Friday, May 25, 2012

የኛ ሰው በላስ ቬጋስ (ክፍል ሁለት)

(PDF):- ባለፈው እትም ስለ ቁማሯ ከተማ ላስ ቬጋስ ሚጢጢ ጨዋታ ጀምሬላችሁ ነበር። እንዲያውም “ስለ ሁለቱ (ስለ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ስለ “ጥቁሩ ሙሴ/ ሙሴ ጸሊም” ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ) እና ሌሎች ቀሪ የቬጋስ ጉዳዮች አካፍላችኋለሁ። ዕድሜ ይስጠንና።” ብዬ ማቆሜን አስታውሳለኹ። ከማያልቅበት መዝገቡ ዕድሜ ከቸረኝ ዘንዳ እኔም ከመዝገበ-ልቡናዬ በብዕሬ ጫፍ እየጠለቅኹ በዓይነ ልቡና ላስጎብኛችሁ።

ሲዖልም መንግሥተ ሰማያትም በአንድ ያሉበት ቦታ ላስ ቬጋስ ሳይሆን አይቀርም። ከነስሟ “የኃጢአት ከተማ” እንደምትባል፣ “ወደ ኃጢአት ከተማ እንኳን ደህና መጡ” የሚል ጽሑፍ ማየት የተለመደ መሆኑን ላስታውሳችሁ። ወደ ቬጋስ የሚመጣ አብዛኛው ጎብኚ አቅሉን ለመሳት፣ የዕብደት ጫፍ ረግጦ፣ በኑሮ ድካም የናወዘ አዕምሮውን በዕብደት ምጥቀት ለማስከን ሽቶ ነው ይባላል። መዝናናትና ስክነት ከዕብደት ጫፍ ደርሶ በመመለስ ይገኝ እንደሆነ እነርሱ ያውቃሉ።

ሲዖሉ በስካሩ፣ በሴተኛ አዳሪው ጋጋታ እና በዚያ ትርምስ የሚታየውን ማለቴ ነው። በርግጥ ለቱሪስቱ ሲዖል ብሎ የሚነግረው የለም። ራሱም አስቀድሞ “ገነት” ብሎ ስለጠራው በዚያው ነው የሚረዳው። መሐል ከተማ የቁማሩን ታላላቅ ሕንጻዎች፣ ብልጭልጭ መንደሮች ለመጎብኘት ስንጓዝ ጎረምሶች በዕኩለ ቀን ስክር ብለው በግሩፕ እየተሳሳቁ ያልፋሉ። ካናቴራዎቻቸው ተከፋፍተዋል። በእጃቸው አልኮል ይዘዋል። በሌላ የአሜሪካ ከተማ ቢሆን የተከፈተ አልኮል ይዞ መሔድ በፖሊስ ያስቀፈድዳል። በቬጋስ ይሄ የተፈቀደ ነው።

ከመኪና ወርደን በእግራችን መጎብኘት ስንጀምር የማስታወቂያው ዓይነት ዓይን ያጥበረብራል። አብዛኛው ከተለያየ “ሾው” እና ሴተኛ አዳሪዎች ጋር የተገናኘ ነው። በደረቁ “ሴተኛ አዳሪ” አልኩት እንጂ ማስታወቂያዎቹስ አስውበው ነው ያቀረቡት። በእግራችን እየተዘዋወርን ጎበኘን። በሺህዎች የሚቆጠሩ ክፍሎች ያሏቸው ሆቴሎች አሸብርቀዋል። ደግሞ ጽዳታቸው። አስፓልቱ ሳይቀር በየቀኑ የሚታጠብባት ከተማ። ውጪ አገር፣ ፈረንጅ አገር የሚለውንና ድሮ በአዕምሮዬ የሳልኩትን አሜሪካ ያየኹት ቬጋስ ነው።

መንገዶቹ ሰፋፊዎች ናቸው። የመንደር ውስጥ መንገድ የሚባለው ባለ ሦስት ረድፍ መሔጃ፣ ሦስት ረድፍ መምጫ ሆኖ ሰፋፊ ጎዳና ነው። የላስ ቬጋስን የመንደር ውስጥ መንገድ እንግሊዝ አገር ብትወስዱት “ትልቅ የቀለበት መንገድ” የሚሆን ይመስለኛል። ጠባብ መንገድ ምሳሌ ሲባል የምትመጣብኝ ለንደን ናት። ሰዉ ሁሉ ከመኪና ከወረደ አልጋው ጫፍ ላይ የሚደርስባት፣ መሬት ውድ የሆነባት ከተማ። ቬጋስና ቴክሳስ የዚያ ተቃራኒ ናቸው።

