Wednesday, February 15, 2012

ፊደል የመቁጠር ዕዳ

READ IN PDF.
“የተማረ ይደለኝ” የሚል ተረት ስሰማ ሁሌም ያስቀኛል። እንዲያው በቀጥታውና በጥሬ ትርጉሙ “ከሞትኩ አይቀር” … “ፊደል የቆጠረው ጭጭ ያድርገኝ” ማለት ሳይሆን “የተማረ ሰው ምንም ቢሆን ይሻላል፣ ምሥጢር ይገለጥለታል፣ ክፉና ደጉን ይለያል” የማለት ዓይነት ምስጋና አዘል አባባል ነው። በእርግጥ “የተማረ ይግደለኝ” ብለን ብንል ምሳሌያዊ አባባሉን በጥሬው እንደመነዘሩ ሁሉ፣ የተማሩት ገድለውን፣ እርስ በርሳቸውም ተገዳድለዋል። ቀድሞ በቀይ እና ነጭ ሽብር አልቋል፣ ወይም አገር ጥሎ ተሰዷል፣ ወይ እንትኑን ልፎ ተቀምጧል። ወይም የነእንቶኒ አገልጋይ ሆኗል። እንዲህ እንዲህ እያልኩ “ልወርድበት” አሰብኩና ተወት አድርጌው፣ አስቀድሜ “ይኼ የተማረ ሰው ምን ሊያደርግ ይጠበቅበት ኖሯል?” ብዬ መጠየቅን መረጥኹ።

የተማረ ሰው የምለው ፊደል የቆጠረውን ሰው ለማለት ነው። በጥንቱ ኢትዮጵያዊ ትምህርት ዕውቀት የዘለቃቸው ሰዎች “የተማረ፣ ባለሙያ” ሲባሉ ፊደል ያልቆጠሩት ደግሞ “ግራና ቀኛቸውን የማይለዩ፣ ጨዋዎች” ይባሉ ነበር።  ጥንታዊው የኢትዮጵያ ትምህርት ሃይማኖታዊ እንደመሆኑ የተማረ ሲል ነገረ ሃይማኖትን የለየ፣ ያልተማረ/“ጨዋ” ሲል ደግሞ ደግሞ ነገረ ሃይማኖትን የማያውቅ እንዲያው በደፈናው መጣፍ ማንበብ የማይችለውን ነው። በእርግጥ የአፍርንጁንም-ይሁን-የአገር ቤቱን ተምረው ነገር ግን እንዳልተማሩ የሚሆኑም አሉ። ገጣሚው ደበበ ሰይፉ “ጥሬ ጨው፣ ጥሬ ጨው፣ ጥሬ ጨዋዎች” ያላቸው ዓይነት።

በዘመናችን፣ የአስኳላ ትምህርት (ዘመናዊው ትምህርት) በተስፋፋበት በአሁኑ ጊዜ የተማረ ስንል ያው ከአንደኛ እስከ 12ኛ ብሎም እስከ ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ የዘለቀውን ለማለት እንደሆነ ግብብነቱ አለ። እንደ ጥንቱ ኢትዮጵያዊውን የአገርኛ ዕውቀት ብቻ ማወቅ “ከተማሩት” ተርታ የማያሰልፍ ሆኗል፤ “እንጀራም አያበላም”። እንጀራ መብላት የፈለገ፣ ኑሮውን ማሻሻል የፈለገ፣ ያው ዞሮ ዞሮ የፈረንጁን ዕውቀት ለመቅሰም መትጋት ይገደዳል። የተማረው ትምህርት ጥቅም ይስጥም አይስጥም፣ የፈረንጁን መማሩ ደሞዝ ያስቆርጥለታል፣ ባህር ያሻግረዋል። አገርኛውን ትምህርት ከፈረንጁ ጋር ማነጻጸሩ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም አቅምም ስላይደለ እዘለዋለኹ። የሆነው ሆኖ የመማር ዓላማውና ውጤቱ፣ ኑሮን ከማሸነፍ እና የሰው እጅ ከማየት በዘለለ፣ ምን ነበር? ፊደል የቆጠረውስ ካልቆጠረው እንዲለይ የሚጠበቅበት ምን ኖሯል?

