Friday, April 13, 2012

ልዩነት በወጥነት እና ብዙነት በአንድነት


(READ ልዩነት በወጥነት እና ብዙነት በአንድነት  IN PDF) ከዕለታት በአንድ ቀን፣ ከአንድ ወዳጄ ጋር ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዘናል። ርዕሳችን ስለምንኖርበት አገር፣ ስለ አሜሪካና አሜሪካውያን ነበር። ያ ወዳጄ በሥራ ቦታው ከገጠመው ነገር እየተነሣ “አሜሪካውያኑ እንዲህ ብለው፣ እንዲህ አድርገው፣ እነዚህ አሜሪካውያን” ይለኛል። እስያውያን የሚመስሉ ዓይነ-ጠባቦቹን በደፈናው “ቻይናዎቹ” ይላቸዋል። ጠቆር ያሉትን “እነዚህ ጥቁሮች”፣ ስፓኒሽ ተናጋሪ አሜሪካውያንን ደግሞ “ስፓኒሾች” በሚል የደፈና ቃል ይጠራቸዋል። ለካስ እርሱ አሜሪካውያን የሚላቸው “ፈረንጆቹን” ብቻ ኖሯል። ይህ መነሻ ሆኖን ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት አንጻርም እየተመለከትነው ብዙ ተጨዋወትን።

በወዳጄ አስተያየት አሜሪካዊነትን ወጥና አንድ ቀለም አድርጎ ሌላውን “የወረቀት ላይ አሜሪካዊ” አድርጎ ተቀብሎታል። አስቦ፣ አውጥቶ እና አውርዶ ሳይሆን እንደ ወረደ ያለው አስተሳሰብ ነው ይኼ። በሌሎች አገሮችም ሲዘዋወር ከሚያውቀው የአንድ አገር ዜግነት መገለጫዎች ተነሥቶ የደረሰበት ድምዳሜ ይመስላል። ቻይናዎችም ሆኑ ጃፓኖች፣ ሶማሌዎችም ሆኑ፣ ኡጋንዶች፣ እንግሊዞችም ሆኑ ጀመርኖች፣ በቋንቋቸው ሆነ በቀለማቸው ወይም በጠቅላላው አኳዃናቸው መገመት ስለሚቻል አሜሪካውያንንም በዚያም የጅምላ መመዘኛ መዝኗቸዋል።

አሜሪካውያን ከተለያየ ዓለም፣ ከተለያየ የዘር ዓይነት፣ በተለያየ ዘመን መጥተው አንድ ትልቅ አገር የመሠረቱ ሰዎች ናቸው። ከየአገሮቻቸው ችግር ሸሽተው የመጡ አይሪሾች፣ እንግሊዞች፣ ጀርመኖች … ስፓኒሾች፣ ጣሊያኖች፣ ግሪኮች … ራሾች፣ ፖላንዶች፣ ቻይናዎች … ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊያውያን፣ ኤርትራውያን … ኢራናውያን፣ ቱርኮች፣ ሊቢያውያን … ነጩ፣ ቢጫው፣ ጥቁሩ፣ ጠይሙ … ክርስቲያኑ፣ ሙስሊሙ፣ ይሁዲው፣ እምነት የለሹ … ሁሉም አሜሪካዊ የሆነባት ምድር ናት። በብዙ መልኩ አሜሪካ ሌላዋ ኢትዮጵያ ትመስለኛለች።

አውሮፓውያን ከየአገሮቻቸው መከራ እና የመብት ጥሰትን ሸሽተው ወደዚህኛው አህጉር ከመጡ በኋላ በጥንታውያን አሜሪካውያን ወይም በእነርሱ አጠራር “ቀይ ሕንዶች” ላይ ብዙ መከራ አድርሰዋል። ከዚያም አልፈው አፍሪካውያንን ከምድራቸው በብረት ሰንሰለት አስረው በማጋዝ ለብዙ መቶ ዓመታት ኢሰብዓዊ በሆነ የባርነት ቀንበር ቀጥቅጠው ገዝተዋቸዋል። ስፓኒሾችን እና ቀለማቸው በመጠኑ ጠየም የሚሉ ዜጎችን በሙሉ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲመለከቷቸው ኖረዋል። እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ ሁኔታም ቢሆን ግን አሜሪካ የምትባል አገር መሥርተዋል። በየአገሮቻቸው ድህነት ያቆራመዳቸውና ያንን ችጋር ለመሸሽ የመጡ ነጮች፣ በባርነት የመጡ ጥቁሮች፣ ፖለቲካዊ ጭቆና አንገፍግፏቸው የሸሹ ራሾች፣ ፖላንዶችና ቻይኖች፣ ድህነት ያባረራቸው ስፓኝ ተናጋሪ ሕዝቦች (ሒስፓኒኮች) ዛሬ የበለጸገች አሜሪካ አካላት ናቸው። እስከነ ልዩነቶቻቸው፣ እስካለፈ የታሪክ ጠባሳዎቻቸው ማንነታቸውን እና ያለፉበትን ክፉውንም ደጉንም ነገር ሳይዘነጉ በአሜሪካዊነታቸው ኮርተው ይኖራሉ።

ማንም ሰው፣ ከየትም አገር ይምጣ ከየትም፣ ሕጋዊ ሆኖ የሚኖር እስከሆነ ድረስ፣ አሜሪካዊ ዜግነት ለማግኘት ጥቂት ዓመታት መቆየት ብቻ ይበቃዋል። የመጣበት አገር፣ ይናገረው የነበረው ቋንቋ ወይም የቆዳው ቀለም በዜግነት ሊያገኘው የሚገባውን ነገር እንደማይቀንስበት ሁሉም ይናገራል። የትም ተወልዶ ይምጣ በአገሪቱ ያለው ማንኛውም ደረጃ ለመድረስ እንደሚችል አሜሪካውያን በኩራት ሲናገሩ ይሰማል። “አሜሪካን ድሪም” ይሉታል። ማንም ሰው በአሜሪካ ሊያሳካው የሚመኘው፣ እናም የሚያገኘው ድንቅ ራእይ መሆኑ ነው። አሜሪካዊ ሆነው ያልተወለዱ፣ ነገር ግን በሒደት ዜግነቱን ያገኙ ሰዎች ሊይዙት የማይችሉት ብቸኛ ቦታ “ፕሬዚደንትነት” ብቻ ነው። ከዚያ በመለስ ምንም ነገር ቢሆን ለማንም አይከለከልም።

በዘመነ ክሊንተን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ማድሊን ኦልብራይት የቼክ (የድሮዋ ቼኮዝላቫኪያ አካል) ተወላጅ ናቸው። ሳይንቲስቱ አሌክሳንደር ግራኻም ቤል ስኮትላንዳዊ፣ አልበርት አይንሽታይን ጀርመናዊ፣ ደራሲው አይዛክ አሲሞቭ ራሺያዊ፣ ጋዜጠኛዋ አሪያና ሀፊንግተን (The Huffington Post መሥራች) ግሪካዊት፣ ታዋቂዋ ሞዴል ኢማን ሶማሊያዊት፣ ዲፕሎማቱ ሔንሪ ኪሲንጀር ጀርመናዊ፣ የፊልም አክተሩ አርኖልድ ሽቫርዘንኤገር ኦስትሪያዊ …. ናቸው። ሁሉም ግን በመዝናኛውም፣ በፖለቲካውም፣ በሳይንሱም ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ከማንኛውም ሌላ አሜሪካዊ ባልተናነሰ የሚታወቁ ዝነኞች ናቸው።

ይህ “ከየትም መጥቶ አሜሪካዊ የመሆን” ነገር ለኢትዮጵያውያኑም ሠርቷል። በስደትም፣ በሽሽትም፣ በዲቪም፣ በሥራም የመጣው ያገራችን ሰው ውሎ አድሮ ዜግነቱን እያገኘ “ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ” በሚል ቅጽል ይጠራል። በእርግጥ ብዙ ወገኖች ለረዥም ዓመታት በአሜሪካ ኖረውም የአገራቸውን ፓስፖርት እንደያዙ፣ ዜግነታቸውን እንደጠበቁ፣ የዘለቁ እንዳሉ ይነገራል። በይፋ ሲናገሩ የሰማነው የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅን ይመስለኛል። ሌላው አሜሪካ ኖሮ ወደ አገሩ የሚመለሰው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ዜግነት እንደያዘ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ ወረቀቱ አሜሪካዊ ቢለውም በልቡ ግን ኢትጵያዊነቱ እንደተጠበቀ ይኖራል። ነገሩ የሚለወጠው ከተተኪው ትውልድ ነው። ኢትዮጵያዊው ቅመም ከወላጆቹ ዘንድ ተንጠፍጥፎ ቀርቶ እንደሁ።

   አሜሪካ ኢትዮጵያን ትመስለኛለች ያልኩትን ላስታውስ። አሜሪካ ከመላው ዓለም የሚመጣውን ሁሉ እያስገባች፣ እየቀረጸች፣ እየዳበሰች የሯሷ እንደምታደርገው ሁሉ ኢትዮጵያስ ብትሆን የብዙ ብሔረሰቦች ቅምም፣ ውሑድ አይደለችምን? ብዙነትን በአንድነት ስለማስተናገድም ቢሆን እንደ አሜሪካ እኛም ብዙ ሆነን ሳለን አንድ ሆነን፣ አንድ ሆነን ሳለን ብዙ ሆነን፣ ደግሞስ ኢትዮጵያ ሆነን አልኖርንምን?

