Tuesday, May 8, 2012

አፍንጫ ሲመታ ዓይን የማያለቅስበት ዘመን


(ወልደ ኤስድሮስ ዘልደታ/ PDF)
ተረቱ እንዲህ ነበር “አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል።” ይህ ተፈጥሮአዊ ነው። ሁለቱ የሰውነት ክፍሎቻችን ባላቸው ተፈጥሮአዊ ትስስር ምክንያት የአንዱ ስቃይ ለሌላውም ህመም ነውና አፍንጫ ላይ የወደቀው ዱላ ዓይንን የብሶቱን ልክ በእንባ እንዲገልጥ ግድ ይለዋል። በቃ ትስስራቸው ጥልቅና ጥብቅ ነው። እንኳን ይቅርና የሁለቱ ዓይኖቻችን አካፋይ ድንበር ሁኖ የተቀመጠው የቅርብ ጎረቤት የሆነው አፍንጫ ተመትቶ ዱላው በየትኛውም የሰውነታችን ክፍል ቢያርፍም ዓይን ሆዬ የተጎዳ ጓደኛውን የስቅይ ጩኸት አብሮ መጮሁ አይቀርም- በእንባው።

ይህ ዘመን ግን ይህን የተፈጥሮአዊ እውነት እንድንጠራጠር እያደረገን ነው። እንደኔ እንደኔ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት እንዲሁም በምዕመናኑ መካከል ያለው ትስስር ከአፍንጫና ዓይን ተፈጥሮአዊ መስተጋብር አይለይም። እንዲያውም ከዚያ በላይ ያስተሳሰራቸውና አንድ ያደረጋቸው መንፈሳዊ ኃይል ድርብ ነው። በቀላሉ የማይላላ በጭራሽ የማይበጠስ ነበርና። አሁን ግን የትስስሩ ሐር፣ በሁለት ሺ ዓመት ጉዞ የታነፀው መንፈሳዊ ህብረት ቤተ ክርስቲያንዋ በታነጸችበት የማይናወፅ አለት ላይ የተገነባ፣ ዘመን አመጣሽ ፈተና የማያናውጠው፣ ጊዜ ያነሣው ማዕበል የማያውከው መሆኑን የሚያስተማምንልን ኃይል እያስፈለገን ነው። የአፍንጫ መመታት ዓይንን ሊያስለቅሰው አልቻለምና። አረ ከዚያም አልፈን ዓይን ራሱ እየተመታ ሕማሙን በእንባ ለመተንፈስ የሚያስችል መንፈሳዊ ድፍረትና የሞራል ልዕልና ያጣበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ይህ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚጠበቅ ሥጋን እንጂ ነፍስን መግደል የማይቻላቸውን ምድራዊ ኃይላት ተግዳሮት የማይፈራ መንፈሳዊ ልዕልና ያጣ አባት ቤተ ክርስቲያንዋን የሚመራበት ዘመንን ላለማየት ይሆን እንዴ የጥንቱ የቤተ ክርስቲያንዋ አባቶች ስምንተኛውን ሺ አታሳየን እያሉ የጸለዩት? አዎ ጸሎታቸው ይህን የዓይንና አፍንጫ ተፈጥሮአዊ ጋብቻ ሲፈርስ ላለማየት ነበር። አዎ! ልመናቸው የቤተ ክርስቲያንዋ ልዩ ልዩ የአካል ብልቶች ተለያይተው የጥንታዊው ዋልድባ ገዳም ሲደፈርና የማይተካው ገዳማዊ እሴቱ ዳግም ወደማያንሰራራበት ጥልቅ ሲወረወር የወርዋሪዎችን ነውር የሚያበረታታ ሳውንድ ትራክ ሰርተው እጅ መንሻ የሚያቀርቡ የክርስቶስን መስቀል በእጃቸው እንጂ በልባቸው ያልተሸከሙ “አባቶችን” ላለማየት ነበር። ሌላው ቀርቶ የዕለት ጉሮሮአቸውን የሚደፍኑበትን የዕለት እንጀራቸውን ከቤተ ክርስቲያንዋ መዓድ በሚቆርሱበት እጃቸው  በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ የንቀት ቡጢ ለሰነዘረ አካል የሚያጨበጭቡ ውለታ ቢሶች  በበረቱ ያለውን መንጋ እያወኩት ነው። ታዲያ የተሳሰርንበትን መንፈሳዊ ሐር ባርከው የሚያደረጁበት መስቀል ይዘው በመካከላችን ቁመዋል ብለን የተመካንባቸው “አባቶች” ያስተሳሰረንን ድር የሚበጥሱበት መቀስ ይዘው በበረቱ መካከል ሲገኙ ልባችን እንዴት አይታወክ? ለካ የአፍንጫ ህማም ለዓይን ያልደረሰው ድልድዩን የሚያፈርሱ ፍልፈሎች እንደ አሸዋ በርክተው ምድርን ሞልተዋት ነው። “ ጌታ ሆይ  ከወዳጆቼ ጠብቀኝ ከጠላቶቼ ራሴን እጠብቃለሁ” ያለውን ጸሎተኛ ምሬት በትክክል የተረዳሁት አሁን ነው። የኛ ያልናቸው፣ የኛ በሆነው በቤት ቀለብ የሚሰፈርላቸው፣ የሰበቁብን ዘገር ከተፈታታኛችን ጥቃት ይልቅ እየጎዳን ነው።