የተማረ ሰው በሚኖርበት አካባቢ የማይነቃነቅ ማንነትን የተከለ፣ በምግባሩ ጽኑዕነት ሌሎች ሊረዱት የሚችሉት አሻራ የሚተው ነው። በተለያዩ ተለዋዋጭ ጉዳዮች ውስጥ የተማረ ሰው ፊደል ከመቁጠሩ በሚያገኘው አዕምሯዊ ጥንካሬ ራሱን ጠብቆ ለመዝለቅ ስለሚችል አዋቂ መሆኑን ያስመሰክራል። አንድ አገር እና አንድ ሕዝብ በሚገጥመው ውጣ ውረድ ውስጥ የተማረ ሰው መኖር ትክክል የሆኑ ነገሮችን ካልሆኑት መለያ ሚዛን ነው።

አንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ አጠቃላይ ማኅበራዊ ድቀት (Crisis) ውስጥ በሚገባበት ወቅት የነገሮችን ትክክል ያልሆነ አካሄድ በመመልከት “ቀይ መብራት” ማብራት ለበት የተማረው ሰው ነው። ፈረንጆቹ በማንኛው ድርጅት ውስጥ የሚፈጸሙ ድብቅና ጎጂ ተግባራትን ተመልክተው ውስጥ-አወቅ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ ሰዎችን “ዊስል-ብሎወርስ/whistleblower” እንደሚሏቸው የተማረ ሰውም የአገር-ጉዳይ፣ የሕዝብ-ጉዳይን በተመለከተ “ዊስል ብሎወር” ነው። “ምን አገባኝ?” ሊል እንደማይገባው ሁሉ “ምን አገባህ?” ሊባልም አይችልም፣ አይገባምም።

በምን ምክንያት ነው እንዲህ ያለውን ከባድ ነገር ከተማረ ሰው የምንጠብቀው? በምን ዕዳው?” ከተባለ ይህ “ፊደል የመቁጠር ዕዳ” ነው ባይ ነኝ። አለበለዚያማ ጥሬ ጨው መሆን ነው።

 በእርግጥ የተማረ ሰው ሁሉ እንዲህ አይሆንም። በየሙያቸው ታላላቅ ተግባራትን የፈፀሙ ነገር ግን ከሥራቸው-ቤታቸው ከማለት ባለፈ በማኅበረሰባቸው የዕለት-ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ አሻራ የማይተዉ ታላላሊቃውንት አሉ። እነዚህ የውስጥ-ምሁራን እንጂ የአደባባይ-ምሁራን ስላልሆኑ በሕዝቡ እርምጃ ላይ በጎውን “በጎ”፣ መጥፎውን “መጥፎ” ብለው የመናገር ልማድ የላቸውም። የተማሩም ቢሆኑ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እና በሚተዉት አሻራ ከግምት ውስጥ የሚገቡ አይደሉም። ብዙዎቹም አገራዊ ማንነታቸውን፣ ባህላቸው እና በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያላቸውን ቦታ ፈልገው ለማግኘት ያልደከሙ ስለሚሆኑ የጠፋውን ካልጠፋው - የተበላሸውን ካልተበላሸው ላይለዩም ይችላሉ።