አሜሪካ የሚኖር ማንኛውም ሰው ዛሬ ዕለቱን ከአንዱ ጠቅላይ ግዛት ቤቱን ንብረቱን ነቅሎ በሚቀጥለው ሣምንት በሌላ ሩቅ ጠቅላይ ግዛት አዲስ ኑሮ፣ አዲስ ቤት መሥርቶ ይኖራል። ድንበሩ እስኪመልሰው እግሩ የቻለው ድረስ መሔድና መኖር ይችላል። አገሩ ነዋ ሁሉም። ኢትዮጵያስ ቢሆን ሰሜን ብወጣ ደቡብ ብወርድ፣ ምሥራቅ ብሔድ ወይስ ምዕራብ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለሁ ድረስ “እኮ ማን ነህ? ለምን መጣህ ወዲህ? ምን ፈልገህ? የት ልታርስ? የት ልትቀበር” የሚለኝ ማን ነው? ኢትዮጵያ ሁሉ ቀዬዬ አይደለምን?

ግላዊ ማስረጃ፦ ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት አንድ የሜታ-ሮቢ መልከ መልካም ቆንጆ ወጣት አንዲት የመንዝ ሴት አገባና ልጆች ወለደ። መንዜዋም አማርኛዋን ሳትረሳ ኦሮምኛ ጨምራ ልጆቿ በኦሮምኛ አፋቸውን ፈቱ። በሌላ አካባቢ ደግሞ የሰላሌው ኦሮሞ ጎረምሳ ጎጃሜዋን ቆንጆ አግብቶ ብዙ ልጆች አፈሩ። ሜታ የተወለደችው ወጣት ሰላሌ ካደገው ጋር አዲስ አበባ ላይ ተጋብተው ልጆች አፈሩ። የእነርሱ ልጅ ደግሞ ከወሎዋ ቆንጆ ጋር ተጋብቶ ልጆች ወለደ።  እኮ የነዚህ ዘረ-ብዙዎች አገራቸው ኢትዮጵያ እንጂ የት ይሆናል? ሰላሌ፣ መንዝ፣ ሜታ ሮቢ፣ ወሎ ወይስ ጎጃም?

አሜሪካዊነት በዜጎቹ ትውልድ እና ማንነት ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነው ሁሉ፣ ወይም አሜሪካዊነት የብዙ ዜጎች ድምር ውጤት ብቻ እንዳልሆነው ሁሉ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ማለት እኛ ሰማንያ ምናምን ብሔረሰቦች ብቻ ስለተደመርን የምናመጣው ሳይሆን የነዚህ ሁሉ ማንነቶች ማዋሐጃ እና ማጣበቂያ፣ ማዋደጃ ቅመም ጭምር የተጨመረበት ልዩ ጸጋ ነው። ኢትዮጵያዊነት ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይለያል። አፍሪካ አንድነት የተለያዩ አገሮች ተደምረው የሚያመጡት የሒሳብ ድምር ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያዊነትን በድምር ብቻ ለማምጣት ማሰብ ኢትዮጵያዊነት ከሚባለው ንጥረ ነገር ጋር አለመተዋወቅ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ኦሎምፒክ ላይ ባንዲራዋን ከፍ ሲያደርጋት ዕንባ ዕንባ የሚለን ነው። አድዋን ስናስብ በስሜት የሚንጠን፤ በሰው አገር ተቀምጠን እንኳን አየር መንገዳችንን ከሌሎች አገሮች አውሮፕላኖች መካከል ስናየው የምናውቀውን ሰው እንዳየን ሁሉ ሩጡ ሩጡ፣ እቀፉት እቀፉት የሚያሰኘን። ብዙ ቋንቋዎች ብንናገርም ኢትዮጵያዊነት በአንድ ቋንቋ ከመግባባት በላይ ነው። ቀይ ወይም ጥቁር፣ ጠይም ወይም የቀይ ዳማ ቀለማችን ልዩ ልዩ ቢሆንም ወዛችን አንድ ነው። አሜሪካውያኑ ከየትም ከየትም መጥተው “እኔ አሜሪካዊ ነኝ” ሲሉ በኩራት እንደሚናገሩት ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ ማለት ቢያኮራ እንጂ አንገት የሚያስደፋ አይደለም።

ኢትዮጵያዊነት ብዙነትን የያዘ አንድነት ነው። በአሜሪካ እንደማየው ሁሉ ኢትዮጵያዊም በአገሩ ውስጥ በኑሮ ለመዘዋወር ምንም ዓይነት ድንበር አያስፈልገውም። በአንዲት ቀበሌ ውስጥ ብቻ እንዲኖር ሊፈርድበት የሚችል ማነው። እግሩ እንደወሰደው ወደፈቀደው ቢሄድ፣ ቢያርስ፣ ትዳር ቢመሠርት፣ ልጆች ቢያፈራ ኢትዮጵያዊ መብቱ ነው። ከዚህ ዓመተ ምሕረት በፊት ወደዚህ የመጣህ ከሆንክ መኖር ትችላለህ፣ ከዚህ ዓመት ወዲህ የመጣህ ከሆነ ደግሞ ወደመጣህበት ተመለስ ሊለው የሚችል ልዩ የዜግነት መብት የተሰጠው ልዕለ-ኢትዮጵያዊ ማን ይሆን?