    ልማት በኢትዮጵያችን ሁኖ ማየት ለማንኛውም ዜጋ ልብን በሐሴት የሚያጥለቀልቅ ብስራት ነው። ልማቱ ግን ለዘመናት ያለማነውን መንፈሳዊ እሴት  አጥፍቶና ወደ መቃብር አውርዶ የሚበቅል ከሆነ ልማት መሆኑን ለማመን ብቻ ስንት ክፍለ ዘመን እንደሚያስፈልገኝ አንድዬ ይወቅ። ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ቢኖርም እንኳ የሕይወትን ተፈጥሮአዊ ጣዕም ለማጣጣም እንደማይታደል የሰለጠኑት ሐገራት ሕዝቦች በቁሳቁስ የታጨቀ ግን እንደ በረዶ የቀዘቀዘ፣ እንጨት እንጨት የሚል አኗኗር እያሳየን ነው። እንዲህ እኛ አሁን እንዳለንበት አይነት በልማት ከፍና ዝቅ መካከል ባለፉበት ወቅት ያልተጠነቀቁላቸውና ከእጃቸው ሲሾልክ ያልታወቋቸው በርካታ እሴቶቻቸውን ዛሬ የእውነተኛው ሕይወት ማጣፈጫ እንዲሆናቸው ፈልገውት ከወደቀበት ጥልቅ ቆፍሮ ማውጣት ከባድ ፈተና ሁኖባቸዋል። ያኔ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ዛሬ ቁመው ማውረድ አቅቶአቸው ተቸግረዋል። እኛም ከእነርሱ የምንቀዳው የእድገት ልምድ የመጀመሪያውን ሳይሆን ከተፀፀቱ በኋላ ያለውን ቢሆን የሥጦታቸው እንጂ የጉዳታቸው ተጋሪ እዳንሆን ይረዳናል።
ያስተሳሰረን መንፈሳዊ ድር ተበጥሷል። ባይበጠስማ ሥለ ሐገራቸው ስለ ኢትዮጵያ ስለ ህዝቦቿም ሰላም፣ ስለ ሃይማኖታቸው ተዋህዶ መጠበቅ ብሎም ስለ ዓለም ሕዝብ ደህንነት ያለ እንቅልፍ በትጋት፣ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው የሚጸልዩት ደጋግ አባቶች ላይ እየሆነ ያለውን ግፍ ማየት ባልተሳነን ነበር። መንፈሳዊ የአኗኗር ዘይቤአቸው ከዘሪማ ወንዝ ጋር ተጠራርጎ እንዲጠፋ ሲፈረድበት ብቸኛው ኃይላቸው የሆነውን እግዚአብሔርን ጠረተው ለጮኹትን ጩኸት የማርያም ብቅል እንደምትፈጭ በወፍጮ ዳር እንደተንበረከከች ሴት ልሳናችንን መለጎም ባልተገባን ነበር። በዚህ ታላቅ ገዳም ላይ እየሆነ ያለው ነገር የኛንም ልብ እንዳቆሰለው ለማሳየት ባልተቸገርን ነበር። በዓይኖቻቸን እንባ ምሬታችንን በረጨን ነበር። ይህን ግን አላየንም። አሁን ዘመኑ እንባችንን ወደ ውስጥ አፍስሰን ዝም የምንልበት ጊዜ እይደለም። በፊታችን ላይ ኮለል ብለው የሚወርዱበትና ብሶታችንን ለዓለም ሊያወሩ፣ ለህዝቡም ሊናገሩ የሚገባበት ጊዜ ነው እንጂ። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተወረወረ ያለው ወንጭፍ እንደከዚህ በፊቱ ድንጋዩ በላያችን እያፏጨ የሚያልፍ፣ አስደንግጦን የሚያከትም አይመስልም። ከሰው አዝመራ ዘው ብላ እንደተገኘች ወፍ ሲቻለው ግንባራችንን ብሎ ሊገላግለን ጨክኗል እንጂ።
ቤተ ክርስቲያንዋ ዋልድባ ገዳም ማለት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ለሕዝቡ አላስረደችም። አብዛኞቻችን ሥለ አብርንታት ዋልድባ ገዳም ”አንዳንዴ በዋልድባም ይዘፈናል” ከሚለው አባባል የዘለለ ላናውቅ እንችላለን። የዚህ ታሪካዊና በቅድስና የተሞላ ገዳም የማያልቅ መንፈሳዊ እሴት በቀላሉ መግለጽ እንደማይቻል መናገር እወዳለሁ። መጻህፍት ቅድስናውን ሊያወሩለት ይሞክራሉ። የተቀረፀ ተንቀሳቃሽ ምስልም ሊዘክረው ይችላል። እነዚህ ግን በፍፁም ልድገመውና በፍፁም ገዳሙን  በእርግጥ “ታላቅ” ያሰኙትን እሴቶች በእኩል መጠን ሊያስረዱን አይቻላቸውም። ያለማጓደል የቅድስናውን ልክ ሊያሳዩን እይቻላቸውም። እንኳን ምስል ለመቅረፅ ካሜራ ለደገነ ሙያተኛ ይቅርና ለሱባኤ በጊዜ ገደብ የማሕበረ መነኮሳቱ አባል ለሆነው አማኝ እንኳ በቀላሉ የማይገለፅ ነው-የመነኮሳቱ መንፈሳዊ አኗኗር። ውዳሴ ከንቱን ሸሽቶ፣ ከሰው ህሊና ፈልቆ ከሰው አንደበት የሚቀዳውን  በምድር የሚቀር ውዳሴ የተፀየፈች ነፍስ ያለቻቸው እንጦሳዊያንን መንፈሳዊ ተጋድሎ የወረቀትና የብዕር ጥምረት እንዴት ያለማጓደል ሊተርክልን ይችላል? አይቻለውም።
ሥለ ጠፋው ዓለም፣  ሥለ ሐገር ደህንነትና አንድነት፣ ሥለ ሕዝቡ ቸር ውሎ ቸር ማደር ያለመታከት የሚጋደሉትን ባሕታዊያን ጸጋ፣ ተጋድሏቸውም ለገዳሙና ለአርማደጋ በርሃ የሰጡትን ግርማ የተፃፉ መረጃዎች በዝግጅት የተቀረፁ  ምስሎች ሊገልፁት አይሆንላቸውም። በአካል ተገኝቶ በዓይን ከማየት የሚመጣ የስሜት ትስስር ግን ይህ ይቻለዋል።
