Saturday, June 9, 2012

የኛ ሰው በላስ ቬጋስ … “ሑቨር ዳም - የሑቨር ግድብ” (ክፍል ሦስት)

(ክፍል ሦስት/ PDF)
እንደምን ከረማችሁ? ይህ ጽሑፍ ወደ ላስ ቬጋስ ካደረግኹት የጉዞ ማስታወሻ ቅንጫቢውን እና ሦስተኛውን ክፍለ- ትረካ የያዘው የመጨረሻው ነው። በገባኹት ቃል መሠረት ስለ ታዋቂው የሑቨር ግድብ አጫውታችኋለሁ። እንደምታስታውሱት፣ ባለፈው የ “ገዳመ እንጦንስ” ጉዞዬ ማስታወሻ፣ በኔቫዳ በረሃ ውስጥ የተገነባውን ገዳም አነሣሥ እና የኢትዮጵያዊውን ቅዱስ የሙሴ ጸሊምን ቤተ ክርስቲያን ጅማሮ ጽፌላችሁ ነበር። ዛሬ ደግሞ ከመሐል ላስ ቬጋስም፣ ከበረሃው ገዳምም ወጥተን፣ ወደ 20ኛው መቶ ድንቅ የአሜሪካ የኢኒጂነሪንግ ግኝት ወደሆነው ወደ ሑቨር-ግድብ እንዘልቃለን።
ከአስጎብኚ ወዳጄ ጋር ከቬጋስ የተነሣነው በጠዋት ነው። “ለማኝ እንትን ሳይል” እንደሚባለው ሰማዩ የአህያ ሆድ ሲመስል። በዚያ በጠዋትም ሙቀቱ መጣሁ መጣሁ ይላል። ፊትን በለስላሳ ምላሱ ላስ እያደረገ የሚያልፈው ንፋስ ወደ “Boulder City” አቅጣጫ መንዳት ስንጀምርም በመስኮት ጆሯችን ላይ ሹክሹክታውን ቀጥሏል። ሠራተኛው ወደየሥራው ለመሔድ (ለመንዳት) መንገዱን ከማጨናነቁ በፊት ቀድመን ስለወጣን ጎዳናው በፍጥነት ለመጓዝ ይመቻል። ያውም የቬጋስ አስፓልት።
ወደ ግድቡ ያለው መንገድ ቀና ነው። ከሩቅ የሚታዩት ተራሮች ያምራሉ። የተራራዎቹን ውበት ያየኹት አንድ ቀን ከቬጋስ በሌላ አቅጣጫ ከከተማው ገና ወጣ ሲሉ የሚገኘውን “የቀይ አለት ፓርክ” የጎበኘኹ ጊዜ ነው። የድንጋይ ዘር በእጅ ሥዕል እንዳጌጠ ሁሉ ተከልሎ ጎብኚዎች በየቀኑ ያዘወትሩታል። ተራራ ወጪ የእግር ተጓዥ ስፖርተኞች ወጡታል ይወርዱታል። ሌሎች ደግሞ በመኪና ፓርኩ ድረስ እየነዱ ከመጡ በኋላ መኪናቸውን አቁምው ዳገት ቁልቁለቱን ይሮጣሉ። በንጹነፋሻማ አየር የዕለት ስፖርታቸውን ያጧጡፋሉ። በአዲስ አበብኛ ብናስበው አትሌቶቻችን እንጦጦ ወጥተው፣ ወደ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ (እንጦጦ) ተራራው ላይ፣ እንደሚሮጡት ያለ ነው። ልዩነቱ ይህኛው በፓርክ ሕግ ተከብሮ የተጠበቀ መሆኑ ነው።
ድንጋይም፣ ተራራም፣ ኮረብታም በወግ በወጉ ከያዙት እንዴት እንደሚያምር ወይ “ሬድ ሮክ ፓርክ” ቬጋስ ወይም “ሮኪ ማውንቴንስ”ን ኮሎራዶ ሔዶ ማየት ነው። አሜሪካ ቢሆን ከገረዓልታ ተራሮች ጀምሮ እስከ ደቡብ የወላይታ ሰማይ የሚታከኩ የተራራ ጫፎች (የዳሞት ተራራ) ድረስ እንዴት የቱሪስት መዳረሻ በሆነች ነበር። የሰሜን ተራሮችን ብዙ ጊዜ ስመላለስ አይቻቸዋለኹ። የደቡቦቹን ደግሞ ወደ ጂንካ በምትበርረው ባለ ሁለት ሞተር አውሮፕላን (ዳሽ 6?) ስንሔድ ተመልክቻቸዋለኹ። ሰማዩ መሐል አናታቸውን ታክኮ የቆመ የሚመስሉ መለሎ መለሎ ተራሮች ናቸው። ሰሜኖቹ ደግሞ የአፈር ዘር በሙሉ ከላያቸው ተጠራርጎ የወደቀ፣ አጥንታቸው ብቻ እስከነግርማ ሞገሱ ተገሽሮ ቆሞ ለዓይን ያስደንቃሉ። የእኛ አገር ተራሮች ግን ለእርስበርስ ጦርነት ለመተላለቂያ ካልሆነ ሌላ ብዙም ጀብዱ የላቸው። እማኝ የሚፈልግ ልቦለድ አንባቢ የበዓሉ ግርማን “ኦሮማይ”፤ ታሪክ የሚወድ ደግሞ የብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተ ማርያምን “የጦር ሜዳ ውሎ” ማንበብ ነው።
የኢትዮጵያን ተራሮች ገርተው የተጠቀሙባቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ናቸው። ከገረዓልታ እስከ ደብረ ዳሞ፣ ከዝቋላ እስከ አሰቦት እግራቸው ያልረገጠው ሥፍራ የለም። ድንጋዩን ፈልፍለው፣ አለቱን ጠርበውና አለዝበው ዋሻውንና ፍርክታውን የመንፈሳዊ ተጋድሎ ቤታቸው አድርገውታል። ፈረንጆቹ ደግሞ እንደ ኮሎራዶ አካባቢ ያሉ ተራሮችን እየፈለፈሉ ግማሹን የቦምብ መሞከሪያ፣ ገሚሱን እንደ ጌጠኛ “አምፊ ቲያትር” አድርገው መዝናኛ  አድርገውታል። እንደየ ሕይወት ፍልስፍናችን ኢትዮጵያውያኑም ፈረንጆቹም ተራሮቹን በእጃችን ልንገራቸው ሞክረናል።
እንዲህ እየተደመምኩ ስንጓዝ ቆይተን ለጥ ካለ ሐይቅ ዳርቻ ደረስን። ኩልል ያለና የጠራ ውኃ ተንጣሎ በሩቅ ይታየኛል። ነገር ግን አስጎብኚዬ እስኪነግሩኝ ድረስ በበረሃ ውስጥ ሰው ሠራሽ ሐይቅ መሆኑን አልገመትኩም ነበር። የሑቨር ግድብ ከተሠራ በኋላ አለፍ ብሎ የተፈጠረ ሐይቅ መሆኑን አስጎብኚዬ አጫወቱኝ። እንደ ገፈርሳ ማለት ነው። ቬጋስ ጥሟን የምትቆርጠው በዚህ ውኃ ነው።  Lake Mead - የሚድሐይቅ” ይባላል። በአሜሪካ ትልቁ ሰው ሠራሽ የውኃ ማጠራቀሚያ ነው። ከየተራራው እየቀለጠ የሚወርደው በረዶ እየተንጠባጠበ ይጠራቀምበታል። ከውኃው ጥቅምም ጎን ለጎን በመዝናኛነት ያገለግላል። በጀልባ ይንሸራሸሩበታል። ይዋኙበታል። በየዳር ዳሩ እየተሰጡ ነጭ ገላቸውን በፀሐይ ያስደበድቡበታል (sunbathing)።
ሐይቁን እንዳለፍን ወደ ግድቡ ክልል እንገባለን። መንገዱ ክሽን ብሎ የተሠራ ነው። ከተፈቀደው የመኪኖች ማቆሚያ በስተቀር ማዎም አይቻልም። በየአቅጣጫው የተወደረው ካሜራ የእያንዳንዱን ሰውም ሆነ መኪና እንቅስቃሴ እንደሚከታተል ያስታውቃል። ነገር ግን በየአጥሩ ጥግ መሣሪያውን ወድሮ ሰው ላይ እያፈጠጠ የሚያስደነግጥ ወታደርም ሆነ ፖሊስ አይታይም። እኛም መኪናችንን በተገቢው ቦታ ካቆምን በኋላ በእግር ጉብኝታችንን ቀጠልን። በጠዋቱ ስለደረስን ወደ ውስጥ የሚገባበት ሰዓት አልደረሰም። እስከዚያው የግድቡን የውጪ ክፍሎች ማየት ጀመርን።