 ብዙነታችንን የልዩነት ምልክት አድርገን እንደ ሐውልት እስካላቆምነው ድረስ ብዙነታችን እና ልዩ ልዩ መሆናችንን ከጥፋት አንቆጥረውም። እግዚአብሔር ሲፈጥር እንዲህ ልዩ ልዩ አድርጎ መፍጠሩ ውበት እና ጣዕም ከመሆኑ በስተቀር የጠላትነት ምልክት አልሆነም። ዓለም ሁሉ ዛፍ ብቻ ቢሆን ወይም ፍጥረት ሁሉ አሳ ብቻ ቢሆን እንዴት ይሰለች? በምድር የሚሽከረከረውን፣ በሰማይ የሚበረውን፣ በሆዱ የሚንሸራተተውን፣ በውኃ ውስጥ የሚመላለሰውን ሁሉ በየነገዱ ግሩም አድርጎ ስለሠራው ከምንበላው፣ ከምንነዳው፣ ከምንገዛው የተረፈውን ለአንክሮ-ለተዘክሮ ፈጥሮልን ኑሯችንን ውብ አድርጎታል። ብዙነት ውበት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ታዲያ። ኢትዮጵያዊነትም እንዲህ እንደ ብዙ ፍጥረታት፣ ልብ እንደሚመስጥ ጥንታዊ ሲምፎኒ (symphony) ብዙነቱ አንድ ልዩ ቃና ይፈጥራል። አንድነቱ ከብዙነት ይገኛል።

 

  

  

 

 

 

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

 

 

 

13 comments:

Anonymous said...

ኢትዮጲያዊነት...ተባረክ!!

Anonymous said...

well saied ababa
ኢትዮጵያዊነት በአንድ ቋንቋ ከመግባባት በላይ ነው።

Anonymous said...

Ababa: ጦስ ነናኔ ነከታ ኡባ ናጐ:: ኑ ብትዮ ቶጵዮ ኑ ጐዳ አይያ ማርያማ እስፕተታን መርናው ናጉ::

lamelame europe said...

DN BATAME DASE YELALE
YAKEDOSANE AMELAKE ETHIOPIANE YETABEKELENE

ኤፍሬም እሸቴ said...

I wish I know what you meant here. "ሎኦ ጎዳ ወልቃ" beyalehu lemanegnawem.

ኤፍሬም እሸቴ said...

Amen

Anonymous said...

Living in Diboc or Werder, Shiraro or Moyale is a constitutional right as long as I remember from my civic education classes. Good one, thanks for sharing the article here. I wish there is this common understanding 'the right to live and work any where in the territory of ones own country without any discrimination and disrespect'. Racial difference is born and not a choice issue for every one. I wish school children are also thought the central dogma of being an Ethiopian-the rights, privilages and duties. If unity is strength, we need also to have a system works on it and not against it-one is the central government the others are our civil societies.
I wish I feel free to live and work any where any time in the territories of Ethiopia. I wish every one has this same feeling and opportunity for the betterment of the generations to come.

I hope the future will get better as long as we are open to learn from mistakes in the past and present.

Anonymous said...

D. Epherm , thank you for your article , you didnt mention one thing in ethiopia , now days in ethiopia , due to ethnic division, you cant live or work in any part of ethiopia.

Anonymous said...

but it is headage for the Ethiopian gov't, we have seen the reality happening in SNNP BY Shiferaw Shegute

Anonymous said...

Ethiopiawinet kurate! tnx for sharing!

Anonymous said...

Demissie
Dear Anonymous,I think no need of mention this ONE thing right here.Because he mention that all Ethiopian have great culture interms of this "Abronet".He talking about Ethiopian people culture not some groups feeling or interest.I am 100% sure no one in Ethiopia like this ethnic division except some groups that get bebefits from this division.

Anonymous said...

What every country is poor, she is like our mom, we've to lover our country.

ablelom said...

i agree with the general idea though i have difference, i believe in single person freedom and then to group. but the key is to live and to have good ethiopia, we have to value human being, cancel racism, respect difference. Even though i am also from the conservators of old history but i have comments to be cleared so tha we can live in peace.