Tuesday, March 27, 2012

ኑ “እንፍጠር” - ነፍሰ ቆንጆዎች


(READ THIS IN PDF) የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያምን መጽሐፍ (ትግላችን፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ) እያነበብኩ ነበር - ባለፈው ሰሞን። በራሳቸው በኮሎኔሉ ተጽፎ፣ በፀሐይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት ታርሞ እና ተስተካክሎ በአሜሪካን አገር የታተመ ጥርት ክሽን ያለ ደረጃውን የጠበቀ (ይዘቱን አላልኩም) መጽሐፍ ነው። ብዙ ጊዜ እንዲህ የፊደሉ መጠን ለዓይን ሳይደቅቅ፣ ወይም ባቄላ ባቄላ አክሎ ለአረጋውያን ብቻ ወይም ለሕጻናት ፊደል ማስተማሪያነት የተዘጋጀ ሳይመስል፣ በሌላ አገር ቋንቋዎች በእንግሊዝኛው ወይም በጀርመንኛው ያነበብኳቸውን መጻሕፍት የመሰለ ደረጃውን የጠበቀ መጽሐፍ ነው።

 ፀሐፊው ኮሎኔል መንግሥቱ መሆናቸው በራሱ ማንም የኢትዮጵያን ታሪክ የሚከታተል ሰው ላይ ጉጉት መፍጠሩ አይቀርም። እኔም በዚያው ጉጉት ነው መጽሐፉን መግዛት እና ማንበብ የጀመርኩት። በርግጥ “እኒህን ዓምባገነን ለመጉዳት መጽሐፋቸውን ፎቶ ኮፒ አድርገን ለጠፍን” ያሉ ሰዎች ያሰራጩት ኮፒ እጄ ቢገባም መጽሐፉ ከመደርደሪያዬ ላይ እንዲኖር፣ አንድም በተሰረቀው ነገር ተጽናንቼ ላለመቀመጥ፣ ወጣቱን አሳታሚ ኤልያስ ወንድሙን እኔም ተደርቤ እንዳልጎዳው በሚል መጽሐፉን ለመግዛት አላመነታሁም።

የመጀመሪያዎቹን ምዕራፎች እና ታሪካዊ ትንታኔዎች የሚሰጡባቸውን ገጾች በወፍ በረር ካኼድኹት በኋላ፣ ወደ ዋናውና ከእርሳቸው ብቻ ልሰማውና ላገኘው ወደምችለው ርዕሰ ጉዳይ ለመግባት ተንደረደርኩ። “ሰውየው” (ብዙ ጊዜ ይባሉ እንደነበረው) አንደበታቸው ብቻ ሳይሆን ብዕራቸውም ርቱዕ ኖሯል ለካ? (ዐረፍተ ነገሮቻቸው ልክ እንደ ንግግሮቻቸው ረዣዥሞች ናቸው።) አይዟችሁ፤ እዚህ ገጽ ላይ መጽሐፉን የመገምገም ዓላማ የለኝም።

መንግሥቱ ከአንድ የዳር አገር ድንበር ጠባቂ ሻለቃነት ወደ ፈርጣማ ክንድ ያለው መሪነት ሲሸጋገሩ ያለውን ሁናቴ በግድምድሞሽ አስነብበውናል። “ግድ የለም አንተ ካልመራኸን አይሆንም” እየተባሉ ከተራ ሰውነት ወደ ዓምባገነንነት ሲለወጡ ይታያል። 60ዎቹ ባለስልጣኖች ሲገደሉ የነበሩት መንግሥቱ እና “ጥቂት ጄኔራሎች” ሲገደሉ የነበሩት መንግሥቱ አንድ ዓይነት አይደሉም። እና ኅሊና አንድ ጥያቄ ያቀርባል፦ የሰውየው ጠባይና ማንነት እንዳለ ሆኖ ዓምባገነኖችን በመፍጠሩ ሒደት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ሌላው አብሯቸው ያለው አፋሽ አጎንባሽ ጭምር ወይስ ራሱ ሰውየው ብቻ?

ዓምባገነኖች የኅብረተሰባቸው ውጤቶች እንጂ ከሰማይ ዱብ የሚሉ ልዩ ፍጥረቶች አይደሉም። ወደ ሥልጣን ጉዞ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ እየኮተኮተ፣ እያፋፋ፣ ጥይታቸውን እየተኮሰላቸው፣ እየሞተላቸው፣ እየገደለላቸው፣ “ካንተ በፊት እኔ” የሚልላቸው ከሌላቸው ብቻቸውንማ ደካማ ፍጥረቶች ናቸው። ኮሎኔል መንግሥቱ ዓምባገነን መሆናቸውን አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ቢሆንም ያገነናቸው ግን ያጀባቸው “ዓምባአግናኝ” ተከታያቸው ነው።

ጆሴፍ ስታሊን የቲዎሎጂ ትምህርት ተማሪ፣ ለሰማያዊ አገልግሎት መስክ ሥልጠና የጀመረ ቢሆንም ከዚህ ሕይወት ጋር ወደማይስማማ ጨፍጫፊነት የተቀየረው በብዙዎች ረዳትነት ለመሆኑ ማስረጃ አያሻም። ሒትለር ከምላጭ ምላሱ ውጪ ምን ነበረው? ነገር ግን በሚፈለገው መስክ ሲጠራቸው አቤት፣ ሲልካቸው ወዴት የሚሉ አፋሽ አጎንባሾች ሒትለርን ሒትለር አድርገውታል። ሳይንቲስቶቹ፣ ጄኔራሎቹ፣ አሳሪ ገራፊዎቹ፣ ጠቋሚዎቹ ባይኖሩማ 6 ሚሊዮን አይሁድ ምን አርጎ ይጨርስ ነበር ብቻውን? የኮሎኔል መንግሥቱም ብዙ ተመሳሳይ ነገር ያለው ይመስለኛል።

