Friday, March 16, 2012

ዉኃም አነቀ፤ ምላጭም አበጠ


 (ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፤ ፌስቡክ ላይ ካስቀመጠው። በፀሐፊው ፈቃድ የተወሰደ። Birhanu Admass Anleye on Monday, March 12, 2012 at 4:51am/ READ THIS IN PDF)
 ብዙ ዓይነት ችግሮች እንደሚኖሩ ሁሉ እንዲሁ ብዙ ዓይነት መፍትሔዎችም አሉ፡፡  ችግሩን አስወግደዉ ነገር ግን መጠነኛ ሌላ ችግር ትተዉ የሚሄዱት መፍትሔዎች በእኔ ግምት ሰፊዉን ቦታ የሚይዙ ይመስለኛል፡፡ እንደ መድኃኒት ማለት ነዉ፡፡ ዋናዉን በሽታ ያስወግዳሉ፤ ነገር ግን የራሳቸዉን ተጓዳኝ ተጽእኖም(side effect) ፈጥረዉ ያልፋሉ፡፡ ሆኖም  ዋናዉንና ቢቆይ ሊገድል የሚችለዉን ችግር (በሽታ) ስለሚያስወግዱ ተጓዳኝ ተጽእኗቸዉን እንታገሰዋለን፡፡ ከችግርነታቸዉ ይልቅ ችግር አስወጋጂነታቸዉ በእጂጉ ይበልጣልና፡፡ ዐለማችንና የዐለማችን ሰዎች የኑሮ ሁኔታ በአብዛኛዉ በዚህ ዓይነት የችግር ማስወገጃ ዘዴዎች ይጠቀማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ጠባያት ያሏቸዉ የመፍትሔ መንገዶች መኖራቸዉም  የሚረሳ አይመስለኝም፡፡
ከሌሎቹ የመፍትሔ ዓይነቶች ዉስጥ አንዱ ከላይ ከጠቀስኩት ተጓዳኝ ተጽእኖ ወይም መጠነኛ ችግር ፈጣሪነት አልፎ መፍትሔዉ ራሱ የተፈጠረበትን የመፍትሔነት ባሕርይ መልሶ ለራሱ እንዲሻ ወደሚያደርግ ችግርነት ሊለወጥ የመቻል ሁኔታ መኖሩ ነዉ፡፡ በርግጥ ይህ ሁኔታ የሚከሰተዉ  አንዳንድ ጊዜ፤ ኧረ እንዲያዉም እንደ ተአምር በሚቆጠሩ በጣም ጥቂት ሁኔታዎች ዉስጥ  ነበር፤ አዎን ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን በዚህ ዐይነት የታወቁና የተለመዱ መፍትሔዎች  እንዲህ ዓይነት ችግር ሆነዉ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ስለመሰለኝ ነዉነበር የደጋገምኳት፡፡ ቀደም ብየ እንደጠቆምኩት መፍትሔዎች ችግር የሚሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ሊሆን ቢችልም የራሳቸዉን ተፈጥሮአዊ መፍትሔነት መልሰዉ ለራሳቸዉ የሚሹ ችግሮች ወደ መሆን የሚለወጡት መፍተሔዎች ግን የመከሰት እድላቸዉ እጂግ በጣም ዝቅተኛ (unlikely) መሆኑ እሙን ነዉ፡፡ ሆኖም ግን ፈጽመዉ አይከሰቱም አይባልም፡፡ መፍትሔ ችግር የመሆን ዕድል ፈጽሞ ሊኖረዉ የማይችለዉ  ወይም ፍጹም መፍትሔ ሊሆን የሚችለዉ መፍትሔዉ ራሱ ፈጣሪ ሲሆን ብቻ ነዉና፡፡”  ለምትሉኝ ሊከሰቱ የማይችሉት ብየ ከማስባቸዉ ምሳሌዎች አንድ ብቻ ልጥቀስላችሁ፡፡ አያድርግባትና ፀሐይ ለራሷ ጨልማ ለራሷ የሚሆን ሌላ ፀሐይ ብትሻ ብላችሁ አስቡ፡፡ የማይሆን ነገር ለምን እናስባለን አትበሉ፡፡ እንደኛ ግዕዛን (ነፍስ፣ አእምሮ፣ እዉቀት፣… ) ስለሌላት ይህ በራሷ ላይ እስኪከሰትባት ድረስ በራሷ የምትወስነዉ ስለሌለ እኛዉ አይሆንም አይከሰትም እንልላታለን እንጂ ላለመከሰቱ አሁንም ዋስትና መስጠት አንችልም፡፡ ሆኖም የመከሰት ዕድሉ እጂግ በጣም ትንሽ መሆኑን ያለ ክርክር የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ ሰዉ ግን በራሱ የመወሰን መብት ስለተሰጠዉ የፀሐይን የመሰለ ብርሃንነት፣ ሙቀትነት፣ መድኃቲነት፣ቢሰጠዉም ሌላ ፀሐይ እስኪያሻዉ ድረስ ለራሱ የሚጨልምበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ፡፡ የሀገራችን ሰዉም:
ውኃ ቢያንቅ በምን ይዉጡ፤
ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ፡፡
ሲል  በአባባሉ የሚጠይቀዉም እንዲህ ያለ ችግር ሲያጋጥመዉ ነዉ፡፡ እዉነቱን ለመናገር ምግብ ያነቀዉ ሰዉ ሁሉ ዉኃ በመጎንጨት ያወርደዋል፤ በበሽታ ያበጠ አካልንም በምላጭ በጥተዉ መግሉን እዡን አስወግደዉ ጥዝጣዜዉንና ሕማሙን ያስታግሱለታል፡፡ ስለዚህ  በምግብ ጉሮሯቸዉ ለታነቀ ዉኃ፤ የአካል እብጠት ለገጠማቸዉም (ምንም ዓይነቱ ቢለያይና ቢበዛ)  ምላጭ ተፈጥሮአዊ መፍትሔዎች ሆነዉ ሳለ ራሱ ዉኃ ካነቀ (ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም ነገር ግን የሚያጋጥም ነዉ) ምላጭም ካበጠ (ይህ ደግሞ በተአምር ካልሆነ በቀር ሊሆን የማይችል ነዉ) ግን መፍትሔዉ ችግር መሆኑ ሳያንስ ሌላ የታወቀ መፍትሔም ስለሌለዉ አስጨናቂና አሳዛኝም ይሆናል፡፡ በርግጥም የዉኃን እንቅታ በምን ያወርዱታል ምላጭስ ቢያብጥ በምን ይበጡታል?
ሃይማኖትና የሃይማኖት መሪዎችም ለአማኞቻቸዉ ብቻ ሳይሆን በእነርሱ ሃይማኖት ለማይኖረዉ ሕዝብና የሰዉ ዘር በጠቅላላዉ እንዲሁም ለሀገራቸዉና ለመላዉ ዐለምም ጠቀሜታቸዉ እንደ ዉኃና ምላጭ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከላይ በሰፊዉ ባተትነዉ መሠረት ራሳቸዉ እንደ ምላጭ አብጠዉ ያስገረሙበት፣ እንደ ዉኃም አንቀዉ ያስጨነቁበት ጊዜ ደግሞ አልጠፋም፤ ኧረ እንዲያዉም በተደጋጋሚ መከሰቱም የታወቀ ነዉ፡፡ በአሁኑ ጊዜማ እማኝ የማይፈለግለት እዉነት ወደ መሆንም የደረሰ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለዉ ችግር በእዉነቱ እህህ፣ እህህ፣ እህህ፣የሚያሰኝ ሆድ የሚያስብስና የሚያብከነክን፣ ለሀገርና ለሕዝብም ታላቅ ዉደቀት ዉስጥ እየገቡ መሆኑን የሚጠቁም፣ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን በእጂጉ የሚያስጨንቅና ተስፋ እስከማስቆረጥ የሚያደርስም ታላቅ ችግር ነዉ፡፡ ወደ ዚህ ሀተታ የገባሁትም ይሔዉ ክስተት በአሁኑ ጊዜ በእኛ ሀገር እየተከሰተ ስለመሰለኝ ነዉ፡፡ ባይሆን እንኳ (ወየዉ ባልሆነና) ለእኔ ግን ስለ መሰለኝ ከላይ በጠቀስኩት መንገድ ስለሚያሳስበኝ ብቻ ሳይሆን ስለሚያስጨንቀኝም ትንሽ መነጋገሩ የሚያስከፋ አይመስለኝም፡፡
 እዉነት ለመናገር መጨረሻዉ የማይታወቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እንዲሁ መጀመሪያዉም ያስጨንቃል፡፡ ምክንያቱም የምንሳለቅበትና የምንንቀዉ፣ አርቀን የምንተቸዉና አሳልፈን የምንሰጠዉ ጉዳይ አይደለምና፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከጥፋቱና ከጉዳቱ ብቻ ሳይሆን ከተጠያቂነቱ፣ ከበረከቱ ብቻ ሳይሆን ከመቅሰፍቱ፣ ከሕይወቱ ብቻ ሳይሆን ከሞቱም ስለማናመልጥ የእኛዉ በእኛዉ ስለእኛዉ ነዉና ያሳስበናል፤ ያገባናል፤ ይመለከተናልምና ተጠንቅቀንና ተጠብቀንም ቢሆን እንናገርለታለን፡፡ ተፈጥሮዉ  ባንፈራዉም እንዳንደፍረዉ፣ ባንርቀዉና ብንቀርበዉም እንድንጠነቀቅለት ያስገድደናልና፡፡ስለዚህ  መጻፉና መናገሩ ብቻ ሳይሆን ማንበቡና ማድመጡም ተመሳሳይ የሚሆንብን ይመስለኛል፡፡ቢሆንም አብዮታዊነት ሳይሆን መንፈሳዊነት ያልተለየዉ ጥብዓት መፍተሄ ለሚሆናት መንፈሳዊት ተቋም የሚጠበቅብንን ያህል እንኳ ባይሆን የመሰለንን ያህል ለመታዘዝ ያመቸን ዘንድ የማታዉቁትን ባይሆንም እኔ ለመጻፍ እናንተም ለማንበብ ስሜት ሳይኖረን አልቀረም፡፡

