Saturday, May 4, 2013

ፋሲካ፦ “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”(ኤፍሬም እሸቴ - ኢትዮጵያዊ/ READ IN PDF) በኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ሁኔታ ከሚከበሩት በዓላት መካከል ትንሣኤ ወይም ፋሲካ አንዱና ዋነኛው ነው። ሃይማኖታዊ ትርጓሜው እና ምንነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ባህላዊ አከባበሩ እና ምንነቱም ከኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማንነት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ነው። እንኳን በአገር ቤት ያለው በሰው አገር ያለነውም እንኳን ብንሆን እንደ አቅሚቲ የአገር ቤቱን መንፈስ በያዘ ሁኔታ እናከብራለን። ስለዚህ ፋሲካው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ/ ባህላዊ አንድምታው ከፍ ያለ ነው ማለት ነው።

አለቃ ዘነብ የተባለው የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ፀሐፊ አንባቢውን እያዋዛ የመከረበትን “መጽሐፈ ጨዋታ” የተሰኘውን መጽሐፉን “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” (ሥጋዊ እና መንፈሳዊ) እንዳለው ስለ ፋሲካ ያለችኝን ወግ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ብዬ ብከፍላት ኋላ ለሚከተለው ሐሳብ ጥሩ ገላጭ ይሆናል። ዘነብ ኢትዮጵያዊ ሲል ራሱን እንደገለጸ ኩረጃዬን ሙሉ ለማድረግ ኤፍሬም ኢትዮጵያዊ ብያለሁ፣ ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ። ኢትዮጵያዊነታችንን ከፍ አድርገን በክብር ልናሳይ የሚገባበት ዘመንም ስለሆነ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንልኛል።

በጥንተ ታሪኩ ፋሲካ የሚጀምረው ከእስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት ታሪክ ታሪክ ጋር ተያይዞ ነው። ሕዝበ እስራኤል ለረዥም ዘመን በግብጽ አገር በባርነት ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በቤተ መንግሥቱ ያደገው ሙሴ መሪ ሆኗቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የጀመሩትን ጉዞ መሠረት ያደረገ በዓል ነው። ግብጻዊው ገዢ የሚያየውን ተአምራት ተቀብሎ ሕዝቡን ሊለቅ እና ነጻነታቸውን ሊመልስላቸው ባለመፍቀዱ ከተከሰተው ከባዱ ቅጣት ማለትም የግብጻውያኑ የበኩር ልጆች መቅሰፍታዊ ሞት ጋር ይገናኛል።

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ሞተ በኩር በመጣ ጊዜ ቀሳፊው መልአክ እስራኤላውያን ልጆችን እንዳይቀስፍ እነዚህ ተገዢዎች በየበሮቻቸው መቃን ላይ የበግ ደም ቀብተው፣ ያ መልአከ ሞትም ደሙ የተቀባበትን በር በማለፉና ግብጻውያንን  በመምታቱ በዓሉም ከማለፍ ጋር ተገናኘ እና ማለፍን፣ መሻገርንና መሸጋገርን የተመለከተ ሊሆን ቻለ። በዕብራይስጡ “ፓሳህ” ማለት ማለፍ ማለት ነውና። ሁለተኛው ማለትም የክርስቲያኖች ፋሲካ ወይንም ትንሣኤ ደግሞ ክርስቶስ እውነተኛው በግና መስዋዕት ሆኖ ሰዎችን ከጥፋት ወደ ድኅነት ያሻገረበትን ይመለከታል። ለምን ፋሲካ “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” እንዳልኩት ለመረዳት የቀድሞውን የእስራኤል ፋሲካ ከኋላው ከክርስቲያኖች ፋሲካ ጋር ማነጻጸር ነው።

በቀድሞው በእስራኤል ፋሲካም ሆነ በኋለኛው የክርስቲያኖች ፋሲካ፣ “ፋሲካ” አማናዊ ትርጉሙ ከባርነት ነጻ ከመውጣት (ከነጻነት) ጋር የተገናኘ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ነጻነት ያላት ሥፍራ ምን ያህል ክቡር መሆኑን ያስረዳናል። እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት፣ ከምድራዊ ገዢዎች አስከፊ ተገዢነት ነጻ እንደወጡት ሁሉ በክርስትናው ደግሞ ክርስቶስ የፋሲካው አማናዊ በግ ሆኖ በመሰዋቱ የሰው ልጆች ከሰይጣን ባርነት ነጻ እንደ ወጡ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ባርነት፦ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ።