ቬጋስ ውስጥ ለመዘዋወር ዋነኛው የትራንስፖርት መንገድ እግር መሆን አለበት። መኪና ከአንድ ሩቅ ቦታ ወደ ሌላ ሩቅ ቦታ ለመሔድ ካልሆነ በስተቀር ተመራጭ አይደለም። በተለይም “ሾው” ወዳለባቸው ሥፍራዎች ስንሔድ እግራችን ሊሰበር ምንም አልቀረውም። ከድካሙ የተነሣ። ወገባችን ሁሉ ተንቀጠቀጠ። ውኃው ሲጫወት፣ እሳተ ገሞራው ሲፈነዳ፣ የባሕር ላይ ዘራፊዎች ሲዋጉ የሚያሳዩ ድንቅ ድንቅ የውጪ ቲያትሮች ይታያሉ። ታዲያ ሰዓት ሰዓት አላቸው። አዘጋጆቹ ሆቴሎቹ ናቸው። በተለያዩ ሰዓቶች የሚካሄዱት ዝግጅቶች እንዳያመልጡን አስተናጋጅ ወዳጆቻችን እየመሩን መሮጥ ነው።

አንድ ቦታ ስንገባ ደግሞ የዓለም ታላላቅ ከተሞች በሙሉ ከነምናምናቸው መጥተው ቁጭ ብለዋል። ሮም በለው ፓሪስ በለው እንዲያው ከነመልክ አካላቸው እዚያ ያሉ ይመስላሉ። ግን ቤት ውስጥ ነው። ቀና ስንል ሰማዩ በከዋክብት አጊጦ  ይታያል። ግን የእጅ ሥራ ነው። በጀልባ ብቻ የሚኬድባት የጣሊያኗ የፍቅር ከተማ ቬኒስ ቁጭ ብላለች። ጥንድ ጥንድ ሆነው በጀልባ የሚጓዙ ሰዎችም ይታያሉ። ትንሽ አለፍ ስንል ተራራ የሚመሳስሉ ቋጥኞች ተቆልለዋል። ነገር ግን ድንጋይ አይደሉም። የሰው ልጅ የእጅ ጥበብ ድን……ቅ ይላል።

++++

በበነጋው ጠዋት ከዚህ “ከሲዖሉ” ወጣ ብለን ሌላኛውን ገጽ ለማየት ከቬጋስ እንብርት ሁለት ሰዓት ወደሚርቀው ጭውውው ያለ በረሃ መንዳት ጀመርን። ወደ ግብጽ ኦርቶዶክሶች ገዳም። በቅ/እንጦንስ ስም የተሰየመ ነው። ኔቫዳ በረሃ ላይ ገዳም፤ ያውም ከአፍሪካ የመጡ ሕዝቦች ገዳም። የማይታሰብ ነው። ምናልባት ግብጾች ለበረሃ ለበረሃ ሰሐራን ስላዩ ይሆናል። “ለውኃ ለውኃ ምናለኝ ቀኃ” አለ የጎንደር ሰው።

የአባ እንጦንስ ገዳም ከላስ ቬጋስም ከሎስ አንጀለስም እኩል ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ከካሊፎርኒያ ለሚመጣውም፣ ከወዲህ ከቬጋስ ለሚሄደውም የሚመች መንገድ ነው። አስጎብኚያችን ወዳጃችን ተፈራ ተበጀ መኪናዋን እያሽከረከረ የሚመቸውን አስፓልት ሲጋልብበት ቆይቶ ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ዋናውን አስፓልት ትቶ በጥርጊያ መንገድ ታጥፎ ወደ በረሃው ገባ። የውጪውን ሙቀት ለማወቅ ከመኪናው መውረድ አይጠይቅም። እንዲሁ በዓይን ሲያዩት ያስታውቃል። ዋዕዩ።

ወደ ገዳሙ ስንታጠፍ “Saint Antony Monastery” የሚል ቅስት/ ጽሑፍ በቀስት አቅጣጫ ያመለክታል። ወደ ገዳሙ ስንዘልቅ የገዳሙ መሥራች አባት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ካራስ ሥዕል ከሩቅ ይታያል። ሱዳን ተወልደው፣ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቀው፣ ምንኩስናን መርጠው፣ አሜሪካ መጥተው፣ እዚህ በረሃ ላይ ይህንን ገዳም መሥርተው ከዚያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 ከዚህ ዓለም ድካም በሞት እንደተለዩ ታሪካቸው ያትታል። መቃብራቸውም እዚያው አለ። ይጎበኛል።

