስከ መጨረሻው ከዘለቁ በኋላ ፓርቲውን የሚወክል አንድ ሰው ይሰይማሉ፣ ሌሎቹም እንኳን ደስ ያለህ ብለው እንዲቀናው ይመኙለታል።
እኔ ከሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ መረጣ ሒደት መካከል ላነሣው የፈለግኹት ተወካዮቹ/ተወዳዳሪዎቹ ለምርጫ መሪ ቃልነት የመረጧቸውን ቃላት እና ሐሳቦች በተመለከተ ነው። አሁን ባለው ደረጃ በምርጫው ውስጥ የቀሩት ማለትም ሚት ራምኒ፣ ኒውት ጊንግሪች፣ ሪክ ሳንቶረም እና ጎምቱው ሴናተር ራን ፖል የተጠቀሙባቸውን ብቻ አነሣለሁ። የራምኒ  የምርጫ መሪ ቃል “Believe in America” ሲሆን የጊንግሪች ደግሞ “Rebuild the America We Love” ይላል። ፉክክሩ በሦስተኛነት እና በአራተኛነት የሚከተሉት ሁለቱ ማለትም ሳንቶረም “The Courage to Fight for America" ሲሉ ራን ፖል ደግሞ “Restore America Now” የሚለውን ይጠቀማሉ።

ሚት ራምኒ  Believe in America” (በአሜሪካ እምነታችን የጸና ነው) የሚሉት በዘመነ ኦባማ ሰዎች በአሜሪካ ላይ ያላቸው እምነት እና አመኔታ፣ አሜሪካውያን በአገራቸው ላይ የነበራቸው ኩራት እና ጽንዓት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ለማለት ነው። ዓለም ከተፈጠረች በዚህች ምድር ላይ ከነበሩ መንግሥታት እና ግዛቶች ሁሉ ማንም እንደ አሜሪካ የሚሆን እንዳልነበረ በንግግሮቻቸው የሚያብራሩት የቀድሞው የማሳሹሴትስ ግዛት ገዢ ባዕለ ጸጋው ራምኒ በዚህ “አሜሪካ ልዕለ ኃያልነት” ጽኑዕ እምነት እንዳላቸው የሚያስረዱበት የምርጫ መፈክራቸው ነው። አሜሪካ “እየወደቀች ነው” የሚለው ሐሳብ የሚያንገበግባቸው አርበኛ አሜሪካውያን በሙሉ ከጎናቸው እንዲቆሙ የሚያደርግ ነው።

የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የቀሩት ተፎካካሪዎቻቸው መሪ ቃሎችም በቃላት አቀማመጥ ካልሆነ በስተቀር በይዘት ደረጃ ብዙም ልዩነት አላየሁባቸውም። ጊንግሪች “የምንወዳትን አሜሪካን ድጋሚ እንገንባት” ሲሉ ሳንቶረምና ራን ፖል ደግሞ “ለአሜሪካ ዘብ የመቆም ወኔ” ይኑረን እንዲሁም “አሜሪካን ወደ ቀደመ ክብሯ” እንመልስ ይላሉ። ሲጠቃለል አሜሪካ ታላቅነቷን እንደያዘች እንድትቀጥል “እኔን ምረጡ” ነው።

ባለፉት አሥር ዓመታት የአሜሪካ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እና ሥራ አጥነትም እስከ 9% በማደጉ የሕዝቡ ትልቁ አጀንዳ ይኸው የሥራ አጥነት እና ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። በተለይም ኮሚኒስቷ ቻይና አዲሲቱ ልዕለ ኃያል አገር ለመሆን እየመጣች ነው የሚለው ዜና ብዙዎቹን አሜሪካውያን በእጅጉ ያስቆጫቸዋል። ታዋቂ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አዘጋጆች ይህንኑ በማንሣት ይወተውታሉ። እውነቱ ግን ቻይና እያደገች ነው ቢባልም ኢኮኖሚዋ የአሜሪካንን 1/3ኛ እንኳን በቅጡ አልሞላም። ይሁን እንጂ በምርጫ የሚሳተፉ ፖለቲከኞች ነገሩን በማጋነን እና በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በማሳጣት የምረጡን ዘመቻ ያደርጋሉ። መሪ ቃላቸው የዚያ ነጸብራቅ ነው።

የፖለቲከኞችን ጮሌነት ቀንሰን ስናስበው እንዲህ ዓይነት አርበኝነት ለማንኛውም አገር አስፈላጊ መሆኑ ላይ እንስማማለን። ያለ አገራዊ እና ወገናዊ አርበኝነት እና ወኔ አገርን አገር ማድረግ አይቻልም። ማንኛውም መንግሥትም ቢሆን አገሩን በአርበኝነት መንፈስ የሚመራ ካልሆነ ተቆርቋሪነት እና አሳዳጊነት አይኖረውም። ሕዝቡን ከልቡ የሚያፈቅር፣ ለባንዲራዋ ዘብ ለመቆም የማይደፍር መሪና መንግሥት የሚመራውን አገር ማንኮታኮቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።