ከፍ ብዬ በጠቀስዃቸው ታሪኮች ቅደም ተከተል ከሄድን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከሰይጣን ባርነት ነጻ ከማውጣቱ በፊት የሚቀድመው የሕዝበ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ መውጣት ነው። ከነፍስ ነጻ መውጣት የሥጋ ነጻ መውጣት ቀድሟል ማለት ነው። ነገር ግን የእስራኤልንም ነጻነት ቢሆን ጠልቀን ብንመለከተው ከምድራዊ ገዢዎቻቸው ነጻ ከመውጣታቸው አስቀድሞ የነፍስ ነጻነት ማለትም የኅሊና ነጻነት ማግኘታቸውን እንረዳለን፤ ነጻነታቸውን በተግባር ከማግኘታቸው አስቀድሞ ራሳቸው ለራሳቸው ነጻነትን ሰጥተዋል። ይህንን ነው የኅሊና ነጻነት ያልኩት።

ማንኛውም ሰው ነጻነትን ከማግኘቱ አስቀድሞ ነጻነት እንደሚያስፈልገው ማወቅ፣ ማመን እና ከማንም ሰጪ ወገን እንዲቸረው ሳይጠብቅ ነጻነትን ለራሱ በራሱ መስጠት/ ማጎናጸፍ እንዳለበት ይሰማኛል። ለራሱ ነጻነት ያልሰጠ ሰው ሰዎች ቢሰጡትም ለመቀበል አይችልም። ማንነቱ ነጻነትን ለማስተናገድ ይሳነዋል። ነገር ግን ነጻነትን ለራሱ የሰጠ ሰው ሰዎች “ነጻነትህን ወስደንብሃል” ቢሉት እንኳን ነጻነትን ለራሱ ሊከለክልና ባሪያ ሊሆን አይቻለውም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ።

ሰውየው ለረዥም ዘመን በእስር ቤት የኖረ ነው አሉ። የዕድሜውን ግማሽ በላይ ያህል በእስር ቤት በመኖሩ እያንዳንዱ ርምጃው በእስር ቤቱ ኃላፊዎች ፕሮግራም ሲቀረጽለት የኖረ። የሚበላበት፣ የሚጠጣበት፣ የሚተኛበት፣ ሰውነቱን የሚታጠብበት፣ ሥራ የሚሔድበትና የሚመለስበት ጊዜ የተሰፈረና የተቆጠረ። ለእርሱ የምግብም ሆነ የመኝታ ሰዓት የሚወስኑት ሌሎች ሰዎች/ እስር ቤቱ ጠባቂዎች ናቸው። ይህንን ኑሮ ለረዥም ዘመን የተለማመደ ሰው አንድ ቀን “ነጻ ነህ፤ ወደ ቤትህ ሒድ” ተባለና ከወኅኒው ተለቀቀ።

ነገር ግን ሰውየው እስረኝነትን እንጂ ነጻነትን፣ በሰው ሰዓት መኖርን እንጂ በራሱ ሰዓት መሔድን አልለመደምና ነጻነቱ ባርነት ሆነበት። እስር ቤቱን ናፈቀ። የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ የተቀጠረበት ቦታ ያሉ አለቆቹን ሽንት ቤት ለመሔድ ያስፈቅድ ጀመር። ጥያቄው ግር የሚላቸው አለቆቹ “ታዲያ ሽንት ቤት ብትሔድ ባትሔድ እኛ ምን ቸገረን? ከገለግኽ ሒድ፣ ካልፈለግህ ቅር” ይሉታል። እርሱ ግን ሳያስፈቅዱ፣ ሌሎች ቡራኬ ሳይቸሩት የሚደረግ ኑሮን አያውቀው ኖሮ ነጻነት ከመርግ ከበደው። ባርነትን የተሸከመ ጫንቃው ነጻነትን ለመኖር ከበደው። (በግብጽ የባርነት ኑሮ መኖርን እንጂ ከፈርኦኖች አገዛዝ ውጪ ያለች አገር አልታይህ አለው።) ለካስ ሥጋው ነጻ ይሁን እንጂ ኅሊናውና ነፍሱ ገና እስረኞች ናቸው። የነፍስ ነጻነት ሳይኖር የሥጋ ነጻነት አይኖርም ያልኩትን ለማስረገጥ ፈልጌ ነው።