መጽሐፉን እያነበብኩ በሄድኩ መጠን እንዴት ታሪክ ራሱን እንደሚደግም እየገረመኝ፣ ከቋንቋ ቋንቋ፣ ከተግባር ተግባር ዓምባገነኖች ሁሌም ተመሳሳይነታቸው እያስደመመኝ ዘለቅኹት። በተለይም “አንተ ካልመራኸን፣ ይኼ አብዮት ዋጋ አይኖረውም፣ አንተ ከሌለህበት ኩሉ ከንቱ” የሚሉት የደርጉ አባላት ድምፆች በብዙ ስብሰባዎች፣ በብዙ አጋጣሚዎች የምሰማቸው ሆነው ተሰሙኝ።

ከትንሽ የኮሚቴ ሥራ ጀምሮ ፈር ቀዳጅ የሆኑ ሰዎች አንዴ ወንበሯን ከተቆናጠጡ በኋላ ራሳቸውም መውረድ አይፈልጉም፣ ሌላውም ተከታይ “እናንተ ጀምራችሁት በዚያው ቀጥሉበት እንጂ፣ ፍሬያችሁን ሳታዩ ከወንበሩ ለምን ትነቃነቃላችሁ” ባዩ ብዙ ነው። ዓምባገነኖች መጀመሪያ ሰሞን ሕዝቡ የሚላቸውን/ ውዳሴ ከንቱ ለመቀበል ይቸገራሉ፤ ሲደጋገም እያፈሩም መቀበል ይጀምራሉ፣ ኋላ ግን ወንበሩ ይገባናል ማለት ያመጣሉ፤ ሲቀጥል ይህንን የማይቀበለውን ይጨፈጭፋሉ።

በ1984 ዓ.ም፣ አንድ ጥቁር ቀሚስ የለበሱ፣ ፀጉራቸው ከሌሎቹ ጳጳሳት በተለየ ሁኔታ ያደገ፣ አንገታቸውን የደፉ ጳጳስ ብቅ አሉ። የ4ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ላይ። ለክርስቲያኖቹ በተዘጋጀ አንድ የምረቃ ዝግጅት። ይዘዋቸው የመጡት ነፍሳቸውን ይማረውና እዚህ አሜሪካ ያረፉት ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ነበሩ። እንግዳውን ብዙም ሰው አላስተዋላቸውም። እርሳቸውም እዩኝ እዩኝ አላሉም። ኋላ አቡነ ዜና ማርቆስ እስኪያስተዋውቋቸው ድረስ። ከአሜሪካ የመጡ ጳጳስ መሆናቸውን ለጉባኤተኛው ተናግረው አስተዋወቋቸው።

ቆይቶ እኒህ አንገታቸውን ደፍተው የተቀመጡት ሊቀ ጳጳስ 5ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ። ከዚያ ከጥቁር ልብስ ወደ ነጭ ተዛወሩ። አንገታቸውን አቀርቅረው ሲሄዱ አይቼ አላውቅም ከዚያ ወዲህ። ያጀባቸው ሁሉ አንገት ማቀርቀሩን በሚያጠፉ፣ መልዕልተ ሕግ መሆናቸውን በሚያሳምኑ ቃላት በአንድ ጊዜ ከአንድ ጳጳስነት ታይቶ ወደማይታወቅ ዓምባገነንነት ቀየራቸው። አሁን ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ሕግ የማይገዛቸው፣ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌላቸው፣ የፈቀዱትን ሁሉ በመናገር ብቻ የሚያስፈጽሙ፣ ምድራዊ ሕግም ሆነ ሰማያዊ ትዕዛዝ የማይዳኛቸው መንፈሳዊ ዓምባገነን ሆነዋል። ያንን የ1984 ዓ.ም የምረቃ በዓል ወቅት የነበረውን የርሳቸውን ሁኔታ እና አሁን ያሉትን ሳስተያይ በርግጥም ዓምባገነን በመፍጠር የተካንን መሆናችንን ያሳየኛል።

ዓምባገነኖች ከተራ ግለሰብነት ወደ አይደፈሬነት ሲጓዙ መንገዳቸው ትክክል አለመሆኑን የሚገነዘቡ ሰዎች አይጠፉም። ነገር ግን ድምጻቸውን የሚሰማ፣ አርቆ አስተዋይነታቸውን የሚገነዘብ ስለማይኖር የማስጠንቀቂያ ደወላቸውን ከምቀኝነት፣ ከተቀናቃኝነት፣ ከእኔ አውቃለሁ ባይነት እየቆጠረባቸው ታፍነው ይቀራሉ። ዓምባገነኖቹን በማፋፋት የሚያበረታታቸው ወገን ጥቂት እንኳን ሊረዳቸው ስለማይችል ዞሮ እነዚያን አድናቂዎቻቸውን ሳይቀር የሚያጠፋው ግለሰብ እየፈረጠመ ሲሔድ በሐዘን ለመመልከት ይገደዳሉ።