የተፈለፈሉ ዛፎች በህይወት ሳሉ የተጋድሎ ባእታቸው በእረፍተ ሥጋቸው ደግሞ መቃብራቸው የመሆኑን ነገር የትኞቹ ቃላት ሊያስረዱልን ይችላሉ? ዛሬ የጉልበኞቹ ዶዘሮች እየገነዳደሷቸው ያሉት እድሜ ጠገብ ዛፎች በየጫካው ከምናውቃቸው ዛፎች በእጅጉ የተለዩ የትናንት የመናንያን ባዕቶች የዛሬ መቃብሮቻቸው መሆናቸውን እንዴት ተደርጎ በወረቀት ላይ መልዕክት ማስረዳት ይሆንልናል? እግር ጥሎዎት በገዳሙ ክልል ቢገኙ ለተለያዩ አገልግሎቶች በየጫካው የሚኳትኑት አርድእት ያገኛሉ። አርድእት ማለት በገዳማት የሚገኙ በምንኩስና ያሉ ወይም በአሞክሮ ለምንኩስና የሚያበቃ ፅናት እንዳላቸው ራሳቸውን የሚፈትሹበት የመሸጋገሪያ ዘመን ላይ የሚገኙና በመላላክ የሚያገለግሉ ባብዛኛው በወጣትነት እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሲሆኑ ረድዕ ማለት ደግሞ ነጠላ ቁጥሩ ነው። እነዚህ አርድዕት ዛፎቹን ባዩ ቁጥር ከጉልበታቸው በርከክ ከወገባቸው ሸብረክ እያሉ የትህትና ሰላምታ ሲያቀርቡና ግልፅ ሁኖ በማይሰማ ቋንቋ ሲያውሩ የመስማት ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ። ያኔ ብቻውን የሚጓዘው ረድዕ ሁኔታ እንግዳ ሊሆንብዎት ወይም አንዳች ነገር የለከፈው ሊመስልዎት ይችላል። እርሱ ግን በዙሪያው ከሰፈሩት የአበው ቅዱሳት መናፍስት ጋር ሰማያዊ ወግ እያወጋ ነው። በዙሪያቸው እንደረበቡ ያውቁታልና የከበረ ሰላምታ ያሰማሉ። እነርሱም ወደዚህ ማዕረግ የሚያደርሳቸውን መንፈሳዊ ብርታት እንዲያገኙ የአበውን ረድኤት ይማፀናሉ። ታዲያ ይህን እንግዳ ቃለምልልስ የትኛው ፅሑፍ ነው ከነላህዩ ይገልፅልን ዘንድ የሚሆነለት?
የአንደበት እሳትነት የመንፈስ ወንድምን፣ የመንፈስ ልጆችን  ልብ መቼና እንዴት ሊያሳዝን እንደሚችል አናውቅምና በሚል ስጋት፣ ነገ ምናልባትም ከቀናቱ በአንዱ ወንድሞቻቸውን በጥቂቱም የሚያሰከፋ የንግግር ቃል እንዳይወጣቸው በመስጋት ለአንደበታቸው ዘላለማዊ አርምሞ የሰጡ በርካታ አፍላጦናዊያን የሚገኙበት የተባሕትዎ ሥፍራ ነው ዋልድባ። አዎ እጅና እግር የአንደበትን ሥፍራ ተክተው የሚናገሩበት የምነና ምድር ነው ዋልድባ። ራሱ ሕያው ምስክር የሆነ የመስኖ ጥበብ የጠብታ ውሃ ዓይነት ቴክኖሎጂ የሚታይበት የተግባር ቤት ነው ዋልድባ። በጥንታዊያኑ መጻሕፍት ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው፣ ግርማ ሌሊቱን ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው ስለኖሩ ቅዱሳን ጻድቃን የሚተረከው ገድል በዚህ በ 21ኛው ከፍለ ዘመን የሚፈጸምበት የቅድስና ሥፍራ ነወ ዋልድባ ገዳም። በዚህ ዘመን ለተመሳሳይ ተጋድሎ የጌታን መስቀል በጽድቅ የተሸከሙ በርካታ የእውነት ምስክሮች የፈሰሱበት የክርስትና አዝመራ ነው ዋልድባ ገዳም። 
ነፍሳቸውን ይማርልንና በቅርቡ በእረፍተ ሞት የተለዩን ሞታቸውም ዓለምን ሁሉ ያስደነገጠው የወንጌል መምህር የኮፕቲኩ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ፫ኛ በአንድ ወቅት በአሁኑ ሰዓት በግብፅ ምድር ስላለው የምንኩስና ሕይወት ተጠይቀው ሲመልሱ “የምነና ሕይወት እኛ ዘንድ ቢጀመርም በአሁኑ ጊዜ የ21ኛው መ/ክ/ዘመን የጥንቱ የጥዋቱ የምንኩስና ሕይወት ከነነፍሱና ከነሙሉ መዓዛው ልታገኙት ከፈለጋችሁ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ” ማለታቸውን ሰምተን ስምዓ ጽድቅነታቸውን አድንቀናል። በእርግጥም የጥንቱን አርምሞና እንጦሳዊ ተጋድሎ፣ ጳኩሚሳዊው ተባትሖና(ብህትውና) መንፈሳዊ ተፋላሚነት የ21ኛው ከ/ዘመን ሉላዊነትን ተቋቁሞ፣ የሦሥተኛው ሺህ ዓለማዊ ክለሳ ሳይደርስበት ከነ ትውፊቱ ይህች ሐገረ-እግዚአብሔር ጠብቃ ይዛዋለች። አቡነ ሺኖዳ የተናገሩለት ይህ የክርስትና ፍሬ በእጅጉ ከሚታፈስበት የተጋድሎ ምድር  መካከል ደግሞ የዋልድባንና የማሕበረ ሥላሴን ገዳማት ያህል ማግኘት ከባድ ነው። ይህ የዓለም ቅርስ የሆነው የምንኩስና ትውፊት ባለአደራ የሆነው ዋልድባ ግን  እንደሰማነው ዛሬ አደጋ ላይ ነው። ይኼን ገዳም ከጉዳት መጠበቅ ማለት ያልተበረዘውንና የቀደመውን ክርስትና ከ21ኛው መ/ክ/ዘመን መንፈሳዊ ዝቅጠት መታደግ ማለት ነው።