መምጣታችንን ያወቁት ገዳማውያኑ ወደኛ መጡ። አንድ ወጣት ግብጻዊ፣ ነጭ ቀሚስ ለብሶ ሊያስጎበኘን መጣ። አረብኛ ወዙ ባልለቀቀው እንግሊዝኛ ለምንጠይቀው ምላሽ ሰጠን። ለነገሩ የቬጋስ ወዳጆቻችንም ብዙ ጊዜ ወደ ገዳሙ ስለሚመላለሱ ሌላ አስጎብኚም አላስፈለገንም። በመጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብተን ከተሳለምን በኋላ አካባቢውን ሁሉ ማየት ጀመርን።

ገዳማውያኑ ለራሳቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አሟልተዋል። ሰው ሠራሽ የአሳ ማርቢያ እና ማስገሪያ ትንሽ ኩሬ፣ ጽድትና ኩልል ባለ ውኃ አዘጋጅተዋል። ግብርናም ይሞክራሉ። በጎች፣ ፍየሎች፣ ዶሮዎች፣ ሌሎችም እንስሳት አሏቸው። ገዳሙን ለመጎብኘት፣ አንድ ሁለት ቀንም በጸሎት ለመቆየት ለሚፈልጉ ሰዎች የተዘጋጀ እንግዳ ማረፊያ አላቸው። ቀድሞ መናገር ብቻ እንጂ ለማረፊያም ሆነ ለምግብ ችግር የለም። እኛም ቆየት ብለን ምሳ አብረናቸው በልተናል።

የሙሴ ጸሊም ቤተ ክርስቲያን

  በአንድ በኩል መጻሕፍት፣ ሲዲዎች፣ ዲቪዲዎች፣ ሌሎች ንዋየ ቅድሳት የሚሸጡበት ሱቅ አላቸው። እንደ ሙዚየም የሚጎበኝ የመሥራቹ አባት መካነ መቃብር እና የቅዱሳን አጽሞች የሚገኙባቸው ቤቶችም አሉ።  ሥዕሎቻቸው፣ መስቀሎቻቸው ሁሉ በሥርዓት በሥርዓት ተሰድረው ተቀምጠዋል። ከቬጋስ ግርግር፣ ከአሜሪካ ኑሮ ትርምስ ወጥቶ ፍጹም መንግሥተ ሰማያዊ ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ በቅርብ ርቀት ማግኘት በራሱ ይደንቃል። ኢትዮጵያውያን የቬጋስ ክርስቲያኖች ወደ ገዳሙ ብዙ ጊዜ ይጓዛሉ። ለመንፈሳዊ ሕክምና።

ከዋናው ቤተ ክርስቲያን አምስት መቶ ሜትር ያህል ርቆ አንድ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ቆሟል። አስጎብኚ ወዳጆቻችን “ይህ ተአምራዊው የሙሴ ጸሊም (የኢትዮጵያዊ ቅዱስ የሙሴ፣ ጥቁሩ ሙሴ/ Moses the Black የሚባለው) ቤተ ክርስቲያን ነው” አሉን። ገዳሙ የቅ/እንጦንስ ነው። የርሱ ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ሆኖ የቅ/ሙሴ ይህንን ያህል ግዙፍ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በራሱ የሚደንቅ ታሪክ ነው። ውስጡን ለማየት፣ ታሪኩን ለመስማት ተጓዝን።

ወደ ውስጥ ከመግባታችን አስቀድሞ ትልቁ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ያለች “መቃኞ”/ የሥዕል ቤት ገብተን ጸሎት አደረግን። ከዚያ ወደ ትልቁ ቤተ ክርስቲያን ገባን። ትልቅነቱ አራት ኪሎ ካለው ከቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ብዙም አይተናነስም።  ሥዕሎቹ በሚገርም ውበት ተስለዋል። ቋሚዎቹ እና ከጣራው ሥር በመስመር የተገጠገጡት ማስዋቢያ እንጨቶች በወይን ዘለላ ቅርጽ የተፈለፈሉ፣ ከግብጽ ድረስ የመጡ ጣውላዎች ናቸው። መቅደሱ በካህናተ ሰማይ ሥዕሎች ተውበዋል። እኛ በጎበኘንበት ወቅት የውስጡ ሥራ ተጠናቆ የማስዋብ ሥራ ላይ ነበሩ።

