Monday, March 12, 2012

አገር በስኳርና በቢራ ፋብሪካ ብቻ አገር አይሆንም፤ በባህልም፣ በቅርስም፣ በማንነት፣ በሃይማኖትም እንጂ

READ IN PDF.

ቅድመ ነገር

ሰሞኑን የተለያዩ ጦማርያን (ብሎገሮች)፣ የአገር ቤት ጋዜጦች እና የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ስለ ዋልድባ ገዳም ይዞታ መነካት ጉዳይ ዘገባዎችን አቅርበዋል። “ደጀ ሰላም” የጡመራ መድረክ (ብሎግ) የገዳሙ አባቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ያቀረቡትን ደብዳቤ ከማቅረቡም ባሻገር “በገዳሙ ክልል እና ዙሪያ (በዓዲ አርቃይ ወረዳ በኩል) የፓርክ ይዞታ ለመከለል እና የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም በሚል በሚካሄደው የጥርጊያ መንገድ ሥራ (ከማይ ፀብሪ እስከ ዕጣኖ ማርያም) የቅዱሳን አበው ዐፅም እየፈለሰ መሬቱ እየታረሰ” መሆኑን (ARTICLE) አስነብቦናል። የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ደግሞ ነገሩን ሰፋ አድርጎ ከገዳሙ ተወካይ ጋር ያደረገውን ውይይት አስደምጦናል።

በዚህም መሠረት የገዳሙ ተወካይ አባቶች ጠ/ሚኒስትሩን ለማነጋገር ሄደው እንዳልቻሉ፣ በፈንታው እንግዶቹን በስልክ ያነጋገሩ የጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ኃላፊ የመነኮሳቱን ጥያቄ ከድፍረት መቁጠራቸውን፣ ቅዱስ ፓትርያርኩን ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካላቸው አስደምጦናል። አክሎም በገዳሙ አካባቢ ወታደሮች መሠማራታቸውን፣ የገዳሙን መነኮሳት በክፉ ዓይናቸው እንደሚመለከቷቸው፣ የአካባቢው ምዕመናን በነገሩ ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ እንደገቡ፣ የቅዱሳን አጽም እንዲፈልስ (እንዲቆፈር) እና እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን በዝርዝር አቅርቧል። የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በመ/ፓትርያርክ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ስታሊን ገ/ሥላሴንም ጠይቆ ሲያበቃ ቤተ ክህነቱ “ጉዳዩን እየተመለከተው” እንደሆነ፣ ለጠ/ቤተ ክህነቱ ደብዳቤው በግልባጭ ብቻ እንደተገለጸለት፣ መንግሥት አካባቢውን ለልማት እንደሚፈልገው እና ላለፉት አምስት ዓመታት ጥናት ሲያደርግ እንደቆየ፣ ልማቱ ገዳሙን የሚነካ አለመሆኑን ሲናገሩ አድምጠናል። (ቤተ ክህነቱ አምስት ዓመት እያወቀ ዝም ብሏል ማለት ነው?)።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን ከመንግሥት በኩል ምንም ሲባል አልሰማንም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዳት እንዳሉት “መነኮሳቱ መንግሥትን ለማናገር መሞከራቸው በራሱ ከድፍረት” ተቆጥሮ ለዚህ ድፍረት ደግሞ መልስ መስጠት እንደማይገባ ታስቦ ይሁን ወይም ጉዳዩ ገና “እየታየ” ይሁን ምንም አልተገለጸም።

 

ታሪክ በአጭሩ

ዋልድባ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኝ ታሪካዊ እና ታላቅ ገዳም ነው። የገዳሙ ታሪክ እንደሚያትተው ከሆነ ገዳሙ የተመሠረተው በ485 ዓ.ም ነው። በተለያየ ዘመን የተለያዩ አበው በገዳሙ ኖረው ያለፉ ቢሆንም ገዳሙን በማቅናት የሚታወቁት ግን የ14ኛው መ/ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ቅዱስ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ናቸው። ከዚያም በኋላ በአጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ገዳሙ በአራት ጅረቶች መካከል እንዲሆን ተከልሎ ገዢ እንዳይገባበት፣ አራሽም እንዳይሠማራበት (“እንበለ ፈላሲ ኢይባዕ ነጋሲ” እንዲል) ሥርዓት ተሠርቶለታል። በዘመነ ግራኝ ደግሞ የመጥፋት አደጋ ከደረሰበት በኋላ በድጋሚ ለመቋቋም እንደበቃ ታሪኩ ያትታል። እነሆ አሁን ደግሞ በነዚህ ሁሉ ዘመናት በአበው ጸሎት እና በገዳማውያኑ ትጋት ተጠብቆ የነበረው የገዳሙ ይዞታና ክልሉ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው።