መቸም በኮሚኒስት አገር ጥርሱን ለነቀለና ላደገ እንደኔ ላለ ሰው መፈክር ብዙ ትርጉም አለው። ልጆች ሆነን ጀምሮ በየአደባባዩ መፈክር ሲፈከር፣ ሲጻፍ፣ በየሪዲዮኑ ሲመፈከር መስማት የተለመደ ነበር። “አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት”፣ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር”፣ “ማይምነት የጨለማ ጉዞ ነው”፣ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ወዘተ የሚሉት መፈክሮች ዛሬም ድረስ አይዘነጉኝም። በአገራችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጠንካራ የመንግሥት እጅ በሕዝቡ ላይ በጸናባቸው ቻይናንና ራሺያን በመሳሰሉ አገራት በሙሉ ብዙ ብዙ መፈክር ማንጋጋት የተለመደ ነው። የኮሚኒስቶቹ ከምዕራቦቹ የሚለየው ያለ ምንም ተፎካካሪ የእነርሱ ብቻ መሰማቱ ሲሆን ዲሞክራሲ ባለባቸው አገሮች ደግሞ ሌላ አማራጭ ድምጽ ለመስማት መቻሉ ነው።

ፕሬዚዳንት ኦባማ በተመረጡበት የ2008 ምርጫ የእርሳቸው መሪ ቃሎች ኦባማ፣ “Hope/ ተስፋ፣ “change/ ለውጥእና Yes We Can!”/ አዎ፣ እንችላለን የሚሉት በጣም ዝነኞች የነበሩ ሲሆን በማስታወቂያዎች እና በዘፈኖች ሳይቀር አምረው ይቀርቡ እንደነበር እናስታውሳለን። ስለ ፖለቲካ ብዙም ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀሩ የኦባማን “አዎ፣ እንችላለን” አይዘነጉትም። ዓላማውም ይኸው ነበር።

ያነበብኩት በየጊዜው የነበሩ መፈክሮችን የሚያብራራ አንድ ጽሑፍ እንደሚያትተው በየጊዜውና በየዘመኑ የነበሩ ፖለቲካዊ ትኩሳቶችን ተመርኩዘው የሚነገሩ መፈክሮች የሰዎችን ሐሳብ በአጭሩ በመግለጥ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ኮሚኒስቱ ቼ ጉቬራ “Hasta la Victoria Siempre፣ ድል እስኪገኝ ትግላችን ይቀጥላል” በሚለው መፈክሩ ሲታወቅ በደብዳቤዎቹ መጨረሻ ላይ ሳይቀር መዝጊያ ሐረጉ ይኸው መፈክሩ ነበር። ሌላው ኮሚኒስት መሪ ጆሴፍ ስታሊን ከጀርመን ናዚዎች ጋር ይዋጋ ለነበረው ቀዩ ጦር ያስተላለፈው “አንዲት ጋት ወደኋላ አናፈገፍግም” የሚለው መልእክትና መፈክር ታዋቂ አባባሉ ነበር። ሁለቱም ዓላማቸው በነዚህ ሐረጎች ስለሚጠቃለል ሐሳባቸውን በአጭሩ ለማስተላለፍ አስችሏቸዋል።
በሌላ በኩል ፀረ ጦርነት አቋም ይዘው የአሜሪካ መንግሥት በቪየትናም አውጆት የነበረውን ጦርነት ለመቃወም በየአደባባዩ የወጡ አሜሪካውያን “ፍቅር እንጂ ጦርነት አትሥሩ/ Make love not war” በሚለው ፉሩንድስ እና ፈገግ የሚያሰኝ መፈክራቸው ሲታወሱ የፈረንሳይ አብዮት ደግሞ  Liberté, Égalité, Fraternité ነጻነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት” በሚለው ይታወቃል።

መፈክሮች በጎ መልእክት ያዘሉ መስለው ቢታዩም አፈጻጸማቸው ግን ሁልጊዜም እንደ ቃሎቹ ያማሩ ላይሆኑ ይችላሉ። በአገራችን እንኳን “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ከሚለው ልብ መሳጭ መፈክር በኋላ ምድሪቱ ደም በደም ሆናለች፣ ኢትዮጵያም ማንንም ሳትቀድም ቀርታለች። ናዚ ጀመርኖች “Jedem das Seine/ ለሁሉም የየራሱን” የሚለውን ጥንታዊ መፈክር አይሁድን ለመጨፍጨፍ ተጠቅመውበታል። ከጥንታዊ የግሪክ የፍትሕ እና የእኩልነት ፍልስፍና የመነጨውን “ለሁሉም የሚገባውን (መብቱን)” የሚለውን ሐሳብ በማጣመም አይሁድ የሚገባቸው መጨፍጨፍ እንደሆነ ሁሉ በጅምላ መግደያ ካምፓቸው ላይ “Jedem das Seine” የሚለውን ለጥፈው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ጨፍጭፈውበታል።