በተራሮች መካከል የተሰነቀረ ድልድይ ነው። ከወዲህ የኔቫዳ ግዛት ሲሆን ከወዲያ ደግሞ አሪዞና ነው። ሁለቱ ግዛቶች የተለያየ የሰዓት አቆጣጠር ነው ያላቸው። ምሳሌ፦ ኔቫዳ ላይ ሁለት ሰዓት ሲሆን፣ አሪዞና ሦስት ሰዓት ይሆናል ማለት ነው። ግድቡ በሁለቱም ግዛቶች መሬት ላይ ስላረፈ ከግድቡ በአንድ በኩል ያለው ላይ የአሪዞና ሰዓት፣ በሌላው የኔቫዳ ሰዓት በትልቁ ተሰቅሎበታል። ማዶና ማዶ የቆመ ሰው “አያ እገሌ ስንት ሰዓት ነው?” ቢል የኔቫዳው ሌላ፣ የአሪዞናው ሌላ ሰዓት ይጠራሉ ማለት ነው።
የግድቡ ግርማ ሞገስ ቁልቁል ለማየት ያስፈራል። ግድቡ ከሁለት መቶ ሜትር በላይ ከፍታ ስላለው በግድቡ የታችኛው ግርጌ በቀጭን መንገድ ላይ የሚሔዱ መኪናዎች (የሠራተኛ መኪናዎች ይመስሉኛል) ከላይ ከአፋፉ ሲታዩ ጥቃቅን ናቸው። ያንን የሚያክል የሰው እጅ የፈጠረው የምህንድስና ጥበብ ሲያዩት የዛሬ መቶ ዓመት የተሠራ አይመስልም። በ1931 ተጀምሮ በ1936 እ.አ.አ የተፈፀመው ይህ ግድብ በወቅቱ 49 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከጎብኚዎችና ከሌሎች በሚያገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ ራሱን እየደጎመ የሚኖር ተቋም ነው።
     ግድቡ ብቻ ሳይሆን የተሠራበት ጊዜው ራሱ አስተማሪ ነው። ወቅቱ “የዓለም የኢኮኖሚ ድቀት” (Great Depression) ወቅት መሆኑ ራሱም ይገርማል። አሜሪካውያን ከዳር ዳር የምግብ ራሽን እና የዕለት ጉርስ በሰልፍ ከመንግሥት በሚታደላቸው ወቅት የተሠራ መሆኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ መከራና ችግር በደስታና በቅንጦት ወቅት የማይሠራ ታላቅ ተግባር ሊፈጸምባቸው ይችላል ማለት ነው። እርግጥም ነው።
ከግድቡ በአንድ አቅጣጫ ርዝመቱ እና ግዝፈቱ የሚደንቅ እጅግ በታም ረዥም የባንዲራ ማማ ቆሞ፣ ከጫፉ ላይ አሜሪካ ባንዲራ ይውለበለባል። ከሥሩ ደግሞ “እነዚያ ምድረ ባዳውን ፍሬያማ የማድረግ ታላቅ ርዕይ ለጠነሰሱ እና ያንንም በጥበባቸው እና በጉልበታቸው እውን ላደረጉት ክብር ሲባል በዚህ ቦታ የአገራችን ባንዲራ ሊውለበለብ ይገባዋል” ይላል። ከሥሩ ገብቼ ወደላ…..ይ ጫፉን ለማየት አንገቴ እስኪሰበር ተጠምዝዤ ለማየት ሞከርኩ። በካሜራዬ በፎቶም በቪዲዮም ቀረጽኩት። የአገር ባንዲራ እንዲህ ባለ ታላቅ ግርማ ሲውለበለብ ማየት ልብን በአንዳች ስሜት ያሞቃል። ለአገር ታላቅ ሥራ ለሠሩ ሰዎች ከዚህ የበለጠ ምን ማስታወሻና መታሰቢያ ይገኛል?