በብዙዎች የሦስተኛው ዓለም አገሮች እንደሚታየው ፊደል የቆጠረው ወገን በባዕዳን የዕውቀት መስመር የተከረከመ ዕውቀት ይዞ ስለሚገኝ አገሩ እና ሕዝቡ ከቅኝ ግዛት በወጡበት ጊዜ ሳይቀር የምሁሩ አዕምሮ ግን በቀደምት ገዢዎቹ ማንነት የተቀየደ ሆኖ ይገኛል። አገርን ነጻ ከማውጣት በላይ ከባድ የሚሆነው የተማረውን ሰው ካለፈው የገዢዎቹ አስተሳሰብ ነጻ ማውጣት ሳይሆን አይቀርም። በብዙዎች የአፍሪካ አገሮች የተስተዋለው ይኸው ነው። አገሮቹ ከፈረንጆቹ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡ በኋላ በራሳቸው ዜጎች ጭቆና ሥር ስለሚወድቁ ለውጡ የገዢዎች እጅ መፈራረቅ እንጂ እውነተኛ ነጻነት ሳይሆን ቀርቷል። በአጭር አገላለጽ “ፈረንጁ በጥቁር ቆዳ” (White man in black skin) ነው። የጥንቱ ነጭ ገዢ ወጥቶ፣ ጥቁር ገዢ ተተክቶ ማለት ነው። “የፈረንጅ ገዢ ቶፋ ውጣ፣ የጥቁር ገዢ ቶፋ ግባ” እንደማለት።

በአገራችን የፈረንጁ ትምህርት በዘፈቀደ እንዲሰለጥንብን መብት ከተሰጠበት ዘመን ጀምሮ (የፈረንጅ ትምህርት መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም) በየዘመናቱ የፈጠርነው የተማረ ሰው ከአገራዊ ማንነቱ በብዙው ተስፈንጥሮ ከመውጣቱ ጋር ያለፈ ማንነቱን ፍለጋ ያደረገው ጉዞ ብዙ ባለመሆኑ (ወይም እኔ በቅጡ ስላላየኹት ይሆናል) አገራችንን የሚመዝንበት ሚዛን ከሌሎች አገሮች የተዋሰው የተውሶ ሚዛን ነው። አንድም “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” ብሎ በጃፓን፣ በፈረንሳዮች ሲመሰጥ በእነርሱ፣ ንጉሳዊ-ፓርላሜንታዊው እንግሊዝ ሲመስጠው በእንግልጣሩ ብሎም በአሜሪካው፣ የራሺያው ሥር ነቀል አብዮት ልቡን ሲስበው በማርክሳዊው-ሌኒናዊው-አልባኒያዊው አሁን ደግሞ በቻይናዊው ሚዛን ነው። ምሁሩ ለፍለጋው የተደላደለ ወደብ ገና አላገኘም። ወይም ፍለጋው ምሁራዊ አይደለም። ወይም ጅማሬው ከውጪ ወደ ውስጥ እንጂ ከውስጥ ወደ ውጪ ባለመሆኑ ትክክለኛ መልስ ማግኘት አልቻለም። አገራችንም አንዴም የዳገት፣ አንዴም የቁልቁሊት ውጥንቅጥ ጉዞዋ አልተገታም።

የተማረ ሰው ካለ በእርግጥም ለውጥ ይጠበቃል። የትምህርትስ ግቡ ለውጥ አይደለም? ይህ ለውጥ ደግሞ ከመመርመር፣ ዘወትር ራስን ከመጠየቅ ይመነጫል። መነሻን፣ አቅጣጫን፣ ግብን ከመጠየቅ። ባዩት ተደላድሎ አያስቀምጥም፣ እኔ ከኖርኩ ሌላው ምን ገዶኝ አያስብልም - መማር። አገርና ሕዝብ ያሉበት አጠቃላይ ሁኔታ ይቆረቁረዋል። ይህ ፊደል የመቁጠር ዕዳ ነው። የመማር ዕዳ። ክፉና ደጉን፣ ግራና ቀኝን የመለየት ዕዳ። በሁኔታዎች ተደላድሎ የሚቀመጥ ያላወቀ-ያልጠነቀቀ ብቻ ነው።