የማሕበረ-ሥላሴ፣ የጎንድ ተ/ሃይማኖት፣ የጣና ገዳማት፣ የደብረ-ቢዘን (የመንፈስ አንድነቱ አይበጠስምና)፣ የሐይቅ እስጢፋኖስ፣ የአቡነ አሮን፣ የደብረ ዳሞ የጉንዳጉንዲ፣ የአሰቦት፣ የደብረ ሊባኖስና በየገዳማቱ ያሉት መነኮሳትና በየበርሐው ጉያ ያሉ ባሕታዊያን፤ አገልግሎቱ ሰርክ የማይታጎልባት የአክሱም ጽዮንና የሮሃው የላሊበላ አብያተ መቃድስ ቀሳውስት ከዋልድባ ጋር ያላቸውን ከአፍንጫና ከዓይን ዝምድና የጠበቅ ትስስር ሊረሱት አይቻላቸውምና ይህ ተግዳሮት እንባቸውን ወደ ሰማይ እስኪፈነጥቁ ድረስ እንደሚያስለቅሳቸው፣ ልብ የሚሰብር ዜና እንደሚሆንባቸው አልጠራጠርም። ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስ መንበረ ጸባኦትን የሚያንኳኳ እንባ እያፈሰሱ እንደሆነ ከማመን ለአፍታም ቢሆን አልሸሽም። እኛ ግን ይህ ሀገራዊ እሴት ፈርሶ በፍርስራሹ ላይ የሚገነባው፣ በሕያው ማንነታችን ጀርባ ላይ የሚታነፀው ፋብሪካ ይዞት የሚመጣው የሥራ እድል አጓጉቶን ወይም ጉልበተኛን ፈርተን እንደተቆጡት ሕፃን አፋችንን በእጃችን ይዘናል። አፍንጫው የተመታበት እንባውን ለማፍሰስ የማንንም ፈቃድ አይጠይቅም። ዝም ብሎ ያወርዳዋል እንጂ።
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እምነት የለሹን የደርግን መንግስት ገርስሶ ወደ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት እንደገባ የእምነት ነፃነትን ሲያውጅ እንደገና ያለፍርሃት እግዚአብሔርን የምናመልክበት ዘመን መጣልን ብለን እልል ብለን ነበር። ቤተ ክርስቲያናትን ሙዚየም አደርጋለሁ የሚለው ኮሚኒስታዊ ጩኸት መከነልን ብሎ ሕዝቡ እፎይታ ተሰምቶት ነበር። ደርጉ ከቤተ ክርስቲያን ነጥቆ የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካል እንዲሆን አድርጎት የነበረውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቤተ ክርስቲያናችን እንደገና ተረክባ እንድትከፍት ሲፈቀድላት የትንሣኤ ዘመን ሆነ ብለን አስበን ነበር። በነካ እጁ በእጁ ያሉትን ሃብቶቿን ይመልሳል የበለጠ ደስታም ይሆንልናል ብለን እየጠበቅን ባለንበት ዘመን ይኸው የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤት የሆነውን፣ ቅድስናውን ጠብቆ የኖረውን ገዳም መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ዋጋ ሊመነዘር በማይችልበት በሥጋ ገበያ መዝኖ ዋጋው ከአንድ የስኳር ፋብሪካ ሊበልጥ አይችልም አለን። ምነው ሃይማኖት የለሽነትን የሚሰብከውን ኮሚኒስታዊ ፍልስፍና ያስተማሯቸው የግብር አባቶቻቸው ሩሳዊያኑ ወደ ልባቸው ተመልሰው የትናንት ስህተታቸውን ለማረም ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ዘመን የኛዎቹ ልባቸውን እልከኛ አደረጉት? የሩሲያ መከላከያ ሚኒስተር በቅርቡ የሾማቸውን 21 የሃይማኖት ጉዳይ አስፈፃሚዎችን (የንስሐ አባቶችን) ጨምሮ ከሁለት መቶ በላይ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት በጦር ሰራዊቱ ውስጥ አገልግሎት ላይ መሆናቸውን ልብ ይሏል። 
የዋልድባ ገዳም ወላድ ማሕፀን ነው። እንደ ሌሎቹ የሃገራችን ገዳማት የቤተ ክርስቲያንዋን የትናንት፣ የዛሬና የነገ አገልጋዮች የሆኑትን መምህራን፣ቆሞሳትንና ጳጳሳትን ያፈራ መክኖ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያንዋ ልጆች መብቀያ ማሳ ነው ዋልድባ። ታዲያ ሥላሴ ኮሌጅን መልሶ ኮሌጁን የነገረ መለኮት ማዕከል ልያደርጉ የሚችሉት መምህራንና መነኮሳት የሚፈልቁበትን መልካም ምንጭ ማድረቅ ምን ይባላል? ነገ ቤተ ክርስቲያንዋን ወደ መንፈሳዊ ከፍታ የሚያወጡትን፣ ከመሪዎቿ ሲጎድል እያየነው አንገታችንን የደፋንበትን መንፈሳዊ ልዕልና የሚመልሱ የእውነት ጳጳሳትን የሚያፈራን ማሳ መረምረም ምን የሚሉት ልማት ነው? በአንድ ወቅት ካደገበት ውሃ ከተራጨበትና ጭካ ካቦካበት የአራት ኪሎው ባሻ ወልዴ ሰፈር “በመልሶ ማልማት” ትግበራ የተፈናቀለ አንድ ብሶተኛ ፀሐፊ የእርሱንና ያሳደገውን ማሕበረሰብ ሲገልፅ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “እኛ ከልማቱ ከምንጠብቀው ይልቅ ልማቱ ከኛ የሚፈልገው ለሕይወታችን አደገኛ እየሆነ መጥቷል”። ያኔ የዓይንን ሚና ከመጫወት ሰነፍኩ ዛሬ እኔው ራሴ የአፍንጫ ዕጣ ደርሷኛል። እኔ ብቻም አይደለሁም  በትንሹ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ አብራክ ያፈራችው ሕዝብ እንጂ። አዎ !! አፍንጫ እየተመታ ነው ዓይን ግን እያለቀሰ አይደለም።  
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