እነዚህ ከሌላው የጅምላ አስተሳሰብ ወጣ ብለው ነገሮችን አርቀው ለመመልከት የሚችሉ ሰዎች ይህ አርቆ አስተዋይነታቸው እና በጅምላ-ሕግ ለመመራት ያላቸው ዳተኝነት ዋጋ ያስከፍላቸዋል። ከጥቂት ጥቅም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት። ዓምባገነኖችን በማቆም ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ሕገ ወጥነትን ለመጋፈጥ የሚሞክሩ በሙሉ የሚከፍሉት ዋጋ ጥቂት አይደለም። በቅርቡ ለሕትመት የበቃ እና በየዘመናቸው ያሉ ሕገወጥነቶችን የተጋፈጡ ሰዎችን ታሪክ ያስነበበ አንድ መጽሐፍ (Beautiful Souls: Saying No, Breaking Ranks, and Heeding the Voice of Conscience in Dark Times) እንዲህ ሉትን ሰዎች “ነፍሰ ቆንጆዎች”/“Beautiful Souls”  ይላቸዋል።

እነዚህ ነፍሰ-ቆንጆ ሰዎች ከሌላው በጅምላ እሺ ባይ እና ዓምባገነን-አፋፊ ሰዎች የሚለዩት ትክክል ያልሆነን ነገር “እምቢ” በማለታቸው፣ እንደ ንጉሡ አጎንብሱ (ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው) አለማለታቸው እና በክፉ ወቅትም ቢሆን ትክክል የሆነውን ነገር ለመሥራት ኅሊናቸውን/ ውስጣቸውን ማዳመጣቸው ነው። የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ከጠቀሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው የስዊዝ ፖሊስ የአገሩን ሕግ በመጣስ ከጀርመን አምልጠው ነፍሳቸውን ለማትረፍ የመጡ አይሁዶችን ወደ አገሩ እንዲገቡ ይፈቅድላቸዋል፤ ሌላው ነፍሰ ቆንጆ ሰርቢያዊ ደግሞ በ1990ዎቹ የሰርብ-ክሮኤሺያ ጦርነት ወቅት ወዳጆቹ የሆኑ ክሮኤሺያውያንን ደብቆ ከሞት አትርፏቸዋል፣ አንድ እስራኤላዊ ወታደር በተያዙ የፍልስጥኤም ግዛቶች ላለማገልገል እምቢ በማለት እና የሚጣልበትን ቅጣት በመቀበል “መንግሥቴ ትክክል አይደለም” ሲል ሌላይቱ ነፍሰ-ቆንጆ ትልቅ የንግድ ድርጅት ኃላፊ ደግሞ ድርጅቷ የሚሠራውን ሕገ ወጥ ሥራ ተመልክታ ዝም ላለማለት ያደረገችውን እና መስዋዕትነት ትከፍላለች ሲል ያትታል።

በየደረጃቸው እና በየነበሩበት የሥራ መስክ ለራሳቸው ከማሰብ ይልቅ የኅሊና ፍርድን በመከተል ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የቆረጡ ሰዎች ውሎ አድሮ ያ ጥሩ ተግባራቸው እስከነ መልካም ውጤቱ የሚያበራበት ዘመን ይመጣል። እንዲህ ዓይነት እምቢ ባዮች የአገር ተስፋዎች ናቸው። የኅሊና ዳኞችም ናቸው። በአንድ ጽሑፌ እንዳልኩት “የጠፋ አዕምሮ ፈላጊዎች” እና ጠቋሚዎች ናቸው። አገር እና መንግሥት፣ ዓምባገነኖች እና አግናኞቻቸው መስመር ሲስቱ ወደ በጎ ኅሊናቸው እንዲመለሱ ቀይ መብራት የሚያበሩት እነዚህ ነፍሰ ቆንጆዎች ናቸው።

ነፍሰ ቆንጆዎች የፓርቲያቸው ሕግ ከኅሊናቸው ሕግ አይበልጥባቸውም። ዝምድና እና ጥቅም፣ ወንዝ እና መወለድ እውነቱን አይጋርድባቸውም። ብቻቸውን ‘እንትን እንደነካ’ እንጨት ሊያስቀራቸው የሚችለውን አቋም ለመያዝ ከባድ ውሳኔ ይወስናሉ። ውሎ አድሮ ሰው ማለት አውሬ አለመሆኑን የምናረጋግጠው በእነርሱ ነው። በእነርሱ ጥሩ ተግባር።

ኢትዮጵያ ብዙ ነፍሰ-ቆንጆዎች እንዲኖሯት የማይመኝ አይኖርም። የተለየም እንኳን ቢሆን እውነት የሆነውን ነገር የሚያሰማ ድምጽ። ትክክል አይደላችሁም ብቻ ሳይሆን፣ ትክክል አይደለንም የሚል ድምጽ። ተሳስታችኋል ብቻ ሳይሆን ተሳስተናል፣ ታረሙ ብቻ ሳይሆን እንታረም የሚል ድምጽ። ከዚህ ውጪ አንድ በተቀደደው መንገድ እንደ ቦይ ውኃ መፍሰስ የሰውነት ምልክት አይደለም። አይቶ አይቶ “እምቢ፣ እንዲህ ማድረግ አይገባም” የሚል ነፍሰ ቆንጆ ያስፈልጋል። ዛሬ ዋጋ የሚከፍል ነገር ግን ፍትሕ ርትዕ እንዲቀጥል፣ ሰው መሆን ዋጋ እንዳለው የሚያሳይ። ከውጪ የመጣ ሳይሆን ከመካከል የሚወጣ። በአገሩ ባይከበርም ነቢይ የሚሆን።