የቀደመውን ፋሲካ ያከበሩት ሕዝበ እስራኤል በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ ብዙ ተአምራት ቢደረግላቸውም አዲሱን ነጻነት ለመቀበል ግን ሁሉም ዝግጁዎች አልነበሩም - ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን። የነጻነታቸውን ፈር ቀዳጅ ሙሴን አንዴም ሲቀበሉት ሌላም ጊዜ ሲያሙት፣ አንዴ ሲያጸድቁት ሌላ ጊዜም ሲያዋርዱት ሲወጡ ሲወርዱ እንመለከታለን። በነጻነት ከሚያገኙት መና ይልቅ በባርነት የሚሰጣቸውን የግብጽ ምግብ (ቅዱስ መጽሐፍ ዓሣ፥ ዱባ፥ በጢኽ፥ ኩራት፥ ቀይ ሽንኩርት፥ ነጭ ሽንኩርትይለዋል) ይናፍቁ ነበር (ኦሪት ዘኍልቍ 11፥5)። ችግሩ ግን ነጻነትን ያለማወቅ ዕዳ ነው።

በታሪኩ ቅደም ተከተል መሠረት ከሔድን እስራኤል 430 ዘመን በግብጽ ኖረዋል። ነጻነቱ በታወጀበት ወቅት የነበሩት በሙሉ በባርነት አገዛዝ ሥር የተወለዱ ናቸው ማለት ነው። የሚያውቁት ባርነትን እንጂ ነጻነትን አይደለም። ሙሴ ከእስራኤላውያን የተወለደ ነገር ግን በጉዲፈቻ በፈርዖኖቹ ቤት መስፍን ሆኖ ያደገ ነጻነትን ያወቀ ሰው በመሆኑ የወገኖቹ ባርነት በቅጡ ይቆጨው ነበር። ኅሊናውና ነፍሱ  ነጻ ነበሩ።

ሌላው እስራኤላዊ ግን የዚህ ተቃራኒ ነበር። “የማያውቁት አገር አይናፍቅም” እንዲባል ነጻነትን የማያውቅ ሰው ባርነቱ ለምን እንዳልከበደው መጠየቅ “ኤሊ በላይዋ ያለው ድንጋይ እንዴት አይከብዳትም?” እንደማለት ነው። የማያውቀው ነጻነት በየት በኩል ይናፍቀዋል? በሚያየው በዚያው ተወስኖ ከመ-እንስሳ ይኖራል፤ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ብቻ እያሰበ። ሙሴ ግን ከፈርዖኖቹ ቤተ መንግሥት ይልቅ ከወገኖቹ ጋር ያለውን መረጠ፣ ነጻነቱን ብቻውን ላለመኖር፣ የነጻነትን አየር ብቻውን ላለመተንፈስ የድሎት ሕይወቱን ለወገኖቹ ነጻነት ለመለወጥ እና የፋሲካው ምክንያት ለመሆን አላንገራገረም። የነጻነትን ጣዕም ለማካፈል ጓጉቷልና።

የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ ነጻነቱ ነው። የማንም እጅ እየገባ የማይበጠብጠው ድንበሩ ነጻነቱ ነው። ነጻነቱ የተገፈፈ ሰው ምን ሀብት ቢኖረው ሰብዓዊ ማንነቱ ጎዶሎ ነው። ኅሊናውና ነፍሱ በማይታይ ሰንሰለት እግር ተወርች ታስረዋል ማለት ነው።