የሃይማኖት መሪዎች ለእምነታቸዉ ወይስ ለታይታ
በዉስጤ ጥያቄም፣ ጭንቀትም፣ መብሰልሰልም እየፈጠሩና እያሳሰቡኝ ከኖሩትና አሁንም  ባሉት ጉዳዮች ላይ እንድጽፍና እንዳካፍል እድሉኝ የፈጠረልኝን የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዝግጂት ክፍልን እያመሰገንኩኝ  ለእኔ መጻፍ ግፊት ከፈጠሩብኝ ክስተቶች ልነሳ፡፡ ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ከዚህ ዐለም ተለይቶ ቀብር ሲፈጸምለት በሀገር አልነበርኩም፡፡ የተመለስኩት እርሱ ሰኞ ተቀብሮ ማክሰኞ ማታ ነበር፡፡ በነጋዉ በታክሲ ስሔድ በከተማችን ካሉት የኤፍ ኤም ሬዲዮኖች ባንዱ ስለ እርሱ በቀረበ ዝግጂት ላይ መሞቱን ስለተረዳሁ ስለ ሁኔታዉ ጓደኞቼን በመጠየቅና ከሸገር ሬዲዮም ስለ እርሱ ቀርበዉ ካመለጡኝ ዝግጂቶች ኢንተርኔት ላይ ገብቼ አዳመጥኩኝ፡፡ ከሁለቱም የተረዳሁት አንዱ አሳዛኝ ነገር ራሱ ቢጠየቅ እንኳ አይሁንብኝ የሚለዉ ዐይነት የጸሎትና የቀብር ሥነ ሥርዓትና አሁንም ራሱ መልስ ቢሰጥሐሰትሊለዉ የሚችል ምስክርነት እንደተሰጠለትና በነገሩኝ ሰዎችም ግምት ቤተሰቦቹ እንኳ ሳይቀሩ ሳይታዘቡ እንዳልቀሩ በሚያሳይ ሁኔታ በእኛዉ ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን ተረዳሁ፡፡ ከምናያቸዉና ከምንሰማቸዉ ችግሮች ይሄ በጣም ቀላሉ ቢሆንም መልእክቱ ግን አሁንም ቀላል እንዳልሆነ ገምቼ ዝም አልኩ፡፡ ነገር ግን በጥቂት ቀናት ልዩነት አርብ መጋቢት 23 ቀን ከምድረ አሜሪካ በሚተላለፈዉ የቪኦኤ የአማርኛ ዜና አገልግሎት የቀረበዉ የዋልድባ ገዳምን የተመለከተዉ ዝግጂት በእጂጉ አስደነገጠኝ፡፡   ምንም እንኳ ባልተፈጠረዉና ሁሉን ቻይ በሆነዉ አምላክ ስላለማመኑ ማስረጃ ማግኘት ባልችልም ለእኔ በሚመስለኝ  ራሱ ጋሽ ስብሐትሼሪኬእያለ በሚጠራዉ፣ ራሱ በፈጠረዉና ለራሱ ብቻ በሆነዉ አምላክ አምኖ፣ ኃጢአትን ሰብኳት፣ በሕይዎት እንደ ኖረአትም በልቦለዶቹ መስክሮላትና አድንቋት ለሞተዉ ለጋሽ ስብሐት እንደሰማሁት እንኳ ቀኖናዉ ሊፈቅደዉ ይቅርና ያን ያክል ራሱም ቢጠየቅ ሊቀበለዉ የማይችል ተብሎ የተነገረለትን ምስክርነት መሰጠቱን ከሰዎችም ከሚዲያም በሰማሁበት ጆሮየ ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ ዐመታት በላይ እልፍ አእላፍ ቅዱሳን ለተጋደሉበት፣ ዐጽማቸዉ ላረፈበትና አሁንም ብዙ ስዉራን ሳይቀር ላሉበት የዋልድባ ገዳም ጉዳይ ለመነኮሳቱ የተሰጠዉን መልስ ከሬዲዮኑ ሳደምጥ በእዉነት በእጂጉ አዘንኩ፡፡