የኢትዮጵያ ዕዳዎች ዓምባገነኖች ብቻ አይደሉም። እነርሱን የሚያፋፉትም ናቸው። አማካሪዎቻቸው፣ ምርኩዞቻቸው፣ ዓይናቸውን የሚያውሯቸው፣ ጆሯቸውን የሚደፍኗቸው ነፍሰ-አዳፋዎች። በየዘመኑ ብዙ ናቸው። በኮሎኔል መንግሥቱ መጽሐፍ ውስጥ አብረዋቸው ጀብ ጀብ የሚሉት ብዙዎቹ እነርሱ ነበሩ። ዛሬም ከሌሎች ዘመነኞች ጋር፣ በሌላ ስም እና ልብስ፣ በሌላ የትውልድ ዘመን፣ በሌላ ፓርቲ ስያሜ ነገር ግን በተመሳሳይ ግብር አሉ። ኢትዮጵያን ከእነርሱ ይሰውራት። እኛንም ዓምባገነን-አፋፊዎች ከመሆን ይሰውረን። ነፍሶቻችንን እናቆንጅ።            

 

     

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

 

 

 

30 comments:

Anonymous said...

Well said Ephrem!!! Yes, we all are PRACTICALLY enemies of our generation and responsible for all the evil our country is facing. We need to STOP standing with the evil- NOW!!!

Anonymous said...

Ababaye; thank you for sharing with us, and I am glad that you make all the blame up on us that is always the case.

Muluemebet said...

Really nice one!

Anonymous said...

It is true and well said. May God bless you.

Anonymous said...

The true meaning of human beigns. This way we differ from other animals. Keep it up!
Thanks!.

Anonymous said...

i love it

Anonymous said...

አሁን ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ሕግ የማይገዛቸው፣ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌላቸው፣ የፈቀዱትን ሁሉ በመናገር ብቻ የሚያስፈጽሙ፣ ምድራዊ ሕግም ሆነ ሰማያዊ ትዕዛዝ የማይዳኛቸው መንፈሳዊ ዓምባገነን ሆነዋል። ያንን የ1984 ዓ.ም የምረቃ በዓል ወቅት የነበረውን የርሳቸውን ሁኔታ እና አሁን ያሉትን ሳስተያይ በርግጥም ዓምባገነን በመፍጠር የተካንን መሆናችንን ያሳየኛል።

Weyra said...

Well said bro! Very true and important for this generation; for the church as well as the palace.

ውቤ said...

ከሆዳቸውም ቀነስ ቢያደርጉም እኮ መጥፎ አልነበረም፤ነፈሰ ቆንጆ እንኳ ለመድረስ ባይችሉ!

Anonymous said...

Efrem Ahun Tnesh tenesh yederowoch abatoch Wenye eyemeta new Berta.Besgam benfsem Yhe melakm newena berta new yemlhe

Anonymous said...

አገር እና መንግሥት፣ ዓምባገነኖች እና አግናኞቻቸው መስመር ሲስቱ ወደ በጎ ኅሊናቸው እንዲመለሱ ቀይ መብራት የሚያበሩት እነዚህ ነፍሰ ቆንጆዎች ,,,,,,,,,ዛሬም ከሌሎች ዘመነኞች ጋር፣ በሌላ ስም እና ልብስ፣ በሌላ የትውልድ ዘመን፣ በሌላ ፓርቲ ስያሜ ነገር ግን በተመሳሳይ ግብር አሉ። ኢትዮጵያን ከእነርሱ ይሰውራት። እኛንም ዓምባገነን-አፋፊዎች ከመሆን ይሰውረን። ነፍሶቻችንን እናቆንጅ። YOUR SOUL IS Beautiful,,,,,EPHERM........

Anonymous said...

Thanks Ephrem I Like it V...e...r...y much

ቁጭቱ said...

በጣም ግሩም ጽሑፍ ነው ኤፍሬም። እውነተኛና በሕሊናቸው መመራት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መሄዱ (ጥቂቶችም ቢኖሩ” ስኳሩን ለመላስ” እያመነቱ መሆኑ) ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው።ሁላችንም ማለት በሚያስደፍር ደረጃ ለምን “አምባአጋናኝ” (የአንተን ቃል ልጠቀምና) ሆንን? የሚለውን ጥያቄም ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል።እንደኔ የሚከተሉት ከምክንያቶቹ ጥቂቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ፤
1. የምናምንበትን ነገር ለማድረግ በማያበረታታ ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ማደጋችን፣
2. ለአምባገነኖች በማጎብደድ በቀላሉ ሆድ መሙላት ስለሚቻል፣
3. በማጎብደድ የምንኖረውን ኑሮ ከኑሮ በመቁጠራችን እና በሕይወት ዘመናችን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውጣ ውረዶች (መታሠር፣ መሰደድ፣ መንገላታት፣መደህየት...) ከሚገባ በላይ ስለሚያሰቅቁን ፣
4. ማኅበረሰቡ ለእውነተኛና በሕሊናቸው መመራት ለሚፈልጉ ግለሰቦች ተገቢውን ክብር የማይሰጥ መሆኑ፣
5. ማኅበራዊ ጽናትንና እውነተኝነትን የሚያበረታቱ ሀገር በቀል ትምህርቶችና ጽሑፎች በተገቢው መጠን ያለመኖራቸው/ያለመዘጋጀታቸው ይልቁንም ማንነትን በሚያሳጡና ለሕሊና ባርነት የሚዳርጉ የሕትመት ውጤቶች ላይ ማተኮራችን፣
6. የሥነ ምግባር ምንጮችና መለኪያ ሊሆኑ የሚገባቸው የሃይማኖት ተቋማት በጥቅመኞች መጠለፋቸውና የመሪነት ሚናቸውን ያለመወጣታቸው ፣