ጀርመን አገር በነበርኩበት ወቅት ይገርመኝ የነበረ አንድ ታሪክ ላካፍል። በአገሪቱ ሕግ መሠረት ጥገኝነት የሚጠይቁ ወይም ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጪ አገር ሰዎች በሙሉ ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር እንዲኖሩ ከተመደቡበት ከተማ እና አካባቢ ተነሥተው እንደፈቀዱ ወደ ሌሎች ከተሞች መጓዝ አይችሉም። ለምሳሌ ጥገኝነት ጠያቂው ሙኒክ አካባቢ እንዲኖር ከተመደበ በራሱ ጊዜ ተነሥቶ ወደ በርሊን ወይም ፍራንክፈርት መሔድ አይችልም። እንደዚያ ቢያደርግ እና መንገድ ላይ መታወቂያ የሚጠይቁት ፖሊሶች ቢያገኙት ቅጣቱ ከባድ ነው። በትምህርት ምክንያት የሚሄዱ እኔን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን በቀለማችን ምክንያት በየመንገዱ ፖሊስ ስንት ጊዜ መታወቂያ ይጠይቀን እንደነበር ሳስታውስ ይገርመኛል። ፖሊስ በየመንገዱ መታወቂያ የማይጠይቀው እኖርበት በነበረው በበርሊን ከተማ ያለው ብቻ ሳይሆን አይቀርም። በተለይ ሙኒክ “ጥቁር ሰው ለምን አይቼ” የምትል ትመስላለች። በየኮርነሩ በፖሊስ መታወቂያ መጠየቅ የተለመደ ነው። አናዳጆች።

ያንን አይቼ አሜሪካ ስገባ የገጠመኝ የዚያ ተቃራኒ ሆኖ ጠበቀኝ። ማንም ዞሮ የሚያየኝ የለም፣ “ከየት አገር መጣህ?” የሚል የለም። ሁሉም በነጻነት ይሄዳል። ጥገኝነት ጠያቂ ሆነ ሳይንቲስት ማንም መንገድ ላይ አያስቆመውም። ወንጀል እስካልሠራ ድረስ። ፖሊስ ሰውየውን ለማስቆም ምክንያት የሚያገኘው ከወንጀል ጋር በተገናኘ የሚያስጠረጥር ነገር ሲኖር ሆኖ አገኙት። ወደድኩት። ነጻነት እንዴት ደስ ይላል። ከእኔ የበለጠ ደግሞ ሌሎች ባዕዳን አገሮች ረግጠው፣ ትንሽ ኩርኩም ቀምሰው የመጡ ኢትዮጵያውያን በነጻ መኖር ማለት ያለውን ትልቅ ትርጉም እያነሱ ሲናገሩ ሰማኹና አሜሪካንን አመሰገንኩ። ታዲያ ነጻነት መታወቂያ ካለመጠየቅ/ ከመጠየቅ ጋር ብቻ እንደይያያዝብኝ። ምሳሌ ዘይሐጽጽ እንዲሉ አበው … ምሳሌ መግለጽ የፈለገውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ ጉልበት ያንሰዋል ሆኖ ነው።

ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት በነጻነት የኖርን መሆናችን እሙን ቢሆንም ነጻነትን በቅጡ እናውቀዋለን፣ ወይም ነጻነትን በቅጡ ኖረነዋል ለማለት ይከብደኛል። ነጻነትን የማናውቅ ነጻ ሕዝቦች ማለት እኛ ነን። ዛሬም ድምጻችንን ከፍ አድርገን ለመናገር የምንፈራቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ሁለት ሦስቴ ዞር-ዞር ብለን ተገላምጠን፣ ድምጻችንን ዝ……ቅ አድርገን የምናወራቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ለራሱ ነጻነት ሰጥቶ የሚያስበውን ፊት ለፊት የሚናገር ቢገኝ እንኳን “ዕብድና ሰካራም የፈለገውን ይናገራል” ብለን ሰውየውን እንዲሰክር አሊያም እንዲያብድ እናበረታታዋለን። ወይም በደፈናው “ጉዱ ካሳ” አድርገን ከባርነት ነጻ ወጥቶ በብቸነት ቀንበር ተረፈ-ዘመኑን እንዲገፋ እናደርገዋለን። ጸጋዬ ገ/መድኅን - ነፍሱን ይማረውና - “ሕብረት ፈራን፣ ፍቅር ፈራን” አለ እንጂ እኛስ የፈራነው “ነጻነትን” ነው። “ነጻነት ፈራን” ተብሎ ይስተካከልልኝ።  