 

ሐተታ

እንዲህ ያለው ከበድ ያለ አገራዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የጉዳዩ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል። በዚህ የዋልድባ ምሳሌነት አንጻር ከተመለከትነው ገዳሙ ስብሐተ እግዚአብሔር የሚደርስበት፣ መናንያን ከአምላካቸው ጋር የሚገናኙበት ሃይማኖታዊ ሥፍራ ስለሆነ ገዳማውያኑ ይመለከታቸዋል። ከዚያም አስከትለን ካየነው ቤተ ክህነቱ በየደረጃው ይመለከተዋል። የሃይማኖት ጉዳይ ነውና ሕዝበ-ክርስቲያኑ ይመለከተዋል። ብዙ ሃይማኖታዊ እና አገራዊ ጉዳዮች የተፈፀሙበት ሥፍራ ነውና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይመለከተዋል። አገሪቱ መንግሥት ስላላት ደግሞ መንግሥትም ይመለከተዋል። ኢትዮጵያውያን፣ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥትም ብቻ ሳይሆኑ በጎ ልቡና ያላቸው ሰዎች ሁሉ ያገባቸዋል። ምክንያቱም በአንድ አገር ያለ ቅርስ በቅርበቱ የዚያ ያለበት ሀገር ንብረት ቢሆንም በስፋት ካየነው ግን የሰው ልጅ ሁሉ ንብረት ነው። ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ቋንቋ ሳይለይ።

እነዚህ ሁሉ “ባለ ድርሻ አካላት” ናቸው። ይሁን እንጂ ባለ ድርሻ አካላቱ መንግሥት እያደረገ ስላለው ስለዚህ ፕሮጄክት እንዲያውቁ ካለመደረጉም በላይ “ያገባናል” ብለው “አቤት” ለማለት ወደ መንግሥት አካላት የመጡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው “አደራ ጠባቂዎቹ” ገዳማውያን “መንግሥትን እንደደፈሩ” በኃይለ ቃል እንደተመለሰላቸው ተናግረዋል።

በአገራችን የሚሠሩ ሥራዎች “ባለ ድርሻ አካላትን” በቅንነት ለማካተት ያላቸው ዳተኝነት ከፍተኛ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትጫወተው ማንኛውም ዓይነት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ ዝቅ እያለ፣ ወደ ዳር እየተገፋች እንደመጣች የዋልድባው ጉዳይ ጉልህ ማሳያ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደማንኛውም የእምነት ድርጅት እና ተቋም ይዞታዎቿን ለማስከበር እና በሕግ አግባብ ድንበሯን ጠብቃ ለመኖር እንድትችል የሚያደርጋት ውስጣዊ አስተዳደር ከማጣቷም ባሻገር በመንግሥት በኩል የሚደረገው “ክብር ለሚገባው ክብርን ያለመስጠት” አካሔድ የሚፈለገውን ልማት ከማምጣት  ይልቅ አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል  ይችላል።   

ልማት ለአገራችን አስፈላጊ መሆኑን በማስረገጥ ማስቀመጥ ያስፈልገናል። ልማት ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ በመንግሥትም ይሁን በግለሰቦች ገንዘብ የሚከናወኑ ልማቶችን መደገፍ እንደሚገባ አምናለኹ። የስኳር ፋብሪካም ሆነ የቢራ ፋብሪካ ቢስፋፋ ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን የስኳር ፋብሪካውም ሆነ የቢራ ማምረቻው ሃይማኖትን፣ ዜግነትን፣ ማንነትን፣ አገራዊ ሀብትን እየዳጠ እና እየገፋ የሚሠራ ከሆነ ግን አንዱን እያጠፉ ሌላውን አለማለሁ ማለት ልማት ሳይሆን ጥፋት ነውና ትክክል አይደለም ብሎ መናገር ያስፈልጋል። ከላይ በመግቢያችን ያየናቸው ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በዋልድባ እየሆነ ያለው እንደዚህ ነው።

ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በእጇ የገቡ ይዞታዎችን ያለ ምንም ጥቅም ይዛ ተቀምጣለች የሚል አስተያየት በብዙ መንገዶች ሲገለጽ በስፋት ይደመጣል። ገዳማቷ፣ አድባራቷ እና የከተማ አብያተ ክርስቲያኗ ያላቸው የባለቤትነት መብት በየጊዜው ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ ነው። በዋልድባ ገዳም እና በዙሪያው ያለው መጠነ ሰፊ ይዞታ በሃይማኖት አንጻር ቅድስናው እንደተጠበቀ ሆኖ ደኑ፣ ተፈጥሮው፣ አፈሩ፣ እና በውስጡ ያለው ሀብት ተጠብቆ በመቆየቱ ረገድ ገዳማውያኑ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፤ ይጫወታሉም። ለዋልድባ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ገዳማት፣ አድባራት እና አብያተ ክርስቲያናትም የሚሠራ ነጥብ ነው። የሰው እግር የደረሰባቸው መሬቶች በሙሉ ከተፈጥሮ ሀብታቸው ተሟጠው ገጥጠው ሲቀሩ፣ አረንጓዴ አጸድ የተረፈው በእነዚህ የተቀደሱ ሥፍራዎች ብቻ ነው። ማስረጃ ለሚፈልግ በአውሮፕላን ወደ ሰሜን ይጓዝና በመስኮት ቁልቁል መመልከት ብቻ ይበቃዋል።

ከዚህ አንጻር በዋልድባ ተጀመረ የተባለው መሬት መቆፈር ከሃይማኖታዊ ትርጉሙ ባሻገር በሁሉም መስክ ያለው ትርጉም በቅጡ ሊጠና እንደሚገባው እሙን ነው። መንግሥት በተፈጥሮ ጥበቃ በኩል በተለይም ከውጪ ተቋማት ተደጋጋሚ ወቀሳ እንደሚደርስበት ይታወቃል። ለምሳሌ በግልገል ጊቤ ቁጥር 2 ግድብ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ተቋማት “የተፈጥሮ ሚዛን” ያናጋል በሚል ሲቃወሙ ሰንብተዋል። በዋልድባ ያለው ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሥፍራን የመግፋት እንቅስቃሴ ግን በዋነኝነት ከአገር ውስጥ ያውም ከሕዝበ ክርስቲያኑ እና ቀና ልቡና ካላቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሁነኛ ተቃውሞ ሊቀሰቅስ እንደሚችል ከግምት ውስጥ ሊገባ ያስፈልጋል። ምናልባት ቤተ ክህነቱ (አቶ ስታኒል እንዳሉት) የተለየ ድምጽ አለማሰማቱ እንደማጽናኛ ሆኖ ካልተቆጠረ በስተቀር ማለት ነው።

ቤተ ክህነቱ ከመንግሥት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት የአቻ ተቋማት የእኩል ውይይት ሳይሆን፣ የሎሌና የአለቃ ፣ የታዛዥና አዛዥ ፣ የመልእክት አስፈጻሚ/ አድራሽና የመልእክት-ላኪ ዓይነት ነው። መንግሥት ለማድረግ ያሰበውን ቀርቶ ገና ሊያስበው ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ተሽቀዳድሞ በማስፈጸም ላይ ያተኮረ ከመሆኑ አንጻር በዋልድባ ጉዳይ ቤተ ክህነቱ ትክክል የሆነውን፣ ታሪካዊውን ገዳም ክብሩንና ማንነቱን እንደጠበቀ የሚያቆየውን እንዲሁም ለአገሪቱ በሚጠቅም መልኩ ውጤታማ ልማት የሚያመጣውን ዓይነት እንቅስቃሴ ያካሒዳል ተብሎ አይጠበቅም።

ከዚህ አንጻር ስንመለከተው በዋልድባ ተጎራባች አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ልማት ሲካሔድ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በትክክል ማግኘት ይገባል። በሥራ አጋጣሚ መሠረታዊ የአካሔድ ስሕተቶች በሚኖሩበትም ጊዜ በስሕተት ከመግፋት ይልቅ የተጀመረውን ነገር ገትቶ ለሌላ ተግባር መነሣት አላዋቂነት አይደለም። በዋልድባ የተጀመረው ሃይማኖትን፣ ታሪክን፣ ማንነትን እና መልክዓ ምድራዊ ሀብትና ያላገናዘበ ልማት አሉታዊ ውጤቱ የከፋ ስለሚሆን መንግሥት ሊገታው ይገባል። አንድ የጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ኃላፊ መልሰዋል እንደተባለው ይህንን የገዳማውያኑን ተቃውሞ “መንግሥትን ከመናቅ” መቁጠር መንግሥትነትን፣ የመንግሥት ሥልጣን መያዝን፣ የሥልጣን ምንጭ ማን እንደሆነ፣ ሥልጣን ሁሉ የተገደበ መሆኑን አለመረዳት ካልሆነ ሌላ ትርጉም የለውም።