መንግሥት ምን እየሠራ ነዉ?
መንግሥታት የሕዝባችንን ኑሮ ይለዉጣል ብለዉ ካመኑ መሰናክል የሚመስላቸዉን ሁሉ በተማቻቸዉ መንገድ እያስወገዱ የፈቀዱትን ማድረጋቸዉ የተለመደ ነገር ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ከዘመነ ሰማዕታት በኋላ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለሰባ ዐመታት ያህል በኮሚኒስቶች እንደ ተፈጸመዉ ያለ ግፍና በደል በሌሎች ላይ መፈጸሙን የሚያሳይ ታሪክ ባላነብብም ብዙዎች ከዚህ ዐይነት ችግር ተላቀዉ እንደማያዉቁ ግን ብዙ ምስክሮች ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የየእምነቶቹ መሪዎች የሚጠበቅባቸዉን ማንኛዉም መሥዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ በመታመን ችግሩን ለፈጠሩባቸዉ ሳይቀር ሁነኛ መፍትሔና ጠቃሚ መድኃኒት በመሆን ግዴታቸዉን ሲወጡ ኖረዋል፡፡ ሩሲያንም ለሩሲያነትና አሁን ላለችበት ማንነትም አስተዋጽኦ ያደረገችዉና የአወንታዊ ለዉጡ አንዷ ማዕዝን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን በጉዳዩ ላይ ጥናት ሄዱ ሰዎች መጻሕፍት መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ያች በራሷ መቅደስ ዉስጥ ቅዳሴ ተከልክላና ለልማትና ለእድገት ማነቆ ተደርጋ ስትቆጠር የነበረች ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ኮሚኒዝም ከወለደዉ ሙሰኝነትና ምግባረ ብልሹነት ሀገሪቱን ለማላቀቅ  የሞራልና የበጎ ምግባር ትንሣኤ ለማምጣት ለሚደረገዉ ትግል ግንባር ቀደም ሓላፊነት ከመንግሥት ተቀብላ ሥርዐተ ትምሕረት ቀርጻ በዐለማዊ ትምህርት ቤቶች ሁሉ የሚሰጥ የሥነምግባር ትምህርት እስከ መስጠት የደረስ ልዕልና ላይ ለመገኘት የበቃችዉ የምላጭነትና የዉኃነት ተግባሯን ባለመዘንጋቷ፣ በመከራዉ ዘመን ሰማዕትነት በመክፈሏና ለዉጡም ሲመጣ ደም በበቀል እንዳይፈስ በመንፈሳዊ ልዕልናዋ ተከላክላ አስቁማ ሀገርና ሕዝብን ከሌላ ጥፋት በመታደጓ ነበር፡፡ በዚህም ኮሚኒዝምን አስወግዳ ለራሳቸዉ ሊያጠፏት ብዙ ዐመታት ለታገሉት ኮሚኒስቶች ሳይቀር በይቅርታና በምሕረት አምባ መጠጊያ በመሆን በምድራችን ያለች ከርቀት የምትሸት ብርቱ መድኃኒት መሆኗን አስመስክራለች፡፡ ገዳሞቿን በመጠበቅና በማስመለስ ልትታማ ቀርቶ ከልዕልናዋ የተነሣ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ለዮኒበርስቲዎች ብቻ ሳይሆን ለገዳሞቿም የመሰናዶ ቦታዎች ለማድረግ በቅታለች፡፡
በእኛ ግን ተገላበጠ፡፡ እኔ በግሌ መንግሥት ይህን ቦታ በተጠቀሰዉ መንገድ ለልማት ማሰቡ አያስከፋኝም፡፡ ምን እንዳደረገ ባላዉቅም (ምንም አታመጣም ብሎ ንቆ የሚወዉ ስለማይመስለኝ) ትክክለኛዉንና እዉነተኛዉን የገዳሙን መሠረት የሆኑትን መነኮሳት (ወደ መሰወርና ወደ በረሃ ያልገቡትንና ቢያንስ ሊወያዩ የሚችሉትን) ሳያማክር፣ የእምነቱ ባለቤቶች የሆነዉን ድምጽ ሳያዳምጥ፤ ቢቻል ከገዳሙ ከራሱ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ሊገኝ የሚችለዉን ጠቀሜታ በአግባቡ ሳያጠና፣ ከዚህም ካለፈ በሌላ አቅጣጫ ማልማት የሚቻል አለመሆኑን ሳይምረምር እንዲሁ በወታደር አጥሮ ሥራ መጀመሩ ፍላጎቱን በግልጽ የሚያስረዳ ነዉ፡፡ ይህ ያሳዝነኛል፡፡ ምክንያቱም ለሕዝብ ጥቅም እሠራለሁ የሚል መንግሥት የባለቤትነት መብት ያለዉን ብዙዉን ሕዝብ ፍላጎት ግምት ዉስጥ ሳያስገባ ምን ዓይነት ልማት ሊያመጣ ይችላል? ምክንያቱም የዋልድባ ገዳም ከዚያ ቦታ መጥተዉ የሚጮሁት መነኮሳት ንብረት ብቻ አይደለም፡፡ ንብረትነቱ መልክአ ምድራዊ አቀማመጡና ተፈጥሮአዊ ይዞታዉ ብቻ ሳይሆን በብዙ መቶ ዐመታት ዉስጥ የተገነባዉ መንፈሳዊ ሁናቴና ታላቅ ሃይማኖታዊ ዋጋ ሁሉ ነዉና የሁላችንም የምእመናኑ ነዉ፡፡ በተለይ እንደዚህ ያለ ታሪካዊና ዘርፈ ብዙ (የሚታወቅም የማይታወቅም) ጠቀሜታን የሚሠጥ ገዳም እንደተነገረዉ ከሆነ የቅዱሳኑ ዐጽም ሳይቀር በግሬደር እየተቆፈረ በመኪና እየተጋዘ ሲወሰድ፣ ልማቱ ሌላ አማራጭ በማይገኝለት ሁኔታ አስፈላጊ ከሆነም ያሉትን መንፈሳዊ ዕሴቶች ሳይጥስ ሊከናወን የሚቻልበት ሁኔታ ስላለመኖሩ ጥናት ሳይደረግ እንዲህ ያለ ድርጊት ሲፈጸም ከማየት በላይ አስደንጋጭ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱም ዎች ሌላዉ ቢቀር አምላከ ቅዱሳን ሃይልና ተአምራት በቤተ ክርስቲያን እንዲያደርግ እንደ ዐጽመ ኤልሣዕ ምክንያት የሚሆኑትን በትዉፊታችንም (ለሌሎች እንኳ ቀኖናዊ ግዴታም ስለሆነ እንደ ግብጽ፣ ሶርያና ሩስያ ግሪክ ያሉት ከዐጽመ ቅዱሳን አፈር በብልቃጥም ቢሆን መንበራቸዉ ላይ ሳያደርጉ እንደ ቤተ ክርስቲያን አይጠቀሙበትም) መሠርትም በአዲስ ቤተ ክርስቲያን እንኳ እንዲገኝ የሚደረገዉን ዐጽመ ቅዱሳንን እንኳ በአግባቡ ለማንሣት አለመጠየቅና በሥዓትም አለማስቀመጥ ለምን ይሆን? ሌላዉ ቀርቶ በየዕለቱ ለተዘክሮተ ቅዱሳን የምናነበዉ ስንክሳር በብዛት የሚተርክልን ፍልሰተ ዐጽምን መነሻ አድርጎ ነዉ፡፡ ስለዚህም ገዳማት ምድራቸዉ ሁሉ የሚከበረዉና ጥበቃ የሚደረግለት ስለ ዐጽመ ቅዱሳንም ጭምር ነበር፡፡
የግብጽ እስላማዊ መንግሥት  ቅርብ ጊዜ ከሥልጣናቸዉ በወረዱት በሆስኒ ሙባረክና በመንግሥታቸዉ  ጠንካራ ዉትወታ ከዩኔስኮ በተገኘ እርዳታ በሀገሩ የሚገኘዉን ታሪካዊዉን ገዳመ አስቄጥስን 14 ሚሊዮን ዶላር ማሳደሱን ከቢቢሲ ቴሌብዥን ጣቢያ ዘገባ የሰማነዉ በቅርቡ ነበር፡፡ ከሦስተኛዉ እስከ አምስተኛዉ ክፍለ ዘመን የነበሩ የምዕራቡና የምሥራቁ ዓለም ታላላቅ ታሪክ ጸሐፊዎች በአካል ወርደዉ ያዩትና የአሁኑ ዐለም ሰዉ የሚደነቅባቸዉና የዚያን ዘመን የምናኔና የምንኩስና ሕይዎትን የሚመሰክሩልንን መጻሕፍት ለመጻፋቸዉ መነሻ የሆነዉ ይህ ታሪካዊ ገዳም ይህ ቢደረግለት የሚደንቅ ሆኖ ሳይሆን እስላማዊ መሪዎችና ባለሞያዎች ያደረጉት ተጋድሎ ግን ከሃይማኖታዊ ፍላጎታቸዉ ባሻገር ለሀገራዊ ሀብትና ቅርስ ያላቸዉን ተቆርቋሪነትና የሓላፊነት ስሜት ሕያዉ አድርጎ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ገዳመ አስቄጥስ የጥንቱን የምናኔ ሕይዎት እንደ ማሳያ (model) እንኳ ሊያሳይ የሚችል ሕይዎት በአሁኑ ጊዜ አይገኝበትም፡፡ ራሳቸዉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እንደመሰከሩት በግብጽ የነበረዉ ከሰዉና ከተለምዷዊ  ሕይዎት ርቆ በበረሃ በአራዊት መኖሪያ ተሰዉሮ ከኣጋንንትና ከዚህ ዐለም ፍላጎት ጋር በመጋደል የሚኖሩ መናኞችና ስዉራን በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት እንደ ዋልድባ ባሉ ጥቂት የኢትዮጵያ ገዳማት ነዉ፡፡ ይህን ብቻ በማስተዋወቅና ይህ ሕይዎት እስካሁን በምድር ላይ የሚፈጸም መሆኑን በማሳየት ከገዳማዊ መንፈሳዊ በረከት ያለፈ ገዳማዊ ሥርዓትን በማያፋልስ መልኩ የቱሪስት መስሕብ አድርጎ ብዙ ዐይነት ጥቅሞችም ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ከዚሁም ጋር የገዳሙን መነኮሳት በማሳተፍ መንፈሳዊ ይዘቱን