እንግዲህ ለአምባ ገነኖች “ቀኝ እጅ” ሳንሆን ቢያንስ በተፈጥሮ የተሰጠንን ኅሊና ተጠቅመን ቢቻል ለሌሎች አርአያ ለመሆን፣ ቢያንስ ከነክብራችን ለመሞት መኖር፤ ወይንም ደግም በውርደትና በአጎብዳኝነት ኖረን ወደ መቃብር መውረድ። ምርጫው የእያንዳንዳችን ነው። ደይ እዴከ ሃበ ዘፈቀድከ እንዲል መጽሐፍ።

Anonymous said...

wedaje Ephrem;
It seems that you want to be so generous in saying "በፀሐይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት ታርሞ እና ተስተካክሎ በአሜሪካን አገር የታተመ ጥርት ክሽን ያለ ደረጃውን የጠበቀ (ይዘቱን አላልኩም) መጽሐፍ ነው። ".
For your info I noted a little more than 600 errors in the book. It really needs heavy editing. Mr. Elias and his associates should work hard in this regard.
Ye kanadaw wedajih

lele said...

tabarake

Anonymous said...

Bless you !

Anonymous said...

melkam new D ephrem seleabatochen maweratu asfelagenetu altayegnem...coz belela bekul yebetekrestian andeneten ykemifetatenu sewoch degafe endemestet ayhonem wey??yalew cheger endale hono.
maryland

Anonymous said...

I DON'T KNOW WHERE YOU GOING DN EPHREM IM REALLY AFREAD TO SAY THIS BECUSE I DON'T KNOW YOU LIKE THIS ...ANY WAY
GOD BE WITH YOU!!


EYOB

Abel said...

“ነፍሰ ቆንጆ እንፍጠር“ አልህ? ማለፊያ ነው፤ ለዚህ አይነት አመለካከት መታደል። ነገር ግን እነዲህ አይነት ሰዎች ሲፈጠሩ ና ባደባባይ መውጣት ሲጀምሩ አፉን ከፍቶ የሚጠብቃቸው አለ። የነፍሰ ቆንጆዎችን አፍ መዝጊያ፤ እድሜ ማሳጠሪያ፤ አእምሮ ማበላሻ፤ተስፋ ማስቆረጫ፤በመጨረሻም ከዚህ አለም ማሰናበቻ ስልታዊ በሆነ እና በተቀነባበረ መልኩ አለም ወጥመዷን ዘርግታለች። አንዳንዶችም ዝም የሚባሉት የጎላ ተጽእኖ እስካላመጡ ድረስ ነው። በላያችን ላይ የተዘረጋውን ወጥመድ ያናጋል ተብሎ ከተፈራ፤ ያ ነፍሰ ቆንጆ እንዳልሆነ ሆኖ ከአለም ይሰናበታል። አለም የረከሰ አመለካከት፤ ለሆዳቸው እንጅ ለህሊናቸው ያደሩ ሰዎችን አትፈልግም። አስመስላ ግን ማቅረብ ትችልበታለች። ከራባት አድርገው፤ ማይክ ጨብጠው እውነተኞች ነን እያሉ የሚያደነቁሩ ምሰለኔዎችን አሰማርታልናለች። አሁን አሁንማ፤ ክርስቶስ ያለውን ሕግጋት በአፋቸው እያነበነቡ፤ መስቀሉን ጨብጥው፤ ቆቡን ደፍተው፤ ቀሚሱን ለብሰው ሚንጎራደዱ ውስጠ ባዶዎችን በአደባባይ መገልገያ አድርጋቸዋለች። ክርስቶስን ጠርተው ሲዋሹ ትንሽ የማይሸማቀቁ ጉዶች አለምን ሞልቷታል። እንኳን አገርን፤ ነፍሳቸው እስካልወጣች ድረስ ለተሰማሩበት ነገር ሰውነታቸውን ከፍለው የሚሰጡ ምናምንቴዎች ሞልተዋታል! በዚህ መሃል ቆንጆ ማግኘት ቢቻል እንዴት ያስደስታል። ግን አይመስለኝም! ምኞቱ ግን አይከፋም! እንደ እኔ ከሆነ-አለም ተሎ ብትጠፋ፤ ኢትዮጵያ እስከነ ሙሉ ክብሯ ወደ አምለኳ ታቀናለች የሚልህ ጽኑ እምነት አለኝ!

Anonymous said...

gobez berta yemelewen comment new yemetawetawena GOBEZ BRAVO BERTA GEFABET AHUNEM YE BETEKRESTYANEN GEBENA BEDENB EYAWETAH POLETICANOCHEN KEBA ATETACHEW!! SO GOBEZ!?

Anonymous said...

ehimmm comment eye meretu makireb ambagenenenet yehone??

yenealem said...

በዚህ ጊዜ ቆንጆ ማግኘት ቢቻል እንዴት ያስደስት!!!!

Mehari said...

በስመ ውሸት፣ ወትዕቢት፣ ወአልጠግብ ባይነት አሐዱ አምባገነን፡፡ ኢአሜን፡፡
የአምባገነኖችን ብሔረ ሙላድ ጥንተ ነገድ እንደሚከተለው እንጥፋለን፡፡ ለዚህም የአምባገነኖችን የምሕረት ዓይን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም አምባገነኖች በሰፈሩባት ዓለም የእነርሱን የምሕረት ዓይን ተስፋ ካላደረጉ በስተቀር ልጻፍ ላሳትም፤ ልማር ላስተምር ቢሉ የሚቻል አይደለምና፡፡ እነርሱ እንደሰም አቅልጠው፣ እንደገል ቀጥቅጠው በሚገዟት፣ እንደ በሶ ጭብጥ፣ እንደ ትቢያ ርግጥ አድርገው በሚያስተዳድሯት ዓለም አንዳችም ነገር ያለነርሱ ደስታ አይደረግምና፡፡ ስለዚህም ዓይነ ምሕረታቸውን ተስፋ አድርገን የቡችሎቻቸውን ንክሻ ተሰቅቀን እኛ የአፍሪካ ልጆች ከአምባገነንነት፣ ከዕውቀት፣ ከበጎ ኅሊና፣ ከልምላሜ፣ ከመንፈሳዊነት፣ ከእውነተኝነት፣ ከትጉኅነት፣ ከደግነት ነጻ በወጣችው፣ እምዬ ሀገራችን፣ ድንግሊቱ ኢትዮጵያ ላይ ሁነን የአምባገነኖችን የዘር ግንድ እንደሚከተለው እናስረዳለን፤ እንተነትናለን፤ እናስተነትናለንም፡፡

ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ አምባገነኖች በሰማይም በምድርም ነበሩ አሉ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ጥንት መሠረታቸው በሰማይ አለቃውን ማየት ሲያቅተው አለቃዬ አልታየኝም ሳይሆን አለቃ የለኝም በማለቱ ነገደ ሰማይን ያበጣበጣቸው ዲያብሎስ ነው፡፡ ስሙ የተገኘው ዲያ እና ቦሎስ ከሚሉ ሁለት የግሪክ ቃላት ሲሆን ትርጓሜውም የሚለያይ ማለት እንደሆነ አብነት አለ፡፡ (ሙሉ ታሪኩ ለሌላ ጊዜ ይቆየን፡፡)

ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር (ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስ) አምባገነኖች ከአራት ወላጆች ይገኛሉ፡፡ እኒህ ወላጆቻቸው ህልውና ካላገኙ በስተቀርም እነርሱ የሚያቆጠቁጡበት ሥር የላቸውም፡፡ እነዚህ ወላጆቻቸው ታዲያ በጠባያቸው አራት ይሁኑ እንጂ በግብር አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህም አንድነትና አራትነት አላቸው ማለት እንችላለን፡፡ እንዲህም ስለሆነ እንደሚከተለው የአንድነታቸውንና የአራትነታቸውን ነገር እንደሚከተለው እንናገራለን፡፡

በቅድሚያ የአራትነታቸውን ነገር፡-

ፈሪ ጀሌና ግድ የለሽ፡- ለማበብ እንጂ ለማሰብ የማይፈቅዱ፣ “ለምን” ብሎ ለመጠየቅም ሆነ “እንዴት” ብሎ ለመመርመር እንግዳ የሆኑ ሰው መሰል ነገሮች ናቸው፡፡ አጠር ባለ አገላለጥ “‘ለምን’ ለምኔዎች” ልንላቸው እንችላለን፡፡ እነዚህ እንደአበባ ማበብ ማለትም መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት፣ መራባት ከሚለው የአበባ (የእንስሳ ጠባይ) በስተቀር ሌላ ነገር የማይታያቸው የሚናገሩ እንስሶች ናቸው፡፡ ለእነርሱ አሳሳቢው ጉዳይ ለምለም ሣር መጋጥ፣ ጥሩ ምንጭ መጎንጨት፣ ጥሩ ዋሻ ማግኘት፣ የዓይን አምሮት የሥሪያ ፍላጎት ሲንር ደግሞ የሚሠረር ማግኘት ነው፡፡ “ለምን” ብለው ከጠየቁ እንዴት ብለው ከመረመሩ ሣሩንም፣ ምንጩንም፣ ዋሻውንም፣ ሥሪያውንም እናጣዋለን፤ “ዓለምን መቅጨታችን ቀርቶ አንገታችን ይቀጫል፡፡” ብለው ስለሚፈሩ ይህን የሰጣቸው ሁሉ እንደልቡ ሊጌተይባቸው ይችላል፡፡ ሣሩን መጋጥ እስከቻሉ ድረስ ቢገረፉ፣ ቢለጠለጡ፣ ቢለመጠጡ ግድም የላቸው፡፡

አቤ ጉበኛ በዘመኑ እነዚህ በዝተውበት ነው መሰለኝ “ሰው፣ ሰው፣ ሰው፣ የሰው ያለህ!” ያለው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሞገደኛው ደራሲ ብርሃኑ ድንቄ ቢያገኟቸው “ከሁሉ አስቀድሞ የሰውልጅ መማር ያለበት ሰው መሆኑን ነው፡፡” ብለው ያስተምሩልኝ ነበረ፡፡ ምን ያደርጋል አማርኛ አይገባቸው!