በተመሳሳይ መልኩ “አብዮት የራት ግብዣ አይደለም” በሚለው አባባላቸው የሚታወቁት የቻይና አብዮት መሐንዲስ ሊቀመንበር ማዖ “አብዮት ተለሳልሰው፣ በቀስታ፣ በአክብሮት፣ በትህትና” የሚያካሒዱት ሳይሆን “በአመጽ፣ በንቅናቄና መንግሥት በመለወጥ ላይ ያነጣጠረ አመጽ” ነው፣ እንዲሁም “ሕዝቡን እናገልግል” ካሉ በኋላ ደም አፋሳሽ አብዮት አካሂደዋል። ፋሺስት ጣሊያን በበኩሏ “Tutto nello Stato, niente al di fuori dello Stato, nulla contro lo Stato ሁሉም ነገር ለመንግሥት (ይሁን)፣ ከመንግሥት ውጪ ምንም (አይሁን)፣ መንግሥትን መቃወም በጭራሽ” በሚለው መሪ መፈክር ከሮም እስከ አዲስ አበባ የብዙ ሰዎችን ደም አፍስሳለች።

መፈክር ከፊት ችግርና መከራ ከኋላ የሚከታተሉበት ጊዜ ብዙ ነው። ድሃውን ለማጥፋት የሚፈልጉ ሰዎች “ድህነት በዲክሽነሪያችን ከዚህ በኋላ ይገኝም” የሚል መፈክር ሊያስነግሩ ይችላሉ። ደሃውን ከየቆሼ መንደሩ ሊመነጥሩት ሲፈልጉ “ከተማችንን የከተሞች ገነት እናስመስላታለን” ሊሉ ይችላሉ። ሥልጣን ላለመልቀቅ ከወሰኑ “መጪው ዘመን ከእኛ ጋር የተሳካ ይሆናል” ቢሉስ ማን ይከለክላቸዋል?

ለሥራ ሊያነሣሣ ይችላል እንጂ መፈክር ሥራ አይደለም። በመፈክር ብን ብሎ የሚጠፋ ችግር የለም። ጨቋኝ መንግሥታት ሕዝባቸውን ቀጥቅጠው ከመግዛት ጎን ለጎን የሚዝናኑበት ነገር ቢኖር የመፈክርና የቃላት ድሪቶ ነው። እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት እና ሚጢጢ ቀበሌ ሁሉ የራሱ መፈክር እያወጣ ሕዝቡን በማይገባው የቃላት ጋጋታ እና ስብሰባ ሥራ ማስፈታት የዕድገት ደረጃ ይመስለዋል። ለወጣት የሚሆን መፈክር፣ ለሴቶች የሚሆን፣ ለገበሬው የሚሆን፣ ለሠራተኛውና ለሮጦ-አደሩ የሚሆን፣ ለወታደሩ የሚሆን መፈክር ስንፈበርክ ማንኪያ ማምረት ሳንችል፣ ሞፈራችንን ቀንበራችንን ሳናሻሽል፣ ከራሺያ የመጣ መፈክር፣ ከቻይና የመጣ መፈክር፣ ከኩባ የመጣ መፈክር ስንተረጉም ልብስ መልበስ አያውቁ የነበሩ አገሮች በዕድገት ጥለውን ተመነጠቁ፤ እኛ አሁንም እዚያው ነን። ከቃላት ጋጋታ ወጥተን ወደ ሥራ እና የአንድነት ዕድገት የምንመጣበትን ቀን በብዙ እናፍቃለሁ። የአሜሪካኖቹ በአገራዊ አርበኝነት የታቀኘውና በሥራ የሚገለጠው መሪ ቃላቸው ዓይኔን የሳበው ለዚያ ሳይሆን አይቀርም። ጽሑፌን “መፈክሮች ያልበዙበት አገር እንዲኖረን መፈክር እናሰማለን” በሚል ሌላ መፈክር ቢጤ ሐሳብ ላጠቃልል?    © ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::   3 comments:

Anonymous said...

ግሩም ነው ኤፍሬም!!! ለወደፊቱም በዲያስፖራ ለምንኖረው የሚሆኑ ተመሳሳይ ጽሑፎችን እንደምታስነብበን ተስፋ አለኝ። የጽሑፎችን ብዛትና ዓይነት በማብዛት በመጽሔት መልክ ማሳተምንም ብታስብበት ምን ይመስልሃል?

asbet dngl said...

ትልቅ አባባል አለው ::በርታ!

Mehari said...

“Tutto nello Stato, niente al di fuori dello Stato, nulla contro lo Stato”

“ጠቅል”፣ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር”፣ “አውራ ፓርቲ” የሚሉት ነገሮች ከዚህ ከጣልያን መፈክር ጋር ይመሳሰላሉ ልበል ወይስ ዓይኔ ነው? የዘንድሮ ዓይን መቼም እንደምታውቁት በሕልሙ ብር በእውኑ ደግሞ በረሮ ሲያይ ስለሚኖር ችግር ያጋጥመዋል፡፡