ምናልባት በባዶ እግራቸው፣ ባደፈ ልብሳቸው፣ በትሕትና ሰበር ባለ አንገታቸው (አትህቶ ርዕስ)፣ ዝቅ ባለ ንግግራቸው አላዋቂ እና ደንቆሮ መስለዋቸው ካልሆነ በስተቀር አገር ቆርጠው ለአቤቱታ የመጡትን ከተማ-ለምኔ ብለው በብህትውና የሚኖሩ አበው አለመቀበል ከአዋቂነት ሊያስቆጥር አይችልም።

የመንበረ ፓትርያርኩ የኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ እንዳሉት በርግጥ መንግሥት በማካሔድ ላይ ያለው እንቅስቃሴ የገዳሙን ይዞታ የማይነካ፣ ይፍረሱ የተባሉትን አብያተ ክርስቲያናት የማይነካ፣ ለብዙ ዘመናት በክብር ያረፉ የቅዱሳን አባቶችን አጽም የማያፈልስ (Desecration of cemetery; desecration of human corpse) ከሆነም በትክክለኛ መልኩ ተጠንቶ ከመግባባት ላይ መደረስ አለበት። የገዳማውያኑም ጥያቄ መመለስ አለበት። ልማቱ ይልማ፣ ማንነታችንም ይጠበቅ። አገር በስኳርና በቢራ ፋብሪካ ብቻ አገር አይሆንም፤ በባህልም፣ በቅርስም፣ በማንነትም፣ በሃይማኖትም እንጂ

 

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

 

 

 

14 comments:

Tsegaye Girma said...

Well written, Ephrem! It’s a pity that the current Ethiopian government is continually disregarding the concerns of Christians. However, the saddest fact is that the ‘betekihinet’, which is supposed to guard the interests of the church, is turning a blind eye to the problem. If things keep on going the wrong way, I think we should hold a peaceful demonstration here in Addis to demand a halt to this destructive project.

Anonymous said...

Yes, peaceful demonstration or whatever it is should be done to protect our churches and monasteries.If they want to build something by force, it is known a lot of monks will give their lives to protect the place and if still they keep going and build sugar or beer factory, I am sure our KIDUSAN ATSIM didn't sit their without reason. They will die in it. They factory will fall down on them. I promise to you GOD will show us what that place means for us and those monks. Those Betekihinet people, God forgive them, the guy seems to worry much about that they didn't get the letter first. They got the copy after it is sent to the prime minister. How could anyone can think when his church is torn down. The guy said he didn't see the place and he still argues that it doesn't touch the monastery. Now just forget these people and lets do our part. Lets have peaceful demonstration in Ethiopia.

Anonymous said...

It is very nice observations and analysis, we have to keep our cultural, traditional and religious heritage’s to make our development and economical progress meaningful, it is not the matter of orthodox, Muslims or others religion it is the matter of moral value. I’m eager to see the development of my country in all aspects but sugar or brewery factory never bring any moral assets to the society. "የስኳር ፋብሪካም ሆነ የቢራ ፋብሪካ ቢስፋፋ ተቃውሞ የለኝም።"በምሳሌው ግን አልስማማም

Anonymous said...

Even though the development of the country is our wish it should not be by destructing religious and traditional values which reflect the society as well as the country.So the government must think wisely regardless of the higher betkihnet leaders who act as puppet leader.

Anonymous said...

የመንበረ ፓትርያርኩ የኮሙኒኬሽን ክፍል: is there no term for communication in our language amharic/geez. why our church use the word communication as it is? it seems direct copy form government structure. but our church has its own structure before the government. i think it is not good for us to have a name የመንበረ ፓትርያርኩ የኮሙኒኬሽን

Anonymous said...

አገር በስኳርና በቢራ ፋብሪካ ብቻ አገር አይሆንም፤ በባህልም፣ በቅርስም፣ በማንነትም፣ በሃይማኖትም እንጂ።

ena betekirstiyan eyeferese birrana sikuar fabrika mekefete alebete???

Anonymous said...

ካለመደረጉም በላይ “ያገባናል” ብለው “አቤት” ለማለት ወደ መንግሥት አካላት የመጡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው “አደራ ጠባቂዎቹ” ገዳማውያን “መንግሥትን እንደደፈሩ” በኃይለ ቃል እንደተመለሰላቸው ተናግረዋል። tarikna hagerin lematifat kekorete mengist kezih lela min yitebekal.Amilak yesiltan edmewun yasatirilin enji gena.....