ራስ ወዳድ ወሰነፍ፡- አንዲት ሥራ ስትሰጥ የሥራዋን ኃላፊነት መቀበል የሚያመጣባቸውን ምቾት ማጣት ፈጽሞ የማይፈቅዱ እነርሱ ጥቂት ደክመው ሌላው ብዙ ከሚጠቀም ይልቅ እነርሱ ተመችቷቸው እስከኖሩ ድረስ ሌሎች ገደል አልያም ገሃነም ቢገቡ ደንታ የማይሰጣቸው ናቸው፡፡ እስከጠቀማቸው ድረስ ለማንም ቢሆን ለመስገድ ዝግጅታቸው ሁሌም ምሉዕ ነው፡፡ አምባገነኖቹ በሌላ አምባ ገነን ሲተኩም የፍንደዳ አቅጣጫቸውን በብርሃን ፍጥነት ቀን ወደሞላለት አምባገነን የማዞር ልዩ ብቃት አላቸው፡፡ የኑሮ ኮምፓሳቸውም “ምቾት” ወደሚባለው የምድር ጫፍ ብቻ ያመለክታል፡፡

አሁን ትናንትና አንድ የ77 ዓመት ሽማግሌ በችግር ምክንያት ራሳቸውን አጠፉ ተብሎ ግሪካውያን ከልሒቅ እስከ ደቂቅ በእንባና በኡኡታ ተተራምሰዋል፡፡ ይህን ባዩ ጊዜም እነዚህ የአምባገነኖች ወላጆች “ምናገባቸው! አርፈው ግሪካዊ እንጀራቸውን አይበሉም? ጥጋበኞች! አንድ የሰባ ሰባት ዓመት ሼባ ሞተ ኖረ ምን ሊፈይድ?” ብለዋል፡፡ ለእነርሱ ሽማግሌው አንድ ችግር ጢምቢራቸውን ያዞረው እብድ ናቸው፡፡ ሰው መሆን አይታያቸውም፡፡ እንደ ሰው ተከብሮ መኖር አይገለጥላቸውም፡፡

ጥቅም እስካስገኘ “ከእግረ መስቀልዎ ሥር ወድቄ እለምናለሁ፡፡” በሚል ደብዳቤ ጳጳሱ የያዙትን የአምላክ መስቀል ለጥቅማቸው ሲሉ ለጳጳሱ ይገብሩታል፡፡ የጳጳሱ ንብረት ያደርጉታል፡፡ ጥቅም እስካስገኘ ድረስ የእምነት ተቋማታቸውን በአማናዊ ለውጥ ከማሻሻል ይልቅ በብስባሹ ውስጥ መኖርን ይመርጣሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲውን ነገን በብሩኅ ዓይኖች የሚመለከት የነገው ትውልድ ፓርቲ ከማድረግ ይልቅ የፓርቲውን መሪዎች “ያለእናንተ ማን አለን!” በሚል ግልብ ሽንገላና የዓይጥ ምስክር ድንቢጥ የሚሉት ዓይነት የተምታታ ቁጥር ሪፖርት በማሳወር ሰዎቹ ራሳቸውን አምላክ አከል እንደሆኑ አድርገው እንዲያስቡ ያደርጓቸዋል፡፡ ሕዝብ ማለት እነርሱ አጎንባሽ አከንፋሾቹ ወይም አቆላማጮቹ ብቻ ይሆናሉ፡፡

አንዷ የቀድሞ እመቤት የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ስንት ነው ተብሎ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እኛ የሰው ልጆቹ እንደው ከዚህም ከዚያም ተብሎ ተለቃቅመን 500 እንሞላለን፡፡” እንዳሉት ሕዝብ ማለት እነርሱና እነርሱ ብቻ ይሆናሉ፡፡ የሾሟቸው አለቆቻቸው ቢሆኑም የአለቆቻቸውን ስም ተጠቅመው ራሳቸውን የሕዝብ አፍ፣ ሆድ፣ ኩላሊትና ሳንባ ሳይቀር አድርገው በመሾም የመንግሥትን የአየር ብክለት የመከላከል ፖሊሲ ብቃት፣ በመጠጥ ውኃው ንጽሕናና ሞልቶ መትረፍ የተነሣ ኵላሊት በደስታ ሊፈነዳ እንደደረሰ፣ እንዲያውም በቅርቡ ድጋፌን የማሳይበት ሰልፍ ለብቻዬ ካልወጣሁ ብሎ በመሟገት ላይ መሆኑን፣ ከምግብ እኽል ዋጋ ቁጥጥር ስኬት የተነሣ ሆድ በየቤቱና በየጎዳናው በሚዘጋጀው በነጻ የሚታደል ምግብ በቁንጣን መከራውን በማየት ላይ እንደሆነ፣ አፍም ከመናገር ነጻነት መብት ፍጹም ልዕልና የተነሣ ምን ላውራ እያለ እንደተቸገረ ይነግሩላችኋል፡፡ የጭንቅላት ጉዳይማ አይነሣ! ጭንቅላት ከትምህርቱ ፖሊሲ ጥራት የተነሣ በዕውቀት ወፍሮ ለመንቀሳቀስ እንኳ እንደተቸገረ በሰፊው ይተርኩላችኋል፡፡ በቴሌቪዥንም የጭንቅላቱ ስባት ለልዩ ልዩ የሊቅነት ችግሮች ያጋለጠውንና በጂምናስቲክ ሊያጠፋው የሚሮጥን ሰው ያሳዩዋችኋል፡፡ “አንዳንድ የምናምን አካባቢ ነዋሪዎች እንዳሉት፡፡” ተባብለው ራሳቸውን ምስክርም ይጠራሉ፡፡