ፊደል የቆጠረ ሰው ኅሊናዊ ማንነቱ በብዙው ይጠይቀዋል። ከሚዘርፈው ጋር ዘርፎ፣ ከሚገድለው ጋር ገድሎ፣ ከሚዋሸው ጋር ዋሽቶ … ብቻ ሆዱን ሞልቶ … ለማደር አይተጋም። አዕምሮው አይፈቅድለትም። አንድም በግዞት፣ አንድም ራሱ ላይ በፈቃዱ ግዞት ጥሎ ለመኖር የሚገደደው ለዚህ ነው። ግፋ ሲልም እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱን ሐሰት ብሎ ይናገራል፤ የሚደርስበትንም ይቀበላል። ከመምህራን እስከ ጋዜጠኞች፣ ከአገር ሽማግሌዎች እስከ ሃይማኖት መሪዎች ድረስ በዚህ መልኩ በየዘመኑ እውነትን በማሳየት የቆሙ አብነቶች እናውቃለን። ከእውነት ጋር ለመቆማቸው የሚከፈላቸው ግን የአበባ ጉንጉን ላይሆን ይችላል። በአብዛኛውም የብረት ሰንሰለት ጠብቋቸዋል። የማወቅ ዕዳው ይህ ነው።

ለምን ዕዳ አልኩት? ምክንያቱም ፊደል የቆጠረ ሰው የሚኖረውና የሚመራው ሕይወት እውነትን ተገን ያደረገ ከመሆኑ አንጻር ሊያጋጥመው የሚችለው ውጣ ውረድ ብዙ ስለሚሆን ነው። ይሁን እንጂ ፊደል የቆጠረ ሰው ሁሉ እንዲህ አይደለም። እንዲያውም ከሐሰት ጋር ለሚቆሙት፣ ሕቡን በብረት በትር ለሚቀጠቅጡት፣ ድሃውን የችጋር ቀንበሩን ለሚያከብዱበት አንደበት የሚሆኑት ፊደል የቆጠሩ በልቶ-አደሮች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ሙያ እና ዕውቀት አያንሳቸውም። በንግግር አፍ የሚያስከፍቱ፣ በአዕምሮ ብስለታቸው ከማንም የማይተናነሱ፣ በብዕራቸው የሚያስደምሙ፣ በሊቅነታቸው ሊመሰከርላቸው የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን ከእውነት ጋር ለመቆም ዳተኞች ናቸው። ለዚህም ነው ከክፉ ሰዎች - ከጨቋኝ ገዢዎች አጠገብ አንቱ የተባሉ ሊቃውንት የማናጣው። ያውም ምርጥ ሊቃውንት። ነገር ግን የፊደል መቁጠርን ዕዳ ለመሸከም ያልቻሉ ራስ ወዳዶች። ደበበ ሰይፉ “ጥሬ ጨው” በሚለው ግሩም ግጥሙ እንዲህ ያላቸው፦

መስለውኝ ነበረ

የበቁ የነቁ

ያወቁ የረቀቁ

የሰው ፍጡሮች

ለካ እነሱ ናቸው

ጥሬ ጨው…ጥሬ ጨው ጥሬ ጨዋዎች

መፈጨት-መሰለቅ-መደለዝ-መወቀጥ-

መታሸት-መቀየጥ

ገና እሚቀራቸው

“እኔ የለሁበትም!”

ዘወትር ቋንቋቸው።

 በሌላ አገራዊ አነጋገር “እንደ ንጉሡ አጎንብሱ” ባዮች ማለት ነው። የትኛውም አገር ከሚገባበት አዘቅት መውጣት የቻለው ትክክለኛው ፊደል የቆጠረው ሰው አስተሳሰብ እና መስዋዕትነት የ“በልቶ-አደር” ምሁራንን መጋረጃ ማለፍ ሲችል ይመስለኛል። አገር ችግር ላይ ካለ “ችግር ላይ ነን”፣ መንገዱ ስሕተት ከሆነ “ትክክል አይደለንም” ለማለት በደፈሩ ፊደል-ቆጠሮች ብርታት ነው መንግሥታትም ሆኑ ማኅበረሰቦች ከተሳሳተ መንገዳቸው መውጣት የሚችሉት። “አይዟችሁ ጅቡ እግራችንን እየበላው ነው እንጂ ምንም ችግር የለም” የሚሉ የቤተ መንግሥታት ምሁራን መበራከት ግን ለአገር መጥፎ መርዶ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የሚፈለጉት የገዢዎቻቸው አስተሳሰብ ትክክል መሆኑን ለመመስከር ነው እንጂ መሪዎቻቸው እውነቱን እንዲያገኙ ለመርዳት አይደለም።