ሰዓቱ ደርሶ የማስጎብኛ ክፍሎች በሮች ተከፍተው ስንገባ ግድቡ ከተወጠነበት ጊዜ አንስቶ የነበሩ ታሪኮች በፎቶም በቪዲዮም ተቀርጸው ይጎበኛሉ። ለካስ በዓመት አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ሊያየው የሚመጣው ለዚህ ኖሯል? ይገባዋልም። የኮሎራዶ ወንዝን በመግታት፣ አቅጣጫ በማስቀየር፣ ግድቡን በመሥራት፣ ድጋሚ ወደ ቀድሞው መንገዱ በመመለስ፣ ከበታቹ ያደርስ የነበረውን ማጥለቅለቅ በመግታት ለመስኖም፣ ለመጠጥም፣ ለመዝናኛም፣ ለአሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነትም የዋለ ግድብ ነው።

ኮሎራዶ ወንዝ በዚያ ግርማ ሞገሱ ከአፍ እስከ ገደፉ እየሞላ ከበታቹ ያሉ ግዛቶችን በሙሉ ሲያስጨንቅ ኖሮ በዚህ ግድብ ልጓም ተበጅቶለት ተገርቷል። አዋሽ ይኼንን እንዳይሰማ። ጉልበተኛ ሆኖ አገሩን ሁሉ እንዳላጥለቀለቀ ልባም ኢትዮጵያዊ ቢያገኝ እንደ ኮሎራዶ ወንዝ ልኩን ያገኝ ነበር። ሸበሌስ ቢሆን፣ ዓባይስ ቢሆን? ማን ይፈራቸዋል? እንዳልተገራ ፈረስ እንዲህ የሚፏንኑት ጥሩ እጅ ስላላገኙ ነው። ቢያገኙማ ልክ ይገቡ ነበር። ከዚያማ የምን ረሃብ፣ የምን ድርቅ። የምሥራቅ ኢትዮጵያ በረሃዎችም እንደ ኔቫዳ በግድብ እና በሰው ሠራሽ ሐይቅ ይታደሉ ነበር። ደረታቸውን ፀሐይ እያነደዳቸው ከሚኖሩ የሰው መደሰቻ ይሆኑ ነበር።

የሑቨር ግድብ ስያሜውን ያገኘው ከ31ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ከኢንጂነሩ ከ“Herbert Hoover/ ኸርበርት ሑቨር” ሲሆን ፕሬዚደንቱ የንግድ ሚኒስትር ሆነው ለግድቡ እውን መሆን በሙያቸውና በርዕያቸው ላበረከቱት ድጋፍ የተቸራቸው ነው። ይህንን ግድብ እውን ለማድረግ 112 ሠራተኞች ሞተዋል። ለመታሰቢያቸው በተገነባ ሐውልት አጠገብ “በረሃው ያበበ እንዲሆን ሞቱ” ("They died to make the desert bloom") የሚል ጽሑፍ ተቀርጿል።

 

 © ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
    

11 comments:

Anonymous said...

wow , Thanks Dn. Ephrem....It's great view and article.

Anonymous said...

የኢትዮጵያን ተራሮች ገርተው የተጠቀሙባቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ናቸው። ከገረዓልታ እስከ ደብረ ዳሞ፣ ከዝቋላ እስከ አሰቦት እግራቸው ያልረገጠው ሥፍራ የለም። ድንጋዩን ፈልፍለው፣ አለቱን ጠርበውና አለዝበው ዋሻውንና ፍርክታውን የመንፈሳዊ ተጋድሎ ቤታቸው አድርገውታል።
ፈረንጆቹ (አሜሪካውያኖቹ) ደግሞ እንደ ኮሎራዶ አካባቢ ያሉ ተራሮችን እየፈለፈሉ ግማሹን የቦምብ መሞከሪያ፣ ገሚሱን እንደ ጌጠኛ “አምፊ ቲያትር” አድርገው መዝናኛ አድርገውታል። እንደየሕይወት ፍልስፍናችን ኢትዮጵያውያኑም ፈረንጆቹም ተራሮቹን በእጃችን ልንገራቸው ሞክረናል።
ኤፍሬም ስለ ማራኪ ስዕላዊ የጉብኝት ጽሑፎችህ እግዚአብሔር ይስጥልን!

Abel said...