ከሕንጻው ወጥተን ወደ ጓሮ ስንዞር አንድ ሐውልት ቆሟል። ለዚህ ቤተ ክርስቲያን መሠራት ምክንያት የሆነ ተአምር የተፈጸመበት ቦታ ላይ የቆመው ይህ ምልክት ጻድቁ ሙሴ በተአምራት ተገልጾ በግልጽ የታየበት እንደሆነ አስጎብኚዎቻችን ገለጹልን። አጠገቡ ያለች አንዲት ዛፍም ቅዱሱ በተገለጸ ጊዜ ለተአምሩ እማኝ እንዲሆን በጣቱ የነካትና፣ የሚፈውስ ቅዱስ ቅብዓት የፈለቀባት ሲሆን በወቅቱ ከፈለቀው ዘይት/ ቅብዓት ለእማኝነት በገዳሙ ተቀምጧል። በዚህም ተአምር መነሻ ራእዩ በተገለጸላቸው ክርስቲያኖች አማካይነት ይህ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሊገነባ ችሏል። ጻድቁ ሙሴ በ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ቅዱስ ሲሆን የኖረውና ያረፈው በግብጽ ነው።   

ያንን ቀን በገዳሙ ስንዘዋወር፣ ጸሎት ስናደርግ፣ ኃላም ከመጻሕፍት መሸጫው ገብተን የምንፈልጋቸውን መጻሕፍት፣ መንፈሳዊ ዲቪዲዎችና ሲዲዎች እንዲሁም መስቀሎች ስንገዛ ቆይተን በምሳ ሰዓት ወደ መመገቢያ አዳራሻቸው ገባን። በኩሽና የሚሠሩት ምእመናን የምንበላውን የምንጠጣውን ሰጥተው አስተናገዱን። የከፈልነው ነገር አልነበረም። መርዳት የምንፈልገው ነገር ቢኖር ኋላ በባንክ ልናደርግላቸው እንደምንችል ወረቀቶቹ ያመላክታሉ። እኛም አድራሻችንን ሰጥተን፣ ገዳሙ የሚያዘጋጀውን መጽሔት በፖስታ እንዲልኩልን ስማችንን አስፍረን ወደ መጣንበት ተመለስን። እየተገረምን። ላስ ቬጋስ - ሲዖልና ገነት ይሏል እንዲህ ነው።

ማንም ገዳሙን ያየ ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊ ቅናት ቢጤ መሰማቱ የግድ ነው። “እነዚህ ግብጻውያን በቁጥር ከእኛ አነስተኛ ሆነው እንደዚህ ሲሠሩ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በቁጥር በዝተን ሳለ አንድ ገዳም እንኳን የሌለን ምን ሆነን ነው?” ማለቱ አይቀርም። “አብራችሁ ብሉ እንጂ አብራችሁ ሥሩ” ማን አለንና? ስለዚህም በየሔድንበት ከቁጥራችን ጋር የሚመጥን አሻራ ሳንተው፣ ሁሌም አዲሶች እንደሆንን፣ እንደተበታተንን፣ የማይረባ የታዳጊ አገር ፖለቲካ ይዘን እንደተናተፍን ይኸው ዘመን ጥሎን ይሄዳል። በውስጤ ይኼንን እያመላለስኩ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያደርገው ራሴን እየወቀስኩ፣ ከራሴ ጋር እየተጫወትኩ ወደ ቬጋስ ተመለስኩ።

አዪዪዪ፣ ስለ ሑቨር ግድብ ላጫውታችሁ ብዬ ቦታ ሊገድበኝ ነው ማለት ነው? በሚቀጥለው እትም፣ አዘጋጆቹ ከፈቀዱ፣ ስለ ግድቡ እና እጅግ ልቡናን ስለሚመስጠው የተራራ ሰንሰለት እና ተያያዥ ጉዳዮች ልነግራችሁ እሞክራለሁ። ዕድሜውን እና ጊዜውን ይስጠንና። ካልሆነም በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንገናኛለን። አስተያየታችሁን ደግሞ በኢ-ሜይል ephremeshete@Gmail.com ብትልኩልኝ ደስታውን አልችለውም።


የፌስቡክ ተጠቃሚ አንባብያን፣  ያነሳኋቸውን ፎቶዎች ከዚህ መመልከት ትችላላችሁ።

 

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ-ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
   

    

16 comments:

kassahun alemu said...