በዘመነ አጼ ምኒልክ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባከዳኝ ዘመኑን “ለመጠየቅ፣ እውነቱን ለመፈለግ” እንደሞከረው፣ ጣሊያን ከአገራችን ከተባረረ በኋላ ባለው ዘመን የነተሡ ብዙ ምሁራን የአገራቸው ኋላ ቀርነት አንገብግቧቸው “ለምን እንዲህ ሆንን?” ብለው በቁጭት እንደጠየቁት፣ ከ50ዎቹ ማግስት ብሎም በ60ዎቹ የሕዝቡ ድህነት ያሰቀቃቸው ፊደል-ቆጠሮች ከበድ ያሉ አገራዊ ጥያቄዎችን ለማንሣት እንዳላፈሩት ሁሉ ዛሬም ፊደል የቀመሰ ሰው የመማር እና ፊደል የመቁጠር ዕዳውን ለመሸከም መብቃት አለበት። አሊያማ የመማር፣ ፊደል የመቁጠር ትርፉ ምንድር ነው?

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

14 comments:

Mehari said...

ይኸውልህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማሪያ ክፍል ወንበር ላይ ተጽፎ ያገኘሁት ግጥም እንዲህ ይላል፡-
የተማረ ይግደለኝ ይላል ያገሬ ሰው፤
ይኸው ተማርኩለት መጣሁ ልጨርሰው፡፡

ይህንን ግጥም እኔ የፈጠርሁት ወይም እያጋነንሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ የእውነት ተጽፎ ያገኘሁትን ነው፡፡ ያውም የሩቅ ጊዜ እንዳይመስላችሁ ዘንድሮ ነው ያየሁት፡፡ ዘንድሮ!
እንግዲህ ምንተረፈን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ተማሪ መፎከሪያው “ሳይማር ያስተማረኝን…” ሳይሆን “መጣሁ ልጨርሰው” ከሆነ ከየደመወዛችን ላይ ግብር የምንገፈግፈው፣ ገበሬውም አፈር ገፍቶ አፈር መስሎ ግብር የሚከፍለው አንድ ምሁር እንዳሉት "ጃርት ለማሳደግ" ነው ማለት ነው፡፡ እኚህ ሰው በዚሁ ባጋመስነው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ የሀገሪቱን የትምህርት ሚኒስትር “አሁን እያፈራን ያለነው ሀገር የሚበላ ጃርት ነው፡፡” ሲሉ በምሬት ማጠንቀቃቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ጃርቶቹ ክፋታቸው ተክሉን ማውደማቸው ብቻ አይደለም፤ ማንም ሊከለክላቸው የሚሞክረውን በእሾሃቸው ድራሹን ማጥፋታቸው እንጂ፡፡

ስለሆነም ስለትምህርት ስታስቡ ይህቺን ግጥም እንዳትረሷት አደራ!
የተማረ ይግደለኝ ይላል ያገሬ ሰው፤
ይኸው ተማርኩለት መጣሁ ልጨርሰው፡፡

የት እየሄድን ነው?

Mehari said...

ይኸውልህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማሪያ ክፍል ወንበር ላይ ተጽፎ ያገኘሁት ግጥም እንዲህ ይላል፡-
የተማረ ይግደለኝ ይላል ያገሬ ሰው፤
ይኸው ተማርኩለት መጣሁ ልጨርሰው፡፡