29 comments:

Anonymous said...

ejeg betam leb yemeneka new.enba begunche eyewered new yanabebkut.

Anonymous said...

ejeg betam lib yemeneka tsehuf new.eyalekesku new yanebebekut.amlak bete kirstiananchenene yetebek.yehen yemesele tiru neger selasnebebeken enamesegnalen.

yemelaku bariya said...

አንባቢ ካለማ ተጽፏል!

Anonymous said...

Ye Rahelin Enba yetemeleke Amlak ye abatochachin enba yabisilin.

Anonymous said...

ende berdow ye kezekezewn lebachenen egzeabehere yefewselene.ye abtochanene menfes ersu yemelselen.amen.

Anonymous said...

lemalikes metadelin yifeligal yezih zemen tiwulid yatanew gin yihenin newu

Anonymous said...

ኣባቶቻችን ኣትሳደብ
ስለ ገዳሙ ብለህ ከልብህ ከጻፍከው መልካም ነው
ነገር ግን ኣይመስለኝም

Anonymous said...

እያለቀስኩ አነበብኩት፡፡ እናም ባዶነት ተሰማኝ፡፡

Its me said...

What the reality is expressed here but still w turned our deaf ears and blind eyes for this fact. May God come to us in his aid

Kinfe Michael said...

That is very true, my brother. Tears are powerful. Tears clean our sins, heal our souls and make our prayers heard. Tears bring God's mercy upon His people and take His wrath away. Tears are weapons of Christians against the odds of times. Every sad thing that is currently happening around our Church reminds us that we are far from God. We need to look into our hearts and ask if we really are in God's path. My fellow Ethiopian Orthodox Christians, the key to the solution for our problems is in our hands. The first step is to kneel before God and weep. Let's cry and promise God that we will live by the teachings of our Church and never return to our sins. Once we have done this, God will hear our prayers, bless our efforts to protect our Church and delivers us from the current waves of war against our religion. It is our move, friends. It is our turn, not God's this time. Let us move the game in the right direction before it is too late. Let's move our heart. God is waiting for us!!

Anonymous said...

ኤፍሬሜ እንኳን ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም የልደት በዓል አደረሰህ። መልካም ብለሃል። መቼም በእግዚአብሔር ተስፋ ተቆርጦ የት ይገባል እንጂ፤ በእውነቱ የቤተ ክርስቲያናችን ነገር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው።
" ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፤
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ ።"

የሚለው ተረት በእኛ ዘመን እየደረሰብን ነው።
እስኪ መልካሙን ያሰማን። መልካም ከተገኝ

Tade Tekle said...

ሁላችንም በየተሰማራንበት የአገልግሎት ሞያ ምን መሥራት እንዳለብን እናስተውል ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ልብ ይስጠን፡፡

lele said...

kale heiwot yasamalen.
tekekele................................

Anonymous said...

Egziabher Yibarkih . It is a clear message and true situation. I think it is a very hard case. Out of man Power. Let us PRAY.... God knows everything! Thanks a lot Efrem

Abel said...

ውድ ወንድሜ፤
የአእምሮ ጓዳችን እንድንፈትሽ ለሚያደርገው መጣጥፍህ በጣም አመሰግናለሁ። ለምን ለከት የሌለው የሞራል ዝግጠት ውስጥ እንደገባን መልስ ማግኘት አልቻልሁም። አምላክ የለሾች ምዕራባውያን እንኳ በአሁኑ ከእንዲህ አይነት ድርጊቶች ተቆጥበዋል። ለሆድ ማደር መቼ ይሆን የሚያበቃው? መስቀል ጨብጦ ውሸትን መደስኮር ክርስቶስን ከመስቀል አይተናነስም። አውደ ምህረቷ ላይ ቆሞ መቀለድ፤ ክርስቶስን ከመሸጥ አይተናነስም። አንዳንድ ጊዜ የማይገቡኝ ነገሮች አሉ። አለም ከአጓጓቻቸው፤ ለምን ክርስቶስንና ቤቱን ጥለው እንደ ዴማስ ወደ አለም አይኮበልሉም? ለምን ማፈራረስ ፈለጉ? ተባባሪ መሆናቸው ምን መንፈሳዊ ጥቀም ይፈይድላቸዋል? ቢያንስ ቢያን አለም አጓጉታቸው ዛሬ ጥለዋት ቢሄዱ፤ ነገ ልብ ሲገዙ መመለሻ ቤት ትሆናቸው ነበር። እንዴት ይሄን ያጡታል?
እኛስ እስከ መቼ ነው የምናለቅሰው? በየጊዜው ስሜትን የሚኮረኩሩ ጽሑፎችን እያነበብን እስከመቼ ነው የምንዘልቀው? ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ ነው? ለምን ከሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንማርም? የአሁኑ እንቅስቃሴአቸው ብዙ እርቀት ሳይራመዱ መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለኝም? እኛስ መቼ ነው መብታችንን የምናስከብር? እኔ ስደተኛ፤ ያኛው አገረኛ እያሉ የሚያደነቁሩንን አባቶቻችንን መስመር ማስያዝ የእኛ የምዕመናን ስራ ሃላፊነት ይመስለኛል። ባቡር የተሰራለትን አላማ የሚያሳካ መስመሩን እስካለቀቀ ድረስ ነው። አሁን በሁለቱም ጫፍ ያሉትን አባቶች ሃይ ማለት አለብን።
አምላከ እስራኤል በቤቱ የተሰገሰጉትን ወንደዴዎች የምናስወጣበት ጥበብን ይሰጠን።

Anonymous said...

ብዙ እንድትጽፍ ብዙ እድሜ ይስጥህ! የኢየሩሳሌምን ጥፋት አያሳየን

asbet dngl said...

የኢየሩሳሌምን ጥፋት አያሳየን

Anonymous said...

it is not insulting but awaring to the concerned person

Anonymous said...

We will stand together and fight them.this is the only solution for TPLF:

Anonymous said...

Qale hiwot yasemalen Dn. Efi. yemnaleqsebet lebona yadelan Fetari Amlak.
Habtamu the GA

Anonymous said...

እግዚአብሔር እጆችህን ያበርታ

Anonymous said...