ተባይ ያፈራውን ቤት አፍርሶ መሠረቱን አስተካክሎ ሳይለቅ በመልካም መሠረት ላይ ከማነጽ ይልቅ አንድ አንድ ትኋንና ቅምቡርስ እየለቀሙ “ጀግንነታቸውን” ማስመስከር በዚያም ምቾታቸውን ማስጠበቅን ይመርጣሉ፡፡ ቅምቡርሱ ከጠፋ የሚሠራ ስለሚያጡና “ጀግንነታቸው፣ የቁርጥ ቀን ልጅነታቸው” ስለሚረሳ በተቻለ መጠን ቅምቡርሱን የመጠበቅ ኅቡዕ ሥራ ይሠራሉ፡፡

እንግዲህ እነዚህ ወላጆች ትዕቢትና ግርግር የሚባለው ወርኃ ርቢ በደረሰ ጊዜ አምባገነኖችን ይፀንሳሉ፡፡ ይወልዳሉም፡፡


አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን በእነርሱ ረድኤት ላገኘነው የጨጓራ በሽታችን መድኃኒት ይዘዝልን፡፡

Anonymous said...

beautiful content, beautiful expression....
i wish you keep on writing.

Anonymous said...

Wow,better to say wow!!!Amazing summary. I liked the finishing a lot.Amen Medihanitun Yizezilin!
God bless D.Ephrem

Hunegnaw said...

I like it Dn. Ephrem berta but take care. ufa anjete kibe teta (wuy leka kibe yelem)endih mastenfesha sigegn medhanit new larere koshit.

Anonymous said...

You said so?! Cool. Let's start to be recognizing being beautiful souls could have its price.

Anonymous said...

Beautifully written. Yes, If our country start to have from the higher govenmental administrator humans like those with " BEAUTIFUL SOULS" we would not hae all these miseries we see aound. And the actual governers seems to be not lucky to be in this category, So that they become AMBAGENENS. I think we all need to see the future of the Country and our children future and we need to start to be responsible for every and each behavoural action we do today to form the best and beautiful soul society.

Anonymous said...

Every thing is not simple as saying. Deacon Efrem are you ready to come here in Ethiopia and be one of the beautiful souls ? If that is the case, you might produce more beautiful souls like yours. Otherwise, being in a well developed country and leading a beautiful life and preaching others to have beautiful souls doesn't hold water.

Anonymous said...

ኧረ ምነው!ኧረ ምን ላድርግ!...በውኑ የነኣብርሓም፣ይስሓቅና ያእቆብ ኣምላክ በእውነት ኣለህ?በውነትስ ይህን ሁሉ ነገር ዝም ብለህ እያየህ ነውን?...
እኔስ ጨነቀኝ..እውነቱም ተደባለቀብኝ!የቱን ትቼ የቱን ልያዝ?የቱንስ ትቼ የቱንስ ልከተል?..ኧረ ምነው?ምንስ ልታሰማን ነው?
...በእውነት ጥንት ምድርን በሃይልህ ስታጠፋት መልኩ የተለየ ቢሆንም ከዚህ ዘመን የተለየ የምንፍቅና ሥራ ነበረ ማለት ነውን?...
ወይስ ለቃልህ መለወጥ ለኪዳንህ መንጠቅ ለፍርድህንም መጓደል የለበትምና ያ ከኣባታችን ኖኅ ጋራ ያደረግከው ቃል ኪዳን ስለያዘህ ነው? ?
ኧረ እኔስ ጨነቀኝ...በእውነት ዓለም በሰፊው ጠበበኝ...ምን ላድርግ? ? ? ምንም!ልክ እንደ ኣባቴ ኢዮብ የተወለድኩባትን ቀን ረግሜ ዝም እላለሁኝ...
ቀሪው 'ማ ልብንና ኩላሊትን የምትመረምር የኣባቶቼ ኣምላክ እግዚኣብሔር ኣንተ ታቃላህ...ሁሉም ባንተ ነው..ሁሉምም ካንተ ነው...ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያም
ካንተና ያንተ ናትና ምሕረት ያዘሉና የያዙ ዓይኖችህ ያዩዋት ይጎብኙዋትም እንጂ እኔ ምን ሥልጣኝ ኣለኝ?ምንስ መሥራት እችላለሁኝ?የተሰራውን፣የተነገረውን፣
የተወራውን....ሁሉ ኣንተ በሰጠሀኝ ጆሮየ ዝም ብየ እሰማለሁኝ....
ኣሁን ደግሞ እኔ ጠቦትህ ይጠብቁኝ ዘንድ የሰጠሀኝን ቅዱስ ኣባት ከነ "ሂትለር"፣ከነ ኮለኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም እናም ከሌሎች ኣምባገነኖች ጎን ተሰልፈው
እየሰማሁ ነው....ቆይቼስ ምን ልሰማ ይሆን ? ? ከዚህ ያለፈ የሚሰማ መጥፎ ነገር ይኖር ይሆን?!!!....
ይትባረክ እግዚኣብሔር ኣምላከ ኣበዊነ ወረዳኤ ኣበዊነ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም ኣሜን.....ቸር ቸሩ ያሰማን እንጂ ምን እንላለን!

Blog Archive