ሳያጣ ማልማትና ከልማቱም ከገዳሙ እስከ ሀገሪቱ ድረስ ተጠቃሚ ማድረግ እየተቻለ ወደዚህ ሁኔታ መገባቱ አልገባኝም፡፡  እዉነቱን ለመናገር የዋልድባ ጥቅም በዚህም ብቻ የሚሰላም አልነበረም፡፡ ይነሳሉ የተባሉት ዐሥራ ስድስቱ አብያተ ክርስቲያናቱ ቀርቶ በቅጡ  ያልተጠኑት እጂግ ብዙ የሕይዎት ፍልስፍናዎችና ብዙ ታሪኮቹ ራሳቸዉ ሊያስከብሩትና ወደ ዐለም ቅርስነት ሊያስመዘግበዉም ይገባ ነበረ፡፡ ስለዚህ ነዉ የዋልድባ ጉዳይ ዝም ብሎ የመሬትና የልማት ጉዳይ ብቻ ሊሆን የማይችለዉ፡፡ ይህን ሁሉ ነገር ማስረዳትና በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናት እንዲደረግበት ማሳየት የነበረባት ቤተ ክርስቲያኒቱ እና ወይም መሪዎቿ ግን እኒያ በሬዲዮን የሰማኋቸዉ አባትም እንደመሰከሩትለታዋቂሰዎች ቀብር ሥርዓት ከሚሰጡት ሰዓት ከፍለዉ እንኳ ሊያደምጧቸዉ  አልቻሉም፡፡ በእምነታችን ላይ ለመሳለቅ ፊልም ለመሥራት ለመጡ ፈረንጆች  ”የጠየቁት  ይፈቀድላቸዉደብዳቤ የሚሰጥ ቤት ከገዳማት አቤቱታ ይዘዉ ለመጡት ለራሱ ሰዎች እናደርስላችኋለን ብሎ ብቻ መመለሱ ለምን ይሆን? ዜጎች በሆኑባት ሀገር ዉስጥ ጠቅላይ ሚኒስትራቸዉን ለማናገር በመጠየቃቸዉደፋሮችተብለዉ ለመመለስ የተገደዱት ያነቀዉን እንጀራ ሊያወርዱት የሚገባቸዉ ዉኃዎች ከቦታዉ መጥፋታቸዉ ሳያንስ ወደ እነርሱም ሲኬድ ማነጋገር ካልቻሉ  “ ዉኃ ሲያንቅ… “ ማለት እንደምን ሊያንስ ይችላል?  ነገሩ ሰሚ ጠፍቶ ወይም እንደ ልማዱ የሚደረገዉ ጠፍቶ ይሆናል እንጂ የእኛ ዉኃ ማነቁስ ሰነባብቷል፡፡ በአንድ ሌላ ምሳሌ ባስረዳ የሚሻል ሳይሆን አይቀርም፡፡
የቀድሞዋ ሶቤት ኅብረት ስትፈራርስና ሀገራት ወደ ቀደመ ሉዓላዊነታቸዉ ሲመለሱ በሞስኮዉ ፓትርያርክ የሚመራዉ ኦርቶዶክሳዊ የቤተ ክህነት አስተዳደር ግን አልተለያየም አልተከፋፈልምም እስከአሁንም ድረስ፡፡ በቅርቡ (ዐራት ዐመት ገደማ ይመስለኛል) በጥምቀት በዓላችን ላይ በጃን ሜዳ የሩሲያ ኦርቶዶክስን መልእክት ይዘዉ የተገኙት ሊቀ ጳጳስ የዩክሬን ጳጳስ ለዚህ ማሳያችንም ነበሩ፡፡ የልዕልናቸዉን መጠን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ የእኛ ግን እንኳን የኢትዮጵያና የኤርትራ ቤተ ክህነት የሁለቱንም ሀገር መሪዎች ፖለቲካዊ ፍልስፍና ተሻግሮ በአንድነት ሊጣመር ቀርቶ በዚሁ በቤታችን የተፈጠረዉ ልዩነት እርቅ ሳይወርድለት ችግሩም ሳይፈታ እንዲያዉም እያገረሸና እያዋገዘ ሁለት ዐሥርት ዐመታትን ይሄዉ አስቆጠረ፡፡ አሁን የተጀመረዉ የዕርቅ ሂደት ለፍጻሜ ከበቃ እሰየዉ የሚያሰኝ ቢሆንም ተስፋዉን ጥያቄ ዉስጥ የሚከቱ ብዙ ነገሮች ግን ከየመገናኛ ብዙኃኑ  አሁንም ይደመጣሉ፡፡ ለደርግ ባለሥልጣናት መንግሥት ይቅርታ እንዲያደርግ መጠየቁ ጥሩ ሆኖ ሳለ ራስ ሳይታረቁ ለማስታረቅ መጣሩ ግን የጥያቄዉን መንሳዊነት ጥያቄ ዉስጥ ይከትተዋል፡፡ ቢሆን ቢሆን ሳይከሰት ቢቀር መልካም ነበረ፤ ከሆነስ በኋላ ይቅርታን የሚሰብኩን ይቅር ማለትን ወይም ይቅርታ መጠየቅን ለመፈጸም የሚቸግራቸዉ ከሆነ ከዚህ በላይ የምላጭ ማበጥ ወዴት ይገኛል? ሰይጣንን ለማስማር እግዚአብሔርን ሳይቀር በቅድስናቸዉ ያስገደዱ ቅዱሳንን ታሪክ የሚናገሩ ሰዎች ከራሳቸዉ ሰዎች ጋር ለመነጋገር እንኳን ያሳቀቃቸዉ ምን ይሆን? የሶቤት ኅብረት አባል ሀገራት ዉስጥ ያሉ ኦርቶዶክሳዊ መሪዎች እንዳደረጉት በተለያዩ መንግሥታት እየኖሩ አንድ እንደሆኑት ባይቻለንና ሃይማኖታዊ ጠቀሜታን ፓስፖረት ከሚያስጠይቅ ድንበር ማሻገር እንኳ ቢያቅተን በዚሁ አንድ ሀገርና ሃይማኖት ዉስጥ እንኳ አንድ ሃሳብ ለመሆነን ለምን ተሳነን?