ፋሲካ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ማለት ይኸው ይመስለኛል። እኛስ ብዙ ፋሲካ አያስፈልገንም? አንዱ ያንሰናል። ፋሲካዎች፣ ሙሴዎች ያስፈልጉናል። ሙሴውም ቢመጣ ግን ለራሳችን ነጻነት ሳናውጅ ከቆየነው ትርጉም አይኖረውምና በነጻነት መኖርን እንለማመድ። የፋሲካው ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ትርጉም ይረዳን። ለራሳችን ሕይወት ራሳችን ወሳኝ የምንሆንበት፣ ድምጻችንን ዝቅ አድርገን በመሳቀቅ የማናወራበት ድኅረ-ፋሲካ ይኖረን ዘንድ። ይሁን ይሁን፣ ይደረግ ይደረግ እንዲል መጽሐፍ።          


 

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

 

 

 

12 comments:

Anonymous said...

ቃለ ሕይወት ያሰማለን እንዴት ነው ባክህ በዚህ ሰሞን እንደዚህ የዕውቀት ብርሃን ፍንትው ብሎ እየተቀጣጠለ ያለው። ጸጋውን ያብዛልህ።

Anonymous said...

"ነጻነትን የማናውቅ ነጻ ሕዝቦች ማለት እኛ ነን።" Dn. Epherem well said and interesting !!! Yibel yibel endil!!!!

Eshetu Haile said...

Kale hiwotin yasemalin wondim Ephrem. Betam konjo new birtatun yistih.

Anonymous said...

እኛስ ብዙ ፋሲካ አያስፈልገንም? አንዱ ያንሰናል።

Anonymous said...

That is really true. I believe that there in no freedom of speech in Ethiopia. We need freedom of speech! Freedom ..............Thank you Dn Efrem Ewedihalehu. God Bless Ethiopia and Ethiopians!

ጥቁር ሰው said...

Great insight! ነፃነት የሌለን ነፃ ባሮች ማለት እኛ ነን if there is such thing at all

Anonymous said...

Tsihufu tiru new. Neger gin Ethiopia wust minim netsanet endelele adrigeh silakerebkew, yeteganene meselegn. Mikiniyatum tinish ye Netsanet chilanchil yitayalina. Lemisale Yegil gazeta ende "Fitih" ayinet yemeselachewun yawim tekilay ministiruna amakariwochachew bedemb eyetechu yitsifalu. Endihum kezih befit be Atse Hailesilasse ena Be derg Yalineber ke 70 belay yetekawami party endefelegu mengistu yitechalu. Ena Ende America ayinet Netsanet endinoren bizu yemikeren bihonim, tinish yalechiwun netsanet eyadenikin mengist yebelete endiyashashil binigefafa tiru yimeslegnal. Betely ende ante yebetekiristiyan lij yehone ende chifin tekewamiwoch yalewun tinish lewti minim ende lele adrigo makireb, tirfu tizibt lay new yemitilih ena Le ewunet bitikom tiru yimeslegnal. Antem tinish netsanet silale yimeslegnal yihinin tsihufuh be Adis Guday metsihet yawetahew yimeslegnal.

galela said...

sela netsanate asebalaho gene edemaya yaterale beya efaralaho
tabarake

Anonymous said...

ቃለ ህይወት ያሰማልን ረጅም እድሜ ይስጥልኝ

Teklu Abate said...

ይሄን ጽሁፍ በሸገር ራዲዮ ሲነበብ ስሰማው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር ከዚያም ጽሁፍን ለማግኘት ተመኘሁ ወደአደባባይም ወጣሁ ተሳካልኝም

ምስጋና ለኤፍሬም

Anonymous said...

kale hiwoet yasemalin enameseginalen

Anonymous said...

kalehiwet yasemalin amen