እግዚአብሔር ይስጥህ እያሳዩ መጻፍ ትልቅ ነው፤ ለሚያነበው ምስልን፣ ለሚያይና ለሚመለከት ደግሞ ቁጭትን ይፈጥራልና፡፡ ‹ሁሌም አዲሶች እንደሆንን፣ እንደተበታተንን፣ የማይረባ የታዳጊ አገር ፖለቲካ ይዘን እንደተናተፍን ይኸው ዘመን ጥሎን ይሄዳል።› ትልቅ መልክት ነው፡፡

Anonymous said...

Dn Thanks .God Bles U?

Anonymous said...

Dn Efrem, thank you dear. your visiting makes me happy and add a hope on my life i don't know the reason behind this.
thank you again

ኤፍሬም እሸቴ said...

Thank you.

Anonymous said...

thank you brother god bless you.

Anonymous said...

“እነዚህ ግብጻውያን በቁጥር ከእኛ አነስተኛ ሆነው እንደዚህ ሲሠሩ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በቁጥር በዝተን ሳለ አንድ ገዳም እንኳን የሌለን ምን ሆነን ነው?” ማለቱ አይቀርም። “አብራችሁ ብሉ እንጂ አብራችሁ ሥሩ” ማን አለንና? ስለዚህም በየሔድንበት ከቁጥራችን ጋር የሚመጥን አሻራ ሳንተው፣ ሁሌም አዲሶች እንደሆንን፣ እንደተበታተንን፣ የማይረባ የታዳጊ አገር ፖለቲካ ይዘን እንደተናተፍን ይኸው ዘመን ጥሎን ይሄዳል።

Anonymous said...

እድሜ ይስጥልን! ዲን ኤፍሬም እኛኮ ለምን እንደ ግብጻውያኑ በሁለቱም መንገድ (በመንፈሳዊም በሥጋዊም እውቀት) የተካኑ መናኞች እንደማይኖረን ሳስብ ይጨንቀኛል. የተማረው መንፈሳዊ በሙሉ ማለት ይቻላል ልቡና ፊቱ ወደጋብቻ የዞረ ነው. ግብጽ ደግሞ እጅግ የተማሩ ብዙዎች አሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በምንኩስና ሲወሰኑና በሃገራቸውና ከሃገር ውጭ የነፍስ ሥራ ሲሰሩ እናያለን ምናለ ከእነርሱ ተምረን ለቤተክርስቲያን ቅድሚያ የሚሰጥ ህይወት ቢኖረን???

Anonymous said...

I was thinking of a spiritual retreat for myself, me God and me. I would like to spend sometime alone, with God. You know how that could be difficult in the US. Coptic Monasteries were the first to come to my mind. This has given me further strength for my pursuit towards a short calm time, Go willing. Thank you!!!

Anonymous said...

Danke

Anonymous said...

Nice view

Anonymous said...

amazing thankyou dn ephrem!!

mary land

Anonymous said...

we need part 3 pls.

Anonymous said...

YIBEL dN EPHREAM!!!

Anonymous said...

nice ....what can i say go 4 it....

Anonymous said...

I visited this place too. It is really amazing. I was soooo jelouse really. When you get there, you just feel safe and peace inside of you. I wished to stay there for longer time but I couldn't. Thank you for sharing, Ababa.

Anonymous said...

I really appreciet you and GOD BLESS YOU ! “እነዚህ ግብጻውያን በቁጥር ከእኛ አነስተኛ ሆነው እንደዚህ ሲሠሩ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በቁጥር በዝተን ሳለ አንድ ገዳም እንኳን የሌለን ምን ሆነን ነው?” ማለቱ አይቀርም። “አብራችሁ ብሉ እንጂ አብራችሁ ሥሩ” ማን አለንና? ስለዚህም በየሔድንበት ከቁጥራችን ጋር የሚመጥን አሻራ ሳንተው፣ ሁሌም አዲሶች እንደሆንን፣ እንደተበታተንን፣ የማይረባ የታዳጊ አገር ፖለቲካ ይዘን እንደተናተፍን ይኸው ዘመን ጥሎን ይሄዳል።

from Sweden