ውድ ዲያቆን ኤፍሬም
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል አደረሰህ፡፡
ጥሩ ብለሃል፡፡
በልማት ሰበብ ዋልድባ ገዳም፤ ባቦጋያ መድኃኔዓለም ጌታቸው ዶኒን በመሰሉ መናፍቃንና እሱን የመሰሉ ሆዳሞችን በሚሾሙ በተላላኪ ሆዳም ሰዎች ኃይማኖታችንን ቅርሳችንን ታሪካችንን. . .ሁሉ እንዳናጣ እሰጋለሁ፡፡
በባቦጋያ መድሃኔዓለም ምክንያት ብዙ ሕዝበ ክርስቲያን እየታሠረ፤ካህናት እየተንገላቱ ምዕመናን ቤተክርስቲያን እንዳይስሙ እየተደረገ ነው፡፡ በቅርቡም ቄሰ ገበዙን አሠሩት፡፡ ብዙዎቸን እያሳደዱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚመራው ደግሞ በመናፍቁ ፤ ሆዳሙና ቦክሰኛው ጌታቸው ዶኒ ነው፡፡
የዋልድባው ምኑ ተነግሮ ምኑ ይቀራል…..?
ይህን ሁሉ ከማየት ደግሞ ሞት ሳይሻል አይቀርም፡፡
“አባቶቻችን” ሆዳሞችን፤መናፍቃንን መሾም ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የሲሞን መሠሪን ሕይወት መኖርም ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡
የቅዱስ እንጦስ ሕልም እውን ከሆነ ቆየ መሰለኝ፡፡
በመጨረሻው ዘመን የሚሾሙ መነኮሳት እንደቁራ ጠቁረው ቢያያቸው አዝኖ ትርጉሙን ሲረዳ፤
1. ከክርስቶስና ከመስቀሉ ፍቅር ይልቅ ለራሳቸው፤ለዘራቸው፤ለማንነታቸው የሚተጉ
2. ከመሳፍንት (ከካድሬዎች) ጋር በጠዋት ማዕድ የሚበሉ ሆዳሞች
3. ርካሽ ፖለቲካ በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚዘሩ
4. ከኃይማት ይልቅ ቢዝነስ፤ገንዘብ፤ሕንጻ የሚመርጡ አዋልደ ይሁዳዎች ሆነዋል፡፡
በንሥሐ መጠራታቸውንም እኔ እንጃ . . .
መንግሥትም ከዚህ ነገር ዳር ላይ ቆሞ የሚቀላውጥ ከሆነ ሕዝብ እየባሰው ነውና ችግሮች ተባብሰው ከመገንፈላቸው በፊት ሕዝቡ ቁጣውን መግለጥ ሳይጀምር የማይሳሳት የለምና ቢመለስ ጥሩ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ ሳይሆን እየገጠማችሁ ያላችሁት ስልጣንን የሠጣችሁ እግዚአብሔርን ስለሆነ ተጠንቀቁ!!!!
ካልሆነ ግን እንደ ምርጫ 97 በምርጫ 2007 የምርጫ ካርዱን በመጠቀም የመንግሥት ለውጥ ማድረግ ግድ ሳይል አይቀርም፡፡ እስከዛሬ ወገቤን አስሬ ለኢህአዴግ መከራከሬ ስህተት መሆኑ የገባኝ አሁን ነው፡፡
የስኳር ልማቱ ለአዜብ መስፍንና ለዘመዶቿ ከሆነ እነርሱ እምነታቸውን እንደሚመርጡ አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም እምነታቸውን፤ባህላቸውን፤ማንነታቸውን ሽጠው ስኳርን አይመርጡምና ምክንያቱም እኔም የተዛመድኩ በመሆኔ ሁሉን አውቀዋለሁ፡፡
መቸም የኢትዮጵያ ሕዝብ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም በእነዚህ ዐመታት ያስተዋለው ብዙ ነገር እንዳለ አያጠራጥርም፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከሕዝብ አይሰወርምና መንግሥት ረጋ ብሎ ነገሮችን ቢያስተውል መልካም ይሆናል እንላለን፡፡ እየባሰ ከሆነ ግን ይህ ሕዝብ ከምንም በላይ ራሱን ስለኃይማኖቱ፤ስለሐገሩና፤ስለማንነቱ መስዋዕት በማድረግ የመለስ ቀዮ አድዋ ራሷ ትመሰክራለች፡፡
ፈጣሪያችነ ለሃይማኖትና ለአገር መሪዎቻችን ልቦና ይስጥልን!

Anonymous said...

ለቤተ ክርስቲያን ያለህ ቅንአት እንደ ናቡቴ ነው ልበል? ጸጋውን ያብዛልህ፡፡ ብዙ ይጻፋል፣ ብዙ ይነበባል፣ ብዙ ይደመጣል፣ ግን ያው እንደኑሮው ውድነት ተላምደነዋልና ምንም ለውጥ አይመጣም ባልልም እስካሁን ለውጥ አላመጣም፡፡ ምንአልባት እንደእስራኤላውያን ‹‹አዳኝ›› እስኪመጣ መጠበቅ ካልሆነ፡፡ በቅርቡ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳነብ ቅዱስነታቸው የአዲስ አበባን ገዳማትና አድባራት የይዞታ ማረጋገጫ ከሚመለከተው ክፍል መቀበላቸውን የሚገልጽ ርዕስ አየሁና በተመስጦ ከአንዴም ሁለቴ አነበብኩት፡፡ ታዲያ በዚህ ጽሑፍ ላይ ቅዱስነታቸው ‹‹ ቦታ መያዙ ብቻውን ዋጋ የለውም፣ ለልማት ካልዋለ›› ብለው ነበር የተናገሩት፡፡ ጽሑፉን እንዳነበብኩ ልቡናየ በሰከንድ ውስጥ ዋልድባ ገዳም ደረሰ፡፡ በመንፈሳዊ መዓዛ የተሞሉት የገዳማት ይዞታዎች ወደፊት በህንጻና በሐውልት ካላሸበረቁ አንተ የዘረዘርካቸው በገዳሙ የሚገኙ መንፈሳዊ ቅርሶች በ‹‹ ሥጋዊ ልማት›› ቫይረስ ለተበከሉ ሰዎች ትርጉምም ዋጋም የላቸውም፡፡ የብርቱካንን ጣዕም የሚያውቀው አጣጥሞ የቀመሰው እንጅ ያየው ወይም ስለብርቱካን ያነበበው አይደለም፡፡ እናም አንድ ጸሐፊ እንደተናገረው ‹‹ምላጭ ያበጠበት ውሃ ያነቀበት›› ዘመን ነው፡፡ ስለመብትና ስለይገባኛል ጥያቄ ማንሳት ‹‹ጸረ-ልማት፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የራሳቸውን ጥቅም የሚያራምዱ፣ ወዘተ›› የሚል የወዮልህ አፈሙዝ ተደግኖ ምን ማድረግ ይቻላል? ‹‹አዳኝ›› እስኪመጣ መጠበቅ ካልሆነ፡፡ እኔ ከማንበብ ወደ መጻፍ ልሻገር፣ አንተ ደግሞ ከመጻፍ ወደመተግበር ብታድግ መልካም ነው፡፡

Anonymous said...