ውድ ኤፍሬም፤ስለ ጣፋጩ ትረካህ እግዚአብሔር እጆችህን ይባርክ፤አእምሮህ የሰላ ሆኖ እንዲቆይ ያድርግልን። ስለኛዎቹ ወንዞች-በምናብ ስታመጣን፤ የአጼ ሐይለስላሴ-ሳይፈጠም የቀረው እቅድ ትዝ አለኝ። አባይን ለመግራት ሕልም ነበራቸው። ጊዜው 1950ዎቹ አመታት ውስጥ ነበር። የአገሬው ሰው እውቀቱ እምብዛም ሰለነበር፤ የግድቡ ዝርዝር ጥናት በአሜሪካ ሰዎች ነበር የተጠናው። ጥናቱ-አባይ ከመነሻው ጀምሮ ሃገሪቱን ጥሎ እስከ ሚወጣበት ድረስ ለግድብ የሚሆኑ ቦታወችን ለይቶ ዝርዝር ፕላን ማውጣት ነበር። አራት ገደማ አካባቢዎች ተመረጡ። የእያንዳንዳቸው ዝርዝር ጥናት ተሰራ። እንደ አለመታደል ሆኖ-ንጉሱ ወረዱ። ጥናቱ በኢትዬጵያ ውሃ ሐብት ሚንስቴር መደደርደሪያ ላይ-ተቀምጦ ዙሮ የሚያየው ጠፋ። ባለፈው አመት-ያሁኑ “መሪያችን“-ንፋስ ወደ ሃገሪቱ እየገባ ሲያስጨንቃቸው፤ ማስቀየሻ ሲያፈላልጉ ይሄንን ጥናት ጨበጥ አደረጉ። ተመለከቱት። በወቅቱ ከአራቱ ውስጥ፤ የመጨረሻውን አማራጭ ከሱዳን ጠረፍ 40 ኪ.ሜ ገደማ የሚርቀውን፤ ለኤሌክትሪክ ብቻ ተብሎ የተጠናውን ላፍ አደረጉና አባይን ልገድበው ነው አሉ። ጥናቱ መቼ እንደተጀመረ ማንም እንዲያውቅ አይፈለግም፤ ብቻ እገድባለሁ። ብር አምጡ፤ እኔም አባይን የደፈረ መሪ ልባል እያሉ-ያን መከረኛ ሕዝብ ያሰቃዩታል። በእኔ አመለካከት-የሚሳካ አይመስለኝም! እራሱን የቻለው-የውሃ ፓለቲካ እየዘወረው ስለሆነ። እንዲህ አይነትን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ፤ ሕዝቡ ልብ ወስጥ የገባ፤ የሰከነና አስተዋይ መሪ ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን ጦሱ-ያው እንደ አጼው እሳቸውም ይወርዳሉ፤ ሕዝቡም ባልገባው ነገር እርስ በራሱ እየተላለቀ አበሳውን ያያል! ይሄን የምንቋቋምበት ጥበብ ያድለን። ልክ እንደ አሜሪካኖቹ-ማለት ነው።

Anonymous said...

thankyou dn ephrem[Adisu Tesfaye]??????

ኤፍሬም እሸቴ said...

You are very welcome. I don't know why you need to add "Adisu Tesfaye" here.

Anonymous said...

የኢትዮጵያን ተራሮች ገርተው የተጠቀሙባቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ናቸው። ከገረዓልታ እስከ ደብረ ዳሞ፣ ከዝቋላ እስከ አሰቦት እግራቸው ያልረገጠው ሥፍራ የለም።
አባቶች በጊዜያቸው አለምን ድንቅ ያሰባሉ ሰራዎች በመሰራታቸው እኛም እነኮራባቸዋል እኛስ ምን የሚያኮራ ስራ እንሰራ ይሆን ...0

Getaneh said...

Dn. Ephrem Where is the pdf format? i cant read amharic fonts. Please make it in pdf and let us to read it

God Bless you

Anonymous said...

Keep it up,bro! Share your visit experience now and then. I like ur writing as u compare things @Eth. as well! God bless u,dear!!

Anonymous said...

u like to show, the good thing is you cover your eyes, which need to be covered.

Anonymous said...

thank you;our country will be good by her children like you

afi said...

Thank you indeed for what you are contributing for people, many more please keep up all your goodness in such beautiful narration!
Then just a comment I need to forward you; as you have told us in this fabulous article the most of Ethiopian mountains, rivers and lakes need to mobiles to overcome on poverty and celebrate a mile stone development. Dear; no doubt it is true and it has to be. However I could not found any encouraging tips about what Ethiopia has been doing on such firm, we have done a lot regarding to ensure irrigation needs and many projects are under contractions which would be secured the country's power demand and many deals to be mentioned in such above articles.