ይህንን ግጥም እኔ የፈጠርሁት ወይም እያጋነንሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ የእውነት ተጽፎ ያገኘሁትን ነው፡፡ ያውም የሩቅ ጊዜ እንዳይመስላችሁ ዘንድሮ ነው ያየሁት፡፡ ዘንድሮ!
እንግዲህ ምንተረፈን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ተማሪ መፎከሪያው “ሳይማር ያስተማረኝን…” ሳይሆን “መጣሁ ልጨርሰው” ከሆነ ከየደመወዛችን ላይ ግብር የምንገፈግፈው፣ ገበሬውም አፈር ገፍቶ አፈር መስሎ ግብር የሚከፍለው አንድ ምሁር እንዳሉት "ጃርት ለማሳደግ" ነው ማለት ነው፡፡ እኚህ ሰው በዚሁ ባጋመስነው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ የሀገሪቱን የትምህርት ሚኒስትር “አሁን እያፈራን ያለነው ሀገር የሚበላ ጃርት ነው፡፡” ሲሉ በምሬት ማጠንቀቃቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ጃርቶቹ ክፋታቸው ተክሉን ማውደማቸው ብቻ አይደለም፤ ማንም ሊከለክላቸው የሚሞክረውን በእሾሃቸው ድራሹን ማጥፋታቸው እንጂ፡፡

ስለሆነም ስለትምህርት ስታስቡ ይህቺን ግጥም እንዳትረሷት አደራ!
የተማረ ይግደለኝ ይላል ያገሬ ሰው፤
ይኸው ተማርኩለት መጣሁ ልጨርሰው፡፡

የት እየሄድን ነው?

Anonymous said...

thank u

ኤፍሬም እሸቴ said...

ውድ መሐሪ፣
ግሩም ታዝበዋል።

ቁጭቱ said...

በጣም ድንቅ ጽሑፍ ነው ኤፍሬም በርታ! በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ፊደል የመቁጠር ዕዳው ተከፍሎ የሚያልቅ አይመስልም። ፊደል የቆጠርነውም ሆነ እየቆጠሩ ያሉት ያለብንን ኃላፊነት በአግባቡ የተረዳነው አይመስልም። እንዲያውም በዘመናችን የተማረ ሰው መገለጫው ፍራቻ ሆኗል። የማንፈራው ስንተኛም ስንነቃም ከእኛ የማይለየውን ህሊናችንን ብቻ ሆኗል። ህይወታችን ደስታ አልባ የሆነውም ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል። መቼ ይሆን እውነቱን ተናግረን የመሸበት የምናድረው? እንኳንስ በሃገር ደረጃ በቡና ላይ ውይይት ላይ እንኳ ብዙኃኑ የተስማሙበትን ሳይሆን የምናምንበትን ደፍረን መናገር የማንችል “ምሁራን” በመበራከታችን ማሕበረሰባችንን ለቀቢጸ ተስፋ እየዳረግነው እንገኛለን። እውነቱን ለመናገር በየመንደራችን ሲናገሩ የሚደመጡ ፣ቢቆጡ የሚፈሩ አባቶችና እናቶች እየጠፉ የመጡት “ያልተማሩት“ “ፊደል የቆጠሩት”ን ተስፋ በማድረግ “ለተሻሉት” ላሏቸው ቦታውን በመልቀቃቸው ይመስለኛል። በአንጻሩ “የተማሩት” በማንኛውም መመዘኛ (በተጨባጭ ዕውቀት፣ በሞራል ፣ በጽንዓት፣ በእውነተኝነት፣...ወዘተ)ከ”ተርታው” ማኅበረሰብ የማይሻሉ ሆነው በመገኘታቸው እነሆ ከማንወጣበት አዘቅጥ ውስጥ እንገኛለን። ምን ብናደርግ ይሻል ይሆን? እንደ እኔ እንደ እኔ ፊደል የቆጠርነው ሰዎች፤
1. የክፋት ሁሉ ምንጭ ከሆነው ከፍቅረ ንዋይ በመራቅ የተመጠነ ህይወት መኖር፣
2. ህሊናንና ክብርን አዋረዶ መኖር በቁም መሞት መሆኑን ማመን፣
3. የራስን፣ማኅበረሰቡንና የሃገርን ክብር ከሚነኩ ማናቸውም ተግባራት መለየት፣
4. ከተጠናወተን “የጠላቴ ጠላት ሁሉ ወዳጄ ነው!” ከሚል ቢሂል መላቀቅ፣
5. በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት ስም የሚራመዱ “ትውልድ ገዳይ” አስተሳሰቦችን ለመቃወም መድፈር ፣
6. ከቀደሙት ምሁራንና ከታላላቆቻችን ለመማር መዘጋጀት፣
7. ከማንኛውም ምንጭ የምናገኘውን ዕውቀት ከመቀበላችንና ከማቀባበላችን በፊት በጎና ጎጂ ጎኖችን መመዘን ፣
8. ከሁሉ በላይ በተሰጠን እውቀት የተጠያቂነት ሰሜት ሊሰማንና በታሪክና በእግዚአብሔር ፊት የምንጠየቅ መሆናችንን አለመዘንጋት ጥሩ ይመስለኛል ::
እስቲ እናንተም የሚመስላችሁን በመግለጽ ከፊደል መቁጠር እዳችሁ ሽርፍራፊ ሳንቲም ቀንሱ።
ቁጭቱ