To Anonymous May 9, 2012 5:14 AM: You are right but wrong! read the article again. ስለገዳሙም ቢሆን መሳደብ ኃጢአት ነው፡ሌባውን ስለሌብነቱ ሌባ ማለት ግን ስድብ አይደለም፡፡

Anonymous said...

betame yemimesete Tshufe newe asetewaye lebuna lalewe sewe Egeziabehera Lebonachenene Yekefetelene, yaberalene

Anonymous said...

ቃለ ውግዘት።
«ዛሬ ካለው የቤተ ክርስቲያን አመራር ጋራ ወደ ትግል ሰልፍ እንድገባ ያደረገኝ የኔ ፈቃድ፥ ዐቅምም አይደለም። በ፲፱፻፹፭ ዓመተ ምሕረት ሐምሌ ፭ ቀን ኦፕራሲዮን ሆኜ በሰመመን ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ በሥርዓተ ሙታን ወደ አምላኬ ፊት ቀርቤ የተሰጠኝ ትእዛዝ ነው። በዚያች ሰዓት፤ ከቅዱስ ማርቆስ እስከ ሳድሳዊ ቄርሎስ የነበሩ የእስክንድርያ ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከአትናቴዎስ፥ ከሰላማ እስከ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የነበሩ የኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርኮች የእሳት ነበልባል በከበበው፥ የእሳት ልሳን ያለው መጋረጃ በተንጣለለበት በዚያ አዳራሽ፥ በዚያ የግርማ ዙፋን ግራና ቀኝ ተሰልፈው ቁመው ነበር። በኤፌሶን ጉባኤ ንስጥሮስን ያወገዘው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ በመንበሩ ፊት ለፊት ቆሟል። ቀድሞ የተወገዘው ንስጥሮስ የማዕረግ ልብሱን ተገፎ በስተጀርባው ቆሟል። አባ ጳውሎስ በማዕረጋቸው እንዳሉ ተከስሰው ከንስጥሮስ ጎን ቁመዋል። በዐጸደ ነፍስ የሚገኙት የእስክንድርያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አበው፤ «አባ ጳውሎስ ሺ ስድስት መቶ ዓመት የኖረ ውግዘት ጥሰው፥ በሥጋው በደሙ የማሉትን መሓላ አፍርሰው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የሮም ቅኝ ግዛት ስላደረጉ፤ ፍርድ ይሰጥልን፤» ሲሉ ለኀያሉ አምላክ አቤቱታ አቀረቡ። ከዙፋኑ የመጣው መልስ ግን፤ «እስከ ዕለተ ምጽአት ፍርድ የቤተ ክርስቲያን ነው፤» የሚል ነበረ። ይህ ሁሉ በሚከናወንበት ጊዜ የማላውቀው ኀይል ከዚህ ዓለም ነጥቆ ከቅዱስ ቄርሎስ ጎን አሰልፎኝ ከቆየ በኋላ ከዙፋኑ የመጣው ድምፅ፤ «አንተ ያየኸውን፥ የሰማኸውን ለቤተ ክርስቲያን፥ ለምእመናን ንገር፤» ሲል አዝዞ ወደ ነበርኩበት መለሰኝ። ይህ ትእዛዝ ነው እዚህ ሰልፍ ውስጥ ያስገባኝ። ኢትዮጵያዊ፥ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሁሉም ስለ ቤተ ክርስቲያኑ አጥብቆ መታገል አለበት።» አለቃ አያሌው ታምሩ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ የተከሰቱትን የሃይማኖት ትምህርትና የሥርዓት መበላሸት በማስመልከት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ ችግሩ ሥር ሳይሰድ ገና ከጅምሩ እንዲታረም ማሳሰቢያና ተማጽኖ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተደጋጋሚ ተማጽኖ አቅርበው ነበር። ነገር ግን ጥያቄአቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ዘንድ በቸልታ በመታየቱ ምክንያት፤ አለቃ አያሌው ታምሩ ባላቸው ከፍተኛ ሥልጣንና ኀላፊነት፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ዐመጽ የሚፈጽሙትን ፓትርያርኩንና ተከታዮቻቸውን ለማውገዝ ተገደዋል። ቃለ ግዝታቸው በመጀመሪያ የወጣው ሰኔ ፳፯ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በ«መብሩክ» ጋዜጣ ላይ ነበር።
ከአሁን ጀምሮ ማለት ይህ ቃል በነጻው ፕሬስ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃልና እጅ፥ በሲኖዶሱ ዋና ጸሓፊ በአቡነ ገሪማ ቃልና እጅ፥ ይህን አሁን የተጻፈውን ሕግ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ብለው አጽድቀው በተባባሪነት አሳልፈዋል የተባሉ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ እውነት ሆኖ ከተገኘ የበደሉ ተባባሪዎች ናቸውና በነሱ ቃልና እጅ ቡራኬ እንዳትቀበሉ፥ እንዳትናዘዙ፤ ስማቸውን በጸሎተ ቅዳሴ የሚጠሩ አለቆች፥ ቀሳውስት፥ ካህናት ካሉም የአምልኮተ ጣዖት አራማጅ ናቸውና ተጠንቅቁባቸው፤ ምክር ስጧቸው፤ እንቢ ካሉም ተለዩዋቸው። እንዲሁም ሐምሌ ፭ ወይም ፮ ቀን ይከበራል ተብሎ ሽርጉድ የሚባልለት በዓለ ሢመት የአሮን የወርቅ ጥጃ መታሰቢያ ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ሊከበር የማይገባው ስለ ሆነ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የሲኖዶሱ አባላት በአስቸካይ ተሰብስበው ሕጉን ካልሻሩና በጣዖትነት የተሰየሙትን አቡነ ጳውሎስን ከሥልጣናቸው ካላነሡ ምእመናን ይህንን በዓል እንዳታከብሩ ለቤተ ክርስቲያን ደሙን ባፈሰሰ አምላክ ስም፥ ቤተ ክርስቲያንን በሚመራና በሚጠብቅ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥያቄዬን አስተላልፋለሁ። ምናልባት የሕጉን ጽሑፍ አንብቦ መረዳት የተሳነው፥ ግን በልዩ ልዩ ደጋፊዎቻቸው ተጭበርብሮ በቸልታ የሚመለከተው፤ ከዚያም ዐልፎ በሥልጣናቸው እየተመኩ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ጆሯችንን አንሰጥም ብለው ይህን በደል ያደረሱትን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን፥ በሦስት የሹመት ስም የሚንቀባረሩትን አባ ገሪማን፥ ለነሱ ድጋፍ የሚሰጡትንም ሁሉ፤ ጌታዬ አምላኬ፤ «በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤» ሲል በሰጠው ቃል በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን፤ በጴጥሮስ፥ በጳውሎስ፥ በማርቆስ፥ በቄርሎስ፥ በባስልዮስ፥ በቴዎፍሎስ፥ በተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ቃል፤ ኃጥእ ደካማም በምሆን በእኔም በቀሲስ ወልደ ጊዮርጊስ ቃል አውግዤአለሁ። ይህን ሕግ የተቀበሉና ከሥራ ላይ ያዋሉ ሁሉ እንደ አርዮስ፥ እንደ መቅዶንዮስ፥ እንደ ንስጥሮስ፥ እንደ ፍላብያኖስ፥ እንደ ኬልቄዶን ጉባኤና ተከታዮቹ እሱራን፥ ውጉዛን ይሁኑ። በማይፈታው በእግዚአብሔር ሥልጣን አስሬአለሁ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን አሜን።
ማስጠንቀቂያ፤ አምላኬ ሂድ ተናገር ያለኝን ትእዛዝ ለእናንተ አድርሻለሁ። ሩጫዬንም ጨርሻለሁ። ከእንግዲህ ተጠያቂነቱ የእናንተ የምእመናንና ታሪክ ተጠያቂ ያደረገው የመንግሥት ነው። ለዚህም ምስክሬ ራሱ እግዚአብሔር፥ ቅዱሳን መላእክት፥ ሰማይና ምድር ናቸው።
አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዮርጊስ።