ሃይማኖትና ፖለቲካ ምንናምን
በርግጥ  ብዙ ሰዎች ለዚህ አቅም ማነስ ምክንያት የሚያደርጉት በሁለቱም በኩል አለ የሚባለዉን የፖለቲከኞች ተጽእኖ ነዉ፡፡ ይህ ግን ባይሆን ጥሩ ነበረ ከመባል የሚያልፍ አይመስለኝም፡፡ ፖለቲከኞችን ልዩነት አታስፉብን፤ እንቅፋትም አትሁኑን ልንላቸዉ አንችልምና፡፡ ላመኑበት ፖለቲካዊ ጎዳና (ቢጠቅማቸዉም ባይጠቅማቸዉም) መንገዳቸዉንና ስልታቸዉን የመምረጥ መብት በእነርሱ እጂ ነዉና፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የእነርሱን ሀሳብ መዝኖ ለጊዜያዊ  ጥቅሙ ሳይሳሱ ሃይማኖት የሚጠይቀዉን ጥብዐት ገንዘብ አድርጎ ለመንፈሳዊ ነጻነትና ለእዉነት መቆም ይጠበቅ ነበረ፡፡  የፖለቲከኞችን ጽንፈኝነት ገርቶ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላምና በመግባባት ሀገርን ያለ ደምና ያለ በቀል እንድትራመድ ማድረግ የሚጠበቅባቸዉ መንፈሳዊ መሪዎች ይህን መፈጸም እንኳ ቢያቅታቸዉ ጭራሽ ለፖለቲከኞቹ ጠመንጃና ጥይት ሆነዋል ተብለዉ እስኪታሙ ለምን ደረሱ? ፖለቲከኞቹን ለነፍሳቸዉ እንዲያድሩ ማድረግ ቢያቅት ለእነርሱ ሀሳብ አደሩ ተብሎ እስከመታማት ምን አደረሰ? በርግጥም በምድር ላይ ሰዎች በፖለቲካዊ ሃሳብ አንድ እንዲሆኑ ማድረግ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ ነጻነት እንዲኖራቸዉ ብናደረግ ኖሮ በአንድ መቅደስ ሊያስቀድሱ፤ በአንድ ሰንበትም ሊታረቁ ይችሉና በልዩነታቸዉ ያለ ደምና በቀል ዕድገትና አወንታዊ ለዉጥ ለማምጣት ሊፎካከሩ እስኪችሉ ድረስ አእምሮአቸዉን ማበልጸግ ሲገባ በእነርሱ ልዩነት ወደ መጠመቅ ምን አደረሰ? የፖለቲካዊዉን ስግብግብነት በመንፈሳዊዉ በቃኝ ባይነት ካላስታገሱ፤ ከዐለማዊነት የሚመጣዉን የመጠፋፋት ቆሻሻ ከመንፈሳዊነት በሚመነጭ ይቅርታ አድራጊነት ዉኃ አጥበዉ ካለጸዱ፤ ግፍና በደል ባለማስተዋል እንዳይፈጸም በእነርሱ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት ካልተከላከሉ ምድሪቱን ለሰላምና ለልማት ነፍሳትንም ለገነትና ለመንግሥተ ሰማያት ካላዘጋጁ መንፈሳዊ ሃይማኖታዊ መሪዎች ለምን ሊጠቅሙ ይችላሉ? ጭራሹን ሊያስገኟቸዉ የሚገቧቸዉን አጥተዉ ራሳቸዉ በዚሁ ድርቅ ተመትተዉ ለራሳቸዉ ባዕድ መድኃኒት ፍለጋ  የሚቃትቱ ከሆነማ በርግጥም ምላጩ አብጧል፤ ሀገራችንም ዉኃዉ አንቋታል ያሰኛል፡፡
 በጣም አስገራሚዉ ነገር ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ ዉስጥ ሰርገዉ በመግባት ከመሠረተ እምነቷና ከነባር ሥርዐቷ ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱትን ተሐድሶዎችም እንኳ የሉም መባሉ ነዉ፡፡በእዉነት ይህን እንደማድመጥ ያለ ጥልቅ የጥፋት ዋዜማ ወዴት አለ፡፡ ተሐደሶዎቹ መጽሐፍ ጽፈዉ፣ ጋዜጣና መጽሔት እያሳተሙ፣ እንዲሁም በብሎጎቻቸዉእኛ አለን፣ ዓላማችን ኦርቶዶክስን መቀየር ነዉ እያሉ፤ ስልታቸዉን በይፋ በመጽሔት አሳትመዉ በዚህ መንገድ ሠርተን ይሳካልናል ሲሉ፣ በመድረኮቿም የስህተት ትምህርታቸዉን በድፍረት አሰምተዉ በምእምናን ተከሰዉ ሲቀርቡ ሌላ አጥቢያ የሚዛወሩ ከሆነ፣ የተሐድሶዎቹን እንቅስቃሴ አንድም ጊዜ ሳይነቅፉ የእነርሱን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚካሔደዉን ራስን የማዳን ተልእኮ ለመግታት ደብዳቤ ከተጻፈ ከዚህ በላይ የምላጭ ማበጥ ወዴት አለ?ለነገሩ የግብረ ሰዶማዉያንን በሀገራችን ወንጀልነት ባይቻል ኃጢአትነት አስመልክቶ  መግለጫ ማዉጣትና መቃዎም እንኳ ካቃተ ሌላዉንማ እንዴትስ መጠበቅ ይቻላል? በነገር ሁሉ በገዛ ዳቦየ ልብ ልቡን አጣሁት የሆነባቸዉስ  ምእመናኑስ ለምን አይከፉ? ለምንስ አይዘኑ? እንዲያዉ ለቢዮንሴ ወረብ ያቀረበ ቤት  እንዴት ተሳስተዉና ነገሩን አጋንነዉ እንኳ ቢመጡ የዋልድባን አቤቱታ ማዳመጥና ችግሩን ተረድቶና ሁኔታዉን አስረድቶ መፍታት  እንዴት ሊከብድ ይችላል?