Anonymous said...

ካለመደረጉም በላይ “ያገባናል” ብለው “አቤት” ለማለት ወደ መንግሥት አካላት የመጡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው “አደራ ጠባቂዎቹ” ገዳማውያን “መንግሥትን እንደደፈሩ” በኃይለ ቃል እንደተመለሰላቸው ተናግረዋል። Hagerinina Tarikin lematifat kekorete mengist kezih lela min yitebekal.Amilak yesiltan edmewun yasatirilin enji gena.....

ኤፍሬም እሸቴ said...

ከምን ይሆን የዘገየኹት? መች ነበር ይሆን ቀጠሮው?

awliniya said...

ባያውቁት እንጂ ባይገባቸው አገርን እንደ አገርቷ ለመጠበቅ መንፈሱ የተነሳው ከእነዚሁ ገዳማት ነው፡፡ በተጫማሪም አገርን በልማት የማሳደግን እውነታ ከሚታይ ነገር ጋር ብቻ ማያያዛቸው በራሱ የግንዛቤ ማጣት ሳይሆን የማጥፋት አላማ ነው፡፡ …..እንዲያው ለነገሩ አገርን የሚያሳድገውና የሚያለመው የፋብሪካ ጋጋታ ነው እንዴ…... እውነት እንነጋገር ከተባለ የተዘራው እንዲበቅል የበቀለው እንዲባረክ የበቀለውም ለሰው ልጅ ጥቅም እንዲውልና ገንቢ እንዲሆን የሚያደርገው እኮ የእነዚህ ገዳማውያን አባቶች ባርኮትና ልመናም ጭምር ነው፡፡ እባካችሁ መንገዳችሁና አሳባችሁ ቀና ይሆን ዘንድ ከፊት ያለውን መላክ አታስቆጡት አታስመረርሩት ትህግስቱ የተሟጠጠ ጊዜ ያ የእናንተ መጨረሻ ይሆናል… ዋልድባ ለኢትዮጵያ እኮ ከሚሰራው ስኳር ፋብሪካ በላይ ብዙ ነገር ያመርታል…..


እዚያ ማዶ ሰፈር ልብ እየጠበሱ
ያንንም ይህንንም ማጣፈጫ ብለው እያግበሰበሱ
ላይበሉት ላያስበሉት እንዳይሆን አድርገው
ይህው ጥለውታል በደንብ አሳርረው

Anonymous said...

የምሰማው ነገር በሚሊዪኖች ከሚቀጠሩ መንግስት እየሰራቸው ካላቸው ስህህተቶች አንዱ ነው ይህ ነገር መንግስትን እንደፈለጉ እየጠመዘዙ ካሉ የጊዜው ግራኝ መሀመዶች የመጣ ነው በየቦታው ያለን ክርስቲያኖች ይህን የግራኝ እንቅስቃሴ በችልታ ማለፍ የሚገባን አይመስለኝም ለማንኛውም በማንኛውም የመንግስት መስሪያቤቶች የሚገኝ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሰራተኛ ሁሉ እንቅስቃሴያቸውን በንቃት መከታተል ይጠበቅበታል

Anonymous said...

Ande kamet eske amet ye Eme Birhan kdassie yemaykwaretbet mdrawi mengste semay letewahoddo emenet memekiyachin esu neber demo besum tefetenn. Ay Eme Birhan lemn lemn.....?

Anonymous said...

ene yemilew wondimoche ena ehitoche lemindin new gin egna hager lay yemaninet tiyake sinesa tolo tebilo wode politicaw yemiwosedew? lenegeru siltan yalewum yelelewum HOD AMILAKU hono new enji zare endih biye binager nege yehone bota lay eshomalehu bilo silemiasib enji siltanu ke eminetu belito endalihone asamiro yakewal. sile MEDHANEALEM bilachihu tinshm bithon siltan alen yemitlu sewoch sile ewunet nuru sile ewunet siru.

Anonymous said...

Kidassiew newe sehetetu.............Mamo lela metawekiaw lela............moto afer wede hone ayetseleyem!!! Dile wede nesaw wede Eyesus Kiristos tseley............lenegeru tselotachinen yemetasizu denkarawoch aydelachehu?? meche yegebachehual?? Wede Berehan enat sayhon wede Berhanu Eyesus tseley........woie afehen zega ena yegna tselot yesema!!!! yehem sele ande tsadik eskemimeta malet newe!!!!!!!!!!!

Blog Archive