Anonymous said...

አገርና ምሁርን ማሰብ እህህ ነው ትርፉ… ፅሑፍክን ግን ወድጄዋለሁ፡፡ አንጀቴን አራስከው፡፡ እግዜር አብዝቶ ይባርክህ!አገርና ምሁርን ማሰብ እህህ ነው ትርፉ… ፅሑፍክን ግን ወድጄዋለሁ፡፡ አንጀቴን አራስከው፡፡ እግዜር አብዝቶ ይባርክህ!

Dawit Worku said...

ይደንቃል!! ይሄ ነው እንግዲህ ባፍ ይጠፉ በለፈለፈፉ ማለት፡፡

Anonymous said...

ያልተማረ ይግደለኝ

ትላነትን አፈቀረኩት!...ዛሬን ግን ጠላሁት
አፌን ለሆድ ብቻ ሲጮህ አገኘሁት
ትንሽ መግፋት ቢቻል ጊዜን ወደ ኋላ
እኔስ በተሰየምኩ ከአባቴ ፊት ከአያቴ ኋላ
ወይ ታሪኬ ሲፃፍ ወይ ግፌ ሲሰላ፡፡
አባባ ገድልክ ለምን ነው የነገርከኝ
ከትላንት አሳቅለህ ዛሬን አስጠላኸኝ
የተማረ ይግደለኝ ብለህ አጓጉተኸኝ
በፅልመት አስኳላ አረንቋ ውስጥ ጣልከኝ
ብከፍተው ገለባ
ህይወት ትግል አልባ
ትግልም ህይወት አልባ
ይልቅስ ልንገርህ ሞትህን በተማረ መመኘትን እርሳው
ፅድቁን ከፈለከው
ፊደል ያልቆጠረ ያገርህ ገበሬ ተኩሶ ይጣልህ ይግደልህ ከማሳው…
written by አለኝታ ፈለቀ on graduation bulletin

Abiy sweden said...

WELL ARTICULATED!!

lily said...

“አይዟችሁ ጅቡ እግራችንን እየበላው ነው እንጂ ምንም ችግር የለም” weyi grum biyalehu Ababaye

ፈይሳ said...

አጃኢበ ረቢ ብያለሁ!!!

Anonymous said...

ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የሚፈለጉት የገዢዎቻቸው አስተሳሰብ ትክክል መሆኑን ለመመስከር ነው እንጂ መሪዎቻቸው እውነቱን እንዲያገኙ ለመርዳት አይደለም።

Anonymous said...

bizu asikehegnal. mihuris yet ale? fidelus yet ale? fidel sanor endet ne mihurinet?????

Anonymous said...

Yetwededk Ephrem betam ejege betam new yasedesetkeng yezendero sew menun temarew ? yetmare yemibalew endat ayentu endehon melyet eskiyaketn honale andane geza alememara mebareke new elalhu mekenyatum yemare sew aredo chersen be hulum melku endew behulum YTEMAR YEGEDELNG ALENE BANELEM EYGEDELEN NEW !!!!!!!!!!!!!!!!betam amsegenalhu Egziabeher yebarekeh