የምእመኑ ሮሮ በዛቷል
  ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት ከሰሞናዊዉ ጉዳት በመነሳት ለማሳያ ያህል ጥቂቶቹን ብቻ አቀረብኩ እንጂ ችግሮቻችን እነዚህ ብቻ ሆነዉ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት ፍርድ ተጓደለብን ብለዉአቤትለማለት ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ብዙ መኪናዎችን አሰልፈዉ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ ከተሞች የሚመጣዉ ምእምን ከመቼዉም ጊዜ በላይ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የፊርማ ማሰባሰብ፣ የገዳማት መነኮሳት አቤቱታ፣ የምእመናን እሮሮና የመሳሰሉት የተለመደ ክስተተት ሆኖአል፡፡ ቤተ ክህነቱ በደል ደረሰብን በሚሉ አገልጋዮች በየጊዜዉ ይከሰሳል፤ ደግሞም ይረታል፡፡ አንዳንድ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና የመምሪያ ሓላፊዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ አድባራት አለቆች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣…. ወዘተርፈ በየጊዜዉ ምክንያቱ በዉል በማይታወቅ ምክንያት በዘወሮ እንደ ካርታ ይበወዛሉ፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን የምእምናን ሐዘኔታ እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ሀገሪቱን ከሙስና ለመታደግ ንጹሕ ዜጋ ማፍራት የሚጠበቅባት ትልቋ ተቋም ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ ቤተ ክህነቷ በየጋዜጣዉና በየግለሰቡ በዚሁ ግብር ስሙ የሚነሣ፣ በሲሞናዊነት የሚታማ፣ …. ከሆነ  ምኑን መፍትሄ ሆነዉ?ለሌሎች ያበራል ሲባል ራሱ ሌላ ፀሐይ እስከሚያስፈገዉ ድረስ በፈቃዱ የጨለመ ፀሐይ ከዚህ በቀር ወዴት ይገኛልም ያሰኛል፡፡ ሌሎቹን ይፈዉሳል ተብሎ የሚጠበቅ መድኃኒት አለማዳኑ አንሶ በደረሰበት ብክለት ከበሽታዉ ቀድሞ የሚገድል መድኃኒት ከሆነ ለራሱ ፈዉስ የሚሻ የተበከለ መድኃኒት ሆነ ተብሎ ሊጠቀስበት ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ይህንና ሌሎቹንም ችግሮቻችን ሳስባቸዉ አሁን በሀገራችን ምላጭም ያበጠ ዉኃም ያነቀ መሰለኝ፡፡ በርግጥ የምላጭ ማበጥ ተፈጥሮዉ አይፈቅደለትምና ያለመሆኑ ስሜት ይሰማናል፤ ልክ ነዉ ምላጭ የተባለ ሃይማኖት ተፈጥሮዉ አይፈቅድለትምና አይበላሽም፡፡ ነገር ግን ምላጭን አበጠ የሚያሰኘዉ (ወይም የሚያስመስለዉ) ባለቤቱ ነዉ፡፡ እርሱ ግን መቼም መች አያብጥም፤ ሃይማኖታችን ወይም ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲሁ ናት፡፡ ነገር ግን ቤተ ክህነቱ ሲያብጥ (ሲበድልና ሲያጠፋ ወይም የሚጠበቅበትንም ሳይሰራ ሲቀር) ቤተ ክርስቲኒቱ( ቤተ ክርስቲያን የሚለዉ ቃል ትርጉሙ ሰፊና በሃይማኖታዊ ትርጓሜ እዉነተኞችንና ትክክለኞቹን  የሚመለከት ቅዱሳንን በሙሉና ጌታን የሚጨምር በመሆኑ በቤተ ክህነቱ አስተዳደር ብቻ አይወከልም)ያበጠች ያስመስላል፡፡ የዉኃ ማነቅ ግን ሊከሰት የሚችለዉ በሰዎች የመጠጣት ሒደት ዉስጥ ስለሆነ በርግጥም ከአስተዳደራችን ፍትህን እንጠጣለን ብለዉ የተጎነጩ ሁሉ አነቀን ማለት ጀምረዋል፡፡ በርግጥም ዉኃዉም አንቋል፤ ምላጩም አብጧልና እንግዲህ ለዉኃም ፈጣሪዉን ለምላጩም ሰሪዉን እናስቸግረዉ ካልሆነ ወደ ማን አቤት ይባላል?