Anonymous said...

እጅግ እጹብ ድንቅ መልዕክት ነው። በውኑ በደሙ ያዳነንን አምላክ የምንከተል አለን? ውጣ ውረዱን አልፋ፤ ሰማዕታትን በየጊዜው አስተናግዳ፤ ክርስቶስን የምትሰብከዋ ቤተክርስቲያን ልጆች አለን? ፍራት ቀፍዶ ያልያዘን፤ ጥግ ይዘን ያልተቀመጥን፤ የቤቱ ቅናት የሚበላን፤ አሁንዝ በዛ የሚል ወኔ ውስጣችንን የሚንጠን የተዋህዶ ልጆች አለን? ለጊዜያዊ ስሜት ያልተገዛን፤ አሸብራቂዋ አለም ማርካ በመዳፏ ያላስገባችን የቁርጥ ቀን ልጆች አለን ይሆን? ትናነት እንዲህ ነበር፤ ዛሬ እንዲህ ሆነ እያልን እንደ ዉሃ ማስተላለፊያ ቧንቧ ነገር ከማስተናገድ ተቆጥበን፤ የመጣውን አደጋ ለመቀልበስ ከልብ የቆርጥን አለን ይሆን? ስንቶቻችን ነን ስለ ሰማዕታት ታምር መናገር ሳይሆን፤ ራሳችንን ለዚህ ድንቅ ጥሪ ያዘጋጀን ማናችን እንሆን? እስከ ሰራዊታቸው ዘው ብለው ገብተው፤ የላይኛውን ቦታ ተፈናጠው ቤተክርስቲያኗን የሚያሳድዷት፤ ቆራጥ ጠባቂ የላትም ብለው አይደለምን? ከንፈር መምጠጥ ይጠቅመን ይሆን? እምነት የለሽ ከሃዲ ሆነን በኢትዮጵያዊነት ስም መኖር የምንችል ይመስላችዃል? መቼ ይሆን ሃይ አሁንስ በዛ የምንል? መቼ ይሆን ቁስሉ ዘልቆ አንጀታችን የሚገባው? መቼ ይሆን የሚያቃጥለን? ራሳችንን እንጠይቅ። ቤተክስቲያን የሚያስፈልጋት አንድ ወይም ጥቂት ቆራጥ ልጆችዋን ነው። ዲያቢሎስ በአንድ ጠንካራ ሰው ይመለሳል። ልፍስፍስ የሆን ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ ኦርቶዶክስ አማኞች አግኝቶ እንደ ፈለገው እየጨፈረብን ነው። ቁጭት አደረብን የምንለውም ቢሆን ቁጭትን በቃል ወይም በጽሑፍ ከማስተጋባት ባለፈ፤ ተግባር ያለው እንቅስቃሴ ስናደርግ አንታይም። አምላክ የተግባር ጥያቄ ነው የሚጠይቀን-በዃለኛው ስዓት። ዝም ብለን ከንፈር መጣጭ ሰዎችን ማብዛቱ ምንም አይጠቅመንም። “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ“ የሚባለው ተረት ደርሶብን፤ እልም ያሉ ሌቦች፤ ጭልጥ ያሉ ዱርዬዎች፤ የሞራል ለከት የሌላቸው ውሸታሞች፤ እኔ “ዲያቆን፤ ቀሲስ፤ አቡነ እከሌ“ እባላለሁ እያሉ ከፋፋይ እና አደንቋሪ መልዕክቶቻቸውን ባደባባይ መርጨት ከጀመሩ ይሄው አመታት ተቆጠሩ። በአንዳንድ የከርስቶስን መስቀል ጨብጠው ከፋፋይ የሆኑ መልዕክቶችን መስማት የተለመደ ሆኗል። እናም ሀላፊነት የምንወስድ አለን ይሆን? እራሳችንን እንጠይቅ!

Anonymous said...

What an impressive article!....Wolde Esdros Zelideta...yene bathon yikochegn neber!

Anonymous said...

all things solve by God so we are pray our chruch