9 comments:

ሳሚ ወ/ሚካኤል said...

ኡሁሁሁሁሁሁ…ምን ልሁነው ኢትዮጵያየ አልቅሸ እንዳልቀብርሽ የናት ሞት ህመሙን አውቀዋለሁ! ! ቆይ ግን እማማየ የሲኦል ደጆች ላይችሉሽ በቤተክርስቲያንሽ በኩል የተገባልሽ ቃል ኪዳንሽ የት ደረሰ? አስራት ተደርገሽ የተሰጠሻት ንግስትስ ወዴት አለች?? በመቅደስሽና በመጻኅፍቶችሽ ላይ ያለው የአምላክሽ ቃል ሲደፈር የለለ እስኪሆን ድረስ ባለቤቱ እንዴት ረሳሽ??! በወንጌል ምሳሌ የምናውቀው ስንዴ በተዘራበት እርሻ ውስጥ ጠላት እንክርዳድ ሲዘራ ነው! ባንች ምድር እያየነው ያለነው ግን የሚ'ዘራውም እየበቀለ ያለውም እንክርዳድ ትውልድ ነው! ዳቦ ሆነው የሚያጠግቡን ስንዴዎችሽ ማን በላቻው?? ባህር ከፋይ አምላክሽ ጠላትን ሲመለከት እኛን ግን ለምን ረሳን ለምንስ አልተመለከተንም??? አዎዎዎዎ ልጠይቅሽ ብየ እንጅ ይህ የሆነበትን ምክንያት በቅዱሳን መጻህፍቶችሽ አቀዋለሁ!! የህዝብሽ ሃጥያት መብዛቱ ለጽዮኒቱ መቅደስ መማረክ ምክንያት ነው!!! በዘር በጎሳ ተከፋፍለን ያነደድነው እሳት የራሳችንን ፊት ለበለበን!!! አምላክሽ ካልተመለከትን በቀር የተደበላለቀውን ቁዋንቁዋ መልሶ የሚያግባባን ከወዴት ይመጣል??? እሱ ብቻ መፍትሄሽ እሱ ብቻ መድሃኒትሽ! ትንሳኤሽ በኅዝብሽ በደል ተቀብሮዋልና በንስሃ አካፋ የትንሳኤሽን ብርሃን እንገልጥ ዘንድ የእግዚአብሄርንን ቃል እየነገሩን ያሉትን ጦማሪ መምህራኖቻችንን ሰሚ ጆሮ ይስጠን!! አቤቱ አንድ አድርገን!!!!!!!!!!!!! አቤቱ የሆነብንን አስብ! አህዛብ ውደርስታችን ገቡ! የቅዱሳኑን መጽሃፍ ለአሞሮች የመቅደስህን ቅርሶችም ለአራዊት ሰጡ!!!አቤቱ ወደኛ ተመልከት! ረድኤታችን ሰማይና ምድርን ከፈጠርክ ካንተ ነውና ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!!!!!!

muller said...

አሁንስ በዛ:: የሀገር እና የሀይማኖት መሪዎች ግፍ አንገፈገፈኝ::ምን ይበጃል ጎበዝ?

Anonymous said...

Thank you dear Fr. Ephrem and Dn. Birhanu for the article. I read it with great attention. But I would like to ask a question: Do you believe that these people, the leaders of our church, trust in God? Are sure whether they are a people of faith? Look within ten years we lost about 10,000,000 our church members. Within few years we lost much of our sacred church antiques. Within few years we lost much of parish churches' properties. Within all these challenges the people from whom we are seeking solution have kept silent. During persecution they drove out the innocent students who sheltered in the church compound. so how we trust them whether they are a men of faith? So please do not lift your eyes towards them, but to the Almighty. They are thorns which have planted in the garden of our Lord and Saviour. So how you search for grapes from thorns unless you fool yourself? I believe as the remedy will be from God, not from any human power. All my dera brothers and sisters let us present our application to God with tear and a broken heart. But before that let us confess for sins and transgreses. Who knows whether all the difficulties we are suffering from the government and from the church leaders are rewards to our sins? Let us look inward and then cleanse our heart and thenafter let us come near to God. Please ddo not forget what was said by the prophet "Cursed is the man who trusts in man And makes flesh his strength." Do not forget that our LOrd is He who saved Jerusalem from being falling under the sword of Sennacherib? Oh Lord raise your hand, and save your people who have not any helper, but you alone.

Anonymous said...

Bire, thank u very much, God be with you..

male said...

My dear brother, things will be aggravated until the Ethiopian day comes!

Anonymous said...

every body is talking about problems currently facing our "betekrstiyan". I am not against the way we make the problem public. To day, Betekrstiyan is in a big trouble more than any other time, I think. What I want to say is that please try to say not only on the problems but also on how we can solve them too. If we have to face the gov't let's do something, If we have to blame the Betkihnet let's do it or if there is something to do let's do it. It is worrysome to hear that forests around Betekrstiyan being burned, to hear land of the Betekrstiyan being taken by gov't, on top of this to hear the ruling body of betekristyan being not responsible to solve the problems? What sall we do then? pleae let's para to God to forbid this siyuation and let's do something! God be with us.

Anonymous said...

thank you so much,Dn. Efrem. May God bless you!

lele said...

Abeto amelke hoy eredane

Anonymous said...

yezih negeris baynesa yishalal. libachin demto cherisowal. be tinishu beyalenibet yebekulachinin enadrig. egzier yibarikih.

Blog Archive